የመጽሐፉ ይዘት
የመጽሐፉ ይዘት
በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ መጻሕፍት የገባ ሰው በየመደርደሪያዎቹ ተደርድረው የሚገኙትን መጻሕፍት ሲመለከት ግራ መጋባቱ አይቀርም። ይሁን እንጂ መጽሐፎቹ እንዴት ባለ ሥርዓት እንደተደረደሩ የሚያስረዳው ሰው ካገኘ የሚፈልጋቸውን ነገሮች እንዴት ለማግኘት እንደሚችል ያውቃል። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንዴት እንደተደራጁ ብታውቅ የፈለግኸውን መረጃ ለማግኘት ቀላል ይሆንልሃል።
“ባይብል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የፓፒረስ ጥቅሎች” ወይም “መጻሕፍት” የሚል ትርጉም ካለው ቢብልያ የተባለ የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው።1 መጽሐፍ ቅዱስ ከ1513 ከዘአበ እስከ 98 እዘአ ባሉት 1,600 ዓመታት ውስጥ የተጻፉ 66 ነጠላ መጻሕፍት ስብስብ ነው። ራሱን የቻለ ቤተ መጻሕፍት ነው ማለት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን ሦስት አራተኛ ክፍል የያዙት የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት በአብዛኛው በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፉ በመሆናቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ መጻሕፍት ደግሞ በሦስት ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ:- (1) የታሪክ መጻሕፍት ከዘፍጥረት እስከ አስቴር፣ 17 መጻሕፍት (2) የግጥም መጻሕፍት ከኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን፣ 5 መጻሕፍት (3) የትንቢት መጻሕፍት ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ 17 መጻሕፍት ናቸው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የምድርንና የሰው ልጆችን ቀደምት ታሪክ እንዲሁም የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ታሪክ ከተቋቋመበት ዘመን ጀምሮ እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ድረስ ያለውን ይሸፍናሉ።
የቀሩት 27 መጻሕፍት የዘመኑ ዓለም አቀፍ ቋንቋ በነበረው በግሪክኛ የተጻፉ በመሆናቸው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ መጻሕፍት በይዘታቸው መሠረት በሦስት ክፍሎች ይመደባሉ:- (1) አምስቱ የታሪክ መጻሕፍት—ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ፣ (2) ሃያ አንዱ መልእክቶች (3) ራእይ። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ባስተማሯቸው ትምህርቶችና ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኩራሉ።