በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳሳተ ግንዛቤ የተሰጠው መጽሐፍ

የተሳሳተ ግንዛቤ የተሰጠው መጽሐፍ

የተሳሳተ ግንዛቤ የተሰጠው መጽሐፍ

“ምድር በራስዋ ዛቢያና በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች የሚለው የሁለት ዓይነት አዟዟር መሠረተ ትምህርት ሐሰትና ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚቃረን ነው።” ይህን የጻፈው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ በ1616 ባስተላለፈው ድንጋጌ ነው።1 መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንሳዊ ሐቆች ጋር ይጋጫል? ወይስ የሚጋጭ የሚመስለው የተሳሳተ ግንዛቤ ስለተሰጠው ነው?

በ1609/10 የክረምት ወራት ጋሊልዮ ጋሊሌ አዲስ የሠራውን አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር ወደ ሰማይ አነጣጥሮ ሲመለከት ጁፒተር በተባለችው ፕላኔት ዙሪያ አራት ጨረቃዎች ሲሽከረከሩ አየ። ይህ የተመለከተው ነገር እስከዚያ ጊዜ ድረስ አላንዳች ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረውን የጠፈር አካላት በሙሉ በምድር ዙሪያ ይሽከረከራሉ የሚለውን እምነት ሙሉ በሙሉ የሚሽር ሆነ። ከዚህ ቀደም ብሎ በ1543 ኒኮላውስ ኮፐርኒከስ የተባለው ፖላንዳዊ የጠፈር ተመራማሪ ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ ይዞራሉ የሚል መላ ምት አቅርቦ ነበር። ጋሊልዮ ይህ መላምት ሳይንሳዊ ሐቅ መሆኑን አረጋገጠ።

ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት መናፍቅነት ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለበርካታ ዘመናት ምድር የመላው ጽንፈዓለም እምብርት ነች ብላ ታምን ነበር።2 ይህ አመለካከት “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት” የሚለውን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን አነጋገር ቃል በቃል ከመረዳት የመጣ ነበር። (መዝሙር 104:​5) ጋሊልዮ ወደ ሮማ ተጠርቶ መናፍቃንን ለመዳኘት በተሰየመ ችሎት ፊት ቀረበ። በተካሄደበት ከባድ የፍርድ ምርመራ ሳይንሳዊ ግኝቱን እንዲክድ ከተደረገ በኋላ ቀሪ ሕይወቱን በቁም እስር እንዲያሳልፍ ተደረገ።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋሊልዮ ልክ እንደነበረ ያመነችው አሁን በቅርቡ በ1992 ነው። ጋሊልዮ ከሞተ ወደ 350 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።3 ታዲያ ጋሊልዮ ትክክል ከነበረ የተሳሳተው መጽሐፍ ቅዱስ ነበረን?

የመጽሐፍ ቅዱስን ምንባቦች ትክክለኛ ትርጉም መረዳት

ጋሊልዮ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል እንደሆነ ያምን ነበር። ሳይንሳዊ ግኝቶቹ በጊዜው ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረው የአንዳንድ ጥቅሶች አተረጓጎም ጋር በሚጋጩበት ጊዜ የሃይማኖት ሰዎች በትክክል ያልተረዱት ነገር መኖር አለበት ብሎ ያምን ነበር። “ሁለት እውነቶች በምንም መንገድ እርስ በርሳቸው ሊጋጩ አይችሉም” ሲል ጽፏል።4 ትክክለኞቹ የሳይንስ ቃላት የመጽሐፍ ቅዱስን የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ ቃላት አይቃረኑም የሚል ሐሳብ ሰጥቷል። የሃይማኖት ሊቃውንት ግን ይህን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። ስለ ምድር የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫዎች በሙሉ ቃል በቃል መረዳት ይኖርብናል ይሉ ነበር። በዚህም ምክንያት የጋሊልዮን ግኝቶች ሳይቀበሉ ከመቅረታቸውም በላይ እንደነዚህ ያሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መግለጫዎች ትክክለኛ ትርጉም ሳይረዱ ቀሩ።

ማንኛውም ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ አራቱ የምድር ማዕዘናት’ ሲናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ምድር የአራት ማዕዘን ቅርጽ እንዳላት ያምኑ ነበር ብሎ እንደማያስብ ግልጽ ነው። (ራእይ 7:​1) መጽሐፍ ቅዱስ በተራ ሰዎች ቋንቋ የተጻፈ ከመሆኑም በላይ ሥዕላዊ በሆኑ አገላለጾች አዘውትሮ ይጠቀማል። ስለዚህ ምድር ‘አራት ማዕዘናት፣’ የጸና “መሠረት” ወይም ‘የማዕዘን ድንጋይ’ እንዳላት ሲናገር በዕለታዊ አነጋገራችን እንደምናደርገው በምሳሌያዊ ቃላት መናገሩ እንጂ ስለምድር ሳይንሳዊ መግለጫ መስጠቱ አይደለም። *​—⁠ኢሳይያስ 51:​13፤ ኢዮብ 38:​6

ኤል ጌሞናት የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ ጋሊልዮ ጋሊሌ በተባለው መጽሐፋቸው “ሳይንስን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከታቸው ለመገደብ የሚፈልጉ ሐሳበ ጠባብ የሃይማኖት ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒነት እንዲያጣ ከማድረግ የበለጠ የሚፈይዱት ነገር የለም” ብለዋል።5 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒነት እንዲያጣ አድርገዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ለሳይንስ ማነቆ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የሃይማኖት ሊቃውንቱ አተረጓጎም ነበር።

በዘመናችን የሚኖሩ ሃይማኖታዊ አክራሪዎችም ምድር የተፈጠረችው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከር መጽሐፍ ቅዱስን ያጣምማሉ። (ዘፍጥረት 1:​3-31) ይህ ዓይነቱ አመለካከት ከሳይንስም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማማም። “ቀን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ በዕለታዊ አነጋገር የተለያየ ርዝመት ያለውን የጊዜ መጠን የሚያመለክት ተለዋዋጭ ትርጉም ያለው ቃል ነው። በዘፍጥረት 2:​4 ላይ ስድስቱም የፍጥረት ቀናት እንደ አንድ “ቀን” ተደርገው ተጠርተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አንድን ረዥም ጊዜ” ሊያመለክት ይችላል።6 ስለዚህ የፍጥረት ቀናት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ነበራቸው የሚያሰኝ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያት የለም። ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ከዚህ የተለየ ትምህርት በማስተማራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ግንዛቤ አዛብተዋል።​—⁠በተጨማሪም 2 ጴጥሮስ 3:​8ን ተመልከት።

ባለፉት የታሪክ ዘመናት የሃይማኖት ሊቃውንት የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም በተደጋጋሚ ሲያዛቡ ኖረዋል። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የወከሉባቸውን ሌሎች መንገዶች እንመልከት።

ሃይማኖቶች የተሳሳተ አመለካከት እንዲስፋፋ አድርገዋል

መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን የሚሉ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ቅዱስ አድርገን እንመለከተዋለን በሚሉት መጽሐፍ ስምና ዝና ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል ሆኗል። ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች በአምላክ ስም አንዳቸው የሌላውን ደም አፍስሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የክርስቶስን ተከታዮች በሙሉ ‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ ሲል ይመክራል።​—⁠ዮሐንስ 13:​34, 35፤ ማቴዎስ 26:​52

አንዳንድ ካህናት መንጎቻቸው ጥረው ግረው ያገኙትን ገንዘብ በመውሰድ በቁማቸው ላጭተዋቸዋል። ይህ ደግሞ “በነጻ ተቀበላችሁ፣ በነጻ ስጡ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ፈጽሞ የሚጻረር ነው።​—⁠ማቴዎስ 10:​8 NW፤ 1 ጴጥሮስ 5:​2, 3

መጽሐፍ ቅዱስ በአንደበታቸው ብቻ እንመራበታለን የሚሉ ወይም ከመጽሐፉ የሚጠቅሱ ሰዎች በሚናገሩት ወይም በሚያደርጉት ነገር ሊመዘን እንደማይችል ግልጽ ነው። ስለዚህ ክፍት በሆነ አእምሮ የሚመረምር ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምን ነገር እንደሚናገርና ይህን ያህል አስደናቂ መጽሐፍ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመረዳት መፈለጉ አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ለምሳሌ ያህል በዛሬው ዘመን የሚኖር ስለ ጠፈር አካላት የጠለቀ እውቀት ያለው የሳይንስ ሊቅ እንኳን ፀሐይ፣ ከዋክብት ወይም የከዋክብት ስብስቦች “ወጡ” ወይም “ጠለቁ” ብሎ ይናገራል። እነዚህ የጠፈር አካላት ግን ምድር በመዞርዋ ምክንያት የሚንቀሳቀሱ መስለው ይታያሉ እንጂ የሚወጡ ወይም የሚጠልቁ አይደሉም።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለቱ የጋሊልዮ አቅርቦ ማሳያ መነጽሮች

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋሊልዮ በችሎት ፊት