የትንቢት መጽሐፍ
የትንቢት መጽሐፍ
ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ ይፈልጋሉ። ከአየርና ከኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጀምሮ ስለተለያዩ ጉዳዮች አስተማማኝ የሆነ ትንበያ እንዲነገራቸው ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ትንበያዎች ሲከተሉ ያልጠበቁት ነገር ይፈጸምና ይበሳጫሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ። እነዚህ ትንቢቶች ትክክለኛነታቸው ምን ያህል ነው? ከፍጻሜያቸው በፊት የተጻፉ ታሪኮች ናቸውን? ወይስ ከተፈጸሙ በኋላ ትንቢት አስመስለው የጻፏቸው ክንውኖች ናቸው?
ካቶ የተባለው ሮማዊ ርዕሰ ብሔር (234-149 ከዘአበ) “አንድ ንግርተኛ ሌላውን ንግርተኛ ሲመለከት አለመሳቁ ያስገርመኛል” እንዳለ ይነገራል።1 በእርግጥም እስከዛሬ ድረስ ሰዎች ጠንቋዮችን፣ ኮከብ ቆጣሪዎችንና ሌሎች ንግርተኞችን በጥርጣሬ ይመለከታሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሚናገሯቸው ትንቢቶች በግልጽ ለመረዳት በሚያስቸግሩ ቃላት ታጅበው ሲሆን የተለያየ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚችሉ ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችስ? እነዚህን ትንቢቶች በጥርጣሬ የምንመለከትበት ምክንያት ይኖራል? ወይስ እንድንተማመንባቸው የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን?
በተወሰኑ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ግምታዊ አስተያየቶች አይደሉም
አዋቂ የሆኑ ሰዎች አንዳንድ አዝማሚያዎችን ተመልክተው ስለወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛ የሆነ ግምታዊ አስተያየት ለመስጠት ይሞክሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ግምታቸው ሁልጊዜ ትክክል አይሆንም። ፊውቸር ሾክ የተባለው መጽሐፍ “እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሊደርሱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ ሊያጋጥሙ በሚችሉና በሚፈለጉ ሁኔታዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ያጋጥሙታል” ብሏል። በማከልም “እርግጥ ነው፣ ማንም ሰው ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእርግጠኝነት ‘ሊያውቅ’ አይችልም። ልናደርግ የምንችለው ስለወደፊቱ ጊዜ የሚኖረን ግምት በሥርዓት የሚመራና ጥልቀት ያለው እንዲሆን ማድረግና የየትኛው ግምት ተፈጻሚነት የበለጠ ዕድል እንደሚኖረው ለማወቅ መሞከር ነው” ብሏል።2
ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ትንቢት የተናገሩት እንዲሁ ‘አንዳንድ ክንውኖች መፈጸም የሚችሉበትን አጋጣሚ በማመዛዘን’ አይደለም። በተጨማሪም ትንቢቶቻቸው የተለያየ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚችሉና በግልጽ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ናቸው የሚባሉ ዓይነቶች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ብዙዎቹ ትንቢቶች በጣም ግልጽ በሆኑ ቃላት የተነገሩ፣ ስለ አንድ የተወሰነ ርዕሰ ጉዳይ የሚናገሩና አብዛኛውን ጊዜም ይፈጸማል ተብሎ ከሚጠበቀው ነገር ተቃራኒ የሆነ ነገር የሚተነብዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቷ ባቢሎን ከተማ በቅድሚያ የተናገረውን እንውሰድ።
‘በጥፋትም መጥረጊያ ትጠረጋለች’
“የጥንቷ ባቢሎን የመንግሥታት ክብር” ሆና ነበር። (ኢሳይያስ 13:19) ባቢሎን ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወደ ሜድትራንያን ባሕር በሚወስደው የንግድ መስመር ላይ የምትገኝ ታላቅ ከተማ የነበረች ሲሆን በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም ይካሄድ ለነበረው የባሕርና የምድር ላይ ንግድ ማዕከል ሆና ታገለግል ነበር።
በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ባቢሎን ፈጽሞ ልትደፈር የማትችል የምትመስል የባቢሎን አጼያዊ ግዛት ዋና ከተማ ሆና ነበር። ከተማይቱ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተገነባች ስትሆን ወንዙ ከጠላት ወረራ የሚከላከል ሰፊና ጥልቅ የሆነ የውኃ ጉድጓድ በከተማይቱ ዙሪያ ለመሥራት ከማገልገሉም በላይ በበርካታ ቦዮች ተከፋፍሎ እንዲፈስ ተደርጎ ነበር። በተጨማሪም ከተማይቱ በጣም ግዙፍ በሆነ ድርብ የአጥር ግንብ የተከበበች ነበረች። በአጥሩም ላይ በርካታ የሆኑ የመከላከያ ግንቦች ነበሩ። የከተማይቱ ነዋሪዎች ምንም ነገር አይደርስብንም ብለው ተረጋግተው መኖራቸው የሚያስደንቅ አይደለም።
ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የባቢሎን ክብር ታላቅ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ባቢሎን ‘በጥፋት መጥረጊያ እንደምትጠረግ’ ተነበየ። (ኢሳይያስ 13:19፤ 14:22, 23) በተጨማሪም ኢሳይያስ ባቢሎን የምትወድቅበትን ሁኔታ በግልጽ ተንብዮአል። ወራሪዎቹ ባቢሎን መከላከያ አድርጋ ወደምትጠቀምባቸው ቦዮች ወንዝ ‘እንደሚያደርቁና’ ያለ መከላከያ እንደሚያስቀሯት ተናግሯል። እንዲያውም ኢሳይያስ ወራሪው “በፊቱ በሮቹ ክፍት የሚሆኑለትና መዝጊያዎቹ ሁሉ የማይዘጉበት” ታላቁ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንደሚሆን ተንብዮአል።— ኢሳይያስ 44:27–45:2 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
እንዲህ ያለውን ትንቢት መናገር ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። ታዲያ ትንቢቱ በትክክል ተፈጽሟል? ታሪክ መልሱን ይሰጠናል።
“አላንዳች ውጊያ”
ኢሳይያስ ትንቢቱን ከጻፈ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ በ539 ከዘአበ ጥቅምት 5 ቀን ምሽት ላይ በታላቁ ቂሮስ አዝማችነት የወጣው የሜዶ ፋርስ ሠራዊት በባቢሎን አቅራቢያ ሠፈረ። ባቢሎናውያን ግን ምንም ዓይነት የሚያሸንፋቸው ኃይል እንደማይኖር እርግጠኞች ነበሩ። ሄሮዶቱስ (በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደተረከው ለብዙ ዓመታት የሚበቃ ምግብ አከማችተው ነበር።3 በተጨማሪም የኤፍራጥስ ወንዝና የባቢሎን ታላቅ የግንብ አጥር ከጥቃት ይጠብቋቸው ነበር። ቢሆንም የናቦኒደስ ዜና መዋዕል እንደሚለው በዚያው ምሽት “የቂሮስ ሠራዊት አላንዳች ውጊያ ወደ ባቢሎን ገባ።”4 ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ሄሮዶቱስ እንደተረከው የባቢሎን ሰዎች በከተማይቱ ውስጥ ሆነው “ባዘጋጁት ድግስ ይጨፍሩና ይፈነጥዙ ነበር።”5 ከከተማይቱ ውጭ ግን ቂሮስ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ አስለውጦ ነበር። የውኃው መጠን ሲቀንስ ወታደሮቹ እስከ ጭናቸው ይደርስ የነበረውን ውኃ ተሻገሩ። ትላልቆቹን የግንብ አጥሮች አልፈው ከሄዱ በኋላ ሄሮዶቱስ “በወንዙ በኩል የነበሩ ክፍት በሮች” ብሎ በገለጻቸው መግቢያዎች በኩል ገቡ፤ በሮቹ በጥንቃቄ ጉድለት ሳይዘጉ ቀርተው ነበር።6 (ከዳንኤል 5:1-4፤ ከኤርምያስ 50:24፤ 51:31, 32 ጋር አወዳድር።) ዜኖፎን ጨምሮ (431-352 ከዘአበ ገደማ) ሌሎች ታሪክ ጸሐፊዎች እንዲሁም በአርኪኦሎጂስቶች የተገኙ የኩኒፎርም ጽላቶች ባቢሎን በድንገት በቂሮስ እጅ መውደቋን አረጋግጠዋል።7
ስለዚህ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን የተናገረው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። ይህ በእርግጥ አስቀድሞ የተነገረ ትንቢት አልነበረምን? ይህ ክንውን ትንቢት ሳይሆን ባቢሎን ከወደቀች በኋላ የተጻፈ ታሪክ ሊሆን ይችላልን? ስለ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል።
በትንቢት ሽፋን የተጻፈ ታሪክ ነውን?
ኢሳይያስን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት፣ ትንቢት ነው ብለው የጻፉት ሲፈጸም የተመለከቱትን ታሪክ ከነበረ እነዚህ ሰዎች ብልሃተኛ አታላዮች ነበሩ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ ማታለል የሚፈጽሙበት ምን ምክንያት አላቸው? እውነተኛ ነቢያት በጉቦ ሊደለሉ የማይችሉ መሆናቸውን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠዋል። (1 ሳሙኤል 12:3፤ ዳንኤል 5:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች (ብዙዎቹ ነቢያት ነበሩ) የሚያፍሩባቸውን የገዛ ራሳቸውን ስህተቶች ሳይቀር ይፋ ለማውጣት ወደ ኋላ የማይሉ ታማኝ ሰዎች እንደነበሩ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ተመልክተናል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የተፈጸመውን ታሪክ ትንቢት አስመስለው በመጻፍ ይህን የመሰለ ማጭበርበር ይፈጽማሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።
ሌላም ልንገነዘበው የሚገባ ነገር አለ። ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የነቢያቱ ወገን የሆኑትን ሕዝቦች፣ ካህናቱንና ገዥዎቹን ሳይቀር የሚያወግዙ መልእክቶች ያለባቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ በዘመኑ የነበሩት እስራኤላውያን፣ መሪዎቹም ሆኑ ተራዎቹ ሕዝቦች ተዘፍቀውበት የነበረውን አሳዛኝ የሆነ የሥነ ምግባር ውድቀት አውግዟል። (ኢሳይያስ 1:2-10) ሌሎች ነቢያትም የካህናቱን ኃጢአት በጠንካራ ቃላት አጋልጠዋል። (ሶፎንያስ 3:4፤ ሚልክያስ 2:1-9) የገዛ ራሳቸውን ሕዝቦች ክፉኛ የሚያወግዝ ትንቢት ፈልስፈው የሚናገሩበትንና ካህናቱ ደግሞ በዚህ ተንኮል ተባባሪ የሚሆኑበትን ምክንያት መገመት ያስቸግራል።
በተጨማሪም እነዚህ ነቢያት ተራ አታላዮች ከነበሩ እንደዚህ ያለው አጭበርባሪነት እንዴት ሊሳካላቸው ቻለ? እስራኤላውያን ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ ይበረታቱ ነበር። ልጆች ገና በሕፃንነታቸው መጻፍና ማንበብ ይማሩ ነበር። (ዘዳግም 6:6-9) ቅዱሳን ጽሑፎችን በግላቸው እንዲያነቡ ይመከሩ ነበር። (መዝሙር 1:2) በየሳምንቱ ይከበር በነበረው ሰንበት በምኩራቦች ውስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሕዝብ ይነበቡ ነበር። (ሥራ 15:21) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ ያውቅና ማንበብና መጻፍ ይችል የነበረ ሕዝብ እንዲህ ባለው ማጭበርበር ይታለላል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።
ከዚህም በላይ ኢሳይያስ የተነበየው የባቢሎንን ውድቀት ብቻ አይደለም። በዚህ ትንቢት ውስጥ ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ ሊጻፍ የማይችል ዝርዝር ጉዳይ ይገኛል።
“ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም”
ባቢሎን ከወደቀች በኋላ ምን ትሆናለች? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል:- “ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም። ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም። ዓረባውያን ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፣ እረኞችም መንጎታቸውን በዚያ አያሳርፉም።” (ኢሳይያስ 13:20) ሌላው ቢቀር እንዲህ ባለ አመቺ ቦታ ላይ የተቆረቆረች ከተማ ለዘላለም ሰው የማይኖርባት ትሆናለች ብሎ መተንበይ የማይመስል ነገር መናገር ይሆናል። ኢሳይያስ ይህን ቃል የጻፈው ባቢሎን ባድማ እንደሆነች ከተመለከተ በኋላ ሊሆን ይችላልን?
ቂሮስ ባቢሎንን እጁ ካስገባ በኋላም ቢሆን ቀድሞ ከነበራት ክብር ዝቅ ትበል እንጂ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሰው የሚኖርባት ከተማ ሆና ቀጥላ ነበር። በሙት ባሕር ጥቅልል ውስጥ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈ ነው የሚባል ሙሉ የኢሳይያስ መጽሐፍ እንደሚገኝ ታስታውሳለህ። ይህ ጥቅልል ይገለበጥ በነበረበት ዘመን አካባቢ ፓርታውያን ባቢሎንን በግዛታቸው ሥር አስገብተው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ላይ በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ከመኖራቸውም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጴጥሮስ ከተማይቱን ጎብኝቷት ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:13) በዚህ ጊዜ ላይ የኢሳይያስ የሙት ባሕር ጥቅልል ተገልብጦ ካለቀ ወደ ሁለት መቶ ዓመታት ያህል ሆኖት ነበር። ስለዚህ እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ባድማ ያልሆነች ስትሆን የኢሳይያስ መጽሐፍ ግን ተጽፎ ካለቀ ብዙ ዓመታት አልፈውታል። *
ከጊዜ በኋላ ባቢሎን በትንቢቱ መሠረት ተራ “የድንጋይ ክምር” ሆነች። (ኤርምያስ 51:37) ጄሮም (አራተኛው መቶ ዘመን እዘአ) የተባለው ዕብራዊ ምሁር እንዳለው በእሱ ዘመን ባቢሎን “አራዊት ሁሉ” የሚፈነጩባት ሜዳ ሆና ነበር።9 ባቢሎን እስከ ዛሬም ድረስ ባድማ ነች።
ኢሳይያስ ባቢሎን ሰው የማይኖርባት ባድማ ስትሆን በሕይወት አልነበረም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በኢራቅ ከባግዳድ በስተ ደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የዚህች በአንድ ወቅት ገናና የነበረች ከተማ ፍርስራሽ “ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም” የሚለው የኢሳይያስ ቃል በትክክል የተፈጸመ መሆኑን ይመሠክራል። ባቢሎን ታድሳ የቱሪስቶች መስህብ ብትሆን አገር ጎብኚዎች ይደሰቱ ይሆናል። ከባቢሎን ግን ‘ዘርና ትውልድ’ ለዘላለም ተቆርጧል።— ኢሳይያስ 13:20፤ 14:22, 23
ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ ማንኛውንም የወደፊት ክንውን ሊያመለክት የሚችል ግልጽ ያልሆነ ትንቢት አልተናገረም። ወይም ታሪኩ ከተፈጸመ በኋላ ትንቢት አስመስሎ አልጻፈም። እስቲ ነገሩን አስብ። አንድ አጭበርባሪ የሆነ ሰው ኃያሏ ባቢሎን ለዘላለም ባድማ እንደምትሆን በመናገር ከእርሱ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር “ተንብዮ” ራሱን ሊያጋልጥ የሚችል ነገር የሚናገርበት ምን ምክንያት አለ?
ይህ ስለ ባቢሎን ውድቀት የሚናገረው ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ምሳሌዎች አንዱ ነው። * ብዙ ሰዎች የትንቢቶቹ ፍጻሜ ማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የመነጨው ከሰው የሚበልጥ ኃይል ካለው አካል እንደሆነ ያሳምናቸዋል። አንተም ይህ የትንቢት መጽሐፍ ቢያንስ ሊመረመር የሚገባው መጽሐፍ እንደሆነ ሳትስማማ አትቀርም። አንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ። ዘመናዊ ትንቢት ተናጋሪ ነን ባዮች በሚናገሩት ስሜታዊ ወይም ግልጽ ያልሆነ ትንቢትና ግልጽና ቀጥተኛ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መካከል በጣም ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.24 የኢሳይያስ መጽሐፍን ጨምሮ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ብዙ ቀደም ብሎ ተጽፈው ያለቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ አለ። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ (መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከእርሱ ዘመን ብዙ ቀደም ብለው ተጽፈው ያለቁ መሆናቸውን አመልክቷል።8 በተጨማሪም የግሪክ ሴፕቱጀንት የተባለው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተጀምሮ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተጠናቅቆ ነበር።
^ አን.28 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘትና ትንቢቶቹ በትክክል መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ የታሪክ ማስረጃዎችን ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ከገጽ 117-33 ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ትክክለኛ ነቢያት ነበሩ ወይስ ብልሃተኛ አታላዮች?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሽ