በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ መጽሐፍ ከሳይንስ ጋር ይስማማልን?

ይህ መጽሐፍ ከሳይንስ ጋር ይስማማልን?

ይህ መጽሐፍ ከሳይንስ ጋር ይስማማልን?

ሃይማኖት ሳይንስን እንደ ጠላት የተመለከተባቸው ጊዜያት ነበሩ። ባለፉት መቶ ዘመናት አንዳንድ ሃይማኖተኞች የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎማቸውን አደጋ ላይ የሚጥልባቸው ሆኖ የተሰማቸውን ሳይንሳዊ ግኝት ይቃወሙ ነበር። ይሁን እንጂ በእርግጥ ሳይንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላት ነውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዘመናቸው ሰፊ ተቀባይነት ያገኙትን የሳይንስ አመለካከቶች ቢያንጸባርቁ ኖሮ ይህ መጽሐፍ በርካታ ሳይንሳዊ ስህተቶች ደምቀው የሚታዩበት መጽሐፍ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ ጸሐፊዎቹ እንደነዚህ ያሉትን ሳይንሳዊ ያልሆኑ ግንዛቤዎች አላስፋፉም። እንዲያውም በተቃራኒው ትክክለኛ የሆኑ ሳይንሳዊ ሐቆችን ከመጻፋቸውም በላይ በኖሩባቸው ዘመናት ተቀባይነት ያገኙ አመለካከቶችን በቀጥታ የሚቃረን ነገር ጽፈዋል።

የምድር ቅርጽ እንዴት ያለ ነው?

ይህ ጥያቄ የሰው ልጆችን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ግራ ሲያጋባ የኖረ ነው። በጥንት ዘመናት የነበረው አጠቃላይ አመለካከት ምድር ጠፍጣፋ ነች የሚል ነበር። ለምሳሌ ያህል ባቢሎናውያን ጽንፈ ዓለም እንደ ሣጥን ወይም እንደ አንድ ክፍል ያለ ሲሆን ምድር የጽንፈ ዓለሙ ወለል ናት ብለው ያምኑ ነበር። የሕንድ የቬዳ ቀሳውስት ምድር ጠፍጣፋ ስትሆን ለመኖሪያነት የሚያገለግለው አንደኛው ገጽዋ ብቻ እንደሆነ ያስቡ ነበር። አንድ በእስያ የሚኖር ኋላ ቀር ጎሣ ምድር ትልቅ የሻይ ማቅረቢያ ሳህን እንደምትመስል ያምናል።

ፓይታጎረስ የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ ጨረቃና ፀሐይ ክብ ከሆኑ ምድርም ክብ መሆን አለባት የሚል ንድፈ ሐሳብ ያቀረበው ገና በስድስተኛ መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። ቆየት ብሎም አርስቶትል (በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) የምድር ክብ መሆን በጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ በሚታየው ሁኔታ ሊረጋገጥ ይችላል ሲል ገልጿል። ምድር በጨረቃ ላይ የምትጥለው ጥላ ደጋን የመሰለ ነው።

ይሁን እንጂ ምድር ጠፍጣፋ ነች (ለመኖሪያነትም የሚያገለግለው የላይኛው ክፍሏ ብቻ ነው) የሚለው አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። አንዳንዶች ምድር ክብ ነች የሚለው አስተሳሰብ ያለውን አንድምታ ማለትም የአንቲፖድስን ጽንሰ ሐሳብ መቀበል አዳጋች ሆኖባቸዋል። * በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ክርስትናን ደግፎ የጻፈው ላክታንቲዎስ ይህን የመሰለውን አስተሳሰብ ነቅፏል። እንዲህ አለ:- “የእግራቸው ኮቴ ከአናታቸው በላይ የሆኑ ሰዎች አሉ ብሎ የሚያምን ደንቆሮ ሰው ሊኖር ይችላልን? . . . አዝርዕትና ዛፎች ወደ ቁልቁል ሊያድጉ፣ ዝናብና በረዶ ከታች ወደ ላይ ሊፈስሱ ይችላሉን?”2

አንቲፖድስ ለጥቂት ሃይማኖታዊ ሊቃውንት ለመቀበል የሚያዳግት ጽንሰ ሐሳብ ሆኖባቸው ነበር። አንዳንድ ንድፈ ሐሳቦች በተቃራኒው የምድር ገጽ የሚኖሩ ሰዎች ቢኖሩ በመካከል በመርከብ ሊቋረጥ የማይቻል ሰፊ ባሕር ወይም በምድር ወገብ አካባቢ ንዳድ የሆነ በረሐ ስለሚኖር በዚያ ከሚኖሩት የሰው ልጆች ጋር ሊገናኙ አይችሉም ይሉ ነበር። ታዲያ እነዚህ አንቲፖዳውያን ከየት ሊመጡ ቻሉ? አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት ግራ በመጋባታቸው ምክንያት አንቲፖዳውያን የሚባሉ ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም፣ እንዲያውም ላክታንቲዎስ እንዳለው ምድር ክብ ልትሆን አትችልም ብለው ለማመን መርጠዋል።

ያም ሆነ ይህ ምድር ክብ ነች የሚለው ጽንሰ ሐሳብ አሸነፈና ሰፊ ተቀባይነት አገኘ። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ወደ ጠፈር ተጉዘው ምድር ሉል መሆኗን አይተው ለማረጋገጥ የቻሉት የጠፈር ዘመን በሆነው በሃያኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ነው። *

በዚህ ጉዳይ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ምን ነበር? ምድር ጠፍጣፋ ነች ተብሎ ይታመን በነበረበት፣ የግሪክ ፈላስፎች ምድር ድቡልቡል ነች የሚል ንድፈ ሐሳብ ከማምጣታቸው በመቶ የሚቆጠሩ ዘመናት በፊትና የሰው ልጆች ጠፈር ላይ ሆነው ምድር ሉል መሆኗን ከማረጋገጣቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ማለትም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢሳይያስ የተባለው ዕብራዊ ነቢይ በጣም ቀላል በሆነ አነጋገር “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል” ብሏል። (ኢሳይያስ 40:​22፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ “ክበብ” ተብሎ የተተረጎመው ቹግ የተባለ የዕብራይስጥ ቃል “ድቡልቡል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።3 ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “በምድር ሉል” (ዱዌይ ቨርሽን) እና “ክብ በሆነችው ምድር” እያሉ ተርጉመዋል።​—⁠ሞፋት *

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ኢሳይያስ በዘመኑ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውን ስለ ምድር የሚነገር መላ ምት አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ የሳይንስ እድገት ሊሽረው ያልቻለ እውነተኛ መግለጫ ጽፏል።

ምድርን ደግፎ ያቆማት ምንድን ነው?

በጥንት ዘመናት የሰው ልጆችን ግራ ያጋቡ ሌሎች ስለ ጠፈር አካላት የሚጠየቁ ጥያቄዎችም ነበሩ:- ምድር ተደግፋ የቆመችው በምን ላይ ነው? ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን በየቦታቸው ደግፎ ያቆማቸው ነገር ምንድን ነው? አይዛክ ኒውተን በፎርሙላ መልክ ስላስቀመጠውና በ1687 ስላሳወቀው የስበት ሕግ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የጠፈር አካላት በባዶ ሥፍራ ላይ የመንጠልጠላቸው ሐሳብ ፈጽሞ የማይታወቅ ነበር። ስለዚህ የሚሰጡት መግለጫ ምድርንና ሌሎቹን የጠፈር አካላት ደግፈው ያቆሟቸው ግዑዝ አካላት እንዳሉ የሚገልጽ ነበር።

ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጥንታዊ ንድፈ ሐሳብ ምድር በውኃ የተከበበች እንደሆነችና በዚህ ውኃ ላይ እንደምትንሳፈፍ ይገልጻል። ይህን ንድፈ ሐሳብ ያመነጩት በደሴት ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሂንዱዎች ደግሞ ምድር እርስ በርሳቸው በተነባበሩ በርካታ መሠረቶች ላይ የቆመች እንደሆነች ያምኑ ነበር። ምድር በአራት ዝሆኖች ላይ የቆመች ስትሆን ዝሆኖቹ በትልቅ ዔሊ ላይ፣ ዔሊው በጣም ግዙፍ በሆነ ዘንዶ ላይ፣ የተጠመጠመው ዘንዶ ደግሞ በጽንፈ ዓለማዊው ውኃ ላይ እንደተኛ ያስቡ ነበር። በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ኢምፔዶክልስ የተባለ ግሪካዊ ፈላስፋ ምድር ክብ እየሠራ በሚሽከረከር አውሎ ነፋስ ላይ የቆመች እንደሆነችና ለጠፈር አካላትም መንቀሳቀስ ምክንያት የሆነው ይህ አውሎ ነፋስ እንደሆነ ያምን ነበር።

ሰፊ ተቀባይነት ካገኙት አስተያየቶች አንዱ የአርስቶትል አስተያየት ነበር። አርስቶትል ምድር ድቡልቡል እንደሆነች ቢናገርም በባዶ ሥፍራ ላይ የተንጠለጠለች መሆኗን አልተቀበለም። ኦን ዘ ሄቨንስ በተባለው ጽሑፉ ላይ ምድር በውኃ ላይ የቆመች ነች የሚለውን አስተሳሰብ ሲያስተባብል “ውኃም ሆነ ምድር በባዶ አየር ላይ ለመንጠልጠል የሚያስችል ባሕርይ የላቸውም። አንድ ያረፉበት ነገር መኖር አለበት” ብሏል።4 ታዲያ “ምድር ተደግፋ የቆመችው” በምን ላይ ነው? አርስቶትል ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ጠጣርና ብርሃን አስተላላፊ በሆኑ ክብ አካላት ላይ የተጣበቁ ናቸው ብሎ ያስተምር ነበር። እነዚህ ብርሃን አስተላላፊ አካላት አንዳቸው በሌሎቹ ላይ ተነባብረው ምድር በመካከል እንዳትንቀሳቀስ ሆና ተቀምጣለች ይል ነበር። አንዳቸው በሌሎቹ ላይ ሲሽከረከሩ በላያቸው ላይ ያሉት ፀሐይ፣ ጨረቃና ፕላኔቶች በሰማይ ላይ ይጓዛሉ።

የአርስቶትል ማብራሪያ ምክንያታዊ መስሎ ነበር። የጠፈር አካላት በአንድ ነገር ላይ የተጣበቁ ካልሆኑ እንዴት በየቦታቸው ላይ ሊቆዩ ይችላሉ? ትልቅ ከበሬታ ይሰጠው የነበረው የአርስቶትል አመለካከት 2,000 ለሚያክሉ ዓመታት እንደ ሐቅ ተደርጎ ይታመንበት ነበር። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚለው በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመን የአርስቶትል ትምህርት በቤተ ክርስቲያን “የሃይማኖታዊ ቀኖና ደረጃ ተሰጥቶት ነበር።”5

አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር ከተሠራ በኋላ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የአርስቶትልን ንድፈ ሐሳብ መጠራጠር ጀመሩ። ቢሆንም ሰር አይዛክ ኒውተን ፕላኔቶች በባዶ ጠፈር ላይ በዓይን በማይታይ የስበት ኃይል ምህዋራቸውን ጠብቀው እንዲዞሩ የተደረጉ መሆናቸውን እስኪያስረዳ ድረስ ለጥያቄያቸው መልስ አላገኙም ነበር። ይህ ንድፈ ሐሳብ ለማመን የሚያስቸግር ሆኖ ነበር። ከኒውተን የሥራ ባልደረቦች አንዳንዶቹ ጠፈር በአብዛኛው ምንም ነገር የሌለው ባዶ ሥፍራ መሆኑን መቀበል ከብዷቸው ነበር። *6

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጥያቄ ላይ ምን ይላል? 3,500 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በጣም አስደናቂ በሆነ ግልጽነት ምድር “አንዳች አልባ” እንደተንጠለጠለች ገልጿል። (ኢዮብ 26:​7) እዚህ ላይ “አንዳች አልባ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል (ቤሊማህ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ምንም ነገር ሳይኖር” ማለት ነው።7 1980 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “በባዶ ቦታ” የሚለውን ሐረግ ተጠቅሟል።

በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ምድር “በባዶ ቦታ” ላይ እንደተንጠለጠለች ሊያስቡ አይችሉም። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ግን ከነበረበት ዘመን ቀድሞ በመሄድ ጠንካራ የሳይንስ መሠረት ያለው መግለጫ ሰጥቷል።

መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ ​—⁠ይስማማሉን?

ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ በሽታ ስለሚዛመትባቸው መንገዶችና በሽታዎችን ልናስወግድ ስለምንችልባቸው መንገዶች በርካታ ነገሮች አስተምሮናል። በ19ኛው መቶ ዘመን የታየው የሕክምና ሳይንስ እድገት ንጽሕና በመጠበቅ በሽታዎች እንዳይዛመቱ መከላከል እንደሚቻል አረጋግጧል። በዚህ ምክንያት የተገኘው ውጤት በጣም የሚያስደንቅ ነው። የበሽታዎች መዛመትና አለ ዕድሜያቸው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀነሰ።

ጥንታውያን ሐኪሞች ግን በሽታ እንዴት እንደሚተላለፍም ሆነ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ንጽሕና በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ እንዳለው ሙሉ በሙሉ አልተገነዘቡም ነበር። የሕክምና አሰጣጣቸው በአብዛኛው ለዘመናዊ ሰዎች በጣም ኋላ ቀር ሆኖ መታየቱ አያስደንቅም።

እጅግ ጥንታዊ ናቸው ከሚባሉት የሕክምና ጽሑፎች አንዱ ከ1550 ከዘአበ ጀምሮ ያለው የግብጻውያን የሕክምና እውቀት የተጠናቀረበት ኤበርስ ፓፒረስ የተባለው ጽሑፍ ነው። በዚህ የመጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ “ከአዞ ንክሻ እስከ ጥፍር በሽታ” ለሚደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች የሚታዘዙ 700 የሚያክሉ መድኃኒቶች ተዘርዝረዋል።8 ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “የእነዚህ ሐኪሞች እውቀት ሙሉ በሙሉ ከልምድና ከተሞክሮ የተገኘ፣ በአብዛኛው ደግሞ በአስማት ላይ የተመሠረተና በአጠቃላይ ሳይንሳዊ ያልሆነ ነበር።”9 አብዛኞቹ መድኃኒቶች ፈዋሽነት የሌላቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ ግን በጣም አደገኞች ናቸው። ቁስል ለማከም ይታዘዙ ከነበሩት መድኃኒቶች አንዱ ቁስሉ ላይ የሚቀባ የሰውን ዓይነ ምድር ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር በመቀላቀል የሚሠራ ነገር ነበር።10

ይህ የግብጻውያን የመድኃኒት መጽሐፍ የተጻፈው የሙሴ ሕግ የተመዘገበባቸው የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተጻፉበት ጊዜ ገደማ ነበር። በ1593 ከዘአበ የተወለደው ሙሴ ያደገው በግብጽ አገር ነበር። (ዘጸአት 2:​1-10) የፈርዖን ቤተሰብ አባል ስለነበረ ‘የግብጻውያንን ጥበብ በሙሉ ተምሯል።’ (ሥራ 7:​22) የግብጻውያንን “ሐኪሞች” በሚገባ ያውቃቸው ነበር። (ዘፍጥረት 50:​1-3) ታዲያ የእነዚህ ሐኪሞች ምንም ዓይነት ፈዋሽነት የሌለው ወይም አደገኛ የሆነ ሕክምና በጻፋቸው ጽሑፎች ላይ ተጽእኖ አሳድሯልን?

በፍጹም አላሳደረም። እንዲያውም በተቃራኒው በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተጻፉበት ዘመን እጅግ የመጠቁ የንጽሕና ሕጎች ተካትተዋል። ለምሳሌ ያህል ስለ ጦር ሠፈር የተሰጠ አንድ ሕግ ዐይነ ምድር ከሠፈሩ ውጭ እንዲቀበር ያዝ ነበር። (ዘዳግም 23:​13) ይህ በጣም ዘመናዊ የበሽታ መከላከያ ዘዴ ነው። የመጠጥ ውኃ ከብክለት ነጻ እንዲሆን ከመርዳቱም በላይ በዛሬው ጊዜ ሳይቀር አስከፊ የንጽሕና ሁኔታዎች በሚገኙባቸው አገሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጩትን እንደ ሺጌሎሲስ ያሉትንና ሌሎች በዝንብ አስተላላፊነት የሚዛመቱ የተቅማጥ በሽታዎች ለማስወገድ ያስችላል።

በሙሴ ሕግ ውስጥ በእስራኤላውያን መካከል ተዛማች በሽታዎች እንዳይስፋፉ የሚከላከሉ ሌሎች የንጽሕና ሕጎችም ተካትተዋል። ተዛማች በሽታ የያዘው ወይም እንደያዘው የሚጠረጠር ሰው ለብቻው ተገልሎ እንዲቆይ ይደረግ ነበር። (ዘሌዋውያን 13:​1-5) የበከተ እንስሳ (በበሽታ ምክንያት የሞተ ሊሆን ይችላል) የነካ ልብስ ወይም ዕቃ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት መታጠብ አለበለዚያም ፈጽሞ መወገድ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 11:​27, 28, 32, 33) ሬሳ የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ እንደሆነ ወይም ንጹህ እንዳልሆነ ተቆጥሮ የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም ይገደድ ነበር። ይህ ሥርዓት ልብሱንና ገላውን መታጠብን ይጨምር ነበር። ርኩስ ሆኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት ከሌሎች ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አይኖረውም።​—⁠ዘኁልቁ 19:​1-13

ይህ የንጽሕና ሕግ የያዘው ጥበብ በአካባቢው በነበሩ የዘመኑ ብሔራት የሚገኙ ሐኪሞች ፈጽሞ ያልነበራቸው ነው። የሕክምና ሳይንስ በሽታዎች ስለሚዛመቱባቸው መንገዶች ከማወቁ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ የሆኑ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎችን አዟል። ሙሴ በዘመኑ የነበሩት እስራኤላውያን ዕድሜ በጥቅሉ ሲታይ 70 ወይም 80 እንደሆነ መናገሩ አያስደንቅም። *​—⁠መዝሙር 90:​10

ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫዎች ሳይንሳዊ መሆናቸውን ትቀበል ይሆናል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሳይንስ ሊረጋገጡ የማይችሉ ሌሎች መግለጫዎች አሉ። ታዲያ ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይጋጫል ማለት ነውን?

በሳይንስ ሊረጋገጡ የማይችሉትን መግለጫዎች መቀበል

አንድ መግለጫ በሳይንስ ሊረጋገጥ ስላልቻለ ብቻ ስህተት መሆን አለበት ማለት አይቻልም። ሳይንሳዊ ማረጋገጫዎች የሰው ልጅ ባለው መረጃ የማግኘትና ያገኘውን መረጃ በትክክል የመተርጎም ችሎታ ላይ የተመኩ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ እውነቶች ተመዝግቦ የቆየ ማስረጃ ባለመኖሩ፣ ማስረጃው ስውር ወይም ገና ያልተገኘ በመሆኑ ወይም ደግሞ ያለው ሳይንሳዊ ብቃትና እውቀት የማያጠያይቅ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የማያስችል በመሆኑ ምክንያት ሊረጋገጡ የማይችሉ ናቸው። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫዎች ነጻ የሆነ ተጨባጭ ማስረጃ ያልተገኘላቸው በዚህ ምክንያት ይሆንን?

ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ አካላት የሚኖሩበት በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ዓለም ስለመኖሩ የሚናገረው ቃል ትክክል ይሁን አይሁን በሳይንስ ሊረጋገጥ አልቻለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው ስለሚገኙ ተአምራቶችም እንዲሁ ማለት ይቻላል። በኖኅ ዘመን ምድር አቀፍ የሆነ የውኃ መጥለቅለቅ አንደነበረ የተገኘው ጂኦሎጂያዊ ማስረጃ አንዳንድ ሰዎችን ለማሳመን የሚበቃ አይደለም። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 7) ታዲያ በዚህ ምክንያት ይህ የውኃ መጥለቅለቅ ፈጽሞ አልነበረም ለማለት እንችላለን? ታሪካዊ ክስተቶች በጊዜና በለውጥ ተሸፍነው ሊቆዩ ይችላሉ። ስለዚህ የውኃ መጥለቅለቅ ደርሶ እንደነበረ የሚያሳዩ ማስረጃዎች በአብዛኛው በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በተፈራረቁት ጂኦሎጂያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠራርገው ሊጠፉ አይችሉምን?

መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በተገኙት ተጨባጭ ማስረጃዎች ትክክለኛነታቸውም ሆነ ስህተትነታቸው ሊረጋገጡ የማይችሉ መግለጫዎች አሉት። ታዲያ ይህ እንግዳ ነገር ሊሆንብን ይገባልን? መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መጽሐፍ አይደለም። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት መጽሐፍ ነው። ጸሐፊዎቹ የአቋም ጽናት ሐቀኝነት ያላቸው ሰዎች እንደነበሩ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። ሳይንስ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በሚያነሱበት ጊዜም የጻፏቸው ቃላት ትክክለኛና ተረት ሆነው ከቀሩ የጥንት “ሳይንሳዊ” ንድፈ ሐሳቦች ፈጽሞ የጠሩ ናቸው። ስለዚህ ሳይንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ክፍት በሆነ አእምሮ የምንመረምርበት በቂ ምክንያት አለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 “አንቲፖድስ የሚባሉት . . . በምድር ሉል ላይ እርስ በርሳቸው ትይዩ በሆኑ ተቃራኒ ጎኖች የሚገኙ ሁለት ቦታዎች ናቸው። በመካከላቸው ቀጥ ያለ መስመር ቢሰመር ይህ መስመር የምድርን እምብርት ሰንጥቆ ያልፋል። አንቲፖድስ ማለት በግሪክኛ እግር ለእግር ማለት ነው። ሁለት ሰዎች በአንቲፖዶች ላይ ቢቆሙ በመካከላቸው የሚኖረው አነስተኛ ርቀት ከእግራቸው እስከ እግራቸው ያለው ይሆናል።”1— ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ

^ አን.9 ሙሉ በሙሉ በትክክል ለመግለጽ ከተፈለገ ምድር በሁለቱ ዋልታዎች ላይ ጠፍጠፍ ያለች ድቡልቡል አካል ነች።

^ አን.10 በተጨማሪም ከየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ክብ ሆኖ ሊታይ የሚችለው እንደ ኳስ ድቡልቡል የሆነ አካል ብቻ ነው። ጠፍጣፋ ሆኖ ክብ የሆነ አካል በሁሉም አቅጣጫ ክብ ሆኖ ሊታይ አይችልም።

^ አን.17 በኒውተን ዘመን ጽንፈ ዓለሙ በአንድ ዓይነት ፈሳሽ የተሞላ እንደሆነና የዚህ ፈሳሽ እንቅስቃሴ ፕላኔቶች እንዲሽከረከሩ እንደሚያደርግ በሰፊው ይታመን ነበር።

^ አን.27 በ1900 በብዙ የአውሮፓ አገሮችና በዩናይትድ ስቴትስ የሰዎች አማካይ ዕድሜ ከ50 ዓመት ያነሰ ነበር። ከዚያ ወዲህ በሽታዎችን መቆጣጠር የሚቻልበት የሕክምና ዘዴ ስለተሻሻለ ብቻ ሳይሆን የንጽሕናና የአኗኗር ሁኔታዎች በመሻሻላቸው ምክንያት ይህ ቁጥር ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ መግለጫ በሳይንስ ሊረጋገጥ ስላልቻለ ብቻ ስህተት መሆን አለበት ማለት አይቻልም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ልጆች ምድር ሉል መሆኗን በጠፈር ላይ ሆነው ለማየት ከመቻላቸው በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ምድር ክበብ” ተናግሯል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰር አይዛክ ኒውተን ፕላኔቶች ምሕዋራቸውን ጠብቀው የሚዞሩት በስበት ኃይል እንደሆነ ገልጿል