ምዕራፍ አሥራ ስድስት
ቤተሰባችሁ ዘላቂ ተስፋ እንዲጨብጥ አድርጉ
1. ይሖዋ ቤተሰብን ሲመሠርት ዓላማው ምን ነበር?
ይሖዋ አዳምና ሔዋንን በጋብቻ ባጣመራቸው ጊዜ አዳም በጥንታዊነቱ ቀደምት ሥፍራ የያዘውን የዕብራይስጥ ግጥም በመግጠም ደስታውን ገልጿል። (ዘፍጥረት 2:22, 23) ይሁን እንጂ ፈጣሪ ጋብቻን ሲመሠርት ዓላማው ሰብዓዊ ልጆቹን ማስደሰት ብቻ አልነበረም። የትዳር ጓደኛሞችና ቤተሰቦች ፈቃዱን እንዲያደርጉ ይፈልግ ነበር። የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች እንዲህ አላቸው:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ሥራ ነበር! አዳምና ሔዋን የይሖዋን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ፈጽመው ቢሆን ኖሮ እነርሱም ሆኑ የሚወልዷቸው ልጆች ምንኛ ደስተኞች በሆኑ ነበር!
2, 3. በዛሬው ጊዜ ቤተሰቦች ከሁሉ የላቀውን ደስታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
2 በዛሬው ጊዜም ቢሆን ቤተሰቦች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ተባብረው ሲሠሩ እጅግ ደስተኞች ይሆናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆን፣” NW] ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ለአምላክ ያደረና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የይሖዋ መመሪያ የሚከተል ቤተሰብ ‘በአሁኑ ሕይወት’ ደስታ ያገኛል። (መዝሙር 1:1-3፤ 119:105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) መላው የቤተሰቡ አባላት ይቅርና አንዱ የቤተሰቡ አባል ብቻ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ቢያውል የተሻሉ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።
3 ለቤተሰብ ደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተብራርተዋል።
ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በመጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተጠቀሱ አስተውላችሁ ይሆናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በተለያዩ የቤተሰብ ሕይወት ዘርፎች ለሁሉም የሚጠቅሙ ጠንካራ እውነታዎችን የሚወክሉ በመሆናቸው ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ለማዋል የሚጥር ቤተሰብ ለአምላክ ማደር በእርግጥም ‘ለአሁኑ ሕይወት ተስፋ እንዳለው’ ይገነዘባል። ከእነዚህ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አራቱን እስቲ ደግመን እንመልከት።ራስን መግዛት የሚያስገኘው ጥቅም
4. በትዳር ውስጥ ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ንጉሥ ሰሎሞን “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 25:28፤ 29:11) ትዳራቸው አስደሳች እንዲሆን የሚፈልጉ ሁሉ ‘መንፈሳቸውን መከልከላቸው’ ማለትም ራሳቸውን መግዛታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እንደ ንዴት ወይም የፆታ ብልግና የመፈጸም ፍላጎትን ለመሰሉ ጎጂ ስሜቶች እጅ መስጠት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመጠገን ብዙ ዓመታት ሊወስድ ይችላል፤ ለዚያውም ሊጠገን ከቻለ።
5. ፍጹም ያልሆነ ሰው ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝለታል?
5 እርግጥ ነው፣ የትኛውም የአዳም ዘር ፍጹም ያልሆነውን ሥጋውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይችልም። (ሮሜ 7:21, 22) ያም ሆኖ ግን ራስን መግዛት የመንፈስ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ ይህን ባሕርይ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ፣ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ፣ እንዲሁም ይህን ባሕርይ ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር የምንወዳጅና ይህን ባሕርይ ከማያሳዩ ሰዎች ደግሞ የምንርቅ ከሆነ የአምላክ መንፈስ በውስጣችን ራስን የመግዛት ባሕርይ ያፈራል። (መዝሙር 119:100, 101, 130፤ ምሳሌ 13:20፤ 1 ጴጥሮስ 4:7) እንዲህ ማድረጋችን ዝሙት እንድንፈጽም በምንፈተንበት ጊዜም እንኳ ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በሌሎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንቆጠባለን፤ የአልኮል ሱስንም እናስወግዳለን ወይም ድል እናደርገዋለን። የሚያናድዱና አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይበልጥ በተረጋጋ መንፈስ ችግሩን ለመፍታት እንጥራለን። ልጆችን ጨምሮ ሁላችንም ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነ የመንፈስ ፍሬ እንኮትኩት።—መዝሙር 119:1, 2
የራስነትን ሥልጣን በተመለከተ ተገቢ አመለካከት መያዝ
6. (ሀ) መለኮታዊው የራስነት ሥልጣን ተዋረድ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ወንድ የራስነት ሥልጣኑ ለቤተሰቡ ደስታ እንዲያስገኝ ከፈለገ ምን ማስታወስ ይኖርበታል?
6 በጣም አስፈላጊ የሆነው ሁለተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ለራስነት ሥልጣን እውቅና መስጠት ነው። ጳውሎስ ትክክለኛውን የሥልጣን ተዋረድ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 11:3) ይህ ማለት አንድ ወንድ ቤተሰቡን በግንባር ቀደምትነት ይመራል፣ ሚስቱ በታማኝነት ትደግፈዋለች፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው ይታዘዛሉ ማለት ነው። (ኤፌሶን 5:22-25, 28-33፤ 6:1-4) ሆኖም የራስነት ሥልጣን ደስታ ሊያስገኝ የሚችለው በተገቢው መንገድ ሲሠራበት ብቻ እንደሆነ ልብ በሉ። ለአምላክ ያደሩ ባሎች የራስነት ሥልጣን አምባገነናዊነት እንዳልሆነ ያውቃሉ። የእነርሱ ራስ የሆነውን ኢየሱስን ይኮርጃሉ። ኢየሱስ ‘ከሁሉ በላይ ራስ’ የሚሆን ቢሆንም እንኳ ወደ ምድር የመጣው ‘ሊያገለግል እንጂ እንዲያገለግሉት አይደለም።’ (ኤፌሶን 1:22፤ ማቴዎስ 20:28) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ወንድ የራስነት ሥልጣኑን ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ሚስቱና ልጆቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ይጠቀምበታል።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5
7. አንዲት ሚስት በቤተሰብ ውስጥ አምላክ የሰጣትን ድርሻ መወጣት እንድትችል የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይረዷታል?
7 ለአምላክ ያደረች ሚስት ደግሞ ባሏን አትቀናቀንም ወይም ለመግዛት አትጥርም። ባሏን መደገፍና ከእሱ ጋር ተባብራ መሥራት ያስደስታታል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ ሚስት የባሏ “ንብረት” እንደሆነች አድርጎ ይገልጻል፤ ይህም ባሏ የእሷ ራስ መሆኑን በማያሻማ መንገድ የሚያሳይ ነው። (ዘፍጥረት 20:3 NW) በጋብቻ አማካኝነት ‘በባልዋ ሕግ’ ታስራለች። (ሮሜ 7:2) ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ረዳት” እና “ማሟያ” ብሎ ይጠራታል። (ዘፍጥረት 2:20 NW) ባሏ የሚጎድሉትን ባሕርያትና ችሎታዎች ታሟላለች፤ የሚያስፈልገውንም እርዳታ ትሰጠዋለች። (ምሳሌ 31:10-31) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሚስት ከባሏ ጎን ሆና የምትሠራ “ባልንጀራ” እንደሆነች ይገልጻል። (ሚልክያስ 2:14) እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ባልና ሚስት የየራሳቸውን ቦታ ለይተው እንዲያውቁና አንዳቸው ለሌላው ተገቢ አክብሮት እንዲያሳዩ ይረዷቸዋል።
‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’
8, 9. በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሁሉ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚረዷቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግለጹ።
8 የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ አስፈላጊነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ለምን? ሰዎች እርስ በርስ ሲነጋገሩና ሲደማመጡ ችግሮችን በተሻለ ሁኔታ መፍታት የሚቻል በመሆኑ ነው። የሐሳብ ልውውጥ ለመሄጃም ለመመለሻም እንደሚያገለግል መንገድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን” ሲል ገልጾታል።—ያዕቆብ 1:19
9 እንዴት መናገር እንዳለብን ማሰቡም በጣም አስፈላጊ ነው። ያልታሰበባቸውና ንትርክ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቃላት መሰንዘር ወይም ክፉኛ መተቸት ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ አያስችልም። (ምሳሌ 15:1፤ 21:9፤ 29:11, 20) የምንናገረው ነገር ትክክል በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ርኅራኄ በጎደለው፣ በኩራት መንፈስ ወይም አሳቢነት በሌለው መንገድ የምንናገር ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አነጋገራችን ጣዕም ያለው ማለትም ‘በጨው የተቀመመ’ መሆን አለበት። (ቆላስይስ 4:6) የምንናገረው ነገር ‘በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ እንኮይ’ መሆን አለበት። (ምሳሌ 25:11) በጥሩ ሁኔታ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ያዳበሩ ቤተሰቦች ደስታ ማግኘት የሚችሉበትን ትልቅ እርምጃ ወስደዋል ማለት ይቻላል።
ፍቅር የሚጫወተው ትልቅ ሚና
10. በትዳር ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነው የፍቅር ዓይነት የትኛው ነው?
10 “ፍቅር” የሚለው ቃል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከዳር እስከ ማቴዎስ 22:37-39) ይሖዋ ለሰው ልጆች ያሳየው ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 3:16) ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን ይህን ፍቅር ማሳየት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!—1 ዮሐንስ 4:19
ዳር በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። በዋነኛነት የተጠቀሰው የፍቅር ዓይነት የቱ እንደሆነ ታስታውሳላችሁ? ፆታዊ ፍቅር (በግሪክኛ ኤሮስ) በትዳር ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው፤ በተጨማሪም ስኬታማ በሆኑ ትዳሮች ውስጥ በባልና ሚስት መካከል የጠበቀ ፍቅርና ወዳጅነት (በግሪክኛ ፊሊያ) እየዳበረ ይሄዳል። ሆኖም ከእነዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው አጋፔ በተባለው የግሪክኛ ቃል የተወከለው የፍቅር ዓይነት ነው። ይህ ፍቅር ለይሖዋ፣ ለኢየሱስና ለሰዎች የምናዳብረው ፍቅር ነው። (11. ፍቅር ለትዳር ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
11 ይህ የላቀ የፍቅር ዓይነት በትዳር ውስጥ በእርግጥም “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” ነው። (ቆላስይስ 3:14 NW) ባልና ሚስትን በአንድነት የሚያጣምር ከመሆኑም በላይ አንዳቸው ለሌላው እንዲሁም ለልጆቻቸው የሚጠቅመውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ያሳድርባቸዋል። ቤተሰቦች ከባድ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው ፍቅር ችግሮቹን በአንድነት ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ባልና ሚስት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ፍቅር እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉና አንዳቸው ሌላውን ከፍ አድርገው መመልከታቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። “ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም፣ . . . ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4-8
12. ባለ ትዳሮች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ትዳራቸውን የሚያጠነክረው ለምንድን ነው?
12 የትዳር አንድነት በትዳር ጓደኛሞቹ መካከል ባለው ፍቅር ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ሲጠብቅ በጣም ጠንካራ ይሆናል። (መክብብ 4:9-12) ለምን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት ልጆቻቸው ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ ማሰልጠን ያለባቸው ስለሚወዷቸው ብቻ ሳይሆን የይሖዋም ትእዛዝ በመሆኑ ጭምር መሆን አለበት። (ዘዳግም 6:6, 7) ከፆታ ብልግና መራቅ ያለባቸው እርስ በርሳቸው ስለሚዋደዱ ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ይህን ማድረግ ያለባቸው ‘በሴሰኞችና በአመንዝሮች ላይ ለሚፈርደው’ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር መሆን አለበት። (ዕብራውያን 13:4) አንደኛው የትዳር ጓደኛ በትዳር ውስጥ ከባድ ችግሮች በሚፈጥርበት ጊዜ እንኳ ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ለይሖዋ ያለው ፍቅር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተሉን እንዲቀጥል ሊገፋፋው ይገባል። በመካከላቸው ያለው ፍቅር ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር እንዲጠናከር ያደረጉ ቤተሰቦች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው!
የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ቤተሰብ
13. እያንዳንዱ ግለሰብ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚወስደው ቁርጥ ውሳኔ ዓይኑ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር የሚረዳው እንዴት ነው?
13 አንድ ክርስቲያን መላ ሕይወቱ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው። (መዝሙር 143:10) ለአምላክ ያደሩ መሆን ማለት ደግሞ ይህ ነው። ቤተሰቦች የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸው ዓይናቸው ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ሰውን ከአባቱ፣ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፣ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።” (ማቴዎስ 10:35, 36) ኢየሱስ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት ብዙ ተከታዮቹ በቤተሰባቸው አባሎች ስደት ደርሶባቸዋል። እንዴት ያለ አሳዛኝና መንፈስን የሚረብሽ ሁኔታ ነው! ሆኖም የቤተሰብ ዝምድና ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ካለን ፍቅር ሊበልጥብን አይገባም። (ማቴዎስ 10:37-39) አንድ ሰው ከቤተሰቡ የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ በጽናት ከተቋቋመ ተቃዋሚዎቹ ለአምላክ ያደሩ መሆን የሚያስገኛቸውን ጥሩ ውጤቶች በመመልከት ሊለወጡ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:12-16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ይህ ባይሆን እንኳ በተቃውሞ ሳቢያ አምላክን ከማገልገል በመታቀብ የሚገኝ ምንም ዘላቂ ጥቅም የለም።
14. ወላጆች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ለልጆቻቸው የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ነገር እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
14 የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ወላጆች ትክክለኛ ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ መዋዕለ ንዋይ አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ እናም በእርጅና ዘመናቸው እንደሚጦሯቸው ይተማመናሉ። ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን መጦራቸው ተገቢና ትክክል ቢሆንም ወላጆች ይህን በአእምሯቸው በመያዝ ልጆቻቸው የፍቅረ ነዋይ ጎዳና እንዲከተሉ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው አይገባም። ወላጆች ልጆቻቸውን ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለቁሳዊ ንብረት የበለጠ ቦታ እንዲሰጡ አድርገው የሚያሳድጓቸው ከሆነ ምንም የሚያስገኙላቸው ጥቅም የለም።—1 ጢሞቴዎስ 6:9
15. የጢሞቴዎስ እናት ኤውንቄ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆና ልትጠቀስ የምትችለው እንዴት ነው?
15 በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው የጳውሎስ ጓደኛ የነበረው የወጣቱ ጢሞቴዎስ እናት የሆነችው ኤውንቄ ናት። (2 ጢሞቴዎስ 1:5) ምንም እንኳ ኤውንቄ የማያምን ባል የነበራት ቢሆንም ከጢሞቴዎስ አያት ከሎይድ ጋር ሆና ጢሞቴዎስ ለአምላክ ያደረ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ አሳድጋዋለች። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ጢሞቴዎስ ለአካለ መጠን ሲደርስ ከቤተሰቡ ተለይቶ የጳውሎስ ሚስዮናዊ ጓደኛ በመሆን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንዲሳተፍ ፈቅዳለታለች። (ሥራ 16:1-5) ልጅዋ የተዋጣለት ሚስዮናዊ ሲሆን ምንኛ ተደስታ ይሆን! በዐዋቂነት ዕድሜው ለአምላክ ያደረ መሆኑ በልጅነቱ ጥሩ ማሠልጠኛ እንዳገኘ በሚገባ ይመሠክራል። ኤውንቄ ምንም እንኳ ልጅዋ አብሯት ባለመኖሩ ቅር ልትሰኝ ብትችልም የጢሞቴዎስን የታማኝነት አገልግሎት በተመለከተ በምትሰማቸው ሪፖርቶች እንደተደሰተችና እንደረካች ጥርጥር የለውም።—ፊልጵስዩስ 2:19, 20
ቤተሰብና የወደፊት ዕጣችሁ
16. ኢየሱስ ከአንድ ልጅ የሚጠበቅ ምን ተገቢ አሳቢነት አሳይቷል? ሆኖም ዋነኛ ዓላማው ምን ነበር?
16 ኢየሱስ ያደገው ፈሪሃ አምላክ በነበረው ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላም አንድ ልጅ ለእናቱ ሊኖረው የሚገባውን አሳቢነት አሳይቷል። (ሉቃስ 2:51, 52፤ ዮሐንስ 19:26) ይሁን እንጂ ዋነኛ ዓላማው የአምላክን ፈቃድ ማሟላት ነበር፤ ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን በር መክፈትንም ይጠይቅበት ነበር። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ቤዛ አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ፈጽሟል።—ማርቆስ 10:45፤ ዮሐንስ 5:28, 29
17. የኢየሱስ የታማኝነት አካሄድ የአምላክን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሰዎች ምን ታላላቅ ተስፋዎች አስገኝቷል?
17 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ከሞት በማስነሣት ሰማያዊ ሕይወት የሰጠው ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ በሰማያዊው መንግሥት ላይ ንጉሥ አድርጎ በመሾም ታላቅ ሥልጣን አጎናጽፎታል። (ማቴዎስ 28:18፤ ሮሜ 14:9፤ ራእይ 11:15) የኢየሱስ መሥዋዕት የተወሰኑ ሰዎች ከእሱ ጋር በዚያ መንግሥት ላይ የመግዛት መብት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የተቀሩት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችም ዳግመኛ ወደ ገነትነት በምትለወጠው ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን በር ከፍቷል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4፤ 21:3-5፤ 22:1-4) በዛሬው ጊዜ ይህን እጅግ አስደሳች የሆነ ምሥራች ለሰዎች የመንገር ታላቅ መብት አግኝተናል።—ማቴዎስ 24:14
18. ለቤተሰቦችም ሆነ ለግለሰቦች ምን ማሳሰቢያና ማበረታቻ ተሰጥቷል?
1 ዮሐንስ 2:17) ስለዚህ ልጅም ሆናችሁ ወላጅ፣ ባልም ሆናችሁ ሚስት፣ ልጆች ያላችሁ ነጠላዎችም ሆናችሁ የሌላችሁ፣ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ጣሩ። ከባድ ተጽዕኖ ሥር በምትወድቁበትና አስከፊ ችግሮች በሚያጋጥሟችሁ ጊዜም እንኳ የሕያው አምላክ አገልጋዮች መሆናችሁን ፈጽሞ አትዘንጉ። በመሆኑም የምታደርጓቸው ነገሮች ይሖዋን ደስ የሚያሰኙ ይሁኑ። (ምሳሌ 27:11) ምግባራችሁ በአሁኑ ጊዜ ደስታ በመጪው አዲስ ዓለም ደግሞ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁ እንዲሆን እንመኛለን!
18 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳመለከተው ለአምላክ ያደሩ መሆን በ“ሚመጣው” ሕይወት እነዚህን በረከቶች የመውረስ ተስፋ ያስገኛል። ደስታ ማግኘት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም! ‘ዓለምና ምኞቱ እንደሚያልፉ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም እንደሚኖር’ አስታውሱ። (