ምዕራፍ 22
ምሥራቹን ለሌሎች መናገር የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ስትማር ‘ይህን ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል!’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎ፣ ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል! ሆኖም የተማርከውን ነገር ለሌሎች መናገር ሊያስፈራህ ይችላል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ፍርሃትህን አሸንፈህ ምሥራቹን ለሌሎች መናገር የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1. የተማርከውን ነገር ለምታውቃቸው ሰዎች መናገር የምትችለው እንዴት ነው?
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” ብለው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 4:20) ለተማሩት እውነት ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራቸው ይህን እውነት ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር ፈልገው ነበር። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ከሆነ የተማርከውን ነገር ለቤተሰቦችህና ለጓደኞችህ በአክብሮት መናገር የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች ፈልግ።—ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።
ምሥራቹን መናገር መጀመር የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች
-
ከቤተሰብህ ጋር ስትጨዋወት ‘በዚህ ሳምንት የተማርኩትን ደስ የሚል ነገር ልንገራችሁ’ በማለት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ንገራቸው።
-
ለታመመ ወይም በጭንቀት ለተዋጠ ጓደኛህ አንድ የሚያበረታታ ጥቅስ አንብብለት።
-
የሥራ ባልደረቦችህ ‘ሳምንቱ እንዴት ነበር?’ ብለው ሲጠይቁህ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራምህ ላይ ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ የተማርከውን ነገር ንገራቸው።
-
ለጓደኞችህ jw.org ድረ ገጽን አሳያቸው።
-
ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራምህ ላይ እንዲገኙ ጋብዝ፤ ወይም jw.org ላይ የሚገኘውን ቅጽ ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር መጠየቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳያቸው።
2. ከጉባኤው ጋር አብረህ ለመስበክ ግብ ማውጣትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን ለሚያውቋቸው ሰዎች ብቻ በመናገር አልተወሰኑም። ኢየሱስ የስብከት ተልእኮ በሰጣቸው ጊዜ ‘እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ከተማ ሁሉ ሁለት ሁለት አድርጎ ልኳቸዋል።’ (ሉቃስ 10:1) በተደራጀ መንገድ ያከናወኑት ይህ የስብከት ሥራ ሌሎች በርካታ ሰዎች ምሥራቹን የሚሰሙበት አጋጣሚ ፈጥሯል። በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ አብረው መስበካቸው ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ሉቃስ 10:17) አንተስ ልክ እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከጉባኤው ጋር አብረህ ለመስበክ ግብ ማውጣት ትችል ይሆን?
ጠለቅ ያለ ጥናት
ፍርሃትህን ማሸነፍና ምሥራቹን በመስበክ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
3. ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሆናል
አንዳንዶች መስበክ ቢፈልጉም ሌሎች ለእነሱ ስለሚኖራቸው አመለካከት ወይም ስለሚሰጧቸው ምላሽ ሲያስቡ ፍርሃት ይሰማቸዋል።
-
የተማርከውን ነገር ለሌሎች መናገር ያስፈራሃል? እንዲህ የሚሰማህ ለምንድን ነው?
ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
በቪዲዮው ላይ የታዩት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው?
ኢሳይያስ 41:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
መስበክ የሚያስፈራህ ከሆነ መጸለይህ የሚረዳህ እንዴት ነው?
ይህን ታውቅ ነበር?
ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል መቼም ቢሆን ምሥራቹን ለሌሎች መናገር እንደማይችሉ ይሰማቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሰርጌ የተባለ ሰው የዋጋ ቢስነት ስሜት ስለሚሰማው ሰዎችን ቀርቦ ማነጋገር ይከብደው ነበር። በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “ፍርሃት ቢያድርብኝም የተማርኳቸውን ነገሮች ለሌሎች መናገር ጀመርኩ። በጣም የሚያስገርመው፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች መናገሬ በራስ የመተማመን ስሜቴን ከፍ አደረገልኝ። እንዲሁም የማምንባቸው አዳዲስ እውነቶች በልቤ ውስጥ ሥር እንዲሰዱ አደረጋቸው።”
4. አክብሮት አሳይ
ለሌሎች ምሥራቹን ስትናገር የምትናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን የምትናገርበት መንገድም ሊያሳስብህ ይገባል። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 2:24ን እና 1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
-
ከሌሎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስትነጋገር በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
-
አንዳንድ የቤተሰብህ አባላት ወይም ጓደኞችህ በምትናገረው ነገር ላይስማሙ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ምን ልታደርግስ አይገባም?
-
ሰዎች የምትናገረውን ነገር እንዲቀበሉ ከመጫን ይልቅ በዘዴ አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ የተሻለ የሚሆነው ለምንድን ነው?
5. ምሥራቹን ለሌሎች መናገር ደስታ ያስገኛል
ይሖዋ ለኢየሱስ ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ሰጥቶት ነበር። ኢየሱስ ለዚህ ሥራ ምን አመለካከት ነበረው? ዮሐንስ 4:34ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
-
ጥሩ ምግብ መመገብ በሕይወት እንድንቀጥልና ደስተኛ እንድንሆን ይረዳናል። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን፣ ለምሳሌ ምሥራቹን መስበክን ከምግብ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?
-
ምሥራቹን መስበክ አስደሳች የሆነው ለምን ይመስልሃል?
ጠቃሚ ምክር
-
በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ፣ ውይይት ለመጀመር የሚረዱ ሐሳቦች ሲቀርቡ በትኩረት ተከታተል።
-
በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተማሪ ክፍል ለማቅረብ መመዝገብ ትችል እንደሆነ አስብበት። የተማሪ ክፍል ማቅረብህ የተማርከውን ነገር ለሌሎች ለመናገር ይበልጥ ዝግጁ እንድትሆን ይረዳሃል።
-
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙትን “አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ” ወይም “አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ?” የሚሉትን ክፍሎች ተጠቅመህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ወይም የተቃውሞ ሐሳቦች መልስ መስጠት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተለማመድ።
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “ምን አዲስ ነገር አለ?”
-
ይህን አጋጣሚ ተጠቅመህ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ላይ የተማርከውን ነገር ለግለሰቡ ልትነግረው የምትችለው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ
ምሥራቹን መስበክ ደስታ ያስገኛል፤ ደግሞም የተማርከውን ነገር ለሌሎች መናገር ከምታስበው በላይ ቀላል ሊሆን ይችላል።
ክለሳ
-
ምሥራቹን ለሌሎች ለመናገር የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?
-
ምሥራቹን ለሌሎች ስትናገር አክብሮት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
-
ምሥራቹን መስበክ የሚያስፈራህ ከሆነ ፍርሃትህን ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?
ምርምር አድርግ
የjw.org አድራሻ ካርድን ተጠቅመህ ምሥራቹን መናገር የምትችልባቸው አራት ቀላል መንገዶች።
ምሥራቹን ለመስበክ የሚረዱህ አራት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
ልጆችም እንኳ ምሥራቹን በድፍረት መናገር ይችላሉ። በዚህ ረገድ የሚያበረታታቸው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው?
ይሖዋን ለማያውቁ የቤተሰብህ አባላት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር የምትችለው እንዴት ነው?