በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 38

በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት ይኑርህ

በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት ይኑርህ

ሕይወት በብዙ አስደሳች ነገሮች የተሞላ ነው። ችግር ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ደስታ የሚሰጡን አንዳንድ ነገሮች አይጠፉም። በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አድናቆታችንን እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያትስ ምንድን ነው?

1. ለሕይወት አድናቆት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

ለሕይወት አድናቆት ሊኖረን የሚገባው አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ የሰጠን ስጦታ ስለሆነ ነው። ‘የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነው’፤ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው እሱ ነው። (መዝሙር 36:9) “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው” ይሖዋ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:25, 28) ይሖዋ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉንን ነገሮችም ይሰጠናል። ከዚህም ባለፈ በሕይወታችን ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያቀርብልናል።—የሐዋርያት ሥራ 14:17⁠ን አንብብ።

2. የይሖዋ ስጦታ ለሆነው ሕይወት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት የጀመረው በእናትህ ማህፀን ውስጥ ከተፀነስክበት ጊዜ አንስቶ ነው። የአምላክ አገልጋይ የነበረው ዳዊት “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ” በማለት በመንፈስ መሪነት ተናግሯል። (መዝሙር 139:16) የአንተ ሕይወት በይሖዋ ፊት በጣም ውድ ነው። (ማቴዎስ 10:29-31⁠ን አንብብ።) የሌላን ሰው ሌላው ቀርቶ የራስን ሕይወት ሆን ብሎ ማጥፋት አምላክን በጣም ያሳዝነዋል። a (ዘፀአት 20:13) ሳያስፈልግ ሕይወታችንን አደጋ ላይ መጣላችን ወይም የሌሎችን ሕይወት ከአደጋ ለመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረጋችንም አምላክን ያሳዝነዋል። የራሳችንን ሕይወት ከአደጋ በመጠበቅና ለሌሎች ሕይወት አክብሮት በማሳየት ግሩም ለሆነው የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።

ጠለቅ ያለ ጥናት

ስጦታ ለሆነው ሕይወት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።

3. ጤናህን ተንከባከብ

የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ራሳቸውን ያቀረቡ ክርስቲያኖች መላ ሕይወታቸውን ይሖዋን ለማገልገል ይጠቀሙበታል። ሰውነታቸውን ለአምላክ መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡ ያህል ነው። ሮም 12:1, 2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ጤናህን እንድትንከባከብ ሊያነሳሳህ የሚገባው ምንድን ነው?

  • እንዲህ ማድረግ የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

4. ጉዳት ወይም ሞት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ አድርግ

መጽሐፍ ቅዱስ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ከማድረግ እንድንቆጠብ ይነግረናል። ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅ ማድረግ የምንችላቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ

ምሳሌ 22:3ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ሁኔታዎች ሥር ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ መጠበቅ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ተወያዩ፦

  • በቤታችሁ

  • በሥራ ቦታችሁ

  • በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ስትካፈሉ

  • ስታሽከረክሩ ወይም መጓጓዣ ስትጠቀሙ

5. በማህፀን ውስጥ ላለ ፅንስ ሕይወት አክብሮት ይኑርህ

ዳዊት ይሖዋ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ሕይወትና እድገት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከት ገልጿል። መዝሙር 139:13-17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በይሖዋ አመለካከት የአንድ ሰው ሕይወት የሚጀምረው ሲፀነስ ነው ወይስ ሲወለድ?

ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለእናቶችና በማህፀን ውስጥ ላሉ ልጆች ጥበቃ ያደርግ ነበር። ዘፀአት 21:22, 23, 25ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ሳያስበው በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ሕይወት ላጠፋ ሰው ምን አመለካከት አለው?

  • ሆን ብሎ እንዲህ ለሚያደርግ ሰው ምን አመለካከት የሚኖረው ይመስልሃል? b

  • አምላክ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስላለው አመለካከት ምን ይሰማሃል?

ቪዲዮውን ተመልከቱ።

ለሕይወት ከፍተኛ አክብሮት ያላት ሴትም እንኳ ውርጃ ከመፈጸም ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላት ሊሰማት ይችላል። ኢሳይያስ 41:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • አንዲት ሴት ውርጃ እንድትፈጽም ጫና በሚደረግባት ጊዜ ማን ሊረዳት ይችላል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “አንዲት ሴት ውርጃ መፈጸም ከፈለገች ትችላለች፤ በራሷ ሰውነት ላይ መወሰን መብቷ ነው።”

  • ይሖዋ የእናትየውንም ሆነ በማህፀኗ ውስጥ ያለውን ፅንስ ሕይወት ከፍ አድርጎ ይመለከታል ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት የይሖዋ ስጦታ ስለሆነ ለዚህ ስጦታ ፍቅርና አክብሮት ማሳየት እንዳለብን ያስተምረናል፤ እንዲሁም የእኛንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ከማድረግ እንድንቆጠብ ያሳስበናል።

ክለሳ

  • ይሖዋ ለሰዎች ሕይወት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ ሆን ብሎ ሕይወት ለሚያጠፋ ሰው ምን አመለካከት አለው?

  • አንተ በግልህ ለሕይወት አድናቆት እንዲኖርህ የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ይሖዋ ሕይወትን ስጦታ አድርጎ ስለሰጠን አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 141—ሕይወት ተአምር ነው (2:41)

አምላክ ቀደም ሲል ውርጃ የፈጸሙ ሴቶችን ይቅር ይላል?

“መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውርጃ ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

አምላክ ለሕይወት ያለውን አመለካከት ማወቃችን በመዝናኛ ምርጫችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይገባል?

“አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ልትካፈል ይገባል?” (ንቁ! ላይ የወጣ ርዕስ)

አንድ ሰው ራሱን የማጥፋት ሐሳብ ቢመጣበትስ? መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳው ይችላል?

“ራሴን የማጥፋት ሐሳብ ሲመጣብኝ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

a ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ከልብ ያስባል። (መዝሙር 34:18) አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት የሚገፋፋውን የስሜት ሥቃይ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ የሚሰማውን ሰው መርዳት ይፈልጋል። አምላክ የሚሰጠው እርዳታ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስቡ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚጠቅም ለማየት በዚህ ምዕራፍ ውስጥ “ምርምር አድርግ” በሚለው ክፍል ሥር የተጠቀሰውን “ራሴን የማጥፋት ሐሳብ ሲመጣብኝ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b ቀደም ሲል ውርጃ የፈጸሙ ሰዎች ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ሊዋጡ አይገባም፤ ይሖዋ ይቅር ሊላቸው ይችላል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ ምዕራፍ ውስጥ “ምርምር አድርግ” በሚለው ክፍል ሥር የተጠቀሰውን “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውርጃ ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።