ተጨማሪ ሐሳብ
1. ታላቂቱ ባቢሎን የምትወክለው ማንን ነው?
“ታላቂቱ ባቢሎን” የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ እንደምትወክል እንዴት እናውቃለን? (ራእይ 17:5) እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦
-
በዓለም ዙሪያ ተጽዕኖ ታሳድራለች። ታላቂቱ ባቢሎን ‘በሕዝብና በብሔራት’ ላይ እንደተቀመጠች ተገልጿል። በተጨማሪም “በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት” እንዳላት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ራእይ 17:15, 18
-
የፖለቲካ ወይም የንግድ ድርጅትን ልታመለክት አትችልም። “የምድር ነገሥታት” እና “ነጋዴዎች” እሷ ስትጠፋ አብረው አልጠፉም።—ራእይ 18:9, 15
-
የአምላክን ስም ታሰድባለች። ለገንዘብ ወይም ለሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ስትል ከመንግሥታት ጋር ጥምረት ስለምትፈጥር “አመንዝራ” ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 17:1, 2) ብሔራትን ሁሉ አሳስታለች። በተጨማሪም ለብዙዎች ሞት ተጠያቂ ናት።—ራእይ 18:23, 24
2. መሲሑ የሚገለጠው መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑ እስኪገለጥ ድረስ 69 ሳምንታት እንደሚያልፉ አስቀድሞ ተናግሯል።—ዳንኤል 9:25ን አንብብ።
-
እነዚህ 69 ሳምንታት የሚቆጠሩት ከመቼ ጀምሮ ነው? ከ455 ዓ.ዓ. አንስቶ ነው። በዚያ ዓመት ገዢው ነህምያ ኢየሩሳሌምን “ለማደስና መልሶ ለመገንባት” ወደዚያ ሄደ።—ዳንኤል 9:25፤ ነህምያ 2:1, 5-8
-
የ69ኙ ሳምንታት ርዝማኔ ምን ያህል ነው? በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ፣ አንድ ቀን አንድ ዓመትን ያመለክታል። (ዘኁልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6) በዚህ መሠረት እያንዳንዱ ሳምንት የሰባት ዓመት ርዝማኔ አለው። በመሆኑም በዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሱት 69 ሳምንታት 483 ዓመታት (69 ሳምንታት x 7 ቀናት) ይሆናሉ ማለት ነው።
-
እነዚህ 69 ሳምንታት የሚያበቁት መቼ ነው? ከ455 ዓ.ዓ. ተነስተን 483 ዓመታትን ስንቆጥር 29 ዓ.ም. ላይ እንደርሳለን። a ኢየሱስ የተጠመቀውና መሲሕ የሆነው በዚሁ ዓመት ነው!—ሉቃስ 3:1, 2, 21, 22
3. ደምን በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎች
አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች የራሱን የታካሚውን ደም መጠቀምን ይጠይቃሉ። ከእነዚህ መካከል ደምን መለገስ ወይም የራስን ደም ቀዶ ሕክምና ከመደረጉ በፊት ማስቀመጥ ይገኝበታል። እንዲህ ያሉት አማራጮች በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም።—ዘዳግም 15:23
ሆኖም ክርስቲያኖች ሊቀበሏቸው የሚችሉ ሌሎች አማራጮች አሉ። ከእነዚህ መካከል የደም ምርመራ፣ ሂሞዳያሊሲስ፣ ሂሞዳይሉሽን፣ ሴል ሳልቬጅ ወይም እንደ ልብና ሳንባ ሆኖ የሚያገለግል መሣሪያ መጠቀም ይገኙበታል። b እያንዳንዱ ክርስቲያን ቀዶ ሕክምና፣ የጤና ምርመራ ወይም ሌላ ዓይነት ሕክምና እየተደረገለት ባለበት ወቅት የራሱ ደም ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በተመለከተ የግሉን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። እነዚህ ሕክምናዎች የሚሰጡበት መንገድ ከሐኪም ሐኪም ሊለያይ ይችላል። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ሕክምናዎችን ከመቀበሉ በፊት ደሙ ጥቅም ላይ የሚውለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት። የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሊያስብባቸው ይገባል፦
-
የተወሰነ ደም ከሰውነቴ ወጥቶ በሌላ መስመር እንዲያልፍ የሚደረግ፣ ምናልባትም ዝውውሩ ለተወሰነ ጊዜ የሚቋረጥ ቢሆንስ? ይህን ደም የሰውነቴ ክፍል እንደሆነና ‘መሬት ላይ መፍሰስ’ እንደማያስፈልገው አድርጌ ለመመልከት ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል?—ዘዳግም 12:23, 24
-
በሕክምና ወቅት ከሰውነቴ ውስጥ የተወሰነ ደም ተወስዶ አንድ ዓይነት ለውጥ ከተደረገበት በኋላ እንደገና ወደ ሰውነቴ እንዲገባ የሚደረግ ወይም ቀዶ ሕክምና በተደረገለት የሰውነቴ ክፍል ላይ የሚቀባ ቢሆንስ? እንዲህ ዓይነቱን ሕክምና ለመቀበል በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል?
4. ከትዳር ጓደኛ መለያየት
የአምላክ ቃል ባለትዳሮች መለያየት እንደሌለባቸው ይናገራል፤ በተጨማሪም መለያየታቸው ድጋሚ ለማግባት ነፃነት እንደማይሰጣቸው ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) ይሁንና አንዳንድ ክርስቲያኖች በሚከተሉት ሁኔታዎች የተነሳ ለመለያየት ሊወስኑ ይችላሉ፦
-
መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆን፦ አንድ ባል ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ቤተሰቡ ለከባድ ችግር ቢዳረግ።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
- ከባድ አካላዊ ጥቃት፦ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ጤንነቱን ይባስ ብሎም ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል የኃይል ጥቃት እንደተሰነዘረበት ቢሰማው።—
-
ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ፦ በትዳር ጓደኛው ምክንያት ፈጽሞ ይሖዋን ማገልገል የማይችልበት ሁኔታ ቢፈጠር።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
5. በዓላት
ክርስቲያኖች ይሖዋን የሚያሳዝኑ በዓላትን አያከብሩም። ሆኖም ከእነዚህ በዓላት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎችን በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት። የሚከተሉትን ሁኔታዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት፦
-
አንድ ሰው “እንኳን አደረሰህ” ቢልህ። ግለሰቡን “አመሰግናለሁ” ልትለው ትችላለህ። ይበልጥ ማወቅ ከፈለገ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅመህ በዓሉን የማታከብርበትን ምክንያት ንገረው።
-
የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያላቸው ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው በበዓል ቀን ከዘመድ አዝማድ ጋር ምሳ ወይም ራት እንዲበሉ ቢጠይቃቸው። ግብዣውን ለመቀበል ሕሊናቸው ይፈቅድላቸው ይሆናል፤ ሆኖም በግብዣው ላይ ከሐሰት አምልኮ ጋር የተያያዙ ልማዶች የሚኖሩ ከሆነ በእነዚህ ልማዶች እንደማይካፈሉ ለትዳር ጓደኛቸው አስቀድመው ሊነግሩ ይችላሉ።
-
አሠሪህ በበዓል ሰሞን ጉርሻ ቢሰጥህ። ጉርሻውን አልቀበልም ማለት ይኖርብሃል? ላይኖርብህ ይችላል። አሠሪህ ጉርሻውን የሰጠህ ለበዓሉ ብሎ ነው? ወይስ ጉርሻ ለመስጠት የተነሳሳው ላከናወንከው ሥራ አመስጋኝነቱን መግለጽ ፈልጎ ነው?
-
አንድ ሰው በበዓል ወቅት ስጦታ ቢሰጥህ። ስጦታውን የሰጠህ ሰው “ይህን በዓል እንደማታከብር አውቃለሁ። ቢሆንም ስጦታዬን ብትቀበል ደስ ይለኛል” ይልህ ይሆናል። ግለሰቡ ይህን ያደረገው በደግነት ተነሳስቶ ብቻ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግን ግለሰቡ እምነትህን ለመፈተን ወይም በዓሉን እንድታከብር ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነ ቢሰማህስ? እነዚህን ነገሮች ካመዛዘንክ በኋላ ስጦታውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰን የራስህ ድርሻ ነው። የምናደርገው ማንኛውም ውሳኔ ንጹሕ ሕሊና ለመያዝና ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ የሚያስችለን እንዲሆን እንፈልጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 23:1
6. ተላላፊ በሽታዎች
ለሰዎች ፍቅር ስላለን ተላላፊ በሽታዎችን ወደ ሌሎች እንዳናጋባ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን። ተላላፊ በሽታ እንዳለብን የምናውቅ ከሆነ ወይም እንዲህ ያለ በሽታ ሊኖርብን እንደሚችል ከጠረጠርን ጥንቃቄ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ’ ስለሚያዘን ነው።—ሮም 13:8-10
ይህን ትእዛዝ እንደምንጠብቅ የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው ሌሎችን እንደ ማቀፍ ወይም እንደ መሳም ያሉ የፍቅር መግለጫዎችን ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርበታል። አንዳንዶች ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲሉ ቤታቸው ባይጋብዙት ቅር ሊሰኝ አይገባም። በተጨማሪም ከመጠመቁ በፊት ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ መናገር አለበት፤ ይህም የሌሎች ተጠማቂዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችላል። ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የነበረ ሰው መጠናናት ከመጀመሩ በፊት በፈቃደኝነት የደም ምርመራ ሊያደርግ ይገባል። እንዲህ ማድረጉ ‘ስለ ራሱ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት እንደሚሰጥ’ ያሳያል።—ፊልጵስዩስ 2:4
7. ገንዘብና ሕግ ነክ ጉዳዮች
ማንኛውንም ገንዘብ ነክ ስምምነት በጽሑፍ ማስፈራችን ብዙ ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳናል፤ ስምምነቱን ያደረግነው ከክርስቲያኖች ጋር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (ኤርምያስ 32:9-12) ያም ሆኖ ክርስቲያኖች ከገንዘብ ወይም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ቀለል ያሉ አለመግባባቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ባለጉዳዮቹ ብቻቸውን ዛሬ ነገ ሳይሉ ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸው።
ይሁንና እንደ ማጭበርበር ወይም ስም ማጥፋት ያሉ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን እንዴት ልንይዝ ይገባል? (ማቴዎስ 18:15-17ን አንብብ።) ኢየሱስ ልንከተላቸው የሚገቡ ሦስት እርምጃዎችን ነግሮናል፦
-
ማንንም ሰው ጣልቃ ሳናስገባ ጉዳዩን ሁለታችን ብቻ ለመፍታት ጥረት ማድረግ።—ቁጥር 15ን ተመልከት።
-
ይህ ካልሠራ፣ አንድ ወይም ሁለት የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ይዘን በመሄድ ግለሰቡን ማነጋገር።—ቁጥር 16ን ተመልከት።
-
እነዚህን ነገሮች አድርገንም ችግሩ ካልተፈታ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር።—ቁጥር 17ን ተመልከት።
በአብዛኛው ወንድሞቻችንን ፍርድ ቤት ማቅረባችን ተገቢ አይሆንም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በይሖዋና በጉባኤው ላይ ነቀፋ ሊያስከትል ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:1-8) ይሁንና እንደሚከተለው ያሉ ጉዳዮችን ፍርድ ቤት ማቅረብ ሊያስፈልግ ይችላል፦ ፍቺ፣ ልጅ የማሳደግ መብት ማግኘት፣ ከፍቺ በኋላ ተቆራጭ ገንዘብ ማስወሰን፣ የኢንሹራንስ ካሳ ማግኘት፣ በድርጅት ላይ የደረሰ ኪሳራን በሕግ ማሳወቅ ወይም ኑዛዜን ማስፈጸም። እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ፍርድ ቤት በማቅረብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመጨረስ ጥረት የሚያደርግ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንደጣሰ ሊቆጠር አይገባም።
ከባድ ወንጀሎችን ለምሳሌ አስገድዶ መድፈርን፣ ሕፃናትን ማስነወርን፣ አካላዊ ጥቃትን፣ ዝርፊያን ወይም ነፍስ ግድያን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሪፖርት የሚያደርግ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር አይጥስም።
a ከ455 ዓ.ዓ. እስከ 1 ዓ.ዓ. 454 ዓመት ነው። ከ1 ዓ.ዓ. እስከ 1 ዓ.ም. አንድ ዓመት ነው (ዜሮ የሚባል ዓመት የለም)። ከ1 ዓ.ም. እስከ 29 ዓ.ም. ደግሞ 28 ዓመት ነው። በድምሩ 483 ዓመት ይሆናል ማለት ነው።
b እነዚህን የሕክምና ዘዴዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በጥቅምት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።