መለኮታዊው ስም ባለፉት ዘመናት
መለኮታዊው ስም ባለፉት ዘመናት
ይሖዋ አምላክ ሁሉ ሰው ስሙን እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት ይፈልጋል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነን በጊዜው ብቸኛ የምድር ነዋሪዎች ለነበሩት ሁለት ሰዎች ስሙን መግለጡ ነው። ሔዋን ቃየንን ከወለደች በኋላ በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ መሠረት “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር [ከይሖዋ አዓት ] አገኘሁ” ስላለች አዳምና ሔዋን የአምላክን ስም በሚገባ ያውቁ እንደነበረ እናውቃለን።—ዘፍጥረት 4:1
ከዚያም በኋላ እንደ ሄኖክና ኖኅ ያሉት ታማኝ ሰዎች አካሄዳቸውን “ከእግዚአብሔር ጋር” እንዳደረጉ እናነባለን። (ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9) እነዚህም ሰዎች ቢሆኑ የአምላክን ስም ያውቁ እንደነበረ አያጠራጥርም። የአምላክ ስም ከኖህና ከቤተሰቦቹ ጋር ከታላቁ የጥፋት ውኃ አልፏል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በባቤል ታላቅ ዓመፅ ቢካሄድም እውነተኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በአምላክ ስም መጠቀማቸውን አልተዉም። አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሷል። በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ብቻ 551 ጊዜ ተጠቅሷል።
በመሳፍንት ዘመንም ቢሆን እስራኤላውያን በአምላክ ስም ከመጠቀም ወደኋላ አላሉም። እንዲያውም እርስ በርሳቸው ሰላምታ ሲሰጣጡ እንኳን የአምላክን ስም ይጠሩ ነበር። በበኩረ ጽሑፉ መሠረት ቦዔዝ ለእህሉ አጫጆች ሰላምታ ሲሰጥ ‘ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሁን’ ብሏል። እነርሱም ‘ይሖዋ ይባርክህ’ በማለት ለሰላምታው ምላሽ ሰጥተዋል።—ሩት 2:4
በእስራኤላውያን ታሪክ በሙሉ፣ ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በይሁዳ እስከ ሰፈሩበት ጊዜ ጭምር የይሖዋ ስም ዕለት ተዕለት በሰፊው ይሠራበት ነበር። ለይሖዋ ልብ የሚስማማ የተባለው ንጉሥ ዳዊት በመለኮታዊው ስም በሰፊው ተጠቅሟል። ራሱ በጻፈው መዝሙር ውስጥ ስሙ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሷል። (ሥራ 13:22) ከዚህም በላይ በብዙዎቹ የእስራኤላውያን መጠሪያ ስሞች ውስጥ የአምላክ ስም ተካትቷል። ለምሳሌ አዶንያስ (“ያህ ጌታዬ ነው” ማለት ሲሆን “ያህ” የይሖዋ ምህጻረ ቃል ነው።) ኢሳይያስ (“የይሖዋ ማዳን”)፣ ዮናታን (“ይሖዋ ሰጥቷል”)፣ ሚክያስ (“እንደ ያህ ያለ ማን ነው?”) እና ኢያሱ (“ማዳን የይሖዋ ነው”) የሚሉ ስሞች ነበሩ።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ
በጥንት ዘመን ሰዎች በመለኮታዊው ስም በሰፊው ይጠቀሙ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስም ውጭ ማግኘት ይቻላል። እዝራኤል ኤክስፕሎረሽን ጆርናል (ጥራዝ 13፣ ቁጥር 2) እንደዘገበው በ1961 ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ምዕራብ ትንሽ ራቅ ብሎ አንድ የመቃብር ዋሻ ተገኝቶ ነበር። በዚህ ዋሻ ግድግዳዎች ላይ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመጨረሻ አጋማሽ ላይ የተጻፉ ናቸው የሚባሉ የዕብራይስጥ ጽሑፎች ይገኛሉ። በጽሑፎቹ ውስጥ “ይሖዋ የመላው ምድር አምላክ ነው” የሚልና ይህንኑ የሚመስሉ ሌሎች መግለጫዎች ተገኝተዋል።
በ1966 በእዝራኤል ኤክስፕሎሬሽን ጆርናል (ጥራዝ 16፣ ቁጥር 1) ላይ በደቡባዊ እስራኤል በአራድ ስለተገኙ የዕብራይስጥ ጽሑፎች ያለባቸው የሸክላ ስብርባሪዎች የሚገልጽ ሪፖርት ወጥቷል። እነዚህ ጽሑፎች የተጻፉት በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ነው። ከእነዚህ ጽሑፎች አንዱ ኤልያሺብ ለሚባል ሰው የተጻፈ የግል ደብዳቤ ነው። ይህ ደብዳቤ በመግቢያው ላይ “ለጌታዬ ኤልያሺብ፣ ይሖዋ ሰላምህን ይጠይቅ” ሲል በመደምደሚያው ላይ ደግሞ “በይሖዋ ቤት ውስጥ ይኖራል” ይላል።
በ1975 እና 1976 በኔጌብ ተሰማርተው የነበሩ የከርሰ ምድር ተመራመሪዎች በግድግዳ ምርጊቶች፣ በትላልቅ ማሰሮዎችና ከጥርብ ድንጋይ በተሠሩ ዕቃዎች ላይ የተጻፉ የዕብራውያንና የፊንቃውያን ጽሑፎች አግኝተዋል። በእነዚህ ጽሑፎች ላይ አምላክ የሚለው
የዕብራይስጥ ቃልና የአምላክን ስም የሚወክሉት የሐወሐ የተባሉ የዕብራይስጥ ፊደላት ተገኝተዋል። በኢየሩሳሌም ውስጥ ደግሞ በቅርቡ ከባቢሎን ምርኮ በፊት የተሠራ ነው ተብሎ የሚታሰብ አነስተኛ የብር ጥቅልል ተገኝቷል። ተመራማሪዎች እንዳሉት ይህ ጥቅልል በሚፈታበት ጊዜ በውስጡ ይሖዋ የተባለው ስም በዕብራይስጥ ተጽፎበት ተገኝቷል።—ቢብሊካል አርኪዎሎጂ ሪቪው፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1983፣ ገጽ 18የአምላክ ስም በሰፊው ይሠራበት እንደነበረ የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ የለኪሶ ደብዳቤዎች በሚባሉት ጽሑፎች ውስጥ ይገኛል። እነዚህ በሸክላ ስብርባሪዎች ላይ የተጻፉት ደብዳቤዎች በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጣት ለኪሶ የተባለች በግንብ የታጠረች ከተማ ውስጥ የተገኙት ከ1935 እስከ 1938 ባሉት ዓመታት ነው። እነዚህ ደብዳቤዎች አንድ አይሁዳዊ የጦር መኮንን በተመደበበት ጦር ሠፈር ሆኖ በለኪሶ ይኖር ለነበረው ያኦሽ ለተባለ የበላይ አለቃው የጻፋቸው ደብዳቤዎች ይመስላሉ። የተጻፉበትም ዘመን በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ገደማ በእስራኤላውያንና በባቢሎናውያን መካከል በተደረገው ጦርነት አካባቢ እንደሆነ ይታሰባል።
ሊነበቡ ከሚችሉት ስምንት ስብርባሪዎች መካከል ስምንቱ መልእክታቸውን የሚጀምሩት “ይሖዋ ጌታዬን በጥሩ ጤንነት ለዚህ ወራት እንዲያደርሰው እመኛለሁ!” እንደሚለው ባሉ ሰላምታዎች ነው። በሰባቱ የሸክላ ስብርባሪዎች ውስጥ የአምላክ ስም በጠቅላላው 11 ጊዜ ይገኛል፤ ይህም በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ገደማ ላይ ሰዎች በአምላክ ስም በሰፊው ይጠቀሙ እንደነበረ ያረጋግጣል።
አረማውያን ነገሥታት እንኳ መለኰታዊውን ስም ያውቁና ስለ እስራኤላውያን አምላክ በሚናገሩበት ጊዜም በዚህ ስም ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል የሞአብ ንጉሥ የነበረው ሚሻ በሞዓባውያን የድንጋይ ጽላት ላይ እስራኤላውያንን ድል ስለመንሳቱ በጉራ ከተናገረ በኋላ ከሌሎች ብዙ ነገሮች በተጨማሪ የሚከተለውን ጽፏል:- “ኬሞሽ ‘ሂድና ኔቦን ከእስራኤል ውሰድ!’ ብሎኛል። በዚህም ምክንያት በሌሊት ወጥቼ ከማለዳ እስከ ቀትር ተዋጋሁ። ከተማዋን ከመውሰዴም በላይ ሁሉንም ገደልኩ። . . . ከዚያም የይሖዋን [ዕቃዎች] ከኬሞሽ ፊት አየጎተትኩ ወሰድኩ።”
ቲኦሎጊሸስ ቨርተርቡኽ ሱም አልተን ተስታመንት (የብሉይ ኪዳን ሃይማኖታዊ መዝገበ ቃላት) በ3ኛው ጥራዝ በ538ኛው አምድ ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ የአምላክ ስም ስለ ተጠቀሰባቸው ስለ እነዚህ ጽሑፎች እንዲህ ብሏል:- “በዚህ ረገድ የማሶሬቲክ ጽሑፍ አስተማማኝ መሆኑን የሚያረጋግጡ ጀሐወሐ የተጻፈባቸው 19 የሚያክሉ የጽሑፍ ማስረጃዎች አሉ። በተለይ ከአራድ መዛግብት ከዚህ የበለጠ ብዙ ነገር መጠበቅ ይቻላል።”—ከጀርመንኛ የተተረጎመ
የአምላክ ስም አልተረሳም
የአምላክ ስም በሰፊው የታወቀና ሰዎች በብዛት የሚጠቀሙበት መሆኑ ኢየሱስ ከመምጣቱ ከ400 ዓመት በፊት ይኖር እስከነበረው እስከ ሚልክያስ ድረስ ቀጥሏል። ሚልክያስ በስሙ በሚጠራውና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው መጽሐፍ ውስጥ 48 ጊዜ ያህል በመለኮታ ዊው ስም በመጠቀም ለስሙ ከፍተኛ የሆነ ቦታ ሰጥቷል።
ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ግን ብዙ አይሁዳውያን ከእስራኤል ምድር ራቅ ባሉ አገሮች መኖር ጀመሩ፤ አንዳንዶችም መጽሐፍ ቅዱስን በዕብራይስጥ ቋንቋ ማንበብ አቃታቸው። በዚህም ምክንያት በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በዘመኑ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (“ብሉይ ኪዳንን”) አዲሱ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ወደሆነው ወደ ግሪክኛ መተርጎም ተጀመረ። ይሁን እንጂ በዚህም ጊዜ ቢሆን የአምላክ ስም ችላ አልተባለም። ተርጓሚዎቹ የዕብራይስጡን አጻጻፍ እንዳለ አስፍረውታል። እስከ ዘመናችን ተጠብቀው የቆዩት የጥንቶቹ የግሪክኛ ሰፕቱጀንት ቅጂዎች ይህንን ያረጋግጣሉ።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረበት ዘመን ሁኔታው እንዴት ነበር? ኢየሱስና ሐዋርያቱ በአምላክ ስም ይጠቀሙ እንደነበረ እንዴት ለማወቅ እንችላለን?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዚህ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመጨረሻ አጋማሽ በሸክላ ስባሪ ላይ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ የአምላክ ስም ሁለት ጊዜ ተጠቅሶአል።
[ምንጭ]
(ሥዕሉ የተገኘው ከእስራኤል የጥንታዊ ቅርሶችና ቤተ መዘክሮች መምሪያ ነው)
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በተጨማሪም የአምላክ ስም በለኪሶ ደብዳቤዎችና በሞዓብ የድንጋይ ጽላት ላይ ይገኛል