በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ስምህ ይቀደስ” — የትኛው ስም?

“ስምህ ይቀደስ” — የትኛው ስም?

“ስምህ ይቀደስ”​—የትኛው ስም?

ሃይማኖተኛ ሰው ነህን? ከሆንክ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ከሁሉ በላይ የሆነ አንድ አካል አለ ብለህ እንደምታምን አያጠራጥርም። በተጨማሪም ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረውና የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ ለሚባለው ከሁሉ በላይ ለሆነው ለዚህ አካል የሚቀርብ በሰፊው ለታወቀው ጸሎት ከፍተኛ አክብሮት ሳይኖርህ አይቀርም። ጸሎቱ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ይጀምራል።​—ማቴዎስ 6:9

ኢየሱስ የአምላክን ስም ‘መቀደስ’ ወይም በአክብሮት ማወደስ የጸሎቱ መጀመሪያ ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ አስበህ ታውቃለህን? ከዚያ በኋላ ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት፣ ስለ አምላክ ፈቃድ በምድር ላይ መሆን፣ ስለ ኃጢአታችን መሠረይና ስለመሳሰሉት ነገሮች ጠቅሷል። የእነዚህ ጸሎቶች ምላሽ ማግኘት በመጨረሻ ላይ በምድር ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስችላል። ከዚህ የበለጠ አስፈላጊነት ያለው ነገር ይኖራል ብለህ ታስባለህን? ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሁሉ አስቀድመን የአምላክ ስም እንዲቀደስ እንድንጸልይ ነግሮናል።

ኢየሱስ ተከታዮቹ በጸሎታቸው ለአምላክ ስም መቀደስ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲሰጡ ያስተማረው በአጋጣሚ አልነበረም። ኢየሱስ ይህንን ስም በጸሎቱ ውስጥ ደጋግሞ ስለጠቀሰ ከፍተኛ ቦታ ሰጥቶት እንደነበረ ግልጽ ነው። ለአባቱ ጮክ ብሎ ይጸልይ በነበረበት አንድ ጊዜ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ብሎ ሲጸልይ ተደምጧል። አምላክ ራሱም “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” ሲል መልሶለታል።​—ዮሐንስ 12:28

ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽትም ወደ አምላክ ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ አዳምጠውታል። በዚህ ጊዜም የአምላክን ስም አስፈላጊነት አጉልቷል። “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ካለ በኋላ “ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” ብሏል።​—ዮሐንስ 17:6, 26

ኢየሱስ ለአምላክ ስም ይህን ያህል ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምን ነበር? እኛም ስለ ስሙ መቀደስ እንድንጸልይ በመናገር ይህ ስም ለእኛም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያመለከተው ለምን ነበር? ይህን ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለስም ይሰጥ ስለነበረው ግምት ግንዛቤ ማግኘት ይኖርብናል።

ስሞች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሚተርክላቸው ዘመናት

የሰው ልጅ ለተለያዩ ነገሮች ስያሜ የመስጠት ፍላጎት እንዲያድርበት ያደረገው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ግልጽ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የሚባል ስም ተሰጥቶታል። ስለ ፍጥረት በሚተነትነው ታሪክ ውስጥ አዳም ካከናወናቸው የመጀመሪያ ሥራዎች አንዱ ለእንስሳት ስም ማውጣት እንደነበረ ተገልጿል። አምላክ ለአዳም ሚስት በሰጠው ጊዜ ወዲያው አዳም “ሴት” (በዕብራይስጥ ኢሽሻህ) ብሎ ሰየማት። ቆየት ብሎም “የሕያዋን ሁሉ እናት” ስለምትሆን “ሕያው” የሚል ትርጉም ያለው ሔዋን የተባለ ስም አወጣላት። (ዘፍጥረት 2:19, 23፤ 3:20) ዛሬም ቢሆን ለሰዎች ስም የማውጣት ልማድ አለን። ስም ባይኖር ኖሮ ኑሯችን ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት እንኳን ያስቸግ⁠ራል።

ይሁን እንጂ በእስራኤላውያን ዘመን ስሞች ያገለግሉ የነበረው ለመለያነት ብቻ አልነበረም። ሌላም አገልግሎት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል “ሳቅ” የሚል ትርጉም ያለው የይስሐቅ ስም በዕድሜ ሸምግለው የነበሩት ወላጆቹ እርሱን አንደሚወልዱ በሰሙ ጊዜ የሳቁትን ሳቅ የሚያስታውስ ነበር። (ዘፍጥረት 17:17, 19፤ 18:12) የዔሳው ስም “ፀጉራም” ማለት ሲሆን አካላዊ መልኩን የሚያመለክት ነበር። “ቀይ” የሚል ትርጉም ያለው ኤዶም የተባለው ሌላው ስሙ ደግሞ የብኩርና መብቱን ለቀይ ወጥ መሸጡን የሚያሳስብ ነበር። (ዘፍጥረት 25:25, 30–34፤ 27:11፤ 36:1) ያዕቆብ መንትያው ከሆነው ወንድሙ በዕድሜ የሚያንሰው በጥቂት ቢሆንም የዔሳውን ብኩርና ገዝቶ አባቱ ለበኩር ልጁ የሚሰጠውን በረከት አግኝቷል። ያዕቆብ ሲወለድ የተሰጠው ስም “ተረከዝ መያዝ” ወይም “ተተኪ” የሚል ትርጉም ነበረው። (ዘፍጥረት 27:36) በተመሳሳይም በግዛት ዘመኑ ለእስራኤላውያን ሰላምና ብልጽግና ያስገኘው ሰሎሞን ስሙ “ሰላማዊ” የሚል ትርጉም ነበረው።​—1 ዜና መዋዕል 22:9

በዚህ ምክንያት ዘ ኢልስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ (ጥራዝ 1፣ ገጽ 572) እንደሚከተለው ብሏል:- “‘ስም’ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚሰጠውን ትርጉም ብናጠና በዕብራይስጥ ቋንቋ ውስጥ ምን ያህል ከፍተኛ ቦታ እንደነበረው ለመረዳት እንችላለን። ስም የባለቤቱን እውነተኛ ባሕርይና ማንነት የሚወክል እንጂ ለመለያነት ብቻ የሚያገለግል አልነበረም።”

አምላክ የመጥምቁ ዮሐንስና የኢየሱስ ወላጆች ለሚሆኑት ሰዎች በመልአክ አማካኝነት የልጆቻቸው ስም ማን መባል እንደሚገባው መናገሩ ለስም ምን ያህል ከፍተኛ ግምት እንዳለው ያመለክታል። (ሉቃስ 1:13, 31) ሰዎች በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚኖራቸውን ቦታ ለማመልከት ሲል ስማቸውን የቀየረበት ወይም ተጨማሪ ስም የሰጠበት ጊዜም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ባሪያ የነበረው አብራም (“የክብር አባት”) ወደፊት የብዙ ብሔሮች አባት እንደሚሆን በተናገረበት ጊዜ ስሙን አብርሃም (“የብዙ ሕዝብ አባት”) ብሎ ለውጦታል። የአብርሃም ሚስት ሦራ (“ተጨቃጫቂ”) ደግሞ የአብርሃም ዘር እናት ስለምትሆን ሣራ (“ልዕልት”) ተብላ እንድትጠራ አድርጓል።​—ዘፍጥረት 17:5, 15, 16፤ ከዘፍጥረት 32:28​ና ከ2 ሳሙኤል 12:24, 25 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስም የስምን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ስለነበረ ለጴጥሮስ የአገልግሎት መብት በሰጠበት ጊዜ ስሙን ጠቅሶ ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:16–19) መንፈሳዊ ፍጡራን እንኳን ስም አላቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሁለቱ ስም ማለትም የሚካኤልና የገብርኤል ስም ተጠቅሷል። (ሉቃስ 1:26፤ ይሁዳ 9) የሰው ልጅ እንደ ከዋክብት፣ ፕላኔቶች፣ ከተሞች፣ ተራሮችና ወንዞች ላሉት ሕይወት ለሌላቸው ነገሮች ስም ሲያወጣ ፈጣሪው ያደረገውን ማድረጉ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሁሉንም ከዋክብት በስም እንደሚጠራ ይነግረናል።​—ኢሳይያስ 40:26

አዎን፣ ስሞች በአምላክ ዓይን በጣም አስፈላጊ ቦታ አላቸው። በሰው ልጅ ውስጥም ሰዎችንና ነገሮችን በስም የመለየት ፍላጎት እንዲያድር አድርጓል። ስለዚህ ሰዎች፣ እንስሳት፣ ከዋክብትና ሕይወት የሌላቸው ሌሎች ነገሮች ስም አላቸው። ታዲያ እነዚህን ሁሉ የፈጠረው አምላክ ስም የለሽ ቢሆን ተገቢ ይሆናልን? በተለይ “ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ” የሚለውን የመዝሙራዊ ቃል ስንመለከት ይህ በፍጹም ተገቢ አይሆንም።​—መዝሙር 145:21

ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ (ጥራዝ 2፣ ገጽ 649) እንዲህ ይላል:- “በጣም መሠረታዊና አስፈላጊ ከሆኑት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጽልን ነገሮች አንዱ አምላክ ስም የለሽ አለመሆኑ ነው። የሚጠራበትና የሚለመንበት የተጸውኦ ስም አለው።” ኢየሱስ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ ባስተማራቸው ጊዜ በአእምሮው ይዞ የነበረው ይህንን ስም እንደነበረ አያጠራጥርም። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)​—ማቴዎስ 6:9

በዚህ ሁሉ ምክንያት የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ማወቅ በጣም እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። ታዲያ የአምላክ የተጸውኦ ስም ማን እንደሆነ ታውቃለህ?

የአምላክ ስም ማን ነው?

በመቶ ሚልዮን ከሚቆጠሩት የሕዝበ ክርስተና አብያተ ክርስቲያናት አባሎች መካከል ብዙዎቹ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚያስቸግራቸው መሆኑ የሚያስደንቅ ነው። አንዳንዶች የአምላክ ስም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ሲል የጸለየው ከራሱ ለተለየ አካል እንደነበረ ግልጽ ነው። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ዮሐንስ 17:6) ልጅ ወላጅ አባቱን እንደሚያነጋግር በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ መጸለዩ ነበር። (ዮሐንስ 17:1) “መቀደስ” ወይም “መወደስ” የሚኖርበት የሰማያዊ አባቱ ስም ነበር።

ሆኖም በብዙዎቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የአምላክ ስም አይገኝም፤ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥም ቢሆን ስሙ እምብዛም አይጠራም። በዚህም ምክንያት ይህ ስም ከመከበርና “ከመቀደስ” ይልቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች እንዳያውቁት ተደርጓል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ቃል ምን እንዳደረጉ ምሳሌ እንዲሆነን የአምላክ ስም የሚገኝበትን መዝሙር 83:18ን ብቻ እንመልከት። ይህ ጥቅስ በአራት የተለያዩ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚከተለው ተተርጉሟል:-

“ስምህ ጌታ እንደሆነ፣ በምድርም ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንህ ይወቁ።” (የ1952 ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን)

ዘላለማዊ ሆይ፣ አንተ ብቻ በመላው ዓለም ላይ የበላይ የሆንህ አምላክ መሆንህን አስተምራቸው።” (ኤ ኒው ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ባይብል በጄምስ ሞፋት፣ 1922)

ያህዌህ የተባለውን ስም የምትሸከም አንተ ብቻ እንደሆንህ፣ በመላው ዓለም ላይም የበላይ እንደሆንህ ይወቁ።” (የ1966 ካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል)

“አንተ ብቻ ስምህም ይሖዋ እንደሆነ በምድር ሁሉ ላይም ልዑል እንደሆንህ ይወቁ።” (ኦቶራይዝድ ወይም ኪንግ ጀምስ ቨርሽን የ16 11 እትም)

“ስምህ እግዚአብሔር እንደሆነ፣ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንህ ይወቁ።” (የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም)

በእነዚህ ትርጉሞች ውስጥ የአምላክ ስም ይህን ያህል የተለያየው ለምንድን ነው? ስሙ ጌታ፣ ዘላለማዊው፣ ያህዌህ ወይስ ይሖዋ? ወይስ እነዚህ ሁሉ ስሞች ተቀባይነት ያላቸው ትክክለኛ ስሞቹ ናቸው?

ይህንን ለመመለስ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈው በእንግሊዝኛ ወይም በአማርኛ አለመሆኑን ማስታወስ ይገባናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በሙሉ ዕብራውያን ሲሆኑ በአብዛኛው የጻፉት በዘመናቸው ይነገር በነበረው የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ ቋንቋ ነበር። አብዛኞቻችን እነዚህን ጥንታዊ ቋንቋዎች አናውቃቸውም። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ዘመናዊ ቋንቋዎች ስለተተረጎመ የአምላክን ቃል ለማንበብ በምንፈልግበት ጊዜ በእነዚህ ትርጉሞች ለመጠቀም እንችላለን።

ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ የሆነ አክብሮት አላቸው። ‘ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ’ እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው። አንድ ተርጓሚ ሆን ብሎ አንድ ቃል ወይም ሐሳብ ቢያጎድል ወይም ቢለውጥ በመንፈስ የተጻፈውን ቃል በረዘው ማለት ነው። እንዲህ ለሚያደርግ ሰው ደግሞ የሚከተለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። “ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጸፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፣ በዚህ መጽሐፍ ከተጸፉት ከሕይወት ዛፍና . . . እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።”​—ራእይ 22:18, 19፤ በተጨማሪ ዘዳግም 4:2ን ተመልከት።

አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው አያጠራጥርም፤ በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች እንዲረዱት ለማስቻልም ልባዊ ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ተርጓሚዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የሚጽፉ ሰዎች አይደሉም። አብዛኞቹ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሐሳቦች ላይ ጠንከር ያለ አቋም ስላላቸው የግል ምርጫቸውና አስተሳሰባቸው በትርጉማቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በተጨማሪም ሰው እንደመሆናቸው መጠን ሊሳሳቱ ወይም ሚዛን ሊጎድላቸው ይች⁠ላል።

በዚህ ምክንያት እንደሚከተሉት ያሉትን አስፈላጊ ጥያቄዎች የመጠየቅ መብት አለን:- ትክክለኛው የአምላክ ስም ማን ነው? የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለአምላክ የተለያየ ስም የሰጡት ለምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ካረጋገጥን በኋላ የአምላክ ስም መቀደስ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ወደሚለው የመጀመሪያ ጥያቄያችን ለመመለስ እንችላለን።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መላእክት፣ ሰዎች፣ እንስሳት እንዲሁም ከዋክብትና ሌሎችም ሕይወት የሌላቸው ነገሮች ስም አላቸው። የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ ስም የሌለው ነው ቢባል ከዚህ ሁኔታ ጋር ይስማማልን?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ የአምላክን ስም በጸሎቱ ውስጥ ደጋግሞ ስለጠቀሰ ለዚህ ስም ከፍተኛ ቦታ እንደሰጠው ግልጽ ነው