በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” (ሮሜ 10:13 አዓት) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በመጻፍ የአምላክን ስም ማወቃችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አበክሮ ገልጿል። ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ አነጋገር ኢየሱስ ባቀረበው ሞዴል ጸሎት ላይ የአምላክን ስም ‘መቀደስ’ ወይም ‘መወደስ’ ከሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ያስቀደመው ለምንድን ነው? ወደሚለው የመጀመሪያ ጥያቄያችን ይመልሰናል። ይህንን ለመረዳት ቁልፍ የሆኑ የሁለት ቃላትን ትርጉም በይበልጥ መረዳት ይኖርብናል።

በመጀመሪያ ደረጃ ‘መቀደስ’ ማለት ምን ማለት ነው? ቃል በቃል ሲተረጎም “ቅዱስ ማድረግ” ማለት ነው። ታዲያ የአምላክ ስም ቀድሞውንም ቢሆን ቅዱስ አይደለምን? በእርግጥ ቅዱስ ነው። የአምላክን ስም ስንቀድስ ከቀድሞው ይበልጥ ቅዱስ አናደርገውም። ከዚህ ይልቅ ለቅድስናው እውቅና እንሰጣለን፣ ከሌሎች ስሞች ሁሉ ለይተን ከፍተኛ ማዕረግና አክብሮት እንሰጠዋለን ማለት ነው። የአምላክ ስም እንዲቀደስ በምንጸልይበት ጊዜ መላው ፍጥረት የአምላክን ስም ቅድስና የሚያከብርበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቃችን ነው።

በሁለተኛ ደረጃ “ስም” የሚለው ቃል ምን አንድምታ አለው ወይም ምን ስሜት ያስተላልፋል? አምላክ ይሖዋ የተባለ ስም እንዳለውና ስሙም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺህ በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል። በተጨማሪም ይህን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደነበረው ትክክለኛ ቦታው መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ተወያይተናል። ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ የማይገኝ ከሆነ “ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፣ አቤቱ፣ [ይሖዋ አዓት] የሚሹህን አትተዋቸውምና” የሚለው መዝሙራዊ ቃል እንዴት ሊፈጸም ይችላል?​—መዝሙር 9:⁠10

ይሁን እንጂ የአምላክን ስም ማወቅ የአምላክ ስም በዕብራይስጥ የሐወሐ፣ በእንግሊዝኛ ጅሆቫ ወይም በአማርኛ ይሖዋ እንደሆነ የአእምሮ እውቀት ከማግኘት የበለጠ የሚጨምረው ነገር የለምን? በእርግጥ ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። ሙሴ በሲና ተራራ በነበረ ጊዜ “እግዚአብሔር በደመናው ውስጥ ወረደ፣ በዚያም ከእርሱ [ከሙሴ] ጋር ቆመ፣ የእግዚአብሔርንም [የይሖዋንም አዓት ] ስም አወጀ።” የይሖዋ ስም ከታወጀ በኋላ ምን ተከተለ? በመቀጠል የይሖዋ ባሕርዮች ተዘረዘሩ:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]፣ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]፣ መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ዘጸአት 34:​5, 6) ሙሴ የሚሞትበት ጊዜ በተቃረበበት ጊዜ ደግሞ ለእሥራኤላውያን “የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት ] ስም እጠራለሁ” ብሏል። ከዚያስ በኋላ? አንዳንዶቹን የአምላክ ታላላቅ ባሕርያት ከጠቀሰ በኋላ አምላክ ለስሙ ሲል ለእስራኤላውያን ያደረገላቸውን አንዳንድ ነገሮች ከለሰላቸው። (ዘዳግም 32:​3–43) ስለዚህ የአምላክን ስም ማወቅ ማለት ይህ ስም የሚወክላቸውን ነገሮች ማወቅና የስሙ ባለቤት የሆነውን አምላክ ማምለክ ማለት ነው።

ይሖዋ ስሙን ከባሕርያቱ፣ ከዓላማዎቹና ከድርጊቶቹ ጋር ስላያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም ቅዱስ ነው የሚልበትን ምክንያት ለመገንዘብ እንችላለን። (ዘሌዋውያን 22:​32) ስሙ ታላቅ ግርማ ያለው፣ አስፈሪና ማንም ሊደርስበት ከሚችለው በላይ ከፍ ያለ ነው። (መዝሙር 8:​1፤ 99:​3፤ 148:​13) አዎን፣ የአምላክ ስም ተራ የሆነ መታወቂያ አይደለም። ማንነቱን የሚወክል ስም ነው። ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አገልግሎ እንደ “ጌታ” ባሉት የማዕረግ ስሞች የሚተካ ጊዜያዊ ስም አይደለም። ይሖዋ ራሱ ለሙሴ እንደሚከተለው ብሎት ነበር:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] . . . ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፤ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።”​—ዘጸአት 3:​15

የሰው ልጅ የፈለገውን ያህል ቢሞክር የአምላክን ስም ከምድር ላይ ፈጽሞ ሊያጠፋ አይችልም። “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፣ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።”​—ሚልክያስ 1:11፤ ዘጸአት 9:16፤ ሕዝቅኤል 36:23

ስለዚህ የአምላክ ስም መቀደስ ከማንኛውም ጉዳይ የበለጠ አስፈላጊነት አለው። የአምላክ ዓላማዎች በሙሉ ከስሙ ጋር የተገናኙ ናቸው። የሰው ልጅ ችግር የጀመረው ሰይጣን አምላክን ውሸታም እንደሆነና ለማስተዳደር ብቃት እንደሌለው በሚያስመስል አነጋገር በመሳደብ ስሙን ባረከሰ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:​1–6፤ ዮሐንስ 8:​44) የሰው ልጅ የሰይጣን ውሸት ካስከተለበት ጉዳት ሊገላገል የሚችለው የአምላክ ስም ቅድስና ተገቢ በሆነ መንገድ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ክርስቲያኖች የአምላክ ስም እንዲቀደስ አጥብቀው የሚጸልዩት በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ እነርሱ ራሳቸውም ቢሆኑ የአምላክን ስም ለመቀደስ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር አለ።

የአምላክን ስም ልንቀድስ የምንችለው እንዴት ነው?

አንደኛው መንገድ ለሌሎች ሰዎች ስለ ይሖዋ በመናገርና ብቸኛው የሰው ልጆች ተስፋ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚተዳደረው ንጉሣዊ አገዛዝ መሆኑን በማሳወቅ ነው። (ራእይ 12:​10) ብዙዎች ይህን በማድረግ የሚከተለውን የኢሳይያስ ትንቢት በመፈጸም ላይ ናቸው። “በዚያ ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት ] ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ።”​—ኢሳይያስ 12:4, 5

ሌላው መንገድ የአምላክን ሕጎችና ትእዛዞች ማክበር ነው። ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሎ ነበር:- “ትእዛዛቴን ጠብቁ፣ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ። የተቀደሰውን ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእሥራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤ የምቀድሳችሁ፣ . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ።”​—ዘሌዋውያን 22:​31–33

እሥራኤላውያን የይሖዋን ሕግ መጠበቃቸው ስሙን የቀደሰው እንዴት ነው? ሕጉ ለእሥራኤላውያን የተሰጠው ስሙን መሠረት በማድረግ ነበር። (ዘጸአት 20:​2–17) ስለዚህ ሕጉን ይጠብቁ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ለዚህ ስም ተገቢ የሆነ አክብሮትና ግምት ይሰጡ ነበር። በተጨማሪም የእስራኤል ሕዝብ በብሔር ደረጃ የይሖዋን ስም ተሸክሞ ነበር። (ዘዳግም 28:10፤ 2 ዜና መዋዕል 7:14) በትክክለኛ መንገድ በሚመላለሱበት ጊዜ በጥሩ አካሄድ የሚመላለስ ልጅ አባቱን እንደሚያስከብር ሁሉ ይህ አካሄዳቸው ይሖዋን ያስከብረው ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ በሚጥሱበት ጊዜ ስሙን ያረክሱ ነበር። በዚህ ምክንያት ለጣዖት እንደ መሠዋት፣ በሐሰት እንደ መማል፣ ድሆችን እንደመጨቆንና እንደ ዝሙት ያሉት ኃጢአቶች ‘የአምላክን ስም እንደሚያረክሱ’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።​—ዘሌዋውያን 18:​21፤ 19:12፤ ኤርምያስ 34:16፤ ሕዝቅኤል 43:7

ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ በአምላክ ስም የተሰጠ ትእዛዝ ተቀብለዋል። (ዮሐንስ 8:​28) በተጨማሪም ‘ለይሖዋ ስም የሚሆን’ ሕዝብ ናቸው። (ሥራ 15:​14) ስለዚህ “ስምህ ይቀደስ” ብሎ ከልቡ የሚጸልይ ክርስቲያን የአምላክን ትእዛዛት በሙሉ በመጠበቅ በአኗኗሩ የይሖዋን ስም ይቀድሳል። (1 ዮሐንስ 5:​3) ይህ ደግሞ ሁልጊዜ አባቱን ያከበረውን የአምላክን ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዛት መፈጸምን ይጨምራል።​—ዮሐንስ 13:31, 34፤ ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20

ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት የአምላክ ስም ለክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ ያለው መሆኑን አጠንክሮ ገልጿል። ለአባቱ “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” ብሏል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ዮሐንስ 17:​26) ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ስም ለማወቅ መቻላቸው የአምላክን ፍቅር በግላቸው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። አምላክን እንደ አፍቃሪ አባታቸው አድርገው እንዲያውቁ ኢየሱስ አስችሏቸዋል።​—ዮሐንስ 17:​3

አንተንስ እንዴት ይነካል?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሽማግሌዎች አድርገውት በነበረ ስብሰባ ላይ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደጎበኘ ስሞዖን ተርኳል።” በዚህ ስም የማትጠቀም ወይም ይህን ስም የማትሸከም ከሆንክ አምላክ “ለስሙ የሚሆን ወገን” አድርጎ ከሚመርጣቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ትችላለህን?​—ሥራ 15:14

ብዙ ሰዎች የአምላክን ስም ለመጥራት የማይፈልጉ ቢሆኑና ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችም ስሙን ከትርጉሞቻቸው ውስጥ ቢያስወጡም በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ስም የመሸከምን፣ በአምልኮታቸው ብቻ ሳይሆን በዕለታዊ ንግግራቸው ጭምር በአምላክ ስም የመጠቀምንና ለሌሎች የማሳወቅን መብት በታላቅ ደስታ ተቀብለዋል። አንድ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሊነግርህ ቢጀምርና ይሖዋ በሚለው ስም ቢጠቀም ወዲያው የየትኛው ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ይሆናል ብለህ ታስባለህ? በመላው ምድር ላይ እንደ ጥንቶቹ የይሖዋ አምላኪዎች በአምልኮቱ የአምላክን ስም አዘውትሮ የሚጠቀም ቡድን አንድ ብቻ ነው። እነርሱም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

ይህ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ ስም የሚሆኑ ሕዝቦች’ መሆናቸውን ለይቶ ያሳውቃል። ይሖዋ ራሱ ለእውነተኛ አምላኪዎቹ የሰጠው ስም ስለሆነ ይህን ስም ለመሸከም በመቻላቸው ኩራት ይሰማቸዋል። ኢሳይያስ 43:​10 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት። ]” አምላክ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ እነማን ነበር? ቀደም ያሉትን ጥቂት ቁጥሮች እንመልከት።

እዚሁ ምዕራፍ ላይ ከቁጥር 5 እስከ 7 ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፣ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን:- መልሰህ አምጣ፣ ደቡብንም:- አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርኩትን፣ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።” በእኛ ዘመን እነዚህ ቁጥሮች የሚናገሩት አምላክ እንዲያወድሱትና ምሥክሮቹ እንዲሆኑለት ከብሔራት ሁሉ ስለሰበሰባቸው ሕዝቦቹ ነው። ስለዚህ የአምላክ ስም ራሱን አምላክን ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ያሉትን እውነተኛ አምላኪዎቹን ጭምር ለይቶ ለማወቅ ያስችላል።​— ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

የአምላክን ስም ከማወቅ የሚገኙ በረከቶች

ይሖዋ ስሙን የሚወዱትን ይጠብቃቸዋል። መዝሙራዊው:- “በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ” ብሏል። (መዝሙር 91:14) በተጨማሪም ያስታውሳቸዋል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [ይሖዋንም አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)​—ሚልክያስ 3:16

ስለዚህ የአምላክን ስም ከማወቅና ከመውደድ የሚገኙት ጥቅሞች በአሁኑ ሕይወት ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በምድራዊ ገነት ውስጥ ዘላለማዊ የደስታ ሕይወት ለመስጠት ቃል ገብቷል። ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት የሚከተለውን ጽፏል። “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)​—መዝሙር 37:​9, 11

ታዲያ ይህ ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ መልሱን ሰጥቷል። “ስምህ ይቀደስ” ብላችሁ ጸልዩ ባለበት የሞዴል ጸሎቱ ላይ “መንግሥትህ ትምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 6:9, 10) አዎን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትተዳደረው የአምላክ መንግሥት የአምላክን ስም ከመቀደስዋም በላይ በዚህች ምድር ላይ ጥሩ ሁኔታዎች እንዲሰፍኑ ታደርጋለች። ክፋትን፣ ጦርነትን፣ ረሀብን፣ በሽታንና ሞትን ታስወግዳለች።​—መዝሙር 46:8, 9፤ ኢሳይያስ 11:9፤ 25:6፤ 33:​24፤ ራእይ 21:3, 4

የዘላለም ሕይወት አግኝተህ በዚህች መንግሥት ሥር በደስታ ለመኖር ትችላለህ። እንዴት? አምላክን በማወቅ ነዋ! “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ይህንን የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ እውቀት እንድታገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ደስ እያላቸው ይረዱሃል።​—ሥራ 8:29–31

በዚህ ብሮሹር ላይ የቀረበው ማብራሪያ ፈጣሪ የግል መጠሪያው የሆነና በጣም ውድ አድርጎ የሚመለከተው ስም ያለው መሆኑን እንዳሳመነህ ተስፋ ይደረጋል። አንተም ብትሆን በጣም ውድ አድርገህ ልትመለከተው የሚገባ ስም ነው። ይህን ስም ማወቅና በተለይ በአምልኮ መጠቀም በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንድትገነዘብ ምኞታችን ነው።

ነቢዩ ሚክያስ ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት በድፍረት እንደተናገረው “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ስም ለዘላለም እንሄዳለን” ለማለት ቁርጥ ውሳኔ እንድታደርግ እንመኛለን።​—ሚክያስ 4:​5

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘የአምላክን ስም ማወቅ’ ማለት ስሙ ይሖዋ ስለመሆኑ የአእምሮ እውቀት ከማግኘት የበለጠ ትርጉም አለው

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ስም ‘ታላቅ ግርማ ያለው፣ አስፈሪና ማንም ሊደርስበት የማይችል ከፍታ ያለው ስም ነው።’ የአምላክ ዓላማዎች በሙሉ ከስሙ ጋር የተዛመዱ ናቸው

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዶክተር ዋልተር ሎውሪ በአንግሊካን ቲኦሎጂካል ሪቪው (ጥቅምት 1959) ላይ የአምላክን ስም ማወቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አጉልተው ገልጸዋል። እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የምንወደውን፣ የምናነጋግረውንና የምንናገርለትን ሰው መጠሪያ ስም ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ሰው ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነትም ከዚህ የተለየ አይደለም። አምላክን በስሙ የማያውቅ ሰው ከአምላክ ጋር በግል ሊተዋወቅ፣ እርስ በርስ ለመነጋገር የሚያስችል እውቀት ሊኖረው አይችልም። (ጸሎት ማለት ራሱ ከአምላክ ጋር መነጋገር ማለት ነው።) የተወሰነ አካል እንደሌለው ኃይል ብቻ አድርጎ የሚያውቀው ከሆነ ሊወደው አይችልም።”