በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ስም — ትርጉሙና አነባበቡ

የአምላክ ስም — ትርጉሙና አነባበቡ

የአምላክ ስም​—ትርጉሙና አነባበቡ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ እንደሚከተለው በማለት ጠይቆ ነበር:- “ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፣ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ምሳሌ 30:4) እኛስ የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ነው። ፍጥረት አምላክ ለመኖሩ ጠንካራ ማረጋገጫ የሚሰጠን ቢሆንም ስሙን ግን አይነግረንም። (ሮሜ 1:20) ፈጣሪ ራሱ ባይነግረን ኖሮ የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ለማወቅ አንችልም ነበር። የራሱ መጽሐፍ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙን ገልጦልናል።

በአንድ ታላቅ ታሪካዊ ወቅት አምላክ ሙሴ እያዳመጠው የራሱን ስም ደጋግሞ ጠርቷል። ሙሴ በዚያ ጊዜ የሆነውን ነገር ጽፎ ያቆየልን ሲሆን ይህም ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (ዘጸአት 34:5) እንዲያውም አምላክ የገዛ ስሙን በራሱ “ጣት” ጽፏል። አምላክ በአሁኑ ጊዜ አሥርቱ ትእዛዛት ብለን የምንጠራቸውን ሕግጋት ለሙሴ የሰጠው ራሱ በተአምር ጽፎ ነው። ታሪኩ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።” (ዘጸአት 31:18) የአምላክ ስም በመጀመሪያው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ስምንት ጊዜ ተጠቅሷል። (ዘጸአት 20:1–17) ስለዚህ አምላክ ራሱ የገዛ ስሙን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ለሰዎች ገልጧል። ታዲያ ይህ ስም ማን ነው?

ስሙ በዕብራይስጥ ቋንቋ יהוה ተብሎ ይጻፋል። እነዚህ ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩት አራት ፊደላት በዕብራይስጥ የሚነበቡት ከቀኝ ወደ ግራ ሲሆን በብዙዎች የዘመናችን ቋንቋዎች የሐወሐ ወይም ጀሐቨሐ በሚሉት ሆሄያት ሊወከሉ ይችላሉ። በእነዚህ አራት ተነባቢ ሆሄያት የሚወከለው የአምላክ ስም በመጀመሪያው የ“ብሉይ ኪዳን” ቅጂ ወይም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ወደ 7, 000 ጊዜ ያህል ይገኛል።

ስሙ ሐዋሕ (הוה) ከተባለው “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግሥ በእርባታ የተገኘ ሲሆን “ይሆናል” ማለት ነው። * ስለዚህ የአምላክ ስም አምላክ የገባውን ቃል ደረጃ በደረጃ የሚፈጽም መሆኑንና ዓላማውን ከመፈጸም የሚያግደው ምንም ነገር የሌለ መሆኑን ያመለክታል። ከአምላክ በቀር ማንም እንዲህ ያለ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ስም ሊኖረው አይችልም።

ቀደም ባለው ክፍል (በገጽ 5 ላይ) የአምላክ ስም በመዝሙር 83:18 ላይ እንዴት ባለ የተለያየ መንገድ እንደተጻፈ ታስታውሳለህን? ሁለቱ ትርጉሞች የአምላክ ስም ምትክ አድርገው ያሰፈሩት የማዕረግ ስሞችን (“ጌታ”፣ “ዘላለማዊው”) ነው። በሁለቱ ትርጉሞች ላይ በሰፈሩት ይሖዋ እና ያህዌህ ግን የአምላክን ስም የሚወክሉት አራቱ ፊደሎች እንደሚገኙ ማስተዋል ይቻላል። ይሁን እንጂ የስሙ አጠራር ወይም አነባበብ የተለያየ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

የአምላክ ስም የሚነበበው እንዴት ነው?

እንደ እውነቱ ከሆነ የመጀመሪያውን የአምላክ ስም አጠራር ወይም አነባበብ አስረግጦ የሚያውቅ ሰው የለም። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ ዕብራይስጥ ሲሆን የዕብራይስጥ ቋንቋ በሚጻፍበት ጊዜ ጸሐፊው የሚጽፈው አናባቢ ሆሄያትን እየጨመረ ሳይሆን ተነባቢ ሆሄያትን ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት የጻፉትም ሰዎች የአምላክን ስም በሚጽፉበት ጊዜ የጻፉት ስሙን የሚወክሉትን ተነባቢ ሆሄያት ብቻ ነው።

የዕብራይስጥ ቋንቋ በየዕለቱ የሚሠራበት የመነጋገሪያ ቋንቋ በነበረበት የጥንት ዘመን ይህ አጻጻፍ ምንም ችግር አላስከተለም ነበር። የአምላክ ስም አጠራር በእስራኤላውያን ዘንድ በሚገባ የታወቀ ስለነበረ ማንኛውም አንባቢ አናባቢዎቹን ፊደል ራሱ ጨምሮ ያለችግር ሊያነብ ይችል ነበር። (አንድ አማርኛ አንባቢ “ዓ.ም.” ወይም “ወ/ሮ” የሚሉትን አሕጽሮተ ቃላት ሲመለከት “ዓመተ ምህረት” ወይም “ወይዘሮ” ብሎ እንደሚያነበው ማለት ነው።)

ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ ምክንያት የሆኑ ሁለት ነገሮች ተፈጽመዋል። የመጀመሪያው በአይሁዳውያን መካከል የአምላክን ስም ጮክ ብሎ መጥራት ትክክል አይደለም የሚል አጉል እምነት መስፋፋቱና መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነቡበት ጊዜ የአምላክ ስም በተጻፈበት ቦታ ላይ ሲደርሱ የአምላክን ስም ከመጥራት ይልቅ አዶናይ (“ሉዓላዊ ጌታ”) ብለው ማንበባቸው ነው። ከዚህም በላይ ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ የጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ መሆኑ እየቀረ በመምጣቱ የመጀመሪያው የአምላክ ስም አነባበብ ወይም አጠራር እየተረሳ ሄደ።

በሁለተኛው ሺህ አጋማሽ እዘአ ይኖሩ የነበሩ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁራን የዕብራይስጥ ቋንቋ አነባበብ ጠፍቶ እንዳይቀር በማሰብ በጽሑፎች ላይ መጨመር የሚኖርባቸውን አናባቢ ሆሄያት የሚያመለክቱበት ሥርዓተ ነጥብ ፈለሰፉ፤ እነዚህንም ነጥቦች በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ተነባቢ ሆሄያት ላይ ጨምረዋል። በዚህ መንገድ ተነባቢዎቹ ሆሄያትም ሆኑ አናባቢዎቹ ተጽፈው ስለቆዩልን በዘመኑ የነበረው አነባበብ ተጠብቆ ሊተላለፍ ችሏል።

አምላክ ስም ላይ ሲደርሱ ግን በተነባቢዎቹ ሆሄያት ላይ ትክክለኞቹን አናባቢዎች ከመጨመር ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ አንባቢው አዶናይ ብሎ እንዲያነብ የሚያሳስቡ ሌሎች አናባቢ ምልክቶችን ጽፈዋል። ኢሁዋህ የሚለው አነባበብ የመጣው በዚህ ምክንያት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ጅሆቫ የሚለው የመለኮታዊ ስም አጠራር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህ አነባበብ ወይም አጠራር ውስጥ የመጀመሪያው ዕብራይስጥ መሠረታዊ ድምፆች ይገኛሉ።

በየትኛው አነባበብ ወይም አጠራር ትጠቀማለህ?

ታዲያ እንደ ያህዌህ ያሉት አጠራሮች የመጡት ከየት ነው? የመጀመሪያውን የአምላክ ስም አጠራር ለማወቅ ሙከራ ያደረጉ ዘመናዊ ምሁራን የተሻሉ ናቸው ያሏቸው አጠራሮች ናቸው። ሁሉም ሳይሆኑ አንዳንድ ምሁራን ከኢየሱስ ዘመን በፊት የነበሩት አይሁዳውያን የአምላክን ስም ያህዌህ ብለው ሳይጠሩ አይቀሩም ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ በእርግጠኛነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም። በዚህ ዓይነት አጠራር ሊጠቀሙም ላይጠቀሙም ይችላሉ።

ያም ሆነ ይህ ብዙዎች ይሖዋ የሚለውን አጠራር ይመርጣሉ። ለምን? ምክንያቱም ያህዌህ ከሚለው አጠራር የበለጠ የተለመደና በሰፊው የሚሠራበት ስለሆነ ነው። ታዲያ ከመጀመሪያው አጠራር ጋር ሊቀራረብ በሚችል አጠራር መጠቀሙ የተሻለ አይሆንም? በመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች ረገድ ይህን የመሰለ ልማድ ስለማንከተል እንደዚህ ለማለት አይቻልም።

በዚህ ረገድ በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችለውን የኢየሱስ ስም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንተ ኢየሱስ በልጅነቱ ይኖር በነበረበት የናዝሬት ከተማ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ዕለት ተዕለት ሲያነጋግሩት ምን ብለው ይጠሩት እንደነበረ ታውቃለህ? የሹዋ (ምናልባትም የሆሹዋ) ብለው ሳይጠሩት እንደማይቀር ቢታሰብም ማንም ሰው በእርግጠኝነት ለመናገር አይችልም። ኢየሱስ ወይም ጂሰስ ተብሎ ይጠራ እንዳልነበረ ግን የተረጋገጠ ነው።

የኢየሱስ ሕይወት ታሪክ በግሪክኛ ቋንቋ በተጻፈበት ጊዜ ግን በመንፈስ አነሣሽነት የጻፉት ጸሐፊዎች የመጀመሪያውን የዕብራይስጥ አጠራር እንዳለ ለማስቀመጥ አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ ወደ ግሪክኛው አጠራር በመለወጥ ኢየሱስ ብለውታል። ዛሬም የስሙ አጠራር መጽሐፍ ቅዱስ እንደተተረጎመበት ቋንቋ ይለያያል። የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ሄሱስ ብለው ያነባሉ። ጣሊያናውያን ጀይዙ ይሉታል። ጀርመናውያን ደግሞ የሱስ ብለው ይጠሩታል።

አብዛኞቻችን፣ እንዲያውም ሁላችንም ለማለት ይቻላል፣ የመጀመሪያውን የኢየሱስ ስም አጠራር ስለማናውቅ በኢየሱስ ስም መጠቀማችንን ማቆም ይገባናልን? እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ መደረግ አለበት ያለ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የለም። ለእኛ ሲል ደሙን ያፈሰሰው ውድ የአምላክ ልጅ ተለይቶ የሚታወቅበት ስም ስለሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚለው ስም መጠቀም ያስደስተናል። የኢየሱስን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አውጥተን “መምህር” ወይም “መካከለኛ” እንደሚሉት ባሉት የማዕረግ ስሞች ብንተካ ኢየሱስን ማክበር ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም! ኢየሱስን በቋንቋችን በተለመደው አጠራር ስንጠራ ከእርሱ ጋር የመቀራረብ ስሜት ሊያድርብን ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለምናነባቸው ስሞች በሙሉ ተመሳሳይ ሐሳብ መስጠት ይቻላል። ስሞቹን በቋንቋችን በተለመደው አጠራር እንጠራለን እንጂ የመጀመሪያውን አጠራር ለመኮረጅ አንሞክርም። “ኤርምያስ” እንላለን እንጂ ይርምያሁ አንልም። በተመሳሳይም ኢሳይያስን በዘመኑ የሸያሁ ተብሎ ሳይጠራ አይቀርም ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም ኢሳይያስ እንለዋለን። የእነዚህን ስሞች ጥንታዊ አጠራር የሚያውቁ ምሁራን እንኳን ስለ ሰዎቹ ሲናገሩ የዘመኑን አጠራር እንጂ የጥንቱን አጠራር አይጠቀሙም።

የይሖዋ ስምም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። በዘመናችን የተለመደው ይሖዋ ወይም ጅሆቫ የተባለው አጠራር ከመጀመሪያው የጥንት አጠራር ጋር አንድ ዓይነት ላይሆን ቢችልም የስሙን አስፈላጊነት በምንም ዓይነት መንገድ አይቀንሰውም። ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ያለው ፈጣሪ፣ ሕያው የሆነው አምላክና የሁሉ የበላይ የሆነው ልዑል ተለይቶ የሚታወቅበት ስም ነው።​—ማቴዎስ 6:9

‘በሌላ ሊተካ አይችልም’

ብዙ ተርጓሚዎች ያህዌህ የሚለውን አጠራር ቢመርጡም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምና አንዳንድ ሌሎች ትርጉሞች ይሖዋ የሚለው ለበርካታ መቶ ዘመናት የተለመደ አጠራር በመሆኑ ምክንያት በዚሁ አጠራር ለመጠቀም መርጠዋል። ከዚህም በላይ የሐወሐ (“YHWH”) ወይም ጀሐቨሐ (“JHVH”) * የሚሉት የቴትራግራማተን ሆሄዮች ከሌሎች አጠራር ባላነሰ መጠን ተካትተዋል።

ከዚህ ቀደም ብሎ ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ጉስታቭ ፍሬድሪክ ኦህለር ከዚህ እምብዛም ባልተለየ ምክንያት ተመሳሳይ ውሳኔ አድርገዋል። ስለተለያዩ አነባበቦች ካብራሩ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድመዋል:- “ይሖዋ የሚለው ስም በሥነ ቃላታችን ውስጥ በጣም የተለመደና የታወቀ በመሆኑና በማንኛውም ሌላ ዓይነት አጠራር ሊተካ የማይችል በመሆኑ ከዚህ በኋላ ይሖዋ የሚለውን ቃል እጠቀማለሁ።” — ቲኦሎጊ ደስ አልተን ተሰታመንትስ (የብሉይ ኪዳን ሃይማኖት) ሁለተኛ እትም፣ በ1882 የታተመው፣ ገጽ 143

ፖውል ዡዋን የተባሉት ኢየሱሳዊ ምሁርም በተመሳሳይ ግራምየር ደ ለብሩ ቢብሊክ (የመጽሐፍ ቅዱስ ዕብራይስጥ ሰዋስው) በተባለው መጽሐፍ በ1923 እትም፣ በገጽ 49 የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በትርጉሞቻችን ውስጥ የመላምት ውጤት ከሆነው ያህዌህ ይልቅ በፈረንሣይኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ባገኘው ዢሆቫ የሚል አጠራር ተጠቅመናል።” ሌሎች ብዙ ቋንቋዎችም በገጽ 8 ላይ ባለው ሠንጠረዥ ውስጥ እንደተመለከተው ከዚህ ጋር በሚመሳሰል አጠራር ይጠቀማሉ።

ታዲያ እንዲህ ሲባል ያህዌህ ከሚለው አጠራር ጋር በሚመሳሰል አጠራር መጠቀም ስህተት ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። ይሖዋ የሚለው አጠራር “በብዙ ቋንቋዎች ጆሮ የተለመደ” አጠራር በመሆኑ ምክንያት በአንባቢዎች ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ስለሚያገኝ ብቻ ነው። ዋናው ነገር በስሙ መጠቀማችንና ስሙን ለሌሎች ማሳወቃችን ነው። “ሕዝቦች ሁሉ ይሖዋን አመስግኑ! ስሙንም ጥሩ። ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ አሳታውቁ። ስሙ ከፍ ያለ መሆኑን ተናገሩ።”​—ኢሳይያስ 12:4 አዓት

የአምላክ አገልጋዮች ባለፉት መቶ ዘመናት ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ያደረጓቸውን ነገሮች እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ፣ 1984 እትም ላይ ተጨማሪ ክፍል (አፔንዲክስ) 1A ተመልከት።

^ አን.22 በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የ1984 እትም ተጨማሪ ክፍል (አፔንዲክስ) 1A ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

(የሐወሐ) ‘YHWH’ ስለሚለው ስም የመጀመሪያ አነባበብ የተለያዩ ምሁራን የተለያየ ሐሳብ ሰጥተዋል።

ዶክተር ኤም ራይዘል ዘ ሚስቲርየስ ኔም ኦቭ Y.H.W.H. በተባለው መጽሐፍ በገጽ 74 ላይ የቴትራግራማተን የመጀመሪያ አጠራር “ዬሁዋህ ወይም ያሁዋህ መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።

የካምብሪጁ ካኖን ዲ ዲ ዊሊያምስ “የቴትራግራማተን እውነተኛ አጠራር ጃህዌህ እንዳልሆነ የሚያመለክት፣ እንዲያውም የሚያረጋግጥ ለማለት ይቻላል ማስረጃ አለ። . . . ትክክለኛ ስሙ ጃህኦህ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል። —ሳይትእሽክሪፍት ፊውር ዲ አልቴስታሜንትልሼ ቪሴንእሽካፍት (የብሉይ ኪዳን እውቀት መጽሔት) 1936፣ ጥራዝ 54፣ ገጽ 269

‘ሪቫይዝድ ሴጐንድ ቨርሽን’ በተባለው የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ የቃላት መፍቻ በገጽ 9 ላይ የሚከተለው አሳብ ተሰጥቷል:- “አንዳንድ የቅርብ ጊዜ ትርጉሞች የተጠቀሙበት ያህቬ የሚለው አጠራር በማያጠራጥር ሁኔታ የተረጋገጠ ሳይሆን በአንዳንድ የጥንት መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ ኤልያስ (ኤልያሁ) ያሉትን መለኮታዊው ስም ተካትቶ የሚገኝባቸውን የተጸውኦ ስሞች ከተመለከትን የአምላክ ስም አጠራር ያሆ ወይም ያሁ ሊሆን ይችላል።”

በ1749 ቴለር የሚባለው ጀርመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ስላነበባቸው የተለያዩ የአምላክ ስም አነባበቦች እንዲህ ብሏል:- “የሲሲሊው ዳዮዶሩስ፣ ማክሮቢዩስ፣ ክሌሜንስ አሌክስንድሪነስ፣ ቅዱስ ዤሮምና ኦሪገን ጃኦ ፤ ሳምራውያን፣ ኤፒፋንዩስ፣ ቴዎዶሬቱስ፣ ጃሔ ወይም ጃቬ ፤ ሉድዊግ ካፕል ጃቮ፤ ዱሩሲዩስ ጃቪ፤ ሖቲንገር ጀህቫ፤ መሪሴሩስ ጅሆቫ፤ ካስቲሊዩ ጃህቫ እና ሊ ክሊርክ ጃዎህ ወይም ጃቮህ ብለው ጽፈዋል።”

በዚህ ዓይነት የመጀመሪያው የአምላክ ስም አነባበብ በአሁኑ ጊዜ እንደማይታወቅ ግልጽ ነው። ደግሞ መታወቁም ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። በጣም አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ አምላክ ራሱ ትክክለኛው አነባበብ ተጠብቆ እንዲቆይና እኛ እንድንጠቀምበት ያደርግ ነበር። በጣም አስፈላጊው ነገር በራሳችን ቋንቋ በተለመደው አጠራር ወይም አነባበብ በአምላክ ስም መጠቀም ነው።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጅሆቫ የሚለው አጠራር በብዙ ብሔራት ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያሳዩ የመለኮታዊው ስም የተለያዩ ቋንቋዎች አጻጻፍ

አማርኛ – ይሖዋ

አዋባካልኛ – የሖዋ

ቡጎቱኛ – ጂሆቫ

ካንትንኛ – የህወዋህ

ዳንሽኛ– ጅሆቫ

ዳችኛ – ጅሆቫ

ኤፊክኛ – ጅሆቫ

እንግሊዝኛ ጅሆቫ

ፍጅያንኛ – ጅዮቫ

ፍንሽኛ – ጅሆቫ

ፈረንሳይኛ – ዢሆቫ

ፍቱናኛ – እሆቫ

ጀርመንኛ –ይሖቫ

ሀንጋሪያንኛ – ጅሆቫ

እግቦኛ – ጅሆቫ

ጣሊያንኛ – ጅኦቫ

ጃፓንኛ – ኢሆባ

ማውሪኛ – እሆዋ

ሞቱኛ – ኢየሆቫ

ሟላ ሟሉኛ – ጅሆቫ

ናሪንያሪኛ – ጅሆቫ

ኔምቤኛ –ጅሆቫ

ፔታትስኛ – ጅሁቫ

ፖላንድኛ –ጅሁቫ

ፖርቱጋልኛ – ጅኦቫ

ሮማኒያንኛ – ኢየሆቫ

ሳሞአንኛ –ኢየወቫ

ሶቶኛ –ጅሆቫ

ስፓንኛ – ጅሆቫ

ስዋሒሊኛ – የሖቫ

ስዊድንኛ – ጅሆቫ

ታሂቲያንኛ – ኢየሆቫ

ታጋሎግኛ – ጅሆቫ

ቶንጋንኛ – ጅሆቫ

ቤንጃኛ – ይሖቫ

ቆሳኛ – ኡይሆቫ

የሩባኛ – ጅሆፋህ

ዙሉኛ – ኡጅሆቫ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ይሖዋ” የአምላክ ስም እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ባሉ ጽሑፎች ላይ እንኳ በሰፊው የታወቀ ሆኗል።

በዮሐን ላዲስላቭ ፒርከር የተደረሰውን “ዘ ኦልማይቲነስ” የተባለውን የዜማ ግጥም በሙዚቃ ያቀናበረው ፍራንዝ ሹበርት ሲሆን በዚህ የዜማ ግጥም ውስጥ ይሖዋ የሚለው ስም ሁለት ጊዜ ተጠቅሷል። በተጨማሪም “ናቡኮ” በተባለው የቬርዲ ኦፔራ ውስጥ በመጨረሻው ትዕይንት ላይ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በፈረንሳዊው የሙዚቃ አቀነባባሪ በአርተር ሆኔገር የተደረሰው “ኪንግ ዴቪድ” የተባለው ዝማሬ ይሖዋ ለሚለው ስም ከፍተኛ ቦታ ሰጥቷል። ቪክቶር ሁጎ የተባለውም እውቅ ፈረንሳዊ ደራሲ ከ30 በሚበልጡ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ውስጥ “ይሖዋ” በሚለው ስም ተጠቅሟል።

የጀርመን ፌደራል ባንክ በ1967 አሳትሞ ባወጣው ዶቸ ታለር (የጀርመን ገንዘብ) የተባለ መጽሐፍ ውስጥ የ“ይሖዋ” ስም የሚገኝበት እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት ሳንቲሞች አንዱ የሆነውና ከሲሌሲያው ግዛት የተገኘው የ1634 ራይኽታለር ሥዕል ወጥቷል። መጽሐፉ በሳንቲሙ ጀርባ ላይ ስላለው ሥዕል እንዲህ ብሏል።:- “የብርሃን ነጸብራቅ ከሚወጣበት ጅሆቫ ከሚለው ስም ግርጌ ከዳመና ውስጥ የሚወጣና አክሊል የደፋ የሲሌስያ ካባ ይታያል።”

በምሥራቅ ጀርመን በሩዶልፍሽታት በሚገኝ ቤተ መዘክር ውስጥ በ17ኛው መቶ ዘመን የስዊድን ንጉሥ የነበረው ዳግማዊ ጉስታፈስ አዶልፍ ይለብሰው በነበረው የጦር ልብስ ኮሌታ ላይ ጅሆቫ የሚለው ስም በትላልቅ ፊደላት ተጽፎ ማየት ይቻላል።

ስለዚህ ለበርካታ መቶ ዘመናት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝቶ የቆየው የአምላክ ስም አጠራር ጅሆቫ የሚለው ነው። ይህንን ስም የሚሰሙ ሰዎችም ስለማን እንደተነገረ ወዲያው ይገነዘባሉ። ፕሮፌሰር ኦህለር እንዳሉት “ይህ ስም በሥነ ቃላታችን ውስጥ በጣም የተለመደ ስለሆነ በማንም ሌላ አጠራር ሊተካ አይችልም።”​— ቲኦሎጊ ደስ አልተን ተስታመንትስ (የብሉይ ኪዳን ሃይማኖት)

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን በሚገኘው የሊቀ ጳጳስ ክሌመንት 13ኛ መቃብር ላይ በሚገኘው የመልአክ ቅርጽ ላይ ያለው የአምላክ ስም ጐላ ብሎ ሲታይ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ስም የያዙ ብዙ ሳንቲሞች ተሠርተው ነበር። ይህ ሳንቲም በ1661 ጀርመን አገር ኑረምበርግ ከተማ የተገኘ ነው። የላቲኑ ጽሑፍ ሲነበብ “በክንፎችህ ጥላ ሥር” ይላል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በቀደሙት ዘመናት በቴትራግራማተን የተጻፈው የአምላክ ስም የብዙ ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች ማስጌጫ ሆኖ ነበር

ፉርቭዬ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሊዮንስ፣ ፈረንሳይ

የቡርዥ ካቴድራል፣ ፈረንሳይ

ላ ሴሌ ዱኗ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን፣ ፈረንሳይ

በደቡብ ፈረንሳይ በዲኝ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን

ሳኦ ፖሎ፣ ብራዚል የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን

ስትራትስበርግ ካቴድራል፣ ፈረንሳይ

የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል፣ ቬነስ፣ ጣሊያን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ቦርደሾልም፣ ጀርመን በሚገኝ ገዳም የይሖዋ ስም እንዲህ ተጽፎ ይታያል

በ1635 በተሠራ የጀርመን ሳንቲም ላይ

በፌህማርን ቤተ ክርስቲያን መዝጊያ ላይ፣ ጀርመን

ሃርማንስችላግ በኦስትሪያ ታችኛው ክፍለ ሀገር በ1845 በተሠራ የመቃብር ድንጋይ ላይ