በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 8

ኢዮስያስ ጥሩ ጓደኞች ነበሩት

ኢዮስያስ ጥሩ ጓደኞች ነበሩት

ትክክል የሆነውን ማድረግ ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል?— ብዙ ሰዎች እንደዚያ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢዮስያስ የተባለ አንድ ልጅ ትክክል የሆነውን ማድረግ ከባድ ሆኖበት እንደነበር ይናገራል። ደስ የሚለው ግን ትክክል የሆነውን እንዲያደርግ የረዱት ጥሩ ጓደኞች ነበሩት። እስቲ ስለ ኢዮስያስና ስለ ጓደኞቹ እንመልከት።

የኢዮስያስ አባት የይሁዳ ንጉሥ የሆነው አሞን ነው። አሞን በጣም መጥፎ ሰው ሲሆን ጣኦት ያመልክ ነበር። ኢዮስያስ አባቱ ሲሞት የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። በወቅቱ ገና ስምንት ዓመቱ ነበር። ታዲያ ኢዮስያስ እንደ አባቱ መጥፎ ሰው የሆነ ይመስልሃል?— በፍጹም!

ሶፎንያስ ሕዝቡ ጣኦት እንዳያመልኩ አስጠንቅቆ ነበር

ኢዮስያስ ትንሽ ልጅ እያለም እንኳ ይሖዋን የመታዘዝ ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም ጓደኛ አድርጎ የመረጠው ይሖዋን የሚወዱ ሰዎችን ብቻ ነው። እነሱም ትክክል የሆነውን እንዲያደርግ ረድተውታል። ከኢዮስያስ ጓደኞች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ነበሩ?

ከጓደኞቹ አንዱ ሶፎንያስ ነው። ሶፎንያስ ነቢይ ሲሆን የይሁዳ ነዋሪዎች ጣኦት የሚያመልኩ ከሆነ መጥፎ ነገር እንደሚደርስባቸው ነግሯቸው ነበር። ኢዮስያስ የሶፎንያስን ማስጠንቀቂያ ሰምቷል፤ በመሆኑም የሚያመልከው ጣኦታትን ሳይሆን ይሖዋን ነበር።

ሌላው የኢዮስያስ ጓደኛ ደግሞ ኤርምያስ ነው። ኤርምያስና ኢዮስያስ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የነበሩ ሲሆን ያደጉትም በአንድ አካባቢ ነው። በጣም የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ስለነበሩ ኢዮስያስ በሞተበት ወቅት ኤርምያስ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለመግለጽ የለቅሶ ግጥም ጽፎ ነበር። ኤርምያስና ኢዮስያስ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲሁም ይሖዋን ለመታዘዝ እንዲችሉ አንዳቸው ሌላውን ያበረታቱ ነበር።

ኢዮስያስና ኤርምያስ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲችሉ አንዳቸው ሌላውን ያበረታቱ ነበር

ከኢዮስያስ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?— ኢዮስያስ ገና ትንሽ ልጅ እያለም እንኳ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ይፈልግ ነበር። ጓደኝነት መመሥረት ያለበት ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንተም ይሖዋን የሚወዱና ትክክል የሆነውን እንድታደርግ የሚረዱህ ጓደኞች እንድትመርጥ እናበረታታሃለን!

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ