ዝግመተ ለውጥ—ሐቁን ከመላ ምቶች መለየት
“ፀሐይ ሙቀት መስጠቷ የማይታበል እውነታ የሆነውን ያህል ዝግመተ ለውጥም የተረጋገጠ ሐቅ ነው” በማለት ታዋቂ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዶኪንስ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።16 ፀሐይ ሙቀት እንደምትሰጥ በሙከራ ብሎም እንዲሁ በማየት ማረጋገጥ እንደሚቻል የታወቀ ነው። ዝግመተ ለውጥ እውነት መሆኑንስ በምናያቸው ነገሮችና በሙከራዎች በማያሻማ መንገድ ማረጋገጥ ይቻል ይሆን?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት ግን አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። ብዙ ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዝርያ ከብዙ ዘመናት በኋላ መጠነኛ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስተውለዋል። ለምሳሌ፣ ሰዎች የሚፈልጉትን የውሻ ዝርያ እየመረጡ በማዳቀል ከጊዜ በኋላ ከቀድሞዎቹ ዝርያዎች አጠር ያሉ እግሮች ወይም ረዘም ያለ ፀጉር ያላቸው ውሾች እንዲወለዱ ማድረግ ችለዋል። * አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንዲህ ያለውን አነስተኛ ለውጥ “ማይክሮኢቮሉሽን” ብለው ይጠሩታል።
ይሁን እንጂ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ትናንሾቹ ለውጦች በቢሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ተጠራቅመው ትላልቅ ለውጦችን በማስገኘት ዓሦችን በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ ወደሚኖሩ እንስሳት፣ ዝንጀሮ መሰል ፍጥረታትን ደግሞ ወደ ሰው መለወጥ እንደቻሉ ያስተምራሉ። እነዚህ ትላልቅ ለውጦች “ማክሮኢቮሉሽን” ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ይህ ጽንሰ ሐሳብ መላ ምት እንጂ የተረጋገጠ ነገር አይደለም።
17 እንደ ዳርዊን አመለካከት ከሆነ ውስብስብ እንዳልሆኑ ተደርገው የሚታሰቡት የመጀመሪያዎቹ የሴል ዓይነቶች በጣም ረጅም በሆነ ዘመን ውስጥ አዝጋሚ ለውጥ በማድረግ በምድር ላይ የሚገኙትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕያዋን ነገሮች አስገኝተዋል፤ ይህም የሆነው ሴሎቹ በጊዜ ሂደት “እጅግ አነስተኛ የሆኑ መሻሻሎችን” በማሳየታቸው እንደሆነ ዳርዊን ገልጿል።18
ለምሳሌ፣ ቻርልስ ዳርዊን በዓይናችን ልናያቸው የምንችላቸው ትናንሽ ለውጦች መኖራቸው ትላልቅ ለውጦችም ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያረጋግጣሉ በማለት አስተምሯል፤ በእርግጥ እነዚህን ትላልቅ ለውጦች ማንም ሰው አላያቸውም።ብዙዎች ይህ አባባል ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ‘በአንድ ዝርያ (species) ውስጥ ትናንሽ ለውጦች ሊከሰቱ ከቻሉ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት በጣም ረጅም በሆነ ዘመን ውስጥ ትላልቅ ለውጦች ሊከሰቱ የማይችሉበት ምን ምክንያት ይኖራል?’ ብለው ያስባሉ። * እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የዝግመተ ለውጥ ትምህርት የተመሠረተው በሦስት መላ ምቶች ላይ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።
መላ ምት 1፦ ለአዳዲስ ዝርያዎች መገኘት መሠረቱ ሚውቴሽን ነው። ሚውቴሽን በዕፅዋትና በእንስሳት ጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥ ነው፤ የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት፣ ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን (species) ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ቤተሰቦችን (families) ሊያስገኝ ይችላል በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው።19
ሐቁ፦ በአብዛኛው የዕፅዋትን ወይም የእንስሳትን ባሕርያት የሚወስነው ጂኖቹ የያዙት መመሪያ ወይም በእያንዳንዱ ሴል ኒውክሊየስ ውስጥ የሚገኘው ንድፍ ነው። * ተመራማሪዎች ሚውቴሽን ዕፅዋትም ሆኑ እንስሳት በሚተኳቸው ዘሮች ላይ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ሚውቴሽን በእርግጥ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ ዝርያዎችን ያስገኛል? ለአንድ ክፍለ ዘመን በጂን ላይ የተደረገው ጥናት ምን አሳይቷል?
በ1930ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ሳይንቲስቶች የደረሱበት አዲስ ሐሳብ አስፈንጥዟቸው ነበር። ተፈጥሯዊ ምርጦሽ (አንድ ሕይወት ያለው ነገር ከሚኖርበት አካባቢ ጋር ከሌሎች በተሻለ ራሱን ማስማማት በመቻሉ በሕይወት ሊቀጥልና ሊራባ የሚችልበት ሂደት) በጂን ላይ በአጋጣሚ በሚከሰት ለውጥ (ሚውቴሽን) አማካኝነት አዳዲስ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ሊያስገኝ እንደሚችል ሳይንቲስቶች ቀድሞውንም ቢሆን ያምኑ ነበር። በመሆኑም ሰዎች በዕፅዋትና በእንስሳት ጂን ላይ ሆን ብለው ለውጥ በማድረግ (ሚውቴሽን) የተሻለውን ዝርያ ቢመርጡ ከተፈጥሯዊ ምርጦሽ ጋር በሚመሳሰል መልኩ አዳዲስ ዝርያዎችን ማስገኘት እንደሚችሉ እንዲያውም ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተሰምቷቸው ነበር። በጀርመን የሚገኘው የማክስ ፕላንክ የዕፅዋት ማዳቀያ ምርምር ተቋም ሳይንቲስት የሆኑት ቮልፍ ኤከሃርት ሎኒግ “አብዛኞቹ የባዮሎጂ ባለሙያዎች በተለይ ደግሞ በጄኔቲክስና ዝርያዎችን በማዳቀል መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች በዚህ ፈንጥዘው ነበር” ብለዋል። * እንዲህ ያስፈነጠዛቸው ምን ነበር? የዕፅዋትን የሚውቴሽን ጄኔቲክስ ለ30 ዓመታት ያህል ያጠኑት ሎኒግ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ተመራማሪዎች ልማዳዊ በሆነው ዕፅዋትንና እንስሳትን የማዳቀል ዘዴ ላይ አብዮት የሚካሄድበት ጊዜ እንደደረሰ ተሰምቷቸው ነበር። ሚውቴሽን በማካሄድና ጥሩ የሆኑትን በመምረጥ አዳዲስ ብሎም የተሻሉ ዕፅዋትንና እንስሳትን ማስገኘት የሚችሉ መስሏቸው ነበር።”20 እንዲያውም አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሙሉ በሙሉ አዳዲስ የሆኑ ዝርያዎችን እንደሚያስገኙ ተስፋ አድርገው ነበር።
በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስያና በአውሮፓ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንደሚያፋጥኑ የታመነባቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ከፍተኛ ገንዘብ የተመደበለት የምርምር ፕሮግራም ማካሄድ ጀመሩ። ከአርባ ለሚበልጡ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ከተደረገ በኋላ ምን ውጤት ተገኘ? ፒተር ፎን ዜንግቡሽ የተባሉት ተመራማሪ “ምርምሩን ለማካሄድ በጣም ብዙ ገንዘብ ቢፈስም በጨረር አማካኝነት [የጂኖችን ባሕርይ ለውጦ] የተሻሉ ዝርያዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት በአብዛኛው ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል” ብለዋል።21 በተጨማሪም ሎኒግ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ሳይንቲስቶች የነበራቸው ተስፋና ደስታ በ1980ዎቹ ዓመታት በመላው ዓለም መና ሆነ። በሚውቴሽን አማካኝነት ማዳቀል በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ራሱን የቻለ የምርምር ዘርፍ መሆኑ ቀረ። በሚውቴሽን የተገኙ ዝርያዎች በሙሉ ማለት ይቻላል . . . ሞተዋል ወይም ከተፈጥሮ ዝርያዎች የበለጠ ደካሞች ሆነው ተገኝተዋል።” *
ያም ቢሆን ለ100 ዓመታት ያህል በጥቅሉ ስለ ሚውቴሽን ከተደረገው ምርምርና በተለይ ደግሞ 70 ዓመት ካስቆጠረው በሚውቴሽን የማዳቀል ዘዴ ከተገኘው መረጃ በመነሳት ሳይንቲስቶች ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን ማስገኘቱን በተመለከተ አንድ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ሎኒግ የተገኘውን መረጃ ከመረመሩ በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “በሚውቴሽን አማካኝነት ነባሩን [የዕፅዋት ወይም የእንስሳት] ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ዝርያ መለወጥ አይቻልም። ይህ መደምደሚያ በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉ የሚውቴሽን ምርምሮች ከተገኙት ተሞክሮዎችና ውጤቶች እንዲሁም ቲዮሪ ኦቭ ፕሮባቢሊቲ ከሚባለው የሒሳብ ሕግ ጋር ይስማማል።”
ታዲያ ሚውቴሽን በጊዜ ሂደት አንድን ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ፍጥረት ለመለወጥ ያስችላል? የተገኘው ማስረጃ እንደሚያሳየው ይህ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው! ሎኒግ ያደረጉት ምርምር የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፦ “ከሌላው የሚለያቸው የራሳቸው የሆነ የጂን ባሕርይ ያላቸው ዝርያዎች በአጋጣሚ በተከሰተ ሚውቴሽን ምክንያት ሊፈርስ ወይም ሊጣስ የማይችል ድንበር አላቸው።”22
ከላይ የተጠቀሱት ሐቆች ምን አንድምታ እንዳላቸው ልብ በል። ከፍተኛ ሥልጠና የተሰጣቸው ሳይንቲስቶች ሚውቴሽን በማካሄድና ጥሩ የሆኑትን በመምረጥ አዳዲስ ዝርያዎችን ማስገኘት ካልቻሉ በአጋጣሚ የተከሰተ ሂደት ከዚህ የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? ሚውቴሽን አንድን ነባር ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ እንደማይችል በጥናት ከተረጋገጠ ታዲያ ማክሮኢቮሉሽን ተካሂዷል ተብሎ እንዴት ሊታሰብ ይችላል?
መላ ምት 2፦ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ዳርዊን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጋር መላመድ የቻሉት ሕያዋን ነገሮች በሕይወት መቀጠል ሲችሉ ሙሉ በሙሉ መላመድ ያልቻሉት ግን በጊዜ ሂደት ሞተው እንደሚያልቁ ያምን ነበር፤ ይህን ሂደት ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ብሎ ጠርቶታል። በዘመናችን የሚገኙ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ደግሞ የሕያዋን ነገሮች ዝርያዎች፣ ከዘመዶቻቸው በመለየት የነበሩበትን አካባቢ ለቀው አዲስ በሆነ አካባቢ መኖር በሚጀምሩበት ጊዜ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በአዲሱ አካባቢ ለመኖር የሚያስችላቸው የጂን ለውጥ ያደረጉ ዝርያዎችን ብቻ ይመርጣል ብለው ያስተምራሉ። በዚህም ምክንያት እነዚህ ተነጥለው መኖር የጀመሩት ዝርያዎች ቀስ በቀስ ተለውጠው ፈጽሞ አዳዲስ ዝርያዎች እንደሚሆኑ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ይናገራሉ።
ሐቁ፦ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ከምርምር የተገኘው ማስረጃ ሚውቴሽን ሙሉ በሙሉ አዳዲስ የሆኑ የዕፅዋት ወይም የእንስሳት ዝርያዎችን ሊያስገኝ እንደማይችል በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል። ቢሆንም የዝግመተ ለውጥ አማኞች ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ጠቃሚ የሆነ ሚውቴሽን ያካሄዱትን ዝርያዎች በመምረጥ አዳዲስ ዝርያዎችን እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፤ ይህንን ሐሳባቸውን ለመደገፍ ምን ማስረጃ ያቀርባሉ? በ1999 የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ያሳተመው አንድ ብሮሹር “ዳርዊን በጋላፓጎስ ደሴቶች ያጠናቸውንና በአሁኑ 23
ወቅት የዳርዊን ፊንቾች ተብለው የሚጠሩትን 13 የፊንች ዝርያዎች” እንደ ማስረጃ ይጠቅሳል።የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ ባልደረባ በሆኑት በፒተርና በሮዝሜሪ ግራንት የሚመራ የምርምር ቡድን በ1970ዎቹ ዓመታት በእነዚህ የፊንች ዝርያዎች ላይ ጥናት ማካሄድ ጀመረ፤ በደሴቶቹ ላይ ከተከሰተው አንድ ዓመት የቆየ ድርቅ በኋላ ትንሽ ተለቅ የሚል መንቆር ያላቸው ፊንቾች ትናንሽ መንቆር ካላቸው ፊንቾች ይልቅ ድርቁን በተሻለ ሁኔታ ተቋቁመው እንዳለፉ የምርምር ቡድኑ ተገነዘበ። አሥራ ሦስቱ የፊንች ዝርያዎች በዋነኝነት የሚለዩት በመንቆራቸው መጠንና ቅርጽ በመሆኑ ይህ ግኝት ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ብሮሹሩ በመቀጠል “ፒተርና ሮዝሜሪ ግራንት፣ በእነዚህ ደሴቶች ላይ በየአሥር ዓመቱ ድርቅ ቢከሰት በ200 ዓመት ውስጥ ብቻ አዲስ የፊንች ዝርያ ሊገኝ እንደሚችል ገምተዋል” ይላል።24
ይሁን እንጂ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ያሳተመው ይህ ብሮሹር ከድርቁ በኋላ ባሉት ዓመታት ትናንሽ መንቆር ያላቸው ፊንቾች እንደገና ቁጥራቸው እየተበራከተ መሄዱን ሳይጠቅስ አልፏል። ተመራማሪዎቹ በደሴቱ ላይ ያለው የአየር ንብረት ሲለዋወጥ በአንዱ ዓመት ረጅም መንቆር ያላቸው በሌላው ዓመት ደግሞ አጭር መንቆር ያላቸው ፊንቾች በዝተው እንደታዩ ተገንዝበዋል። በተጨማሪም የተለያዩ እንደሆኑ ከሚታሰቡት የፊንች ዝርያዎች መካከል አንዳንዶቹ እርስ በርስ ተዳቅለው ከወላጆቻቸው በተሻለ አስቸጋሪ ሁኔታ የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ወፎች እንዳስገኙ አስተውለዋል። ተመራማሪዎቹ፣ ወፎቹ እርስ በርስ መዳቀላቸውን ከቀጠሉ ሁለት “ዝርያዎች” ተቀላቅለው አንድ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።25
ታዲያ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በእርግጥ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ዝርያ ማስገኘት ይችላል? የዝግመተ ለውጥ የባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጆርጅ ክሪስቶፈር ዊልያምስ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ይህን የማድረግ ችሎታ ይኖረው እንደሆነ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ነበር።26 የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተመራማሪ የሆኑት ጀፍሪ ሽዎርዝ በ1999 በጻፉት መጽሐፍ ላይ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ፣ ዝርያዎች በአካባቢያቸው ከሚፈጠረው ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን አስማምተው መኖር እንዲችሉ ይረዳ እንደሆነ እንጂ ምንም አዲስ ነገር እንደማይፈጥር ገልጸዋል።27
በእርግጥም የዳርዊን ፊንቾች ዛሬም ቢሆን እነዚያው ፊንቾች ናቸው እንጂ “ምንም አዲስ ነገር” አልተፈጠረም። እንዲያውም እርስ በርሳቸው መዳቀል የሚችሉ መሆናቸው አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ዝርያ ለሚለው ቃል የሚሰጡት ፍቺ አጠራጣሪ እንዲሆን ያደርጋል። በተጨማሪም ስለ እነዚህ ወፎች የተገኘው መረጃ፣ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሳይንስ ተቋማት እንኳ የተዛባ ማስረጃ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ያመለክታል።
መላ ምት 3፦ ቅሪተ አካላት ትላልቅ የሆኑ ዝግመተ ለውጦች (ማክሮኢቮሉሽን) መካሄዳቸውን ያረጋግጣሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ያሳተመው ብሮሹር፣ ሳይንቲስቶች ያገኟቸው ቅሪተ አካላት ትላልቅ ዝግመተ ለውጦች መካሄዳቸውን በሚገባ እንዳረጋገጡ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል። ብሮሹሩ እንዲህ ይላል፦ “በዓሦችና በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ በሚኖሩ እንስሳት መካከል፣ በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ መኖር በሚችሉና በደረታቸው በሚሳቡ እንስሳት መካከል፣ በደረታቸው በሚሳቡና በአጥቢ እንስሳት መካከል እንዲሁም በዝንጀሮ መሰል ፍጥረታት መስመር ላይ በሚገኙት የተለያዩ እንስሳት መካከል የተካሄደውን ሽግግር የሚያሳዩ በርካታ ቅሪተ አካላት በመገኘታቸው ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው የተደረገው ሽግግር መቼ እንደተከናወነ በውል ለማወቅ ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ይሆናል።”ሐቁ፦ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ የሰነዘረው ይህ ድፍረት የተሞላበት ሐሳብ በጣም የሚያስገርም ነው። ለምን? ዝግመተ ለውጥን በጥብቅ የሚደግፉት ናይልዝ ኤልድሬጅ እንደተናገሩት የተገኙት ቅሪተ አካላት ቀስ በቀስ የተካሄደ ለውጥ መኖሩን አያሳዩም፤ ከዚህ ይልቅ በጣም ረጅም ለሆኑ ዓመታት “በአብዛኞቹ ዝርያዎች ላይ የተካሄደው ለውጥ በጣም ትንሽ መሆኑን ወይም ምንም ዓይነት የዝግመተ ለውጥ ሂደት አለመካሄዱን” ይጠቁማሉ። *29
ከተገኙት ቅሪተ አካላት መረዳት እንደሚቻለው ዋና ዋናዎቹ የእንስሳት ቡድኖች በሙሉ የመጡት በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በአንድ ጊዜ ነው፤ እንዲሁም እምብዛም ለውጥ ሳይታይባቸው ኖረዋል
እስከዛሬ ድረስ በመላው ዓለም የሚገኙ ሳይንቲስቶች 200 ሚሊዮን ያህል ትላልቅና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ትናንሽ ቅሪተ አካላትን ቆፍረው በማውጣት መዝግበው ይዘዋል። በርካታ ተመራማሪዎች በጣም ብዙ የሆኑት እነዚህ ቅሪተ አካላት፣ ዋና ዋናዎቹ የእንስሳት ቡድኖች በሙሉ የመጡት በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በአንድ ጊዜ እንደሆነና እምብዛም ለውጥ ሳይታይባቸው እንደኖሩ እንዲሁም ከእነዚህ ውስጥ በርካታ ዝርያዎች ልክ እንዳመጣጣቸው በአንድ ጊዜ እንደጠፉ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ይስማማሉ።
በዝግመተ ለውጥ ለማመን የሚያበቃ ምን ምክንያት አለ?
ብዙ እውቅ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ማክሮኢቮሉሽን የተረጋገጠ ሐቅ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱት ለምንድን ነው? ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሪቻርድ ለዎንተን፣ ብዙ ሳይንቲስቶች በማስረጃ ያልተረጋገጡ ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳቦችን ለመቀበል ፈቃደኛ የሚሆኑት “ማቴሪያሊዝምን ለመቀበል ቀደም ሲል ቁርጥ አቋም ስለያዙ” እንደሆነ ገልጸዋል። * ለዎንተን፣ ብዙ ሳይንቲስቶች የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ ሊኖር ይችላል የሚለውን ሐሳብ ከግምት ለማስገባት እንኳ አሻፈረን የሚሉበትን ምክንያት ሲገልጹ “አምላክ ደጃፋችን ላይ እንዲደርስ አንፈልግም” በማለት ጽፈዋል።30
በዚህ ረገድ ሮድኒ ስታርክ የተባሉት የሶሽዮሎጂ ባለሙያ “ሳይንሳዊ ሰው መሆን ከፈለግክ አእምሮህ ማነቆ ከሆነው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የጸዳ መሆን ይኖርበታል የሚለው አመለካከት ለ200 ዓመታት ሲሰበክ ቆይቷል” ብለው እንደተናገሩ ሳይንቲፊክ አሜሪካን ጠቅሷል። አክለውም ምርምር በሚካሄድባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ “ሃይማኖተኛ ሰዎች [ስለ አምላክ] ትንፍሽ አይሉም” ብለዋል።31
የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት እውነት እንደሆነ የምትቀበል ከሆነ አምላክ የለሽ የሆኑ ወይም ስለ አምላክ መኖር እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል የሚሰማቸው ሳይንቲስቶች የግል እምነታቸው ሳይንሳዊ ግኝቶችን በሚተረጉሙበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ አይፈቅዱም ብለህ ማመን ይኖርብሃል። ለአንድ ክፍለ ዘመን የተደረገው ምርምር ሚውቴሽን አንድን ዝርያ እንኳ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ እንዳልቻለ የሚያሳይ ቢሆንም ውስብስብ የሆነ አሠራር ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ የተገኙት በሚውቴሽንና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ ነው ብለህ ማመን ይኖርብሃል። ዋና ዋናዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ወገኖች የመጡት በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በአንድ ጊዜ እንደሆነና ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላም እንኳ ቢሆን ወደ ሌሎች ወገኖች እንዳልተለወጡ የሚያሳዩ ቅሪተ አካላት ቢኖሩም አንተ ግን ሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት ከአንድ የጋራ ግንድ በዝግመተ ለውጥ እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው ብለህ ማመን ይኖርብሃል። ታዲያ እንዲህ ያለው እምነት በሐቅ ላይ የተመሠረተ ነው ወይስ በመላ ምት? በእርግጥም በዝግመተ ለውጥ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት የለም።
^ አን.3 የውሻ ዝርያዎችን የሚያዳቅሉ ሰዎች የሚያስገኙት ለውጥ ብዙውን ጊዜ ጂኖች ተግባራቸውን በትክክል ባለማከናወናቸው ምክንያት የሚመጣ ነው። ለምሳሌ፣ ዳክስሁንት የተባለው የውሻ ዝርያ ድንክዬ የሆነው በሰውነቱ ውስጥ የሚገኘው እንደ አጥንት ያለ ለስላሳ ነገር (cartilage) በተገቢው መንገድ ማደግ ባለመቻሉ ነው።
^ አን.6 በዚህ ክፍል ውስጥ “ዝርያ” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠቀስም ቃሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደማይገኝ ልብ ሊባል ይገባዋል። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ‘ወገን’ የሚለውን ቃል ሲሆን ይህ ቃል ሰፋ ያለ ትርጉም አለው። ብዙውን ጊዜ ሳይንቲስቶች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት አዲስ ዝርያ እንደተገኘ የሚገልጹት በአንድ ‘ወገን’ ውስጥ የሚከሰተውን ልዩነት በማየት ነው።
^ አን.8 የአንድን ሕይወት ያለው ነገር ባሕርያት በመወሰን ረገድ የሴሉ ሳይቶፕላዝም (በሴሉ ውጪያዊ ሽፋንና በኒውክሊየስ መካከል ያለው ክፍል)፣ ውጪያዊ ሽፋን እና ሌሎች ነገሮች የሚጫወቱት ሚና እንዳለ በምርምር ተደርሶበታል።
^ አን.9 ሎኒግ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ያምናሉ። በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰው የሎኒግ አስተያየት የራሳቸው እንጂ የማክስ ፕላንክን የምርምር ተቋም የሚወክል አይደለም።
^ አን.10 የሚውቴሽን ሙከራዎች ብዙ ጊዜ እንዳረጋገጡት በሚውቴሽን አማካኝነት አዳዲስ ባሕርያት ያላቸውን ዝርያዎች የማግኘቱ አጋጣሚ እየቀነሰ የሚሄድ ሲሆን ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም የሚገኙት ዝርያዎች ቀደም ሲል ከተገኙት የተለዩ አይሆኑም። በተጨማሪም ከዕፅዋት ሚውቴሽን ውጤቶች ውስጥ ለቀጣይ ምርምር የተመረጡት ከ1 በመቶ ያነሱ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ለንግድ መዋል እንደሚችሉ የታመነባቸውም ከ1 በመቶ ያነሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ አንድም ዝርያ እስከ ዛሬ አልተፈጠረም። እንስሳትን በሚውቴሽን በማዳቀል የተገኘውም ውጤት ዕፅዋትን በማዳቀል ከተገኘው ውጤት የከፋ በመሆኑ ዘዴው ጨርሶ ሥራ ላይ እንዳይውል ተደርጓል።
^ አን.21 ተመራማሪዎች ዝግመተ ለውጥ ለመካሄዱ እንደ ማስረጃ የሚጠቅሷቸው ጥቂት የቅሪተ አካል ግኝቶችም ቢሆኑ አወዛጋቢ ሆነው ተገኝተዋል። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የሚለውን ብሮሹር ከገጽ 22 እስከ 29 ተመልከት።
^ አን.24 “ማቴሪያሊዝም” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው ሁሉንም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ጨምሮ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለው ነገር በሙሉ ወደ ሕልውና የመጣው ከሰው በላይ በሆነ ኃይል እንዳልሆነ የሚገልጸውን ጽንሰ ሐሳብ ነው።