በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመንግሥቲቱ ብቁ ለመሆን መጣጣር

ለመንግሥቲቱ ብቁ ለመሆን መጣጣር

ምዕራፍ 6

ለመንግሥቲቱ ብቁ ለመሆን መጣጣር

1. (ሀ) መንግሥትን በሚመለከት ሰዎች ከሚሰጡት ጋር ሲነጻጸር ይሖዋ ምን አቅርቧል? (ለ) ሕይወታችንን ያለምንም ስጋት በአምላክ ቃል ላይ ለመገንባት የምንችለው ለምንድን ነው?

አንድ በጣም ተፈላጊ የሆነ ነገር ቢቀርብልህ ምን ታደርጋለህ? እጅህን ዘርግተህ አትቀበለውምን? እንግዲያው ይሖዋ አምላክ ፍጹም በሆነ አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶልሃል። እውነት ነው፤ ዛሬ ባሉት መስተዳድሮች ውስጥ ብዙ ፖለቲከኞች ምግባረ ብልሹዎች ናቸው። ይህን ወይም ያን እናደርግላችኋለን እያሉ የሚገቡት ቃል ብዙ ጊዜ ውሸት ሆኖ ይቀራል። ቀና አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎችም ቢሆኑ ከአምላክ ሉዓላዊነት ውጭ ጥሩ መስተዳድር ማምጣት የማይችሉ መሆናቸው ተረጋግጧል። (ምሳሌ 20:24) ይሁን እንጂ አምላክ ከጥንት ጀምሮ ፍጹም ወደሆነችው መንግሥታዊ አገዛዙ መቋቋም የሚያመሩ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ ሲወስድ የቆየ ሲሆን ጽድቅ አፍቃሪ የሆኑ ሰዎችም ከዚህች ንጉሣዊ መስተዳድር ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቦላቸዋል። የእርሱ ዓላማ ትምክህት የሚጣልበትና እውነተኛ ነው። አምላክ ሊዋሽ አይችልም። ሕይወታችንንም በቃሉ ላይ ያለ ምንም ስጋት መገንባት እንችላለን። — ራእይ 21:1–5፤ ቲቶ 1:2

2. (ሀ) አምላክ የጽድቅ መንግሥት ለመመሥረት ያለውን ዓላማ የገለጸው መቼና እንዴት ነው? (ለ) ለመንግሥቱ ተስፋ ራሳቸውን ብቁ ስላደረጉት ሰዎች ዕብራውያን 11:4–7 ምን የሚገልጽልን ነገር አለ?

2 የጽድቅ መንግሥት ለመመሥረት አምላክ ያለው ዓላማ አዲስ አይደለም። በኤደን ውስጥ የአምላክ ሉዓላዊነት ጥያቄ በተነሣበት ጊዜ አምላክ ሰይጣንንና ዘሮቹን ‘የሚቀጠቅጥ’ “ዘር” ለማምጣት ዓላማው መሆኑን አስታወቀ። (ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 16:20) በዚያ በጥንቱ ዓለም ላይ ዓመጽ ነግሦ ሳለ አቤል፣ ሄኖክና ኖኅ በዚህ የይሖዋ ተስፋ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። አምላክ ‘ከልብ ለሚፈልጉት’ ዋጋ እንደሚሰጥ ሙሉ እምነት ስለነበራቸው ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ለማድረግና’ ጽድቅን ለመስበክ መርጠዋል፤ እንዲሁም የደረሰባቸውን ነቀፋ ተቋቁመዋል። (ዕብራውያን 11:4–7) ‘በምትመጣዋ’ የአምላክ መንግሥት ላይ እምነት ላላቸው በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩት ሁሉ እነዚህ እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው!

ትኩረታችንን የሚስብ አንድ የትውልድ መሥመር

3. በዘፍጥረት 12:1–7 መሠረት አብርሃም ድንቅ ምሳሌ የሆነልን እንዴት ነበር?

3 የጥፋት ውኃው ከደረሰ ከ400 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ተስፋ የተደረገበት ንጉሣዊ “ዘር” ከአብርሃም የትውልድ መሥመር የሚመጣ መሆኑን አምላክ ግልጽ አደረገ። ይሁንና ከአብርሃም የትውልድ መሥመር እንዲመጣ የተደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ የላቀ እምነት ስላየበት ነው። የትውልድ አገሩ ከሆነችው ዑር ከምትባል የከለዳውያን ከተማ አብርሃምን ጠርቶ ለእርሱ እንግዳ ወደሆነው የከነዓን ምድር እንዲሄድ ነገረው። አምላክ እንዲህ አለ:-

“የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። . . . ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” (ዘፍጥረት 12:3, 7፤ ሥራ 7:4)

አብርሃም ከወገኖቹ ጋር ተጣብቆ ከመቅረት ይልቅ እንደገና ፈጽሞ ላለመመለስ አገሩን ጥሎ ወጣ። ለሉዓላዊው ገዥ ለይሖዋ ፍጹም ታዛዥነት ለማሳየት ሲል አኗኗሩን ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ ፈቃደኛ ነበር። በእርግጥም ዛሬ ራሳቸውን ለይሐዋ ወስነው ለሚኖሩ ሁሉ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

4. ሣራ በእምነትዋ ምክንያት የተባረከችው እንዴት ነበር? (ዕብራውያን 11:11, 12)

4 ሚስቱ ሣራ እስከ እርጅናዋ ዘመን ድረስ መኻን ሆና ብትቆይም ይሖዋ ለአብርሃም በኋላ እንዲህ በማለት አረጋግጦለት ነበር:- “እባርካትማለሁ፣ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ።” (ዘፍጥረት 17:16) ታማኝዋ ሣራ በ90 ዓመቷ የብዙ ነገሥታት ቅድመ አያት የሆነውን ይስሐቅን ለአብርሃም በመውለድ ተባርካለች። — ማቴዎስ 1:2, 6–11፤ ራእይ 17:14

5. አብርሃምና ይስሐቅ ላሳዩት ታዛዥነት ዋጋ የተቀበሉት እንዴት ነበር?

5 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በአብርሃምና በይስሐቅ ላይ ልብን የሚመረምር ፈተና እንዲመጣባቸው አደረገ። አብርሃም ከሣራ የተወለደውን አንድ ልጁን የሦስት ቀን ጉዞ በማድረግ ወደ ሞርያ ተራራ ወስዶ በዚያ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት አምላክ አዘዘው። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ 25 ዓመት ዕድሜ ሊሞላው ስለሚችል ከባዱን የመሥዋዕት እንጨት ተሸክሞ ወደ ተራራው ለመውጣት ችሎ ነበር። እንዲሁም ቢፈልግ 125 ዓመት የሆነውን ሽማግሌ አባቱን ለመቋቋም በቂ ጉልበት ነበረው። ይሁን እንጂ የአባትና የልጅ ታዛዥነት በዚህ ስሜት ቀስቃሽ ድራማ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ታየ። አብርሃም የሚያርድበትን ቢላዋ ሲያነሣ የይሖዋ መልአክ እጁን ያዘው። በይስሐቅ ምትክ ቦታ አንድ በግ ተሠዋ። — ዘፍጥረት 22:1–14

6. (ሀ) በዚያ የተከናወነው ትንቢታዊ ምሳሌ ምንድን ነው? (ለ) በዘፍጥረት 22:18 ላይ የተገለጸው ተስፋ የአንተን ልዩ ትኩረት የሚስብ ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው?

6 እዚህ ላይ አምላክ የሰውን ዘር ዓለም ኃጢአት ለማስወገድ የራሱን ልጅ እንዴት መሥዋዕት እንደሚያደርግ የሚያሳይ አንድ ትንቢታዊ ምሳሌ እየሠራ ነበር። (ዮሐንስ 1:29፤ ገላትያ 3:16) ይህን የምንልበት ምክንያት ከዚያ በኋላ አምላክ ለአብርሃም እንዲህ አለው:-

“የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ [ራሳቸውን አዓት] ይባርካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና።” — ዘፍጥረት 22:15–18

7. እንዴት ያለ አካሄድ ቢኖረን ይሖዋ ዋጋ ይከፍለናል?

7 አብርሃምና ይስሐቅ በታዛዥነት ረገድ እንዴት ያሉ የላቁ ምሳሌዎች ናቸው! የእነርሱን ዓይነት መሥዋዕት እንድናደርግ ላንጠየቅ እንችላለን። ነገር ግን ልክ እነርሱ እንዳደረጉት ለይሖዋ ካለን ልባዊ ፍቅር የተነሣ አምላክ የሚነግረንን ማንኛውንም ነገር እሺ ብለን መታዘዛችን አስፈላጊ ነው። (ያዕቆብ 4:7፤ 2 ቆሮንቶስ 9:13) ‘ለምትመጣዋ መንግሥት’ ብቁ ለመሆን ሲባል የራስህን ጥቅምና የስስት ፍላጎቶችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን ምን ጊዜም ይሖዋ የሚቀበለውና ዋጋ የሚከፍልበት አካሄድ ነው። — ማቴዎስ 6:33

8. (ሀ) የያዕቆብ አካሄድ ከኤሳው አካሄድ ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? (ለ) ይስሐቅ ያዕቆብን ምን ብሎ ባረከው?

8 ለመንግሥቲቱ ራሱን ብቁ ያደረገው ሌላው ሰው የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ ነው። ነገር ግን መንትያ ወንድሙ ኤሳው ከነዓናውያን ሴቶችን በማፍቀርና ቁሳዊ ነገሮችን በስስት በመውደድ ቅዱስ ነገሮችን አቃለለ። ክቡር የሆነውን የብኩርና መብቱን በተራ የምስር ወጥ ለያዕቆብ ሸጠ! (ዕብራውያን 12:16) መንፈሳዊ አስተሳሰብ የነበረው ያዕቆብ የብኩርናውን መብት ከፍ አድርጎ ተመለከተ፤ ይሖዋም ያዕቆብ ያንን መብት ለማግኘት ይችል ዘንድ የሽማግሌውን የይስሐቅን በረከት እንዲቀበል ሁኔታዎችን አመቻቸ። ኤሳው አጋንንት አምላኪ የሆኑ ሴቶችን አግብቶ ነበር፤ ያዕቆብ ግን በተቃራኒው ይሖዋን ከሚያመልኩት ሕዝቦች መካከል ሚስት ለመፈለግ እስከ መስጴጦምያ ድረስ ረጅም መንገድ ተጉዟል። በዚያን ጊዜ ይስሐቅ ለያዕቆብ እንዲህ በማለት አረጋገጠለት:-

“ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ ይባርክሃል፤ ፍሬያማ ያደርግሃል፣ ያበዛሃል፤ አንተም የብዙ ሕዝብ ጉባኤ ትሆናለህ።” — ዘፍ. 25:27–34፤ 26:34, 35፤ 27:1–23፤ 28:1–4

9. (ሀ) የያዕቆብ ስም እስራኤል ተብሎ የተለወጠው ለምንድን ነው? (ለ) በእርሱ ምሳሌ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

9 በኋላም ያዕቆብ ወደ መቶ ዓመቱ ገደማ ለመንፈሳዊ ነገሮች ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጥ በድጋሚ አሳይቷል። በረከት ለማግኘት ሌሊቱን ሙሉ ከአንድ መልአክ ጋር ሲታገል አደረ። የአምላክ ሞገስ መግለጫ ይሆን ዘንድ ይሖዋ በዚያ ቦታ የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል አለው፤ ትርጉሙም “ከአምላክ ጋር ታግሎ የማይታክት” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 32:24–30) እኛም ዛሬ በዙሪያችን ያለውን የክፉውን ዓለም መንፈስ እየሸሸን መንፈሳዊ ሃብት ለማግኘት ሳንታክት ብንጥር ሽልማት ለማግኘት እንችላለን። — ማቴዎስ 6:19–21

10. (ሀ) በዘፍጥረት 28:3 ላይ የሚገኘው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) በግለሰብ ደረጃ የታመኑ መሆንን በተመለከተ በዕብራውያን 11:1 እስከ 12:1 ላይ የሚገኙት ልብን በደስታ የሚያሞቁ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

10 ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ የያዕቆብን ተወላጆች “የብዙ ሕዝብ ጉባኤ” አድርጎ አደራጅቷቸዋል። በእርሱና በሕዝቡ መካከል በነበረው መካከለኛና መጽሐፍ ቅዱስንም ማስጻፍ ሲጀምር በተጠቀመበት በሙሴ አማካኝነት አምላክ ለዚህ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በማለት ጥሪ አድርጎለት ነበር:-

“ድምፄን በጥንቃቄ ብትታዘዙ . . . እናንተ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” (ዘጸአት 19:5, 6 አዓት)

ነገር ግን ያሳዝናል፤ የአምላክን ድምፅ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሥጋዊ እስራኤላውያን መንፈሳዊ መንግሥት መሆን ሳይችሉ ቀሩ። ቢሆንም ከዚያ ሕዝብ መካከል እንደ እስራኤል መሳፍንት፣ ነቢያትና በመጀመሪያ አመንዝራ እንደነበረችው እንደ ረዓብ ያሉ ብዙ ግለሰቦች በአምላክ ፊት ፍጹም አቋም እንዳላቸው አረጋግጠዋል። ስለነዚህ ታማኝ “ምሥክሮች” በዕብራውያን 11:1 እስከ 12:1 ላይ የቀረበውን መግለጫ ማንበብ እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ለሚገኙትና ‘የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ’ ለሚጠባበቁ ሁሉ እነዚህ እንከን የለሽ አቋም የጠበቁ ሁሉ የጋለ ማበረታቻ ይሆኑናል።

11. እንደነዚህ የታመኑ ምሥክሮች ለመሆን የምትችለው እንዴት ነው?

11 በእምነት ጠንካራ ለመሆን ትፈልጋለህን? ‘ሰማያዊ ለሆነ ለሚበልጠው ሥፍራ’ ይኸውም ‘መሠረት ላላት፣ አምላክ ለሠራትና ለፈጠራት ከተማ’ ተጣጥረህ በመብቃት ዛሬ እንደነዚያ የእምነት ወንዶችና ሴቶች ለመሆን ትፈልጋለህን? (ዕብራውያን 11:10, 16) ‘ግን ያች ከተማ ምንድን ነች?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

አምላክ የሠራት ከተማ

12. እነዚያ የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ለማግኘት ይጣጣሩ የነበሩት የትኛዋን “ከተማ” ነበር? (ዕብራውያን 11:22–32፤ ሩት 1:8, 16, 17 ተመልከት።)

12 ያች “ከተማ” አምላክ አመጣላችኋለሁ ብሎ ቃል የገባልን መንግሥት ነች። ለምን እንዲህ እንላለን? በድሮ ዘመን ብዙ ጊዜ አንዲት ከተማ በአንድ ንጉሥ የምትገዛ መንግሥት ተደርጋ ትታይ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተቀባይነት እንዳለው ሆኖ የተገለጸው የመጀመሪያው ንጉሥ “የሳሌም (ከተማ) ንጉሥ መልከ ጼዴቅ የልዑል አምላክ ካህን” ነበር። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የኢየሩሳሌም ከተማ የተቆረቆረችው በዚያው ቦታ ላይ ነበር። ልክ እንደ ሳሌም ከተማ ሁሉ ኢየሩሳሌምም በታላቁ ንጉሥና ካህን በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራዋን ሰማያዊቱን መንግሥት የምታመለክት ሆነች። (ዘፍጥረት 14:1–20፤ ዕብራውያን 7:1, 2, 15–17፤ 12:22, 28) በዚያን ጊዜ ዝርዝር ሁኔታውን ባያውቁትም እንኳን አብርሃምና ሣራ እንዲሁም ይስሐቅና ያዕቆብ መሲሑ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛባትን “ከተማ” በናፍቆት ይጠባበቁ ነበር። “አብርሃም በተስፋው ሐሴት አደረገ።” አንተም በዚያ መንግሥታዊ ዝግጅት ውስጥ ቦታ ለማግኘት በእምነት ከጣርክ ደስታ ልታገኝ ትችላለህ። — ዕብራውያን 11:14–16፤ ዮሐንስ 8:56

13, 14. ያዕቆብ ሊሞት ሲል አልጋው ላይ ሆኖ የተናገረው ትንቢት መፈጸም የጀመረው እንዴት ነው?

13 ያዕቆብ ከጊዜ በኋላ የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች አባቶች የሆኑ 12 ልጆችን ወለደ። ያዕቆብ ሊሞት ሲል አልጋው ላይ ሆኖ ከ12ቱ ነገዶች ውስጥ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚኖረውንና አምላክ የሚሾመውን ገዥ የሚያስገኘው ነገድ የትኛው እንደሆነ ሲያመለክት እንዲህ አለ:-

ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው። . . . በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ገዥ የሆነው (ሴሎ) [ትርጉሙ ባለመብት የሆነው ማለት ነው] እስኪመጣ ድረስ የአሕዛብ መታዘዝ ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍጥረት 49:9, 10)

ታዲያ ሴሎ ከይሁዳ መጥቷልን? አዎን፣ በትክክል መጥቷል!

14 የያዕቆብ ትንቢት እንዴት እንደሚፈጸም ከ600 ዓመታት በኋላ መገለጥ ጀመረ። ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ ‘እንደ ልቡ የሆነውን ሰው’ የመረጠው ያን ጊዜ ነበር። ይህ ሰው ዳዊት ይባላል። አምላክ ይህንን ደፋር ‘የይሁዳ አንበሳ’ በሕዝቡ በእስራኤል ላይ መሪና ንጉሥ አደረገው። (1 ሳሙኤል 13:14፤ 16:7, 12, 13፤ 1 ዜና መዋዕል 14:17) ይሖዋ ለንጉሥ ዳዊት የዘላለም መንግሥት እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። — መዝሙር 89:20, 27–29

15. ይሖዋ የይሁዳን መንግሥት የገለበጠው ለምንድን ነው? ለምን ያህል ጊዜስ?

15 በ1077 ከዘአበ መግዛት የጀመረው ዳዊት በኢየሩሳሌም ላይ በገዛው የይሁዳ ነገሥታት ሥርወ መንግሥት ውስጥ የመጀመሪያው ንጉሥ ሆነ። ከዚያ በኋላ የተነሣው ማንኛውም የእሥራኤል ንጉሥ ይሖዋን በፈቃደኝነት እስከታዘዘ ድረስ ሕዝቡ በደኅና ይኖር ነበር። ነገር ግን አንድ ንጉሥ ክፉ በሆነና በይሖዋ የጽድቅ ሕግጋት ላይ ባመፀ ጊዜ ሕዝቡ መከራ ይደርስበት ነበር። (ምሳሌ 29:2) የመጨረሻው የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በጣም ክፉ ሰው ነበር። የአምላክ ነቢይ እንዲህ በማለት አስታወቀው:- “ዘውዱን አውልቅ . . . ባድማ፣ ባድማ፣ ባድማ አደርጋታለሁ። [ሕጋዊ መብት ያለው አዓት] እስኪመጣ ድረስ . . . ለእርሱም እሰጣታለሁ።” ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ “ሕጋዊ መብት” ያለው ንጉሥ እስኪመጣ ድረስ ያን መንግሥት ገለበጠው። — ሕዝቅኤል 21:26, 27 አዓት

“ሕጋዊ መብት” ያለው ንጉሥ

16. የመንግሥቲቱን ቋሚ ወራሽ ቅዱሳን ጽሑፎች ለይተው የሚያመለክቱት እንዴት ነው?

16 የዳዊትን መንግሥት ለመረከብ “ሕጋዊ መብት” የሚወርሰው ማን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የማቴዎስ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ 17 ቁጥሮች መልሱን ይሰጣሉ። ቁጥሮቹ ተስፋ የተደረገበትን “ዘር” መሥመር ከአብርሃም እስከ ዳዊት ከዚያም የማርያም ባል እስከሆነው እስከ ዮሴፍ ድረስ ይዘረዝራሉ። ስለሆነም የማርያም የበኩር ልጅ መንግሥቱን የመውረስ “ሕጋዊ መብት” ሊኖረው ቻለ። ይህም በመሆኑ በ2 ከዘአበ መጀመሪያ ላይ መልአኩ ገብርኤል ልጁ በማሕፀንዋ ውስጥ በተአምር የሚፀነስ ስለመሆኑ ማስታወቅ ችሏል።

“ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፣ እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል። እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:26–33)

ይሖዋ በመቶ በሚቆጠሩ ዘመናት ወቅት የዳዊት መንግሥት ቋሚ ወራሽ የሚሆነውን ይህንን ንጉሥ የማምጣት ዓላማውን ለማሳካት በአስደናቂ ሁኔታ ነገሮችን ሲያከናውን ቆይቶ ነበር። እነዚህን ነገሮች ስንመረምር ‘መንግሥቲቱ እንደምትመጣ’ አምላክ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት አያጠነክሩትምን?

17, 18. (ሀ) ሰማያዊቷን መንግሥት የሚወርሱት እነማን ብቻ ናቸው? (ለ) በምድር ላይ ከሞት የሚነሡት አንዳንዶቹ የታመኑ ሰዎች እነማን ናቸው? (ሐ) ይህንን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያበረታታን ይገባል?

17 ይህ ሲባል ሁላችንም በሰማያዊቱ መንግሥት ከኢየሱስ ጋር እንሆናለን ብለን መጠበቅ እንችላለን ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ መብት የተጠበቀው ከደቀ መዛሙርቱ ውስጥ “ታናሽ መንጋ” ለሆኑት ብቻ ነው። (ሉቃስ 12:32) ንጉሥ ዳዊትም እንኳ እንዲህ ያለ ተስፋ አልነበረውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” ብሎ ይነግረናል። (ሥራ 2:34) ዮሐንስ መጥምቁም ሆነ በድሮ ዘመን የነበሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ወደ “መንግሥተ ሰማያት” አይገቡም። — ማቴዎስ 11:11፤ ዕብራውያን 11:39, 40

18 ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት በንጹሕ አቋም የጸኑ ታማኝ ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ትንሣኤ ያገኛሉ። ከእነርሱም ብዙዎቹ በአምላክ መንግሥታዊ ዝግጅት ውስጥ “መሳፍንት” ይሆናሉ። (መዝሙር 45:16) እነርሱን ከመቃብር ለመቀበልና ከእነርሱ ጋር በቅርብ ተገናኝተህ ለመጫወት አትፈልግምን? እንደምትፈልግ አያጠራጥርም! እንግዲያው ዛሬ ያን ታላቅ አጋጣሚ ከሚያደንቁት ጋር “ለአምላክ መንግሥት አብረህ የምትሠራ” በመሆን ተጣጥረህ ለዚያች “ከተማ” ራስህን ብቁ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን። — ቆላስይስ 4:11

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 52, 53 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለአምላክ መንግሥት ብቁ ሆኑ

አቤል 3900 ከዘአበ ገደማ

ኖኅ 2970–2020 ከዘአበ

አብርሃም፣ ሣራ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ 2018–1711 ከዘአበ

ዮሴፍ 1767–1657 ከዘአበ

ሙሴ 1593–1473 ከዘአበ

ረዓብ 1473 ከዘአበ

መሳፍንት 1473–1117 ከዘአበ

ሩት፣ ኑኃሚን 1300 ከዘአበ ገደማ

ዳዊት 1107–1037 ከዘአበ

ነቢያት 1117–442 ከዘአበ

አጥማቂው ዮሐንስ 2 ከዘአበ–31 እዘአ