በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመንግሥቲቱ የቆሙ ታማኝ ጠበቆች

ለመንግሥቲቱ የቆሙ ታማኝ ጠበቆች

ምዕራፍ 15

ለመንግሥቲቱ የቆሙ ታማኝ ጠበቆች

1. ዳንኤል ምን ከፍተኛ ክንዋኔዎች እንደሚኖሩ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር?

የዳንኤል ትንቢት ብዙ ዘመናት ቀደም ብሎ 29 እዘአ መሲሑ የሚገለጥበት ዓመት እንደሚሆንና 1914 ደግሞ ሰማያዊ ክብር በማግኘት ዙፋን ላይ የሚቀመጥበት ዓመት እንደሚሆን አመልክቶ ነበር። ከዚህም በላይ ዳንኤል ዓለምን ስለ መግዛት የተፈጠረው ውዝግብ እንዴት እልባት እንደሚያገኝም በዝርዝር ተንብዮአል።

2. በአሁኑ ጊዜ እልባት ማግኘት የሚገባው የትኛው አካራካሪ ጉዳይ ነው? በየትኛውስ ችሎት?

2 አሁን ምድርን ለመግዛት መብት ያለው ማን ስለ መሆኑ የተነሣው አከራካሪ ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ ውሳኔ ማግኘት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ በየትኛው ችሎት? በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ በሌለው ታላቅ ችሎት እልባት ማግኘት ይኖርበታል! ዳንኤል ይህንን በሚከተሉት ቃላት ይገልጸዋል:-

“ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፣ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፣ የራሱም ጠጉር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበር፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበር፣ መንኮራኩሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፣ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር። ፍርድም ሆነ መጻሕፍትም ተገለጡ።” — ዳንኤል 7:9, 10

3. (ሀ) ዳኛው ማን ነው? (ለ) “መጻሕፍቱ” ምን ያሳያሉ? (ሐ) ምን ፍርድ ተሰጠ?

3 “የዘላለም ንጉሥ” የሆነው ይሖዋ አምላክ ፍርድ ለመስጠት ችሎቱ ላይ ተቀምጧል። (ራእይ 15:3) ይሁን እንጂ በፊቱ ተከፍተው የተዘረጉት “መጻሕፍት” ምንድን ናቸው? በታሪክ ውስጥ የብሔራትን አገዛዝ አሳዛኝ ታሪክ የያዙ መዛግብት ናቸው። የአሕዛብ ዘመናት በ1914 እዘአ ቢያበቁም “ችሎቱ” ‘የመንግሥቶቻቸውን’ ሥልጣን ወስዶባቸዋል። ይህ እርምጃ ተገቢ ነው። “የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ” ማለትም አርማጌዶን ላይ የአምላክ ፍርድ እስከሚፈጸምባቸው ድረስ ይቆያሉ። — ዳንኤል 7:12፤ ራእይ 16:14, 16

4, 5. (ሀ) ግዛት ለማን ተሰጠ? (ለ) የንጉሡን መገኘት ለማስተዋል የምንችለው እንዴት ብቻ ነው?

4 ታዲያ የመግዛት ሥልጣን ለማን መሰጠት አለበት? ዳንኤል ቀጥሎ እንዲህ ይላል:-

“በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፤ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ፤ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” — ዳንኤል 7:13, 14

5 ይህ “የሰው ልጅ የሚመስል” የተባለው ማን ነው? የላቀ ክብር ከተቀዳጀው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ‘የሰማይ ደመናት’ የሚያመለክቱት ከዓይን መሰወርን ስለሆነ የኢየሱስን መገኘትና በ1914 እዘአ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” በሆነበት ጊዜ በምድር ላይ በተፈጸሙት ሁኔታዎች ገሀድ የሆነውን ሰማያዊ “ምልክት” ለማየት የምንችለው በእምነት ዓይናችን ይኸውም በማስተዋል ነው። — ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ራእይ 1:7

6. (ሀ) እነማን ጭምር ተፈረደላቸው? (ለ) እነርሱ ምን ተቀበሉ? እንዴትስ?

6 በዳንኤል ትንቢት ላይ ቀጥሎ “የልዑሉ ቅዱሳን” እንደ ተፈረደላቸውና እነሱም ጭምር “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት” እንደተሰጣቸው እንመለከታለን። (ዳንኤል 7:22, 27) እነዚህ “ቅዱሳን” እነማን ናቸው? ለረጅም ዘመናት ሕዝብን ሲጨቁኑ ከቆዩትና በሰብአዊ መስተዳድር ውስጥ የራሳቸው ጥቅም ብቻ ከሚታያቸው ገዥዎች ጋር የተራራቀ ልዩነት እንዳላቸው ግልጽ ነው። እነዚህ “ቅዱሳን” ቅቡዓኑ 144,000ዎች እንጂ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም። እነርሱ በሰማያዊ መንግሥቱ ‘ከሰው ልጅ’ ጋር ተባባሪ ገዥዎች ለመሆን ‘ከሰው ልጆች መካከል የተዋጁ’ እና ንጹሕ አቋም በመጠበቅ በኩል ‘ነውር የሌለባቸው’ ሰዎች ናቸው። “በመጨረሻው ቀን” ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ከሞት ይነሣሉ። (ራእይ 14:3–5፤ ማቴዎስ 24:30፤ ዮሐንስ 6:40) ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ የእነዚህ “ቅዱሳን” ቀሪዎች በምድር ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ በሕይወት መገኘት አለባቸው። የሚሠሩት ሥራ አላቸው!

ለአምላክ ቃል የቆሙ ጠበቆች

7, 8. (ሀ) የመሰናዶ ሥራ የጀመረው የትኛው ቡድን ነው? መቼ? (ለ) ወደ ጎን የጣሉት ነገር ምንድን ነው? (ሐ) ለምን ነገር ኀይለኛ ጠበቆች ሆነው ቆሙ? (መ) የትኛውን ዓመት አስቀድመው አመልክተው ነበር? (ሠ) የአምላክን መንግሥት ለማሳወቅ በምን መሣሪያ ተጠቅመዋል?

7 “የሰው ልጅ” መንግሥቱን የሚቀበልበት ጊዜ ሲደርስ በዚህ ምድር ላይ አንዳንድ መሰናዶ መደረጉ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ግልጽ ነበር። በ1870ዎቹ ዓመታት ቻርልስ ቴዝ ራስል በፒትስበርግ ፔንሲልቫኒያ ዩናይትድ ስቴትስ ለአምላክ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች አባል የሆኑበት አንድ ትንሽ ቡድን አደራጅቶ ነበር። እነዚህ ሰዎች የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የተመሠረቱት በባቢሎናዊ ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ እንደሆነ፤ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ በማይገኘው ነፍስ አትሞትም በሚለው የፕላቶ ትምህርት ላይ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዚህ አናሳ ቡድን አባሎች የሐሰት ሃይማኖትን ወደ ጎን በመተው ስለ ኢየሱስ ቤዛ፣ ስለ ትንሣኤና የአምላክ መንግሥት በሥቃይ ላይ ላለው የሰው ልጅ ተስፋ መሆንዋን ለሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ኃይለኛ ጠበቆች ሆኑ።

8 ከሐምሌ 1879 ጀምሮ ያለማቋረጥ በመታተም ላይ ባለው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አማካኝነት ራስልና ጓደኞቹ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በመቃወም ለመጽሐፍ ቅዱሱ የፍጥረት ዘገባ ጥብቅና ቆመዋል። ‘ከሰው አካል የወጡ ነፍሳት’ የሚሠቃዩበት እሳታማ ሲኦል ፈጽሞ እንደሌለ በመግለጽና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው “ሲኦል” መቃብርን እንደሚያመለክት ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው በማሳየት ‘በእሳታማው ሲኦል ላይ ውኃ አፍስሰውበታል።’ (መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:29–32) 1914 እዘአ ከአምላክ መንግሥት ‘መምጣት’ ጋር በተያያዘ ልዩ ዓመት እንደሚሆን አስቀድመው አመለከቱ። ባሁኑ ወቅት በ118 የተለያዩ ቋንቋዎች በብዙ ሚልዮን እየታተመ የሚወጣው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ እስከ ዛሬ ድረስ ለሰው ዘር ብቸኛዋ ተስፋ በክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት እንደሆነች ታማኝ ጠበቃ ሆኖ ይከራከራል። — ማቴዎስ 12:21፤ መዝሙር 145:10–12

9. ራእይ 11:7–12 በእነዚህ “ምሥክሮች” ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?

9 ቻርልስ ቴዝ ራስል የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት በመሆን ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት ካገለገለ በኋላ ጥቅምት 31, 1916 አረፈ። በእርሱም ቦታ ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ተተካ። ቄሶች በጊዜው ጦርነት በፈጠረው ግርግር ተጠቅመው በመንግሥቱ መልእክት ላይ ተቃውሞ እንዲነሣ ሽር ጉድ ብለው ነበር። የክርስቲያን ስብሰባዎች እንዲቋረጡ ተደረጉ። በተለያዩ አገሮች የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ታሰሩ። በብሩክሊን ኒው ዮርክ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ራዘርፎርድና ሌሎች የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው ሰባት አገልጋዮች የብዙ ዓመታት እስር ተፈረደባቸው። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደነዚህ ያሉ ስደቶች እንደሚመጡ አስቀድሞ ስለ ተናገረ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች አልተደናገጡም። ለምሳሌ ያህል ራእይ 11:7–12 ‘በአውሬ’ የተመሰሉት ዓለማዊ መንግሥታት በአምላክ “ምሥክሮች” ላይ ጦርነት በመክፈት ‘ሊያሸንፏቸውና ሊገድሏቸው’ እንደሚሞክሩ ይገልጻል። ትንቢት መናገራቸው እንደሚቆም ተገልጿል። በምሳሌያዊ ሁኔታም በድናቸው በሕዝበ ክርስትና “አደባባይ” ላይ መሽተት እስኪጀምር ድረስ ብዙ እንደሚቆይ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። በመላው ዓለም የአምላክ አገልጋዮች ለሕዝብ መሳለቂያ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ይህ ሁሉ ነገር ደርሷል። ሆኖም ጦርነቱ ጋብ እያለ ሲሄድና ታስረው የነበሩትም የሐሰት ክሱ ውድቅ ተደርጎ በነፃ ሲለቀቁ “ከእግዚአብሔር የወጣ መንፈስ ገባባቸው።” ወደ ላይ ከፍ ከፍ በመደረግ የአምላክን ሞገስ አገኙ። ከ1919 ጀምሮም ቅንዓት ወደ ተሞላበት የመንግሥቱ የሥራ እንቅስቃሴ ገቡ። — ኢሳይያስ 52:7, 8፤ ሮሜ 10:15

“ታላቂቱ ባቢሎን” ወደቀች!

10. የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ምን የደም ዕዳ በራሳቸው ላይ አምጥተዋል? እንዴትስ?

10 በእነዚያ የጦርነት ዓመታት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቀንደኛ አሳዳጆች ከመሆናቸውም ሌላ የአምላክ መንግሥት እንደ ቀረበች የሚያሳምነውን ማስረጃ አልተቀበሉም። እነርሱ የራሳቸው የሆነ ሃይማኖታዊ “መንግሥት” አላቸው፤ ማለትም የ“ታላቂቱ ባቢሎን” መንግሥት። (ራእይ 17:5, 6, 18) በጦርነት ጊዜ በሁለቱም ወገኖች የነበሩት ቄሶች ወጣቶች ወደ ጦርነቱ እሳት እንዲገቡ ሰብከዋል፣ ለአሰቃቂው እልቂትም በሙሉ ልብ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ለዚህ አድራጎታቸው የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በጥንት ኢየሩሳሌም እንደ ነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ከባድ የደም ዕዳ መሸከም ይኖርባቸዋል። ስለ ጥንቷ ኢየሩሳሌም ሃይማኖታዊ መሪዎች የይሖዋ ነቢይ “በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቷል” ብሏል። — ኤርምያስ 2:34፤ 19:3, 4፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 23:34, 35 ተመልከት።

11. ሕዝቅኤል 22:3, 4, 16 በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?

11 ሕዝበ ክርስትና ጣኦት አምልኮንና ባቢሎናዊ የሆኑ የሐሰት ትምህርቶች በማስፋፋት በፈጸመችው ወንጀል ላይ ይህ የደም ዕዳ ተጨመረ። ይህም በመሆኑ የሚከተሉት የነቢዩ ሕዝቅኤል ቃላት ለከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትናም ይሠራሉ:-

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! ባፈሰስሺው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም [ይሖዋ አዓት] እንደሆንሁ ታውቂአለሽ።” — ሕዝቅኤል 22:3, 4, 16

12. (ሀ) በ1919 ምን ከፍተኛ ነገሮች ተፈጸሙ? (ለ) ይህስ በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች የጠቀመው እንዴት ነው?

12 ሕዝበ ክርስትና በአንድ በኩል አመልከዋለሁ እያለች በሌላ በኩል ግን ስሙን እንኳ ለመጥራት የሚቀፋት አምላክ ይሖዋ ደም አፍሳሽ ሃይማኖቷን ከልብ አውጥቶታል። ሕዝበ ክርስትና በ1919 እዘአ በመላዋ ምድር ላይ ከሚገኘው ባቢሎናዊ ሃይማኖት ሁሉ ጋር ከፍተኛ ውድቀት ደርሶባታል። ከዚያ በኋላ በልዑሉ አምላክ ፊት የተቀባይነት አቋም አጥታለች። ከዚያ በኋላ እውነተኛዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች ከእጅዋ ወጥተዋል። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን የትኛውም ሌላ ክፍል ቢሆን በቁጥጥሩ ሥር ሊያደርጋቸው አልቻለም። ምክንያቱም ሉዓላዊው “ጌታ ይሖዋ” በምድር ላይ ላሉት ለታማኞቹ “ቅዱሳን” የሚከተለውን ጥሪ አቅርቧል:-

“እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ከባቢሎን ውጡ . . . በእልልታ ድምፅ ተናገሩ ይህንም ንገሩ።” (ኢሳይያስ 48:16, 17, 20)

ይህ “የእልልታ ድምፅ” ምንድን ነው? የተሰማውስ ከየት ነው?

ምድር አቀፍ ምሥክርነት ተጀመረ

13. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በጣም ጐልቶ የሚታየው የትኛው “የእልልታው” ገጽታ ነው? (ለ) ምን ከፍተኛ ጥሪስ ተሰማ?

13 “የሰው ልጅ” ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” በተናገረው ትንቢት ውስጥ የዚህን “የእልልታ ድምፅ” አንዱን ጕልህ ገጽታ እንዲህ በማለት ገልጾታል:-

“ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:3, 14, 37)

ሆኖም “ቅዱሳኑ” ይህ ሥራ ለማከናወን መደራጀት ነበረባቸው። በተጨማሪም በሰው ጉልበት ብቻ ሊያከናውኑት አይችሉም ነበር። ደስ የሚያሰኘው፣ በ1919 እንደገናም በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተዘጋጀው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የይሖዋ መንፈስ በአስደናቂ መንገድ በእነርሱ ላይ ፈሰሰ። ይህም መንፈስ ‘ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ’ የሚለውን ጥሪ ለመፈጸም አደራጃቸው፤ ኃይልም ሰጣቸው። ሰማያዊውን ተስፋ አጥብቀው የያዙትን እነዚህን “የተመረጡ” ሰዎች ከፊታቸው ታላቅ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር። — ማቴዎስ 24:31

14. የኢዩኤል ትንቢት በዚህ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ የተፈጸመው እንዴት ነው?

14 የኢዩኤል ትንቢት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ (በአይሁድ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ) እንደ ተፈጸመ ሁሉ አሁንም በሰይጣን ዓለም የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ ዋነኛ ተፈጻሚነቱን ማግኘት ጀመረ። የይሖዋ ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች’ የሆኑት የዘመኑ ቅቡዓን አዲስ እውቀት አግኝተውና በአምላክ መንፈስ ተነሣስተው በእርግጥ ‘ትንቢት ተናግረዋል።’ “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን” ስለ መቅረቡና ለመዳን በአስቸኳይ ‘የይሖዋን ስም መጥራት’ አስፈላጊ ስለመሆኑ የሰውን ዘር ዓለም የማስጠንቀቁን ሥራ በሰፊው ተያያዙት። — ሥራ 2:16–21፤ ኢዩኤል 2:28–32

ታማኙ “ባሪያ”

15. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? (ለ) በዘመናችንስ ማንነቱ ተለይቶ የታወቀው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ስለ ‘ምልክቱ’ በተናገረው ታላቅ ትንቢት ላይ እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:-

“እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?”

የታማኙ “ባሪያ” ክፍል ታላቁ ክህደት እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መካከል ሲያገለግል ቆይቶ ነበር። ጌታ ኢየሱስ በመንግሥቱ በመጣበት ጊዜስ እንደዚህ ያለው ድርጅታዊ ‘ባሪያ’ መንፈሳዊ ምግብ ሲያዘጋጅ አግኝቶት ይሆን? አዎን። በዚያን ጊዜ “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች” ተብለው ይጠሩ የነበሩት ምድር አቀፍ የሆነ የዝግጅት ሥራ አከናውነው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ አለ:-

“ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ [ደስተኛ] ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” — ማቴዎስ 24:45–47

16. (ሀ) “ባሪያው” የጌታውን ‘ንብረት’ በደንብ የያዘው እንዴት ነው? (ለ) “ባሪያው” በደስታ የተቀበለው የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ነው?

16 ይህን ከጌታው ያገኘውን ሹመት በማድነቅ የቅቡዓኑ “ባሪያ” ቡድን በምድር ላይ የመንግሥቱን ጉዳዮች በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ ነው፤ ‘ምሥራቹ’ እንዲስፋፋ አድርጓል። በ1920ዎቹ ዓመታት በሰይጣንና በድርጅቱ ላይ በተለይም ባቢሎናዊ በሆነ ሃይማኖት ላይ ኃይለኛ የፍርድ መልእክት ታወጀ። በ1931 “ባሪያው” ከሐሰት ሃይማኖት በግልጽ የሚለየውን ስም ማለትም “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚለውን ስም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ካመለከተው ኃላፊነትና መብት ጋር በደስታ ተቀበለው:-

“እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል [ይሖዋ አዓት] . . . እኔ፣ እኔ፣ [ይሖዋ አዓት] ነኝ፣ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። . . . ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣ ይላል [ይሖዋ አዓት] እኔም አምላክ ነኝ።” — ኢሳይያስ 43:10–12

17. አሁን መልስ ማግኘት የሚያስፈልገው ምን ጥያቄ ነው?

17 የ‘ባሪያው’ ክፍል የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች በአሥር ሺዎች ብቻ የሚቆጠሩ ሆነው ሳሉ ‘ምሥክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ምሥራች በምድር ሁሉ ላይ ሰብከው’ እንዴት ማዳረስ ይችላሉ? ይሖዋ መልሱን የሚሰጥበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 148, 149 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት የሆነችው መንግሥት

የመንግሥቱ “ዘር” ይመጣል የሚለው በኤደን የተሰጠው ተስፋ

ንጉሥ የሚሆን “ዘር” በአብርሃምና በዳዊት መሥመር እንደሚመጣ በቅድሚያ ተነገረ

የመንግሥቱ ስብከት፤ ንጉሡ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆነ

በ1914 መንግሥቲቱ ተቋቋመች፤ “መጨረሻዎቹ ቀኖች” ጀመሩ

መንግሥቲቱ የሰውን አገዛዝ ለመደምሰስ ‘ትመጣለች’

የ1,000 ዓመቷ መንግሥት ገነትን መልሳ ታቋቁማለች