በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለምዕራፍ 14 የተሰጠ ተጨማሪ ክፍል

ለምዕራፍ 14 የተሰጠ ተጨማሪ ክፍል

ለምዕራፍ 14 የተሰጠ ተጨማሪ ክፍል

የታሪክ ምሁራን ባቢሎን በቂሮስ ጦር እጅ የወደቀችው በጥቅምት ወር 539 ከዘአበ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚያን ጊዜ ንጉሥ የነበረው ናቦኒደስ ነው፤ ሆኖም ልጁ ብልጣሶርም የሥልጣኑ ተጋሪ በመሆን ባቢሎንን ይገዛ ነበር። አንዳንድ ምሁራን ናቦኒደስ ከገዛበት የመጨረሻ ዓመት ጀምረው ወደ ኋላ በመሄድ እስከ ናቡከደነፆር አባት እስከ ናቦፖላሳር የሚደርስ የባቢሎንን ነገሥታትና የገዙበትን ዘመን የሚያሳይ ዝርዝር አዘጋጅተዋል።

በዚህ የባቢሎን የዘመናት ስሌት መሠረት ናቡከደነፆር አልጋ ወራሽ ሳለ በ605 ከዘአበ በካርኬሚሽ በተደረገው ጦርነት ግብፃውያንን ድል መታ። (ኤርምያስ 46:1, 2) ናቦፖላሳር ከሞተ በኋላ ናቡከደነፆር ሥርዓተ ንግሥናውን ለማከናወን ወደ ባቢሎን ተመለሰ። የመጀመሪያው የንግሥና ዓመቱ የጀመረው በሚቀጥለው የጸደይ ወራት (በ604 ከዘአበ) ነው።

በናቡከደነፆር የሚመሩት ባቢሎናውያን በ18ኛው የግዛት ዘመኑ (የነገሠበት ዓመት ሲጨመር በ19ኛው) ዓመት ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኤርምያስ 52:5, 12, 13, 29) ስለዚህ አንድ ሰው ከላይ ያለውን ዘመናዊ የባቢሎን የዘመናት ስሌት ከተቀበለ ኢየሩሳሌም የጠፋችበት ዓመት በ587/6 ከዘአበ ይሆናል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይህ የዓለም የዘመናት ስሌት የተመሠረተው በምን ላይ ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌትስ ጋር እንዴት ይነጻጸራል?

ለዚህ ዓለማዊ የዘመናት ስሌት ዋነኛ ድጋፍ ሆነው የቀረቡት የሚከተሉት ናቸው:-

የቶሎሚ መዝገብ:- ክላውዲየስ ቶሎሚ በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ግሪካዊ የከዋክብት ተመራማሪ ነበር። የእርሱ መዝገብ ወይም የነገሥታት ዝርዝር እርሱ ካዘጋጀው የከዋክብት ጥናት ጽሑፍ ጋር የተያያዘ ነበር። አብዛኞቹ ዘመናውያን የታሪክ ምሑራን ቶሎሚ (የላባሺ ማርዱክን ግዛት ቢያስቀረውም እንኳ) እርሱ ስለ ባቢሎን ነገሥታትና ስለ ገዙበት ዘመን ርዝመት ያቀረበውን መረጃ ተቀብለውታል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ቶሎሚ ታሪካዊ መረጃውን ያገኘው ቂሮስ ባቢሎንን ከያዘ ከ250 ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ከጀመረው የሴሌውከስ ነገሥታት ዘመን ጀምሮ በተገኙ ማስረጃዎች ነው። ስለዚህ የቶሎሚ ስሌት በሴሌውከስ ነገሥታት ዘመን በባቢሎን ካህን ከነበረው ከቤሮሰስ ዘገባ ጋር የሚስማማ መሆኑ ምንም የሚያስገርም አይሆንም።

የናቦኒደስ የሐራን አምድ (NABON H 1, B):- ይህ በጊዜው የነበረ ጽሑፍ የተቀረጸበት አምድ ከተሰወረበት ቦታ የተገኘው በ1956 ነበር። በዚህ አምድ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ የባቢሎንን ነገሥታት የናቡከደነፆርን፣ የኤቪል ሜሮዳክን፣ የኔሪግሊሳርን የግዛት ዘመን ይጠቅሳል። ለእነዚህ ለሦስቱ ነገሥት የተሰጡት አኀዞች ከቶሎሚ መዝገብ ጋር ይስማማሉ።

ሻት 4956:- ይህ ወደ 568 ከዘአ የተደረገን ከዋክብታዊ ጥናት የሚገልጽ የኩኒፎርም ሰሌዳ ነው። ስሌቱ የተደረገው በናቡከደነፆር 37ኛ ዓመት እንደሆነ የሰሌዳው ጽሑፍ ይገልጻል። ይህም የናቡከደነፆርን 18ኛ የግዛት ዓመት 587/6 ከዘአበ ከሚያደርገው የዘመናት ስሌት ጋር ይስማማል። ይሁን እንጂ ይህ ሰሌዳ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተዘጋጀ ቅጂ መሆኑ ታውቋል፤ ስለዚህ በእርሱ ላይ ያለው ታሪካዊ ዘገባ በሴሌውከስ ነገሥታት ዘመን ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው ዘገባ ሊሆን ይችላል።

የውል ሰሌዳዎች:- በየዘመናቱ የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ የባቢሎን የኩኒፎርም ሰሌዳዎች በግለሰቦች መካከል ውል የተደረገበትን ጊዜ ከባቢሎን ንጉሥ የግዛት ዘመን ጋር አያይዘው ይጠቅሳሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰሌዳዎቸ ተቀባይነት ባገኘው በጊዜው የዘመናት ስሌት መሠረት ታዋቂ የሆኑት የባቢሎን ነገሥታት በገዙባቸው በሁሉም ዓመታት ተገኝተዋል።

በዓለማዊው አንጻር ሲታዩ እንደነዚህ ያሉት ማስረጃዎች የባቢሎንን የዘመናት ስሌት ከናቡከደነፆር 18ኛ ዓመት (እና ከኢየሩሳሌም ጥፋት) ጋር ይኸውም ከ587/6 ከዘአበ ጋር የሚያያይዙት ይመስላል። ይሁን እንጂ የትኛውም የታሪክ ምሁር ቢሆን አሁን ያለው የባቢሎናውያን ታሪክ የተዛባ ወይም ፈጽሞ ስሕተት ሊሆን እንደሚችል አይክድም። ለምሳሌ ያህል የጥንት ካህናትና ነገሥታት አንዳንድ ጊዜ ለግል ዓላማችው ሲሉ የመዝገቦችን ይዘት እንደሚቀይሩ የታወቀ ነው። ወይም አሁን በእጅ ያለው ማስረጃ ትክክለኛ ቢሆንም እንኳ ዘመናዊ ምሁራን አሳስተው ሊተረጕሙት ይችላሉ፤ ወይም ያልተሟላ ይሆንና ገና ያልተገኘው ክፍል ሲገኝ ዘመኑን በከፍተኛ ደረጃ ሊለውጠው ይችላል።

እንደነዚህ ያሉትን ሁኔታዎች በመረዳት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኤፍ ካምቤል የባቢሎንን የዘመናት ስሌት የሚጨምር አንድ ቻርት ከሚከተለው ማስጠንቀቂያ ጋር አቅርበዋል:- “እነዚህ ዝርዝር መግለጫዎች ጊዜያዊ ብቻ ናቸው ብሎ መናገሩ የተገባ ነው። አንድ ሰው በጥንቱ ቅርብ ምሥራቅ የዘመናት ስሌትን በተመለከተ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች ይበልጥ እያወቀ በሄደ መጠን ምንም ማስረጃ ቢቀርብለት የመጨረሻው አድርጎ አይቀበለውም። በዚህም ምክንያት አካባቢ [ገደማ] የሚለውን ቃል አዘውትሮ መጠቀሙ ይበልጥ ተገቢ ይሆናል።” — መጽሐፍ ቅዱስና የጥንቱ ቅርብ ምሥራቅ (የ1965 ዕትም) ገጽ 281

በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረው ቃል ብዙ ትችት ቢደርስበትም በተደጋጋሚ ጊዜያት ትክክለኛና አስተማማኝ ሆኖ አግኝተውታል። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል በመሆኑ የዓለም ታሪክንና አስተሳሰብን ለመገምገም የሚረዳ መለኪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብለው ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ብልጣሶርን የባቢሎን ገዥ እንደነበረ ይናገራል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ ሕልውና፣ ማንነት ወይም ሥልጣን የሚገልጽ ምንም ዓለማዊ መረጃ ባለመገኘቱ ምሁራን ለብዙ መቶ ዘመናት ግራ ተጋብተው ነበር። ሆኖም በመጨረሻ በቁፋሮ ታሪክን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ዓለማዊ መረጃዎችን አገኙ። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ፣ ጸሐፊዎቹ የዘመናት ስሌትን በተመለከተ እንኳ ሳይቀር ያደረጉት ከፍተኛ ጥንቃቄ ክርስቲያኖች በየጊዜው ከሚቀያየረው የታሪክ ሰዎች ሐሳብ በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ማስረጃ አድርገው እንዲቀበሉት ያስገድዳቸዋል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሩሳሌም የጠፋችበትን ዘመን ለማስላት የሚረዳን እንዴት ነው? ይህስ ከዓለማዊ የዘመናት ስሌት ጋር እንዴት ይነጻጸራል?

ነቢዩ ኤርምያስ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉና ከተማዋንና ምድሪቱን ባድማ እንደሚያደርጉ ተንብዮ ነበር። (ኤርምያስ 25:8, 9) በተጨማሪም “ይህች ምድር ባድማ፣ የእፍረት ዕቃ ትሆናለች፤ ይህም ሕዝብ ለሰባ ዓመታት ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛል” ብሏል። (ኤርምያስ 25:11 አዓት) ታላቁ ቂሮስ በመጀመሪያው የግዛት ዓመቱ አይሁዶችን ሲለቅና እነርሱም ወደ ምድራቸው ሲደርሱ ሰባዎቹ ዓመታት አለቁ። (2 ዜና. 36:17–23) ኤርምያስ 25:11 እና ሌሎች ጥቅሶች በቀጥታ ሲነበቡ 70ዎቹ ዓመታት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉበትና የይሁዳን ምድር ባድማ ባደረጉበት ጊዜ እንደጀመሩ ያሳያሉ ብለን እናምናለን። — ኤርምያስ 52:12–15, 24–27፤ 36:29–31

ሆኖም የዘመናትን ስሌት በተመለከተ በዓለማዊ መረጃ ላይ ብቻ ተመርኩዘው የሚያሰሉ ሰዎች ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587/6 ከዘአበ ከሆነ ባቢሎን ድል እስከ ተደረገችበትና ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እስካደረገበት ድረስ ያለው የጊዜ ርዝመት 70 ዓመት እንደማይሆን ያውቃሉ። ነገሮችን ለማስማማት በመሞከርም የኤርምያስ ትንቢት መፈጸም የጀመረው በ605 ከዘአበ ነው ይላሉ። ከዚያ ቆየት ያሉ አንዳንድ ጸሐፊዎች ከካርኬሚሽ ድል በኋላ ናቡከደነፆር የባቢሎንን ግዛት በሁሉም የሶሪያና የፍልስጥኤም ምድር እንዳስፋፋና ወደ ባቢሎን ሲመለስም (በነገሠበት ዓመት በ605 ከዘአበ) የአይሁድ ምርኮኞችን ማርኮ እንደ ወሰደ ቤሮሰስ መጻፉን ይገልጻሉ። በዚህም መንገድ ለባቢሎን ባሪያ ሆነው የሚቆዩባቸው 70 ዓመታት በ605 ከዘአበ እንደሚጀምሩ አድርገው ያሰላሉ። ይህም የ70 ዓመቱ ጊዜ የሚያበቃበትን ዓመት 535 ከዘአበ ያደርገዋል።

ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነቱ ማብራሪያ ብዙ ታላላቅ ጥያቄዎችን ያስነሣል:-

ቤሮሰስ ናቡከደነፆር አይሁዳውያንን ማርኮ የወሰደው በነገሠበት ዓመት እንደሆነ ቢናገርም ይህንን የሚደግፉ የኩኒፎርም መረጃዎች የሉም። እንዲያውም ኤርምያስ 52:28–30 ናቡከደነፆር አይሁዳውያንን ማርኮ የወሰደው በነገሠበት ዓመት ሳይሆን በሰባተኛ ዓመቱ፣ በ18ኛ ዓመቱ፣ እና በ23ኛ ዓመቱ እንደሆነ በጥንቃቄ ይገልጻል። በተጨማሪም የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ የካርኬሚሽ ድል በተገኘበት ዓመት ናቡከደነፆር “ከይሁዳ በስተቀር” ሁሉንም የሶሪያንና የፍልስጥኤምን ምድር ድል አድርጎ እንደያዘ ገልጿል። ይህም ከቤሮሰስ ዘገባ ጋር ይቃረናል። የአይሁዶች የ70 ዓመት ባርነት የጀመረው ናቡከደነፆር በነገሠበት ዓመት ነው ከሚለውም አባባል ጋር ይጋጫል። — አንቲኩቲስ ኦፍ ዘ ጂውስ X, vi, 1

ከዚህም በተጨማሪ ጆሴፈስ በሌላ ስፍራ ላይ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ስለ መጠፋቷ ያትትና “የይሁዳ ምድር በሙሉ፣ ኢየሩሳሌምና ቤተመቅደሷ ለሰባ ዓመት ባድማ ሆነው ቆዩ” ብሏል። (አንቲኩቲስ ኦፍ ዘ ጂውስ X, ix, 7) ጆሴፈስ “ከተማችን ቂሮስ እስኪነሣ ድረስ በነበሩት ሰባ ዓመታት ወቅት ኦና ሆና ነበር” በማለት አበክሮ ገልጿል። (አጌነስት አፕዮን 1, 19) ይህም 70ዎቹ ዓመታት ምድሪቱ ባድማ ሆና የምትኖርባቸው ሙሉ 70 ዓመታት መሆናቸውን ከሚገልጹት ከ 2 ዜና መዋዕል 36:21 እና ከዳንኤል 9:2 ጋር ይስማማል። በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበረው የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ የተባለ ጸሐፊ 70ዎቹ ዓመታት የጀመሩት ሰዴቅያስ 11 ዓመት ገዝቶ ቤተ መቅደሱ ከፈረሰ በኋላ መሆኑን ገልጿል። — በተጨማሪም 2 ነገሥት 24:18 እስከ 25:21 ተመልከት።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ 70ዎቹ ዓመታት የጀመሩት በ605 ከዘአበ ነው፣ እንዲሁም ኢየሩሳሌምም የጠፋችው በ587/6 ከዘአበ የሚለውን አቋም የሚያፈርስ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ማስረጃ ይሰጣል። ቀደም ሲል እንደገለጽነው ከ605 ከዘአበ መቁጠር ከጀመርን 70ዎቹ ዓመታት ወደ 535 ከዘአበ ይደርሳሉ። ነገር ግን በመንፈስ አነሣሽነት ከጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ዕዝራ 70ዎቹ ዓመታት እስከ ‘ፋርሱ ንጉሥ እስከ ቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት’ ያለውን ጊዜ እንደሚሸፍኑና ቂሮስ አይሁዶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል አዋጅ በዚያው ዓመት እንዳወጣ ዘግቧል። (ዕዝራ 1:1–4፤ 2 ዜና መዋዕል 36:21–23) ቂሮስ ባቢሎንን ድል አድርጎ የያዘው በ539 ከዘአበ በጥቅምት ወር እንደሆነና የግዛት ዘመኑ የጀመረው በ538 ከዘአበ መሆኑን የታሪክ ምሁራን ይቀበላሉ። ቂሮስ ትእዛዙን ያወጣው በመጀመሪያው የንግሥናው ዓመት መገባደጃ ላይ ከሆነ አይሁዶች በሰባተኛው ወር (በቲሺሪ) ወደ አገራቸው በቀላሉ ሊደርሱ ይችላሉ። ዕዝራ 3:1​ም የሚናገረው ይህንኑ ነው። ይህም በ537 ከዘአበ የጥቅምት ወር ይሆናል።

ይሁን እንጂ የቂሮስን የመጀመሪያ የግዛት ዘመን ከ538 ወደ 535 ከዘአበ ለመለወጥ የሚቻልበት ምንም ዓይነት ምክንያታዊ መንገድ የለም። ነገሩን ለማድበስበስ የሞከሩ አንዳንድ ሰዎች ዕዝራም ሆነ ዳንኤል “የቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት” ሲሉ ከኦፊሲየላዊው የቂሮስ የግዛት ዘመን አቆጣጠር ልዩ የሆነ የአይሁዶች አመለካከት መጥቀሳቸው ነው ይላሉ። ይህም ቢሆን ድጋፍ የለውም ምክንያቱም አይሁዳዊ ያልሆነ አንድ ገዥና በፋርሳውያን ቤተመዛግብት ውስጥ የተገኘ አንድ ሰነድ ትእዛዙ የወጣው በቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት ላይ መሆኑን ያሳያሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም በጥንቃቄና ለይተው የተናገሩት ይህንን ነው። — ዕዝራ 5:6, 13፤ 6:1–3፤ ዳንኤል 1:21 እስከ 9:1–3

‘መልካሙ የይሖዋ ቃል’ በትንቢት ከተነገሩት 70 ዓመታት ጋር የተያያዘ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ብሏል፤

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።” (ኤርምያስ 29:10)

ዳንኤል 70ዎቹ ዓመታት ከሞላ ጐደል ሳይሆን ሙሉ 70 ዓመታት መሆናቸውን በማመን ያንን ቃል ተሞርኩዞ ማስላት ችሏል። (ዳንኤል 9:1, 2) ስሌቱም ትክክል ሆነ።

እኛም በተመሳሳይ በዓለማዊ ዘገባ ላይ ከተሞረከዘ ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ከሚጋጭ የዘመናት ስሌት ይልቅ በቀደምትነት በአምላክ ቃል ለመመራት ፈቃደኞች ነን። የተለያዩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አነጋገሮች በቀጥታ ከወሰድን 70ዎቹ ዓመታት የጀመሩት ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ የይሁዳ ምድር ፈጽማ በተደመሰሰች ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ይመስላል። (ኤርምያስ 25:8–11፤ 2 ዜና መዋዕል 36:20–23፤ ዳንኤል 9:2) በዚህ መሠረት አይሁድ ወደ አገራቸው ከተመለሱበት ከ537 ከዘአበ ተነሥተን ወደኋላ ብንቆጥር 607 ከዘአበ ላይ እንደርሳለን። በዚህ ዓመት ናቡከደናፆር በ18ኛ የግዛቱ ዘመን ላይ ኢየሩሳሌምን አጠፋ፤ ሰዴቅያስን ከዙፋኑ አወረደው፤ በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሡ የነበሩትን ነገሥታት መሥመር እንዲቋረጥ አደረገ። — ሕዝቅኤል 21:19–27