በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንግሥቲቱ ‘ለመምጣት’ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደባት ለምንድን ነው?

መንግሥቲቱ ‘ለመምጣት’ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደባት ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 5

መንግሥቲቱ ‘ለመምጣት’ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደባት ለምንድን ነው?

1. ሮሜ 8:22⁠ን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?

ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 8:22) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በታሪክ ማኅደር ላይ የሰፈረው ያለፈው የ6, 000 ዓመት ታሪክ እንደሚያሳየውስ አምላክ ጦርነቶችን፣ ወንጀልን፣ በሽታንና ጉስቁልናን ለምን ፈቀደ? በመለኮታዊው ሕግ እየተመራ ለመኖር የተፈጠረው የሰው ዘር በአሁኑ ጊዜ የዓመፅ መቅሰፍት እንዲደርስበት ያደረገ ምን ስሕተት ተፈጸመ? ሰማያዊው አባታችንስ ይህንን ሁኔታ ያላስተካከለው ለምንድን ነው? ለዚህ ሁሉ መፍትሔው መንግሥቲቱ ከሆነች ‘ለመምጣት’ ይህንን ያህል ረጅም ጊዜ የወሰደባት ለምንድን ነው? እነዚህን አስከፊ ሁኔታዎች አምላክ ይለውጣቸዋል ብለን በእርግጥ ተስፋ ማድረግ እንችላለንን?

2. ምድር በአምላክ ሉዓላዊነት ብቻ ብትተዳደር ኖሮ እንዴት ያለ መልክ ሊኖራት ይችል ነበር?

2 የመጨረሻው ከፍተኛ ገዥ ወይም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ብቻ ምድርን ቢያስተዳድር ኖሮ በኤደን ገነት ውስጥ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በምድር ላይ ፍጹም ሁኔታዎች ይሰፍኑ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ልጆችን ሲወልዱና የሰው ዘር በብዙ ሺህ ሚልዮን በሚቆጠሩ ወገኖች እየተባዛ ሲሄድ ጠቅላላዋ ምድር ሰላማዊ በሆኑ፣ ደስታና ሳቅ እንዲሁም የጐረቤት ፍቅር በሚያሳዩ የሰው ዘሮች የተሞላች ውብ ገነት ትሆን ነበር። — ከመክብብ 2:24 ጋር አወዳድር።

3. (ሀ) ሰው የተፈጠረው በማን ምሳሌ ነው? (ለ) የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት ምን ሥራ ተሰጣቸው? (ሐ) አሁን ምን ጥያቄ መጠየቅ ይኖርብናል?

3 አፍቃሪው ፈጣሪ ወንድን በራሱ ሥነ ምግባራዊ ምሳሌ በፈጠረበት ጊዜና ሴትንም ከወንድ እንድትገኝ ባደረገ ጊዜ ለዚህች ምድር የነበረው ዓላማ ይኸው ነበር፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ እንዲህ ሲል ይነግረናል:-

“ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፣ አምላክም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው:- ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን አሳዎችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙ። . . . አምላክም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:26–31)

ታዲያ ዛሬ በምድር ላይ የአምላክ ፍጥረት “መልካም” መስሎ የማይታየው ለምንድን ነው?

የአምላክ ሉዓላዊነት ተገዳዳሪ መጣበት

4. (ሀ) የትኛው የአምላክ ሕግ የላቀ ነው? ለምንስ? (ለ) የተለዩ ሕጎችን ለማምጣት የፈለገው ማን ነው? ይህንንስ ተግባራዊ ያደረገው እንዴት ነው?

4 የፍጥረት መሠረት የአምላክ ሕግጋት ናቸው። ላቅ ብለው ከሚታዩት ሕግጋት አንዱ የፍቅር ሕግ ነው። አምላክ ራሱ “ፍቅር” ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ሆኖም ለሰው ልጆች የተለዩ ሕጎችን ለማውጣት የፈለገ አንድ ግለሰብ ብቅ አለ። ያ “ግለሰብ” መልአክ የሆነ የማይታይ ‘የአምላክ ልጅ’ ነበር። ይሖዋ ምድርንና በላይዋ ያለውን ነገር ሁሉ በፈጠረ ጊዜ “እልል” ካሉት የአምላክ ልጆች መካከል እንደነበረ ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 38:7) ይህ መልአክ ራሱን ሰይጣን ወይም የአምላክ ጠላት አደረገ። ነፃ ሆኖ በራሱ ሐሳብ ለመመራትና ለመመለክ ፈለገ። ከዚያም የዓመፀኝነትን መንፈስ ዘራ። (ኤፌሶን 2:1, 2፤ ከሉቃስ 4:5–7 ጋር አወዳድር።) የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን ለራሱ የስስት ዓላማ ማስፈጸሚያ የሚሆኑበትን የተንኮል ዘዴ ቀየሰ። ይህንን ያደረገው እንዴት ነበር?

5, 6. (ሀ) አምላክ ለአዳም ምን ቀላል ትእዛዝ ሰጠው? (ለ) ሰይጣን ቀርቦ ምን ሙከራ አደረገ? “ዲያብሎስ” የሚል ተገቢ መጠሪያ የተሰጠውስ ለምንድን ነው?

5 ገነት በሆነችው የኤደን የአትክልት ሥፍራ ውስጥ አዳምና ሔዋን የይሖዋ የደግነት አመራር ተጠቃሚዎች ሆነው ነበር። አምላክ እነርሱን በመንፈሳዊና በሥጋዊ ለማኖር አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ለራሳቸው ዘላቂ ደኅንነት ሲልም እርሱን ሉዓላዊ ገዥያቸው አድርገው እንዲታዘዙት ፈለገ። ለዚህም ሲል “መልካምንና ክፉን ከምታስታውቀው ዛፍ” አትብላ በማለት ለአዳም ቀላል ትእዛዝ ሰጠው። ሔዋን ከተፈጠረች በኋላ ይህ ትእዛዝ በእርስዋም ላይ የሚሠራ ሆነ። በአትክልት ሥፍራው ውስጥ ያሉት ሌሎች ዛፎች አስደሳችና ገንቢ የሆኑ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን ለመስጠት የሚችሉ ስለነበሩ አምላክ አንድም ነገር አላጎደለባቸውም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክን ባለመታዘዝ ይህንን አንድ ፍሬ ከበሉ ሞት አይቀርላቸውም ነበር። ዓመፀኛው ሰይጣን በረቀቀ ዘዴ በእባብ ተጠቅሞ በመጀመሪያ ሔዋንን በምንም ዓይነት “ሞትን አትሞቱም፣ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” አላት። — ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1–5

6 ይህ አባባል አምላክን ሐሰተኛ ሆኖ እንዲታይ አደረገው። ይሁን እንጂ በእርግጥ ሐሰተኛ የነበረው ሰይጣን ነው። ይህ “የሐሰት አባት” ዲያብሎስ የሚል ስያሜ አገኘ፤ ይህም ተገቢ ሲሆን ትርጉሙ “ስም አጥፊ” ማለት ነው። (ዮሐንስ 8:44) በይሖዋ ሉዓላዊነት ማለትም በፍጥረቱ ላይ ባለው ንግሥና ላይ ቀጥተኛ የሆነ ግድድር ተነሣ ማለት ነው። ግድድሩ ሰዎች ማወቅ የሚገባቸውን ነገር አምላክ እንዳያውቁ እንዳደረገ፣ የአምላክ አገዛዝ እምነት ሊጣልበት እንደማይችል፣ ሰዎች ‘መልካምና ክፉ’ ስለሚባለው ነገር የራሳቸውን የአቋም ደረጃዎች በማውጣት የመረጡትን ነፃ መንገድ ተከትለው ቢሄዱ የተሻለ እንደሆነ የሚያመለክት ነበር።

7. ሰብዓዊ ባልና ሚስት በፈተና የወደቁት በምን ረገድ ነው?

7 ሴቲቱ ይህን ስም የሚያጠፋ ንግግር ከሰማች በኋላ ምን አለች? ልብዋን ሳትጠብቅ ቀረች። በልቧ ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲበቅል ፈቀደች። ከዚያም ይህ ምኞት አደገና የአምላክን ትእዛዝ በማፍረስ ሆን ብላ ኃጢአት ለመፈጸም ተታለለች። በዚህም ልታማክረው ይገባት የነበረውን የባልዋን የራስነት ሥልጣን ተጋፍታለች። ወንዱስ ይህን ካየ በኋላ ምን አለ? “አዳም አልተታለለም።” ነገር ግን ሆን ብሎ የዓመፅዋ ተባባሪ በመሆን ዕጣውን ከሔዋን ጋር ለማድረግ መረጠ። ያች ቀን ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንና ለጠቅላላው የሰው ዘር ምንኛ አሳዛኝ ቀን ነበረች! — ዘፍጥረት 3:6, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14፤ ከያዕቆብ 1:14, 15 ጋር አወዳድር።

8. (ሀ) አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ምን ትክክለኛ ፍርድ ሰጠ? (ለ) እነርሱስ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ወይም ወደ መቃጠያ ሲኦል የምትሄድ ነፍስ ነበረቻቸውን? (ሐ) በእኛ ላይ የትኛው ንጉሥ ነገሠ? ለምንስ?

8 አዳምና ሔዋን ለአምላክ ሉዓላዊነት ከፍተኛ ንቀት አሳይተዋል። ስለዚህ አሁን አምላክ ከሕጉ ጋር በመስማማት ለአዳም እንዲህ በማለት የሞት ፍርዱን አስታወቀው:-

“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ።” (ዘፍጥረት 3:19)

አምላክ እዚህ ላይ ከአዳም አካል የምትለይ አንዲት ውስጣዊ “ነፍስ” ወይም “መንፈስ” በሰማይ ወይም በሲኦል ሕያው ሆና ስትቀጥል የአዳም አካል ብቻ ይሞታል ማለቱ አልነበረም፤ ምክንያቱም አዳም ራሱ “ነፍስ” ነበር። በዘፍጥረት 2:7 ላይ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ እንደሚገልጸው:- “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፣ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፣ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (አዓት ) አዳምና ሔዋን ማለትም ሁለቱም ነፍሳት ጊዜው ሲደርስ ሞቱ። የሰው ልጆች በጠቅላላ በኃጢአት የተበከለው የአዳም ዘሮች ስለሆኑ ሁላችንም ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። “ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4, 20) አዎን፣ ሰብዓዊ ነፍሳት እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም እንሞታለን። ሞት በእኛ ላይ ነገሠ። — ሮሜ 5:12, 14፤ 6:12፤ መክብብ 3:19, 20፤ 9:5, 10፤ መዝሙር 6:5፤ 115:17

ስለ ፍጹም አቋም ጠባቂነት የተነሣ ጥያቄ

9. በኤደን ውስጥ ምን ሌላ አከራካሪ ጥያቄ ተነሣ?

9 ይሁን እንጂ የኤደኑ ዓመፅ ጥያቄ ላይ የጣለው የአምላክን ሉዓላዊነት ብቻ አልነበረም። ሌላም አከራካሪ ጉዳይ ተነሥቶ ነበር። አምላክ በምድር ላይ ያስቀመጣቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ፈተና ሲደርስባቸው ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ ታዲያ የአምላክ አፈጣጠር ጉድለት ኖሮበት ይሆን? ሥራዎቹ ሁሉ በእርግጥ “ፍጹም” ናቸው ሊባል ይቻላልን?

10, 11. (ሀ) የአምላክ ፍጥረት ጉድለት ነበረበትን? እንዲህ ብለህ የምትመልሰውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሰዎች ‘በአምላክ ምሳሌ’ የተፈጠሩ መሆናቸውን እንዴት ማሳየት ይችላሉ? ዘዳግም 32:4, 5 በዚያን ጊዜ ስለሆነው ነገር ምን የሚሰጠን እውቀት አለ?

10 አምላክ አዳምንና ሔዋንን ወዲያውኑ አጥፍቶ ሌሎች ባልና ሚስት ለመፍጠር ይችል ነበር። ነገር ግን እንደዚያ ቢያደርግ የመጀመሪያው አፈጣጠሩ ጉድለት አለበት ብሎ ማመን አይሆንበትምን? ፍጥረቱ ምንም ጉድለት አልነበረበትም። ችግሩ የመጣው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ሥነ ምግባራዊ የመምረጥ ነፃነታቸውን በተሳሳተ መንገድ ስለተጠቀሙበት ብቻ ነው። በተፈለገው መንገድ የሚሠሩ ተንቀሳቃሽ አሻንጉሊቶች ሆነው ተሠርተው ቢሆን ኖሮ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ስለ መሆኑ በውስጣቸው ምንም ስሜት አይኖራቸውም ነበር። ‘በአምላክ አምሳል’ የተሠሩ አይሆኑም ነበር። ይሖዋ ፍቅር ስለሆነ ምን ጊዜም ነገሮችን የሚሠራው ፍጹም አድርጎ፣ በትክክለኛ መንገድ ነው። በተመሳሳይም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ ትክክለኛ የሆነውን ለማድረግ በፍቅር እንዲነሣሱ ይፈልጋል። — ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 1 ዮሐንስ 5:3

11 ስለ ይሖዋ እንዲህ ተጽፏል:- “እርሱ አምባ ነው፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱ ሁሉ የቀና [ፍትሐዊ አዓት] ነው። የታመነ አምላክ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና [ጻድቅና አዓት] ቅን ነው።” የእርሱ ፍጥረት የሆነው የሰው ዘርም የታመነ፣ ጻድቅና ቅን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አዳምና ሔዋን ልጅ እንዲወልዱ ፈቀደላቸው። ምንም እንኳ እነዚህ ልጆች ከወላጆቻቸው የኃጢአት ባሕርያትን ቢወርሱም ከመካከላቸው ገና በሥጋዊ አለፍጽምና እያሉ በሚደርሱባቸው መራራ ፈተናዎችና ስደቶች ፊት ለፈጣሪያቸው የማይታጠፍ ፍቅርና ንጹሕ አቋም የሚያሳዩ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ። ሌሎች የሰው ልጆች ግን “ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ” በመሆን የአምላክ ልጆች አለመሆናቸውን ያሳያሉ። ይህ የራሳቸው ምርጫ ነው፤ በጉድለቱ ተጠያቂው እነርሱ እንጂ አምላክ አይሆንም። — ዘዳግም 32:4, 5

12, 13. (ሀ) ኢዮብን በተመለከተ ሰይጣን አምላክን የሰደበው እንዴት ነው? (ለ) ኢዮብ ምን ምላሽ ሰጠ? ምንስ ውጤት አገኘበት?

12 ሰው በአምላክ ፊት በንጹሕ አቋሙ ስለ መጽናቱ ሰይጣን ዲያብሎስ አከራካሪ ጥያቄ ያስነሣ መሆኑ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል። አዳም አምላክን ከከዳ ከ2,500 ዓመታት በኋላ የኖረው ኢዮብ የተባለው ሰው “ነውር የሌለበት፣ ቅን፣ አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” ነበር። ኢዮብ በትክክለኛ መንገድ የሚሄደው ልባዊ ፍላጎቱ ስለሆነ አይደለም፤ አምላክን ያገለገለው ጥቅም ስለሚያገኝበት ብቻ ነው በማለት ሰይጣን አምላክን ተከራከረ። ስለዚህም ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው አምላክ ፈቀደለት። ኢዮብ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደረሰበት፣ አሥር ልጆቹ በአደጋ ተገደሉ፣ በኋላም እርሱ ራሱ በአስከፊ በሽታ ተያዘ። በመጨረሻም የገዛ ሚስቱ “እስከ አሁን ፍጹም አቋምህን ጠብቀሃልን? አምላክን ስደብና ሙት” በማለት ዘበተችበት። ከዚያም በመቀጠል ኢዮብ የሦስት ሐሰተኛ አጽናኞችን የምጸት ነቀፋ መቋቋም ነበረበት። — ኢዮብ 1:6 እስከ 2:13 አዓት

13 በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች መሀል ኢዮብ ቀጥሎ ባለው አቋሙ ጸና:-

“እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን (ፍጹም አቋሜን አዓት) ከእኔ አላርቅም!”

እውነተኛ የአምላክ ደጋፊ መሆኑን አረጋገጠ፤ በዚህም ለሰይጣን ክሶች ጠንካራ ምላሽ ሰጠ። ስለዚህ ይሖዋ በፊት ከነበረው ሁሉ እጥፍ በመስጠት ኢዮብን ለታማኝነቱ ካሰው። እንዲሁም ሰባት ወንዶችና በምድሩ ካሉት ሁሉ ይልቅ የተዋቡ ሦስት ሴቶች ልጆች እንደገና በማግኘቱ ተባርኮ ነበር። — ኢዮብ 27:5፤ 42:10–15

14. ሌሎችም ለሰይጣን ክስ ተመሳሳይ መልስ የሰጡት እንዴት ነው? ለዚህስ ከሁሉ የበለጠው ምሳሌ ማን ነው?

14 ይሁን እንጂ ኢዮብ ሰይጣን ላቀረበው ክርክር ይኸውም የይሖዋ ወዳጆች እርሱን የሚታዘዙትና የሚያገለግሉት ለግል ጥቅም ሲሉ ብቻ ነው ለሚለው ሐሰተኛ አባባል መልስ በመስጠት የይሖዋን ልብ ደስ ካሰኙት በመቶ ሺህ ከሚቆጠሩት ሰዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። ለዚህ ነገር ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የራሱን ጥቅም በመሠዋት አምላክ የሰጠውን ሥራ አከናውኖ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል “ውርደትን ከምንም ሳይቆጥር የመከራውን እንጨት የታገሰው” ኢየሱስ ነው። — ዕብራውያን 12:2 አዓት

የተሳዳቢው ግድድር መልስ አገኘ

15. በግድድሩ የይሖዋ አሸናፊነት ተረጋግጧል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

15 ለክርክሩ የተወሰነው ጊዜ አሁን እያለቀ ነው። ባለፉት 6,000 ዓመታት ውስጥ ይሖዋ ለግድድሩ መልስ በመስጠት እውነተኛነቱን ሲያስመሠክር ቆይቷል። ሰይጣን የፈለገውን ዓይነት ስደት ወይም መከራ ቢያመጣባቸውም እንኳ ከፍጹም አቋማቸው ፍንክች የማይሉ ወንዶችና ሴቶች በምድር ላይ ሊኖሩት እንደሚችልና እንዳሉትም ይሖዋ አሳይቷል። ዲያብሎስ በሚቻለው ሁሉ በእነርሱ ላይ ማንኛውንም ዓይነት መሰሪ ዘዴ ቢጠቀምም ሊሳካለት አልቻለም። የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የአባታቸውን ልብ ደስ አሰኝተዋል፤ ምክንያቱም አምላክን ‘ለሚሰድበው’ ለታላቁ ጠላት ለሰይጣን መልስ እንዲሰጥ አስችለውታል። — ምሳሌ 27:11

16. (ሀ) ከአምላክ ታማኞች መሀል አንዳንዶቹ በየትኛው ድል ተካፋዮች ሆነዋል? (ለ) የመንግሥቲቱ ዜጎች በገዥዎቻቸው ላይ ትምክህት ሊኖራቸው የሚችለው ለምንድን ነው?

16 በዚሁም ጊዜ ውስጥ፣ ይሖዋ በአነስተኛ ወጪ ለመሥራት ባለው ችሎታ ከእነዚህ ታማኞቹ መካከል በሰማያዊቱ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ሰዎች ሲመርጥ ቆይቷል። ምንም እንኳ ሰይጣን “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት” ቢከሳቸውም “ከሚመሠክሩት ቃል የተነሣ” ድል ነስተውታል። ‘ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን ለሞት እንኳ አሳልፈው ሰጥተዋል።’ ምሳሌያቸው እንደሆነው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታቸውን ሳይቀር አሳልፈው በመስጠት ለአምላክና ለጎረቤት ያላቸውን ወደር የለሽ ፍቅር ለማሳየት ፈቃደኞች ሆነዋል። ስለዚህ ሁሉም በተግባር ተፈትነው ንጹሕ አቋማቸውን በጠበቁት በክርስቶስና በ144,000 ተባባሪ ነገሥታት በተገነባችው ሰማያዊት መንግሥት ላይ ሰብዓዊው ፍጥረት ከፍተኛ ትምክህት ሊጥል ይችላል! — ራእይ 12:10, 11፤ 14:1–5፤ 20:4፤ ዮሐንስ 15:13

17. የመንግሥቲቱን ምድራዊ ግዛት የሚወርሱት እነማን ናቸው?

17 በቅድመ ክርስትና ዘመን በአምላክ ፊት የታመኑ ሆነው የሞቱት እንደ ኢዮብ ያሉት ሌሎችም “የሚበልጠውን ትንሣኤ” በማግኘት በ“አዲስ ምድር” ውስጥ እንደሚኖሩ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 11:35፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እነርሱ ‘የመልካሙ እረኛ’ የኢየሱስ ክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ክፍል በመሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ከዚህም ሌላ ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ዘመን ውስጥ ለክርስቶስ ቅቡዓን “ወንድሞች” ደግነት የሚያሳዩ በግ መሰል ሰዎች ይህንን የመንግሥቱን ምድራዊ ግዛት እንዲወርሱ ይጋበዛሉ። (ዮሐንስ 10:11, 16፤ ማቴዎስ 24:3፤ 25:31–46) የሰማይ መላእክት “የታላቁን መከራ” ነፋሳት በምድራችን ላይ በሚለቁበት ጊዜ እነርሱ ከመዓቱ በሕይወት ይተርፋሉ። የአምላክ መንግሥት ክፉዎቹን አሕዛብ ለመደምሰስ ‘ስትመጣ’ በሕይወት ከሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” መካከል ለመሆን ትፈልጋለህን? ከፈለግህ ትችላለህ፤ ምክንያቱም ንጹሕ አቋም ጠባቂ በመሆን አንተም ማለቂያ ወደሌለው ሕይወት ሊመራ የሚችለው የአምላክ መንገድ ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ ትችላለህ። — ራእይ 7:1–3, 9, 13, 14

18. (ሀ) የይሖዋን ሉዓላዊነት ዳግመኛ ማረጋገጥ አስፈላጊ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አሁን ብሩህ ተስፋ ያላቸው እነማን ናቸው? (መዝሙር 37:11, 29)

18 የአምላክ መንግሥት አንድ ጊዜ ሰይጣንንና ብልሹ ሥርዓቱን ከደመሰሰች በኋላ የአምላክን ሉዓላዊነት እንደገና ማረጋገጥ ፈጽሞ አስፈላጊ አይሆንም። በዓመፀኛው ሰይጣን የተነሡት አከራካሪ ጥያቄዎች ለአንዴና ለሁልጊዜ መልስ ያገኛሉ። (ናሆም 1:9) እዚህ ምድር ላይ በአምላክ የፍቅር ሕግ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ትክክለኛ፣ ጻድቅ፣ ከሁሉም የላቀ መሆኑ ይረጋገጣል። መንግሥቲቱም መጥታ የልዑሉን ጌታ የይሖዋን ታላቅ ስም የመቀደስ ተግባሯን ትፈጽማለች። ‘በመቃተት ላይ ካለው ፍጥረት’ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ አምላክን ለሚያገለግሉት የአምላክ መንግሥት እንዴት ያለ ብሩህ ተስፋ ይዛላቸዋለች! ይህች መንግሥት ‘እንድትመጣ’ የጋለ ጸሎት እያቀረብክ ነውን? — ሮሜ 8:22–25

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 44 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አምላክ ለዚህን ያህል ረጅም ጊዜ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?

● የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ትክክለኛ፣ ጻድቅ፣ የላቀና ዘላለማዊ መሆኑን ለማረጋገጥ

● ከአምላክ ውጭ የሆነ ማንኛውም ዓይነት የሰው አገዛዝ ወደ ሐዘንና ጥፋት ብቻ የሚመራ መሆኑን ለሁልጊዜው ለማሳየት

● የአምላክ መንግሥት ተስፋዎች ቀስ በቀስ የበለጠ ግልጽ እንዲሆኑ ለማስቻልና የመንግሥቲቱን ወራሾች ለመምረጥና ለመፈተን

● ልክ በፍርድ ቤት እንደሚደረገው የአምላክ አገልጋዮች ከሰይጣን ማንኛውም ፈተና ቢደርስባቸውም እንኳ ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ መቻላቸው እንዲረጋገጥ ጊዜ ለመፍቀድ

● በአምላክ የፍቅር ሕግ ላይ የተመሠረተ ታዛዥነት ደስታ ወዳለበት ዘላለማዊ ሕይወት የሚመራ ብቸኛው መንገድ መሆኑን ለማሳየት

● ለሰይጣን ግድድር የማያዳግም መልስ ለመስጠትና ዳግመኛ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ፈጽሞ አስፈላጊ እንዳይሆን ሕጋዊ መሠረት ለመጣል።