በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንግሥቲቱ ‘የምትመጣው’ ከየት ነው?

መንግሥቲቱ ‘የምትመጣው’ ከየት ነው?

ምዕራፍ 4

መንግሥቲቱ ‘የምትመጣው’ ከየት ነው?

1. በ1 ጢሞቴዎስ 1:17 እና በራእይ 15:3 መሠረት ምን ትልልቅ ጥያቄዎች ይነሣሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የዘላለም ንጉሥ” ብሎ ይገልጸዋል። ታዲያ ስሙን የምትቀድስ መንግሥት ለምን ‘መምጣት’ አስፈለጋት? (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 15:3) የምትመጣውስ ከየት ነው?

2. በመስተዳድር ላይ የሚታዩ የትኞቹ ሁኔታዎች በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ አምጥተዋል? በምንስ መንገድ?

2 ጽድቅን፣ ሰላምንና ደስታን በዚህች ምድር ላይ እንደገና ለመመለስ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ዓይነት አጠቃላይ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ግልጽ ነው። መንግሥታት በተለያዩ መንገዶች የዜጎቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ የተሳናቸው ከመሆኑም ሌላ ብሔራት እርስ በርሳቸው በመበጣበጥ ላይ ይገኛሉ። ጥላቻ፣ ተቀናቃኝነትና የብሔሮች መቃቃር ሕዝቦችንና የተለያየ ዘሮችን ከፋፍሏቸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ፈጣሪያችን ከነበረው ዓላማ ውጭ ናቸው። በስሙ ላይም ብዙ ነቀፋ እንዲቆለል አድርገዋል። — ሮሜ 2:24፤ ሕዝቅኤል 9:9

3. (ሀ) እዚህ ላይ የአምላክ መንግሥት ጉዳይ የሚነሣው እንዴት ነው? (ለ) ይህችን መንግሥት ልዩ የሚያደርጋት ምንድን ነው?

3 ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል አንድ በጣም ልዩ የሆነ መንግሥት ያስፈልጋል። ይሖዋም ያዘጋጀው ይህንን ነው። ይህ መንግሥት የሚመጣው ከየት ነው? በሰማያት ከሚኖረው ከራሱ ከይሖዋ ነው። ይህ መንግሥት የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት መግለጫ የሆነ ጥገኛ መንግሥት ነው። ሥልጣን ያገኘውም ሰማያትና ምድር ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ይሖዋ ይዞት ከቆየው ንግሥና ነው። ከአምላክ ሰማያዊ ድርጅት የተገኘ መንግሥት ስለሆነ ይህ በጣም ልዩ የሆነ መለኮታዊ አገዛዝ የዘመናት ዕድሜ ያለውን የይሖዋን ሉዓላዊነት አስደናቂ ባሕሪያት ይወርሳል። — ራእይ 12:1, 2, 5

የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት

4. የይሖዋን ሉዓላዊነት በተገቢ ሁኔታ የሚገልጸው በራእይ 4:11 ላይ ያለው የትኛው አባባል ነው?

4 አምላክ “ሁሉን የፈጠረ” በመሆኑ የሁሉም ፍጥረቶቹ ሉዓላዊ ገዥ ለመሆን መብት አለው። ሌላው ቀርቶ አምላክ ወደ ሰማያት ወስዶ ንግሥናን በመስጠት ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው ሰዎችም እንኳ ‘በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው መስገድ’ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ቀጥሎ ባለው ስለ እነሱ በተሰጠው መግለጫ መሠረት “የዘላለሙ ንጉሥ” የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለ ሥልጣን መሆኑን በትሕትና ይቀበላሉ።

“አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።” (ራእይ 4:10, 11 ፤ ኤፌሶን 3:9)

አንተ የአምላክን ሉዓላዊነት የምትመለከተው እንደዚህ አድርገህ ነውን? መሆን ይኖርበታል።

5. ከሰብዓዊ መስተዳድሮች ጋር ሲነፃፀር የይሖዋ ንግሥና ሁሉን አቀፍ የሆነው እንዴት ነው?

5 በሰዎች መካከል አንድ መንግሥት ሕግ አውጥቶ ሕዝቡን ያስተዳድራል። ሥርዓትን ለማስጠበቅ እንደዚያ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ መንግሥታት በውስጣቸው በሕግ የሚፈርዱ ዳኞች፣ ሕግ አርቃቂ ፓርላማዎችና ሕጉን የሚያስከብር ንጉሥ ወይም ፕሬዘዳንት አሏቸው። ይሖዋ በፈጠረው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ሦስቱንም ቦታዎች የያዘው ራሱ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ሲያመለክት “ይሖዋ ፈራጃችን ነው፣ ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፣ ይሖዋ ንጉሣችን ነው” ብሏል። (ኢሳይያስ 33:22 አዓት) ንጉሥ ዳዊትም ስለዚህኛው ንጉሥ የሚከተሉትን ቃላት ጨምሮ ይናገራል:- “ይሖዋ ዙፋኑን በሰማያት አጽንቶ መሠረተ፣ ንግሥናውም በሁሉም ነገር ላይ ነው።” (መዝሙር 103:19 አዓት) እስቲ የዚህን ንግሥና አንዳንድ ገጽታዎች እንመርምር።

የአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሕግጋት

6. የአምላክ ሕግጋት ከማንኛውም ሕግ የላቁ መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?

6 የሰዎች መንግሥታት የሰብዓዊ ተገዥዎቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፤ ሕይወታቸውን በጥልቅ የሚነኩትን የተፈጥሮ ኃይሎች ግን መቆጣጠር አይችሉም። የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ይሖዋ ግን ይህን መቆጣጠር ይችላል፤ ይቆጣጠረውማል። የሳይንስ ሰዎች በጠፈር ውስጥ ያሉትን ግዑዛን አካላት ስለሚያንቀሳቅሱት ሕጎች ትክክለኛነት ብዙ ጊዜ ይደነቃሉ። እነዚህ የአምላክ ሕግጋት ናቸው። ሰዎች በጨረቃ ላይ ለማረፍ፣ በሳተላይቶች አማካኝነት ግንኙነት ለማድረግ፣ የግርዶሽን መከሰት አስቀድመው ለመናገር የቻሉትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ውስብስብ የፈጠራ ሥራዎችን ማስገኘት የቻሉት እንደነዚህ ያሉት ሕጎች ያለ ምንም መዛነፍ የሚሠሩ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪ የአምላክ ሕግጋት ፀሐይንና ዝናብንም ይቆጣጠራሉ። አምላክ የሚታዘዙትን ሰዎች ለመባረክ ሲል እነዚህን በተፈጥሮ ያሉ ኃይሎች በተፈለገው መንገድ እንዲሠሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። — መዝሙር 89:8, 11–13፤ ኢዮብ 38:33, 34፤ ዘካርያስ 14:17

7. (ሀ) የይሖዋ ሕግጋት ስለ አምላክነቱ የሚመሠክሩት እንዴት ነው? (ለ) እንደ ኢዮብ እኛም የአምላክን መንገዶች እንዴት መመልከት ይኖርብናል?

7 አንድ የአምላክ ነቢይ አስደናቂ የሆኑትን የሰማያዊ ግዑዛን አካላት በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ዓይኖቻችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው።” (ኢሳይያስ 40:26, 28) በቢልዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋ ግዙፉን አጽናፈ ዓለሙን “የተፈጥሮ” ሕግጋት ተብለው በሚጠሩት ሕጎች ሲቆጣጠር ቆይቷል። ሰዎች የእነዚህን ሕጎች ምሥጢር ለመፍታት ሞክረዋል፤ ሆኖም ገና ያልደረሱበት ብዙ ነገር አለ! ከዛሬ 3, 500 ዓመታት በፊት የነበረ አንድ ታማኝ ሰው ከገለጸው ቀጥሎ ካለው ሁኔታ እምብዛም ፎቀቅ አላሉም:- “እነሆ፤ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም (ስለ እርሱ) የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጎድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?” — ኢዮብ 26:14

8. ይሖዋ ለፍጡሮቹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች የሚያሰናዳ ታላቅ አምላክ መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ የአምላክ ባሕርያት ሲጣመሩ ነው?

8 ይሁን እንጂ ይሖዋ ምድራችንን ሲፈጥር አካላዊ እንቅስቃሴን በሚቆጣጠሩ ሕግጋቱ መሠረት ብቻ አልሠራትም። ጥልቀቱ ወሰን የሌለው ጥበቡና መለኪያ የማይገኝለት ፍቅሩ ከኃይሉና ከሕጎቹ ጋር ተቀናጅተው ለምድር የወደፊት ነዋሪዎች አስደናቂ ዝግጅት እንዲደረግ ምክንያት ሆነዋል። እዚህ ምድር ላይ ባሉት የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የሚታየው እንዴት ያለ ደግነት የተሞላበት አርቆ ተመልካችነትና እንዴት ያለ ድንቅ የፈጠራ ችሎታ ነው! (1 ዮሐንስ 4:8፤ መዝሙር 104:24፤ 145:3–5, 13) ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ለፍጡሮቹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ የሚያሰናዳ ታላቅ አምላክ ነው!

9. አምላክን ልናመሰግንባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

9 ለእነዚህ ሁሉ አስደናቂ ዝግጅቶቹ አምላክን ማመስገን ይኖርብናል። በተጨማሪም እኛን ሰዎችን በፈጠራቸው ነገሮች ደስታ ልናገኝ ከምንችልባቸው አካላዊና አእምሮአዊ ችሎታዎችና የስሜት ሕዋሳት ጋር ስለፈጠረን ልናመሰግነው ይገባል። አዎን፤ ልክ እንደ መዝሙራዊው እኛም ለአምላክ ያለንን አመስጋኝነት መግለጽ አለብን:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ አካሌም በምድር በታች በተሠራ ጊዜ፣ አጥንቶቼም ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” — መዝሙር 139:14–16

10. በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ይሖዋ ሙሉ ችሎታ ያለው መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

10 አጽናፈ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረውንና የነገሮችን ሥርዓት በፍቅሩና በጥበቡ እንዲሁም ከጻድቅ ሕግጋቱ ጋር በሚስማማ መንገድ የመሠረተውን ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለትም ይናገርለታል:- “የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።” (መዝሙር 89:14) በእርግጥም ይሖዋ በምድር ላይ ነገሮችን የምታስተካክል ንጉሣዊ መስተዳድር ለማምጣት ችሎታ አለው። (መዝሙር 40:4, 5) ነገር ግን ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

አንድን ምሥጢር መግለጥ

11. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እውቀት ሊገኝ በመቻሉ ደስተኞች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) “ሚካኤል” ማን እንደሆነ እንዴት ለይተን ለማወቅ እንችላለን? ስሙስ ምን ትርጉም አለው?

11 የአምላክን ስም የምትቀድስና ፈቃዱን በምድር ላይ የምታስፈጽም አንዲት መንግሥት አምላክ ማቋቋሙን የሚያመለክቱ ብዙ ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ከእነዚህም አንዱ የዳንኤል ትንቢት ሲሆን ‘በፍጻሜው ዘመን እውነተኛ እውቀት እንደሚበዛ’ ይናገራል። ዛሬ እንዲህ ያለውን እውቀት ልናገኝ የምንችል በመሆናችን ልንደሰት እንችላለን። ዳንኤል እንዲህ በማለት ይነግረናል:-

“ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን . . . ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።”

ዳንኤል እንደሚገልጸው ይህ የሚሆነው ታላቁ መስፍን ሚካኤል ስለ አምላክ ሕዝቦች በሚነሣበት ጊዜ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሚካኤል የይሖዋን ስም ለመቀደስ ሲል የአምላክን ጠላቶች የሚዋጋው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። እንግዲያው “ሚካኤል” የተባለው ስም “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም የያዘ መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ማንም የይሖዋን ሉዓላዊነት ተገዳድሮ እንደማይሳካለት የሚያረጋግጠው ሚካኤል ነው። — ዳንኤል 12:1, 4፤ ራእይ 12:7–10

12. በዳንኤል 2:31–33 ላይ የተገለጸው የሕልም ምስል ምንድን ነው? ዛሬ ስለ እርሱ የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባውስ ለምንድን ነው?

12 በተጨማሪም የዳንኤል ትንቢት የባቢሎን ንጉሥ ስላየው አንድ ሕልም ይናገራል። ሕልሙ ተራ በተራ ስለሚነሡ መንግሥታት ይገልጻል። ንጉሡ ያየውን ሕልም ወዲያው ጨርሶ ረሳው፤ ቢሆንም ያለማቋረጥ በጣም ያስጨንቀው ነበር። በመጨረሻም ‘ምስጢር ገላጭ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ በዳንኤል ተጠቅሞ ሕልሙን ብቻ ሳይሆን ትርጉሙንም ጭምር ለንጉሡ አሳወቀው። (ዳንኤል 2:29) የዚህ ትንቢታዊ ሕልም ፍጻሜ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የሚቀጥልና ከዚያም አልፎ የሚሄድ በመሆኑ ትርጉሙን ለማወቅ ጥልቅ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። ሕልሙ መልኩ አስፈሪ ስለሆነ ስለ አንድ የሰው ቅርጽ ያለው ‘ግዙፍ ምስል’ ነበር። በዳንኤል 2:31–33 ላይ ስለ እርሱ ማንበብ ትችላለህ። ይህ ምስል ምን ያመለክታል?

13. የምስሉ የተለያዩ ክፍሎች ምን ያመለክታሉ?

13 ዳንኤል ከወርቅ የተሠራው ራስ የባቢሎንን “ንጉሥ” እንደሚያመለክት፤ ከዚያ በታች ያሉት የአካሉ ክፍሎች ደግሞ ከባቢሎን በኋላ የሚነሡትን መንግሥታት እንደሚወክሉ ለናቡከደነጾር አሳወቀው። ዛሬ እኛ እነዚህ መንግሥታት የሜዶ ፋርስ፣ የግሪክና የሮም ኃያል ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛቶች እንደሆኑና ወደ “እግሮቹ” ወረድ ስንል ደግሞ በዘመናችን እስካለው የአንግሎ አሜሪካ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ድረስ የሚቀጥሉ መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ ማወቅ እንችላለን። “እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት” ስለሆኑት ጣቶቹስ ምን ለማለት ይቻላል? ብረቱ ‘ከሸክላው ጋር ለመደባለቅ’ የማይችል በመሆኑ የግዙፉ ምስል ጣቶች ተሰባሪ እንደሆኑ ሁሉ በቅርብ ዓመታት የታዩት የሶሻሊስት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የአንግሎ አሜሪካንን ብረት መሰል የዓለም ኃያል ሥልጣን በጣም አዳክመውታል። በዚህ ምክንያት ይህ አስፈሪ ምስል የአምላክ መንግሥት እስከምታጠፋቸው ድረስ በተከታታይ የሚነሡትን “ነገሥታት” ወይም የዓለም ኃይላት ይወክላል። — ዳንኤል 2:36–44

14, 15. “ድንጋዩ” ምስሉን ምን ያደርገዋል? የዚያን “ድንጋይ” ምንነት እንዴት ማወቅ እንችላለን?

14 ተመልከት! አንድ ድንጋይ “እጅ ሳይነካው” በተዓምር ከተራራው ተፈነቀለ። ይህን ድርጊት ያስፈጸመ ሰብዓዊ ኃይል የለም። ከዚህ ይልቅ በቅዱስ ፈቃዱ መሠረት ይህን ያስደረገው ይሖዋ ራሱ ነው። ድንጋዩ ወደ ኃያሉ ምስል ተወርውሮ መጣና እግሮቹን መታ። የምስሉ ድቃቂ በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ እስኪበተን ድረስ ድንጋዩ ጠቅላላውን የሰብዓዊ አገዛዝ መዋቅር ያንኮታኩተዋል። ከዚያም ድንጋዩ ራሱ መላዋን ምድር የሚሞላ ታላቅ ተራራ ይሆናል። — ዳንኤል 2:34, 35

15 ይህ ድንጋይ ምን ሊሆን ይችላል? ትንቢቱ የሚከተለውን በመግለጽ ስለ ምንነቱ ሊኖር የሚችለውን ማንኛውንም ጥርጣሬ ያስወግዳል:-

“በእነዚያም ነገሥታት [በአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃይልና ከእርሱ በፊት በነበሩት የዓለም ኃይላት ርዝራዦች] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፣ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” — ዳንኤል 2:44

16. “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን ስንጸልይ ምን የሚል ልመና ማቅረባችን ነው?

16 ይህ በዛሬው ጊዜ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? የአምላክ መንግሥት “ትምጣ” ብለን ስንጸልይ ሰማያዊቷ መንግሥት ዛሬ ሰላምንና ብልጽግናን ማምጣት የተሳናቸውን ሰው ሠራሽ አገዛዞች ሁሉ ለመደምሰስ አጥፊ ኃይሏን እንድትጠቀምበት መለመናችን ነው። ደስ የሚለው ግን ያ “ድንጋይ” የማጥፋት ተልእኮውን ከፈጸመ በኋላ መላዋን ምድር የሚሞላ መንግሥታዊ ተራራ እስኪመስል ድረስ በመጠን ከፍ እያለ መሄዱ ነው። ይህ መንግሥት የሰው ልጅ ከንጉሥ ሰለሞን ዘመን ወዲህ ያላየውን ሰላም ያመጣለታል። ‘ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ (ማለትም ለዘላለም) ሰላሙ ብዙ ይሆናል።’ — መዝሙር 72:7

17. (ሀ) “ድንጋዩ” ከዋናው “ተራራ” ጋር ያለው ዝምድና ትምክህት የሚያሳድርብን ለምንድን ነው? (ለ) መንግሥቲቱ ምን ተጨማሪ እርምጃ ትወስዳለች? (ሐ) በመዝሙር 85:8–12 ላይ እንደተገለጸው ምን ትምክህት ሊኖረን ይገባል?

17 ይሁን እንጂ ይህ መንግሥትን የሚያመለክት “ድንጋይ” ስለተፈነቀለበት “ተራራ” ምን ሊባል ይቻላል? (ዳንኤል 2:45) “ድንጋዩ” የተራራው ጥገኛ መሆን አለበት፤ ከተራራው ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለውም መሆን ይኖርበታል፤ ደግሞም ነው። ይህ መንግሥታዊ አገዛዝ የዘላለም ንጉሥ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ሉዓላዊ ገዥነት የተቆረሰ ነው። የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት መልካም ባሕርያቱን በሙሉ እንደሚያንጸባርቅ ሁሉ ከዚህ ሉዓላዊነት የተቆረሰችው መንግሥት ይሖዋ አምላክንና ታላላቅ ዓላማዎቹን ከፍ ከፍ ማድረግ ይኖርባታል። ጠላቶቹን በማጥፋት ስሙን ትቀድሳለች፤ በዚህም እርምጃዋ ይሖዋ የክፉ ሥራቸው ተባባሪ እንዳልሆነ ታሳያለች። ከዚያም በክርስቶስ ኢየሱስ የምትመራው ይህች መንግሥት አምላክ ከመጀመሪያው እንዳሰበው ምድርን ጽድቅ የነገሰባት ሰላማዊ ቦታ አድርጋ በመለወጥ በሕግና በሥርዓት፣ በፍቅርና በደስታ ትሞላታለች። በእውነትም ‘መንግሥቲቱ እንድትመጣ’ እየጸለይን መሆን አለብን! — መዝሙር 85:8–12

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]