በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መንግሥትህ ትምጣ”!

“መንግሥትህ ትምጣ”!

ምዕራፍ 1

“መንግሥትህ ትምጣ”!

1. የአምላክ መንግሥት እዚህ ላይ በስዕል የሚታዩትን ሁኔታዎች በቅርቡ የምታመጣ ከሆነ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖራታል ማለት ነው?

ከላይ የተጠቀሱትን የጸሎት ቃላት ያህል ብዙ ጊዜ ተደጋግመው የተጸለዩ ቃላት የሉም። ምናልባት አንተ ይህን መጽሐፍ በማንበብ ላይ ያለኸውም ይህንን ጸሎት ጸልየህ ይሆናል። በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ታስፈልገናለች! በዚህ ገጽ ላይ በስዕል የተገለጹትን በመሰሉ ሁኔታዎች ሥር መኖሩ ምንኛ ግሩም ነው! የአምላክ መንግሥት የያዘችልንም ተስፋ ይኸው ነው። በመላው ምድር ላይ ሰላምና ስምምነት ይሰፍናል። የሰው ዘሮች በእውነተኛ የፍቅር ሰንሰለት ተያይዘው አንድ ይሆናሉ። ሁሉም ሰው ፍሬያማ ሥራ በመሥራቱ ይደሰታል። ከድካሙም ፍሬ ተጠቃሚ ይሆናል። አየሩም በፍጥረት ጣዕመ ዜማና በደስተኛ የሰው ልጆች ዝማሬና ሳቅ የተሞላ ይሆናል። ማንም የማያረጅበትና የማይሞትበት ጤናማ ምድር አቀፍ ኅብረተሰብ ይኖራል። ከእንሰሳት ጋር በሰላም ለመኖር ስለሚቻል ደስታ ይሰፍናል። የአበቦች መዓዛ፣ በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀ ሜዳና ተፈራራቂ ወቅቶች ይኖራሉ። አዎን፣ ወደፊት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናየው የአምላክ መንግሥት ከመጣች በኋላ እነዚህና ሌሎች ብዙ ነገሮች በምድር ላይ እንደሚመጡ አምላክ ቃል ገብቶልናል።

2, 3. የትኞቹ በቅርብ ዓመታት የተከሰቱ ለውጦች ናቸው የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነት የሚያጎሉት?

2 ይሁን እንጂ ዛሬ ያለው የነገሮች ገጽታ ከዚህ በጣም የተለየ ነው፤ ምክንያቱም ዛሬ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “አስጨናቂ” ብሎ በጠራው ጊዜ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህ አስጨናቂ ጊዜ የገዛ ራስህን ሕይወት እንዴት እየዳሰሰው እንዳለ ታውቃለህ። የዚህን መጽሐፍ ገጾች የሚያነቡ ብዙ ሰዎች በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ በተደረጉት ጦርነቶችና ግጭቶች ሳቢያ ዘመዶቻቸውን አጥተዋል። ይህም ሆኖ ብሔራት ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በተጧጧፈ የጦር መሣሪያ እሽቅድድም ውስጥ ገብተዋል። እስካሁን ድረስም ጠቅላላውን የሰው ዘር ለመደምሰስ ከሚያስፈልገው እጅግ የሚበልጥ የጦር መሣሪያ ክምችት አላቸው።

3 ሌሎች የግል ሕይወታችንን የሚነኩ ችግሮችም ያሳስቡናል። የዝርፊያ፣ የግድያና ሴትን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል እያደገ በመምጣቱ ለብዙዎቻችን በመንገድ ላይ መሄድ እንኳ አደገኛ ሆኖብናል። በዛሬው ጊዜ ስለ ፍቺ፣ ስለፈረሱ ቤተሰቦችና ስለ ወጣቶች ወንጀለኛነት ከቀድሞው ጊዜ የበለጠ እየሰማን አይደለምን? ልቅ የጾታ ብልግናና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛነት መረን በለቀቀበት በዚህ ዘመን ውስጥ ብዙ ሰዎች ልጆቻቸውን ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤት ለመላክ ይፈራሉ። እንደነዚህ ያሉት ችግሮች ባልተስፋፉበት መንደር ወይም አገር የምትኖር ከሆነ በእውነቱ አመስጋኝ መሆን ይገባሃል!

4, 5. (ሀ) ሕይወታችንን የሚዳስሱት የትኞቹ ሌሎች ችግሮች ናቸው? (ለ) ‘የአምላክ መንግሥት መምጣት’ አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን የትኞቹ የዓለም አዝማሚያዎች ያሳያሉ?

4 በዛሬው ጊዜ ምግብ ለማዘጋጀት ምን ያህል ወጪ ይጠይቅብሃል? መኪናህን ለማንቀሳቀስ ምን ያህል ገንዘብ ታወጣለህ? የምግብና የነዳጅ ዋጋ እየናረ ስለሄደ የሚዋዥቀው የዓለም ሁኔታ በወደፊቱ የሰዎች ሕይወት ላይ የመከራ ጥላ አጥልቶበታል። ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው? ነሐሴ 4 1980 በወጣው ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ላይ የቀረበ አንድ ዘገባ የቀውሱን አስከፊነት አስምሮበታል። እንዲህ አለ:- “በከፍተኛ ደረጃ አዳዲስ እርምጃዎች ካልተወሰዱ በስተቀር ከዛሬ 20 ዓመት በኋላ የሚኖረው ዓለም በቢልዮን የሚቆጠሩ ድሆች በቀላሉ የማይገኙ፣ ዋጋቸው ውድ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት በከንቱ የሚንከራተቱበት የተበላሸና ያልተረጋጋ ፕላኔት ይሆናል። ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው በፕሬዘዳንቱ የተሰየመ አንድ ኮሚሽን የሦስት ዓመታት ጥናቱን ባጠናቀቀበት ሐምሌ 4 ቀን ነው።” ይህ ጥናት ሌሎች ነገሮችን ከማሳወቁም በተጨማሪ በ2 000 ዓመት ላይ የዓለም ሕዝብ ብዛት 6.3 ቢልዮን እንደሚደርስ፣ የገንዘብ ዋጋ ከማሽቆልቆሉም ሌላ የምግብ ዋጋ በእጥፍ እንደሚጨምር፣ በረሀዎች እንደሚስፋፉና ደኖቸ እንደሚጠፉ፣ ቢያንስ ግማሹ የዓለም ዘይት እንደሚሟጠጥ አሳይቷል። ይህ የሚሆነው ግን አሁን ያለው ሥርዓት ያን ያህል ከቆየ ነው!

5 መንግሥታት በተናጠል ስለ እነዚህ ቀውሶች ምን አድርገዋል? ሌላው ቢቀር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምን ለማድረግ ችሏል? እስከ አሁን ድረስ ምንም መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም። ይህ ሁሉ የአምላክ መንግሥት ምን ያህል በአስቸኳይ እንደምታስፈልገን ያሳያል!

ይህች መንግሥት ምንድን ነች?

6. የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ የምትገኝ ነገር ብቻ ብትሆን ኖሮ ነገሩ ተስፋ አስቆራጭ ይሆን የነበረው ለምንድን ነው?

6 ይህች መንግሥት በአማኞች ልብ ውስጥ ያደረ ነገር ማለት ነችን? በሌላ አባባል ቁጥራቸው በቂ የሆኑ ሰዎች ወደ ክርስትና በተለወጡ ጊዜ የአምላክ መንግሥት እዚህ ትገኛለች ማለት ነውን? አንዳንድ ሰዎች በኪንግ ጀምስ ቨርሽን ወይም ኦቶራይዝድ ቨርሽን (የእንግሊዝኛው) መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ 17:21 ላይ የሚገኘውን:- “የአምላክ መንግሥት በውስጣችሁ ናት” የሚለውን በመመልከት ነገሩን በዚህ መንገድ ተረድተውታል። የእነርሱ መደምደሚያ ትክክል ከሆነ የአምላክ መንግሥት የባሰውን እየራቀች ሄዳለች ለማለት ያስደፍራል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያን ነን የሚሉት ሰዎች ብዛት ዛሬ ካለው የዓለም ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር ከ25 በመቶ ያነሰ ሲሆን ገና ወደታች እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው። በተጨማሪም እንደ መስከረም ወፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቅ የሚሉ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉ።

7, 8. ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመራችን የሉቃስ 17:21⁠ን ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?

7 የሚከተለውንም ቁም ነገር አስቡ:- ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት በውስጣችሁ ናት” ባለ ጊዜ ይነጋገር የነበረው ከነማን ጋር ነበር? ከግብዞቹ ፈሪሣውያን ጋር ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “ልባችሁ ከእኔ በጣም የራቀ ነው” ብሎ የተናገረው የአምላክ ቃል በእነርሱ ላይ እንደሚሠራ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 15:1, 8 ኦቶራይዝድ ቨርሽን፣ ኢሳይያስ 29:13) ታዲያ በእነዚያ ደንዳና ልቦች ውስጥ መንግሥቲቱ እንዴት ልትገባ ትችላለች? ታዲያ የኢየሱስ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? በኅዳጎቻቸው ላይ አማራጭ ንባቦች ያሏቸው የኪንግ ጀምስ ቨርሽን እትሞች ለመልሱ ፍንጭ ይሰጣሉ። እዚያ ላይ የተሰጠው አማራጭ ንባብ:- “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ይላል። እንደ ካቶሊኩ ጀሩሳሌም ባይብል እና ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ያሉ ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ጥቅሱን የተረጐሙት እንደዚሁ ብለው ነው።

8 ስለዚህ ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው የመንግሥቲቱ እጩ ንጉሥ ራሱ በመካከላቸው ስለመሆኑ ነው። በእውን ወይም በተጨባጭ እዚያው በመካከላቸው ነበር። ይህም ንጉሥዋ እውን እንደሆነ ሁሉ መንግሥቲቱም እውን መንግሥት፣ ተጨባጭ መስተዳድር መሆኗን ሊያስገነዝበን ይገባል።

ዛሬም መንግሥቲቱ በተጨባጭ አለች

9, 10. ተጨባጭ የሆነ መንግሥት ምን ዓይነት ነው? ዜጎቹንስ እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?

9 በጊዜያችን በዚህ ምድር ላይ የቀሩት ንጉሣዊ መንግሥታት በቁጥር ናቸው። እነርሱም በተጨባጭ ያሉ መስተዳድሮች ሲሆኑ ኖርዌይ፣ የዩናይትድ ኪንግደም (እንግሊዝ)፣ ዮርዳኖስና ኔፓል ጥቂቶቹ ናቸው። በእነዚህም አገሮች ውስጥ የፓርላማ፣ የካቢኔ ወይም የሌላ መንግሥታዊ አካል አባል በመሆን ከሚያገለግሉ ባለ ሥልጣኖች ጋር ንጉሥ አለ (ወይም ንግሥት አለች።) ሰፊው ሕዝብ አነስተኛ ቁጥር ባለው በዚህ የገዥ መደብ ሥር ሆኖ ዕለታዊ ኑሮውን ይመራል። እነርሱ በመንግሥታቸው ሥር የሚተዳደሩ ዜጎች ናቸው።

10 ንጉሡና ባለ ሥልጣኖቹ ስለ ሕዝቡ ደኅንነት በጥልቅ በሚያስቡበት አገር መንግሥት ብዙ ጥቅሞች ሊሰጥ ይችላል። የጥንቱ የንጉሥ ሰሎሞን መንግሥት ሁኔታ ልክ እንደዚህ ያለ ነበር። በዚያን ጊዜ ሕዝቡ “እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፣ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።” — 1 ነገሥት 4:20፤ 10:1–9

11. የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ካሉት መንግሥታት ጋር የምትመሳሰለው በምን መንገዶች ነው?

11 የአምላክ መንግሥት ከሰማይ የምትገዛ መሆንዋ ከላይ እንደተጠቀሱት መንግሥታት ተጨባጭ አይደለችም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! በመጀመሪያ ደረጃ ምን ጊዜም ሕያው የሆነና በትጋት የሚሠራ ንጉሥ አላት። እርሱም አምላክ ራሱ የሾመው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱን በማስመልከት መጽሐፍ ቅዱስ “በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። (ሮሜ 15:12) በምድር ላይ እንዳሉት መስተዳድሮች ሁሉ ይህችም ሰማያዊት መንግሥት ከብዙ አባላት የተውጣጣ የአገዛዝ አካል አላት። ይህ አካል በዚህ ምድር ላይ ለአምላክ ያላቸውን ፍጹም አቋም ጠባቂነት ያረጋገጡ ወንዶችና ሴቶች አባል የሆኑበትና ውስን ቁጥር ባላቸው ተባባሪ ነገሥታት የተገነባ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለእነዚህ ሰዎች ኢየሱስ “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:4) መንግሥቲቱ ሰማያዊ ሥልጣን አላት። ይህች ንጉሣዊ መስተዳድር ከሰማያዊ መቀመጫዋ ከሬዲዮ ወይም ከሌዘር ጨረር በበለጠ ፍጥነት ትእዛዟን ወደ የትኛውም የምድር ክፍል ማስተላለፍ ትችላለች።

12, 13. የአምላክ መንግሥት ምን ዓይነት (ሀ) ሕግጋት (ለ) ሥርዓተ ትምህርት (ሐ) የጤና መርሐ ግብር አላት?

12 ሕግጋትን በተመለከተስ ምን ሊባል ይችላል? አዎን፣ የአምላክ መንግሥት የምታስተዳድረው በሕግ ነው፤ ሕዝቡን ለመጥቀም አምላክ ያወጣቸው ከማንኛውም ሕግ የሚበልጡ ሕግጋት አሏት። ሕግጋቱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማንበብ ትችላለህ። (ዘዳግም 6:4–9፤ ማርቆስ 12:28–31) መንግሥቲቱ ሥርዓተ ትምህርት አላትን? በእርግጥ አላት! በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ብሔራት፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙ ቅን ሰዎች በመንግሥቲቱ የጽድቅ አስተዳደር ሥር ለሚገኘው የዘላለም ሕይወት እንዲዘጋጁ የመንግሥቲቱ የትምህርት መርሐ ግብር ተዘርግቶላቸዋል። በየትኛውም አገር ብትኖር አንተ በግልህ ከዚህ የትምህርት መስጫ ፕሮግራም ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለህ። — ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 7:9, 10፤ ኢሳይያስ 54:13

13 መንግሥቲቱ የጤና መርሐ ግብር አላትን? ተወዳዳሪ የሌለው መርሐ ግብር አላት፤ ያውም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ። ይህ መርሐ ግብር ሰዎች ከተሟላ ጤንነት ጋር የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ከተለያዩ በሽታዎቻቸውና ከአካላዊ ጉድለቶቻቸው ነፃ ያደርጋቸዋል። (ኢሳይያስ 25:8፤ ዮሐንስ 10:10) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በሽተኛን የማዳን፣ ዓይነ ስውር እንዲያይ የማድረግ፣ ሽባውን የመፈወስ፣ ሙታንን ሳይቀር ወደ ሕይወት የመመለስ ሥልጣንና ኃይል እንደሚኖረው ለማሳየት ብዙ ተአምራት ሠርቷል። (ሉቃስ 7:20–23) ይህ የመንግሥት መርሐ ግብር ገና ወደፊት የሚፈጸም ቢሆንም ዛሬ ስለዚሁ ጉዳይ የተማሩ ሰዎች ንጹሕ ሥነ ምግባር ጠብቀው ለመኖር የሚያስችል ትምህርት እየቀሰሙ ነው፤ አሁንም እንኳ ሳይቀር አንጸባራቂ መንፈሳዊ ጤንነት እየተመለሰላቸው ነው። ተስፋቸው ተጨባጭ ነው። — ኢሳይያስ 65:14፤ ሮሜ 10:11

14. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በትምህርቱ ውስጥ ምን ነገሮችን ገልጿል?

14 ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ነገሮችን አስተምሮአል። በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር የሰው ኑሮ ምን እንደሚመስል በትንሹ አሳይቷል። (ሉቃስ 4:43፤ ማቴዎስ 12:22–28) ደቀ መዛሙርቱንም ልክ ልጆች አፍቃሪ ከሆነ አባት ጋር በሚኖራቸው ዓይነት ዝምድና ወደ አምላክ በጣም የተጠጉ እንዲሆኑ ስለ አምላክ አስተምሮአቸዋል። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ ሰጥቶአቸዋል። — ዮሐንስ 1:18፤ 14:6

የእውነተኛ ደስታ ምንጭ

15. በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች በዛሬው ጊዜ እንደምንኖረው ሰዎች መጽናናት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

15 ‘የአምላክ መንግሥት ትምጣ’ እያልን የምናቀርበው ጸሎት ኢየሱስ ከገሊላ ባሕር ትይዩ በሆነ ኮረብታ ላይ ሆኖ ያስተማረው የተራራው ስብከት ክፍል ነው። አድማጮቹ ቀደም ሲል የመረጣቸው ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ። ይህ ሕዝብ ራስ ወዳድ በሆኑ ሰዎች ‘ተገፎ ተጥሎም ነበር።’ (ማቴዎስ 9:36) ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ሰሚዎቹን አጽናንተዋል። ዛሬም በተመሳሳይ እኛን ሊያጽናኑን ይችላሉ።

16. እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት እነማን ናቸው? እንዴትስ ያገኙታል?

16 ኢየሱስ ስብከቱን የጀመረው የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ምን እንደሆነ በማመልከት ነበር። ይህ ደስታ በቁሳዊ ሀብት፣ በመዝናኛ፣ ጊዜያዊ ደስታና ስሜትን ለማርካት በሚደረግ ጥረት የሚገኝ ነውን? አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ትኩረት የሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች ነው። ኢየሱስ ‘ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ’ እንዲሁም “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ መንገድ ዘላቂ ደስታ እንደሚያገኙ አመልክቷል። (ማቴዎስ 5:3, 6፤ ሉቃስ 8:1, 4–15) እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ፍላጎት በማዳበር ላይ ነህን?

17, 18. (ሀ) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባናል? (ለ) ኢየሱስ በማቴዎስ 6:26–33 ላይ የሰጠው ዋስትና አንተን እንዴት ይማርክሃል?

17 ኢየሱስ በአምላክ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለግን ሰማያዊ አባታችንን መምሰልን መማር እንዳለብን በስብከቱ መካከል ግልጽ አድርጎታል። ባሕርያቱን ማንጸባረቅና የአቋም ደረጃዎቹን ጠብቀን መመላለስ ይገባናል። (ማቴዎስ 5:43–48፤ ኤፌሶን 5:1, 2) እርሱን ለማስደሰት ከፈለግን አምልኮታችን በሳምንት አንድ ሁለት ጊዜ የሚደረግ የይስሙላ ሥርዓት መሆን አይችልም። ለሌሎች ሰዎች ባለን ፍቅራዊ አሳቢነትና በዕለታዊ ሕይወታችን የሚንጸባረቅ ሕያውና አንቀሳቃሽ አምልኮ መሆን ይኖርበታል።

18 ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ መንፈሳዊ ጥቅምን ብናስቀድም በዛሬው ስግብግብና ለእኔ ብቻ በሚል ኅብረተሰብ ውስጥ ለችግር የሚዳርግ አይሆንምን? በጭራሽ አይሆንም! ‘አስቀድመን መንግሥቱንና ጽድቁን የምንፈልግ’ ከሆነ ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ይጨመሩልናል። ይህንንም ኢየሱስ በማቴዎስ 6:26–33 ላይ ውብ አድርጎ ይገልጸዋል። ጥቅሱን ልታነበው ይገባል።

19, 20. (ሀ) አምላክ አምልኮታችንን እንዴት እንደሚመለከተው ማወቁ ለምን አስፈላጊ ነው? (ለ) በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛውን ቦታ እንድንሰጥ የሚረዳን ምንድን ነው? (ሐ) “የጌታ ጸሎት” የሚባለውን መመርመር ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

19 እንግዲያው ‘መንግሥቱን አስቀድመን የምንፈልገው’ እንዴት ነው? ወደ መረጥነው ቤተ ክርስቲያን ብንሄድ የአምላክን በረከት እንደምናገኝ አንድና ሁለት የለውም ማለት ነው? ወይስ አምላክ ለእኛ የመረጠልንን የአምልኮ ዓይነት ፈልገን ማግኘት ያስፈልገናል? ስለዚህ ነገር ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ በል:- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” ‘በስሙ ትንቢት ተናግረናል፣ በስሙ ብዙ ተአምራት’ አድርገናል የሚሉ አንዳንዶች በአምላክ ዓይን “ዓመፀኞች” እንደሆኑ ግልጽ አድርጓል። (ማቴዎስ 7:21–23፤ በተጨማሪም 7:13, 14 ተመልከት።) አምላክ አምልኮታችንን እንዴት እንደሚመለከተው እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው? በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ በደንብ በማወቅ ብቻ ነው።

20 መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ መመርመራችን ከግል ሁኔታዎቻችን ጋር በሚስማማ መንገድ በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት የሚገባትን ከፍተኛ ቦታ እንድንሰጣት ይረዳናል። ሕይወትን በአዲስ መንገድ እንድንመለከትና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምን እንደሆኑ ያስገነዝበናል። እንግዲያው ቀጥሎ የኢየሱስ የተራራ ስብከት ክፍል የሆነውን “የጌታ ጸሎት” ተብሎ የሚታወቀውን ጸሎት እንመርምር። (ማቴዎስ 6:9–13) ይህንን ለናሙና የተሰጠንን ጸሎት መመርመራችን እውነተኛ ደስታ ለማግኘት አምላክ ከእኛ ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ትክክለኛ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። ከዚህም ሌላ አስደናቂው የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት በኢየሱስ ክርስቶስ በምትመራው መንግሥቱ አማካኝነት የአምላክ ስም መቀደስ መሆኑን ያሳየናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ታስፈልጋለችን?

“አንድ ሜጋቶን የሚመዝን ኑክሌር መሣሪያ በኒውዮርክ ከተማ ላይ ቢፈነዳ 2.25 ሚልዮን ሕዝብ ወዲያውኑ ይሞታል፤ ተጨማሪ 3.6 ሚልዮን ሕዝብ ክፉኛ ይቆስላል፤ . . . በማለት አንድ የሕክምና ባለሙያዎችና የኑክሌር ፊዚስቶች ቡድን በትናንቱ ዕለት ተስማምቶበታል። . . . ይህ መቶ ዘመን ከመዘጋቱ በፊት ዓለም እንደዚህ ያለ ጦርነት እንደሚያጋጥማትና ይህም የሰውን ልጅ ሕልውና የማይቻል ነገር እንደሚያደርገው እምነት አላቸው።” — ኒው ዮርክ “ታይምስ”፣ መስከረም 27, 1980

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአምላክ መንግሥት በተጨባጭ አለች ለማለት የሚያበቁ ነገሮች

ንጉሥ:- ኢየሱስ ሲሆን ለ1 000 ዓመት የመግዛት ሥልጣን አለው።

ሰማያዊ ተባባሪ ገዥዎች:- ከታማኝ የሰው ዘሮች መሀል አምላክ የመረጣቸው ሰዎች

የግዛትዋ ክልል:- እንደገና ዓለም አቀፍ ገነት የምትሆነው ምድራችን

ታማኝ ዜጎቿ:- ትንሣኤ የሚያገኙትን ሙታን ጨምሮ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች

ሕግጋት:- በአምላክ ጽድቅ ላይ የተመሠረተ ንጉሣዊ የፍቅር ሕግ

የትምህርት መርሐ ግብር:- ከሁሉም ዘሮች የተውጣጡትን ሰዎች አሁን ደስታ ያለው ሕይወት እንዲያገኙ የረዳና ገነት በምትሆነዋ ምድር ለሚኖረው የዘላለም ሕይወት የሚያዘጋጃቸው ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]