በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማጭበርበሪያ የሆነች መንግሥት ተነሣች

ማጭበርበሪያ የሆነች መንግሥት ተነሣች

ምዕራፍ 10

ማጭበርበሪያ የሆነች መንግሥት ተነሣች

1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ምሥራቹ” ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር?

ታዳጊው የክርስቲያን ጉባኤ አረመኔነት የተሞላበት ስደት እየደረሰበት ማደጉንና መስፋፋቱን ቀጠለ። በመሲሑ ስለምትመራው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸው የምሥራቹ እውነት ‘ፍሬ ማፍራቱንና በመላው ዓለም እየጨመረ መሄዱን ቀጠለ።’ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ወደ አዳዲስ የግዛት ክልሎች ዘልቀው በመሄድ ሥራውን ሲያስፋፉ ተቃዋሚዎች “ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል” በማለት ኡኡታ አሰሙ። — ቆላስይስ 1:5, 6፤ ሥራ 17:6

2. ዲያብሎስ የእውነትን መስፋፋት ለማቆም ምን ጥረቶች አድርጎ ነበር? ያልተሳካለትስ ለምንድን ነው?

2 ይሁን እንጂ አቅማቸው ውስን የሆኑት ሰዎች የእውነትን መስፋፋት ለማገድ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት እዘአ የሮም ግዛት ቄሣሮች በጥንት ክርስቲያኖች ላይ 10 የተለያዩ የስደት ማዕበሎችን አስነሥተው ነበር፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ከንቱ ነበር። ከእነዚህ ‘በእምነት ጠንካሮች’ የሆኑ የክርስቶስን ፈለግ የተከተሉ ክርስቲያኖች መካከል ‘የሚያገሳው አንበሳ’ ዲያብሎስ ብዙዎቹን ቃል በቃል ለአንበሶች እንዲሰጡ ወይም እስኪሞቱ ድረስ እንዲሠቃዩ ቢያደርግም ፍጹም አቋማቸውን ለማበላሸት እምቢ ብለዋል። — 1 ጴጥሮስ 5:8, 9፤ ከ1 ቆሮንቶስ 15:32፤ ከ2 ጢሞቴዎስ 4:17 ጋር አወዳድር።

3. ‘የአምላክን ሙሉ የጦር ዕቃ’ መያዝ ያለብህ ለምንድን ነው?

3 በስደት አማካኝነት ፊት ለፊት ማጥቃቱ ብዙ ጊዜ ስላልሠራለት ዲያብሎስ የኢየሱስን ተከታዮች በረቀቀ መንገድ ለማጥመድ ዘዴ ቀየሰ። ክርስቲያኖቹ ኩራተኛ በሆነ፣ በሥነ ምግባር የተበላሸ አቋም ባለው፣ በተድላ ፍላጎት ባበደ ዓለም የተከበቡ ነበሩ፤ ሰይጣንም እነርሱን ከአምላክ አገልግሎት ዘወር ለማድረግ በዚህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ሞከረ። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 6:11–18 ላይ እነርሱ ሊጠቀሙበት የሚገባውን መንፈሳዊ ‘የአምላክ የጦር ዕቃ’ በዝርዝር ሲገልጽ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ እንደተናገረው ‘ጸንተው መቆም’ ያስፈልጋቸው ነበር። አንተ ራስህስ ይህንን ‘የተሟላ የአምላክ የጦር ዕቃ’ ታጥቀሃልን? በእነዚህ ‘መጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች ለመቋቋም መታጠቅ ይኖርብሃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ይህ አስፈልጓቸው ነበር። ለምን በተለይ እነርሱ ያስፈልጋቸው ነበር እንላለን?

4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ስለ መንግሥቱ ምን መሠረታዊ እውነቶችን ተረድተው ነበር?

4 የያዙት እምነት ንጹሕና ያልተወሳሰበ እምነት ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት ክርስቲያኖች በሙሉ “ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት” ለመግባት የሚጠባበቁ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ነበሩ። (2 ጴጥሮስ 1:11፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50) ሽማግሌው ሐዋርያው ዮሐንስ ከአምላክ የመጣ ራእይ ከተገለጠለት በኋላ ይኸውም ግፋ ቢል ከ96 እዘአ ጀምሮ የ“ታናሹ መንጋ” ቁጥር 144, 000 እንደሚሆን አውቀው ነበር። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ‘ነገሥታትና ካህናት’ በመሆን ምድርን ለ1, 000 ዓመት ይገዛሉ። መንፈሳዊ እስራኤል የሆኑት 144, 000ዎቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ብቅ እንደሚሉ ለዮሐንስ ተገልጾለታል። እነዚህ ሰዎች በቡድን ደረጃ የመጨረሻውን “ታላቅ መከራ” በሕይወት አልፈው በዚሁ ምድር ላይ በመንግሥታዊ አገዛዙ ሥር ለሺህ ዓመት የሚፈሱትን በረከቶች ለሚያገኘው ሰብአዊ ኅብረተሰብ እምብርት ይሆናሉ። — ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 7:4, 9–17፤ 20:1–6፤ 21:1–5

ታላቁ ክህደት

5, 6. (ሀ) በዚያን ጊዜም ቢሆን ዲያብሎስ ረቂቅ በሆነ የማጥቂያ ዘዴ ይጠቀም እንደነበረ የትኞቹ ጥቅሶች ያሳያሉ? (ለ) በአንድ ቃል ለመናገር ይህ ዘዴ ምን ነበር?

5 ታዲያ ረቂቅ የሆነው የዲያብሎስ ማጥቂያ ምን ነበር? ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ ኋላ መለስ ብሎ እምነት የለሽ የነበረችውን እስራኤልን በመጥቀስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ ነበር:- “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም . . . የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ . . . በመመኘት በተፈጠረ ነገር (እያጭበረበሩ) ይረቡባችኋል።” (2 ጴጥሮስ 2:1, 3) እነዚህ የሐሰት ኑፋቄ አስተማሪዎች ማጭበርበሪያ የሆኑ ሃይማኖታዊ ትምህርቶቻቸውን ይዘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ብቅ አሉ። በ96 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ዮሐንስ “የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ . . . ከእኛ ዘንድ ወጡ፣ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም” ብሎ ነበር። — 1ዮሐንስ 2:18, 19

6 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ምናልባት ሁለተኛ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ በሚታመነው ደብዳቤ ላይ ገና በ51 እዘአ ላይ “የይሖዋን ቀን” በተመለከተ ይነገሩ ስለነበሩ የሐሰት ትምህርቶች አስጠንቅቆ ነበር። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፣ አይደርስምና።” ይህ “የዓመፅ ሰው” ማን ሊሆን ይችላል? ክርስቲያን ነን ብለው እየተናገሩ ‘አምላክን የማያውቁትን’ እና ‘ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን የምሥራች የማይታዘዙትን’ ዓመፀኛና ከሃዲ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎችን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። (2 ተሰሎንቄ 1:6–8፤ 2:1–3) እንደዚህ ያለው የከሃዲዎች ቡድን ከክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዴት ሊነሣ ቻለ?

7. አንዳንዶቹ የኢየሱስ ተከታዮች በወጥመድ የተያዙት እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?

7 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ገና በሕይወት ሳሉ የሐሰት ትምህርት ወደ ጉባኤው ሰርጎ እንዳይገባ አግደው ይዘውት ነበር። ይሁን እንጂ ‘ይህ የዓመፅ ምሥጢር’ ቀደም ብሎ ‘እንደ ሰይጣን አሠራር’ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር፤ በሁለተኛው መቶ ዘመን ላይ ግን ገሃድ ወጣ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ‘ሁላችሁ ወንድማማቾች ናችሁ’ ብሏቸው ነበር፤ ነገር ግን አንዳንዶች ዋና የመሆን ምኞት አደረባቸውና በዲያብሎስ ወጥመድ ተያዙ። እነዚህ ሰዎች ቄሶችና ተራ ምእመናን በማለት ክርስቲያኖችን መከፋፈል ጀመሩ። እያደር በሐዋርያው ጳውሎስ የተተነበየው ቀጥሎ የተገለጸው ሁኔታ ተከሰተ:- “ሕይወት የሚገኝበትን (ጤናማ) ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ፣ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።” — 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4፤ 2 ተሰሎንቄ 2:6–10፤ ማቴዎስ 23:8

8. (ሀ) ሁለቱ የሐሰት ትምህርት ዋነኛ ምንጮች ምን ነበሩ? (ለ) ኢንሳይክሎፔዲያዎች የክርስትናን መበላሸት የሚገልጹት እንዴት ነው?

8 ታዲያ ጆሮአቸውን ወዴት መለሱ? የሐሰት ሃይማኖት መፍለቂያ ከሆነችው ከጥንቷ ባቢሎን ወደተገኙት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና በጊዜው በሮማው ዓለም ውስጥ በሕዝቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝተው ወደነበሩት የግሪካውያን ፍልስፍናዎች ነበር። ማክሊንቶክ ኤንድ ስትሮንግ ሳይክሎፔድያ እንደገለጸው:- “ቀላል የነበረው የወንጌል መልእክት ተበረዘ፤ የተንዛዙ ሥርዓተ ቅዳሴዎችና ወጎች መጡ፤ ለክርስትና አስተማሪዎች ዓለማዊ ክብርና ደሞዝ ይሰጣቸው ጀመር፤ የክርስቶስ መንግሥት በአመዛኙ መልኩ ተለውጦ የዓለም መንግሥት እንዲመስል ተደረገ።” በዚህም ላይ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ የሚከተለውን ሐሳብ ይጨምራል:- “ወደ ክርስትና አረመኔያዊ የሆኑ ወይም በዚያ ላይ የተመሠረቱ አጉል እምነቶች መጡ። እነዚህ ነገሮች ከመግባታቸው የበለጠ ክርስትናን የበከለ ነገር የለም። ክርስትናን መቋቋም የተሳነው የአረመኔነት እምነት ክርስትናን ለመበረዝ ችሏል፤ አልፎ ተርፎም ጥራቱን አጥፍቷል።”

9. (ሀ) የሰው ነፍስ አትሞትም ከሚለው ትምህርት ምን የተለመዱ እምነቶች በቀሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ያሉትን ትምህርቶች ውድቅ የሚያደርጋቸው እንዴት ነው?

9 ከእነዚህ አጉል እምነቶችና አረመኔያዊ ልማዶች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው የግሪኩ ፈላስፋ የፕላቶ ትምህርት ከዋና ዋናዎቹ አንዱ ነው። እንደዚህ ያለው እምነት ከሞት በኋላ ነፍስ ወደ አንድ ቦታ ይኸውም ወደ ሰማያዊ ደስታ፣ አለዚያም ለመንጻት ወደ መንጽሔ ወይም ደግሞ ለዘላለም እንድትሠቃይ ወደ ሲኦል ቃጠሎ መሄድ አለባት የሚል ነው። ይህን ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እንደ መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10፤ ማቴዎስ 10:28 እና ሮሜ 6:23 ያሉት ጥቅሶች ውድቅ ያደርጉታል።

የካቶሊክ እምነት አመሠራረት

10, 11. (ሀ) ካርዲናል ኒውማን ቤተ ክርስቲያናቸው ስለምታስተምራቸው ብዙ ትምህርቶች ምን ብለው አምነዋል? (ለ) የቤተ ክርስቲያን ልማዶችና ትምህርቶች “ከአረመኔዎች የመጡ” ናቸው ብለው ከተናገሩ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ እንደ ቅዱስ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉን?

10 የ19ኛው መቶ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ካርዲናል የነበሩት ጆን ሄንሪ ኒውማን ኢሴይስ ኤንድ ስኬችስ (ድርሰቶችና አስተዋጽኦዎች ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ቤተ ክርስቲያናቸው የምታስተምራቸው ትምህርቶች ከየት እንደመጡ ጠቁመዋል:- “በሁሉም አቅጣጫ ፈጦ የሚታየው ሐቅ ይህ ነው:- የክርስትና እምነት የሚያስተምረው እውነት እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው አብዛኛው ትምህርት በአጠቃላይ መልኩ ወይም በተለያዩ ክፍሎቹ በአረመኔዎች ፍልስፍናዎችና ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኝ ነው። ለምሳሌ የሥላሴ እምነት በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ይገኛል፤ ጠበልም ሆነ ጽዋ መጠጣት እንደዚሁ ነው። ቃል መለኮት ነው የሚለው ሃይማኖታዊ ትምህርት ከፕላቶ የመጣ ነው፤ ሰው ከሞተ በኋላ ሌላ ዓይነት እንስሳ ወይም ሰው ሆኖ ይመጣል የሚለው የኢንካርኔሽን እምነት የመነጨው ከህንድ ነው።” ከዚያም “እነዚህ ነገሮች በአረመኔዎች እምነት ውስጥ ያሉ ነገሮች ናቸው፤ ስለዚህ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች አይደሉም” ብሎ ለተከራከራቸው ተቺ ካርዲናሉ መልስ ሲሰጡ እንዲህ አሉ:- “በተቃራኒው ግን እኛ ‘እነዚህ ነገሮች በክርስትና ውስጥ የሚገኙ ናቸው፣ ስለዚህ የአረመኔዎች ትምህርቶች አይደሉም’ እንላለን።” ሆኖም የሮማ ካቶሊክ እምነት ከመምጣቱ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ባቢሎናውያንና ግሪካውያን ያስተምሯቸው የነበሩ ነገሮች ናቸው። ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም።

11 ታላቁ ክህደት ትምህርቶቹንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቹን ያገኘው ከአረመኔያዊ ሃይማኖት መሆኑን ካርዲናል ኒውማን ዘ ዲቨሎፕመንት ኦቭ ክርስቲያን ዶክትሪን (የክርስትና መሠረተ ትምህርት አመጣጥ ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በሰጡት አስተያየት በይበልጥ ተረጋግጧል። በዚህ መጽሐፍ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል:- “ቆስጠንጢኖስ አዲሱን [የሮማ ካቶሊክን] ሃይማኖት በአረመኔዎቹ ዘንድ ለማስወደድ ሲል እነርሱ የለመዱትን ዓይነት ውጫዊ መልክ ቀባው።” ካርዲናሉ ቤተ ክርስቲያናቸው ከምትከተላቸው ልማዶች ብዙዎቹን ከዘረዘሩ በኋላ እነዚህ “ሁሉ ከአረመኔዎች የመጡና በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት በማግኘታቸው የተቀደሱ ናቸው” በማለት የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ የሐሰት ትምህርት ‘ሊቀደስ’ ወይም ቅዱስ ሊደረግ ይችላልን?

12, 13. (ሀ) ቆስጠንጢኖስ የሮማ ካቶሊክን ሃይማኖት ለማቋቋም የተነሣሣው በምን ሁኔታዎችና በምን ዓላማ ነው? (ለ) ቆስጠንጢኖስ ከልቡ ክርስቲያን መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

12 ካርዲናሉ እዚህ ላይ የጠቀሱት በአራተኛው መቶ ዘመን የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረውን ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ነው። ቆስጠንጢኖስ ወደ ሃይማኖት ዘወር ያለው ምን ፍለጋ ነበር? ሮምን በ312 እዘአ ከወረረ በኋላ ድል ለማድረግ በተቃረበበት ዋዜማ “በዚህ ድል ታደርጋለህ” ከሚል ቃል ጋር አንድ የሚነድ መስቀል በራእይ እንደተመለከተ ቆስጠንጢኖስ አስታውቆ ነበር። ይህንንም ምልክት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ቀረጸው። የፖለቲካ ግቦቹን ለማሳካት የሚረዳ ድጋፍ ለማግኘት ለሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት መሠረት የሆኑትን እምነቶች ተቀበለ፤ ከልቡ ያልራቁትን አረመኔያዊ እምነቶች ‘በክርስቲያን’ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ አደረገ።

13 ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ስለ ቆስጠንጢኖስ እንዲህ ይላል:- “እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ብዙ አረመኔያዊ እምነቶችን ይዞ የቆየው ይህ ሰው የአረመኔዎችን እምነት አሁንም ገና አልተወም ነበር ማለት ነው።. . . ቆስጠንጢኖስ ምን ዓይነት ሰው መሆኑ ታይቶ ሳይሆን ባደረጋቸው ነገሮች ታላቅ ተብሎ ሊጠራ ችሏል። ጠባዩ ሲመረመር በጥንትም ሆነ በዛሬው ዘመን [“ታላቅ”] የሚለው ስያሜ ከተሰጣቸው ሰዎች ሁሉ ዝቅተኛ ከሆኑት የሚመደብ ነው።” ለዚህም ምሥክር የሚሆነው አብዛኞቹን የቤተሰቡን አባሎች መግደሉ ነው። “ፖንቲፌክስ ማክሲመስ” የተባለው አረመኔያዊ የማዕረግ ስሙ ከጊዜ በኋላ ወደ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ተላልፎአል።

14. የሮም ጳጳሳት በእርግጥ የአምላክን መንግሥት ይወክሉ ነበርን? እንደዚህ ብለህ ለምን መለስክ?

14 በጨለማውና በመካከለኛው ዘመን ውስጥ የሮም ጳጳሳት በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዙ ነበር። ክርስቶስ በሰማይ የሺህ ዓመት ግዛቱን እስከሚያቋቁም ድረስ አልጠበቁም። ለራሳቸው የግል ጥቅም ሲሉ በዚያኑ ጊዜ “መንግሥት” አቋቁመው ለመግዛት ፈለጉ። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ይህንን ሁኔታ በሚከተሉት ቃላት ገልጾታል:- “የክርስትና እምነት እንዲበላሽ ካደረጉት ቀደምት ምክንያቶች አንዱ ስለ “አምላክ መንግሥት” የሚናገረውን የክርስትና ትምህርት ለመተግበር በዓይን የሚታይ ንጉሣዊ አገዛዝ ተቋቁሞ ቅዱሳን ምድርን ቃል በቃል እንዲወርሱ መደረጉ ነው።” ቅን የሆኑ ሰዎች እንደዚህ ያለውን ‘የክርስትና መበላሸት’ በመቃወም መታገላቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሃዲ የምትላቸውን እየለቀመች በግንድ ላይ ታስረው እንዲቃጠሉ በማድረግ የወሰደችው የጭካኔ እርምጃ ብቻ ከ30, 000 በላይ ሰዎችን አጥፍቷል። ይህም ተቃዋሚዎችን ለመግታት ለረጅም ዘመን አገልግሏል። ይሁን እንጂ አፈናው ለሁልጊዜው የሚቀጥል አልነበረም!

ስለ ፕሮቴስታንት እንቅስቃሴስ ምን ለማለት ይቻላል?

15. (ሀ) የፕሮቴስታንት የተሐድሶ እንቅስቃሴ በመጨረሻው ምን ሆነ? (ለ) የፕሮቴስታንት እምነት እስከ ዘመናችን ድረስ በባርነት ሥር ነው ሊባል የሚቻለው በምን መንገድ ነው?

15 ጥቅምት 31, 1517 እኩለ ቀን ላይ ማርቲን ሉተር የተባለ የሮማ ካቶሊክ ቄስ ዊትንበርግ በምትባል የጀርመን ከተማ ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስቲያን በር ላይ 95 የተቃውሞ ነጥቦችን ጽፎ ለጠፈ። የፕሮቴስታንት የተሐድሶ ንቅናቄ ጀመረ። ይሁን እንጂ የተሐድሶው ንቅናቄ እውነተኛውን የክርስትና እምነትና ለአምላክ የሚቀርበውን ንጹሕ አምልኮ መልሶ በማምጣት ፋንታ በአብዛኛው ፖለቲካዊ ዓላማን የሚያራምድ ሆነ። በሃይማኖት እየተሳበበ በተካሄዱ ጦርነቶች አማካኝነት ግዛት ለማስፋፋት ብዙ ትግል ይደረግ ነበር። ለምሳሌ ከ1618–1648 በአውሮፓ 30 ዓመት የፈጀ ጦርነት ተደርጎ የሚልዮኖችን ሕይወት ቀጥፏል። ሌሎች ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ጦርነቶችም ተደርገዋል። ብዙ አገሮች የየራሳቸውን የመንግሥት ሃይማኖት አቋቋሙ። እነዚህም ሃይማኖቶች ‘ነፍስ አትሞትም’፣ መሠቃያ ሲኦል፣ ሥላሴ፣ ሕፃናትን ማጥመቅንና የመሳሰሉትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸውን ሌሎች ቁልፍ የሆኑ መሠረተ ትምህርቶች ማስተማራቸውን ቀጠሉ። እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ታላቁ ክህደት ካመጣቸው ከእነዚህ ትምህርቶች አልተላቀቁም።

“ታላቂቱ ባቢሎን”

16, 17. (ሀ) ኤርምያስ 51:6 ዛሬ ለምንኖረው ምን ትርጉም አለው? (ለ) የባቢሎን ሃይማኖት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

16 የሐሰት ሃይማኖት ያላቸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:-

“ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፣ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ።” (ኤርምያስ 51:6)

ይህ ዛሬ ለምንኖረውም ትርጉም ያለው ነው። በኤርምያስ ዘመን ሳይቀር ባቢሎን ወራዳ ምግባር በሚፈጸምባቸው የሃይማኖት ሥርዓቶቿና በአማልክቶችዋ ብዛት የታወቀች ነበረች። ዘመናዊቷ ባቢሎን ግን ዓለም አቀፍ ይዘት ያላት ናት። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

17 በኖኅ ዘመን ያ የጥፋት ውሃ ከደረሰ በኋላ አያሌ ዘመናት ቆይቶ ናምሩድ የተባለ ክፉና ‘ይሖዋን በመቃወም ኃያል የሆነው አዳኝ’ የከተማ መንግሥት አቋቋመ። ምናልባትም ሰማይ ጠቀስ የሆነ ሃይማኖታዊ ግንብ የሠራው እርሱ ነው። ይሖዋም የሰውን ዘር ቋንቋ በማዘበራረቅና ሰዎቹንም ‘በሁሉም የምድር ገጽ ላይ’ በመበተን እቅዳቸውን አከሸፈው። ሆኖም የሐሰት ሃይማኖታቸውን ይዘው ሄዱ። በአሁኑ ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ የዓለም ሃይማኖቶች የበቀሉበት ሥር ይህ ነው። — ዘፍጥረት 10:8–10፤ 11:1–9

18. ከየትኛው የማጭበርበሪያ መንግሥት መሸሽ ይኖርብናል? ወዴትስ?

18 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ቆስጠንጢኖስ የሮማን ካቶሊክ ሃይማኖት መሠረት ሲጥል እንደዚህ ያለውን የሐሰት ሃይማኖት ወደ ክርስትና ትምህርቶች አስርጎ አስገብቷል። ለአብዛኛው የፕሮቴስታንት እምነት መሠረተ ትምህርት መነሻ የሆነው ይህ ነው። “ክርስቲያን” ያልሆኑ በምድር ላይ ያሉ ሃይማኖቶችም ቢሆኑ የበቀሉት ከባቢሎን ነው። ክርስቲያን የሚባሉትም ሆኑ “ክርስቲያን” ያልሆኑት ሃይማኖቶች በአንድነት የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ታላቂቱ ባቢሎን . . . በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ (ሃይማኖታዊት መንግሥት የሆነች) ታላቂቱ ከተማ ናት” በማለት የጠቀሳት ማጭበርበሪያ መንግሥት ይህች ነች። (ራእይ 17:5, 18) ስለዚህ ‘እያንዳንዱ ሰው ነፍሱን ለማዳን’ ከፈለገ ከአጭበርባሪዋ ባቢሎናዊት “መንግሥት” በመውጣት ወደ አምላክ መንግሥት እንዲሸሽ ተመክሯል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 95 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሰይጣን በሚከተሉት መንገዶች በአምላክ አገልጋዮች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል:-

● ፊት ለፊት በሚሰነዘር ጥቃት፤ ይኸውም በተሳሳተ ወሬ ጥላቻ ያደረባቸው ዘመዶች፣ መንግሥታትና ሃይማኖተኞች በሚያመጡት ስደት

● በዛሬው ልቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ወደ ጾታ ብልግና እንዲሳቡ በማድረግ

● በሥልጣን፣ በሀብት፣ በዘር፣ የብሔር ኩራትን በማነሳሳት

● በመዝናኛዎች እንዲዋጡ በማድረግ ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ እንዲሆኑ በመሞከር

● አምላክ የለም የሚሉትንና የዝግመተ ለውጥ ትምህርቶችን በማስፋፋት

● ከሀዲዋ ሕዝበ ክርስትና ያቋቋመችው ማጭበርበሪያ መንግሥት እውነተኛውን ክርስትና እንዲወክል በማድረግ

● በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ጥርጣሬን ለመዝራት፣ ብሎም በረቀቀ ዘዴ ለማዳከም የሐሰት አስተማሪዎችን በማስነሣት

በእምነታችን የሰይጣንን ዓለም ልናሸንፈው እንችላለን