በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው!

ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው!

ምዕራፍ 14

ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው!

1, 2. (ሀ) 1914 ሰዎች ከሚያስቡት ይበልጥ ምን የላቀ ትርጉም ያለው ዓመት ነው? (ለ) የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ 1914⁠ን ለይቶ ያመለከተው እንዴት ነበር?

ያለ አንዳች ጥርጥር 1914 በብሔራትና በሰው ዘር ጉዳዮች ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ይሁን እንጂ ይህ ዓመት ብዙዎቹ የታሪክ ጸሐፊዎች ከሚገምቱት የበለጠ ትርጉም ያለው ነው። ከመንግሥቲቱ ‘መምጣት’ ጋር የተዛመዱ አስደሳች ሁኔታዎች የተፈጸሙበት ዓመት ነው። ጠንቃቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብዙ ዓመታት ቀደም ብለው ያንን ዓመት በከፍተኛ ጉጉት ይጠብቁት ነበር። ምንን መሠረት በማድረግ?

2 1914 ከመድረሱ ከሠላሳ አራት ዓመታት በፊት የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለው መጽሔት ታኅሣሥ 1879 እና መጋቢት 1880 ባወጣው እትሙ ላይ 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ለየት ያለ ዓመት እንደሚሆን አመልክቶ ነበር። በሰኔ 1880 እትም ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “የአሕዛብ ዘመን” (ሉቃስ 21:24) የሚያበቃበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን አመልክቶ ነበር። ምንም እንኳን ይህን የጻፈው ሰው በጊዜው ሁኔታዎቹ እንዴት እንደሚፈጸሙ በተሟላ መልኩ ባይረዳም በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር በመጠቀም የጥንትዋ ኢየሩሳሌም መጀመሪያ ከጠፋችበት ጊዜ የሚጀምሩት “ሰባት ዘመናት” ወይም 2,520 ዓመታት ‘በ1914 ዓ.ም.’ እንደሚያበቁ ጠቁሟል። ጸሐፊው እንዲህ ብሎ ነበር:- “2,520 ዓመታት ርዝመት ያለው ረጅም ጊዜ . . . በአራዊት (በሰብአዊ መንግሥታት) ግዛት ሥር በቆዩት በአምላክ ሕዝቦች ላይ የደረሰው መራራ ታሪክ በዳንኤል 4 ላይ በሚገኘው ናቡከደነፆር ‘ለሰባት ዘመናት’ በአራዊት መካከል በደረሰበት መራራ ሁኔታ በግልጽ ታይቷል።” እንግዲያው እነዚህ “ሰባት ዘመናት” ምንድን ናቸው?

አንድ ሕልም ተፈታ

3. በዳንኤል 4:25 ላይ ምን መሠረታዊ የሆነ እውነት ተገልጿል?

3 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 4 አስደናቂ ስለሆነ አንድ ትንቢታዊ ሕልም ይገልጻል። ሕልሙ ‘ልዑሉ በሰው ዘር መንግሥት ላይ ገዥ እንደሆነና ለሚወደውም እንደሚሰጠው’ በምሳሌ ያስረዳል። (ዳንኤል 4:25) ሕልሙን ያየው የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሲሆን እንዲተረጉምለት ለዳንኤል ነገረው።

4-6. (ሀ) ናቡከደነፆር ምን ሕልም አየ? (ለ) ዳንኤልስ ሕልሙን እንዴት ብሎ ፈታው? (ሐ) የተፈጸመውስ እንዴት ነው? (መ) ናቡከደነፆር እንደገና ወደ ሥልጣኑ ሲመለስ የትኛውን ሐቅ መቀበሉን በይፋ አሳወቀ?

4 ናቡከደነፆር እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሊታይ የሚችል እጅግ ግዙፍ የሆነ ዛፍ በራእይ ተመለከተ። ይህም ዛፍ ለሁሉም ፍጥረት ምግብን የሚሰጥና መጠለያ የሚሆን ነበር። ይሁን እንጂ ከሰማይ “ቅዱሱ” ዛፉ እንዲቆረጥና ጉቶው በብረትና በናስ ማሰሪያ እንዲታሰር አዘዘ። ብረትና ናስ በጊዜው በጥንካሬያቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው ማዕድናት ነበሩ። ዛፉ በዚህ ሁኔታ እንደታሠረ “ሰባት ዘመናት” ማለፍ ነበረባቸው።

5 ዳንኤል ይህን ትንቢታዊ ሕልም ሲተረጉም ትልቁ ዛፍ ናቡከደነፆርን እንደሚያመለክት ገለጸ። እርሱ ‘ሊቆረጥ’ ወይም ዝቅ ሊደረግ ነው። ናቡከደነፆር እንደ ሜዳ አራዊት በመሆን “ሰባት ዘመናት” ያሳልፋል። ቢሆንም ልክ “ዛፉ” ድምጥማጡ እንዲጠፋ እንዳልተደረገ ሁሉ “ሰባቱ ዘመናት” ካለቁ በኋላ ንጉሡ ወደ ቀድሞ ሥልጣኑ ይመለሳል። — ዳንኤል 4:19–27

6 በናቡከደነፆር ላይ ይህ በትክክል ደርሷል። እርሱ በፊት ከነበረው ቦታ ዝቅ ተደርጎ ሰው ከሚኖርበት አካባቢ በመውጣት እንደ እንስሳ ሣር በላ። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው እነዚያ “ሰባት ዘመናት” ናቡከደነፆር ‘በአራዊት መካከል እየኖረ የተሠቃየባቸው’ ሰባት ዓመታት ናቸው። የራሱ ጠጉር እንደ ንስር ላባ፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፎች ጥፍር ረዘሙ። በመጨረሻው ግን አእምሮው እንደገና ጤናማ ሆነና ወደ ንግሥናው ተመለሰ። ይህም ሲፈጸም “መንግሥቱ ለልጅ ልጅ” የሆነውንና የመግዛት መብት ያለውን “የሰማይ ንጉሥ” አመሰገነ፤ አከበረም። — ዳንኤል 4:28–37

7–9. (ሀ) ኢየሱስ ስለ አሕዛብ ዘመናት ፍጻሜ የጠቀሰው በየትኛው ትንቢት ላይ ነው? (ለ) ስለዚህ የትኞቹ ጥያቄዎች ሊያመራምሩን ይገባል?

7 ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከ1914 እዘአ ጋር ምን ግንኙነት አለው?

“የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት”

8 ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የነገሮች ሥርዓትን የመደምደሚያ ዘመን ምልክት’ በገለጸበት ጊዜ ቀጥሎ ያለውን ተናገረ:-

“የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።” (ሉቃስ 21:24 አዓት)

እዚህ ላይ ኢየሱስ የጠቀሳቸው “አሕዛብ” አይሁዳዊ ያልሆኑ ያልተገረዙ አሕዛብ ናቸው። በብዙዎች ዘንድ የታወቀው የኪንግ ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እዚህ ላይ “ያልተገረዙት አሕዛብ ዘመናት” ይላል። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ‘የአሕዛብ ዘመናት ምንድን ናቸው? ኢየሱስ በአእምሮው ይዞት የነበረው የትኛውን ጊዜ ነው? መቼ ጀመረ? የሚያበቃውስ መቼ ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ።

9 ኢየሱስ ስለ “ምልክቱ” የሰጠው የኢየሱስ ታላቅ ትንቢት ዛሬ ለእኛ ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው ቀደም ሲል ተመልክተናል። እንግዲያው ለእነዚህ ጥያቄዎች ጭምር መልስ ማግኘት ያስፈልገናል።

“ኢየሩሳሌም” ሲባል ምን ማለት ነው?

10-12. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ በተናገሩት መሠረት ከ29–70 እዘአ ድረስ የተፈጸሙት ታሪኮች ለምን ነገር ምሳሌ ይሆናሉ? (ለ) ይሁን እንጂ በሉቃስ 21:24 ላይ “ኢየሩሳሌም” ምን ከፍተኛ ትርጉም ሊኖራት ይችላል? (ሐ) አንድ ታዋቂ ሳይክሎፔድያ ይህንን አመለካከት የሚደግፍልን እንዴት ነው? (መ) ታዲያ “ኢየሩሳሌም” ለምን ነገር የቆመች ናት?

10 ፕሮፌሰር ኤ ቲ ሮበርትሰን * ኢየሱስ በተናገረው ትንቢት ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “በ70 እዘአ በዚያን ጊዜ በነበረው ትውልድ ላይ የደረሰው የቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም መፍረስ በዓለም መጨረሻ ወይም ዘመኑ በሚያልቅበት ጊዜ ዳግመኛ ለመምጣቱ ምሳሌ አድርጎ ኢየሱስ ተጠቅሞበታል” ብለዋል። ስለዚህ “በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት በተጨማሪ ኢየሱስ በሉቃስ 21:24 ላይ ከጠቀሳት “ኢየሩሳሌም” ጋር ያያያዘው ምን ከፍተኛ ወይም ረዘም ያለ ትርጉም ያለውን ነገር ነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

11 ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ከዳዊት ንጉሣዊ መሥመር በይሖዋ የተሾሙ ነገሥታት እርሱን በመወከል “በይሖዋ ዙፋን ላይ” የሚቀመጡባት የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጎ ይመለከታት ነበር። በተጨማሪም የከተማዋ ቤተ መቅደስ ለምድር በሙሉ የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል ነበር። (1 ዜና. 28:5፤ 29:23፤ 2 ዜና. 9:8) በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “ኢየሩሳሌም የመላው የእስራኤል ሕዝብ ንጉሠ ነገሥት መኖሪያ ተደርጋ ነበር። ብዙውን ጊዜ ‘የይሖዋ ቤት’ እየተባለ ይጠራ የነበረው ቤተ መቅደስም የቲኦክራሲያዊው መንግሥት ርዕሰ ብሔር የሆነው የነገሥታት ንጉሥ መኖሪያ ነበረች። . . . ኢየሩሳሌም ከፖለቲካ አንፃር ትልቅ ቦታ አልነበራትም። የሌሎች አገሮችን ጉዳዮች የምትመራ የአንድ ኃያል ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ዋና ከተማ አልነበረችም። ከዚህ ይልቅ ዳዊት ስለ መሲሑ መምጣት [መዝሙር 2:6፤ 110:2] ያለውን እምነት በሚገልጽበት ጊዜ በተነበያቸው ብሩህ ተስፋዎች ከፍተኛ ቦታ ነበራት። — ጥራዝ 4፣ ገጽ 838

12 በዳዊት የትውልድ መሥመር የተነሡት ነገሥታት “በይሖዋ የንግሥና ዙፋን ላይ” መቀመጣቸው መንግሥቱ የአምላክ መንግሥት የመሆኑን ሐቅ አጠንክሮ ያስገነዝባል። ኢየሩሳሌምን ማዕከሉ ያደረገው የእስራኤል መንግሥት ምሳሌያዊ የአምላክ መንግሥት ነበር። ስለዚህ “ኢየሩሳሌም” የአምላክን መንግሥት የምትወክል ነበረች።

13, 14. በሉቃስ 21:24 ላይ የተገለጸው ‘መረገጥ’ የጀመረው መቼና እንዴት ነው?

13 “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አስታውስ። (ሉቃስ 21:24) ይህ ‘መረገጥ’ የተጀመረው መቼ ነበር? ኢየሱስ በቤተልሔም ከመወለዱ ከብዙ ጊዜ በፊት መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ከዳዊት ንጉሣዊ መሥመር የተነሡ ነገሥታት ከኢየሩሳሌም መግዛት ካቆሙ ረጅም ጊዜ ሆኗቸው ነበር። ንጉሥ ሴዴቅያስ በናቡከደነፆር በሚመራው የባቢሎን ወራሪ ሠራዊት ከዙፋኑ በወረደ ጊዜ የዳዊት የነገሥታት ሥርወ መንግሥት አቆመ።

14 ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በሕዝቡና በንጉሥ ሴዴቅያስ ክፋት ምክንያት ምን ነገር እንደደረሰ ይነግረናል። እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ . . . የከለዳውያንን (የባቢሎናውያንን) ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጎልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ . . . ሁሉንም [አምላክ ለናቡከደነፆር] በእጁ አሳልፎ ሰጠው። የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ፣ ታላቁንና ታናሹን፣ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፣ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፣ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።” (2 ዜና. 36:11, 12, 16–20) በዚህ ጊዜ ነበር ኢየሩሳሌምን ‘መርገጥ’ የተጀመረው።

‘ተረግጣ’ የምትቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

15-17. (ሀ) የዳዊትን መንግሥት ይዞ ለመቀጠል “ሕጋዊ መብት” ያጣው ማን ነው? እንዴትስ? (ለ) ይህንን መብት መልሶ የሚያገኘው ማን ይሆናል? ለምንስ ያህል ጊዜ? (ሐ) ስለዚህ ጉዳዩን የሚመለከት ምን ጥያቄ ይነሣል? (መ) ዳንኤል ይህን ጥያቄ ለመመለስ ትክክለኛው ሰው የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 ነቢዩ ሕዝቅኤል በዳዊት የንጉሣዊ መሥመር የመጨረሻው የሆነው ሴዴቅያስ ከዙፋኑ እንደሚወርድ እንደሚከተለው በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር:-

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- መጠምጠሚያውን አውልቅ፣ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ . . . ባድማ፣ ባድማ፣ ባድማ አደርጋታለሁ፤ [ሕጋዊ መብት አዓት] ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፣ ለእርሱም እሰጣታለሁ።” — ሕዝቅኤል 21:26, 27

16 ምንም እንኳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በዚያን ጊዜ በዳዊት መንግሥት ላይ ለመቆየት የነበረውን “ሕጋዊ መብት” ቢያጣም ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ያንን “መብት” እንደገና በማግኘት በአምላክ መንግሥት ላይ “ለዘላለም” ይገዛል። (ሉቃስ 1:32, 33) ይሁን እንጂ ዋና ከተማው ኢየሩሳሌም የነበረው ምድራዊ የእስራኤል መንግሥት ምሳሌ የሆነለት መሲሐዊ መንግሥት መግዛት እስኪጀምር ድረስ ምን ያህል መቆየት ነበረበት?

17 ይሖዋ አምላክ ጊዜውን ያውቅ ነበር። እርሱም ወደፊት የሚፈጸሙ ሌሎች ብዙ ነገሮችን አስቀድሞ እንደተናገረ ሁሉ በቃሉ ውስጥ ያንን የጊዜ ሰሌዳ ለማመልከት ይችላል። በሰማይና በምድር ወደፊት የሚከሰቱ ብዙ ሁኔታዎችን አምላክ በትክክል የገለጸበትን የዳንኤልን ትንቢት ኢየሱስ ስለ ‘ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን’ በሰጠው ንግግር ላይ ደጋግሞ ጠቅሶታል። (ማቴዎስ 24:3, 15, 21, 30⁠ን ከዳንኤል 9:27፤ 11:31፤ 12:1፤ 7:13 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ በዳንኤል 9:24–27 ላይ የሚገኘው “የሰባ ሳምንታት” ትንቢት ለመሲሑ የመጀመሪያ መምጣት ትክክለኛ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ሰጥቶ አልነበረምን? ታዲያ ይኸው ነቢይ መሲሑ ሁለተኛ የሚመጣበትን ጊዜ ቢያመለክት ተገቢ አይሆንምን? ይህንን እኛን በቀጥታ የሚነካንን ትንቢታዊ መልእክት የምናገኘው በዳንኤል መጽሐፍ አራተኛ ምዕራፍ ላይ ነው።

የትንቢቱ ዋነኛ ፍጻሜ

18. (ሀ) የዓለም የታሪክ መዝገቦች የናቡከደነፆርን ዕብደት ሳይጠቅሱ የቀሩት ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) እዚህ ላይ የአምላክ ቃል የሚናገረውን መስማት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

18 ቀደም ብለን ዳንኤል ስለ “ሰባቱ ዘመናት” የተናገረውን ትንቢት የመጀመሪያና ምሳሌያዊ አፈጻጸም መርምረናል። ይህ ትንቢት ናቡከደነፆር ቃል በቃል በእብደት ባሳለፋቸው ዓመታት በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ተመልክተናል። ናቡከደነፆር ለሰባት ዓመታት ያህል በሥልጣኑ ላይ እንዳልነበረ የሚገልጽ ሐተታ በዓለማዊ ታሪክ ላይ አለመገኘቱ ሊያስገርመን አይገባም። ጥንታውያን የግብጽ፣ የአሦርና የባቢሎን የታሪክ መዛግብት የአገራቸውን ገዥ የሚያዋርድ ታሪክ ካለ ሳይጠቅሱት ማለፋቸው የታወቀ ነገር ነው። በመንፈስ አነሣሽነት እንደተጻፈው እንደ አምላክ ቃል አስተማማኝ መመሪያ የማይሆኑበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። በሕልም የታየው ራእይ እንደተፈጸመ የሚያረጋግጥልን የአምላክ ቃል ነው። የትንቢቱ አነጋገር ከዚህ የበለጠ ሰፊ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ያመለክታል፤ ይህም በትክክል ተፈጽሟል። በምን መንገድ?

19. ይህ ራእይ የአሕዛብን ዘመናት ርዝመት ለማስላት ሊረዳን የሚገባው ለምንድን ነው?

19 ሕልሙ የተሰጠው በምድር ላይ የነበረውን የአምላክን ምሳሌያዊ መንግሥት ለመገልበጥና አሕዛብ ገዥ የሚሆኑበትን የዓለም አገዛዝ ለማቋቋም እንደ መሣሪያ ሆኖ ላገለገለው የዓለም ገዢ ለባቢሎኑ ንጉሥ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በተጨማሪም ሕልሙ የተሰጠው ይህ ታላቅ ለውጥ ከተከናወነ ማለትም የይሖዋ ሉዓላዊነት መግለጫ የሆነው ምሳሌያዊ መንግሥት መግዛት ካቆመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ዳንኤል ምዕራፍ 4 ‘ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንደሚሠለጥንና ለወደደውም እንደሚሰጠው’ የሚለውን ዋና መልእክት በተደጋጋሚ እየጠቀሰ ያጎላዋል። (ዳንኤል 4:17, 26, 34, 35) በዚህ ምክንያት አሕዛብ ምድርን የሚገዙበትን የጊዜ ርዝመት ለማወቅ ይህንን ራእይ የምንመረምርበት ጥሩ ምክንያት አለን።

20. ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን? መልሱንስ ለማግኘት ፊታችንን ወዴት ልናዞር እንችላለን?

20 በዳዊት መሥመር የመጣ ንጉሥ የሚገዛበት ምሳሌያዊው የአምላክ መንግሥት ከተገለበጠበት ጊዜ ጀምረን ስንቆጥር ከዳዊት የንግሥና መሥመር የሚመጣው መሲሕ ንጉሥ የሚሆንበት መንግሥት ተቋቁሞ አምላክ እንደገና ሉዓላዊነቱን የሚገልጥበት ጊዜ ምን ያህል መቆየት ነበረበት? ዳንኤል ምዕራፍ 4 እነዚህ አሕዛብ ‘ኢየሩሳሌምን’ ወይም የአምላክን መንግሥት የሚረግጡበት የአሕዛብ ዘመን ወይም ‘የተወሰኑትን የአሕዛብ ዘመናት’ ርዝመት ለማስላት የሚያስችል መሠረት ይሰጠናል። — ሉቃስ 21:24

21. ሴዴቅያስ ከዙፋኑ ከተወገደ በኋላ ስለ ሆነው ሁኔታ ዳንኤል 4:15–17 እና ኢዮብ 14:7 ምን ያመለክታሉ?

21 ይህ መረገጥ መቆጠር የሚጀምረው ናቡከደነፆር ንጉሥ ሴዴቅያስን በኢየሩሳሌም ከነበረው ዙፋን ካስወገደበት ዓመት ጀምሮ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በይሁዳ የነገሥታት መሥመር ይወከል የነበረው የይሖዋ ሉዓላዊነት ወይም የበላይ ገዥነት ‘ተቆረጠ።’ ልክ በናቡከደነፆር ሕልም የታየው የዛፍ ጉቶ እንዲታሠር እንደተደረገ ሁሉ ይህም መንግሥት ምንም የማይንቀሳቀስ ሆነ። እንደ አውሬ ያሉ የአሕዛብ መንግሥታዊ ኃይሎች መላዋን ምድር ተቆጣጠሩ። ይሁን እንጂ “ዛፉ” እንደገና ለማቆጥቆጥ ተስፋ ነበረው። ከዚያን በኋላ ሰዎች “ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን” ያውቃሉ። — ዳንኤል 4:15–17፤ ኢዮብ 14:7፤ ከኢሳይያስ 11:1, 2፤ 53:2 ጋር አወዳድር።

22. የመንግሥቱ “ዛፍ” እንደገና የሚያቆጠቁጠው መቼና በምን መንገድ ነው?

22 በዚህ እንደገና በሚቋቋመው መንግሥት ልዑሉ በመሲሑ አማካኝነት ይገዛል። ሆኖም ይህ የሚሆነው መሲሑ ፍጹም ሰው በመሆን በምድር ላይ በተገለጠበት የመጀመሪያ ጊዜ ላይ አይደለም። በዚያን ጊዜ አይሁዶች ንቀውትና እንደ ንጉሥ አድርገው ሳይቀበሉት ቀርተው ነበር። ይሁን እንጂ “ከሰውም የተዋረደው” ወይም ከሁሉም የሰው ልጆች ዝቅ ብሎ የነበረው በሁሉም ብሔራት ለሚገኙት ሕዝቦች ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን በክብር ሲመጣ የዛፉ ጉቶ ተፈትቶ ይህ መንግሥታዊ “ዛፍ” እንደገና አቆጥቁጦ ይንሰራፋል። ከዚያም የአሕዛብ ዘመናት ያበቁና የዓለም መንግሥት “ለጌታችንና እርሱ ለቀባው ክርስቶስ” ይሆናል። — ራእይ 11:15፤ ዳንኤል 4:17, 25

‘ሰባቱ ዘመናት’ ምን ያህል ርዝመት አላቸው?

23. የአሕዛብ ዘመናት እስከ ዘመናችን ድረስ መዝለቅ የሚገባቸው ለምንድን ነው?

23 እንግዲህ የአሕዛብን ዘመን የሚወክሉት “ሰባት ዘመናት” ቃል በቃል ከሰባት ዓመታት በጣም የሚበልጥን ጊዜ የሚያመለክቱ መሆናቸው ግልጽ ነው። ኢየሱስ የእነዚህን የአሕዛብ ዘመናት ‘መፈጸም’ ወይም ማለቅ ‘ከነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን’ ጋር አያይዞ እንደተናገረ አስታውሱ። (ሉቃስ 21:7, 24፤ ማቴዎስ 24:3) ስለዚህ እስከ ዘመናችን ድረስ የሚዘልቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ታዲያ ርዝመታቸው ምን ያህል ነው?

24. ‘የሰባቱን ዘመናት’ ርዝመት እንዴት ልናሰላው እንችላለን?

24 ራእይ ምዕራፍ 12⁠ን አውጥተን ብንመለከት በቁጥር 6 እና 14 ላይ የ1,260 ቀናት ርዝመት ያለው ጊዜ “አንድ ዘመን፣ ዘመናትም የዘመንም እኩሌታ” እንደሆነ ወይም 1 + 2 + 1⁄2 በጠቅላላው 3 1⁄2 ዘመናት እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ “አንድ ዘመን” 360 ቀኖች ወይም እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው 12 የጨረቃ ወራት ይሆናል ማለት ነው። “ሰባት ዘመናት” ደግሞ 2,520 ቀኖች ይሆናሉ። “አንድ ቀን ለአንድ ዓመት” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ስሌት እነዚህ ቀኖች በትክክል 2,520 ዓመታትን እንደሚሸፍኑ ያሳያል። (ዘኁልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6) እንግዲያው የአሕዛብ ዘመናት ይኸውም ‘የሰባቱ ዘመናት’ ርዝመት ይኸው ነው።

25. የአሕዛብ ዘመናት የሚጀምሩበትን ጊዜ ለማወቅ በኤርምያስ 25:11 ላይ የሚገኙት “ሰባ ዓመታት” የሚሰሉት እንዴት ነው?

25 የአምላክን ቃል በማንበብ የአሕዛብ ዘመናት የሚጀምሩበትን ጊዜ ለማወቅ የሚረዳንን ሐሳብ እናገኛለን። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ይሖዋ ባቢሎናውያን ሕዝቡን ድል እንዲያደርጉ፣ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደስዋን እንዲደመስሱ፣ ሴዴቅያስን ‘ከይሖዋ የንግሥና ዙፋን’ እንዲያስወግዱና አይሁዳውያንን ማርከው ወደ ባቢሎን እንዲያፈልሱ ፈቅዶላቸዋል። (1 ዜና. 28:5) ከዚያ ‘በሰባተኛው ወር’ ላይ የተፈጸሙት ሁኔታዎች በምድሪቱ ቀርተው የነበሩት ጥቂት አይሁዶች ወደ ግብጽ እንዲሸሹና የይሁዳ ምድር ሙሉ በሙሉ ባድማ እንድትሆን አድርገዋል። (2 ነገሥት 25:1–26፤ ኤርምያስ 39:1–10፤ 41:1 እስከ 43:7) የይሖዋ ነቢይ የሆነው ኤርምያስ ምድሪቱ ለ70 ዓመት ባድማ ሆና እንደምትቆይ ተንብዮ ነበር። (ኤርምያስ 25:8–11) ከዚያ በኋላ ይሖዋ ‘የባቢሎን ንጉሥ ለፈጸመው በደል መልስ እንዲሰጥ ይጠይቀዋል። ሕዝቡንም ወደዚህ ቦታ ማለትም ወደ ትውልድ አገራቸው ይመልሳል። — ኤርምያስ 25:12፤ 29:10

26. ሀ) ዳንኤል የዓይን ምሥክር የሆነው ለምን ነገር ነው? ምንስ አስተዋለ? (ለ) ዳንኤል እሥራኤላውያን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ስለ መመለሳቸው የተናገረው ትንቢት የተፈጸመበትን ወርና ዓመት ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) ይህ የሆነበት ጊዜ በትክክል የትኛው ነው?

26 ዳንኤል ራሱ በባቢሎን ምርኮኛ ሆኖ ብዙ ዓመታት ኖሯል። ባቢሎን በሜዶ ፋርሳውያን እጅ በወደቀችበት ሌሊት ስለ ከተማዋ እርሱ የተናገረው ትንቢትና ሌሎች ትንቢቶች ሲፈጸሙ የዓይን ምሥክር ሆኗል። (ዳንኤል 5:17, 25–30፤ ኢሳይያስ 45:1, 2) የታሪክ ጸሐፊዎች ባቢሎን የወደቀችው በ539 ከዘአበ በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ በስሌት ደርሰውበታል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ዳንኤል ኢየሩሳሌም በምርኮና በመፍረስ የምትቆይባቸው 70 ዓመታት የሚያልቁበት ጊዜ መድረሱን ከኤርምያስ ትንቢት ተረድቶ ነበር። (ዳንኤል 9:2) ትክክልም ነበር! በፋርሳዊው ቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት (አብዛኞቹ የታሪክ ጸሐፊዎች በ538 ከዘአበ በጸደይ ወራት መግዛት እንደ ጀመረ ይስማማሉ።) አይሁዶች ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ምድሪቱን እንደገና እንዲሞሏትና በዚያም የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ ቂሮስ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። (2 ዜና. 36:20–23፤ ዕዝራ 1:1–5) በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ታሪካዊ መዝገብ አይሁዳውያኑ ቂሮስ ላወጣው ትእዛዝ ያለ ማወላወል እሺ የሚል ምላሽ እንደሰጡ ይነግረናል። ስለዚህም “ሰባተኛው ወር በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው” ነበሩ። (ዕዝራ 3:1) ይህም በጎርጎሮሳውያን የቀን መቁጠሪያ 537 ከዘአበ ጥቅምት ወር ላይ ይውላል። ስለዚህ በትንቢት የተነገረላቸው 70 የባድማነት ዓመታት ያበቁት ያን ጊዜ ነበር።

27. (ሀ) እንግዲያው 70ዎቹ ዓመታት የጀመሩት መቼ መሆን ይኖርበታል? በዚያን ጊዜስ ምን ነገር ተፈጸመ? (ለ) “ሰባቱ ዘመናት” ምን ያህል ርዝመት ነበራቸው? እንግዲያው ያበቁት መቼ ነው? (ሐ) በዚሁ ጊዜ ላይ ምን ሌላ ታላቅ ትንቢት መፈጸም ጀመረ? (መ) መጠበቂያ ግንብ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት የትኛውን ቁም ነገር ለማሳመን ሲታገል ቆይቷል?

27 ይህ ታሪካዊ መረጃ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” የጀመሩበትን ጊዜ ለማወቅ በጣም ያስፈልገናል። የ70 ዓመቱ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ባድማነት ያበቃው በ537 ከዘአበ ከሆነ የጀመረው በ607 ከዘአበ ነው ማለት ነው። ሴዴቅያስ “በይሖዋ የንግሥና ዙፋን” ላይ መቀመጥ ያቆመበት ዓመት ይህ ነበር። በዚህም ምክንያት የአሕዛብ ዘመናት የጀመሩት ያን ጊዜ ነው። ከ607 ከዘአበ ጥቅምት ወር ጀምረን ስንቆጥር 2,520 ዓመታት ርዝመት ያላቸው “ሰባቱ ዘመናት” ወደ 1914 እዘአ የጥቅምት ወር መጀመሪያ ያደርሱናል። ይህም ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ኢየሱስ ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የተናገረው ታላቅ ትንቢት መፈጸም የጀመረበት ጊዜ ነው። ለዚህ ድምዳሜ መሠረት የሚሆነን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው አስተማማኝ መረጃ ነው። የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትም ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ለዚህ ሐቅ ጥብቅና በመቆም አቋሙን በይፋ ሲያሳውቅ ቆይቷል።

28, 29. (ሀ) በአምላክ ቃል ውስጥ ተጠብቀው ስለ ቆዩት ዝርዝር ታሪኮች አመስጋኝ እንድንሆን የሚያደርገን ምን ስለ ዓለም የታሪክ መዛግብት የምናውቀው ነገር ነው? (ለ) የአሕዛብ ዘመናት ያበቁበትን ጊዜ በተመለከተ ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ጥቅምት 1914⁠ን ለመቀበል የሚያስደፍር ጠንካራ ምክንያት ያለው ለምንድን ነው?

28 ይሖዋ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረውን የአይሁዶች፣ የባቢሎናውያንና የሜዶ ፋርሳውያን ሁኔታ የሚያስረዱ ዝርዝር ታሪኮች በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ ስላደረገ በእርግጥም አመስጋኞች መሆን ይገባናል። እንደዚህ ባይሆን ኖሮ በዚያን ጊዜ የተፈጸሙትን ታሪካዊ ሁኔታዎች ትክክለኛ ጊዜያቸውን ለማገጣጠም አስቸጋሪ ይሆን ነበር፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የተጻፉትና አሁን ሊገኙ የቻሉት ዓለማዊ የታሪክ መዝገቦች ያልተሟሉ ናቸው።

29 ሆኖም አንዳንድ ሰዎች እንደነዚህ ባሉት ዓለማዊ የታሪክ መረጃዎች ላይ ተመርኩዘው ኢየሩሳሌም በ587–6 ከዘአበ እንደ ጠፋችና አይሁዶችም በእነርሱ ስሌት መሠረት በናቡከደነፆር የንግሥና ዓመት በ605 ከዘአበ * በባቢሎናውያን አገዛዝ ሥር እንደ ወደቁ ይናገራሉ። በዚህም መሠረት “ምድሪቱ ሁሉ ባድማ ትሆናለች፤ በአሕዛብም አገዛዝ ሥር ለሰባ ዓመታት ይቆያሉ” የሚለው የኤርምያስ 25:11 ትንቢት መፈጸም የሚጀምርበት ጊዜ 605 ከዘአበ ነው ይላሉ። (የባግስተር ግሪክ ሴፕቱጀንት ) ነገሩ እንደዚያ ቢሆንና የአሕዛብም ዘመናት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቢቆጠሩ ትንቢታዊ “ሰባት ዘመናት” የዓለም ጦርነት ይካሄድበት በነበረው ዓመት በ1916 ላይ ያልቁ ነበር። ሆኖም ከላይ እንደ ገለጽነው የአሕዛብ ዘመናት በ607 ከዘአበ ጥቅምት ወር ላይ እንደ ጀመሩና በጥቅምት 1914 እዘአ እንዳበቁ የሚያመለክተውን በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መረጃ ለመቀበል ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ምክንያት አለን።

30. ከ1914 ወዲህ ያሉት ጊዜያት “የመጨረሻ ቀኖች” መሆናቸውን የሚያሳውቁ ምን ጣምራ ማስረጃዎች አሉ?

30 አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት በቃሉ ውስጥ ኢየሱስ በ29 እዘአ መሲሕ በመሆን የሚመጣበትንና ከ1914እዘአ ጀምሮ ደግሞ ክብር የተቀዳጀ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን ‘የሚገኝበትን’ ጊዜ በግልጽ የሚያሳዩ ትንቢቶች ስለ መዘገበልን ልንደሰት ይገባናል። “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” እየገፋ ሲሄድ ኢየሱስ እንድንጠብቃቸው የነገረን በዙሪያችን የሚታዩ ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ እንመለከታለን። የዓለም ጦርነቶች፣ ረሀብ፣ ቸነፈር፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ዓመፅ፣ የፍቅር መጥፋት፣ ጥላቻና ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅና በቆሙት ላይ የሚደርሰው ስደት፣ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ተዳምረው ‘የመጨረሻዎቹን ቀናት’ ለማወቅ ያስችሉናል። — 2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 24:3–12፤ ማርቆስ 13:7–13

የሺው ዓመት ግዛት መቼ ነው?

31. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ዘመናችን ምን ምክር ሰጠ? ለምንስ? (ለ) ምን ጥያቄ ለመጠየቅ እንገፋፋለን? የይሖዋስ መልስ ምንድን ነው?

31 ይህ አስፈሪ ሁኔታ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ክርስቶስ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ስለተቀመጠ በአምላክ ጠላቶች ላይ ፍርዱን ለመፈጸም ብዙ አይቆይም ብሎ ለማመን በቂ ምክንያት አለ። “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት የሚያውቅ ማንም የለም።” ስለዚህ በራሳችን አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዘን ጊዜውን ለመገመት ብንሞክር የምናተርፈው ነገር የለም። ቢሆንም “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለውን የኢየሱስ ማሳሰቢያ መስማት ይኖርብናል። (ማርቆስ 13:32፤ ማቴዎስ 24:42) በምድር ላይ እየተባባሱ የሚሄዱትን ሁኔታዎች ስንመለከትና በአጠቃላይ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች እንደማይቀበሉት ስናይ እኛም እንደ አምላክ ነቢይ ስለ ስብከታችን “እስከ መቼ ድረስ ነው ይሖዋ?” ብለን ለመጠየቅ እንገፋፋ ይሆናል። ይሖዋም ለዚህ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል:-

“ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፣ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ . . . ነው።” (ኢሳይያስ 6:10–12)

ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ይህንን ፍርዱን መጀመሪያ በሕዝበ ክርስትና ላይ በኋላም በቀሩት የሰይጣን ዓለም ክፍሎች ላይ ይፈጽማል። ከዚያ ከተል ብሎ የክርስቶስ የ1,000 ዓመት ግዛት ይመጣል። — ራእይ 20:1–3, 6

“ይህ ትውልድ” የተባለው የትኛው ነው?

32. ማቴዎስ 24:34⁠ን በተመለከተ ምን ጥያቄ ይነሣል?

32 ኢየሱስ ስለ “ምልክቱ” በተናገረው ታላቅ ትንቢቱ ላይ “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:34) የአንድ ትውልድ ዕድሜ ይህን ያህል ነው ብሎ የተወሰነ የጊዜ ርዝመት አልሰጠም። ታዲያ “ይህ ትውልድ” የሚለውን አባባል የምንረዳው እንዴት ነው?

33. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን የነበረው “ትውልድ” የትኛው ነው? (ለ) ከዚህ ጋር በማመሳሰል ከ1914–1918 ስለነበረው “ትውልድ” ምን ሊባል ይቻላል?

33 በኢየሱስ ዘመን የትንቢት ቃሉን ከሰሙት ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ አንዳንዶቹ እንዲሁም እርሱ በኖረበት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ላይ እስከመጣው የመጨረሻ “መከራ” ድረስ በመቆየት ከመከራው በሕይወት ተርፈዋል። በኢየሱስ ዘመን “ትውልዱ” እነርሱ ነበሩ። ይህ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ በተጻፈበት ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ1914–1918 የደረሰውን “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ለማየት የቻሉ ከ10,000,000 የሚበልጡ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ገና ጥቂት ዓመታት ሊቆዩ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ከማለፉ በፊት “የሰው ልጅ” ሆኖ እንደሚመጣና በሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ላይ ፍርዱን እንደሚፈጽም አረጋግጦልናል። (ማቴዎስ 24:8, 21, 37–39) እንግዲህ ‘የመንግሥቲቱን መምጣት’ እየተጠባበቅን በንቃት መኖር ይገባናል። — ሉቃስ 21:31–36

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ወርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታሜንት የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 188

^ አን.29 በገጽ 186 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 135 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ሰባቱን ዘመናት’ ማስላት

7 “ዘመናት”= 7 × 360 = 2,520 ዓመታት

(አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ “ዘመን” ወይም ዓመት 354 ቀናት ርዝመት ባለው የጨረቃ ዓመትና 365 14 ቀናት ርዝመት ባለው የፀሐይ ዓመት መካከል ያለው መካከለኛ ጊዜ ነው)

ከ607 ከዘአበ እስከ 1 ከዘአበ = 606 ዓመታት

ከ1 ከዘአበ እስከ 1 እዘአ = 1 ዓመት

ከ1 እዘአ እስከ 1914 እዘአ = 1,913 ዓመታት

ከ607 ከዘአበ እስከ 1914 እዘአ = 2,520 ዓመታት

[በገጽ 140 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የ1914 ትውልድ”

ከላይ ያለው ርዕስ በተሰጠው አንድ መጽሐፍ ውስጥ ሮበርት ዎል “ትውልዶች በዓመታት ብዛት በአኀዝ ሊገለጹ የሚችሉ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ በታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖች ዙሪያ የነበሩ እንደ አንድ ትውልድ ይቆጠራሉ። ለዚህም አንደኛው የዓለም ጦርነት ትልቅ ምሳሌ ይሆነናል።” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። — “ዘ ኤኮኖሚስት” መጋቢት 15, 1980