በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጉሡ አርማጌዶን ላይ ይዋጋል

ንጉሡ አርማጌዶን ላይ ይዋጋል

ምዕራፍ 17

ንጉሡ አርማጌዶን ላይ ይዋጋል

1, 2. የዓለም ሰዎች ስለ አርማጌዶን ምን ይላሉ?

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ማብቃቱ እየተቃረበ ሲሄድ አሜሪካዊው ጄኔራል ዳግላስ ማካርተር እንዲህ ብለው ነበር:- “ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ሰላምን ለማምጣት ሲጥሩ ኖረዋል። . . . ወታደራዊው ኅብረት፣ የኃይል ሚዛን፣ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበሮች ተሞከሩ። ሆኖም ሁሉም ውጤት አልባ ሆኑ። መፍትሔው የጦርነት መንገድ ብቻ ሆነ። አሁን ያለው የጦርነት አውዳሚነት ደግሞ ይህን አማራጭ ገለል ያደርገዋል። የመጨረሻ ዕድል አግኝተን ነበር። አንድ ታላቅና የተስተካከለ ሥርዓት ካልፈጠርን አርማጌዶን በራችንን ያንኳኳል።”

2 ከ35 ዓመታት በኋላ ብሔራት ይህንን “የመጨረሻ ዕድል” በተመለከተ ምን ያደረጉት ነገር አለ? በእንግሊዝ አገር በለንደን የሚታተመው ታይምስ መጽሔት “ምዕራብ ጀርመናውያን አርማጌዶን እንዳይነሣ ሰግተዋል” ከሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ብሎ ነበር:- “ዓለም አቀፋዊው ሁኔታ በሁሉም አቅጣጫ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ሲሄድ የጦርነት ስጋት በምዕራብ ጀርመን ላይ እንደገና ፍርሃት ለቋል።” እንዲሁም “ዓለም ተደነባብራ ጨለማ ውስጥ ገብታለች” በሚል ርዕስ በዩናይትድ ስቴትስ የሚታተመው የማያሚ ሄራልድ ዋና አዘጋጅ አንባቢዎቻቸውን “አርማጌዶን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ መሆኑ ቀርቶ እውን ነገር እንደሆነ አሁን አልተገለጸላችሁምን?” በማለት ከጠየቁ በኋላ “መለስተኛ የማመዛዘን ችሎታ ያለው ማንኛውም ሰው ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጸሙትን እንደ መቅሠፍት የሆኑ ነገሮች አዳምሮ ዓለም በታሪካዊ ደፍ ላይ መቆሟን ለማየት ይችላል። . . . ይህም የሰዎችን የአኗኗር መንገድ ለዘላለም ይለውጣል” አሉ።

3, 4. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አርማጌዶን የሚሰጠው መግለጫ ከዚያ የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

3 እውነት ነው፤ የሰው ልጅ ከፍተኛ ለውጦች በሚከሰቱበት ደፍ ላይ ቆሟል። ይሁን እንጂ አርማጌዶን አሁን አፍጥጦ መጥቶብናልን? አርማጌዶን ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ሊያስገርማችሁ ቢችልም አርማጌዶን አብዛኞቹ ሰዎች ከሚያስቡት የተለየ ነገር ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአርማጌዶንን ጦርነት የሚገልጸው በምድራዊ ብሔራት መካከል እንደሚካሄድ አውዳሚ መቅሠፍት አድርጎ ሳይሆን “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ የሚደረግ ጦርነት” እንደሆነ አድርጎ ነው። አርማጌዶን ‘በመላዋ ምድር ነገሥታት’ ላይ የሚከፈት የአምላክ ጦርነት ነው። በሌላ አነጋገር የአምላክ መንግሥት ፈቃድዋን በምድር ላይ ለማድረግ ‘ስትመጣ’ አሻፈረን፣ አንቀበልም በሚሉት ገዥዎች ላይ የሚመጣ የአምላክ ጦርነት ነው። (መዝሙር 2:6–12፤ ዳንኤል 2:44) ይህ ጦርነት ለመሲሑ የ1,000 ዓመት ሰላማዊ ግዛት መንገድ ለመጥረግ ሲል አምላክ ክፉ ብሔራትንና ሰዎችን ለማጥፋት የሚወስደው የራሱ ታላቅ እርምጃ ነው። — ራእይ 16:14, 16፤ መዝሙር 46:8, 9፤ 145:20፤ ኢዩኤል 3:9–17፤ ናሆም 1:7–9

ከጦርነቱ በፊት መሆን ያለባቸው ነገሮች

5. በራእይ 17 ላይ የተጠቀሰችውን “ታላቅ ጋለሞታ” ማንነት ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

5 ራእይ ምዕራፍ 16–18 ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት ደረጃ በደረጃ ስለሚከናወኑት ነገሮች ይነግረናል። በትንቢቱ መሐል “ና በብዙ ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ” የሚል ግብዣ ቀርቧል። ትንሽ ቆየት ብሎ ይህች “ታላቅ ጋለሞታ” “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት” እንደሆነች ተገልጾልናል። የጥንቷ ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ተመቻችታ በመቀመጥ ከባቢሎን ተነሥቶ በመላዋ ምድር ላይ ለተስፋፋው የሃይማኖት ምሥጢራዊ ሥርዓት “እናት” እንደሆነች ሁሉ የዛሬዋ ታላቂቱ ባቢሎንም ‘በወገኖችና በብዙ ሰዎች በአሕዛብም በቋንቋዎችም’ ላይ ተቀምጣ የምትቆጣጠራቸው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናት። ሥራዋ ግን ሕዝቦችን የሚጐዳ ነው። (ራእይ 17:1, 5, 15) ታላቂቱ ባቢሎን “ክርስቲያን” ነን የሚሉትንና ሌሎችንም፣ ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ እውቅና የማይሰጡትንና የማያገለግሉትን፣ በሺህ የሚቆጠሩ የሃይማኖት ቡድኖችን ያቀፈች ነች።

6. ራእይ 16 የጥንትዋ ባቢሎን ትዝ እንድትለን የሚያደርግ ምን ነገር እንደሚፈጸም ይናገራል?

6 ለአርማጌዶን መቅድም ይሆን ዘንድ አንድ መልአክ ‘የአምላክን የቁጣ ጽዋ’ ሲያፈስስ ታይቷል። የፈሰሰው የት ላይ ይሆን? “ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።” (ራእይ 16:1, 12) ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ትንቢት ከመጻፉ ከ600 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ዳርዮስ የተባለው የሜዶኑ ንጉሥና ቂሮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ከምሥራቅ የባቢሎንን ምድር ወረሩ። ቂሮስ ጨለማን ተገን በማድረግ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ወደ ሌላ ስፍራ እንዲፈስ አደረገ። ውኃው ከጐደለ በኋላ ሠራዊቱ የደረቀውን ወንዝ አቋርጦ ወደ ከተማዋ እንዲገባ አዘዘ። የባቢሎን ገዥዎችና መኳንንት ሰክረውና ይሖዋን በመሳደብ ላይ ሳሉ በአንድ ሌሊት የታላቂቱ ከተማ መንግሥት ተገለበጠ። — ዳንኤል 5:1–4, 30, 31

7. ዛሬ ምን ዘመናዊ ተመሳሳይነትን እንመለከታለን?

7 በዘመናችን ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር እናያለንን? አዎን፣ አለ! ይሖዋ ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ በተለይም የእርስዋ “ሴት ልጆች” በሆኑት የሕዝበ ክርስትና ድርጅቶች ላይ ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ መጥቷል። የሕዝበ ክርስትና የክህደትና የደም አፍሳሽነት ጽዋ ሞልቶ ፈሷል። (ራእይ 18:24፤ ኤርምያስ 51:12, 13) ቀደም ሲል ሃይማኖትዋን ይደግፉ የነበሩት “ውኃዎች” ማለትም “ሕዝቦች” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥለዋት እየወጡ ነው። ብዙ ሰዎች ወደ ዳርዊን፣ ማርክስ፣ ሌኒንና ማኦ ትምህርቶች ዘወር በማለታቸው ለሃይማኖት የሚሰጠው ድጋፍ እየነጠፈ በመሄድ ላይ ነው። በተጨማሪም ‘የመጨረሻዎቹን ቀኖች’ በተመለከተ አስቀድሞ እንደተገለጸው ሰዎች “ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነዋል። — 2 ጢሞቴዎስ 3:1, 4

8. (ሀ) የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች የትኛውን ጥሪ ነው የታዘዙት? (ለ) በአሁኑ ጊዜ የሐሰት ሃይማኖት ሁኔታ ከእውነተኛው ሃይማኖት ሁኔታ በጣም የሚለየው እንዴት ነው?

8 ‘ለውኃዎቹ’ መጉደል አስተዋጽዖ ካደረጉት ነገሮች አንዱ “ታላቂቱ ባቢሎንን” በተመለከተ ከሰማይ የቀረበውን የሚከተለውን ጥሪ የታዘዙት የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች የወሰዱት እርምጃ ነው:-

“ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።” (ራእይ 18:4)

የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በተለይም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች በመዘጋታቸው፣ የጸሎት ቤት ወንበሮች ባዶ በመሆናቸውና የቄሶችና የመነኮሳት ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ እየዬ ብላ እያለቀሰች ነው። በአሁኑ ጊዜ በታላቁ ዳርዮስ በይሖዋ አምላክና በታላቁ ቂሮስ በክርስቶስ ኢየሱስ ጎን የተሰለፉት ግን አስደናቂ ወደሆነ መንፈሳዊ ብልጽግና ገብተዋል። አንተስ ከእነዚህ አንዱ ነህን?

እንደ ጋለሞታ ናት

9, 10. (ሀ) በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ምን አስፈሪ “አውሬ” ብቅ ብሏል? (ለ) በ1942 በተደረገ አንድ የሕዝብ ንግግር ላይ የአውሬው ምንነት የተገለጸውና አካሄዱ የተብራራው እንዴት ነበር?

9 “ታላቂቱ ባቢሎን” የአምላክ አገልጋይ እንደሆነች እየተናገረች ምን ጊዜም ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ስታደርግ ቆይታለች። በዚህም መንገድ ‘የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ጋር ሴስነዋል።’ ይሁን እንጂ አሁን በእነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ አንድ አጋጣሚ አላት! ምን? ‘አንድ ቀይ አውሬ’ መጣላት። ይህ “አውሬ” ምን ይሆን? በምድር ላይ ያሉትን የፖለቲካ መንግሥታት እንደሚያመለክት ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም እነዚህ መንግሥታት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ‘አራዊት’ ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 13:1–4, 11–15፤ ዳንኤል 7:3–8, 17–25፤ 8:5–8, 20–22) እዚህ ላይ ግን የሚታየው የተለያዩ አራዊት ድብልቅ የሆነ “አውሬ” ነው፤ ምክንያቱም ይህ አስፈሪ እንስሳ “ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች” አሉት። — ራእይ 17:3

10 በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ውስጥ ልዩ ልዩ አራዊትን አጣምሮ የያዘ ምን “አውሬ” ብቅ ብሏል? በዓለም መድረክስ ላይ ምን ሚና ይጫወታል? በ1942 በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ “ሰላም — ሊዘልቅ ይችላልን?” በሚል ርዕስ የቀረበው የሕዝብ ንግግር በራእይ 17:7, 8 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ ያተኮረ ነበር። ተናጋሪው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዝዳንት ናታን ኖር “አስቀድሞ ነበረ” የተባለለት “አውሬ” በ1920 የተቋቋመው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እንደሆነ አሳወቀ። ሆኖም በዚያ የጦርነት ዓመት ማለትም በ1942 “የቃል ኪዳኑ ማኅበር አሁን በድን ሆኗል፤ እንዲንቀሳቀስ ከተፈለገ ሕይወት እንዲሰጠው ያስፈልጋል። አሁን ግን በድን ሆኖ ወደማይንቀሳቀስበት ጥልቅ ውስጥ ገብቷል። ‘አሁን የለም’ የለም’፤” ብሎ ነበር። ፕሬዝዳንት ኖር ይህን ጉዳይ የበለጠ ሲያብራራ ‘አስቀድሞ የነበረው አሁንም የሌለው አውሬ ከጥልቁ ይወጣ ዘንድ እንዳለውና ወደ ጥፋትም እንደሚሄድ’ ገለጸ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እውነተኛ ሆኖ ተገኘ፤ ያ “አውሬ” የተባበሩት መንግሥታት ሆኖ በ1945 እንደገና ሕይወት አገኘ።

11. (ሀ) ይህ “አውሬ” “የስድብ ስሞች የሞሉበት” ተብሎ የተገለጸው ለምንድን ነው? (ለ) “አውሬው” ምን ፍርድ ይጠብቀዋል?

11 ይህ በዓለም መንግሥታት መካከል “ሰላምና ደኅንነት” ለማምጣት የተቋቋመው ብሔራት አቀፉ “አውሬ” በክርስቶስ ኢየሱስ የምትመራዋ የአምላክ መንግሥት ብቻ ልትፈጽመው የምትችለውን ነገር እኔ ላደርገው እችላለሁ ስለሚል በእርግጥም “የስድብ ስሞች የሞሉበት” ነው። (ራእይ 17:3) ሐዋርያው ጳውሎስ ጉረኞቹ የሰይጣን ዓለም ገዥዎች ሰላም አምጪ ነን እያሉ ራሳቸውን የሚያወድሱበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል:-

“የእግዚአብሔር ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3)

በአምላክ ቃል መሠረት “ሰላምና ደኅንነት” አምጥቻለሁ ባዩ አውሬ ከይሖዋ ፈጣንና ወሳኝ ፍርድ ይመጣበታል!

ለጋለሞታይቱ “ወዮላት”

12. ዮሐንስን እንዲገረም ያደረገው የትኛው ስለ “ጋለሞታይቱ” የተሰጠ መግለጫ ነው?

12 አምላክ ተሳዳቢ የሆነውን አውሬ ማለትም የተባበሩት መንግሥታትን እንደማይቀበለው በግልጽ ቢያሳውቅም “ታላቂቱ ባቢሎን” ከእርሱ ጋር ለመወዳጀት ትጥራለች። አዎን፣ “በአውሬው” ላይ እንደተቀመጠች ንግሥት ሆና ተገልጻለች። “ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቆችም ተሸልማ ነበር፣ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች።” ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ዮሐንስ:- “ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ” ብሎ መጻፉ ብዙም የሚያስደንቅ አይሆንም። — ራእይ 17:4, 6

13, 14. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖትን ምን ወዮ የሚያሰኝ ፍጻሜ ይጠብቃታል? (ለ) ይህስ የሚመጣው እንዴት ነው? (ሐ) ለታላቂቱ ባቢሎን የሚያለቅሱት እነማን ናቸው? ከሩቅ ሆነው የሚያለቅሱላትስ ለምንድን ነው?

13 ባቢሎናዊ በሆነው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛትና “ሰላምና ደኅንነት” ለማምጣት በተቋቋመው አውሬ’ ማለትም በተባበሩት መንግሥታት መካከል ያለው ይህ ወዳጃዊ ግንኙነት በመጨረሻው መልኩን ለውጦ አውዳሚ ጥል ይፈጠራል። በጋለሞታ የተመሰለችው “ባቢሎን” በዓለም አቀፉ አካል ላይ ተመቻችታ እንደተቀመጠች አድርጋ ብታስብም የአምላክ ቃል ስለ እርስዋ የሚከተለውን ይተነብያል:-

“ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:16)

የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ፍጻሜዋ ይህ ስለሚሆን በእርግጥም ወዮላት!

14 “ታላቂቱ ባቢሎን” የምትጠፋው በፍጥነት ይሆናል።

“ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጣሉ፣ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” (ራእይ 18:8)

ሆኖም የሚያለቅሱላት ይኖራሉ። እነርሱም ወዳጅነታቸውን በመካድ የዞሩባት ወታደራዊ “አሥር ቀንዶች” ሳይሆኑ ከፖለቲካ ገዥዎች መካከል ለታይታና ድብቅ ድርጊታቸውን ለመሸፋፈን ሲሉ ከቄሶች ጋር ተወዳጅተው የነበሩ ፖለቲከኞች ናቸው። የእርስዋ ዕጣ ይደርስብናል ብለው በመፍራት ራቅ ብለው ያለቅሱላታል። እንዲህ ይላሉ:-

“አንቺ ታላቂቱ ከተማ፣ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፣ ወዮልሽ፣ ወዮልሽ፣ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና።” — ራእይ 18:9, 10

15. እነማንም ጭምር የኀዘን እሮሮ ያሰማሉ? ለምንስ?

15 ከነዚህም ሌላ ለመጥፎ ድርጊታቸው “የቅድስና” ሽፋን ለማድረግና ሕሊናቸው እንዳይቆረቁራቸው ሲሉ በሃይማኖታዊ ቁርኝታቸው ሲጠቀሙ የቆዩ የትልልቅ ንግድ ባለቤቶች፣ ወንጀለኞችና ሕገ ወጥ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ይኖራሉ። እነርሱም ጭምር እንዲህ በማለት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ:-

“ወዮላት፣ ወዮላት፣ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና።” (ራእይ 18:11–19)

ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸው ካቴድራሎች፣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲያግበሰብሱት የነበረው መሬትና ሀብት፣ በባንክ የተቀመጠ ከፍተኛ ገንዘብና የዓለም ሃይማኖት በንግድ ላይ ያዋለው ኢንቨስትመንት ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ።

16. የትኞቹ ሦስት ቡድኖች ጥፋት ይጠብቃቸዋል?

16 ሦስቱም የሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ቅርንጫፎች ማለትም ግብዝ የሆነው የዓለም ሃይማኖት፣ ስግብግብ የሆነው የንግድ ዓለምና ምግባረ ብልሹ የሆነው ፖለቲካ የይሖዋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። ታዲያ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ የሚቀጥለው ማን ይሆናል?

ንጉሡ እርምጃ ለመውሰድ ተንቀሳቀሰ!

17, 18. (ሀ) “ታላቂቱ ባቢሎን” ከጠፋች በኋላ ምን ይቀጥላል? ለምንስ? (ለ) በመጨረሻ ድል የሚያደርገው ማን ይሆናል? (ሐ) በሕይወት እንዲያልፉ የሚደረጉት እነማን ናቸው? (መ) አንተስ ከእነዚህ አንዱ ለመሆን የምትችለው እንዴት ነው?

17 የዓለምን ሃይማኖት የሚደመስሱት እነዚህ ሥር ነቀል የፖለቲካ ኃይሎች መንፈሳዊ የማስተዋል ዓይን የላቸውም። በ1914 የተቋቋመችውን መሲሐዊት መንግሥት አይቀበሉም። ከዚህ ይልቅ ያችን መንግሥት የሚያውጁትንና የዓለምን ‘መንግሥታት’ ፖለቲካና ጦርነቶች በተመለከተ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም የሚይዙትን ሰዎች ክፉኛ ይቃወማሉ። — ራእይ 12:17፤ ዮሐንስ 17:14, 16

18 እነዚህ የአውሬ ጠባይ ያላቸው “ቀንዶች” “ታላቂቱን ባቢሎን” ካጠፉ በኋላ መከላከያ የሌላቸው መስለው በሚኖሩት የበጉ ተከታዮች ማለትም በክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የመጨረሻ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ሊጠበቅ ይቻላል። (ሕዝቅኤል 38:14–16፤ ኤርምያስ 1:19) እነዚህ ጠላቶች ከዚህ ውጊያ ምን ውጤት ያገኙ ይሆን? ትንቢቱ መልሱን ይሰጠናል:-

“እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፣ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” (ራእይ 17:14)

በምድር ላይ ገና የቀሩት የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮችና “ለቅዱስ አገልግሎት” የቀረበላቸውን ጥሪ እሺ ብለው የተቀበሉት ጓደኞቻቸው በዚህ ጦርነት ተሳታፊ ባይሆኑም ከውጊያው ተጠብቀው በሕይወት ያልፋሉ። ታዲያ አንተስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን ‘እንድትመጣ’ ከሚጸልዩት አንዱ ነህን? — ሮሜ 12:1, 2፤ ከ2 ዜና 20:5, 6, 12–17 ጋር አወዳድር።

19. (ሀ) ለየትኛው ነገር የዓይን ምሥክር ለመሆንና ከእርሱ ለመትረፍ ትችላለህ? (ለ)በዚያን ጊዜ ምን ውድ የነበሩ ነገሮች ዋጋ ያጣሉ?

19 አዎን፣ ታላቅ እልቂት ለሚደርስበት የአርማጌዶን ጦርነት የዓይን ምሥክር ለመሆንና ከዚያ መዓት ለመትረፍ ትችላለህ። “የነገሥታት ንጉሥ” ከሰማያዊ የመላእክት ሠራዊቱ ጋር በመሆን የይሖዋን የበላይ ገዥነት ለማስከበር ሲዋጋ ቆመህ ለማየት ትችላለህ። በክፉዎች፣ በትዕቢተኛ መንግሥታትና በኃያል ጦር ሠራዊቶቻቸው እንዲሁም እነርሱን በሚደግፉት ሀብታም “ነጋዴዎች” ላይ የሚከፈተውን ወሳኝ ፍልሚያ ልታይ ትችላለህ። ብዙ ቢልዮን ዶላር ወጥቶ የተመረተው የኑክሌር መሣሪያቸው በዚያ ጦርነት ከምንም ነገር አያስጥላቸውም! ነዳጅ ዘይትና ምግብ እየሸጡ ብዙ ትርፍ የሚያግበሰብሱ ስግብግብ ነጋዴዎች የዓለም የምንዛሪ ተቋሟት ሲንኰታኰቱና ምንም ቢሆን ዋጋውን አያጣም የሚባልለት ወርቅ ፈላጊ አጥቶ ሲራከስ በግፍ ያግበሰበሱት ትርፋቸው ዋጋ ቢስ ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ክፉ ነገር፣ አንድ ክፉ ነገር፣ እነሆ፣ ይመጣል። ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። . . . እኔም [ይሖዋ አዓት] እንደሆንሁ ያውቃሉ።” — ሕዝቅኤል 7:5, 19, 27

20. ለሕይወትህ ጥላ ከለላ ልታገኝ የምትችለው የት ነው?

20 በዚያ የአርማጌዶን ቀን ምንም ዓይነት ሥጋዊ ሀብት ጥላ ከለላ አይሆንልህም። ለሕይወትህ ዋስትና የምታገኘው ከይሖዋና እርሱ ከሾመው “የነገሥታት ንጉሥ” ጎን ጸንተህ በመቆም ብቻ ነው። ይህም ለሚከተሉት የነቢዩ ቃላት በምታሳየው ታዛዥነት ላይ የተመካ ነው:-

“እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” (ሶፎንያስ 2:3፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 26:20, 21፤ ዳንኤል 12:1 ተመልከት።)

አርማጌዶን ላይ በምሳሌያዊ ነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ንጉሥ “በጽድቅ ይፈርዳል ይዋጋልም።” አሕዛብን ‘በብረት በትር በመጠበቅ’ ያጠፋቸዋል። ነጭ ልብስ የለበሱትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ግን በፍቅር ይጠብቃል፤ ‘ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም እየመራ’ “ከታላቁ መከራ” ያወጣቸዋል። አንተንም ከእነዚህ አንዱ እንድትሆን እንመኝልሃለን! — ራእይ 19:11–16፤ 7:9, 14, 17

21. በአርማጌዶን ጊዜ እነማን ወደ አንድ ቦታ ይከማቻሉ? ሆኖም ሴራቸው ከንቱ የሚሆነው ለምንድን ነው?

21 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና እርሱን የሚደግፉት ብሔራት እንዲሁም ያከማቹት የወታደራዊ ኃይል ወዮላቸው! በአርማጌዶን ጊዜ ‘ነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠውንና ሰማያዊ ሠራዊቱን ለመውጋት’ ይሰብሰቡ። ይህ ሁሉ ግን በከንቱ ነው! “የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው “በእሳት ባሕር” ውስጥ በመጣል ድምጥማጣቸውን ያጠፋል። በምድር ላይ የሚቀሩ የሰይጣን ድርጅት ርዝራዦች በተመሳሳይ ይደመሰሳሉ፤ ምክንያቱም የንጉሡ ረጅም ሰይፍ የትኛውንም ጠላት ፈልጎ ለመደምሰስ ኃይል አለው። — ራእይ 19:17–21

22. የአርማጌዶንን ውጊያ የአምላክ ነቢያት የሚገልጹት እንዴት ነው?

22 ይሖዋ ከሰማይ በሚያወርዳቸው ፍላፆችና መቅሠፍቶች መንግሥቱን በመቃወም የሚዋጉትን አሕዛብ ሁሉ ይመታቸዋል። እነርሱም ግራ በመጋባት አውዳሚ መሣሪያዎቻቸውን አንዱ በሌላው ላይ እንደሚተኵስ አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ‘እጅም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል’ ተብሏል። አንተ ግን የይሖዋን ስም ከሚጠሩት አንዱ ከሆንህ “ትድናለህ።” — ኢዩኤል 2:31, 32፤ ዘካርያስ 14:3, 12, 13፤ ሕዝቅኤል 38:21–23፤ ኤርምያስ 25:31–33

23. (ሀ) ይህስ ለየትኛው ነገር ታላቅ መደምደሚያ ይሆናል? (ለ) የትኞቹ የኢየሱስ ቃላት ሊያስደስቱን ይገባል?

23 የኢየሱስ ትንቢታዊ “ምልክት” ታላቅ መደምደሚያ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል።” እነዚያ ቀኖች “ስለተመረጡት” ሲባል ‘የሚያጥሩ’ በመሆናቸው ምንኛ ደስተኞች ልንሆን እንችላለን! አንተም ኢየሱስ ‘መንግሥቱን ውረሱ’ በማለት ከሚጋብዛቸው በጎች አንዱ በመሆን ከጥፋቱ ለመትረፍ ትችላለህ። — ማቴዎስ 24:21, 22፤ 25:33, 34

24. (ሀ) በዚያን ጊዜ በሰይጣን ላይ ምን እርምጃ ይወሰዳል? ለምንስ? (ለ)ከዚያስ ምን ይቀጥላል?

24 የአርማጌዶን ጦርነት ሲያበቃ ሰው ምድርን አለ አግባብ እንዲገዛ የቀሰቀሰው ክፉው ሰይጣን ራሱ ይያዝና ይታሰራል፤ “ለአንድ ሺህ ዓመት” በጥልቅ ውስጥ ይጣላል። ለምን? “አሕዛብንም ወደፊት እንዳያስት” ነው። (ራእይ 20:2, 3) ከዚያ በኋላ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ግሩም ዘመን እንደ ንጋት ፀሐይ ይወጣል። ታዲያ ለአምላክ መንግሥት ሲሠሩ ለቆዩትና ‘እንድትመጣ’ ሲጸልዩ ለኖሩት ታማኞች የ1,000 ዓመቱ ግዛት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ይህን ለማወቅ እንደምትፈልግ አያጠራጥርም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 169 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ጋለሞታይቱ” እና “አውሬው”

የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ‘ሰላምና ደኅንነት’ ለማምጣት ከተቋቋመው አውሬ ጋር ምን ዝምድና መሥርታ ቆይታለች? “ታላቂቱ ባቢሎን” በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ድርጅት ውስጥ በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ እጅዋን በማስገባት ተቆጣጣሪ ለመሆን ፈልጋ ነበርን? እስቲ ማስረጃዎቹ መልሱን ይስጡን:-

በ1918 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን ለማቋቋም ዕቅድ ከተያዘ በኋላ በአሜሪካ የሚገኙ የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ፌዴራላዊ ምክር ቤት ያወጣው “አጭር የጽሑፍ ማስታወሻ” እንደሚከተለው በማለት እስከ መናገር ደርሶ ነበር:- “ክርስቲያን እንደ መሆናችን መጠን በሚቀጥለው የሰላም ስብሰባ ላይ የነፃ መንግሥታት የቃል ኪዳን ማኅበር እንዲቋቋም እናሳስባለን። እንደዚህ ያለው የቃል ኪዳን ማኅበር ተራ ፖለቲካዊ መሣሪያ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በምድር ላይ የአምላክ መንግሥት መግለጫ ነው። . . . ድል ተገኝቶ ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ምድር ካልመጣች በስተቀር የሞቱት ጀግኖች ሁሉ በከንቱ ሞተዋል ማለት ይሆናል።”

በ1965 20ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልደት በዓል ሲከበር አሶሽየትድ ፕሬስ ከሳን ፍራንሲስኮ የሚከተለውን ዘገባ አስተላልፎ ነበር:- “በዓለም ዙሪያ ከ2,000 ሚልዮን በላይ አባላት ያሏቸው የሰባት ሃይማኖቶች መሪዎች የተባበሩት መንግሥታት ለዓለም ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ በአንድ ጣሪያ ሥር ሆነውና እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ ጸሎት አቅርበዋል። ፓፓ ጳውሎስ ስድስተኛ ከካቶሊክ፣ ከፕሮቴስታንት፣ ከአይሁድ፣ ከሂንዱ፣ ከቡድሂስት፣ ከእስላምና ከምሥራቅ (ከግሪክ) ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ለተውጣጣው ጉባኤ ከሮም ቡራኬያቸውን ልከዋል። . . . ረቢ ሉዊስ ጃኮብስ . . . ‘የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የዓለም ኅልውና የቆመበትና ዘላቂ ሰላም የሚያገኝበት ብቸኛ ተስፋ ነው’ ሲሉ ገልጸውታል።”

ጥቅምት 1965 ላይ ፓፓ ጳውሎስ ስድስተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ከብሔራት አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ የላቀው ድርጅት” እንደሆነ ከገለጹ በኋላ “የዓለም ሕዝቦች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የስምምነትና የሰላም የመጨረሻ አለኝታ አድርገው በመመልከት ፊታቸውን ወደ እርሱ ዘወር ያድርጉ” ብለዋል።

ጥቅምት 2, 1979 በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዲህ ብለው ነበር:- “እኔ ዛሬ በዚህ ቦታ የተገኘሁበት ዋነኛ ምክንያት የሐዋርያትን መንበረ ፓትርያርክ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በሚያስተሳስረው ልዩ የአንድነት ማሠሪያ ምክንያት ነው። . . . የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛው የሰላምና የፍትሕ መድረክ፣ ሕዝቦችና ግለሰቦች የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ ላላቸው ጉጉት እውነተኛው የነፃነት ፋና ሆኖ እስከ መጨረሻው እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ።” ጳጳሱ ለ62 ደቂቃ ባደረጉት ንግግር ላይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ሆነ መንግሥቱን አንድም ጊዜ እንኳ አልጠቀሱም።

የሐሰት ሃይማኖት በአምላክ መንግሥት ቦታ ሰው ሠራሽ ድርጅቶችን ማስቀመጧ ከንቱ ተስፋ ነው። መዝሙር 146:3–6 [አዓት] በሰብአዊ ገዥዎች ከመመካት እንድንጠነቀቅ ከነገረን በኋላ “ተስፋውም በአምላኩ በይሖዋ የሆነ ሰው ደስተኛ ነው፤ እርሱም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ነው” ብሏል። ሉቃስ 2:10–14 የሰው ልጆች አዳኝ “ክርስቶስ ጌታ” እንደሆነ ይገልጻል።

[በገጽ 173 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአርማጌዶን መዳረሻ የሆኑ ተከታታይ ክንውኖች

● ዓለምን የመግዛቱ ጉዳይ ዐብይ ጥያቄ ይሆናል፤ መንግሥታትም የጦር መሣሪያቸውን ብዛት ይጨምራሉ

● የዓለም ሃይማኖቶች የነበራቸው የሰዎች ድጋፍ ይነጥፋል

● ብሔራት “ሰላምና ደኅንነት” ሆነ የሚል ከፍተኛ ጩኸት ያሰማሉ

● ወታደራዊ የሆኑት የተባበሩት መንግሥታት “አሥር ቀንዶች” የዓለምን ሃይማኖት ያጠፋሉ

● የአውሬ ጠባይ ያላቸው “ቀንዶች” ‘በበጉ’ ተከታዮች ላይ የመጨረሻ ጥቃት ይከፍታሉ

● “የነገሥታት ንጉሥ” አርማጌዶን ላይ ብሔራትንና ሠራዊታቸውን ይደመስሳል

ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ሲጣሉ ክብራማው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል