በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እጅግ ብዙ ሰዎች” ንጉሡን አወደሱት

“እጅግ ብዙ ሰዎች” ንጉሡን አወደሱት

ምዕራፍ 16

“እጅግ ብዙ ሰዎች” ንጉሡን አወደሱት

1, 2. (ሀ) ይሖዋ በኢሳይያስ 60:22 ላይ የሚገኘውን ትንቢት የፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) በ1935 ምን አስደናቂ የሆነ የመለኮታዊ እውነት አዲስ እውቀት ተገለጸ?

ይሖዋ በነቢዩ በኩል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 60:22) እውነትም ይሖዋ በሚያስደንቅ መንገድ ‘አፋጥኖታል።’ በ1935 የይሖዋ ምሥክሮች በዋሽንግተን ዲ ሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ስብሰባ አደረጉ። በዚያ ስብሰባ ላይ ይሖዋ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” መሰብሰብ እንደ ጀመረ ተገለጸ። እነዚህም የአምላክ መንግሥት ‘ስትመጣ’ ገነት በምትሆን ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ናቸው። — ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9

2 ይህንን ራእይ ምዕራፍ 7 እንደሚከተለው ይገልጸዋል:- ቁጥራቸው 144,000 የሆነው መንግሥቲቱን የሚወርሱት “ታናሽ መንጋ” ከታተሙ በኋላ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” በአምላክ ዙፋን ፊት ቆመው ታዩ። እነርሱም የአምላክ ቅቡእ በሆነው ክርስቶስ በኩል የተገለጸውን የይሖዋን ሉዓላዊነት መቀበላቸውን በይፋ ያሳውቃሉ። መዳን የሚገኘው ከአምላክና ከበጉ መሆኑን በደስታ ይናገራሉ። በቡድን መልክ ሲታዩ ሞትን ፈጽሞ አያዩም፤ ምክንያቱም በጸዳችው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ “ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” ተብሎ ተነግሮላቸዋል። — ራእይ 7:4, 9, 10, 14፤ ሉቃስ 12:32

3. (ሀ) “ታናሹ” በእርግጥ “ሺህ” ሆኗልን? (ለ) በራእይ 7:15–17 አፈጻጸም አንተም ድርሻ ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው?

3 አንተስ ዛሬ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከተባሉት ይሖዋን ከሚያመልኩት አንዱ በመሆን ቦታህን ይዘሃልን? በአሁኑ ጊዜ በመላዋ ምድር ላይ ‘ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ ከሚያቀርቡት ከ4,700,000 በላይ ከሆኑት አንዱ ነህን? እርግጥ ነው፤ ክፉና ጨቋኝ የሆነው ዓለም ዙሪያውን የከበበህ ስለሆነ በዕለታዊ ኑሮህ ብዙ ተጽዕኖዎችን መቋቋም ይኖርብህ ይሆናል። ሆኖም ከጌታ “በጎች” አንዱ ከሆንክ በአምላክ ከለላ ሥር ትሆናለህ። ከእንግዲህ ወዲያ መንፈሳዊ ምግብ በማጣት መራብ ወይም መጠማት አያስፈልግህም። በጉ እረኛህ ስለሆነና “ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ” ስለሚመራህ የአምላክን ሞገስ ማጣት ማለት የሆነውን የቁጣው ትኩሳት መፍራት አያስፈልግህም። በዚህ መንገድ “እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል” የሚለው ተስፋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ሲፈጸም ተካፋይ ሆነሃል። — ራእይ 7:15–17

ንጉሡ “በጎቹን” ይባርካል

4. ኢየሱስ ‘ከታናሹ መንጋው’ ጋር ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

4 በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በእኛ ዘመን እረኛ ከበጎቹ ጋር ልክ እንደ ቅርብ ጓደኛቸው ነው። እያንዳንዳቸውን በየስማቸው ይጠራቸዋል። እነርሱም ድምፁን ስለሚያውቁ ወደ በረቱ ሲያስገባቸውም ሆነ ሲያስወጣቸው ወዲያውኑ እሺ ብለው ይታዘዙታል። በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ኢየሱስ ይህንን ሁኔታ በመጀመሪያ በእርሱና “ታናሽ መንጋ” በሆኑት 144,000 ቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ያለውን ፍቅራዊ ዝምድና በምሳሌ ለማስረዳት ተጠቅሞበታል። እንዲህ አለ:- “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፣ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።” እነዚህኞቹ የኢየሱስ በጎች “የምድር ነገዶች ሁሉ” ራሳቸውን የሚባርኩበት “የአብርሃም ዘር” ክፍል ይሆናሉ። — ዮሐንስ 10:14, 15፤ ዘፍጥረት 12:3፤ ገላትያ 3:28, 29

5. (ሀ) በዮሐንስ 10:16 ላይ ምን ሌላ አስደሳች ዝምድና ተጠቅሷል? (ለ) “ሌሎች በጎች” በአሁኑ ጊዜ ምን አስደሳች መብቶችን አግኝተዋል? ለዚህስ ቡድን የተዘጋጀው የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው?

5 ታዲያ “መልካሙ እረኛ” በምድር ላይ ለዘላለም ከሚኖሩት የሰው ዘሮች ጋር የሚኖረው ዝምድና ምንድን ነው? እጅግ በጣም የተባረከ ዝምድና ነው! ምክንያቱም ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:-

“ከዚህም በረት [ከታናሹ መንጋ በረት ] ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።”

ዛሬ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘ከታናሽ መንጋ’ ጋር ለግጦሽ ተሰማርተው ማየት ይቻላል። ሁሉም በአንድነት የእረኛቸውን ድምፅ በመስማት ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ምሥራች’ በመላዋ ምድር ላይ ለሚኖሩ ለሁሉም ሕዝቦች ይሰብካሉ። ከእነዚህ አንዱ ከሆንክ በጣም ታድለሃል! (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 24:14) አምላክ ምድርን በጻድቃን ሰዎች ለመሙላት ያለው ዓላማ በመንግሥቱ ሥር ወደ ፍጻሜው ሲጓዝ በምድር ላይ ያሉት ሙታን ትንሣኤ ስለሚያገኙ ‘የሌሎች በጎች’ ቁጥር በብዙ ቢልዮን መቆጠር እስኪችል ድረስ በጣም ይጨምራል። — ዘፍጥረት 1:28

6. “ሌሎች በጎች” መቼ ጐላ ብለው መታየት እንደሚጀምሩ የኢየሱስ ትንቢት ያመለከተው እንዴት ነው?

6 “ሌሎች በጎች” ጐላ ብለው የሚታዩት “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ዘመን ላይ ለመሆኑ ኢየሱስ መገኘቱን ስለሚያረጋግጠው “ምልክት” በተናገረበት ትንቢት መዝጊያ ላይ የሰጠው ምሳሌ ያሳያል። (ማቴዎስ 24:3) እንዲህ አለ:-

“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።” (ማቴዎስ 25:31–33)

የላቀ ክብር የተቀዳጀው ንጉሥም ሆነ መላእክቱ ከሰው ዓይን የተሰወሩ ናቸው። ታዲያ ሰዎችን በየወገኑ የመለያየቱን ሥራ የሚያከናውነው እንዴት ነው?

7. (ሀ) ሰዎችን በሁለት ወገን የመለያየቱ ሥራ የሚካሄደው እንዴት ነው? (ለ) ጥሩ ፍርድ ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባሃል? ለምንስ?

7 ቅዱሳን መላእክት ለዚህ ሥራ አመራር ይሰጣሉ። (ራእይ 14:6–12፤ ከሥራ 8:26–29፤ 10:1–8 ጋር አወዳድር።) ገና ምድር ላይ ያሉት በማቴዎስ 25:40 ላይ የንጉሡ “ወንድሞች” ተብለው የተጠሩት “የታናሽ መንጋ” ቀሪዎችም “ምሥራቹን” በመስበኩ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው ይመራሉ። ንጉሡም ሰዎችን የሚዳኘው ‘ለወንድሞቹ’ እና እነሱ ለሚሰብኩት መልእክት በሚሰጡት ምላሽ መሠረት ይሆናል። ‘ለወንድሞቹ’ የተደረገውን ነገር ለእርሱ እንደተደረገ አድርጎ ይቆጥረዋል። የንጉሡን “ወንድሞች” በጥሩ መንፈስ የሚቀበሉ ሰዎች በረከቶች ይጠብቋቸዋል። ታዲያ ከእነዚህ አንዱ ነህን? እርግጥ የመንግሥቱን መልእክት ከሰማህ በኋላ በሙሉ ልብ በመቀበልና ‘መዳን በሌላ በማንም ስለሌለ’ በኢየሱስ ስም ራስህን ለይሖዋ የወሰንክና የተጠመቅህ አገልጋዩ መሆን ይኖርብሃል። — ሥራ 4:12፤ ማቴዎስ 25:35–40

8. በምን ግብዣና ተስፋዎች ተካፋይ ልትሆን ትችላለህ?

8 ከጌታ “ሌሎች በጎች” አንዱ እንደመሆንህ ወደፊት ምን አገኛለሁ ብለህ ልትጠብቅ ትችላለህ? ‘የመልካሙን እረኛህን’ እና ‘የንጉሥህን’ “ድምፅ” ሰምተህ ስትታዘዝ የምታገኘው ውጤት ምን ይሆናል? ንጉሡ ፍርዱን ሲያስታውቅ ሞገስን በሚያመለክተው ቀኙ በኩል ላሉት ትሑታን “በጎች”:- “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ይላቸዋል። ‘ጻድቃን ወደ ዘላለም ሕይወት ሲሄዱ’ ከአባታችን የሚዘንቡትን እነዚህን በረከቶች ከሚካፈሉት አንዱ እንደምትሆን ልትጠብቅ ትችላለህ። (ማቴዎስ 25:34, 46) አዎን፣ በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰውን የመሰሉ ብዙ ትንቢታዊ ተስፋዎች ሲፈጸሙ አንተም ተካፋይ ለመሆን ልትጠብቅ ትችላለህ። ትንቢቱ ስለ ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።” ክፉ ሰዎች የሚሰድቡህ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በይሖዋ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ በቅርቡ ‘በአዲስ ምድር’ ላይ መልካም ነገሮች ወደሚትረፈረፉበት “ግብዣ” እንደሚገቡ አምላክ ቃል ገብቷል። በዚያ ግብዣ ተካፋይ ለመሆን ትፈልጋለህ፤ አይደለም እንዴ? — ኢሳይያስ 25:6–9፤ 66:22

“ፍየሎች” እና ስደቶች

9, 10. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ጽድቅን መከተል ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ለተቃዋሚዎች ሊኖርህ የሚገባው ዝንባሌ ምንድን ነው? ከአምላክስ ምን እርዳታ ልትጠብቅ ትችላለህ?

9 በእነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” የጽድቅን መንገድ መከተሉ ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። ሰይጣንና እርሱ አታሎ እጁ ውስጥ ያስገባቸው ሰዎች ምድርንና በላይዋ ላይ የሚገኘውን የሰው ዘር ለማጥፋት የመጨረሻ ሙከራቸውን በሚያደርጉበት ባሁኑ ጊዜ ይዘብቱብህ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) የመንግሥቱን መልእክት ይዘህ በአካባቢህ ያሉትን ሰዎች ለማነጋገር ስትሞክር የፍየል ዓይነት ባሕርይ የሚያሳዩ ሰዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ይህንንም የሚያደርጉት ለመልእክቱ ደንታ ቢስ በመሆን፣ ወይም ክፉ ቃል በመናገር፣ ወይም የለየለት ተቃውሞ በማሳየት ነው። — ማቴዎስ 25:33, 42–45

10 ይሁን እንጂ ከጌታ “በጎች” እንደ አንዱ ሆነህ ስትሠራ ይህ ሰው ወይም ያ ሰው “ፍየል” ነው ብለህ ለመፍረድ መሞከር አይገባህም። የመፍረድ ሥልጣን ያለው ንጉሡ ነው እንጂ በዚህ ምድር ላይ ያሉት “በጎች” አይደሉም። (ከሮሜ 14:10–12 ጋር አወዳድር።) “የምሥራቹ” ሰባኪ በመሆንህ ምክንያት ተቃውሞ ቢያጋጥምህ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት እንዳመለከተው አምላክ ያጠነክርሃል:- “የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችኋል ያበረታችሁማል።” (1 ጴጥሮስ 5:10፤ ከ2 ቆሮንቶስ 12:10 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ጥሩ ምክር ይሰጣል:- “ለ[መንግሥቱ] ሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።” — ሮሜ 12:11, 12

11. ምሳሌነት ያለው ክርስቲያናዊ ጠባይ ማሳየት ምን አስደሳች ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

11 በመጀመሪያ “ፍየሎች” መስለው የታዩት ሰዎች ከይሖዋ ጐን በታማኝነት በመቆም በምታከናውነው አገልግሎትና ልባዊ ጸሎት በማቅረብህ፣ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ጠባይ በምታሳየው ምሳሌነትህ ተስበው “በጎች” ሊሆኑ ይችላሉ። ክርስቲያን ሚስቶች የትዕግሥትና የአክብሮት ጠባይ በማሳየታቸው ብዙ የማያምኑ ባሎች “ያለ ቃል” ወደ እውነት መጥተዋል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ‘ሰዎች ወደ ዘላለም ጥፋት ሲሄዱ’ ለመመልከት እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ የፍየል ዓይነት አቋማቸውን ጨርሶ በመተው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ልንረዳቸው መፈለግ ይኖርብናል። — ማቴዎስ 25:41, 46

ታማኞቹ “በጎች” ፍጹም አቋማቸውን አያጐድፉም

12. የንጉሡ “ወንድሞች” እና “በጎቹ” በዘመናችን እርስ በርስ የተረዳዱት እንዴት ነው?

12 በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት “በጎች” የንጉሡ “ወንድሞች” ታመውና ታስረው በነበሩበት ጊዜ ሄደው እንዳገለገሏቸው ማስታወስ ያስፈልጋል። ዛሬ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች እጦት፣ ስደት፣ በሽታና እስር ‘በታናሹ መንጋ’ ላይ ብቻ ሳይሆን ከጐናቸው ቆመው በታማኝነትና በአንድነት በሚያገለግሉት ‘ሌሎች በጎችም’ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል የናዚው ሂትለር ዓለምን ለመግዛት በተነሣባቸው ከ1933 እስከ 1945 በነበሩት ዓመታት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በመጀመሪያ በናዚና በፋሺስት አገሮች፣ በኋላም በተዋጊዎቹ አገሮች በሙሉ መራራ ስደቶች ደርሰውባቸዋል። ‘ከታናሹ መንጋ’ ክፍልም ሆነ የጌታ “ሌሎች በጎች” ከሆኑት ውስጥ ብዙዎች ተገድለዋል። ቢሆንም ለንጉሡና ለመንግሥቱ ያላቸውን ንጹሕ አቋም ሳያጐድፉ በመቆም አስደናቂ ድል ተቀዳጅተዋል።

13, 14. በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች አቋምና በይሖዋ ምሥክሮች አቋም መካከል ምን ልዩነት ተስተውሏል?

13 ተጽዕኖ በሚደርስበት ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ባሳዩት የአቋም መላላትና የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩት የአቋም ጽናት መካከል ያለውን ልዩነት ብዙ ጊዜ የታሪክ ሰዎች አስተያየት ሰጥተውበታል። ለምሳሌ ያህል በ1976 በለንደን፣ እንግሊዝ አገር በታተመው ኤ ሒስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ (የክርስትና ታሪክ ) በተባለው መጽሐፍ ላይ ፖል ጆንሰን በሂትለር በምትገዛው ጀርመን ውስጥ ስለነበሩት የካቶሊክና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ብለዋል:- “በተለይ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ለአገዛዙ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተዋል። የካቶሊክ ጳጳሳት ‘በጀርመን መንግሥት ውስጥ የተፈጠረውን አዲስና ጠንካራ የሥልጣን ኃይል’ እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውታል። ጳጳስ ቦርንዋሰር በትራየር ካቴድራል ለተሰበሰቡ ወጣቶች እንዲህ ብለው ነበር:- ‘ራሳችንን ቀና አድርገን በቆራጥ እርምጃ ወደ አዲሱ መንግሥት ዘመን ገብተናል። በአካላችንና በነፍሳችን ኃይል ሁሉ ልናገለግለውም ተዘጋጅተናል።’ በጥር ወር 1934 ሂትለር ከአሥራ ሁለት የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ተገናኝቶ ነበር። ከዚህም ስብሰባ በኋላ . . . ‘የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሦስተኛው ንጉሣዊ አገዛዝና ለመሪው ያላቸውን ፍጹም ታማኝነት የሚያረጋግጥ’ አንድ መግለጫ አወጡ።”

14 በመቀጠልም ጸሐፊው “የቆምንለትን መሠረታዊ ሥርዓት በፍጹም አናፈርስም” ብለው ስለተጋፈጡት ክርስቲያኖች በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል:- “ከእነዚህ ሁሉ በድፍረታቸው ወደር የሌላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የመሠረተ ሐሳብ ተቃውሞ ይዘው ተጋተሩ። በዚህም ምክንያት ብዙ ሥቃይ ደረሰባቸው። ሙሉ በሙሉ ዲያብሎሳዊ እንደሆነ አድርገው ካወገዙት የናዚ መንግሥት ጋር በምንም ዓይነት ለመተባበር አሻፈረን አሉ። . . . ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት እምቢ በማለታቸው ብዙዎች ሞት ተፈረደባቸው፤ . . . ወይም በዳካው ማጎሪያ ካምፕ ወይም የአእምሮ ሕመምተኞች በሚታከሙባቸው ቦታዎች እንዲታጐሩ ተደርገዋል። አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ተገድለዋል፤ በዚህም ሆነ በዚያ ዘጠና ሰባት በመቶ የሚሆኑት ስደት ደርሶባቸዋል። ከሂምለር አድናቆትን ያተረፉት የክርስቲያን ቡድን እነርሱ ብቻ ነበሩ።”

15. (ሀ) ብዙዎች ለጻፏቸው ደብዳቤዎች ናሙና የሚሆነውን እዚህ ላይ ያለውን ደብዳቤ ስታነብ እንዴት ይሰማሃል? (ለ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሰይጣን ምን ጥረት አድርጎ ነበር? ጥረቱ ለመክሸፉ ምን ማስረጃ አለ?

15 የሰላም ታጋዮች በመሆን ሳይሆን መጪውን የአምላክ መንግሥት የሚደግፉ ክርስቲያን ገለልተኞች በመሆን ወጣት ምሥክሮች ፍጹም አቋሟቸውን ከማጉደፍ ይልቅ እስራትንና ሞትን ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል። ለዚህም ምሥክር የሚሆን ለአንድ ቤተሰብ የተጻፈ ‘የመጨረሻ ደብዳቤ’ እዚህ ላይ ትመለከታላችሁ። በጀርመንና በደጋፊዎቿም ሆነ ኅብረት በፈጠሩት አገሮች ውስጥ የንጉሡ “ወንድሞች” እና ጓደኞቻቸው የሆኑት “በጎች” በዓለም ዙሪያ በሕዝብ ረብሻ ተፈጥሮባቸዋል፣ በዱላ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተንገላተዋል። ቢሆንም በመንፈሳዊ ውጊያቸው አሸናፊ ሆነዋል። ዲያብሎስ ለመንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነት ለመስበር አልቻለም። ከእነርሱ በፊት እንደነበረው እንደ ኢየሱስ እነርሱም የሰይጣን ዓለም ‘ክፍል እንዳልሆኑ’ አሳይተዋል። — ዮሐንስ 15:19

የመንግሥቲቱ የትምህርት መርሐ ግብር

16, 17. (ሀ) በዚህ ጊዜ ምን የትምህርት ፕሮግራም ተዘርግቶ የሥራ መስፋፋት መጣ? (ለ) የዚህን ሥራ ምን ፍሬ ነው ማየት የሚቻለው?

16 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በ1942 ሲሞት በቦታው ናታን ኤች ኖር ተተካ። ብዙም ሳይቆይ በሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቶች ተቋቋሙ። እነዚህም ትምህርት ቤቶች ወንዶችና ሴቶች የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ይበልጥ ውጤታማና አሳማኝ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንዲችሉ ይህ ነው የማይባል እገዛ አድርገውላቸዋል። ባለፉት ዓመታት ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ የተለያዩ መጻሕፍት ወጥተዋል። የሚሲዮናዊውም መስክ ቢሆን አልተረሳም። የካቲት 1, 1943 በኒው ዮርክ ክፍለ ሀገር ውስጥ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተቋቋመ። ከብዙ አገሮች የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሞክሮ ያላቸው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች (“አቅኚዎች”) ወደ አሜሪካ መጥተው ከሠለጠኑ በኋላ “ይህን የመንግሥት ምሥራች” ለመስበክ ወደ ‘ሁሉም የምድር ክፍል’ ተልከዋል። — ማቴዎስ 24:14፤ ሮሜ 10:18

17 ከዚህ ምድር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ በጣም አስገራሚ የሆነ ፍሬ ተገኝቷል። ወደ 1990ዎቹ ዓመታት ስንገባ ብዙዎቹ የንጉሡ “ወንድሞች” ምድራዊ ጉዞአቸውን ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እየጨረሱ ስለሄዱ በዓመታዊው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ተስፋቸው በሰማያዊው መንግሥት ከእርሱ ጋር መተባበር መሆኑን ለማሳየት ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ከ9,000 ዝቅ ብሏል። ይሁን እንጂ የመንግሥቲቱ ተገዢዎች በመሆን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ፍላጎት ያላቸው የሌሎቹ ተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ11,000,000 በላይ ሆኗል። በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ በሚገኙት ከ70,000 በላይ በሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የምሥክርነቱን ሥራ በአመዛኙ እያከናወኑ ያሉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው። ከእነዚህ አንዱ በመሆንህ እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ተከፍቶልሃል!

18. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” አገልግሎቱን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ በየትኛው ከፍተኛ ሥራ ልትካፈል ትችላለህ?

18 “ታማኝና ልባም ባሪያ” የተባሉት የኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” ክፍል የሆኑ ቅቡዓን ቀሪዎች ቁጥራቸው እየቀነሰ ቢሄድም እንኳን የመንግሥቱን ሥራ በበላይነት መምራታቸውን ቀጥለዋል። (ማቴዎስ 24:45–47) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይህንን ለማከናወን ከመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አደረጃጀት ጋር በሚመሳሰል ዝግጅት ይኸውም በአስተዳደር አካሉ አማካኝነት ይጠቀማል። (ሥራ 15:6፤ ሉቃስ 12:42–44) ኤን ኤች ኖር በ1977 ሲሞት ኤፍ ደብልዩ ፍራንዝ በ83 ዓመት ዕድሜው አራተኛው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ሆነ። ሐምሌ 1, 1979 ላይ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት መታተም ከጀመረ 100 ዓመት ሞልቶታል። ከመጽሔቱ በስተጀርባ የመቶ ዓመት የመንግሥት ምሥክርነት ታሪክ አስጽፏል። አዎን፤ በታተሙ ጽሑፎችና በአፍ በሚነገር ቃል ስለ ተቋቋመችው መንግሥት የሚገልጸው ይህ “ምሥራች” ምሥክር እንዲሆን በዓለም ሁሉ ታውጆአል። ኢየሱስ የተወልንን ምሳሌ በመከተል በዚህ ልዩ መብት በሆነው ሥራ ከሚካፈሉት አንዱ ነህን? ጳውሎስ እንዳሳሰበው:-

“እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት።” — ዕብራውያን 13:15

19. (ሀ) ጳውሎስ “ልብን” እና “አፍን” በሚመለከት ምን ማበረታቻ ሰጠ? (ለ) እዚህ ላይ ምን ወቅታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ቀርበዋል? ምን ምላሽስ ትሰጣለህ?

19 ሐዋርያው ጳውሎስ በሌላ ደብዳቤው ላይ “ለመጽደቅ ሰው በልቡ ያምናል፤ ለመዳንም በአፉ ለሕዝብ ምሥክርነት ይሰጣል” ሲል ገልጾ ነበር። (ሮሜ 10:10 አዓት) አንተስ ከ1914 ጀምሮ በሰማይ በተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት ላይ የሚያተኩረውን “ምሥራች” ታምንበታለህን? የአምላክ መንግሥት ከምድር ላይ የሰይጣንን ድርጅት ለመደምሰስ አጥፊ ኃይልዋን ሁሉ ይዛ ‘እንድትመጣ’ እየጸለይክ ‘ለመዳን ለሕዝብ ትመሠክራለህን?’ ‘የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በቅርቡ በምድር ላይም ሲሆን’ ለሰው ዘር በሙሉ ስለሚፈስሱት የመንግሥት በረከቶች ‘በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት’ በመሄድ በቅንዓት ትናገራለህን? የመንግሥቱን መልእክት “በምድር ሁሉ ላይ . . . እስከ ምድር ዳርቻ” በማሰማት የመሪነቱን ቦታ ይዞ ወደፊት እየገሰገሰ ያለውን፣ ‘አሕዛብን ሁሉ እያስተማረ ደቀ መዛሙርት በማድረግ’ ላይ የሚገኘውን፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቡድን፣ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ስብስብ የሆነውን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በታማኝነት በመደገፍ ላይ ነህን? — ማቴዎስ 6:10፤ 24:14, 45–47፤ 28:19, 20፤ ሥራ 5:42፤ 20:20፤ ሮሜ 10:18

20. በአሁኑ ጊዜ ምን ታላቅ መብት አግኝተህ መደሰት ትችላለህ?

20 በዛሬው ጊዜ ‘በአምላክ ዙፋን ፊት በዚህ መንገድ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ’ ታላቅ መብት ልታገኝ ትችላለህ። በዚሁም ላይ ውብ በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ከሚወርሱት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጐን ትሰለፋለህ። (ራእይ 7:9–17) በመጀመሪያ ግን መንግሥቲቱ ከአርማጌዶን ጦርነት ጋር ‘መምጣት’ ይኖርባታል! አርማጌዶን ለሰው ዘርና ለምድራችን ምን ማለት ይሆናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 159 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እስከ ሞት ድረስ ገለልተኛ መሆን

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ገለልተኝነት አቋማቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሕይወታቸውን ሠውተዋል። ቀጥሎ ያለው ደብዳቤ ደፋር የሆኑ ምሥክሮች ለቤተሰቦቻቸው ከጻፏቸው ከብዙዎቹ ‘የመጨረሻ ደብዳቤዎች’ አንዱ ነው። ይህ ደብዳቤ በነሐሴ ወር 1942 በጀርመን አገር በቶርጋው እስር ቤት በመጥረቢያ አንገቱ ተቆርጦ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በአልሴስ ሎሬይን ነዋሪ በነበረው የ23 ዓመት ወጣት በማርሴል ሱተር የተጻፈ ነው።

“በጣም የምወዳችሁ ወላጆቼና እኅቶቼ፣

“ይህ ደብዳቤ ሲደርሳችሁ እኔ በሕይወት የለሁም። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እሞታለሁ። ብርቱና ደፋሮች እንድትሆኑ እለምናችኋለሁ፤ ድል አድርጌአለሁና አታልቅሱ። ጉዞዬን ጨርሻለሁ፤ እምነቴንም ጠብቄአለሁ። እስከ መጨረሻው ድረስ ይሖዋ አምላክ ይርዳኝ። ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ለመግባት የቀረን ጊዜ አጭር ነው። በቅርቡ በተሻለ የሰላምና የጽድቅ ዓለም ውስጥ እንገናኛለን። ያንን ቀን ሳስበው እደሰታለሁ፤ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ምንም ኀዘን የለም። ምንኛ አስደናቂ ቀን ይሆናል! ሰላምን እናፍቃለሁ። በእነዚህ የመጨረሻ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ስለ እናንተ ብዙ አሰብሁ። ስሜያችሁ ለመሰነባበት ባለመቻሌ ልቤ ትንሽ ከፍቶታል። ቢሆንም መታገሥ ይኖርብናል። ይሖዋ ስሙን የሚቀድስበትና ለሁሉም ፍጥረታት እውነተኛው አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጊዜ ቀርቧል። አሁን የቀረችኝን የመጨረሻ ሰዓት ለእርሱ ለመስጠት እፈልጋለሁ። ስለዚህ በቅርቡ እንደገና እስከምንገናኝ ድረስ ደህና ሁኑ ብዬ ይህን ደብዳቤ እዘጋለሁ። አምላካችን ይሖዋ የተባረከ ይሁን! ከጋለ ፍቅርና ከሰላምታ ጋር፣

“የምትወዱት ልጃችሁና ወንድማችሁ፣

ማርሴል”