በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንግሥቲቱ መምጣት ለምድራችን የሚኖረው ትርጉም

የመንግሥቲቱ መምጣት ለምድራችን የሚኖረው ትርጉም

ምዕራፍ 3

የመንግሥቲቱ መምጣት ለምድራችን የሚኖረው ትርጉም

1, 2. የመንግሥቲቱ መምጣት አምላክ ለምድርና ለሕዝቦችዋ እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

የኢየሱስ የናሙና ጸሎት በመቀጠል “መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ይላል። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ ለምድራችን፣ አሁን በእርስዋ ላይ ለሚኖሩትና ከዚህ በፊት ለኖሩት ሁሉ በጥልቅ ያስባል። መንግሥቲቱ የምትመጣውም ለዚህ ነው። ‘ምድርን የሚያጠፉትን ለማጥፋት’ የሞቱትን ለማስነሣት፣ ጠላታችንን ሞትን አስወግዳ ምድራችንን አስደሳችና ሰላማዊ የሰው ልጆች መኖሪያ ለማድረግ መንግሥቲቱ ትመጣለች። — ራእይ 11:15, 18፤ 21:1, 3, 4

2 እንግዲያው “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለውን ጸሎት እንዴት ባለ የጉጉት ስሜት መጸለይ ይገባናል! ይህች መንግሥት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራ የአምላክ መንግሥት ነች። በእርስዋ አማካኝነት “የዘላለም ንጉሥ” የይሖዋ ዓላማ ያለ ጥርጥር በዚህች ምድር ላይ ይፈጸማል። ለሁሉም ብሔራት ሕዝቦች ይህ ምን ማለት እንደሚሆን እስቲ እንመልከት።

“የሰላሙ መስፍን” በመግዛት ላይ ነው

3, 4. (ሀ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትኞቹን ትንቢታዊ ቃላት ለራሱ አውሎ ሳይሳካለት ቀርቷል? ለምንስ? (ለ) ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችለው ምን ብቻ ነው? በምንስ አማካኝነት?

3 አንዱ የአምላክ ነቢይ ወደፊት የሚቋቋመውን የክርስቶስ መንግሥት አሻግሮ በመመልከት ክርስቶስን ‘የሰላም መስፍን’ በማለት ይገልጸውና ‘ለመስፍናዊ አገዛዙና ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም’ ይላል። ይኸው ነቢይ “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም [ጦርነትም] ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” በማለት ያረጋግጥልናል። እነዚህ በመጨረሻው የተጠቀሱ ቃላት ከተባበሩት መንግሥታት ፊት ለፊት ያለውን ጎዳና ተሻግሮ በሚገኝ አደባባይ ውስጥ በአንድ ግንብ ላይ የተቀረጹ ቢሆንም ትንቢቱን የሚፈጽመው ይህ አምባጓሮ የከፋፈለው ዓለም አቀፍ አካል አይደለም፤ ምክንያቱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመንግሥታት መካከል ሰላምንና ደኅንነትን ማስፈን ተስኖታል። — ኢሳይያስ 2:4፤ 9:6, 7

4 እውነተኛና ዘላቂ ሰላም አለ ለማለት የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው ፍትሕ ሲያገኝና ጽድቅ በሥራ ላይ ሲውል ብቻ ነው። ይህን ዓይነት ሁኔታ ለማምጣት ዋስትና ለመስጠት የምትችለው “የሰላሙ መስፍን” መንግሥት ብቻ ናት። ይህች መንግሥት ‘ጥብቅ መሠረት ያላትና በጽድቅ ላይ የቆመች’ ትሆናለች። አዎን፣ ‘በምድር ላይ የአምላክ በጎ ፈቃድ’ ባላቸው ሰዎች መካከል ሰላምን የምታመጣው የአምላክ መሣሪያ ይህች መንግሥት ነች። — ኢሳይያስ 9:7፤ 32:17፤ ሉቃስ 2:14

5. መንግሥቲቱ እውነተኛ ሰላም ስታመጣ ምን አስደናቂ ነገሮችን ታከናውናለች?

5 መንግሥቲቱ ይህን ሁኔታ የምታመጣው እንዴት ነው? ይህ የሚሆነው በተለይ ‘በሰላሙ መስፍን’ የምትመራው የአምላክ መንግሥት ጦርነት ወዳድ በሆኑት የዓለም መንግሥታት ላይ መጥታ እርምጃ በመውሰድ ነው። መዝሙር 46:8, 9 [አዓት] የሚከተለውን ግብዣ ያቀርብልናል:- “የይሖዋን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም አስደናቂ ታሪክ እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፣ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይሰባብራል፤ (የጦር) ሠረገላን በእሳት ያቃጥላል።” መንግሥቲቱ የዓመፅ መሣሪያዎችን ሁሉ ታስወግዳለች። ከዚህም ሌላ ክፉ ወንጀለኞችና ሰውን አስገድደው የሚደፍሩ ሰዎች በየመንገዱ እንዲያደቡ አትፈቅድላቸውም፤ ምክንያቱም በአምላክ መንግሥት ሥር “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” — መዝሙር 37:9–11

አንድ ትንቢታዊ ምሳሌ

6. በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ታላቅ ፍጻሜ አግኝቷል?

6 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከጥንቷ እስራኤል በጠላት መማረክ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ባቢሎንን ለ70 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ታማኝ እስራኤላውያን ቀሪዎች በ537 ከዘአበ ወደ ገዛ ምድራቸው ተመለሱ። በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ምድሪቱ ባድማ ሆና ስለቆየች ወደ ምድረ በዳነት ተቀይራ ነበር። አሁን ግን የይሖዋ በረከት በሕዝቡ ላይ በመሆኑ አስደናቂ የሆነ ለውጥ እየተደረገ ነበር። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፈ አንድ ትንቢት ወደ ታላቅ ፍጻሜው መጣ:-

“ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሃውም ሐሴት ያደርጋል እንደ ጽጌረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፣ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርን ክብር፣ የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።” — ኢሳይያስ 35:1, 2 በተጨማሪም ኢሳይያስ 65:18–25⁠ን፤ ሚክያስ 4:4⁠ን ተመልከት።

7. እንግዲያው የአምላክ መንግሥት ስትመጣ ለምድራችን ምን ነገር ለመጠበቅ እንችላለን?

7 ታሪክ እንደሚመሰክረው የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ነፃ ከወጡ በኋላ ባለው መቶ ዘመን ውስጥ እነዚህ ትንቢቶች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው በተመለሱት ላይ አስደናቂ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ልጆች ሁሉ ለመባረክ ‘በምትመጣበት’ ጊዜ ገነታዊ ሁኔታዎችን ለምድራችን ለመመለስ የምታደርገው ከዚህ ያነሰ ነገር ይሆናልን? መልሱ በሚያስተጋባ ድምፅ አይሆንም የሚል ነው። መንግሥቲቱ የሰው ልጆች ምድርን እንዲገዙ፣ መላዋንም ምድር ወደ ኤደናዊ ገነትነት እንዲለውጧት አምላክ ያወጣውን የመጀመሪያ ዓላማ በእርግጥ ወደ ፍጻሜው እንዲደርስ ታደርጋለች። — ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8–14፤ ኢሳይያስ 45:18

ምድር አቀፍ ገነት

8. በመንግሥቲቱ ሥር ምግብንና የነዳጅ አቅርቦትን በተመለከተ ምን ነገር ይሆናል? ይህስ የሚሆነው የትኛውን ሕግ በሥራ ላይ በማዋል ነው?

8 የአምላክ መንግሥት ‘ስትመጣ’ የምግብ እጥረትና የገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል አይኖርም፤ ምክንያቱም ‘በምድር ላይ ብዙ እህል ይኖራል፣ በተራሮችም ጫፍ ላይ ይትረፈረፋል።’ አፍቃሪው አባታችን እንደገና ‘እንጀራን ከምድር ያወጣል፣ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኘውንም ወይን ከምድር ያወጣል፤ ፊትም በዘይት እንዲወዛ ያደርጋል። የሰውን ጉልበት የሚያጠነክረውንም እህል ይሰጣል።’ (መዝሙር 72:16፤ 104:14, 15) በሕዝቦች መካከል ምግብን የማከፋፈል ምንም ችግር አይኖርም። ራሽን የለም፤ ነዳጅ ለማግኘት መሰለፍ አያስፈልግም። ስግብግብ ትርፍ አግበስባሾች ይወገዳሉ። ሁሉም የሰው ዘር “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ በመታዘዝ ሁሉንም ነገር እንደ አስፈላጊነቱ እርስ በርሳቸው ይካፈላሉ። — ያዕቆብ 2:8

9. በዚያን ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ምንም ነገር እንደማይኖር ምን ዋስትና አለ?

9 ከዚህም በላይ እንደ ምድር መናወጥና ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ያሉትን ድንገተኛ የተፈጥሮ ክስተቶች መንግሥቲቱ እንደምትቆጣጠር ለመጠበቅ እንችላለን። ኢየሱስ ‘ብርቱ አውሎ ነፋስን’ ጸጥ ባደረገ ጊዜ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ “ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት” መሆኑን አስተውለዋል። (ማርቆስ 4:37–41) በመላው የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ውስጥ ብልሽትና ጉዳት ወይም ጥፋት የሚያስከትል ምንም ነገር አይኖርም። — ከኢሳይያስ 11:6–9 ጋር አወዳድር።

10. ኢየሱስ ያደረጋቸው ብዙ ተአምራት መንግሥቲቱ ወደፊት ስለምታከናውናቸው ነገሮች ምን የሚጠቁሙት ነገር አለ?

10 ከዚያ በኋላ የአካልና የአእምሮ ሕመምተኞችን ለማስተናገድ የተሰናዱ ታላላቅ ሆስፒታሎች አያስፈልጉም። ታላቁ ሐኪም ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ “አሕዛብን ለመፈወስ” ስለሚጠቀምበት የልብ ሕመም፣ ካንሰርና ሌሎች ሽባና አካለ ጎዶሎ የሚያደርጉ በሽታዎች ይጠፋሉ። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የታመሙትን በመፈወስና ሙታንን በማስነሣት ያደረጋቸው ብዙ ተአምራት ኃያል በሆነው መንግሥታዊ አገዛዙ ከሚያከናውናቸው ነገሮች ጋር ሲወዳደሩ ጨረፍታ ብቻ ናቸው። “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚል ማረጋገጫ ስለተሰጠን የተወረሰው የሰው ዘር ሟችነት እንኳ ሳይቀር ይወገዳል። — ራእይ 21:4፤ 22:1, 2፤ ማቴዎስ 11:2–5፤ ማርቆስ 10:45፤ ሮሜ 5:18, 19

11. የኢየሱስ ንጉሣዊ አገዛዝ ምን የደስታ አክሊል ያስገኛል?

11 ከዚያም የሚያስፈነድቅ ደስታ ይመጣል! የመቃብር ሥፍራዎች ባዶ ስለሚሆኑ ከዚያ ወዲያ የምድርን መልክ አያበላሹም። በትንሣኤ “በኩራት” የሆኑት 144,000ዎቹ ታማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንግሥቱ አስተዳደር ተካፋይ በመሆን በሰማይ አብረውት ይሆናሉ። ከዚያም የቀሩት ሙታን ይኸውም ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው በትንሣኤ ይወጣሉ’ በማለት ኢየሱስ የሰጠው አስደናቂ ተስፋ ይፈጸማል። እነዚህ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ የመንግሥቲቱ ተገዢ በመሆን ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና የመመለስ አስደሳች አጋጣሚ ይኖራቸዋል። — ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 14:1–5፤ 20:4–6, 11, 12

12. (ሀ) በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር መፈለግ ያለብህ ለምንድን ነው? (ለ) በገነት ውስጥ ለመኖር በዮሐንስ 17:3 መሠረት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 ይህች ምድር ከክፋት ሁሉ ጸድታና ወደ ደስታ ገነትነት ተለውጣ ለማየት በሕይወት ከሚኖሩት አንዱ ለመሆን ትመኛለህን? ከሞት የሚነሡትን ለመቀበል እዚሁ ለመቆየት ትመኛለህን? ማንም በእርጅና ምክንያት እየደከመ በማይሄድባት ወይም የእያንዳንዱ ቀን ሕይወት የሚያስገኛቸው አስደሳች ነገሮች አሰልቺ በማይሆንባት ውብ በተደረገች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህን? አምላክ ሕይወት ማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ ያወጣቸውን ብቃቶች በማሟላት እነዚህን ልታገኝ ትችላለህ። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንደሚከተለው በማለት ይህንን ብቃት በአጭሩ አስቀምጦታል:- “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም።) ‘ውሃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የይሖዋን ክብር በማወቅ በምትሞላበት’ በዚያን ጊዜ በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ምንኛ ታላቅ መብት ይሆናል! — ዕንባቆም 2:14

“የዕለት እንጀራችንን”

13. “የዕለት እንጀራችንን” ለማግኘት በትምክህት ለመጸለይ የምንችለው ለምንድን ነው?

13 ይሁን እንጂ እኛን ዛሬ በጥልቅ የሚያሳስበን አሁን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማግኘቱ ነው። ብዙዎቻችን መተዳደሪያ ገንዘብ ማግኘትና ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማቅረብ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ስለዚህ አብ መንግሥቱን በማምጣት ታላቁን ስሙን እንዲቀድስና ፈቃዱን በምድር ላይ እንዲፈጽም ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች፤ ‘ስለ ዕለት እንጀራችንም’ ጭምር ወደ አምላክ መጸለይ ያስፈልገናል። ይህን ጸሎት በሙሉ ትምክህት ማቅረብ እንችላለን ምክንያቱም በአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመራን ለመኖር ከጣርንና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በሕይወታችን ውስጥ ካስቀደምን አምላክ ታላቅ ሰጪ እንደመሆኑ የበኩሉን ያደርጋል። ይህም ልክ ኢየሱስ ቀጥሎ እንደተናገረው ነው:- “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፣ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ። ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋቸሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” — ማቴዎስ 6:11, 31–33

“በደላችንን ይቅር በለን”

14, 15. (ሀ) በማቴዎስ 6:12 ላይ የሚገኙትን ቃላት በምንጸልይበት ጊዜ በእኛ በኩል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆን ያለብን እንዴት ነው? (ለ) በዚህስ ጉዳይ የትኞቹን ግሩም ምሳሌዎች ለመከተል እንችላለን?

14 ከአባታችን ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመገንባት የእርሱ ባለዕዳዎች መሆናችንን በትሕትና መቀበልና በአምላክና እኛን በሚመስሉት ሰዎች ላይ የሠራናቸውን በደሎች ማመን ይኖርብናል። ስለዚህ “ለእኛ ዕዳ ያለባቸውን ይቅር እንዳልን አንተም ዕዳችንን ይቅር በለን” በማለት መጸለያችን ተገቢ ነው። — ማቴዎስ 6:12 አዓት

15 አምላክ ልጁን ኢየሱስን ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ እንዲሰጥ’ ወደ ዓለም በመላክ ፈጽሞ የማይገባንን አስደናቂ ደግነት አሳይቶናል። ለኃጢአቶቻችን ይቅርታ የምናገኝበት መሠረት ይህ ነው። (ማቴዎስ 20:28) በዚህ መንገድ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር የተገለጸው የአምላክ ምሕረት ምንኛ ታላቅ ነው! እንግዲያው መሰሎቻችን የሆኑት ሰብዓዊ ፍጡሮች የሚያሳዩአቸውን ድክመቶች ለማለፍ የሚያስገድድ እንዴት ትልቅ ምክንያት አለን! እንዲያውም ከዚህም አልፈን በመሄድ በእኛ ላይ የተፈጸመ ከባድ ኃጢአትም እንኳ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ይሆናል በማለት የገለጸውን ጥልቅ የፍቅር ባሕርይ ለሌሎች ማሳየት እንችላለን። — ዮሐንስ 13:35፤ ቆላስይስ 3:13፤ 1 ጴጥሮስ 1:22

“ከክፉም አድነን”

16, 17. (ሀ) ‘ወደሚያስት ፈተና አታግባን’ የሚሉትን ቃላት መረዳት ያለብን እንዴት ነው? (ለ) ‘ከክፉው አድነን’ ብለን ከምንጸልየው ጸሎት ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 በመጨረሻ ላይ ኢየሱስ “ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” ብለን ወደ አምላክ እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:13) አምላክ በመንገዳችን ላይ የሚያስቱ ፈተናዎችን አስቀምጦ እንድንወድቅ ያደርጋል ብለን አናስብ። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ እንድናፈነግጥ የሚፈልገው በእርሱ ላይ የተነሣው ክፉ ዓመፀኛ ሰይጣን ነው።

17 ይሁን እንጂ አባታችን “የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም” እንድንችል፤ አዎን፣ ከእርሱና እርሱ ከሚቆጣጠራቸው ክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር የምናደርገውን ትግል በአሸናፊነት እንድንወጣ ያስታጥቀናል። ‘ወደሚያስት ፈተናም እንዳንገባ’ አምላክ የተሟላ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ አዘጋጅቶልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በኤፌሶን 6:10–18 ላይ አብራርቶ ገልጾታል። ይህን ከአምላክ የተገኘ ትጥቅ ይዘን፣ ጸሎትን ሳናቋርጥ ጸንተን ከቆምን አባታችን ‘ወደሚያስት ፈተና እንዳንገባ’ ያደርገናል፤ ‘ከክፉውም እንድናለን።’ — 1 ጴጥሮስ 5:6–9

18. ለማጠቃለል ያህል የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ይዘት ምንድን ነው?

18 በቅርቡ መንግሥቲቱ መጥታ ገናናው የይሖዋ ስም ይቀደስ። ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድና ይህችን ምድር ለእርሱ ምስጋና የምታመጣ ገነት በማድረግ ፈቃዱ በምድር ይሁን። የአሁኑ ክፉ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች ይስጠን፣ ከሌሎችም ሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ይርዳን፣ ከሰይጣን መዳፍም ያድነን። ኢየሱስ በጸሎታችን እንድንጠቅሳቸው ያስተማረን ነገሮች እነዚህ ናቸው። የእርሱ የናሙና ጸሎት እነዚህን ሁሉ ያካተተ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአምላክ መንግሥት የምታደርጋቸው ነገሮች

● የይሖዋን ሉዓላዊነት ማስከበር፤ የሰይጣንን አገዛዝ ማክሰም።

● የሐሰት ሃይማኖትንና ጨቋኝ ገዥዎችን ከምድር ማስወገድ።

● “የሰላም መስፍን” የሆነውን የክርስቶስን አገዛዝ ማምጣት።

● መላዋ ምድር አስደሳች ገነት ሆና በአበቦች እንድታሸበርቅ ማድረግ።

● የቤት፣ የምግብና የነዳጅ እጥረትን ሁሉ ማስቀረት።

● በጎረቤት ፍቅር ላይ የተመሠረተ ኅብረተሰብ እንዲያብብ ማድረግ።

● የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች መቆጣጠር፣ አውዳሚ አደጋዎችን መከላከል።

● ጭንቀትን፣ ስጋትን፣ ሕመምን፣ ሥቃይን፣ እርጅናን ማስቀረት።

● ጠላት የሆነውን ሞትን፣ በሽታንና ሐዘንን ሁሉ ማጥፋት።

● በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሙታንን ከሞት ማስነሣት።