በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንግሥቲቱ ምሳሌዎች

የመንግሥቲቱ ምሳሌዎች

ምዕራፍ 11

የመንግሥቲቱ ምሳሌዎች

1. የኢየሱስ ምሳሌዎች አምላክን የሚያገለግሉትን ሁሉ ትኩረት የሚስቡት ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረበት ጊዜ ብዙ ምሳሌዎችን ተናግሮ ነበር። እነዚህ ምሳሌዎች የመንግሥተ ሰማያት አባል ለመሆን ምን ነገሮች እንደሚያስፈልጉ የሚያሳዩ ነበሩ። የመንግሥቱ ወራሾች የሆኑት “ታናሽ መንጋ” እና በመንግሥቱ ሥር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ሁሉ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያመለክቱ ነበሩ። እነዚህ “ሌሎች በጎች” ስለ መንግሥቲቱ የተነገረውን ትንቢት በማወቃቸው ይደሰታሉ፤ መንግሥቲቱ ‘እንድትመጣም’ የጋለ ጸሎት ያቀርባሉ። — ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16፤ 1 ተሰሎንቄ 5:16–20

2, 3. (ሀ) ኢየሱስ በምሳሌዎች የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ያልሆኑት ምሳሌውን ሳይረዱ የቀሩት ለምንድን ነው? (ሐ) በማቴዎስ 13:13–15 ላይ እንደተጠቀሱት ሰዎች ባለ መሆን እኛ የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ከእነዚህ ምሳሌዎች አንዱን ከተናገረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ መጡና “ስለ ምን በምሳሌ ትናገራቸዋለህ አሉት።” ሲመልስም እንዲህ አለ:-

“ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።” (ማቴዎስ 13:10, 11)

ለእነርሱ ያልተሰጣቸው ለምን ነበር? ምክንያቱም “ምሥራቹ” የሚፈልግባቸውን እርምጃ እንዲወስዱ ልባቸው ያነሣሣቸው ዘንድ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ትርጉም ቆፍረውና በጥልቅ መርምረው ለማወቅ ፈቃደኞች አልነበሩም። መንግሥቲቱን እንደ “ውድ ሀብት” ወይም ‘ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጣ ዕንቁ’ አድርገው አልተመለከቷትም። — ማቴዎስ 13:44–46

3 ኢየሱስ የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ በእነዚህ የማያምኑ ሰዎች ላይ እንደተፈጸመ ተናገረ:- “መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፣ ማየትን ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።” (ማቴዎስ 13:13–15) አድናቆት እንደጎደላቸው እንደነዚህ ሰዎች ከመሆን መራቅ ፍላጎታችን መሆን ይኖርበታል። እንግዲያው የአምላክን ቃል ለማጥናት እንትጋ።

4. (ሀ) ከቃሉ ሳይጠቀሙ የቀሩት ምን ዓይነት ልቦች ናቸው? (ለ) ቃሉን ለመረዳት ብንጥር እንዴት ልንባረክ እንችላለን?

4 ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 13:3–8 ላይ በተናገረው ምሳሌው ላይ ራሱን በአንድ “ዘሪ” መስሏል። እርሱም በተለያዩ ዓይነት ልቦች ላይ “የመንግሥቱን ቃል” ይዘራል። የአንዳንድ ሰዎች ልብ በመንገድ ዳር እንዳለ አፈር ነው። የተዘራው ዘር በቅሎ ሥር ከመስደዱ በፊት ዲያብሎስ ‘አምነው እንዳይድኑ ከልባቸው ውስጥ ቃሉን’ ለመንቀል እንደ “ወፍ” ያሉ ወኪሎቹን ይልካል። ሌሎች ልቦች ደግሞ እንደ ጭንጫ ናቸው። በመጀመሪያ ቃሉን በደስታ ይቀበላሉ፤ መከራ ወይም ስደት ሲደርስ ግን ለጋው ተክል ይደርቃል። አንዳንዱ ዘር “በእሾህ” መካከል ወደቀ፤ በዚያም “የዚህ ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል” አንቆ አስቀረው። ይሁን እንጂ በጥሩ ዓይነት አፈር ላይ የወደቀም “ዘር” ነበር!

“በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።” (ማቴዎስ 13:18–23፤ ማርቆስ 4:3–9, 14–20፤ ሉቃስ 8:4–8, 11–15)

አዎን፣ ቃሉን በአድናቂ ልብ ላይ ብናኖረውና ለአምላክ መንግሥት ብዙ ብንደክም እንባረካለን፤ ለአምላክ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎትም በእርግጥ ፍሬያማ ይሆናል።

ሌላ “ዘሪ”

5. (ሀ) አሁን ለየትኛው ሌላ ምሳሌ ትኩረት እንድንሰጥ ሐሳብ ቀርቦልናል? (ለ) ይህ “ሰው” ጌታችን ኢየሱስ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

5 ከወንጌሎች መካከል ማርቆስ የጻፈው ታሪክ ብቻ ከዚህ “የዘሪ” ምሳሌ በመቀጠል ስለ አንድ የተለየ “ዘሪ” የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ ያቀርባል። ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት በግል ለደቀ መዛሙርቱ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ” ብሏቸው ነበር። ከዚህ ጋር በማያያዝ የሚቀጥለውን ምሳሌ ተናገረ:-

“በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፣ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ይበቅላል ያድግማል።” (ማርቆስ 4:24–27)

በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ “ሰው” ታላቅ ክብር የተጎናጸፈው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፤ ምክንያቱም እርሱ አሁን የምድራዊ ሌሊት እንቅልፍ አያስፈልገውም። በተጨማሪም ሁሉ ነገር ሲፈጠር ከአባቱ ጋር ሆኖ የሠራው የአምላክ ልጅ አትክልት እንዴት እንደሚያድጉ ‘አያውቅም’ ብሎ መናገር አይቻልም። (ቆላስይስ 1:16) ስለዚህ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በመመልከት ‘ሰውዬው’ “ከአምላክ መንግሥት” ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ‘በጥንቃቄ መከታተል’ የሚገባውን ግለሰብ ክርስቲያን እንደሚያመለክት መገንዘብ እንችላለን።

6. እያንዳንዱ “ዘሪ” ጥንቃቄ ሊያደርግባቸው የሚገቡት ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው? ለምንስ?

6 እያንዳንዱ “ዘሪ” ምን ዓይነት የግል ባሕርያትን እያዳበረ እንዳለና በምን ዓይነት አካባቢ ላይ ይህን የባሕርያት ዘር እንዳበቀለ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልገዋል። ክርስቲያናዊ ጠባዮችን ለማዳበር በምናደርገው ጥረት የምንኖርበት አካባቢ ይኸውም በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ዘወትር የምንገናኛቸውና የምንቀራረባቸው ሰዎች ምንም ሳይታወቀን ጠባያችንን ጥሩ ወይም መጥፎ አድርገው ሊቀርጹት ይችላሉ። (ከ1 ቆሮንቶስ 15:33 ጋር አወዳድር) በመጨረሻም ፍሬው ይጐመራል፤ እኛም የዘራነውን ዓይነት እናጭዳለን። (ማርቆስ 4:28, 29) ስለዚህ ‘የታናሹ መንጋ’ ክፍል የሆኑት በሙሉ፤ እንዲሁም በአምላክ መንግሥታዊ ዝግጅት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እየተዘጋጁ ያሉት ሁሉ የክርስቶስን የመሰሉ ባሕርያት ለማዳበር ምንና የት እንደሚዘሩ በጥንቃቄ መመልከት አለባቸው! — ኤፌሶን 4:17–24፤ ገላትያ 6:7–9

ማጭበርበሪያ የሆነች መንግሥት

7. የተለያዩ ምሳሌዎች መንግሥቲቱን እንዴት እንድንመለከት ይረዱናል?

7 ማርቆስ የጻፈው ወንጌል ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ በማለት እንደተናገረ ይገልጻል:-

“የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን?” (ማርቆስ 4:30)

ከዚህም በመቀጠል መንግሥቲቱን ከአንድ የተለየ የትኩረት አቅጣጫ እንድንመለከት ይጋብዘናል። አንድን ሕንፃ ከውጭና ከውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ ማዕዘኖች እንደምንመለከተው ሁሉ እነዚህም ምሳሌዎች መንግሥቲቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንድንመለከት ይረዱናል።

8. (ሀ) የሰናፍጩ ዘር ከፍተኛ እድገት የመንግሥቱን ወራሾች ሊያመለክት የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ምሳሌ ሕዝበ ክርስትና ላቋቋመችው “መንግሥት” ተስማሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) አምላክ የከሃዲዋን እስራኤል ሁኔታ የገለጸበት መንገድ ለዚህ አመለካከት ድጋፍ የሚሆነው እንዴት ነው?

8 እንግዲያው መንግሥቲቱን ከምን ጋር ልናመሳስላት እንችላለን? ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይመልስልናል:-

“እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፣ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፣ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።” (ማርቆስ 4:30–32)

በጣም ከፍተኛ የሆነ እድገት ነው። “መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነው” የተባለለትና 144,000 አባላት ያሉት “ታናሽ መንጋ” ከሚደርስበት የቁጥር እድገት የሚበልጥ ነው። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 14:1, 3) ይህ የሚያመለክተው አስመሳይ “ዛፍ” የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ኢየሱስ ተክሎት ከሄደው ጉባኤ ተገንጥላ እንዴት ተንሰራፍታ እንደምታድግ ነው። (ሉቃስ 13:18, 19) ዛፉ በጣም ግዙፍ ነው! በመላዋ ምድር ላይ ከ900,000,000 በላይ አባላት አሉኝ በማለት በኩራት ትናገራለች፤ ሁሉም የመንግሥተ ሰማያት ተስፋ ተሰጥቷቸዋል። ከብዙ ዘመናት በፊት ይሖዋ ከዚህ በታች ያሉትን ቃላት የተናገረላት ተንሸራታችዋ እስራኤል ለዚህ የክህደት መንግሥት ጥላ ናት፤ “እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ?” — ኤርምያስ 2:21–23፤ በተጨማሪም ሆሴዕ 10:1–4 ተመልከት።

9. (ሀ) “ወፎቹ” እና ‘የዛፉ’ ቅርንጫፎች እነማን ናቸው? (ለ) በ2ኛ ተሰሎንቄ 1 እና በማቴዎስ 7 መሠረት ከዚህ “ዛፍ” ፈንጠር ብለን መቆም የሚገባን ለምንድን ነው?

9 ስለዚሁ “ዛፍ” ማቴዎስ በሰጠው ገለጻ መሠረት ‘የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቹ ይሰፍራሉ።’ በግልጽ ከሚታየው ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ወፎች ቀደም ሲል በተጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ ከተጠቀሱትና በመንገድ ዳር የወደቀውን “የአምላክ ቃል” ከለቀሙት “ወፎች” ጋር አንድ ናቸው። (ማቴዎስ 13:4, 19, 31, 32) እነዚህ “ወፎች” በዛፉ ቅርንጫፎች ይኸውም በብዙ መቶ በሚቆጠሩት ኑፋቄዎች ላይ ጎጆ ሠርተው ሰፍረዋል። እነርሱም ከሃዲውን “የዓመፅ ሰው” ማለትም የሕዝበ ክርስትናን ቄሶች ያመለክታሉ። አምላክ ይህንን “ዛፍ” ከሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ጋር ቆርጦ ሲጥለው መጠለያቸውን ያጣሉ። ይህ “ዛፍ” የሚገነደስበት ጊዜ በጣም ስለቀረበ አሁንኑ ራቅ ብለህ ቁም! — ከ2 ተሰሎንቄ 1:6–9፤ 2:3፤ ማቴዎስ 7:19–23 ጋር አወዳድር።

10, 11. (ሀ) ማቴዎስና ሉቃስ “የሰናፍጩን ቅንጣት” ምሳሌ ያቀረቡት በምን ጉዳዮች መሀል ነው? ይህስ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የመንግሥቲቱ የእርሾ ምሳሌ ምን ምክርና ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል?

10 ሉቃስ ‘የሰናፍጩን ቅንጣት’ ምሳሌ በዘመኑ የነበሩትን ከሃዲ ሃይማኖተኞች ኢየሱስ ማውገዙን ከሚገልጸው ሐሳብ ቀጥሎ ማቅረቡ ተገቢ ነው። ነጥቡን ለማጉላት ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ከዚያ በማስከተል ኢየሱስ ስለ “እርሾ” የተናገረውን ምሳሌ አቅርበዋል። (ማቴዎስ 13:32, 33፤ ሉቃስ 13:10–21) እርሾ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ መንገድ ከተጠቀሰ ምን ጊዜም ጥሩ ያልሆነ ነገርን ያመለክታል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስጠነቅቅ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ብሏል። ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያኖች ‘የክፋትንና የግፍን እርሾ’ እንዲያስወግዱ መክሯቸዋል። — ማቴዎስ 16:6, 11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 5:6–8፤ ገላትያ 5:7–9

11 በምሳሌው ውስጥ አንዱ ‘የመንግሥተ ሰማያት’ ገጽታ አንዲት ሴት በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሰወረችውን እርሾ እንደሚመስል ተገልጿል። ስለዚህ ሊጡ በሙሉ ይቦካል። ይህም የክርስቲያን ጉባኤ ነኝ ባዩ ድርጅት በባቢሎናዊ የሐሰት ትምህርቶችና ልማዶች ውስጥ ውስጡ እንደሚበከልና ከዚህ የተነሣ የሕዝበ ክርስትና የማጭበርበሪያ መንግሥት ሰፊ መዋቅር እንደሚዘረጋ ያመለክታል። ይህ እንደ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ክህደት የፈጠረውን አሳዛኝ ውጤት በመመልከት “ታናሽ መንጋ” የሆኑት የመንግሥቱ ወራሾችና ጓደኞቻቸው ዛሬ የሐሰትና የማታለያ ትምህርቶች “እርሾ” ‘ለመንግሥቱ ቃል’ ንጽሕናና እውነተኛነት ያላቸውን ልባዊ አድናቆት እንዳይበክልባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።

ዘሪውና ‘ጠላቱ’

12, 13. (ሀ) ‘በስንዴውና በእንክርዳዱ’ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ የተዋናዮቹን ማንነት ለይቶ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) መከሩ ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ መከሩ እየተካሄደ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?

12 በሌላ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያትን” ‘በእርሻው መልካም ዘርን ከዘራ ሰው’ ጋር አመሳስሏታል። ከዚያ በኋላ “ሰዎቹ ሲተኙ ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ።” ከዚያ እርሻ ምን ዓይነት ፍሬ መጠበቅ ይቻላል? ኢየሱስ ዘሪው “የሰው ልጅ” ማለትም ራሱ እንደሆነ ገለጸ። እርሱም የዘራው የመንግሥት ዘር “የመንግሥት ልጆች” የሆኑትን ስንዴ መሰል ክርስቲያኖች ያፈራል። ጠላት የተባለው “ዲያብሎስ” ሲሆን “እንክርዳዱ” የእርሱ ግብዝ ሃይማኖታዊ “ዘር” የሆኑት “የክፉው ልጆች” ናቸው። (ከዘፍጥረት 3:15 ጋር አወዳድር።) በትንቢቱ አፈጻጸም ላይ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ ችፍግ ብሎ በበቀለው “እንክርዳድ” መካከል አንዳንድ እውነተኛ ክርስቲያኖች ማደጋቸውን ቀጥለው ነበር። በ20ኛው መቶ ዘመን ላይ ግን የመከር ጊዜ ደረሰ፤ ‘መላእክት አጫጆች የሆኑበት የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን’ መጣ። — ማቴዎስ 13:24–30, 36–39

13 በመጨረሻም በመላእክት መሪነት ‘ስንዴው’ ‘ከእንክርዳዱ’ እንዲለይ ተደረገ። በሁለቱ መካከል ያለው ግልጽ ልዩነትም ታየ። በኋላ እንደምንመለከተው ዛሬ “የሰው ልጅ” በሰማያዊው መንግሥቱ ላይ እንደተገኘና ስንዴ መሰል የሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ወደ መንግሥቱ ሥራ በመሰብሰብ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ሕዝበ ክርስትናና በውስጧ ያሉት የክህደት አስተማሪዎችስ ምን ይደርስባቸዋል? የኢየሱስ ምሳሌ በመቀጠል እንዲህ ይላል:-

“የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፣ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ።”

ለብዙ ክፍለ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በሐሰት መሠረተ ትምህርቶቻቸውና ውጭ ውጩን በሚያሳዩት የሃይማኖተኛነት መልክ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች አደናቅፈዋል። ሆኖም የአምላክ ፍርድ መጥቶባቸው ‘በማልቀስና ጥርሳቸውን በማፋጨት’ ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ደጋፊዎቻቸው የሆኑ ምእመናን እየተመናመኑ በመሄዳቸውና ከውስጥ በሚፈጠረው መከፋፈል ምክንያት ዋይታ ያሰማሉ። በአንጻሩ ግን ስንዴ መሰል የይሖዋ አገልጋዮች ስለ መንግሥቱ በደስታ በመመሥከር ላይ ይገኛሉ። “በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ።” ማቴዎስ 13:40–43፤ ከኢሳይያስ 65:13, 14 ጋር አወዳድር።

ውጤቱ የሰመረ ‘ዓሣ አጥማጅነት’

14, 15. (ሀ) ኢየሱስ ታላቅ ‘ዓሣ የማጥመድ’ ሥራ የጀመረው እንዴት ነው? ከዚያስ ወዲህ ምን ሌላ ዓይነት ‘ዓሣ የማጠመድ’ ሥራዎች ተካሂደዋል? ምንስ ለመያዝ ቻሉ? (ለ) በዚያን ጊዜስ መላእክት ምን ሲያደርጉ ነበር? ዓሣዎቹን እየለዩ የሚጥሉት እንዴት ነው? (ሐ) ስለዚህ የትኛውን አጋጣሚ በማግኘታችን አመስጋኞች መሆን ይገባናል?

14 ኢየሱስ በመቀጠል “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች” አለ። (ማቴዎስ 13:47) ኢየሱስ ይህን ዓሣ የማጥመድ ሥራ የጀመረው የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርቱን መረባቸውን ትተው እንዲከተሉትና “ሰዎችን አጥማጆች” እንዲሆኑ በጠራበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 4:19) ይሁን እንጂ ታላቁ ክህደት ከመጣ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ የታመኑ አናሳ ቡድኖችና የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በየፊናቸው ተከታይ ለማፍራት ‘ዓሣ ማጥመዳቸውን’ ቀጥለው ነበር። በዚህ ጊዜ የሚደረገውን ሁሉ መላእክት እየተከታተሉ ሲመለከቱ ነበር። ሆኖም በመረብ የተያዙት በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩት ምሳሌያዊ የባሕር ፍጥረታት ‘ጥሩ ዓሦች’ ሆነው ተገኝተዋልን? ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ትምህርቶቻቸውን የመሠረቱት በፕላቶ የግሪክ ፍልስፍናና በጥንታዊቷ ባቢሎን ሃይማኖታዊ “ምስጢሮች” ላይ ነው። ያፈሩት ፍሬ በመካከላቸው ባለው ጥላቻ፣ ጠብና የሕዝበ ክርስትናን ታሪክ ባሳደፈው ደም አፍሳሽነት እንዲሁም በ20ኛው መቶ ዘመናችን ውስጥ የተደረጉትን የዓለም ጦርነቶች በመደገፋቸው ታይቷል።

15 በመጨረሻም ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ውስጥ’ መላእክት “መረብ” የሚጥሉበት ጊዜ መጣ። ይህ መረብ የሚያመለክተው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ ሁሉ (እውነተኞቹም ውሸተኞቹም) በምድር ላይ ያሏቸውን ድርጅቶች ነው። “ለመንግሥተ ሰማያት” ‘የማይስማሙ ሆነው የተገኙት ዓሦች ወደ ውጭ ተወርውረው ደብዛቸውን ወደሚያጠፋ “እቶነ እሳት” መጣል ይኖርባቸዋል። “በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” (ማቴዎስ 13:48–50) ሆኖም መላእክቱ ከምሳሌያዊው መረብ ‘ጥሩ አሦችንም’ ጭምር እየለዩ በማውጣት ላይ ናቸው። የይሖዋን ስም ለመቀደስ ራሳቸውን ከወሰኑትና መንግሥቱ ‘እንድትመጣ’ ትርጉም ያለው ጸሎት ከሚያቀርቡት ከእነዚህ ልዩ ሰዎች ጋር ለመቆጠር አጋጣሚ በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል!

16. ይህ የመጨረሻ ምሳሌ ምን ጥያቄዎችን ያስነሣል? መልሶቹን ለማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

16 ነገር ግን ኢየሱስ በዚህ የመጨረሻ ምሳሌው ላይ ጠበቅ አድርጎ የተናገረለት “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” ምንድን ነው? በርካታ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የጻፉለት “የመጨረሻ ቀን” ምንድን ነው? አሁን እኛ የምንኖረውስ በዚህ ቀን ውስጥ ነውን? ነገሩ እንደዚያ ከሆነ ይህ ለእኛና ለሁሉም የሰው ዘር ምን ትርጉም አለው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 104 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኢየሱስ የተናገራቸውን የመንግሥት ምሳሌዎች ልብ በሏቸው

● ምሳሌዎቹ መንግሥቲቱ ልክ እንደ “ውድ ሀብት” ወይም “ዕንቁ” ተፈላጊ እንደሆነች ይገልጻሉ። እርሷንም የሚፈልጓት በ“መልካም መሬት”፣ “ስንዴ” እና በ“ጥሩ ዓሣ” ተመስለዋል።

● አጭበርባሪዋ መንግሥት እንደ ሰናፍጭ፣ ብዙ ቅርንጫፎች እንዳሉት “ዛፍ”፣ እርሾ እንዳለበት ዱቄት ሆና ተገልጻለች። ደጋፊዎቿ “ወፎች”፣ “እንክርዳድ”፣ ‘ክፉ ዓሦች’ ናቸው።

● የመንግሥቲቱን ሂደት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት በዛሬው ጊዜ በሰው ዘር ፊት የተደቀነውን ታላቅ ጥያቄ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን፤ መንግሥቲቱም በታማኝነት በመደገፍ ጽኑ አቋም ለመያዝ እንበረታታለን።