በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንግሥቲቱ ፈረሰኛ በመጋለብ ላይ ነው

የመንግሥቲቱ ፈረሰኛ በመጋለብ ላይ ነው

ምዕራፍ 13

የመንግሥቲቱ ፈረሰኛ በመጋለብ ላይ ነው

1, 2. (ሀ) አሁን ትኩረታችንን በማን ላይ እናደርጋለን? እርሱስ በቀኝ እጁ ምን ይዟል? (ለ) ዮሐንስ ለቅሶውን እንዲያቆም የተነገረው ለምንድን ነው? (ሐ) የይሁዳ “አንበሳ” ማን ነው? ማኅተሞቹንስ ለመፍታት ብቁ የሚሆነው ለምንድን ነው?

እስቲ የራእይን መጽሐፍ አምስተኛ ምዕራፍ እናውጣ። እዚህ ላይ ከአምላክ መንግሥት ‘መምጣት’ ጋር በቀጥታ ስለተያያዘ ከአምላክ ለሐዋርያው ዮሐንስ ስለተላከ አንድ ራእይ እናነባለን። ራእዩ በተለይ የሚያተኩረው ‘በዙፋን ላይ በተቀመጠው’ ሉዓላዊ ጌታ በይሖዋ ላይ ነው። በቀኝ እጁ ‘በሰባት ማኅተም በጥብቅ የታሸገ’ የመጽሐፍ ጥቅልል ይዟል። ሆኖም ሐዋርያው ዮሐንስ በኃይል አለቀሰ። ለምን ይሆን? ምክንያቱም በአጽናፈ ዓለም በሙሉ የመጽሐፉን ጥቅልል ሊፈታና መልእክቱን ሊያሳውቅ ብቃት ያለው ማንም አልተገኘም ነበር። ሆኖም በኋላ ለዚህ የሚበቃ ተገኘ! እርሱም የዳዊት መንግሥት ወራሽ የሆነው “የይሁዳ አንበሳ” እንጂ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል! — ራእይ 5:1–5

2 እርሱ ‘ድል በማድረጉ’ ማኅተሙን ለመፍታት ብቁ ሆኗል። በምድር ላይ ፍጹም ሰው ሆኖ ሲኖር በመከራ እንጨት ላይ በጭካኔ እስከ መገደል ቢደርስም ለአባቱ ያለ ማወላወል ታማኝ ሆኖ ቆሟል። “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ፍጹም አቋሙን ሊያበላሽበት አልቻለም። ስለዚህ ኢየሱስ “ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ሊል ችሏል። — ዮሐንስ 14:30፤ 16:33

3. ራእይ 5:9, 10 በመፈጸሙ መደሰት የሚገባን ለምንድን ነው?

3 ዓለምን ያሸነፉ ሌሎች ሰዎችም አሉ። ይህ ደፋር “አንበሳ” ክርስቶስ ኢየሱስ እንደ መንፈሳዊ “ወንድሞቹ” አድርጎ ይቆጥራቸዋል። (ማቴዎስ 25:40) እነዚህ ሰዎች ሰማያዊ ትንሣኤ በማግኘት በሺው ዓመት መንግሥት ከእርሱ ጋር ይገዛሉ። የቤዛዊ መሥዋዕቱንም ጥቅሞች በምድር ላይ ለሚኖሩት በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በማዳረሱ ሥራ ከእርሱ ጋር ይተባበራሉ። በዚህም ምክንያት በሰማይ የአዲስ መዝሙር ድምፅ እያስተጋባ ነው። ዘማሪዎቹ ክፋት የሌለበት በግ ሆኖ ታርዶ ለነበረው እንደሚከተለው ይላሉ:-

“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፣ ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ።” (ራእይ 5:9, 10)

ይህ ንጉሥና ተፈትነው ታማኝነታቸውን ያስመሠከሩት ተባባሪ ነገሥታቱ ብዙ ጭቆና የደረሰበትን የሰው ዘር ለመባረክ ዝግጁ መሆናቸው እንዴት ያለ በረከት ነው! ሆኖም ይህ ከመሆኑ በፊት በመጀመሪያ ጦርነት መደረግ ይኖርበታል።

የነጩ ፈረስ ጋላቢ

4. (ሀ) ‘ነጩ ፈረስ’፣ ጋላቢው የያዘው “ቀስት” እና “አክሊል” መቀበሉ ምን ያመለክታል? (ለ) የነጩ ፈረስ ጋላቢ ማን ነው? ንጉሣዊ ሥልጣኑን የተቀበለውስ መቼ ነው?

4 “በጉ” የመጽሐፉን ጥቅልል ወስዶ የመጀመሪያውን ማኅተም ሲፈታ ከሰማይ እንደ ነጎድጓድ ያለ “ና!” የሚል ድምፅ ተሰማ። ምን ልንመለከት ይሆን? “እነሆ” የጽድቅ ጦርነት ምልክት የሆነው “ነጭ ፈረስ” ይታያል። የፈረሱ ጋላቢ ቀስት ይዟል። ሰው ሠራሽ የሆኑት አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይሎች ከማይደርሱበት በጣም ሩቅ ቦታ ሆኖ ጠላቶቹን መደምሰስ ይችላል። “አክሊል” ተሰጠው። ይህም ይሖዋ ለእርሱ በአሕዛብ ላይ ንጉሣዊ ሥልጣን የሰጠበትን ዓመት 1914⁠ን የሚያመለክት ነው። ኢምንት ከሚያክሉት ሰብአዊ ጌቶችና ነገሥታት በጣም የሚበልጥ ኃያል ስለሆነ ይህ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ከእርሱ ጋር በሰማያዊው መንግሥቱ አብረውት ከሚገዙት ‘ከተጠሩትና ከተመረጡት ታማኝ’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ሆኖ የጽድቅ ጠላቶች የሆኑትን ሁሉ በመዋጋት ድል ይነሣል። — ራእይ 6:1, 2፤ 17:14

5. (ሀ) ይህ ጋላቢ ምን የመጀመሪያ ድል ተቀዳጀ? (ለ) ይህስ በሰው ዘር ላይ ምን ውጤት አስከትሏል? ሆኖም በማርቆስ 13:32–37 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ መስማት የሚገባን ለምንድን ነው?

5 ይህ ‘የነጩ ፈረስ ጋላቢ’ ኃያል ተዋጊ ነው። እንግዲያው ግልቢያውን ሲጀምር ‘የቀድሞውን እባብ’ ሰይጣንንና አጋንንት መላእክቱን ከሰማይ ከማባረር ሌላ ምን የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላል? ወደዚች ምድር አሽቀንጥሮ ጣላቸው። በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ ታላቅ ቁጣ መቆጣቱ አያስደንቅም። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የቁጣውን ውርጅብኝ በሰው ልጆች ላይ በማውረድ ‘በምድርና በባሕር ላይ ወዮታን’ አመጣ። ዲያብሎስ “ጥቂት ዘመን እንዳለው” ያውቃል፤ ቢሆንም አሠራሩ ሁሉ የረቀቀ ነው። “የመጨረሻዎቹ ቀኖች” ገና ረጅም ጊዜ ይቆያሉ ብለን እንድናስብ በማድረግ ሊያዘናጋን ይጥራል። ስለዚህ አንዳችንም ብንሆን በዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ተታለን እንቅልፍ እንዳያሸልበን እንጠንቀቅ። — ራእይ 12:9–12፤ ማርቆስ 13:32–37

ዳማ ፈረስ

6. (ሀ) በራእይ 6:3, 4 መሠረት በዓለም ላይ ድንገት የፈነዳው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አንደኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ሲል ከነበሩት ከሁሉም ጦርነቶች የሚለየው እንዴት ነው?

6 “በጉ” ሁለተኛውን ማኅተም ፈታ። ‘አንድ ዳማ ፈረስ’ እየጋለበ ወጣ። “በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” (ራእይ 6:4) በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። ከጥቂት ብሔራት ብቻ ሳይሆን ከመላዋ “ምድር” ላይ ሰላም ተወሰደ፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ እጅግ ብዙ ጦር ሠራዊቶችና የባሕር ኃይል ወታደሮች ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ሊደመስሱ በሚችሉ አስፈሪ የጦር መሣሪያዎች በመጠቀም እርስ በርሳቸው መፋጀት ጀመሩ። ከዚያ በፊት ጦርነቶች የተደረጉት በመደበኛ ጦር ሠራዊት ሲሆን ጥቂት አገሮች ብቻ ይሳተፉባቸው ነበር፤ አንደኛው የዓለም ጦርነት ግን አጠቃላይ ጦርነት ሆነ። በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የብዙ ብሔራት ጠቅላላ ሀብት ለጦርነቱ ዋለ፤ ሕዝቡም ለውጊያ እየተመለመለ በጦርነቱ ተማገደ።

7–9. ‘መተራረድን’ በተመለከተ 1914 በታሪክ ውስጥ ከመቼውም ይበልጥ ግድያ የበዛበት ዘመን የጀመረበት ጊዜ ለመሆኑ ምን የእስታትስቲክስ መረጃዎችና ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች አሉ?

7 ትንቢቱ ‘እርስ በርስ መተራረድ’ እንደሚኖር ይናገራል፤ እውነትም እርስ በርስ መተላለቅ ነበር የታየው። በሶም በተደረገው ውጊያ አዲስና ብዙ ገዳይ የሆነው መሣሪያ ይኸውም መትረየስ ተፈለሰፈ። ይህም መሣሪያ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የእንግሊዝና የፈረንሣይ ወታደሮችን እንደ ቅጠል አረገፈ። በአንዳንዶች ግምት ከጠቅላላው ሟቾች ውስጥ 80 በመቶ የሚያክሉት ያለቁት በዚህ መሣሪያ ነበር። በቬርዳን ላይ በዘጠኝ ወር ውስጥ ብቻ ከናፖሊዮን ጋር ወደ ሩሲያ ከዘመቱት ወታደሮች የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተጨፈጨፉ። በቬርዳም በሚገኝ በአንድ መቃብር ላይ በደም የተጻፈ አንድ ጽሑፍ “በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰዎች የታረዱበት ቄራ ይገኛል” ይላል። በዚያ አራት ዓመታት በፈጀ ታላቅ ጦርነት በአጠቃላይ 9,000,000 ወታደሮች ተገድለዋል።

8 ‘በዳማ ፈረስ’ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ ከምድር ሰላምን የወሰደበት ዓመት 1914 ነበርን? ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን አስተሳሰብ ይደግፋሉ። ለምሳሌ ያህል ከጦርነቱ በኋላ 50 ዓመት ቆይቶ አሜሪካን ሄሪቴጅ የተባለው የታሪክ መጽሔት አዘጋጅ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በ1914 የበጋ ወራት ላይ ብሔራት በሰላም ይኖሩ ነበር፤ የወደፊቱም ጊዜ የተረጋጋ ይመስል ነበር። ከዚያ በኋላ ጠመንጃዎች መናገር ጀመሩ፣ ነገሮች እንደገና እንደ ድሮው ሊመለሱ አልቻሉም። . . . የ1914 ዓመት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የክፉ ዘመን መክፈቻ ሆነ። . . . በዚያ ዓመት ላይ የዓለምን የጉዞ አቅጣጫ በጣም የሚለውጥ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ በአንድ ሺህ ዓመት ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ የሚደርስ ነው። ምናልባት 1914 ወደ ምን ዓይነተ አዘቅት እንደከተተን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ረጅም ጊዜ ይወስድብን ይሆናል፤ ነገር ግን ቢያንስ ቢያንስ ምን እንደነጠቀን አሁንም ማየት እንችላለን።” በእርግጥም ‘የዳማው ፈረስ’ ጋላቢ ከምድር ሰላምን ነጥቆ ወስዷል። ይህም የሆነበት ዓመት 1914 ነው።

9 ይህ ፈረሰኛ የግድያ ግልቢያውን ባለማቆም 16,000,000 ወታደሮች የሞቱበትን ሁለተኛ የዓለም ጦርነት አመጣ። በ1980ዎቹ ላይ አንድ የሃንጋሪ ፕሮፌሰር ባሰሉት መሠረት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ በተደረጉ ጦርነቶች ተጨማሪ 25,000,000 ወታደሮች ሞተዋል። ፕሮፌሰሩ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት 33 ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ምንም ጦርነት ያልነበረባቸው 26 ቀኖች ብቻ እንደነበሩ ገልጸዋል።

10. ይህ ፈረሰኛ ‘በታላቅ ሰይፍ’ የተጠቀመው እንዴት ነው?

10 ትንቢቱ ለዚህ ፈረሰኛ “ታላቅ ሰይፍ” እንደተሰጠው ይነግረናል። በእርግጥም በዚህ 20ኛ መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች ውስጥ ለደረሰው እልቂት የግድያ መሣሪያዎች ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ ግልጽ ነው። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የመርዝ ጋዝ፣ አውቶማቲክ መሣሪያዎች፣ የጦር ታንኮች፣ አውሮፕላኖችና ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውለዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአየር ውጊያ ከተሞችን እንዳልነበሩ አድርጎ ደምስሷቸዋል። የዚህ ውጊያ ሰለባዎች ከሆኑት ውስጥ አብዛኞቹ ሰላማውያን ሴቶች፣ ልጆችና አረጋውያን ነበሩ። የእንግሊዝ ከተማ የሆነችው ኮቨንትሪ በአንድ ሌሊት ወደመች። ከዚያም የኅብረ ብሔራቱ የአየር ጥቃት ድሬስደን በተባለች የጀርመን ከተማ ውስጥ የ135,000 ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ። ከዚህም በኋላ በአቶሚክ ቦምቦች አማካኝነት ዕልቂቱ ቀጠለና በጃፓን ቢያንስ 92,000 የሚያክሉ ሰዎች በሂሮሺማ እንዲሁም 40,000 የሚያክሉ በናጋሳኪ አለቁ። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሲቪሎች ነበሩ። ዛሬ የኑክሌር ጦርነት ቢነሣ ‘ታላቁ ሰይፍ’ ምን እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ለግምት ያስቸግራል!

“እነሆም፣ ጉራቻ ፈረስ”

11, 12. (ሀ) ‘የጥቁሩ ፈረስ’ ጋላቢ የሁለተኛው ፈረሰኛ ጓደኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ግልቢያው እስከ ዘመናችን እንደቀጠለ የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 “በጉ” ሦስተኛውን ማኅተም ሲፈታ አንድ “ጉራቻ (ጥቁር) ፈረስ” እየጋለበ ወጣ። “በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ።” (ራእይ 6:5) አጠቃላይ ጦርነትን የሚያመለክተው ፈረሰኛ ጓደኛ የሆነ ጋላቢ ነው። ረሃብን የሚያመጣው ፈረሰኛ ይህ ነው። በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ወቅት ረሀብ ብዙ አገሮችን እንደ መቅሰፍት ወርዶባቸዋል። ‘በሚዛን’ የተመሰለው ምግብን በራሽን የማከፋፈሉ ሁኔታ በተዋጊዎቹ ብሔራት ለሚገኙት ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ሆነ። አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ረሀብ መጣ። ሰኔ 7, 1919 የወጣው ዘ ኔሽን የተባለ ጋዜጣ በህንድ ውስጥ 32,000,000 የሚያክሉ ሰዎች “በአውዳሚ ረሀብ አፋፍ ላይ ናቸው” በማለት ዘግቦ ነበር። መጋቢት 1921 የወጣው ወርልድስ ወርክ የተባለ ጋዜጣ በሰሜናዊ ቻይና ብቻ በየቀኑ በረሃብ ምክንያት 15,000 ሰዎች ይሞቱ እንደነበረ ገልጾ ነበር። የኒው ዮርክ ታይምስ እትም የሆነው መጋቢት 1921 ላይ የወጣ ከረንት ሂስትሪ ማጋዚን አንድን የእንግሊዝ ዘገባ በመጥቀስ በሩሲያ ውስጥ ስለነበረው ሁኔታ:- “ከ35,000,000 የማያንሱ ሰዎች አሰቃቂ የሆነ ረሀብና ቸነፈር ቀስፎ ይዟቸዋል” ብሎ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ተመሳሳይ የረሀብ ሁኔታዎች ተከስተው ነበር። ሰኔ 11, 1946 የወጣው ሉክ የተባለ መጽሔት “ዛሬ የዓለም ሩቡ በረሃብ ይሠቃያል” ብሎ ነበር።

12 አጠቃላይ የሆነ ጦርነት ባይኖርም እንኳ በዘመናችን ባለው ዓለም ውስጥ በድርቅ ምክንያት እህል ሳይመረት መቅረቱ በጋዜጦች ላይ ብዙ ጊዜ እንደሚከተሉት ያሉ ርዕሰ አንቀጾች እንዲወጡ አድርጓል:- ለምሳሌ በ1974:- “ህንድ ሦስተኛው ፈረሰኛ አጠላባት” የሚል፤ በ1976:- “ከምን ጊዜውም ይበልጥ የተራበው ዓለም ትልቅ የምግብ ቀውስ ይጠብቀዋል” የሚል፣ እንዲሁም በ1979:- “450 ሚልዮን ሰዎች ተርበዋል” የሚሉ ናቸው። የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በጦርነት እሳት በሚለበለቡት ታዳጊ አገሮች ውስጥ ያለው የምግብ ሁኔታ የበለጠ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል። ግንቦት 1975 በወጣው ኒው ሳይንቲስት በተባለው መጽሔት ላይ በታተመ የዓለም ዜናዎች ማጠቃለያ ላይ እንዲህ ተብሎ ተገልጾ ነበር:- “ዓለምን ያጋጠማት ድርብ ችግር ነው። ረሀብ የዚህ አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። ሌላው ለረጅም ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ነው። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ከ97 ታዳጊ አገሮች ውስጥ 61 የሚሆኑት በ1970 ሕዝቦቻቸውን ለመመገብ ያመረቱት ወይም ከውጭ ያስመጡት ከሚያስፈልጋቸው እህል ውስጥ አነስተኛ የሆነውን ብቻ እንደሆነ ገምቷል። ይህ ድርጅት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በትንሹ 460 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች ይሠቃያሉ ብሏል። ከዚህ ከፍ ያለ ግምት ደግሞ ቁጥሩን ወደ 1 ቢልዮን ከፍ ያደርገዋል።” አሁን ሁኔታው በጣም የባሰ ነው።

13. በራእይ 6:6 ላይ በዘመናችን የሚታዩ ምን ሁኔታዎችና ፍርሃቶች አስቀድመው ተገልጸዋል?

13 ሦስተኛው ፈረሰኛ ግልቢያውን ሲቀጥል ከሰማይ አንድ ድምፅ:- “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፣ ዘይትንና ወይንንም አትጉዳ” ሲል ጮኸ። (ራእይ 6:6) አንድ ዲናር ለአንድ ቀን ሥራ የሚከፈል ገንዘብ ስለሆነ አንድ ሠራተኛ በዚህ በከፍተኛ ደረጃ በሚንረው የኑሮ ዋጋ በጣም መቆጣቱ አይቀርም። ታዲያ ዛሬ የዋጋ መናር የተራ ሰዎችን ገቢ ማመናመኑን ተያይዞት የለምን? ሰዎች ዕለት በዕለት የሚጠቀሙባቸው እንደ “ዘይት” እና “ወይን” የመሳሰሉት ነገሮች እጥረት ይኖራል። ስግብግብ የሆኑ ትርፍ አግበስባሾች የቅንጦት አኗኗራቸው እንዳይነካባቸው ለመከላከል ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ይሳካላቸው ይሆንን? ‘ጥቁሩ ፈረስ’ በምድር ላይ ወዲያ ወዲህ እያለ ሲጋልብ የዚህን ሁኔታ ለማየት እንችላለን።

‘ሞት የተቀመጠበት ሐመር ፈረስ’

14. የአራተኛው ፈረስ ጋላቢና ጓደኛው ከ1914 ወዲህ ከተፈጸሙት ሁኔታዎች ጋር የተያያዙት እንዴት ነው?

14 አራተኛው ማኅተም ተፈታ፤ አንድ “ሐመር ፈረስ” በመጋለብ ካሉት ፈረሰኞች ጋር ተቀላቀለ። ጋላቢው ሞት ነው። እርሱንም በቅርብ እየተከተለ ሐዴስ መጣ። እርሱ በሌላ ፈረስ ላይ ይቀመጥ ወይም አይቀመጥ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ሁለቱም አስፈሪ ተልእኮ አላቸው። “በታላቅ ሰይፍና በራብም በሚገድል መቅሰፍትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ በምድር አራት ክፍሎች ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።” (ራእይ 6:7, 8 አዓት) የዓለምን የወደፊት ሁኔታ ከለወጠው ዓመት ከ1914 ወዲህ የሞትና የሲኦል ጥላ በእርግጥም በአራቱም የምድር ማዕዘኖች አጥልቷል።

15, 16. (ሀ) ይህ ትንቢት ከ1918–1919 ትልቅ ፍጸሜ ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ይህ ፈረስ ከ1914 ጀምሮ ያለ ማቋረጥ እየጋለበ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

15 “የሚገድል መቅሰፍት” መጣ! ይህንንም የ1918–1919 ወረርሽኝ ወይም ስፓኒሽ ፍሉ ወይም የኅዳር በሽታ ብለው ጠሩት። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሽታው የገደላቸው ሰዎች ቁጥር በአንደኛው የዓለም ጦርነት የጦር ሜዳዎች ከሞቱት እጥፍ ሆነ። ቢያንስ 21,000,000 ሰዎች አለቁ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይፋ የወጣው በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 548,452 ሲሆን ይህም በጦርነቱ ከሞቱት የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር ከ10 ጊዜ በላይ የሚበልጥ ነው። በአብዛኛው የዚህ በሽታ ሰለባዎች ወጣቶችና ለበሽታ የማይበገሩ የሚመስሉት ሰዎች ናቸው። በህንድ አገር ከ12,000,000 የሚበልጡ ሞተዋል። ከሴንት ሄለና ደሴት በስተቀር ያልደረሰበት የዓለም ክፍል ወይም ደሴት አልነበረም። በኤስኪሞዎችና በማዕከላዊ አፍሪካ የነበሩ መንደሮች በጠቅላላ ሰው አልባ ቀሩ። በታሂቲ ውስጥ በ15 ቀናት ውስጥ ብቻ 4,500 ሰዎች ሞተው ሬሳቸው በእሳት ተቃጥሏል። ከሰሜናዊ ሳሞአ 38,000 ነዋሪዎች ውስጥ 7,500 የሚሆኑት በበሽታው ምክንያት ሞተዋል።

16 ‘የሐመር ፈረስ’ ጋላቢው ያመጣው ገዳይ በሽታ የኅዳር በሽታ ብቻ አይደለም። የኒው ዮርክ ታይምስ በ1915 ጋሊፖሊን ለመያዝ በተደረገው ጦርነት የተቅማጥ በሽታ ጥይት ከገደላቸው የበለጡ ወታደሮችን እንደጨረሰ ዘግቦ ነበር። ከ1914 እስከ 1923 ድረስ ኮሌራ በህንድ ውስጥ 3,250,000 ሰዎችን ገድሏል። በ1915 በሩሲያ ከደረሰው “ከሁለት ሚልዮን ተኩል እስከ ሦስት ሚልዮን የሚሆነው ሞት” በአንጀት ተስቦ ምክንያት የመጣ ነው። ፈረሰኛው ግልቢያውን በቀጠለባቸው በቅርብ ዓመታትም የልብ በሽታና ካንሰር ዋነኛ ገዳዮች ሆነዋል፤ “በንክኪ ከሚተላለፉት በሽታዎች መካከል ብዙ ሕዝብ በመፍጀት ረገድ ቂጥኝ ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።” ‘በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋው’ የሄፕታይተስ በሽታም አለ።

በመጨረሻው እፎይ እንላለን!

17, 18. (ሀ) አንድ ታዋቂ የፖለቲካ ሰው በሁለተኛው፣ በሦስተኛውና በአራተኛው ፈረሰኞች መካከል ያለውን ዝምድና በማመልከት ምን ብለው ተናገሩ? (ለ) ይሁን እንጂ የዓለም መሪዎች ልብ ያላሉት ማንን ነው? (ሐ) ታላቁ ንጉሥ ወደፊት ምን እንደሚያደርግ በማሰብ ልንደሰት የምንችለው ለምንድን ነው?

17 ዛሬ ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት “ዳማው ፈረስ፣” “ጥቁሩ ፈረስ” እና “ሐመሩ ፈረስ” ጎን ለጎን ሲጋልቡ የቆዩ ሲሆን ሲኦልም ተከትሏቸዋል። በእርግጥም ሲኦል በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሟቾችን እየዋጠ ነው። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኸርበርት ሁቨር በ1941 ሦስቱን ፈረሰኞች በአንድ ላይ በማያያዝ እንዲህ ብለዋል:- “ብዙውን ጊዜ ታላላቅ ጦርነቶች ረሀብንና ቸነፈርን ያስከትላሉ። . . . ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተደረገው የዓለም ጦርነት በ300,000,000 ሰዎች ላይ ረሀብን አስከትሏል። . . . የአሁኑ ጦርነት [ሁለተኛው የዓለም ጦርነት] አንድ ዓመት ተኩል ካለፈው በኋላ ወደ 100,000,000 የሚጠጉ ተጨማሪ ሰዎች ባለፈው ጦርነት ከሦስት ዓመት በኋላ ከደረሰው የበለጠ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።” ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ቢነሣ በሰው ዘር ላይ እንዴት ያለ እልቂት ይደርስ ይሆን!

18 የዓለም መሪዎች ‘የዳማው’ ‘የጥቁሩ’ እና ‘የሐመሩ’ ፈረስ ጋላቢዎች ያስከተሉትን ውድመት ሙሉ በሙሉ ተገንዝበውታል። ነገር ግን ‘የነጩን ፈረስ’ ጋላቢ ልብ አላሉትም። ይህ ታላቅ ንጉሥ የነገሮችን ሥርዓት ለመለወጥ እርምጃ የሚወስድበት አስደሳች ቀን ቀርቧል። እርሱም በጦርነት ፋንታ ሰላምን ያመጣል። በረሀብ ፋንታም የተትረፈረፈ ምግብ ይሰጣል። በበሽታም ፋንታ ለሰው ልጆች ፍጹም ጤንነት ይመልስላቸዋል። ሲኦልም ሙታኖቹን ይሰጣል። በመዝሙር ውስጥ የሚገኝ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ ምንባብ ይህንን ‘የነጭ ፈረስ’ ጋላቢ እንደሚከተለው ሲል ይገልጸዋል:-

“ኃያል ሆይ፣ በቁንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ [እውነትና ስለ ትሕትና አዓት] ስለ ጽድቅም [ተዋጋ ] ተከናወን ንገሥም፤ ቀኝህም በክብር ይመራሃል።” (መዝሙር 45:3, 4)

የመንግሥቱ ፈረሰኛ ድል ቀርቧል!

19. (ሀ) የራእይ 6:2–8 ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑ ሊያሸብረን ይገባልን? (ለ) በእምነታችን ጠንካሮች እንድንሆን እኛን ለማበረታታት ምን ምሳሌ ተጠቅሷል?

19 እንግዲያው ዛሬ በምድር ላይ እየተባባሰ ባለው ሁኔታ ምክንያት ከሚገባው በላይ አንሸበር። ከዚህ ይልቅ ከ1956 እስከ 1978 ለ20 ዓመታት በአንድ የሶሻሊስት አገር እሥር ቤት ውስጥ ያሳለፈችው አንዲት የይሖዋ ምሥክር የነበራት አስተሳሰብ እኛም ይኑረን። በአንድ ወቅት የሞት ፍርድ ተፈርዶባት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእጆችዋ ላይ የሥቃይ ምልክቶች ይታያሉ። በእምነትዋ ጠንካራ ሆና ለመቀጠል የቻለችው እንዴት ነው? ቀደም ሲል ታደርገው ከነበረው ትጋት የሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትዋ በምታስታውሳቸው ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ላይ በማሰላሰል ነው። ከእነዚህም ጥቅሶች አንዱ ራእይ 6:2 እንደነበረ ትናገራለች። ‘የነጩ ፈረስ’ ጋላቢ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣኑን እንደጨበጠ እርግጠኛ ነበረች። እርሱ ‘ድሉን እስኪፈጽምም’ ድረስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ነበር። የአምላክ መንግሥት ‘እንድትመጣ’ የሚጸልዩ ሁሉ ንጉሡ ሙሉ በሙሉ ድል አድራጊ እስከሚሆን ድረስ የታመኑ ሆነው እንዲኖሩ እንመኛለን!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥቁሩ ፈረስ ግልቢያውን ቀጥሏል

“የዓለም ባንክ በምድር ዙሪያ 780 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በፍጹም ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ ገምቷል፤ ይህም ከማንኛውም ሰብአዊ ክብር በጣም ዝቅ ያለ ሁኔታ ነው።” — ዲትሮይ “ፍሪ ፕሬስ” መስከረም 1, 1980