በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘላለሙ ንጉሥ

የዘላለሙ ንጉሥ

ምዕራፍ 2

የዘላለሙ ንጉሥ

1. አምላክን እንደ እውን አባት አድርገን በማሰብ በእርሱ ላይ ትምክህት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ አምላክን “አባታችን ሆይ” ብሎ በመጥራት “የጌታን ጸሎት” ከፍቷል። እርሱ አባት የሚሆነው የኋላ ኋላ ይህንን አፍቃሪ “ጸሎት ሰሚ” በታዛዥነት ለሚያመልኩት የሰው ዘሮች ሁሉ ጭምር እንጂ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም። (መዝሙር 65:2) “የዘላለም ንጉሥ” እንደመሆኑም አንድ ጥሩ ሰብዓዊ አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው ለፍጥረቶቹ ልባዊና የማያቋርጥ አሳቢነት ያሳያል። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) እርሱ የሚያስብልን እውን አካል እንደሆነ አድርገን በመመልከት “በአባታችን” ላይ ትምክህት ሊኖረን ይገባል። ቋንቋችን፣ የቆዳችን ቀለም ወይም የኑሮ ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ወደ እርሱ ለመቅረብ ነፃነት ሊሰማን ይገባል፤ ምክንያቱም ‘አምላክ ለሰው ፊት አያደላም፣ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።’ — ሥራ 10:34, 35

2, 3. አባታችን ሕይወት ሰጪና የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ ታላቅ አቅራቢ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 1:1, 2, 31)

2 ‘በሰማያት የሚኖር አባታችን’ ለሰው ልጆች ሕይወትን የሰጠ ፈጣሪ ነው። (ማቴዎስ 6:9፤ መዝሙር 36:9) ነገር ግን ሕይወት ሰጪአችን ብቻ አይደለም፤ የሚያስፈልገንን ሁሉ በታላቅ ልግስና አዘጋጅቶ የሚያቀርብልንም ነው። ኃላፊነት የሚሰማው ሰብዓዊ አባት ብዙ ጊዜና ጥረት ቢጠይቅበትም እንኳ ለልጆቹ ቤትና ምግብ እንደሚያቀርብ እንጠብቃለን። ሰማያዊ አባታችን ይህንንና ከዚህም የበለጠ ብዙ ነገር አትረፍርፎ ሰጥቶናል።

3 ይህ “የዘላለም ንጉሥ” ምድር መኖሪያችን እንድትሆን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንዳዘጋጃት እስቲ አስብ። በጠፈር ውስጥ በትክክለኛ ቦታ ላይ አስቀመጣት። ሁሉን ማድረግ በሚያስችለው ኃይሉም የሰው ልጆች በደስታ እንዲኖሩ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ በምድር ላይ አዘጋጀ። ከዚያም ወንድና ሴትን ፈጥሮ በዚህ አስደሳች ቤት አስቀመጣቸው። በእርግጥ ይህ “ለሰው ልጆች” ታላቅ ስጦታ ነው! — መዝሙር 115:16፤ 19:1, 2

4. (ሀ) አባታችን መኖሪያችንን ሲያዘጋጅ ምን ደግነት ያለበት አርቆ ተመልካችነት አሳይቷል? (ለ) እኛ ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚያረጋግጥልን ምንድን ነው?

4 ሰማያዊው አባታችን እዚህ ምድር ላይ ለሚገኙት ልጆቹ እንዴት ያለ ውብ መኖሪያ አዘጋጀላቸው! ብራ ሆኖ ከዋለበት የሥራ ቀን በኋላ ቀዝቀዝ ያለ የዕረፍት ሌሊት እንዲመጣ አድርጓል። ለጥቅማችንና ለደስታችን ሲል ወቅቶች እንዲፈራረቁ አዘዘ። (ዘፍጥረት 8:22) ውኃ የተባለውን ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ነገር በብዛት በማዘጋጀት በተፈለገበት ቦታ ሁሉ ቀድተን እንድንጠቀምበት በምድር ሁሉ ላይ እንዲገኝ አደረገ። መኖሪያችን በሆነችው ሉል ላይ ብዙ ሚልዮን ካሬ ኪሎሜትር የሚሸፍን አስደሳች አረንጓዴ ምንጣፍ ዘርግቷል። ውብ ኅብረ ቀለም ባላቸው አስደሳች አበቦችም አስጊጧታል። አስደሳች በሆኑ ደኖች፣ ሐይቆችና ተራራዎች መካከልም ውብ ገጽታ ሰጥቷታል። በምድር “ጎተራ” ውስጥ በጣም ብዙ የሆነ ከሰል፣ ዘይትና ሌሎች የኃይል ምንጮች አከማችቷል። የምድርን ጓዳ በጥራጥሬዎች፣ በፍራፍሬዎች፣ በአትክልቶችና በሌሎች ጣፋጭ ምግቦች ያለማቋረጥ አትረፍርፎ ይሞላዋል። የሰማዩ አባታችን እንዴት ያለ ጥበበኛና አሳቢ የሆነ ሰጪ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ አምላክ” ብሎ ይጠራዋል። እኛም ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። — 1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት፤ ኢሳይያስ 25:6–8

የአባታችን “ስም”

5. የኢየሱስን የናሙና ጸሎት መክፈቻ ቃላት ስንጸልይ የልባችን ፍላጎት ምን መሆን ይኖርበታል?

5 አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን በለጋስነቱ “ጥሩ ስም” ወይም መልካም ዝና አለው። ማንኛውም ሰብዓዊ አባት የግል ስም እንዳለው ሁሉ እርሱም የግል መጠሪያ ስም አለው። አክብሮት የሚገባው ሰብዓዊ አባት ካለን ስሙና ዝናው ሲነቀፍ ብናይ በጣም ሊያስጠላን ይገባል። ስሙ ተከብሮ የማየት ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። ከዚህ ይበልጥ ግን የሰማያዊ አባታችን ስም ሲከበር ማየት ምኞታችን መሆን ይኖርበታል። እንግዲያው ኢየሱስ ናሙና እንዲሆነን በሰጠን ጸሎት ውስጥ የመጀመሪያ ቦታ የተሰጣቸውን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ” የሚሉትን ቃላት የምንጸልየው ከልባችን መሆን አለበት። — ማቴዎስ 6:9፤ ምሳሌ 22:1 አዓት የግርጌ ማስታወሻ።

6. የአምላክን ስም በተመለከተ ምን ለማየት ትፈልጋለህ?

6 የሰማይና የምድር ታላቅ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ስም በከፍተኛ ደረጃ እንዲከበር፣ ከሌሎች ስሞች ሁሉ በላይ ከፍ እንዲልና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ክቡር፣ ትርጉም ያለው፣ ተወዳጅ ስም ሆኖ እንዲታይ ምን ጊዜም የጋለ ጸሎታችን መሆን አለበት። ከእኛ መዳን ይልቅ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ነገር ይህ የአምላክ ቅዱስ ስም መቀደስ ነው። ስሙና ዝናው መቀደስና ክፉ ስም ያላቸው ፍጥረታት ከቆለሉበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ መሆን ይኖርበታል።

7. የአምላክ የግል መጠሪያ ስም ማን ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያሳያል?

7 የሰማዩ አባታችን የግል መጠሪያ ስም ማን ነው? ስሙ ማን እንደሆነ የዚህ ታላቅ ስም ባለቤት ጠላቶች እንዳሉት በሚናገሩ ጥቅሶች ዙሪያ ተገልጿል። በእንግሊዝኛው የኪንግ ጀምስ ትርጉም ላይ መዝሙር 83 ቁጥር 17 እና 18 ጠላቶቹን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ይፈሩ፣ ለዘላለም ይታወኩ፣ ይጎስቁሉ ይጥፉም። አሕዛብ ስምህ ይሖዋ የሆንከው አንተ ብቻ በምድር ሁሉ የበላይ እንደሆንክ ይወቁ።” — በተጨማሪም መዝሙር 100:3 አዓት ተመልከት።

8. የአምላክ ጠላቶች ስሙን ምን ለማድረግ ጥረዋል? ከምንስ ውጤት ጋር?

8 ስለዚህ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው። ይሁን እንጂ እርሱን እናመልካለን የሚሉ ብዙ ሰዎች ይህንን ስም አቃለዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ስሙን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው እየለቀሙ አጥፍተውታል። በዚያ ፈንታ “ጌታ” እና “እግዚአብሔር” የሚሉትን መጠሪያዎች ተክተዋል። ይህ ድርጊት የአምላክን ገናና ስም የሚሰውር ብቻ ሳይሆን ጌታ ይሖዋን ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሌሎች “ጌቶችና” “አማልክት” ለመለየት የሚያደናግር ነው። (መዝሙር 110:1፤ ዘዳግም 10:17፤ ሮሜ 1:4፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ሰዎች ይህንን ስም ለመቅበር ጉድጓድ እየቆፈሩለት ስምህ ይቀደስ እያሉ እንዴት በሐቅ መጸለይ ይችላሉ?

9. (ሀ) የአምላክ ስም በዕብራይስጥ በምን ሁኔታ ተጽፎ ይገኛል? በሌሎች ልሳኖችስ እንዴት ይጠራል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስንት አካል መሆኑን ይገልጻል?

9 ወደር የለሹ የአምላክ መጠሪያ ስም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ በዕብራይስጥ יהוה በሚሉት ፊደላት የሚጻፍ ሲሆን አንዳንዶች እነዚህን ፊደላት ያህዌህ ብለው ያነቧቸዋል። በአብዛኛው ተቀባይነት ያለው የእንግሊዝኛ አጠራር “Jehovah” (ጅሆቫ) ሲሆን በአማርኛ ይሖዋ ነው፤ በሌሎች ልሳኖችም ስሙ ተመሳሳይ አጠራር አለው። ይሖዋ በሚለው ስም ከተጠቀምን ማንን ማለታችን እንደሆነ በግልጽ ለማመልከት እንችላለን። ይሖዋ “አንድ ይሖዋ” ነው። ይሖዋ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም። ምክንያቱም ኢየሱስ የአምላክ ታማኝ ልጅ፣ “የማይታይ አምላክ ምሳሌ . . . ከፍጥረት ሁሉ በኩር” ነው። — ቆላስይስ 1:15፤ ማርቆስ 12:29፤ ዘዳግም 6:4

10. የአምላክ ስም ትርጉም ምንድን ነው? ይህንንስ በተግባር የገለጸው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ የተባለው ስም ኃይለኛ ትርጉም አለው። “የሚያስሆን (ወይም ሆኖ የሚገኝ)” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። ይህም ነገሮችን ከመፍጠሩ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ራሱን በተመለከተ ነው። በዚህም ምክንያት ሕዝቡን እስራኤልን ከግብጹ ፈርዖን እጅ በተአምር ለማስለቀቅ በተዘጋጀበት ጊዜ ይሖዋ የተባለው የእርሱ “መታሰቢያ” ስም እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። (ዘፀዓት 3:13–15) በኋላም ነቢዩ ኤርምያስ ሉዓላዊው ይሖዋ ‘በታላቅ ኃይሉና በተዘረጋች ክንዱ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ’ እና ‘በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ’ መሆኑን በተናገረ ጊዜ ይሖዋ ለነቢዩ ራሱ በወሰነው ጊዜ ሕዝቡን ከባቢሎናዊው ምርኮ ነፃ አውጥቶ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ የማይቻል የሚመስል ድርጊት እንደሚያከናውን አረጋግጦለት ነበር። ይህንንም አድርጎታል! — ኤርምያስ 32:17–19, 27, 44፤ 2 ዜና. 36:15–23

11. ዛሬ የአምላክ ስም ከመንግሥቱ ጋር ሊያያዝ የሚችለው እንዴት ነው?

11 ዛሬም ይሖዋ ያሰበውን “የሚያስሆን” ታላቅ አምላክ ነው። ማንኛውንም የተፈለገ ሚና ለመጫወት፣ በመንግሥቱ አማካኝነት ድንቅ ነገሮችን ለማከናወን፣ ስሙን ለመቀደስና ለሕዝቡ ጥቅም ሲል የተፈለገውን መሆን ይችላል። ያሰበው ነገር ሁሉ ይሳካል፣ ይፈጸማል። — ኢሳይያስ 48:17፤ 55:11

የአምላክ ስም ተቀድሷልን?

12. የሰው ልጆች አምላክን በምን መንገድ ይመለከቱታል?

12 የሰው ልጆች ለዚህ እንከን ለማይወጣለትና በምድር ላሉት ፍጥረቶቹ በሙሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሚያስደንቅ መንገድ ላዘጋጀው ገናና አምላክ አድናቆትን፣ አክብሮትንና ፍቅርን አሳይተዋልን? በምድር ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ብትመለከት መልሱ ግልጽ ይሆንልሃል። ክርስቲያን ብሔራት ተብለው በሚታወቁት አገሮች ባሉት ሃይማኖቶች አምላክ በሚያሳዝን ሁኔታ ያልሆነ ስም ሲሰጠው ቆይቷል። ከእነዚህ ብሔራት ውስጥ ብዙዎቹ እርሱን ወገናዊ አምላክ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር መሰሎቻቸው የሆኑትን ሌሎችን ሕዝቦች ለመውጋት ሲነሡ እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ጸልየዋል። ሌሎቹ ደግሞ “ከሥጋ የተለዩ ነፍሳትን” ወደሚያሠቃይ ዘላለማዊ እሳት የሚጥል ጨካኝ አምላክ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ ሕይወት አልባ በሆኑ የእንጨትና የድንጋይ ምስሎች በመመሰል ዝቅ አድርገውታል። ብዙዎችም አምላክ አያይም ወይም ግድ የለውም በማለት ሆን ብለው የጽድቅ ሕግጋቱን ጥሰዋል። — ከሥራ 10:34, 35፤ ከኤርምያስ 7:31፤ ከኢሳይያስ 42:8፤ እና ከ1 ጴጥሮስ 5:7 ጋር አወዳድር።

13. ሌሎች ያሳሳቷቸው ሰዎች ፍቅር በጎደለው መንገዳቸው እንዲቀጥሉ ቢፈቀድላቸው የመጨረሻው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል?

13 ይሁን እንጂ በመሪዎቻቸው የተሳሳቱ ሰዎች አምላክን የማይወዱና ስሙን የማይቀድሱ ከሆኑ መሰሎቻቸው የሆኑትን ሰብዓዊ ፍጡሮች እንዴት ለመውደድ ይችላሉ? (1 ዮሐንስ 4:20, 21፤ 5:3) በሰው ዘር መካከል እንደገና ፍቅር ካልተመለሰ ዓለም በመጨረሻ መለያየት፣ ዓመፅና ሥርዓት አልበኛነት የሞላባት ጫካ መሆንዋ አይቀርም። በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም እንኳ ሁኔታው እንደዚህ ሆኗል። በብሔራት መካከል የኑክሌር መሣሪያዎች እየተሰራጩ በመሆኑ አንድ ቀን ጦርነት የሚያስደስታቸው ሰዎች ጠቅላላውን የሰው ዘር ሊደመስሱ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ አፍቃሪው አባታችን ፈጽሞ የማይፈቅደው ነገር ነው! — መዝሙር 104:5፤ 119:90፤ ኢሳይያስ 45:18

አምላክ ስሙን የሚቀድሰው እንዴት ነው?

14, 15. የአምላክን ስም ለመቀደስ በግንባር ቀደምትነት የሚዋጋው ማን ነው? እንዴትስ?

14 የአምላክን ስም ለመቀደስ ቀዳሚ ሆኖ የሚዋጋው ማን ነው? ይሖዋ ራሱ ነው! ይህንንም የሚያደርገው የጽድቅ የአቋም ደረጃዎቹን ለማስከበር እርምጃ በመውሰድ ነው። መሰሎቻቸው የሆኑትን ሰዎች የሚጨቁኑትንና ስለ አምላክ ሐሰት የሆነ ትምህርት የሚያስተምሩትን ጨምሮ ቅዱስ ፈቃዱን በሚያራክሱ ሁሉ ላይ ፍርዱን ይፈጽምባቸዋል። (መዝሙር 140:12, 13፤ ኤርምያስ 25:29–31) ይሖዋ ራሱን መካድ አይችልም። እርሱ በሁሉም ፍጥረቶቹ ሊመለክ የሚገባው እውነተኛ አምላክ ነው። ሁሉም ፍጥረታት ሊታዘዙት የሚገባ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው። — ሮሜ 3:4፤ ዘፀዓት 34:14መዝሙር 86:9

15 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ስሙን ለመቀደስ ሲል ከዓላማው ጋር በመፃረር ብልሽት ለመፍጠር የሚሯሯጡትን ሰዎች በሙሉ ከዚህ ምድር ጠራርጎ ያስወግዳል። ይህንንም የሚያደርግበት ምክንያት ክፋትን ስለሚጠላና ጽድቅን ስለሚወድ ነው። (መዝሙር 11:5–7) እርሱ ራሱ “ታላቅ እሆናለሁ፤ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንሁ ያውቃሉ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 38:23) እንግዲያው የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ስሙን እንደ ቅዱስና የተሟላ አክብሮት እንደሚገባው አድርገን በመያዝ እንዲሁም ከፈቃዱ ጋር ተስማምተን በመኖር ስሙን መቀደስ እንዳለብን ግልጽ ነው።

16. የአምላክን ስም በመቀደስ በኩል አኗኗራችን ምን ድርሻ አለው?

16 ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ የአምላክን ስም ያስከብረዋል አለዚያም ያዋርደዋል። እንግዲያው ሁላችንም ሌሎች ሰዎች ስለምናገለግለው ስለዚህ ታላቅ አምላክ ጥሩ እንዲናገሩ በሚያደርግና የይሖዋንም ልብ ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንኑር። (1 ጴጥሮስ 2:12፤ ምሳሌ 27:11) ታዛዥ ልጆች በመሆን ስለ ስጦታዎቹ ሁሉ፤ በልጁ መንግሥታዊ አገዛዝ ሥር የበለጠ ክብር ስለምትለብሰው አስደሳች ምድራችንም ጭምር አባታችንን እንደምናመሰግን ለማሳየት መፈለግ ይኖርብናል። — ኢሳይያስ 6:3፤ 29:22, 23

17. ወደ “ዘላለሙ ንጉሥ” በጸሎት መቅረብ ያለብን ምን ዓይነት ዝንባሌ ይዘን ነው?

17 በዚህ “የዘላለም” ንጉሥ ተቀባይነት አግኝቶ ከእርሱ ጋር ዝምድና መመሥረት ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! ይሁን እንጂ ሁላችንም ኃጢአተኛ ከሆኑ ወላጆች የተፀነስንና ፍጽምና ጎድሎን የተወለድን በመሆናችን ለዚህ መብት የታደልነው በራሳችን ጥሩነት ምክንያት አይደለም። ነገር ግን ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት:- “ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፤ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ብለን ለመጸለይ እንችላለን። (መዝሙር 51:5–10) “በሰማያት የሚኖረው አባታችን” ከእኛ የሚፈልገው ምን እንደሆነ እየተማርን መንግሥቱ ከምታመጣቸው ዘላለማዊ በረከቶች ተካፋይ እንድንሆን ልንጸልይ እንችላለን። አዎን፣ የአምላክ መንግሥት ትምጣ ብለን በልበ ሙሉነት ለመጸለይ እንችላለን። የዚህች መንግሥት መምጣት በዚህ ምድር ላይ ለሚኖሩት የሰው ዘሮች ምን ማለት ይሆናል? እስቲ እንመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]