በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል!

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል!

መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል!

በሕይወትህ ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ “የሰው ልጅ መከራና ሥቃይ እንዲህ የበዛው ለምንድን ነው?” ብለህ ጠይቀህ ይሆናል። የሰው ዘር ለብዙ ሺህ ዓመታት በጦርነት፣ በድህነት፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ በወንጀል፣ በፍትሕ መጓደል፣ በበሽታና በሞት በእጅጉ ሲሠቃይ ኖሯል። በተለይ ያለፈው መቶ ዓመት ደግሞ ከሁሉ የከፋ ነበር። ታዲያ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ የሚያከትምበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

አዎን። እንዲያውም ይህ ጊዜ በእጅጉ እንደቀረበ ማወቁ በጣም የሚያጽናና ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት ይናገራል። ገሮች ምድርን የሚወርሱት ለምን ያህል ጊዜ ነው? የአምላክ ቃል “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት መልሱን ይሰጠናል።—መዝሙር 37:10, 11, 29

አምላክ ክፋትንና ሥቃይን ካስወገደ በኋላ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። ከዚያም ሰዎች ፍጹም ጤንነት አግኝተውና ደስተኞች ሆነው ለዘላለም ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም” በማለት ይናገራል።—ራእይ 21:4

በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ሙታን እንኳ ተነስተው ከዚህ በረከት ተቋዳሽ የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። የአምላክ ቃል “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ላይ እምነት እንዳለው ለገለጸው ንስሐ የገባ ክፉ አድራጊ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ያለው ለዚህ ነበር።—ሉቃስ 23:43

መከራና ሥቃይ የጀመረው ለምንድን ነው?

አምላክ የሰው ልጆች እንዲህ ያለ አስደሳች ሕይወት እንዲኖሩ ዓላማው ከነበረ ሥቃይና መከራ እንዲጀምር የፈቀደው ለምንድን ነው? ለዚህን ያህል ረጅም ዘመን የሰው ልጅ ሲሠቃይ ዝም ብሎ የተመለከተውስ ለምንድን ነው?

አምላክ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹም አድርጎ ነበር። እጅግ ውብ በሆነ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደረገ ከመሆኑም በላይ አርኪ ሥራ ሰጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:31) አምላክን ታዝዘው ቢሆን ኖሮ ፍጹም የሆኑ ልጆችን መውለድ ይችሉ የነበረ ሲሆን መላዋ ምድርም ሰዎች በሰላምና በደስታ ለዘላለም የሚኖሩባት ገነት ትሆን ነበር።

አምላክ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው የማሰብ ችሎታ የሌለው ሮቦት ወይም ማሽን አድርጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ደስተኞች ሆነው መቀጠል የሚችሉት ይህንን ነፃነታቸውን በትክክል ከተጠቀሙበት ማለትም የአምላክን ሕግ ከታዘዙ ብቻ ነው። አምላክ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 48:17) ሰዎች ከአምላክ አመራር ውጭ የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ሆነው ስላልተፈጠሩ የመምረጥ ነፃነትን አላግባብ መጠቀም የከፋ መዘዝ ያስከትላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” ይላል።—ኤርምያስ 10:23

የሚያሳዝነው ነገር የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከአምላክ አመራር ውጭ ሆነው ራሳቸውን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና ለአምላክ አገዛዝ ጀርባቸውን ሰጥተው የእሱን ድጋፍ ማግኘትና ፍጹም ሆነው መቀጠል አይችሉም። በዚህም ምክንያት ለእርጅና ብሎም ለሞት ተዳረጉ። እኛም የእነሱ ልጆች ስለሆንን ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል።—ሮሜ 5:12

ሉዓላዊነትን በሚመለከት የተነሳ አንገብጋቢ ጥያቄ

አምላክ አዳምና ሔዋንን አጥፍቶ ሌላ ባልና ሚስት ለምን አይፈጥርም ነበር? ይህን ያላደረገው የእሱን ሉዓላዊነት ወይም አጽናፈ ዓለምን የመግዛት መብት በተመለከተ የተነሳ ጥያቄ ስለነበረ ነው። ጥያቄው:- የመግዛት መብት ያለው ማን ነው? ትክክለኛውስ አገዛዝ የማን ነው? የሚል ነበር። በሌላ አነጋገር ሰዎች ከአምላክ አገዛዝ ወጥተው ራሳቸውን ቢያስተዳድሩ ይሳካላቸዋል? ‘ሰዎች የሚበጃቸው በአምላክ አገዛዝ ሥር ቢቀጥሉ ነው ወይስ ሙሉ በሙሉ ከእሱ አመራር ወጥተው ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ?’ የሚለው ጥያቄ የማያዳግም መልስ እንዲያገኝ አምላክ በቂ ጊዜ ሰጥቷል። ይህ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት በበቂ ሁኔታ መሞከር እንዲችሉ ረጅም መሆን ነበረበት።

ውጤቱስ ምን ሆኖ ተገኘ? ብዙ መቶ ዘመናትን ያስቆጠረው የሰው ልጅ ታሪክ የሚመሰክረው ችግሩና መከራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መሄዱን ነው። ባለፈው መቶ ዓመት የሰው ዘር ያሳለፈው መከራና ሥቃይ ከምንጊዜውም የከፋ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በ100 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በተለያዩ ጦርነቶች ተማግደዋል። ወንጀልና ዓመጽ ዓለማችንን አጥለቅልቀዋታል። አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች እንደ ሰደድ እሳት መዛመታቸውን ቀጥለዋል። በረሃብና በበሽታ ሳቢያ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይረግፋሉ። ቤተሰብ እየፈራረሰ ሲሆን የሰዎች ሥነ ምግባር ከምንጊዜውም ይበልጥ አዝቅጧል። የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት አልቻለም። ከእነዚህ መንግሥታት መካከል አንዱም ቢሆን እርጅናን፣ በሽታንና ሞትን አላጠፋም።

የሰው ዘር ያለበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናችን በትንቢት እንደተናገረው ነው። የአምላክ ቃል ያለንበትን ጊዜ የዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ በማለት የሚጠራው ሲሆን ይህ ዘመን ‘አስጨናቂ’ እንደሚሆንም ይገልጻል። ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ክፉዎችና አታላዮች በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ በመሄድ’ ላይ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13

መከራና ሥቃይ የሚያከትምበት ጊዜ ደርሷል

ማስረጃዎቹ ሁሉ፣ የሰው ልጅ ከአምላክ አመራር ወጥቶ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያደረገው ከንቱ ሙከራ የሚያበቃበት ጊዜ ላይ እንደደረስን ይጠቁማሉ። ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር እንደማይችሉ በግልጽ ታይቷል። ሰላም፣ ደስታ፣ ፍጹም ጤንነትና የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ የሚችለው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው። ስለዚህ ይሖዋ ክፋትንና መከራን የታገሠበት ጊዜ ሊያበቃ ተቃርቧል። በቅርቡ አምላክ ምንም ሊሳካለት ያልቻለውን ይህን ሥርዓት በማስወገድ በሰው ዘር ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ይገባል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት ይናገራል። (ዳንኤል 2:44) ይሖዋ በሰማይ ባቋቋመው መንግሥት አማካኝነት ሉዓላዊነቱን ወይም የመግዛት መብቱን ያረጋግጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በዋነኝነት በዚህ ላይ ያተኮረ ነው። ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡን የሚጠቁመው ዋነኛው ምልክት ምን እንደሆነ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:14

ይህ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት የሚተርፉት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ምሳሌ 2:21, 22) እዚህ ላይ ቅኖች የተባሉት የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ተምረው በተግባር የሚያውሉ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) በእርግጥም “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት “በ1993 ዓ.ም ከታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። አንዳንዶቹን ጥቅሶች በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።