መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 1
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ዛሬ የምንኖረው ችግሮች በሞሉበትና ውሉ በጠፋው ዓለም ውስጥ ነው። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዘወትር በረሃብ ይሰቃያሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች እየሆኑ ነው። በየጊዜው ብዙ ቤተሰቦች ይፈራርሳሉ። በሥጋ ዘመዳሞች መካከል ስለሚፈጸም የጾታ ብልግናና በቤተሰብ ውስጥ ስለሚፈጸመው ግፍ በየጊዜው በዜና እንሰማለን። የምንተነፍሰው አየርና የምንጠጣው ውኃ ቀስ በቀስ እየተመረዘ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎቻችን ለወንጀል ጥቃት ተጋልጠናል። እንደነዚህ ያሉት ችግሮች መፍትሔ ይኖራቸዋል ብለህ ታስባለህ?
1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) የሰው ልጅ መመሪያ እንደሚያስፈልገው የሚያሳዩት የትኞቹ የዘመናችን ችግሮች ናቸው?
ከዚህም በተጨማሪ የምንኖረው ቁርጥ ያለ ምርጫ ማድረግ አስቸጋሪ በሆነበት ዘመን ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ውርጃ ያልተወለደውን ሕፃን ነፍስ ማጥፋት እንደሆነ ስለሚሰማቸው ይህን ድርጊት አጥብቀው ይቃወማሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሴቶች በገዛ አካላቸው ላይ ሥልጣን ስላላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ውሳኔ ሊያደርጉ ይገባል የሚል ጽኑ አቋም አላቸው። ብዙዎች ግብረ ሰዶምን፣ ምንዝርንና ከጋብቻ በፊት የሚፈጸምን የጾታ ግንኙነት እንደ ትልቅ ብልግና አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ እነዚህን ድርጊቶች መፈጸምና አለመፈጸም የግል ምርጫ ነው ብለው ያምናሉ። የትኞቹ ወገኖች ትክክል የትኞቹ ደግሞ ስህተት እንደሆኑ ሊነግረን የሚችለው ማን ነው?
2, 3. ዛሬ ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል?
2 መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን በሚመለከት መመሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ እንደ ወንጀል፣ ረሃብና የአካባቢ መበከል ያሉት ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ይገልጻል። ችግሩ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የሚናገረውን ነገር ብዙ ሰዎች በቁም ነገር መመልከት
ትተዋል። ከዚህ ቀደም ይህ መጽሐፍ ቢያንስ በምዕራቡ ዓለም እንኳ ትልቅ ተሰሚነት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በሰዎች አማካኝነት ቢሆንም እንኳ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች የአምላክ ቃል መሆኑንና መልእክቱም አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው እንደሆነ ያምኑ ነበር።3 ይሁን እንጂ ዛሬ እያንዳንዱን ነገር መጠራጠር የተለመደ ሆኗል። ሰዎች ባህላቸውን፣ የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን፣ የሥነ ምግባር ደንቦችንና የአምላክን መኖር እንኳ ሳይቀር ይጠራጠራሉ። በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚነት በተመለከተ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ጊዜ ያለፈበትና አላስፈላጊ እንደሆነ አድርገው የሚያዩት ይመስላል። ከዘመናችን ምሁራን መካከል መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው የሚመለከቱት በጣም ጥቂት ናቸው። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ከምሁሩ ጄምስ ባር አባባል ጋር ይስማማሉ:- “ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልማዶች ያለኝ አመለካከት የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት ናቸው የሚል ነው። የሰው ልጅ የራሱን እምነት ያሠፈረበት መጽሐፍ ነው።”1
4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆን አለመሆኑን ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ምንድን ነው?
4 የአንተም አመለካከት እንደዚህ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ብለህ ነው የምታስበው ወይስ የሰው? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን ይህን ነጥብ ልብ በል:-
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የጻፉት ተራ መጽሐፍ ከሆነ ለሰው ልጅ ችግሮች ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ መልስ አይገኝም ማለት ነው። የሰው ልጆች በገዛ እጃቸው በሚያመጡት ጣጣ ከሕልውና ውጭ እንዳይሆኑ ወይም በኑክሌር ጦርነት እንዳያልቁ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በጭፍን መዳከር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ከሆነ ግን ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ የሚያስፈልገን ዋነኛው ነገር እርሱ ይሆናል።5 መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀርበዋል። የመጽሐፉ አዘጋጂዎችም እነዚህን ማስረጃዎች ከመረመርክ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጅ ችግሮች ትክክለኛውን መልስ የያዘ ብቸኛ መጽሐፍ መሆኑን ትገነዘባለህ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ልትመረምረው የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ልንጠቁምህ እንወዳለን።
በብዛት በመሸጥ አቻ ያልተገኘለት
6, 7. መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ አንዳንድ አስገራሚ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ታትሞ በመሸጥና በሰፊው በመሠራጨት ረገድ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። ጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሬኮርድስ የተባለው መጽሐፍ በ1988 እትሙ እንደገለጸው ከ1815 እስከ 1975 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 2,500,000,000 የሚገመቱ ቅጂዎች ታትመዋል። ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ሊሠራጭ ይቅርና ወደዚያ ቁጥር የተጠጋ እንኳን መጽሐፍ በታሪክ አልታየም።
7 ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ አይገኝም። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ከ1,800 በሚበልጡ የተለያዩ ቋንቋዎች ይገኛል። የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሪፖርት እንዳደረገው ዛሬ 98 በመቶ የሚሆነው የፕላኔታችን ነዋሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ይችላል። እነዚህን ሁሉ ትርጉሞች ማዘጋጀት ምን ያህል ጥረት እንደሚጠይቅ እስቲ አስበው! ይህን ያህል ትኩረት የተሰጠው ሌላ መጽሐፍ ይገኛልን?
ተደማጭነት ያለው መጽሐፍ
8, 9. መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ተደማጭነት በሚመለከት አንዳንድ ሰዎች ምን አስተያየት ሰጥተዋል?
8 ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ መጽሐፍ ቅዱስን “በታሪክ ዘመናት ከታዩት ጽሑፎች ሁሉ ይበልጥ ተደማጭነት ያለው የመጻሕፍት ስብስብ” ሲል ጠርቶታል።2 የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ ባለቅኔ ሄንሪክ ሃይነ እንዲህ ሲል አምኗል:- “ይህን ሁሉ ማስተዋል ያገኘሁት ከአንድ መጽሐፍ ነው። . . . መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ። ቅዱስ መጽሐፍ መባሉ ይገባዋል። አምላኩን ያጣ ሰው ካለ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ሊያገኘው ይችላል።”3 በዚሁ መቶ ዘመን የኖረውና የፀረ ባርነት እንቅስቃሴ አራማጅ የነበረው ዊልያም ኤች ሴዋርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የሰው ልጅ የመሻሻል ተስፋ የተመካው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ተደማጭነት ላይ ነው።”4
9 የዩናይትድ ስቴትስ 16ኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “አምላክ ለሰው ልጅ ከሰጠው ስጦታ ሁሉ የላቀ ስጦታ ነው። . . . መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ መልካሙንና ክፉውን ለይተን ማወቅ ባልቻልን ነበር።”5 የብሪታንያው የሕግ ሰው ሰር ዊልያም ብላክስተን “ሁሉም ሰብዓዊ ሕጎች የተመሠረቱት በእነዚህ ሁለት ሕጎች ማለትም በተፈጥሮ ሕግና አምላክ ለሰዎች በገለጸው ሕግ [መጽሐፍ ቅዱስ] ላይ ነው፤ እንግዲያው ሰብዓዊ ሕጎች ከእነዚህ ሕጎች ጋር እንዲጋጩ ማድረግ አይገባም ማለት ነው”6 ብለው ሲናገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ተደማጭነት እንዳለው ጎላ አድርገው መግለጻቸው ነበር።
የተጠላና የተወደደ
10. ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹት እንዴት ነው?
10 በአንጻሩ ደግሞ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የከረረ ተቃውሞ ብሎም ጥላቻ የገጠመው መጽሐፍ አለመኖሩን ልብ ልንል ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ከመካከለኛው ዘመን አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ በአደባባይ ተቆልሎ እንዲቃጠል ተደርጓል። በዛሬው ዘመን እንኳ ሳይቀር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባቸው ወይም በማሠራጨታቸው ምክንያት የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ወይም በእስራት የተቀጡ ሰዎች አሉ። ባለፉት መቶ ዘመናት እንዲህ ያለው “ወንጀል”
ብዙውን ጊዜ አሰቃቂ ለሆነ ድብደባ አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ ነበር።11, 12. ቲንደል ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ውስጥ ያሳደረው ፍቅር ከዚሁ ጎን ለጎን የሚታይ ነው። ብዙዎች የማያቋርጥ ስደት ቢደርስባቸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸውን ገፍተውበት ነበር። ለምሳሌ ያህል በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረውንና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አስተማሪ የነበረውን ዊልያም ቲንደልን ተመልከት።
12 ቲንደል ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ነበረው። ይሁን እንጂ በዘመኑ የነበሩት ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣኖች መጽሐፍ ቅዱስ ሙት በነበረው በላቲን ቋንቋ ተወስኖ እንዲቀር ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገቱ ነበር። ቲንደል ግን የአገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ እንዲኖራቸው በማሰብ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም ቆርጦ ተነሣ። ይህ ተግባሩ ከሕጉ ጋር የሚቃረን ስለነበር ቲንደል ጥሩ የማስተማር ሥራውን ትቶ መሰደድ ግድ ሆነበት። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን (“አዲስ ኪዳን”) እና አንዳንዶቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (“ብሉይ ኪዳን”) ወደ አገሩ ቋንቋ ተርጉሞ እስከሚጨርስ ድረስ ኑሮውን በስደት ለመግፋት ተገዷል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ በመያዙና መናፍቅ ነው ተብሎ በመወንጀሉ ተሰቅሎ እንዲሞትና በድኑም በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል።
13. መጽሐፍ ቅዱስን በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ነገር ምንድን ነው?
13 ቲንደል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወይም ለሌሎች ሰዎች
እንዲዳረስ ለማድረግ ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ከከፈሉት በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ከሌላው ሰው የተለየ ምንም ነገር ያልነበራቸውን ብዙ ወንዶችና ሴቶች ይህን ያህል ድፍረት እንዲኖራቸው ያነሳሳ ሌላ መጽሐፍ በታሪክ ውስጥ አልታየም። ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም አቻ አይገኝለትም።የአምላክ ቃል መሆኑ ተገልጿል
14, 15. የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ በተደጋጋሚ ምን ተናግረዋል?
14 ብዙዎቹ ጸሐፊዎች ስለእሱ የተናገሩት ነገርም መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ያደርገዋል። አርባ የሚያክሉ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን የተለያዩ ክፍሎች በመጻፉ ሥራ የተካፈሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ነገሥታት፣ እረኞች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ካህናት እንዲሁም ቢያንስ አንድ ጄኔራልና አንድ የሕክምና ሰው ይገኙባቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጸሐፊዎች ያሰፈሩት የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ገልጸዋል።
15 ከዚህ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበር” ወይም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚሉትን የመሰሉ መግለጫዎች በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እናገኛለን። (2 ሳሙኤል 23:2፤ ኢሳይያስ 22:15) ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል ሥራ አብሮት ለተሰማራ ሰው በጻፈው መልእክት ላይ እንዲህ ብሏል:- “ቅዱስ መጽሐፍ ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሰጽ፣ ስህተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 የ1980 ትርጉም
16. መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል?
16 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንጂ የሰው አይደለም ከሚለው አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ አምላክ ብቻ ሊመልሳቸው ለሚችላቸው ጥያቄዎች መልስ ይዟል። ለምሳሌ ያህል ሰብዓዊ መንግሥታት ዘላቂ ሰላም ሊያመጡ ያልቻሉበትን ምክንያት፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ጥልቅ እርካታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የምድርና በእርሷ ላይ የሚኖሩት ሰዎች የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነ
ይገልጻል። የማስተዋል ችሎታ ያለህ እንደ መሆንህ መጠን እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች በአእምሮህ ውስጥ ሳይጉላሉ አይቀሩም። ታዲያ ቢያንስ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆን አለመሆኑን እንዲሁም አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ብቸኛ መጽሐፍ መሆኑን ለማረጋገጥ ለምን አትመረምርም?17, 18. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘሩትና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተነሱት አንዳንዶቹ ክሶች ምንድን ናቸው? (ለ) የትኞቹ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችም ይነሣሉ?
17 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡትን ማስረጃዎች በጥንቃቄ እንድታገናዝብ እናበረታታሃለን። አንዳንዶቹ ምዕራፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተደጋጋሚ ሲሰነዘሩ የምንሰማቸውን ትችቶች የሚዳስሱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢ-ሳይንሳዊ ነውን? እርስ በእርሱስ ይጋጫልን? በውስጡ የያዘው እውነተኛ ታሪኮችን ነው ወይስ ተረት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ተዓምራት በእርግጥ የተፈጸሙ ናቸውን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ምክንያታዊ ማስረጃ ቀርቧል። ከዚያም በኋላ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚያሳዩት ጠንካራ ማስረጃዎች ተብራርተዋል። እነዚህም በውስጡ የያዛቸው ትንቢቶች፣ ጥልቀት ያለው ጥበቡ እንዲሁ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያመጣው አስገራሚ ለውጥ ናቸው። በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ በአንተ ሕይወት ላይ ምን ውጤት ሊኖረው እንደሚችል እንመለከታለን።
18 በመጀመሪያ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እኛ የደረሰው እንዴት እንደሆነ እንወያያለን። ይህ አስገራሚ መጽሐፍ ያሳለፈው ታሪክ ራሱ የሰው ሥራ ውጤት እንዳልሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት በመሠራጨትና በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ በታሪክ አቻ ያልተገኘለት መጽሐፍ ነው
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ15ኛው መቶ ዘመን በእንጨት ላይ የተቀረጸው ይህ ሥዕል እንደሚያሳየው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ “ወንጀል” ተከሰው ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለዋል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በአምላክ መንፈስ እየተነዱ መጻፋቸውን ተናግረዋል