በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ወዳጅ

የመጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ወዳጅ

ምዕራፍ 3

የመጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ወዳጅ

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ክርስቲያን ባልሆኑ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ የሚሉበትን ዋነኛ ምክንያት እንወያያለን። ሕዝበ ክርስትና በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምታምንና የመጽሐፍ ቅዱስ ባለአደራ እንደሆነች ሲነገር ኖሯል። ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ከመካከለኛው ዘመን የመስቀል ጦርነቶችና የጅምላ ጭፍጨፋዎች አንስቶ በዘመናችን እስከተፈጸሙት እልቂቶች ድረስ እጅግ አረመኔያዊ ተብለው በታሪክ በሰፈሩ ድርጊቶች ውስጥ እጃቸው አለበት። የሕዝበ ክርስትና አድራጎት መጽሐፍ ቅዱስን ውድቅ ለማድረግ ምክንያት ይሆናልን? ሐቁ እንደሚያሳየው ሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ወዳጅ ናት። እውነትም ደግሞ ሕዝበ ክርስትና በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ብቅ በማለቷ መጽሐፍ ቅዱስ ህልውናውን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ትግል አበቃ ማለት አልነበረም።

1, 2. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አምነው ለመቀበል አሻፈረኝ የሚሉት ለምንድን ነው? (ለ) በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ምን ጥሩ ሥራ ተከናውኗል? ይሁን እንጂ ምን አደገኛ ሁኔታ ብቅ ማለት ጀምሮ ነበር?

በአንደኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተጠናቅቀው ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በመገልበጡና በማሠራጨቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ክርስቲያኖች ነበሩ። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በወቅቱ በሰፊው ይሠራባቸው ወደነበሩ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም ደፋ ቀና ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ የክርስቲያን ጉባኤ በዚህ የሚደነቅ ተግባር ተጠምዶ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስን ህልውና ስጋት ላይ የሚጥል አንድ አደገኛ ሁኔታ ብቅ ማለት ጀመረ።

2 መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይህ ሁኔታ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ በእርሻው ላይ ምርጥ የስንዴ ዘር ስለዘራ አንድ ሰው ምሳሌ ተናግሯል። ይሁን እንጂ “ሰዎቹ ሲተኙ” ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘራበት። ሁለቱም ዘሮች በቀሉና ለጊዜው እንክርዳዱ ስንዴውን ውጦት ቆየ። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ አማካኝነት የእርሱ ሥራ ውጤት እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሚሆኑ ነገር ግን እርሱ ከሞተ በኋላ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ወደ ጉባኤው ሾልከው እንደሚገቡ ገልጿል። ውሎ አድሮ እውነተኛውን ከሐሰተኛው መለየት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።​—⁠ማቴዎስ 13:​24-30, 36-43

3. ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው እንደ እንክርዳድ ያሉ “ክርስትያኖች” ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ በሚኖራቸው እምነት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምንድን ነው?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደ እንክርዳድ ያሉ እነዚህ “ክርስቲያኖች” ሌሎች ሰዎች ለክርስትና እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በሚመለከት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል:- “በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል።”​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​1, 2፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

4. ኢየሱስና ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገሯቸው ትንቢቶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሳይቀር ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

4 ኢየሱስና ጴጥሮስ የተናገሯቸው ትንቢቶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳ ሳይቀር ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀምረው ነበር። የሥልጣን ምኞት የተጠናወታቸው ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው በመግባት መከፋፈልን ዘርተው ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:​16-18፤ 2 ጴጥሮስ 2:​21, 22፤ 3 ዮሐንስ 9, 10) በቀጣዮቹ ሁለት መቶ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በግሪካውያን ፍልስፍና ተበርዞ የነበረ ሲሆን ብዙዎች በስህተት የአረማውያንን መሠረተ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆኑ አድርገው ተቀብለዋል።

5. በአራተኛው መቶ ዘመን “ክርስትናን” በሚመለከት ምን ለውጥ ተደርጓል?

5 በአራተኛው መቶ ዘመን “ክርስትና” የሮማ ንጉሣዊ ግዛት ኦፊሴላዊ ሃይማኖት ሆነ። ይሁን እንጂ ይህ “ክርስትና” ኢየሱስ ከሰበከው ሃይማኖት በእጅጉ የተለየ ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘እንክርዳዱ’ ተንሰራፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሲሆን እውነተኛውን ክርስትና የሚወክሉና መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን ተቀብለው በእርሱ መሠረት ለመሄድ የሚጥሩ ሰዎች እንደነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙ ሥራ ተቃውሞ ገጠመው

6. ሕዝበ ክርስትና አሁን ያላትን መልክ መያዝ የጀመረችው መቼ ነው? የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ከመጽሐፍ ቅዱሱ ክርስትና የሚለዩበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

6 ሕዝበ ክርስትና ዛሬ ያላትን መልክ መያዝ የጀመረችው በቆስጠንጢኖስ ዘመን ነው። ሥር የሰደደው ብልሹ ክርስትና ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሃይማኖታዊ ድርጅት ብቻ መሆኑ ቀርቷል። መሪዎቹን በፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አቀንቃኞች አድርጎ ያሰለፈ የፖለቲካ አካል ሆኗል። ቆየት ብሎ ደግሞ ከሀዲዋ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተደማጭነት የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና ሙሉ በሙሉ በሚቃረን መንገድ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ሥጋት ላይ የሚጥል ሌላ አደገኛ ሁኔታ ፈጥራለች። እንዴት?

7, 8. ሊቀ ጳጳሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹት መቼ ነው? ይህንንስ ያደረጉት ለምን ነበር?

7 ላቲን የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋ መሆኑ እየቀረ ሲመጣ ­አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መዘጋጀት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አልተዋጠላትም። ከጊዜ በኋላ የቦሄሚያ ንጉሥ የሆነው ቨራቲስላውስ በ1079 መጽሐፍ ቅዱስን በዜጎቹ ቋንቋ ለመተርጎም የሚያስችል ፈቃድ ይሰጡት ዘንድ ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛን ጠይቆ ነበር። የሊቀ ጳጳሱ መልስ አሉታዊ ነበር። እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ብዙውን ጊዜ በጉዳዩ ላይ ለሚያስቡበት ሰዎች ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ቅዱሳን ጽሑፎች በአንዳንድ ቦታዎች ምሥጢር ሆነው በመቅረታቸው የሚደሰተው ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው። ይኸውም ሁሉም ሰው እንደልቡ የሚያገኘው ነገር ከሆነ ምናልባት ለመጽሐፉ የሚኖራቸው ግምት ዝቅተኛ ይሆንና ሊንቁት ወይም ባለቻቸው ጥቂት እውቀት በተሳሳተ መንገድ ሊረዱትና ወደ ስህተት ሊመራቸው እንደሚችል በማሰብ ነው።”1

8 ሊቀ ጳጳሱ መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ሙት በሆነው የላቲን ቋንቋ ተወስኖ እንዲቀር ፈልገው ነበር። የመጽሐፉ ሐሳብ ተራው ሕዝብ በሚግባባባቸው ቋንቋዎች ሳይተረጎም “ምሥጢር” ሆኖ እንዲቀመጥ ፈልገው ነበር። * ሁሉም ሰዎች እንዲያነቡት ተብሎ በ5ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀውን የጄሮም ላቲን ቩልጌት መጽሐፍ ቅዱስን ለማፈን እንደ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበት ጀመር።

9, 10. (ሀ) የሮማ ካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራን በመቃወም የምታደርገው እንቅስቃሴ እየሰፋ የሄደው እንዴት ነው? (ለ) ቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ቅዱስን የተቃወመችበት ዓላማ ምን ነበር?

9 የመካከለኛው ዘመን እየተገባደደ ሲመጣ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስ በአገሬው ሰው ቋንቋ መተርጎም የለበትም የሚለውን አቋማቸውን እያጠናከሩ ሄዱ። በ1199 ሊቀ ጳጳስ ኢኖሰንት ሦስተኛ በሜትስ ጀርመን ለሚገኙት ጳጳስ መጽሐፍ ቅዱስ በአገሬው ቋንቋ መኖሩን የሚያወግዝ ጠንካራ ደብዳቤ ስለላኩላቸው ጳጳሱ በእጃቸው ሊገቡ የቻሉትን በጀርመንኛ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ በእሳት አቃጥለዋል።3 በ1229፣ በፈረንሳይ ቱሉዝ ከተማ የሚገኘው ሲኖዶስ “ምዕመናን” ብዙሐኑ በሚግባባበት ቋንቋ የተዘጋጀ ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይዘው መገኘት አይችሉም የሚል ድንጋጌ አውጥቷል።4 በ1233 በስፔይን ታራጎና የሚገኘው የክልሉ ሲኖዶስ “የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን” መጻሕፍት በሙሉ ተወርሰው መቃጠል አለባቸው የሚል ትእዛዝ አስተላልፏል።5 በ1407 በጳጳሱ ቶማስ አረንደል ተጠርቶ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ የተቀመጠው የቀሳውስቱ ሲኖዶስ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እንግሊዝኛም ሆነ ወደ ሌሎች ዘመናዊ ቋንቋዎች እንዳይተረጎም በጥብቅ ከልክሏል።6 በእንግሊዝም እንዲሁ የዌልስ ግዛት ጳጳስ የሆኑት ስታፎርድ በ1431 መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ መተርጎምንም ሆነ እንዲህ ዓይነት ትርጉሞችን ይዞ መገኘትን ከልክለው ነበር።7

10 እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጥረታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት አልነበረም። ጥረታቸው ጥቂቶች ብቻ ሊያነቡት በሚችሉት ቋንቋ እንዲወሰንና ቅርስ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነበር። በዚህ መንገድ እነርሱ መናፍቅነት ብለው ያሰቡትን እንደውነቱ ከሆነ ግን ሥልጣናቸውን የተፈታተነውን እንቅስቃሴ መግታት እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው ነበር። ይህ ጥረታቸው ቢሰምር ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ የምሁራንን ብቻ ትኩረት የሚስብና በሌሎቹ ተራ ሰዎች ሕይወት ላይ እምብዛም ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ምንም ኃይል የሌለው መጽሐፍ ይሆን ነበር።

ለመጽሐፍ ቅዱስ የቆሙ ሰዎች

11. ጁሊያን ሄርናንዴዝ በስፓንኛ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን በድብቅ ወደ ስፔይን ለማስገባት መሞከሩ ምን አስከትሏል?

11 ደስ የሚያሰኘው ግን ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እነዚህን ውሳኔዎች ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አቋም አደገኛ ነበር። ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው ተገኝተዋል በሚል “ወንጀል” ከባድ ስቃይ ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ጁሊያን ሄርናንዴዝ የተባለውን የስፔይን ተወላጅ ሁኔታ ተመልከት። ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያን ማርቲየርደም በተባለው መጽሐፉ ላይ ፎክስ እንደገለጸው ጁሊያን (ጁሊያኖ) “በርካታ ቁጥር ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሶች በእንጨት በርሜል ውስጥ ካጨቀ በኋላ የራይን ወይን ጠጅ አስመስሎ ከጀርመን ወደ አገሩ ለማስገባት አቅዶ ነበር።” ይሁን እንጂ ይጠቆምበትና በሮማ ካቶሊክ ኢንክዊዚሽን ይያዛል። የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ባለቤት ሊሆኑ የነበሩትን ሰዎችም “እገሌ ከገሌ ሳይሉ ካሰቃዩአቸው በኋላ አብዛኛዎቹ የተለያየ ቅጣት ተበየነባቸው። ጂሊያኖ በእሳት እንዲቃጠል ሲደረግ ሃያ የሚያክሉ ደግሞ በብረት ላይ ተሰክተው በእሳት ተጠብሰዋል፣ በርከት ያሉት ዕድሜ ይፍታህ ተብይኖባቸዋል፣ አንዳንዶችም በሕዝብ ፊት በጅራፍ ተገርፈዋል፣ ብዙዎቹም ጀልባ ቀዛፊ እንዲሆኑ ተደርጓል።”8

12. በመካከለኛው ዘመን የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና የሚወክሉ እንዳልነበሩ እንዴት እናውቃለን?

12 ሥልጣንን መከታ በማድረግ የተፈጸመ እንዴት ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት ነው! ጭፍን የሥልጣን ብልግና ነው! እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በምንም ዓይነት መንገድ የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና የሚወክሉ ሊሆኑ አይችሉም! መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እነዚህ ሰዎች ከየት ወገን እንደሆኑ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት:- እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም።”​—⁠1 ዮሐንስ 3:​10-12

13, 14. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው ያረጋገጠው በመካከለኛው ዘመን የተፈጸመው የትኛው ሁኔታ ነው? (ለ) በአውሮፓ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው?

13 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለማግኘት ብቻ ሲሉ እንዲህ ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ እንኳን ሳይቀር ለመጋፈጥ ፈቃደኛ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች መገኘታቸው እጅግ የሚያስደንቅ ነው! ደግሞም እስከዚህ ዘመን ድረስ ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎች ታይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ የተከለው ጥልቅ ፍቅር፣ ሰዎቹ የሚያሰቃዩአቸውን ወገኖች መልሰው ለመበቀል ሳያስቡ በጽናት መከራን ለመቀበል እንዲሁም ሳያጉረመርሙ አሰቃቂ ሞት እንኳ ለመሞት ፈቃደኛ ሆነው መገኘታቸው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​21

14 ቆየት ብሎ የሮማ ካቶሊክን ሥልጣን በመቃወም በ16ኛው መቶ ዘመን ከተደረገው የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ በኋላ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ራሷ በአውሮፓ በሚገኙ የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ተገድዳለች። ይህም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም የሚታወቁት ፕሮቴስታንቶች እንጂ ካቶሊኮች አልነበሩም። የሮማ ካቶሊክ ቄስ የሆኑት ኤድዋርድ ጄ ሲውባ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የፕሮቴስታንት ተኃድሶ ካስከተላቸው አሳዛኝ ውጤቶች አንዱ በካቶሊክ ተከታዮች ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ ቸል እንዲባል ማድረጉ መሆኑን አንድ ሰው በሐቀኝነት ሊቀበለው የሚገባ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ተረስቷል ማለት ባይሆንም ለአብዛኛዎቹ ካቶሊኮች የተከደነ መጽሐፍ ሆኖ ነበር።”9

የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት

15, 16. መጽሐፍ ቅዱስን በመቃወም ረገድ የፕሮቴስታንት እምነትም ቢሆን ከተጠያቂነት ነፃ የማይሆነው ለምንድን ነው?

15 ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በመቃወም ረገድ ከተጠያቂነት ነፃ አይደሉም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አንዳንድ የፕሮቴስታንት ምሁራን በመጽሐፉ ላይ ሌላ ዓይነት ጥቃት ይኸውም ምሁራዊ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት (high­er criticism) በተባለ ዘዴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከአፈታሪክና ተረት የተውጣጣ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ኢየሱስ የሚባል ሰው ኖሮ አያውቅም እስከማለት ደርሰዋል። እነዚህ የፕሮቴስታንት ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ሳይሆን የሰው ቃል ለዚያውም የተምታታ ቃል ነው ብለውታል።

16 ከእነዚህ አስተያየቶች መካከል በጣም የተጋነኑት አንዳንዶቹ አመኔታ ቢያጡም የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ዛሬም በአንዳንድ ሃይማኖታዊ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጥ ትምህርት ከመሆኑም ሌላ የፕሮቴስታንት ቀሳውስት የማይናቅ መጠን ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በአደባባይ ሲያጣጥሉ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል። በመሆኑም አንድ የአንግሊካን ቄስ ለአንድ የአውስትራሊያ ጋዜጣ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው አብዛኛው ነገር “ጨርሶ ስህተት ነው። አንዳንዶቹ ታሪኮች የተሳሳቱ ናቸው። አንዳንዶቹ ዝርዝር ጉዳዮችም የተዛቡ መሆናቸው በግልጽ ይታያል።” ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘረው ትችት የወለደው አስተሳሰብ ነው።

‘የተሰደበ’

17, 18. የሕዝበ ክርስትና አድራጎት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነቀፋ ያመጣው እንዴት ነው?

17 ሆኖም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው እንዳይቀበሉ ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸው የሕዝበ ክርስትና አድራጎት ሳይሆን አይቀርም። ሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስን እከተላለሁ ትላለች። አድራጎቷ ግን በመጽሐፍ ቅዱስና ክርስቲያን በሚለው ስም ላይ ትልቅ ነቀፌታ አምጥቷል። ሐዋርያው ጴጥሮስ አስቀድሞ እንደተናገረው የእውነት መንገድ ‘ተሰድቧል።’​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​2

18 ለምሳሌ ያህል በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራዎችን ስታግድ በሌላ በኩል ደግሞ ሊቀ ጳጳሱ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙትን ሙስሊሞች ለመውጋት የሚካሄደውን ግዙፍ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ይደግፉ ነበር። እነዚህ ጦርነቶች “ቅዱስ” ተብለው ይጠሩ እንጂ ቅዱስ የሚያሰኝ አንዳች ተግባር አልነበራቸውም። “የሕዝቦች ጦርነት” ተብሎ የተሰየመው የመጀመሪያው ጦርነት ወደፊት ምን እንደሚከተል ያመላከተ ነበር። በሰባኪዎች ልፈፋ ስሜቱ ተቀጣጥሎ ሆ ብሎ የተነሣው ሠራዊት አውሮፓን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት በጀርመን ወደነበሩት አይሁዳውያን ፊቱን በመመለስ በየከተማው በሰይፍ አርዷቸዋል። ለምን? ሀንስ ኤበርሃርድ ማየር የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “አይሁዳውያን የክርስቶስ ጠላቶች በመሆናቸው ቅጣት ይገባቸዋል የሚለው ሰበብ እውነተኛውን ዓላማቸውን ማለትም ስስታቸውን ለመሸፈን የተደረገ ሰንካላ ሙከራ ነው።”10

19-21. የሠላሳ ዓመቱ ጦርነት፣ በአውሮፓ የተደረገው የሚስዮናውያን እንቅስቃሴ እንዲሁም የቅኝ አገዛዝ መስፋፋት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነቀፋ ያመጡት እንዴት ነው?

19 በ16ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው የፕሮቴስታንቶች ዓመፅ በብዙ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የሮማ ካቶሊክን ከሥልጣን ያፈናቀለ ነበር። ለሠላሳ ዓመታት (1618-48) የተካሄደው ጦርነት አንዱ ውጤት ሲሆን ዘ ዩኒቨርሳል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ እንዳለው ከሆነ ይህ “በአውሮፓ ታሪክ ከተደረጉት ጦርነቶች ሁሉ እጅግ የከፋ ነው።” የጦርነቱ ዋነኛ መነሾ ምንድን ነው? “ካቶሊኮች ለፕሮቴስታንቶች ፕሮቴስታንቶችም ለካቶሊኮች የነበራቸው ጥላቻ ነው።”11

20 በዚህ ወቅት ሕዝበ ክርስትና ከአውሮፓ ውጭ መስፋፋትና ‘የክርስትናን’ ሥልጣኔ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ማዳረስ ጀምራ ነበር። ይህ ወታደራዊ መስፋፋት የሚታወሰው በተፈጸሙት የጭካኔና የስስት ድርጊቶች ነው። በአሜሪካ አገሮች ውስጥ የስፔይን ድል አድራጊዎች የአካባቢውን ሥልጣኔ ለማውደም ጊዜ አልወሰደባቸውም። አንድ የታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በጥቅሉ ሲታይ የስፔይን ገዥዎች የአገሬውን ሥልጣኔ ያወደሙት የአውሮፓውያኑን ሥልጣኔ ሳያስተዋውቁ ነው። ወደ አዲሱ ዓለም ያዘመታቸው አንገብጋቢ ነገር የወርቅ ጥማት ነበር።”12

21 የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያንም እንዲሁ ከአውሮፓ ወደሌሎች አሕጉሮች ሄደዋል። የሚስዮናውያን እንቅስቃሴ ካፈራቸው ነገ​­ሮች አንዱ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ነው። የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ያደረጉትን ጥረት በሚመለከት ዛሬ ሰፍኖ የሚገኘው አመ​­ለካከት ይህን ይመስላል:- “አብዛኛውን ጊዜ የሚስዮናውያኑ ድርጅት በሕዝቦች ላይ ለሚደርሰው ጭቆና ማስተባበያ ወይም ሽፋን ሆኖ አገልግሏል። በሚስዮን፣ በቴክኖሎጂና በኢምፔሪያሊዝም መካከል ያለው የእርስ በርስ ትስስር በግልጽ ታውቋል።”13

22. ሕዝበ ክርስትና በ20ኛው መቶ ዘመን በክርስትና ስም ላይ ነቀፋ ያመጣችው እንዴት ነው?

22 በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችና በመንግሥት መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር እስከ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች የተደረጉት የ“ክርስቲያን” አገሮች በሚባሉት ወገኖች መካከል ነው። በሁለቱም ወገን የነበሩት ቀሳውስት ወጣቶቻቸው እንዲዋጉና ጠላቶቻቸውን እንዲገድሉ አበረታተዋል። ጠላት የተባሉት ሰዎች በብዙ አጋጣሚዎች ተመሳሳይ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ሆነው ተገኝተዋል። ኢፍ ዘ ቸርችስ ዋንት ዎርልድ ፒስ (አብያተ ክርስቲያናት ለዓለም ሰላም እንዲመጣ ከፈለጉ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው “ዛሬ ያለው የጦርነት ሥርዓት ጎልብቶ ለክርስትና እምነት አድረናል በሚሉት መንግሥታት መካከል ከፍተኛ እልቂት ለማድረስ መብቃቱ [አብያተ ክርስቲያናት] ጥሩ ስም እንዲያተርፉ የሚያደርግ አይደለም።”14

የአምላክ ቃል አይጠፋም

23. የሕዝበ ክርስትና ታሪክ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚጠቁመው እንዴት ነው?

23 ይህን ረጅምና አሳዛኝ የሆነ የሕዝበ ክርስትና ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን የዳሰስነው ሁለት ነጥቦችን ለማጉላት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ናቸው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስትና ላይ ስድብ እንደሚያመጡ አስቀድሞ የተነገረ ሲሆን ይህ ነገር ፍጻሜውን ማግኘቱ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። የሆነ ሆኖ ግን የሕዝበ ክርስትና አድራጎት የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና እንደማይወክል ልንዘነጋ አይገባም።

24. እውነተኛው ክርስትና ተለይቶ እንዲታወቅ የሚያደርገውና ሕዝበ ክርስትናም ክርስቲያናዊ እንዳልሆነች የሚያጋልጣት ነገር ምንድን ነው?

24 ኢየሱስ ራሱ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው ስለሚታወቁበት መንገድ ገልጿል:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:​35) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:​16) ከሁለቱም አንጻር ሲታይ ሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና እንደማትወክል ራሷን በራሷ አጋልጣለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጅ እንደሆነች ትናገር እንጂ የሐሰት ወዳጅ ናት።

25. መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ የገጠሙትን መከራዎች ሁሉ ተቋቁሞ ሊቆይ የቻለው እንዴት ነው?

25 ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ የሚከተለው ነው:- ሕዝበ ክርስትና በጥቅሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ለማሰናከል ይህን ሁሉ ነገር ብታደርግም መጽሐፉ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቶ አሁንም በብዙ ሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር መቻሉ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዳይተረጎም የተነሡበትን መራራ ተቃውሞዎች፣ ከዘመናዊ ምሁራን የተሰነዘረበትን አደገኛ ጥቃት እንዲሁም የሐሰት ወዳጁን የሕዝበ ክርስትናን ክርስቲያናዊ ያልሆነ አድራጎት ሁሉ አሸንፎ እዚህ ደርሷል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች የጽሑፍ ሥራዎች የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊሞት አይችልም። የአምላክ ቃል ነው። ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”​—⁠ኢሳይያስ 40:​8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በአገሬው ሰው ቋንቋ ጥቂት የትርጉም ሥራዎች ተዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ በእጅ የሚጻፉ የትርጉም ሥራዎች ብዙውን ጊዜ የሚዘጋጁት አድካሚ በሆነ ሁኔታ ተጊጠው ስለነበረ ብዙሃኑ ሕዝብ ጨርሶ ሊያገኛቸው የሚችሉ አልነበሩም።2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 34 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ግንባር ቀደም የሆኑት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተሰነዘሩ ከፍተኛ ምሁራዊ ጥቃቶች ውስጥ እጃቸው አለበት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሕዝበ ክርስትና ታሪክ የጀመረው ቆስጠንጢኖስ በዘመኑ ለነበረው “ክርስትና” ሕጋዊ እውቅናን በሰጠ ጊዜ ነው

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ ሰባተኛና ኢኖሰንት ሦስተኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቡ ዕለት ተዕለት በሚግባባባቸው ቋንቋዎች እንዳይተረጎም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በምታደርገው ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ነበሩ

[በገጽ 33 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝበ ክርስትና ያሳየችው አሳፋሪ የሆነ አድራጎት ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል

[በገጽ 35 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እነዚህ የሩሲያ ወታደሮች “ክርስቲያን” ወንድሞቻቸውን ለመግደል ከመሄዳቸው በፊት ሃይማኖታዊ ምስል ተሳልመዋል