በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የአምላክ ቃል ሕያው ነው”

“የአምላክ ቃል ሕያው ነው”

ምዕራፍ 13

“የአምላክ ቃል ሕያው ነው”

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችግሮችን ለመፍታትና ስህተት ከመሥራት ሊጠብቀን እንደሚችል ከዚህ ምዕራፍ በፊት በነበረው ምዕራፍ ተመልክተናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ጊዜ የማይሽረው መሆኑ መጽሐፉ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንዲህ ይላል:- “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሰጽ፣ ስህተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​16 የ1980 ትርጉም ) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የጥበብ ምክር በመለገስ ብቻ አይወሰንም። የአምላክ ቃል እንደመሆኑ መጠን ሰዎችን ይለውጣል።

1-3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የባሕርይ ለውጥ የማድረጉን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ባሕርይ የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳየን የትኛው ተሞክሮ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ሰዎችን መለወጥ ይችላልን? አዎን፣ አልፎ ተርፎም ባሕርያቸውን ይቀይራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ልብ በል:- “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”​—⁠ኤፌሶን 4:​22-24

2 በእርግጥ አዲስ ሰውነት መላበስ ይቻላል? አዎን፣ ይቻላል! እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን መሆን ከፍተኛ የባሕርይ ለውጥ ማድረግ ይጠይቃል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9-11) ለምሳሌ ያህል አንድ በደቡብ አሜሪካ የሚገኝ ወጣት ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ ይሞቱበታል። ያለ ወላጅ መመሪያ በማደጉ በጣም መጥፎ ባሕርያት አዳበረ። እንዲህ ሲል ስለ ሁኔታው ተናግሯል:- “አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ ሙሉ በሙሉ የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ሆኜ ነበር። ሱሴን ለማርካትም ስል ስሰርቅ ተይዤ የተወሰነ ጊዜ በእስር ቤት አሳልፌያለሁ።” ከጊዜ በኋላ ግን የይሖዋ ምሥክር የሆነችው አክስቱ ረዳችው።

3 እንዲህ ብሏል:- “አክስቴ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ጀመር። ከዚያም ከሰባት ወራት በኋላ ከዕፅ ሱሰኝነት ተላቀቅኩ።” እንዲሁም የቀድሞ ጓደኞቹን በመተው ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አዳዲስ ጓደኞች አፈራ። ሐሳቡን ሲቀጥል “እነዚህ አዳዲስ ጓደኞቼና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እድገት እንዳደርግና በመጨረሻም አምላክን ለማገልገል ሕይወቴን እንድወስን ረድተውኛል።” አዎን፣ ይህ ቀደም ሲል የዕፅ ሱሰኛና ሌባ የነበረ ሰው ጎበዝ ክርስቲያን ሆኗል። ይህን ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ነው። በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።’​—⁠ዕብራውያን 4:​12

በእውቀት አማካኝነት የተለወጡ ሰዎች

4, 5. በቆላስይስ 3:​8-10 መሠረት አዲሱን ሰውነት ለማዳበር ምን ያስፈልጋል?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን የሚለውጠው እንዴት ነው? የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መልሱን ይሰጠናል:- “አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቊጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፣ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፣ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል።”​—⁠ቆላስይስ 3:​8-10

5 የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹን ባሕርያት ማስወገድ እንዳለብንና የትኞቹን ማዳበር እንዳለብን ይነግረናል። አንድ በደቡብ አውሮፓ የሚገኝ ወጣት እንዳስተዋለው እንዲህ ያለው እውቀት ራሱ ትልቅ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ይህ ወጣት በጣም ግልፍተኛ ነበር። በልጅነቱ ሁልጊዜ ይደባደብ ነበር። በኋላም የጠበኝነት ስሜቱን ለማርካት ቦክሰኛ ሆነ። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የግልፍተኝነት ባሕርይው አልበረደለትም። ውትድርና ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድ ሌላ ወታደር ደብድቦ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር። ከሠራዊቱ ከወጣ በኋላም ሚስት ያገባ ሲሆን እርሷንም ይደበድባት ነበር። ሌላው ቀርቶ በአንድ ወቅት በቤተሰቡ ውስጥ የሆነ ጭቅጭቅ ተነስቶ እየተነጋገሩ ሳሉ የገዛ አባቱን በቡጢ መትቶ ዘርሯቸዋል። በእርግጥም በቁጣ የሚገነፍል ጠበኛ ወጣት ነበር!

6, 7. በደቡብ አውሮፓ የሚገኝ አንድ ወጣት ባሕርይውን እንዲለውጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት የረዳው እንዴት ነው?

6 ከጊዜ በኋላ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠና እንደሚከተለው ያለውን ምክር ሰማ:- “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ።” (ሮሜ 12:​17-19) ይህ ጥቅስ በቁጣ መገንፈሉ ትልቅ ድክመት እንደሆነ እንዲያስተውል ረዳው። ሰላማዊ ከሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ጋር እንደማይጣጣም ስላስተዋለ ቦክሰኛነቱን ተወ። ይሁን እንጂ ከኃይለኛነት ባሕርይው ጋር የሚያደርገው ትግል ገና አላበቃም ነበር።

7 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለውን እውቀት እያሳደገ መሄዱ ረድቶታል። ይህም ጥሩ ሕሊና እንዲኖረውና በቁጣ የመገንፈል ባሕርይውን እንዲቆጣጠር አስችሎታል። አንድ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ጥሩ ከገፋ በኋላ አንድ ሰው ሙልጭ አድርጎ ሰደበው። ይህ ወጣት የቀድሞው ዓይነት የቁጣ ስሜት በውስጡ ሲገነፍል ተሰማው። ወዲያው ግን ኃፍረት ተሰማው። ይህም ለቁጣው እንዳይሸነፍ ረድቶታል። ‘ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን’ ከመመለስ ይልቅ ቁጣውን መቆጣጠር ችሏል። ዛሬ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ምስጋና ይግባውና ይህ ሰው ተለውጦ አዲስ ሰው ሆኗል።

አምላክን ማወቅ

8. (ሀ) አዲሱ ሰውነት የተፈጠረው በማን ምሳሌ ነው? (ለ) አዲሱን ሰውነት ለመቅረጽ የሚረዳው ትክክለኛ እውቀት ስለ ማን ማወቅን ይጨምራል?

8 ብዙ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባው ትክክለኛ ነገር ምን እንደሆነ እንደሚያውቁ አይካድም። ይሁን እንጂ ለሥጋ ድክመቶች ይሸነፋሉ። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ማወቅ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ሰዎች እንዲለወጡ የረዳቸው ሌላ ነገር አለ። ይህ ምንድን ነው? ቀደም ሲል የጠቀስነው ጥቅስ እንዲህ ይላል:- “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል።” (ቆላስይስ 3:​10፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዳም በመጀመሪያ በአምላክ መልክ እንደተፈጠረ ሁሉ አዲሱም ሰውነት በአምላክ ምሳሌ የተፈጠረ መሆኑን ልብ በል። (ዘፍጥረት 1:​26) በመሆኑም እነዚህን ሁለት ወጣቶች የረዳቸው ትክክለኛ እውቀት ስለ አምላክ የሚገልጸውንም እውቀት የሚጨምር መሆን አለበት። ይህም የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት ያስታውሰናል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”​—⁠ዮሐንስ 17:​3

9. ስለ አምላክ የምናገኘው እውቀት ባሕርያችንን እንድንለውጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ስለ አምላክ የምናገኘው እውቀት ባሕርያችንን እንድንለውጥ የሚረዳን እንዴት ነው? ለመለወጥ የሚያንቀሳቅስ ኃይል ይሆነናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አማካኝነት አምላክን እያወቅን ስንሄድ ስለ መለኮታዊ ባሕርይዎቹ እንማራለን እንዲሁም ለእኛ ያሳየንን ፍቅር እናስተውላለን። ይህ ደግሞ እኛም በአጸፋው እንድንወደው ያደርገናል። (1 ዮሐንስ 4:​19) ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የመጀመሪያይቱና ታላቂቱ ትእዛዝ ሲል የተናገረለትን “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ መፈጸም እንችላለን። (ማቴዎስ 22:​37) ለአምላክ የሚኖረን ፍቅር እርሱን ደስ የሚያሰኘውን አዲሱን ሰውነት ለመልበስ እንድንጥር ያደርገናል። ምንም ያህል ትግል የሚጠይቅብን ቢሆን እንኳ ይበልጥ እርሱን ለመምሰል እንድንጥር ያደርገናል።

ሥር የሰደደ ድክመት

10, 11. ትክክለኛ እውቀት በሰሜን አሜሪካ የምትኖረው ወጣት ባሕርይዋን መለወጥ እንድትጀምር የረዳት እንዴት ነው?

10 አንዳንድ ጊዜ እውነትም ትልቅ ትግል ይጠይቃል። አንዲት በሰሜን አሜሪካ የምትኖር ወጣት ለመለወጥ ከፍተኛ ትግል ማድረግ አስፈልጓታል። በልጅነቷ በፆታ ተነውራ የነበረችው ይቺ ወጣት ያደገችው ጠበኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ስለነበር የኋላ ኋላ የዕፅ ሱሰኛ ሆነች። ይሁንና ዕፅ በውድ ዋጋ የሚገኝ ነገር በመሆኑ ሱሷን ለማርካት የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ስትል በዝሙት አዳሪነት ተሠማራች። ጎብኚዎችን በማወክና በመዝረፍ በተደጋጋሚ እስር ቤት ትገባ ስለነበር በቤቷ ካሳለፈችው ጊዜ በእስር ቤት ያሳለፈችው ጊዜ ይበዛ ነበር።

11 የይሖዋ ምሥክሮች ሲያገኟት ለበርካታ ጊዜ ውርጃ ስትፈጽም ቆይታ በመጨረሻው አንድ ዲቃላ ወልዳ ነበር። የሆነ ሆኖ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሰማችው ነገር ደስ ስላሰኛት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረትና አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ጀመረች።

12, 13. ትክክለኛ እውቀት አንድ ጊዜ በውስጣችን ከተተከለ ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል የሚሆነን እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

12 ይሁን እንጂ አሮጌው ሰውነት ሥር ሰድዶ ስለነበር ከፊት ለፊቷ ትልቅ ትግል ይጠብቃት ነበር። በአንድ ወቅት ለራሷ ጥቅም ሲባል በተሰጣት ምክር ስለተከፋች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን አቆመችና ወደ ቀድሞው መጥፎ አኗኗሯ ተመለሰች። ይሁን እንጂ በውስጧ የተተከለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልትረሳው አልቻለችም። እንዲህ ስትል አምናለች:- “አሁንም አሁንም የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማትና በ2 ጴጥሮስ 2:​22 ላይ የሚገኙት ‘ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፣ ደግሞ:- የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች’ የሚሉት ቃላት በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር።”

13 በመጨረሻ ይህ እውቀት በድጋሚ ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ አነሳሳት። “በሩን ለይሖዋ ክፍት ማድረግና እርሱ እንዲረዳኝ ደግሜ ደጋግሜ መጸለይ ጀመርሁ” ብላለች። ከባድ ጥረት ማድረግ ቢጠይቅባትም አሁን አዲሱ ሰውነት በውስጧ ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ማድረግ ቻለች። በአንድ ወቅት ደከም በማለቷ ከልክ በላይ ጠጥታ በፆታ ብልግና ተሸነፈች። ይሁንና በዚህ ጊዜ የተሰማት ስሜት እየተለወጠች እንደነበር የሚያሳይ ነበር። ይህን በማድረጓ ራሷን ተጸየፈችው። “ብዙ እጸልይና አጠና ነበር” ብላለች። በመጨረሻ የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ንጹሕና የተከበረ ኑሮ የምትኖር ትጉሕ ክርስቲያን እንድትሆን አስችሏታል። በልጅነቷ ብዙ በደል የደረሰባት፣ የዕፅ ሱሰኛ የነበረችውና ልቅ አኗኗር የነበራት ይህች ሴት ሙሉ በሙሉ ከተለወጠች ዛሬ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በአምላክ ቃል የተለወጠ ሕዝብ

14, 15. (ሀ)  በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሠራው የአምላክ ኃይል ምንድን ነው? (ለ) ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያንጸባርቋቸው አንዳንድ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ ትሑት በሆኑ ሰዎች ሕይወት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ተራ የሰው ልጅ የሥራ ውጤት እንዳልሆነ ያሳያል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደመሆኑ መጠን የአምላክ መንፈስ እንዲሠራ የሚያስችል መስመር ነው። ኢየሱስን ተዓምራት እንዲሠራ ያስቻለው ያው መንፈስ ዛሬም መጥፎ ባሕርያትን አሸንፈን ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድንለብስ ይረዳናል። እንዲያውም ክርስቲያኖች ሊኮተኩቷቸው የሚገቡት እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሉት መሠረታዊ ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የመንፈስ ፍሬ” ተብለው ተጠርተዋል።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

15 ዛሬ ይህ መንፈስ የሚሠራው በጥቂት ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ‘ከይሖዋ በተማሩና ብዙ ሰላም ባገኙ’ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ነው። (ኢሳይያስ 54:​13) እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ኢየሱስ እነርሱን ለይቶ ማወቅ የሚቻልበትን አንድ ምልክት ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:​35) ክርስቲያናዊ ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ሲሆን የአዲሱ ክርስቲያናዊ ሰውነት ዋነኛ ክፍል ነው። ዛሬ ኢየሱስ የተናገረለትን ዓይነት ፍቅር የሚያሳይ ቡድን ይኖራልን?

16, 17. ጋዜጦች ‘ከይሖዋ የተማሩና ብዙ ሰላም ያገኙት’ እነማን መሆናቸውን ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ ምን አስተያየት እንደሰጡ ጥቀስ።

16 በሰሜን አሜሪካ ለሚታተመው ኒው ሃቨን ሬጂስተር የተባለው ጋዜጣ ከተላከው ደብዳቤ ተቀንጭቦ የተወሰደውን የሚከተለውን አስተያየት ልብ በል:- “ሰዎችን ወደ እነርሱ ሃይማኖት የመለወጥ ሥራቸው እንደ እኔ አበሳጭቷችሁና ተቆጥታችሁ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለእምነታቸው ያላቸውን ቅንዓት፣ ጥሩ ምግባራቸው እንዲሁም ሰብዓዊ ባሕርያትን በማሳየትና በጤናማ አኗኗር ረገድ የሚያሳዩትን ግሩም ምሳሌ ልታደንቁ ይገባል።” ሚውንሽነር ሜርኩር የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ስለ እነዚሁ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በ[ጀርመን] ፌደራል ሬፑብሊክ ውስጥ እንደ እነርሱ ሐቀኛና በወቅቱ ቀረጥ የሚከፍል የለም። መኪናቸውን ከሚያሽከረክሩበት ሁኔታም ሆነ ከወንጀል ስታትስቲካዊ መረጃ ማየት እንደሚቻለው ሕግ አክባሪ ሰዎች ናቸው።”

17 እነዚህ ሁለት ጋዜጦች የተናገሩት ስለ እነማን ነው? በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ የሚታተመው ሄራልድ ጋዜጣ ስለ እነዚሁ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ባለፉት ብዙ ዓመታት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች አገሪቱ የምትፈልጋቸው ዓይነት ታታሪ፣ ጭምት፣ ጥንቁቅና አምላክን የሚፈሩ ዜጎች መሆናቸውን አሳይተዋል።” በኅብረተሰብ ጥናት መስክ በዛምቢያ የተካሄደውን የምርምር ውጤት ይዞ የወጣው አሜሪካን ኤትኖሎጂስት ስለ እነዚሁ ሰዎች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ሁሉ ይበልጥ ዘላቂ ትዳር በመመሥረት ረገድ በእጅጉ የተሳካላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።”

18, 19. በኢጣሊያና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች በሚመለከት ምን ተብሏል?

18 በኢጣሊያ የሚታተመው ላ ስታምፓ የተባለውም ጋዜጣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሁሉ የሚመኛቸው ዓይነት ታማኝ ዜጎች ናቸው። ከቀረጥ ለመሸሽ ቀዳዳ አይፈላልጉም ወይም ለገዛ ጥቅማቸው ሲሉ ምቹ መስሎ ካልታያቸው ሕግ ለማምለጥ አይሞክሩም። (አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች እሁድ እሁድ ብቻ ከመድረክ ሲተላለፉ የሚሰሟቸው እንጂ የማይሠሩባቸው መመሪያዎች) ጎረቤትን መውደድን፣ ሥልጣን አለመፈለግን፣ ሰላማዊና ለራስ ሐቀኛ መሆንን የመሳሰሉት የሥነ ምግባር ደረጃዎች ‘የዕለታዊ’ ሕይወታቸው ክፍል ናቸው።”

19 በደቡብ አፍሪካ በነበረው የዘር ልዩነት ሕግ መድሎ የተፈጸመባቸው አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የይሖዋ ምሥክሮች “ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች በመማራቸው የቆዳ ቀለም ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል። ይህን ጉዳይ ሲያብራሩ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “የሰዎችን ውስጣዊ ማንነት እንጂ የቆዳ ቀለማቸውን የማያዩ ሰዎች ናቸው። ዛሬ እውነተኛ ወንድማማችነት የመሠረቱት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።”

20. የይሖዋ ምሥክሮች ለየት ብለው እንዲታዩ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?

20 እነዚህ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ልባቸውን ለመጽሐፍ ቅዱስ የከፈቱና የአምላክ መንፈስ በእነርሱ ላይ እንዲሠራ የፈቀዱ ሰዎች አሉ። ቀደም ሲልም ቢሆን ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንዲሰበክ የሰጠውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ያሉት እነዚሁ ሰዎች መሆናቸውን እንደተመለከትን ልብ ማለት ጥሩ ነው። (ማቴዎስ 24:​14) የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ መንገዶች ከሌሎች ለየት ብለው የሚታዩት ለምንድን ነው? ከብዙ አቅጣጫ ሲታይ እነርሱ ከሰው የተለዩ አይደሉም። ሥጋዊ ድክመት አለባቸው፣ የኢኮኖሚ ችግር ይገጥማቸዋል እንዲሁም ሌላው ሰው የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጓቸዋል። ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ አምላክን ይወዳሉ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አላቸው እንዲሁም ቃሉ በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ ይፈቅዱለታል።

21. ጥላቻ በተሞላው በዛሬው ዓለም ውስጥ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሰዎች መገኘት መቻላቸው ምን ነገር የሚያረጋግጥ ነው?

21 ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። የተለያየ ዘር፣ ቋንቋና ማኅበራዊ ደረጃ ያላቸው ናቸው። ይሁንና አንድነትና ሰላም ያለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር መሥርተዋል። በሚኖሩበት አገር ሁሉ ጥሩ ዜጎች ናቸው። ይሁንና ከሁሉ አብልጠው የሚገዙት ለአምላክ መንግሥት ሲሆን ሁሉም የዚህን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በመንገሩ ሥራ ይሳተፋሉ። በዚህ በተከፋፈለና ጥላቻ በሞላበት ዓለም ውስጥ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ያለ ቡድን ሊገኝ መቻሉ በእርግጥም ድንቅ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች መኖራቸው ራሱ የአምላክ መንፈስ ዛሬ በሰው ዘር መካከል እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሕያውና የሚሠራ’ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 177 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ሰዎችን ይለውጣል

[በገጽ 181 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስለ አምላክ ማወቅ እርሱን ለመምሰል እንድንጥር ያደርገናል