በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበላይ አካሉ መልእክት

የበላይ አካሉ መልእክት

‘አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችኋል።’ (ዕብ. 5:12) በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ አስተማሪ የሆነው ይሖዋ፣ ስለ እሱ ሌሎችን እንድናስተምር እኛን መጋበዙ በጣም የሚያስገርም ነው! ስለ ይሖዋ የሚገልጸውን እውነት በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ወይም በአገልግሎት ላይ ለሌሎች ማስተማር ታላቅ መብት ቢሆንም ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። ታዲያ በዚህ ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ሐሳብ መልሱን ይጠቁመናል፤ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ” ብሎት ነበር። አክሎም “ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ” ብሎታል። (1 ጢሞ. 4:13, 16) አንተም ሕይወት አድን የሆነውን መልእክት ለሌሎች የማካፈል መብት ተሰጥቶሃል። በመሆኑም የማንበብና የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ይህን ለማድረግ እንዲረዳህ ታስቦ ነው። እስቲ ከብሮሹሩ ገጽታዎች አንዳንዶቹን እንመልከት።

በእያንዳንዱ ገጽ ላይ አንድ ጥቅስ ይገኛል። ጥቅሱ፣ ከሚብራራው ነጥብ ጋር የሚዛመድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አሊያም ነጥቡ እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ የያዘ ነው

ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ ነው። (ኢሳ. 30:20) ይህ ብሮሹር የማንበብም ሆነ የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል የሚረዳህ ቢሆንም የምንሰብከው መልእክት ከይሖዋ የመጣ መሆኑንና ሰዎችን የሚስበው እሱ መሆኑን መዘንጋት የለብህም። (ዮሐ. 6:44) እንግዲያው ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ሁልጊዜ ጸልይ። በአምላክ ቃል አዘውትረህ ተጠቀም። የአድማጮችህን ትኩረት ወደ ራስህ ከመሳብ ይልቅ በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ መርዳት ይኖርብሃል። አድማጮችህ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዲያዳብሩ ለመርዳት ጥረት አድርግ።

ለሰው ልጆች ከተሰጡት መልእክቶች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን መልእክት የማስተላለፍ መብት ተሰጥቶሃል። “አምላክ በሚሰጠው ኃይል” ከተማመንክ እንደሚሳካልህ እርግጠኞች ነን።—1 ጴጥ. 4:11

አብረናችሁ የምንሠራ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል