በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ የሚገባው ማን ነው?’

‘መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ የሚገባው ማን ነው?’

ምዕራፍ 15

‘መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ የሚገባው ማን ነው?’

1. ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ አሁን ምን ነገር ተፈጸመ?

ዕጹብ ድንቅ ነው፤ የሚያስፈራ ግርማ ያለው ነው። በእሳት መቅረዞች፣ በኪሩቤሎች፣ በ24 ሽማግሌዎችና እንደ መስተዋት በጠራው ባሕር ታጅቦ የታየው የይሖዋ ዙፋን ይህን ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ቀጥሎ ምን ተመለከተ? ዮሐንስ የሚከተለውን በማለት በዚህ ሰማያዊ ትርዒት ማዕከላዊውን ሥፍራ ወደ ያዘው አካል እንድናተኩር ያደርገናል። “በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። ብርቱም መልአክ:- መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹን ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። መጽሐፉንም ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ።”—ራእይ 5:1-4

2, 3. (ሀ) ዮሐንስ ጥቅልሉን የሚከፍት ሰው እንዲገኝ አጥብቆ የፈለገው ለምን ነበር? ይሁን እንጂ ይህ የሚቻል መስሎ ነበርን? (ለ) በዘመናችንስ የአምላክ ቅቡዓን ምን ነገር በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል?

2 ይህን የመጽሐፍ ጥቅልል የያዘው የፍጥረት ሁሉ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ጥቅልሉ በጀርባውም ሆነ በፊቱ የተጻፈበት ስለሆነ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት የያዘ ሳይሆን አይቀርም። ይዘቱን የማወቅ ጉጉታችንን ይቀሰቅሳል። በጥቅልሉ ውስጥ ምን ነገር ይኖር ይሆን? ይሖዋ ለዮሐንስ ያቀረበውን ግብዣ እናስታውሳለን። “ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ” ተብሎ ነበር። (ራእይ 4:1) ስለ እነዚህ ነገሮች ለማወቅ በታላቅ የጉጉት መንፈስ እንጠባበቃለን። ይሁን እንጂ የመጽሐፉ ጥቅልል ተዘግቶ በሰባት ማኅተሞች ታሽጎአል።

3 ኃያሉ መልአክ ጥቅልሉን ለመክፈት ብቃት ያለው ሰው ያገኝ ይሆንን? ኪንግደም ኢንተርሊንየር እንደሚለው ጥቅልሉ የሚገኘው በይሖዋ “ቀኝ እጅ” ነበር። ይህም ክፍት በሆነው የእጁ መዳፍ ይዞት እንደነበር ያመለክታል። ይሁን እንጂ ጥቅልሉን ተቀብሎ ለመክፈት ብቃት የሚኖረው በምድርም ሆነ በሰማይ የሚገኝ አልመሰለም። ሞተው ከምድር በታች ከሚገኙት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መካከል እንኳን ይህን ታላቅ ክብር ለመቀበል ብቃት ያለው አልተገኘም። ዮሐንስ በጣም አዝኖ መታየቱ አያስደንቅም። ምናልባት “ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር” ሳያውቅ ሊቀር ነው። በዘመናችንም ቢሆን የአምላክ ቅቡዓን ሕዝቦች ይሖዋ የራእይን መጽሐፍ እስኪያብራራላቸውና የዕውቀቱንና የእውነቱን ብርሃን እስኪያበራላቸው ድረስ በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ሕዝቦቹን ‘በታላቅ የመዳን’ ጎዳና ለመምራት ሲል ይህንን የሚፈጽምላቸው ለትንቢቱ በተወሰነው ዘመን ውስጥ ደረጃ በደረጃ ነው።—መዝሙር 43:3, 5

የሚገባው

4. (ሀ) ጥቅልሉን ለመክፈትና ማህተሞቹንም ለመፍታት ብቁ ሆኖ የተገኘው ማን ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ተባባሪዎቻቸው እንዴት ባለ ሽልማትና መብት ተካፍለዋል?

4 አዎ፣ ጥቅልሉን ለመክፈት ብቃት ያለው አለ። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል:- “ከሽማግሌዎቹም አንዱ:- አታልቅስ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ የዳዊትም ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነስቶአል አለኝ።” (ራእይ 5:5) ስለዚህ ዮሐንስ፣ አሁን እንባህን አድርቅ። የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ታማኝ ጓደኞቻቸው የዕውቀት ብርሃን የሚያገኙበትን ጊዜ እየተጠባበቁ የብዙ ዓመታት የፈተናና የመከራ ጊዜ አሳልፈዋል። በአሁኑ ጊዜ የዚህን ራእይ ትርጉም ለመረዳት መቻላችን በጣም ትልቅ ሽልማት ነው። የራእዩንም መልእክት ለሌሎች ሰዎች በማወጅ በትንቢቱ ፍጻሜ ለመካፈል መቻላችን ምን ያህል ታላቅ መብት ነው!

5. (ሀ) ስለ ይሁዳ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር? የይሁዳ ተወላጆች የሆኑትስ የገዙት በየት ነበር? (ለ) ሻይሎ ማን ነው?

5 “ከይሁዳ ነገድ የሆነ አንበሳ”! ዮሐንስ የአይሁዳውያን አባት የሆነው ያዕቆብ ስለ አራተኛ ልጁ ስለ ይሁዳ የተናገረውን ትንቢት ያውቅ ነበር። “ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው። ልጄ ሆይ ከአደንህ ወጣህ። እንደ አንበሳ አሸመቀ፣ እንደ ሴት አንበሳም አደባ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፣ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍጥረት 49:9, 10) የአምላክ ሕዝቦች ንጉሣዊ ሥርወ መንግሥት የተገኘው ከይሁዳ ነበር። ከዳዊት ጀምሮ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እስካጠፉበት ጊዜ ድረስ በዚህች ከተማ የነገሡት ነገሥታት በሙሉ የይሁዳ ተወላጆች ነበሩ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ያዕቆብ የተነበየውን ሻይሎ አልሆኑም። ሻይሎ ማለት “[መብት] ያለው” ማለት ነው። ይህ ስም የሚያመለክትው የዳዊት ቤተሰብ መንግሥት ዘላለማዊ ወራሽ የሆነውን ኢየሱስን ነው።—ሕዝቅኤል 21:25-27፤ ሉቃስ 1:32, 33፤ ራእይ 19:16

6. ኢየሱስ የእሴይ “ቁጥቋጦ”፣ “የዳዊት ሥር” የሆነው እንዴት ነው?

6 ዮሐንስ “የዳዊት ሥር” የሚለውን ሐረግ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ተስፋ የተደረገው መሲሕ ‘ከእሴይ [ከዳዊት አባት] ግንድ የወጣ በትር . . . ቁጥቋጥ’ ወይም ‘ለአሕዛብ ምልክት ይሆን ዘንድ የቆመ የእሴይ ሥር’ እንደሆነ በትንቢት ተነግሮአል። (ኢሳይያስ 11:1, 10) ኢየሱስ የእሴይ ልጅ ከሆነው ከዳዊት ንጉሣዊ መስመር ስለ ተወለደ የእሴይ ቁጥቋጦ ነበር። ከዚህም በላይ የዳዊት ሥር በመሆን የዳዊት ሥርወ መንግሥት ዳግመኛ እንዲያቆጠቁጥና ዘላለማዊ ሕልውና እንዲያገኝ ያስቻለው ኢየሱስ ነው።—2 ሳሙኤል 7:16

7. ኢየሱስ ጥቅልሉን በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው እጅ ለመውሰድ ብቁ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ፍጹም ሰው በነበረበት ጊዜ ፍጹም አቋሙን ጠብቆ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሎአል። በጣም ከባድ በሆነ ፈተናም ጸንቶአል። ሰይጣን ላቀረበው ግድድር የተሟላ ምላሽ ሰጥቶአል። (ምሳሌ 27:11) በዚህም ምክንያት መስዋዕታዊ ሞት ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት እንደተናገረው “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ለማለት ችሎአል። (ዮሐንስ 16:33) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ከሙታን ለተነሳው ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ . . . በሰማይና በምድር” ሰጥቶታል። ከአምላክ አገልጋዮች መካከል ጥቅልሉን ለመቀበልና በጥቅልሉ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ለማሳወቅ ብቁ ሆኖ የተገኘው ኢየሱስ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 28:18

8. (ሀ) በመንግሥቱ ረገድም ቢሆን ኢየሱስ ብቁ መሆኑን ያረጋገጠው ምንድን ነው? (ለ) ጥቅልሉን ለመክፈት ብቁ የሆነው ማን እንደሆነ ለዮሐንስ ያሳወቀው ከ24ቱ ሽማግሌዎች አንዱ መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምን ነበር?

8 በእውነትም የመጽሐፉን ጥቅልል መፍታት የሚገባው ኢየሱስ መሆኑ ተገቢ ነው። ከ1914 ጀምሮ የአምላክ መሲሐዊ መንግስት ንጉሥ በመሆን ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል። ጥቅልሉም በአብዛኛው የሚገልጸው ስለዚህ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለመንግሥቱ እውነት በታማኝነት መሥክሮአል። (ዮሐንስ 18:36, 37) ተከታዮቹም የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ እንዲጸልዩ አስተምሮአቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የክርስትና ዘመን በጀመረበት ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች ስብከት ሥራ ያቋቋመውና ይህ የስብከት ሥራ በፍጻሜው ዘመን የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ትንቢት የተናገረው ኢየሱስ ነው። (ማቴዎስ 4:23፤ ማርቆስ 13:10) ከ24ቱ ሽማግሌዎች መካከል አንደኛው፣ ማኅተሙን የሚፈታው ኢየሱስ መሆኑን ለዮሐንስ መግለጹም የተገባ ነበር። ለምን ቢባል እነዚህ ሽማግሌዎች ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ወራሾች በመሆን በዙፋኑ ላይ ስለተቀመጡና ዘውድ ስለጫኑ ነው።—ሮሜ 8:17፤ ራእይ 4:4

‘የታረደው በግ’

9. ዮሐንስ “በዙፋኑ መካከል” ቆሞ ያየው አንበሳ ሳይሆን ምን ነበር? ያየውንስ የገለጸው እንዴት ነው?

9 ዮሐንስ “ከይሁዳ ነገድ የሆነውን አንበሳ” ለማየት አቀና። ይሁን እንጂ የተመለከተው በጣም አስደናቂ ነገር ነበር። ፈጽሞ የተለየ ምሳሌያዊ ምስል ታየ። “በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎቹም መካከል እንደታረደ በግ ቆሞ አየሁ፣ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።” ራእይ 5:6

10. ዮሐንስ የተመለከተው “በግ” ማን ነበር? ይህስ ስያሜ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?

10 በመካከል ባለው በዙፋኑ አጠገብ አራቱ እንስሳትና 24ቱ ሽማግሌዎች በፈጠሩት ክብ ውስጥ አንድ በግ ቆሞአል። ዮሐንስም ይህ በግ “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” እና “የዳዊት ዘር” መሆኑን ወዲያውኑ አውቆ እንደነበረ አያጠራጥርም። አጥማቂው ዮሐንስ ከ60 ዓመታት በፊት ኢየሱስን ቆመው ይመለከቱ ለነበሩት አይሁዳውያን ሲያስተዋውቅ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ብሎ እንደነበረ ያውቃል። (ዮሐንስ 1:29) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ነውር እንደሌለበት በግ ከዓለም እድፈት ሁሉ ርቆ ስለነበረ ንጹሕ ሕይወቱን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ ይችል ነበር።—1 ቆሮንቶስ 5:7፤ ዕብራውያን 7:26

11. ከፍተኛ ክብር የተቀዳጀውን ኢየሱስ ‘ታርዶ የነበረው በግ’ ብሎ መጥራት እርሱን ማዋረድ የማይሆነው ለምንድን ነው?

11 ከፍተኛ ክብር የተጎናፀፈውን ኢየሱስ ‘በታረደ በግ’ መመሰል እርሱን ማዋረድ ወይም ማቃለል ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን ጠብቆ መኖሩ ለሰይጣን ትልቅ ሽንፈት ለይሖዋ ደግሞ ታላቅ ድል ነበር። ኢየሱስን በዚህ ዓይነት ምሳሌ ማቅረብ በሰይጣን ዓለም ላይ ያገኘውን ድል በግልጽ ከማሳየቱም በላይ ይሖዋና ኢየሱስ ለሰው ልጆች ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ያስታውሳል። (ዮሐንስ 3:16፤ 15:13፤ ከ⁠ቆላስይስ 2:15 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ኢየሱስ የተስፋው ዘር እንደሆነና የመጽሐፉን ጥቅልል ለመክፈት ሙሉ ብቃት እንዳለው ተጠቅሶአል።—ዘፍጥረት 3:15

12. የበጉ ሰባት ቀንዶች ምን ያመለክታሉ?

12 ለዚህ “በግ” ያለንን አድናቆት የሚጨምርልን ሌላ ምን ነገር አለ? ሰባት ቀንዶች አሉት። ቀንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የኃይል ወይም የሥልጣን ምሳሌ ነው። ሰባት ቁጥር ደግሞ ሙሉነትን ያመለክታል። (ከ⁠1 ሳሙኤል 2:1, 10፤ መዝሙር 112:9፤ 148:14 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የበጉ ሰባት ቀንዶች ይሖዋ ለኢየሱስ የሰጠውን የኃይልና የሥልጣን ሙላት ያመለክታሉ። እርሱ “ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ” ነው። (ኤፌሶን 1:20-23፤ 1 ጴጥሮስ 3:22) ኢየሱስ በተለይ ይሖዋ ሰማያዊ ንጉሥ አድርጎ በዙፋን ላይ ካስቀመጠው ከ1914 ጀምሮ የመንግሥት ሥልጣን ተረክቦአል።—መዝሙር 2:6

13. (ሀ) የበጉ ሰባት ዓይኖች የምን ምሳሌ ናቸው? (ለ) በጉ ከዚህ ቀጥሎ ምን አደረገ?

13 ከዚህ በላይ ‘የእግዚአብሔር ሰባት መናፍስት’ ምሳሌ በሆኑት የበጉ “ሰባት ዓይኖች” እንደተመሰለው ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ተሞልቶአል። ኢየሱስ የይሖዋ አንቀሳቃሽ ኃይል ሙላት ለምድራዊ አገልጋዮቹ የሚፈስበት መስመር ወይም ቦይ ነው። (ቲቶ 3:6) በሰማይ ሆኖ በዚህ ምድር ላይ የሚደረገውን ሁሉ የሚመለከተውም በዚህ መንፈስ አማካኝነት እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ፍጹም የሆነ የማስተዋል ኃይል አለው። ሳያየው ወይም ሳያስተውለው የሚያመልጥ ነገር የለም። (ከ⁠መዝሙር 11:4⁠ና ከ⁠ዘካርያስ 4:10 ጋር አወዳድር።) ይህ ፍጹም አቋሙን ጠብቆ ዓለምን ድል ያደረገው ልጅ፣ ይህ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር፣ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሲል የሰዋው፣ ከይሖዋ አምላክ ሙሉ ሥልጣን፣ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና ፍጹም የሆነ የማስተዋል ችሎታ የተቀበለው ኢየሱስ የመጽሐፉን ጥቅልል ከይሖዋ እጅ ለመቀበል ሙሉ ብቃት አለው። ከፍ ባለው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተሰጠውን ይህን የሥራ ምድብ ለመቀበል ያመነታ ይሆንን? አያመነታም። ከዚህ ይልቅ “መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው።” (ራእይ 5:7) ግሩም የሆነ የፈቃደኝነትና የተባባሪነት ምሳሌ ነው።

የውዳሴ መዝሙር

14. (ሀ) አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና 24ቱ ሽማግሌዎች ኢየሱስ የመጽሐፉን ጥቅልል በመውሰዱ ምን ተሰማቸው? (ለ) ስለ 24ቱ ሽማግሌዎች ለዮሐንስ የተሰጠው መረጃ ማንነታቸውንና ማዕረጋቸውን ያረጋገጠው እንዴት ነው?

14 በይሖዋ ዙፋን ፊት የነበሩት የቀሩት ፍጥረታት ምን ተሰማቸው? “መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ። እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።” (ራእይ 5:8) 24ቱ ሽማግሌዎች በአምላክ ዙፋን ፊት እንደነበሩት አራት ኪሩቤላዊ ፍጥረታት የኢየሱስን ሥልጣን በመቀበል ሰገዱለት። ይሁን እንጂ በገናና ዕጣን የሞላበት ዕቃ የያዙት እነዚህ ሽማግሌዎች ብቻ ነበሩ። * አዲስ መዝሙር የዘመሩትም እነዚህ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። (ራእይ 5:9) ስለዚህ በገና ይዘው አዲስ መዝሙር ከሚዘምሩት 144,000 ቅዱስ የእግዚአብሔር እሥራኤል ጋር ይመሳሰላሉ። (ገላትያ 6:16፤ ቆላስይስ 1:12፤ ራእይ 7:3-8፤ 14:1-4) ከዚህም በላይ በጥንታዊቷ እሥራኤል በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለይሖዋ ዕጣን እያጨሱ የክህነት አገልግሎት ይፈጽሙ እንደነበሩት ካህናት 24ቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ የክህነት አገልግሎት ሲፈጽሙ ታይተዋል። ምድራዊው የክህነት አገልግሎት ያከተመው አምላክ የሙሴን ሕግ በኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ ጠርቆ ከሥፍራ ባስወገደው ጊዜ ነበር። (ቆላስይስ 2:14) ከዚህ ሁሉ ምን ለመደምደም እንችላለን? እዚህ ላይ ቅቡዓኑ ድል አድራጊዎች ‘የአምላክና የክርስቶስ ካህናት በመሆን ከኢየሱስ ጋር ለሺህ ዓመት ለመግዛት’ ሹመታቸውን እንደተቀበሉ ለመመልከት እንችላለን።—ራእይ 20:6

15. (ሀ) በጥንትዋ እስራኤል ወደ መገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት መብት የነበረው ማን ብቻ ነበር? (ለ) ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከመግባቱ በፊት ዕጣን ማጨሱ የሞትና የሕይወት ጉዳይ የነበረው ለምንድን ነው?

15 በጥንታዊቷ እሥራኤል ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይገኝ ወደነበረበት ቅድስተ ቅዱሳን የመግባት መብት የነበረው ሊቀ ካህኑ ብቻ ነበር። በሚገባበትም ጊዜ ዕጣን ካልያዘ ተቀስፎ ይሞት ነበር። የይሖዋ ሕግ እንዲህ ይል ነበር:- አሮን በይሖዋ “ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል። ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉ ይወስዳል። ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል። እንዳይሞትም የጢሱ ዳመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል።” (ዘሌዋውያን 16:12, 13) ሊቀ ካህናቱ ዕጣን ካላጨሰ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ፈጽሞ ሊገባ አይችልም ነበር።

16. (ሀ) በክርስቲያናዊው ሥርዓት የጥንትዋ ምሳሌ ወደ ሆነችላት ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት የሚችሉት እነማን ናቸው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ዕጣን ማጨስ’ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

16 በክርስትና ሥርዓት ውስጥ ግን እውነተኛው ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን 144,000ዎቹ የበታች ካህናት በሙሉ ይሖዋ ወደሚገኝበት ሰማያዊ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባሉ። (ዕብራውያን 10:19-23) እዚህ ላይ በ24 ሽማግሌዎች የተወከሉት ካህናት ዕጣን ካላጨሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሊገቡ ፈጽሞ አይችሉም። ዕጣን ማጨስ ማለት ደግሞ ዘወትር ቀንና ሌሊት ለይሖዋ ጸሎትና ምልጃ ማቅረብ ማለት ነው።—ዕብራውያን 5:7፤ ይሁዳ 20, 21፤ ከ⁠መዝሙር 141:2 ጋር አወዳድር።

አዲስ መዝሙር

17. (ሀ) 24ቱ ሽማግሌዎች የትኛውን አዲስ መዝሙር ዘመሩ? (ለ) “አዲስ መዝሙር” የሚለው አነጋገር አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ምንን ለማመልከት ያገለግል ነበር?

17 አሁን በጣም የሚጥም ዜማ ያለው መዝሙር ተሰማ። መዝሙሩን ለበጉ የዘመሩት ካህናት ባልንጀሮቹ የሆኑት 24ቱ ሽማግሌዎች ናቸው። “መጽሐፉን ትውስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፣ ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ . . . እያሉ፤ አዲስ ቅኔን ይዘምራሉ።” (ራእይ 5:9) “አዲስ ቅኔ” ወይም “አዲስ መዝሙር” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜም የሚያመለክተው ይሖዋ ለሰጠው ታላቅ ማዳን እርሱን ለማወደስ የቀረበን መዝሙር ነው። (መዝሙር 96:1፤ 98:1፤ 144:9) ስለዚህ ዝማሬው ይሖዋ ስለ ፈጸመው አዲስና አስደናቂ ነገር ለመግለጽ፣ ስለ ታላቅ ስሙ አዲስ ዓይነት አድናቆት እንዳደረበት ለመናገር ስለቻለ መዝሙሩ ወይም ቅኔው አዲስ ይሆናል ማለት ነው።

18. 24ቱ ሽማግሌዎች ኢየሱስን በአዲሱ መዝሙር ያመሰገኑት ምን ስላደረገ ነበር?

18 ይሁን እንጂ እዚህ ላይ 24ቱ ሽማግሌዎች አዲስ መዝሙር የዘመሩት በይሖዋ አምላክ ፊት ሳይሆን በኢየሱስ ፊት ነው። መሠረታዊ ሥርዓቱ አልተለወጠም። በአምላክ ልጅነታቸው ስላደረገላቸው ነገሮች ኢየሱስን ያወድሱታል። በደሙ አማካኝነት ለአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖላቸዋል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ልዩ ንብረት የሆነ አዲስ ሕዝብ ሊገኝ ችሎአል። (ሮሜ 2:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 11:25፤ ዕብራውያን 7:18-25) የዚህ መንፈሳዊ ብሔር አባሎች የተውጣጡት ከብዙ ሥጋዊ ብሔራት ቢሆንም ኢየሱስ እንደ አንድ ሕዝብ ወይም ብሔር አድርጎ በአንድ ጉባኤ ውስጥ አድርጎአቸዋል።—ኢሳይያስ 26:2፤ 1 ጴጥሮስ 2:9, 10

19. (ሀ) ሥጋዊ እስራኤላውያን ታማኝ ባለመሆናቸው ምክንያት ምን ዓይነት በረከት ሳያገኙ ቀርተዋል? (ለ) አዲሱ የይሖዋ ሕዝብ ወይም ብሔር ምን ዓይነት በረከት አግኝቶአል?

19 ይሖዋ በጥንቱ የሙሴ ዘመን እሥራኤላውያንን በአንድ ብሔር ባደራጀበት ጊዜ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። ለዚህም ቃል ኪዳን ታማኝ ሆነው ከኖሩ በእርሱ ፊት የካህናት መንግስት እንደሚሆኑለት ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6) እሥራኤላውያን ግን ታማኞች ሆነው ስላልተገኙ ይህን ቃል አልፈጸመላቸውም። ኢየሱስ መካከለኛ በሆነለት አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት የተገኘው አዲስ ብሔር ግን በታማኝነት ጸንቶአል። ንጉሥና ካሕናት በመሆን ቅን ልብ ያላቸውን የሰው ዘሮች ከይሖዋ ጋር እንዲታረቁ ይረዳሉ። (ቆላስይስ 1:20) አዲሱ ዝማሬ . . . ለአምላካችን መንግሥትና ካሕናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ” ይላል። (ራእይ 5:10) እነዚህ 24 ሽማግሌዎች ይህን አዲስ የውዳሴ መዝሙር ከፍ ያለ ክብር ለተጎናጸፈው ለኢየሱስ ለመዘመር በመቻላቸው ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!

ሰማያዊ ዝማሬ

20. አሁን የተሰማው የትኛው ለበጉ የቀረበ የውዳሴ መዝሙር ነው?

20 በጣም ታላቅ የሆነው የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ሠራዊት ይህን አዲስ መዝሙር እንዴት ተቀበለው? ከመዝሙሩ ጋር መስማማታቸውን ከልባቸው ሲገልጹ በማየቱ ዮሐንስ በጣም ተደስቶአል። “አየሁም፣ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበረ፣ በታላቅም ድምፅ የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።” (ራእይ 5:11, 12) እንዴት ያለ ልብ የሚነካ የውዳሴ መዝሙር ነው!

21. በጉ መወደሱ የይሖዋን ሉዓላዊነት ወይም ደረጃ የሚጋፋ ነውን? ግለጽ።

21 ታዲያ ይህ ሲባል ኢየሱስ የይሖዋ አምላክን ቦታ ወስዶ ፍጥረት ሁሉ በአባቱ ፋንታ ኢየሱስን ወደ ማወደስ ዞር አለ ማለት ነውን? በፍፁም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ የውዳሴ መዝሙር ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ከጻፈው ጋር የሚስማማ ነው። “እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2:9-11) ኢየሱስ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በፍጥረት ሁሉ ፊት ለተደቀነው ዋነኛ ግድድር መልስ በማስገኘትና የይሖዋን ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ በፈጸመው ድርሻ ምክንያት ነው። ይህም ለአባቱ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር አምጥቶአል!

እየጎላ የሚሄድ ታላቅ የሕዝብ መዝሙር

22. ከምድራዊ ግዛት የተሰማው ሕዝባዊ ድምፅ ከየትኛው መዝሙር ጋር ተባብሮአል?

22 ዮሐንስ በገለፀው ትዕይንት የሰማይ ሠራዊቶች የኢየሱስን ታማኝነትና ሰማያዊ ሥልጣን መቀበላቸውን የሚገልፅ ውብ ዝማሬ አስምተዋል። በዚህም ዝማሬያቸው በምድር ላይ ሆነው አብንና ልጁን የሚያወድሱ ሰዎች ዝማሬ ተጨምሮበታል። የአንድ ሰብዓዊ ልጅ የሥራ ክንውን ወላጆቹን ሊያስመሰገን እንደሚችል ሁሉ የኢየሱስ የታማኝነት አካሄድም በፍጥረታት ሁሉ ፊት ‘ለአምላካችን ለአብ ክብር’ የሚያመጣ ሆኖአል። በዚህም ምክንያት ዮሐንስ በመቀጠል እንዲህ ብሎአል:- “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ:- ‘በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፣ ለበጉም ይሁን’ ሲሉ ሰማሁ።”—ራእይ 5:13

23, 24. (ሀ) ይህ መዝሙር በሰማይ መሰማት የጀመረበትን ጊዜ የሚያመለክተው ምንድን ነው? በምድር ላይ መሰማት የሚጀምረው መቼ ነው? (ለ) መዝሙሩ ዓመታት እያለፉ በሄዱ መጠን የበለጠ ድምቀት እያገኘ የሚሄደው እንዴት ነው?

23 ይህ ከፍተኛ የሕዝብ መዝሙር የተሰማው መቼ ነው? መሰማት የጀመረው በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ነበር። ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ከተጣሉ በኋላ ‘በሰማይ ያለ ፍጥረት ሁሉ’ በዚህ የውዳሴ መዝሙር ሊተባበር ችሎአል። በተጨማሪም የታሪክ መዝገብ እንደሚያሳየው ከ1919 ጀምሮ ከጥቂት ሺህ ተነስቶ ቁጥሩ በመጨመር በ2005 ከስድስት ሚልዮን በላይ የሆነው እጅግ ብዙ ሕዝብ ይሖዋን ለሚያወድሰው ዝማሬ ድምቀት ለመስጠት ድምፁን አስተባብሮአል። * ምድራዊው የሰይጣን ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ‘የምድር ፍጥረት ሁሉ’ የይሖዋንና የልጁን ውዳሴ ይዘምራል። ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ ደግሞ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን መነሳት ስለሚጀምሩ ‘ከምድር በታች ያለው ፍጥረት በሙሉ’ ማለትም በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉ በሙሉ የሕዝብ መዝሙሩን የመዘመር አጋጣሚ ያገኛሉ።

24 አሁንም እንኳን ቢሆን ‘ከምድር ዳርቻዎች፣ ከባሕሮችና ከደሴቶች’ የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከምድር አቀፉ የይሖዋ ድርጅት ጋር በመተባበር አዲስ መዝሙር በመዘመር ላይ ናቸው። (ኢሳይያስ 42:10፤ መዝሙር 150:1-6) ይህ የደስታ ውዳሴ የሰው ልጅ በሙሉ ፍጽምና በሚያገኝበት የሺህ ዓመት ፍጻሜ ላይ የመጨረሻውን ከፍተኛ ድምቀት ያገኛል። በዚህ ወቅት የቀደመው እባብ ማለትም ቀንደኛው አሳሳች ሰይጣን ስለሚጠፋ ዘፍጥረት 3:15 ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል፤ ከዚያ በኋላ መንፈሳዊም ሆኑ ሰብዓዊ ፍጥረታት በሙሉ በአንድ ድምፅ “በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን” ብለው በታላቅ ደስታ ይዘምራሉ። በጽንፈ ዓለሙ በሙሉ ከዚህ የተለየ ድምፅ አይሰማም።

25. (ሀ) ዮሐንስ ስለ ጽንፈ ዓለማዊ መዝሙር የሰጠውን ገለጻ ማንበባችን ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል? (ለ) ራእዩ በሚፈጸምበት ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና 24ቱ ሽማግሌዎች ምን ጥሩ ምሳሌ አሳይተውናል?

25 በጣም ታላቅ የሆነ የደስታ ጊዜ ይሆናል። በእርግጥም ዮሐንስ የገለጸልን ነገር ልባችን በደስታ እንዲፈነድቅ ከማድረጉም በላይ ከሰማይ ሠራዊት ጋር በመተባበር ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ልባዊ የውዳሴ መዝሙር እንድንዘምር ያነሳሳናል። ትክክለኛ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁርጠኝነት አልተሰማንምን? በዚህ ውሣኔያችን ከጸናን በይሖዋ እርዳታ በዚያ ታላቅ የደስታ ጊዜ ላይ ለመገኘትና በአጽናፈ ዓለሙ በሙሉ የሚያስተጋባውን የውዳሴ መዝሙር ለመዘመር እንደምንችል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ራእዩ የተደመደመው “አራቱም እንስሶች:- አሜን አሉ፣ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ” በሚሉ ቃላት ስለሆነ አራቱ ኪሩቤላዊ እንስሳትና ከሙታን የተነሱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሙሉ ስምምነት አላቸው።—ራእይ 5:14

26. በምን ነገር ማመን ይኖርብናል? በጉስ ምን ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ነው?

26 አንተም የተወደድህ አንባቢ ሆይ፣ በበጉ መሥዋዕት እንድታምንና ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን ይሖዋን ለማገልገል’ በምታደርገው ትሕትና የሞላበት ጥረት እንድትባረክ እንመኛለን። ‘ተፈላጊውን ምግብ በተገቢው ጊዜ የሚሰጠው’ የዘመናችን የዮሐንስ ክፍል አስፈላጊውን እርዳታ ይስጥህ። (ሉቃስ 12:42) አሁን በጉ ሰባቱን ማኅተሞች ሊፈታ ተዘጋጅቷል። ምን አስደናቂ የሆነ ነገር ሊገልጽልን ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 “በገናና ዕጣን የሞላበት የወርቅ ዕቃ” ያዙ የሚለው አነጋገር በሰዋስዋዊ አገባቡ ለሽማግሌዎቹም ሆነ ለአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ ከቃሉ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ለ24ቱ ሽማግሌዎች ብቻ የሚያመለክት እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል።

^ አን.23 በገጽ 64 ላይ የሚገኘውን ቻርት ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ  86 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]