በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራእይ፣ አስደሳች የሆነው መደምደሚያው!

ራእይ፣ አስደሳች የሆነው መደምደሚያው!

ምዕራፍ 1

ራእይ፣ አስደሳች የሆነው መደምደሚያው!

1. አምላክ ደስ እንዲለን እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?

የዮሐንስ ራእይ! መለኮታዊ መዝገብ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች በሆነ ሁኔታ የሚደመደመው የዮሐንስ ራእይ በተባለው አስደናቂ መጽሐፍ ነው። “አስደሳች” የምንልበት ምክንያት ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ “ደስተኛ አምላክ” ስለተባለና ለሚወዱት ሁሉ “የተከበረ ምሥራች” የሚሰጥ አምላክ እንደሆነ ስለተገለጸ ነው። እኛም ጭምር ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። በዚህም ምክንያት ራእይ ገና ከመጀመሪያው “ይህን የትንቢት መጽሐፍ የሚያነብ ደስተኛ ነው” ይላል። በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደግሞ “የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚፈጽም ደስተኛ ነው” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ ራእይ 1:3፤ 22:7 NW

2. ከራእይ መጽሐፍ ደስታ ለማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2 ከራእይ መጽሐፍ ደስታ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? የምሳሌዎቹንና የምልክቶቹን ትርጉሞች መርምረን በመረዳትና ከተረዳነው ጋር በሚስማማ ሁኔታ በመኖር ነው። ሁከት የበዛበት የሰው ልጅ ታሪክ በቅርቡ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ክፉ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርዳቸውን ፈጽመው በቦታው ሞት እንኳን የማይኖርበትን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ሲተኩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይደመደማል። (ራእይ 21:1, 4) ታዲያ፣ ማናችንም ብንሆን እንዲህ ባለው አዲስ ዓለም እውነተኛ ሰላምና ደህንነት አግኝተን ለመኖር አንፈልግምን? የአምላክን ቃልአስደናቂውን የራእይ ትንቢት ጭምር በማጥናት እምነታችንን ከገነባን እንዲህ ባለው ዓለም ውስጥ ለመኖር እንችላለን።

አፖካሊፕስ ምንድን ነው?

3. ብዙ ሰዎች የአፖካሊፕስና የአርማጌዶን ትርጉም ምን ይመስላቸዋል?

3 ራእይ በአንዳንድ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አፖካሊፕስ ይባል የለምን? አዎ፤ ይህም የሆነው ራእይ የሚለው ቃል የተተረጎመው አፖካሊፕሲስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል ስለሆነ ነው። ብዙ ሰዎች አፖካሊፕስ ዓለም በኑክሌር ጦርነት መጥፋትዋን የሚያመለክት ቃል ይመስላቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ብዙ የኑክሌር የጦር መሣሪያዎች ይሠሩበት በነበረው በቴክሳስ ከተማ የሚኖሩ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች “የመጀመሪያዎቹ ጠፊዎች እኛ ነን” ይሉ ነበር። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ቀሳውስት “አርማጌዶን የማይቀር ከመሆኑም በላይ በጣም እንደቀረበና በደግነትና በክፋት ኃይሎች መካከል፣ በአምላክና በሰይጣን መካከል የሚደረገው የመጨረሻ ጦርነት በኑክሌር እልቂት እንደሚፈጸም እርግጠኞች” መሆናቸው ተገልጾአል። *

4. “አፖካሊፕስ” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው? የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ “ራእይ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ይሁን እንጂ አፖካሊፕስ ምንድን ነው? ብዙ መዝገበ ቃላት ለዚህ ቃል “ከጠፈር የሚመጣ ታላቅ ጥፋት” የሚልና ይህንን የሚመስሉ ሌሎች ትርጉሞችን ቢሰጡም አፖካሊፕስ የተባለው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ሽፋንን ማውለቅ”፣ “ማራቆት”፣ ወይም “የተከደነውን መግለጥ” ማለት ነው። ስለዚህ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ “ራእይ” ወይም በእንግሊዝኛ “ሬቬሌሽን” መባሉ ተገቢ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ስለ ዓለም ጥፋት የሚናገር ተስፋ አስቆራጭ መልእክት ሳይሆን በልባችን ውስጥ ደስ የሚያሰኝ ተስፋና የማይናወጥ እምነት የሚገነባ የመለኮታዊ እውነቶች መግለጫ ነው።

5. (ሀ) በአርማጌዶን የሚጠፉት እነማን ናቸው? ከዚያ የሚተርፉትስ? (ለ) ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ምን ታላቅ ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

5 እውነት ነው፣ አርማጌዶን “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ የሚደረግ ጦርነት” መሆኑ በዚህ በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጾአል። (ራእይ 16:14, 16 NW) ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት ከኑክሌር እልቂት ፈጽሞ የተለየ ነው። የኑክሌር እልቂት ቢመጣ ምድር ሕይወት አልባ ትሆናለች። የአምላክ ቃል ግን አምላክ በሚቆጣጠራቸው ኃይሎች የሚጠፉት ክፉ የአምላክ ተቃዋሚዎች ብቻ እንደሆኑ ዋስትና ይሰጠናል። (መዝሙር 37:9, 10፤ 145:20) የአምላክ ፍርድ ለመጨረሻ ጊዜ በአርማጌዶን ሲፈጸም ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሕይወት ይተርፋሉ። እነዚህንም ከጥፋት የተረፉ ሰዎች እረኛው ክርስቶስ ኢየሱስ ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ወደሚገኘው የዘላለም ሕይወት ይመራቸዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ለመገኘት አትፈልግምን? የራእይ መጽሐፍ ለመገኘት እንደምትችል ማመልከቱ እንዴት ያስደስታል!—ራእይ 7:9, 14, 17

መለኮታዊ ምሥጢሮችን መመርመር

6. ባለፉት ዓመታት ስለ ራእይ የሚገልጹ ምን መጻሕፍት በይሖዋ ምሥክሮች ታትመው ወጥተው ነበር?

6 የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል በ1917 ያለቀለት ምሥጢር የተባለ መጽሐፍ አሳትመው ነበር። ይህ መጽሐፍ የሕዝቅኤልንና የራእይን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ቁጥር በቁጥር የሚተነትን ነበር። ከዚያም በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ የሆኑ የተለያዩ የዓለም ሁኔታዎች በመከሰታቸው በ1930 ወቅታዊ የሆነ ብርሃን የተባለ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ወጣ። በዚህ መጽሐፍ ከጊዜው ጋር የተስማማ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተደረገ ጥናት ቀርቦ ነበር። ለጻድቃን የፈነጠቀው ብርሃን በይበልጥ እየፈካ በመሄዱ የይሖዋ ምሥክሮች በ1963 “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች የአምላክ መንግሥት ትገዛለች!” የተባለውን ባለ 704 ገጽ መጽሐፍ አወጡ። ይህ መጽሐፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን የታላቂቱ ባቢሎንን አነሳስና አወዳደቅ በስፋት ከመተረኩም በላይ የራእይን መጽሐፍ የመጨረሻ ዘጠኝ ምዕራፎች ይተነትን ነበር። ‘የጻድቃኑ መንገድ’ በተለይ በጉባኤ አሠራር ረገድ በይበልጥ እየበራ ሲሄድ በ1969 “ከዚያ በኋላ የአምላክ ምሥጢር ተፈጸመ” የተባለ የመጀመሪያዎቹን አሥራ ሦስት የራእይ መጽሐፍ ምዕራፎች የሚተነትን ባለ 384 ገጽ መጽሐፍ ወጣ።—መዝሙር 97:11፤ ምሳሌ 4:18

7. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ስለ ራእይ የሚገልጽ መጽሐፍ ያዘጋጁት ለምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፉ ውስጥ አንባቢዎችን የሚያግዙ ምን የማስተማሪያ እርዳታዎች ይገኛሉ?

7 ታዲያ አሁን ስለ ራእይ መጽሐፍ የሚገልጽ ሌላ መጽሐፍ ማዘጋጀትና እንደገና ማሳተም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዚህ በፊት በእነዚህ መጻሕፍት ላይ የተገለጸው ትምህርት በጣም ሰፋ ያለ ስለነበረ ትምህርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች በቀላሉ ሊዘጋጅ የሚችል የራእይን መጽሐፍ የሚያብራራ ባለ አንድ ጥራዝ መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ከዚህም በላይ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንባቢዎች የዚህን አስደናቂ ትንቢት ቁምነገሮች በግልጽ እንዲረዱ የሚያግዙ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ሠንጠረዦችና የማጠቃለያ ሐሳቦች ተጨምረዋል።

8. ይህን መጽሐፍ ማሳተም ያስፈለገበት ይበልጥ ጠንካራ የሆነው ምክንያት ምንድን ነው?

8 ይህን መጽሐፍ ማሳተም ያስፈለገበት ይበልጥ ጠንካራ የሆነው ምክንያት በየጊዜው ከታወቁት አዳዲስ እውነቶች ጋር እኩል መራመድ አስፈላጊ መሆኑ ነው። ይሖዋ የቃሉን ትርጉም በመረዳት ረገድ የበለጠ ብርሃን መፈንጠቁን አላቋረጠም። ወደ ታላቁ መከራ እየቀረብን በሄድን መጠን በራእይና በሌሎች መጻሕፍት ስለተገለጹት ትንቢቶች ያለን እውቀት ይበልጥ የጠራና የተስተካከለ እንደሚሆን ሊጠበቅ የሚችል ነው። (ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 7:14) በቂ መረጃ ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ መለኮታዊ ትንቢት እንደጻፈው “ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ በጨለማ እንደሚያበራ መብራት አድርጋችሁ ብትጠነቀቁለት መልካም ነው።”—2 ጴጥሮስ 1:19 የ1980 ትርጉም

9. (ሀ) ራእይ ከሌሎች ትንቢቶች ጋር በመሆን አምላክ ምን እንደሚፈጥር ይናገራል? (ለ) አዲሱ ዓለም ምንድን ነው? አንተስ ከጥፋት ተርፈህ በዚያ ለመኖር የምትችለው እንዴት ነው?

9 ራእይ ይሖዋ አምላክ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለማቋቋም ዓላማ እንዳለው በመግለጽ በሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ተጨማሪ ምሥክርነት ይሰጣል። (ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-5) መልእክቱ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያተኩረው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር በአዲሱ ሰማይ እንዲገዙ በደሙ በዋጃቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ነው። (ራእይ 5:9, 10) ይሁን እንጂ ይህ የምሥራች በክርስቶስ መንግሥት ሥር የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም እምነት ያጠነክራል። አንተስ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነህን? ከሆንክ የአዲሱ ምድር ክፍል በመሆን በብዙ ሰላም፣ በፍጹም ጤንነትና ማለቂያ በሌለው የተትረፈረፈ የአምላክ በረከት እየተደሰትክ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋህን ያጠነክርልሃል። (መዝሙር 37:11, 29, 34፤ 72:1, 7, 8, 16) በሕይወት አልፈህ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከፈለግህ አሁኑኑ በአስቸኳይ በሥዕላዊ መንገድ የተገለጸውን ታሪካዊና ታላቅ የሆነ የራእይ ፍጻሜ በጥሞና መከታተል ይኖርብሃል።—ሶፎንያስ 2:3፤ ዮሐንስ 13:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ሱድዶቸሳይ ቱንግ፣ ሙኒክ፣ ጀርመን ጥር 24, 1987

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ  7 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]