በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራእይ እና አንተ

ራእይ እና አንተ

ምዕራፍ 44

ራእይ እና አንተ

1. (ሀ) መልአኩ ለዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተገለጹት አስደናቂ ተስፋዎች ምን ማረጋገጫ ስጥቶታል? (ለ) ‘ፈጥኜ እመጣለሁ’ ያለው ማን ነው? ይህስ መምጣት የሚፈጸመው መቼ ነው?

አስደናቂ የሆነውን የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም መግለጫ ካነበብክ በኋላ ‘እንዲህ ያለው አስደናቂ ነገር በእርግጥ ሊመጣ ይችላልን?’ ብለህ ለመጠየቅ ሳትገፋፋ አትቀርም። ዮሐንስ የሚከተሉትን የመልአኩን ቃላት በመጻፍ መልሱን ይነግረናል:- “እርሱም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፣ የነቢያትም መናፍስት ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፣ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው አለኝ።” (ራእይ 22:6, 7) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተነገሩት አስደናቂ ትንቢቶች በሙሉ በትክክል ይፈጸማሉ። መልአኩ በኢየሱስ ስም በመናገር “በቶሎ” እንደሚመጣ ተናግሮአል። ይህ ‘መምጣት’ ኢየሱስ የይሖዋን ጠላቶች ለማጥፋትና የራእይን ታላቅና አስደሳች ፍጻሜ ለማምጣት “እንደ ሌባ” ሆኖ የሚመጣበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆን አለበት። (ራእይ 16:15, 16) ስለዚህ በዚያ ጊዜ “ደስተኞች” እንድንባል ከፈለግን ሕይወታችንን ከዚህ ከራእይ መጽሐፍ ጋር ማስማማት ይኖርብናል።

2. (ሀ) ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ነገር ስለተገለጸለት ምን ተሰማው? መልአኩስ ምን አለው? (ለ) መልአኩ “ተጠንቀቅ” “ለእግዚአብሔር ስገድ” ሲል ከተናገረው ቃል ምን እንማራለን?

2 ዮሐንስ ይህ ሁሉ አስደናቂ ነገር ከተገለጠለት በኋላ በጣም መደነቁ የሚገባ ነገር ነው። “ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። እርሱም:- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።” (ራእይ 22:8, 9ከ⁠ራእይ 19:10 ጋር አወዳድር።) መላእክትን እንዳያመልክ ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ለዮሐንስ ዘመን በጣም የሚያስፈልግ ነበር፤ ምክንያቱም በዚያ ዘመን መላእክትን ማምለክ ወይም ከመላእክት ልዩ ነገር ተገልጦልናል ማለት የጀመሩ ሰዎች ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 13:1፤ ገላትያ 1:8፤ ቆላስይስ 2:18) ዛሬም ቢሆን ይህ አነጋገር አምላክን ብቻ ማምለክ እንደሚገባን አበክሮ ይገልጻል። (ማቴዎስ 4:10) ማንንም ወይም ምንንም ነገር በማምለክ ንፁሑን አምልኮ ማርከስ አይገባንም።—ኢሳይያስ 42:5, 8

3, 4. መልአኩ በመቀጠል ለዮሐንስ ምን ነገረው? ቅቡዓን ቀሪዎች ይህን ቃል የታዘዙት እንዴት ነው?

3 ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ለእኔም:- ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፣ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ አለ።”—ራእይ 22:10, 11

4 የዘመናችን ቅቡዓን ቀሪዎችም የመልአኩን ቃላት ታዝዘዋል። የትንቢቱን ቃል በማኅተም አልዘጉትም። የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለው መጽሔት የመጀመሪያው እትም እንኳን (ሐምሌ 1879) በተለያዩ የራእይ መጽሐፍ ቁጥሮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። በመክፈቻ ምዕራፋችን ላይ እንደተገለጸው የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ራእይ መጽሐፍ የሚያብራሩ የተለያዩ መጻሕፍትን አውጥተው ነበር። አሁንም እንደገና እውነት ወዳድ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ትኩረታቸውን በራእይ መጽሐፍ ትንቢቶችና በትንቢቶቹ ፍጻሜዎች ላይ እንዲያተኩሩ አድርገናል።

5. (ሀ) ሰዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸውን ምክርና ማስጠንቀቂያ አንሰማም ቢሉስ? (ለ) ቅኖችና ጻድቃን የሆኑ ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

5 ሰዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን ማስጠንቀቂያዎችና ምክሮች ችላ ለማለት ከመረጡ በምርጫቸው ይግፉበት። “ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ።” በዚህ ስድ ዓለም እድፍ እንደተጨማለቁ ለመኖር ከመረጡ እንደተጨማለቁ ሊሞቱ ይችላሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ፍርድ በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። ቅን ልብ ያላቸው ሁሉ “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” የሚለውን የነቢዩን ምክር ለመፈጸም ይትጉ። (ሶፎንያስ 2:3) ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ ደግሞ “ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ” የሚለውን ምክር በትጋት ይፈጽሙ። ጠቢባን የሆኑ ሁሉ ከኃጢአት የሚገኝ ማንኛውም ጊዜያዊ ጥቅም የጽድቅንና የቅድስናን መንገድ የሚከታተሉ ሰዎች ከሚያገኙአቸው ዘላቂ በረከቶች ጋር ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ያውቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፣ ራሳችሁን ፈትኑ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) በመረጣችሁትና ስትመላለሱበት በቆያችሁበት መንገድ ላይ የተመሠረተውን ሽልማት ትቀበላላችሁ።መዝሙር 19:9-11፤ 58:10, 11

6. ይሖዋ ለራእይ መጽሐፍ አንባቢዎች ለመጨረሻ ጊዜ ምን አላቸው?

6 አሁን የዘላለሙ ንጉሥ ይሖዋ በዚህ ትንቢት ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ለራእይ መጽሐፍ አንባቢዎች በቀጥታ ተናገረ:- “እነሆ፣ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው። ውሻዎችና አስማተኛዎች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።”—ራእይ 22:12-15

7. (ሀ) ይሖዋ ‘ፈጥኖ የሚመጣው’ ምን ለማድረግ ነው? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተካፋይነት የማይኖራቸው ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ አምላክ አሁንም በድጋሚ ዘላለማዊ ሉዓላዊነቱንና ያወጣውን ዓላማ ሳይፈጽም የማይቀር መሆኑን አበክሮ ገለጸ። ፍርዱን ለሚፈጽሙና ከልባቸው ለሚፈልጉት ሰዎች ዋጋቸውን ለመስጠት “በቶሎ” ይመጣል። (ዕብራውያን 11:6) ሽልማት የሚያገኙትና ወደ ውጭ የሚጣሉት ሰዎች የሚወሰኑት በራሱ ሕግጋትና ደንቦች መሠረት ነው። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ይሖዋ እዚህ ላይ ለገለጻቸው ነውረኛ ድርጊቶች ዓይኖቻቸውን በመጨፈናቸው ‘አንደበት እንደሌላቸው ውሾች’ ሆነዋል። (ኢሳይያስ 56:10-12፤ በተጨማሪም ዘዳግም 23:18 ባለማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችንና ቀኖናዎችን ስለወደዱ “ውሸትን የሚወዱና የሚያደርጉ” ሆነዋል። ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የሰጠውን ምክር ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽሙ ቀርተዋል። ስለዚህ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ምንም ዓይነት ድርሻ አይኖራቸውም።

8. (ሀ) ወደ “ሕይወት ዛፍ” የሚሄዱት እነማን ብቻ ናቸው? ይህስ ምን ማለት ነው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን ያጠቡት እንዴት ነው? ንጹሕ አቋም የሚያገኙትስ እንዴት ነው?

8 “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ” መብት የሚኖራቸው በይሖዋ ዓይን ንጹሕ ሆነው ለመታየት ‘ልብሳቸውን ያጠቡት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በሰማያዊ ቦታቸው ሞት የማይደፍረው ሕይወት የማግኘት መብትና ሥልጣን ይሰጣቸዋል ማለት ነው። (ከዘፍጥረት 3:22-24፤ ከ⁠ራእይ 2:7⁠ና ከራእይ 3:4, 5 ጋር አወዳድር።) ሰብዓዊ ሞት ከሞቱ በኋላ ከሙታን ተነስተው ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ይገባሉ። 12ቱ መላእክት ሰማያዊ ተስፋ አለን እያሉ በሐሰትና በእርኩሰት የሚመላለሱትን ወደ ውጭ አስቀርተው እነዚህን ግን ወደ ውስጥ ያስገባሉ። በተጨማሪም በምድር ላይ ያሉት እጅግ ብዙ ሰዎች “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም” አንጽተዋል። ይህንን ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ይሖዋ እዚህ ላይ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸውን የእርኩሰት ሥራዎች በማስወገድና ኢየሱስ ለጉባኤዎች በላከው ሰባት መልእክቶች የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ነው።—ራእይ 7:14፤ ምዕራፍ 2⁠ና 3

9. ኢየሱስ ምን ቃል ተናገረ? የእርሱም መልእክት ሆነ መላው የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በአንደኛ ደረጃ ለማን ነው?

9 ከይሖዋ ቀጥሎ ኢየሱስ ተናገረ። እርሱም የራእይን መጽሐፍ ለሚያነቡ የቀና ልብ ያላቸው ሰዎች እንዲህ በማለት የማጽናኛ ቃል ተናገረ:- “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” (ራእይ 22:16) አዎ፣ እነዚህ ቃላት በመጀመሪያ ደረጃ የተነገሩት “ለጉባኤዎቹ” ነው። ይህ መልእክት በአንደኛ ደረጃ በምድር ላይ ለሚኖሩት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የተላከ ነው። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች ሁሉ በአንደኛ ደረጃ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለሚሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተነገሩ ናቸው። እጅግ ብዙ ሰዎችም በዚህ ጉባኤ አማካኝነት የእነዚህን ውድ የሆኑ ትንቢታዊ እውነቶች የመረዳትና የማስተዋል መብት አግኝተዋል።—ዮሐንስ 17:18-21

10. ኢየሱስ ራሱን (ሀ) “የዳዊት ሥርና ዘር” (ለ) “የሚያበራ የንጋት ኮከብ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ ክርስቶስ ራእይን ለዮሐንስበዮሐንስ በኩል ደግሞ ለጉባኤው የማስተላለፍ ሥራ ተሰጥቶት ነበር። ኢየሱስ “የዳዊት ሥርና ዘር” ነው። የዳዊት የሥጋ ዝርያ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ መንግሥት ንጉሥ የመሆን ብቃት አለው። በተጨማሪም የዳዊት “የዘላለም አባት” ስለሚሆን የዳዊት “ሥር” ይሆናል። (ኢሳይያስ 9:6፤ 11:1, 10) ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚፈጽምበት ከዳዊት መስመር የመጣ ዘላለማዊና ሕያው ንጉሥ ነው። በሙሴ ዘመን ትንቢት የተነገረለት ደማቅ “የንጋት ኮከብ” እርሱ ነው። (ዘኍልቁ 24:17፤ መዝሙር 89:34-37) ቀኑ እንዲነጋ የሚያደርገው “የንጋት ኮከብ” እርሱ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:19) ታላቅ ጠላት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን ክፋትና ተንኮል ይህ ኮከብ እንዳይወጣ ሊያግድ አልቻለም።

“ና” ይበል

11. ዮሐንስ ለሰው ሁሉ ምን ነፃ ግብዣ አቀረበ? ይህንንስ ግብዣ እነማን ሊቀበሉ ይችላሉ?

11 አሁን ደግሞ ዮሐንስ ራሱ የሚናገርበት ተራ ደረሰ። ልቡ ለተመለከተውና ለሰማው ነገር ሁሉ በአድናቆት ተሞልቶ እንዲህ አለ:- “መንፈሱና ሙሽራይቱም:- ና ይላሉ። የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 22:17) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች ለ144,000ዎች ብቻ ተወስነው የሚቀሩ አይሆኑም። እዚህ ላይ ለሁሉ ሰው ግብዣ ቀርቦአል። የይሖዋ ቀስቃሽ መንፈስ የሚሠራው በሙሽራይቱ ክፍል በኩል ነው። “የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለው መልእክት በግልጽ ሲደመጥ የቆየው በዚህ ምክንያት ነው። (በተጨማሪም ኢሳይያስ 55:1፤ 59:21 ተመልከት።) የጽድቅ ጥማት ያለበት ሁሉ እንዲመጣና ከይሖዋ ልግስና እንዲሳተፍ ተጋብዞአል። (ማቴዎስ 5:3, 6) የቅቡዓን የዮሐንስ ክፍል አባሎችን ግብዣ የተቀበሉ የምድር ወራሾች ሁሉ ባለ ታላቅ መብቶች ናቸው።

12. እጅግ ብዙ ሰዎች የ⁠ራእይ 22:17⁠ን ግብዣ እንዴት ተቀብለዋል?

12 በቁጥር እየጨመሩ የሄዱት እጅግ ብዙ ሰዎች ከ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ ግብዣውን ሲሰሙና ይኸውም ልብ ብለው ሲያስተውሉት ቆይተዋል። ባልንጀሮቻቸው እንደሆኑት ቅቡዓን ባሮች በይሖዋ ፊት ንፁሕ አቋም አግኝተዋል። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ወርዳ ለሰው ልጅ በሙሉ በረከቶችዋን የምታዳርስበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። እጅግ ብዙ ሰዎች ቀስቃሽ የሆነውን የራእይ መልእክት ካዳመጡ በኋላ “ና” በማለት ብቻ ሳይወሰኑ ሌሎች ሰዎችን ወደ ይሖዋ ድርጅት እየሰበሰቡ እነርሱም በተራቸው “የተጠማም ይምጣ” እያሉ እንዲጋብዙ ያሰለጥኑአቸዋል። በዚህም ምክንያት የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር በጣም አድጐ ከ6,000,000 የሚበልጡ ሰዎች ከ235 በሚበልጡ አገሮች ከ9,000 ከሚያንሱ የሙሽራይቱ ክፍል አባሎች ጋር በመተባበር “የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ በማሰማት ላይ ናቸው።

13. ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጠ?

13 ቀጥሎ የተናገረው ደግሞ ኢየሱስ ነው። እንዲህ አለ:- “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፣ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።”—ራእይ 22:18, 19

14. የዮሐንስ ክፍል የራእይን ትንቢት እንዴት ይመለከተዋል?

14 የዮሐንስ ክፍል አባሎች የሰውን ትኩረት ወደ ራእይ “የትንቢት ቃል” መሳብ ይኖርባቸዋል። ትንቢቱን መደበቅ ወይም በትንቢቱ ላይ መጨመር አይገባቸውም። መልእክቱ ከሰገነት ላይ ሆኖ እንደሚነገር ቃል በይፋና በግልጽ መሰበክ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 10:27) ራእይ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። አምላክ ራሱ በተናገረውና በነገሠው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ባስተላለፈው ቃሉ ላይ አንዳች ነገር ሊለውጥ የሚደፍር ማን ነው? ይህን ለማድረግ የሚደፍር ሰው በእውነትም ለሕይወት ከሚያደርገው ሩጫ መውደቅና በታላቂቱ ባቢሎንና በመላው ዓለም ላይ ከሚደርሰው መቅሠፍት መቀበል ይገባዋል።

15. ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች “የምመሰክር እኔ ነኝ” ማለቱና ‘እነሆ ፈጥኜ እመጣለሁ’ ማለቱ ምን ትርጉም አለው?

15 አሁን ኢየሱስ አንድ የመጨረሻ ማበረታቻ መልእክት ይጨምራል:- “ይህን የሚመሰክር:- አዎን፣ በቶሎ እመጣለሁ ይላል።” (ራእይ 22:20ሀ) ኢየሱስ “የታመነውና እውነተኛው ምስክር” ነው። (ራእይ 3:14) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተገለጹት ራእዮች ከመሰከረ ራእዮቹ እውነት መሆን ይኖርባቸዋል። ኢየሱስም ሆነ ይሖዋ በቶሎ የሚመጡ መሆናቸውን በመደጋገም አጠንክረው ተናግረዋል። ኢየሱስ ለአምስተኛ ጊዜ መናገሩ ነው። (ራእይ 2:16፤ 3:11፤ 22:7, 12, 20) የሚመጡት በታላቂቱ ጋለሞታ፣ በፖለቲካዊ “ነገሥታትና” “የጌታችንንና [የይሖዋንና] የክርስቶስን መንግሥት” በሚቃወሙ ሁሉ ላይ የቅጣት ፍርድ ለመፈጸም ነው።—ራእይ 11:15፤ 16:14, 16፤ 17:1, 12-14

16. ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ፈጥነው እንደሚመጡ ስላወቅህ ምን ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርብሃል?

16 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ በቶሎ እንደሚመጡ ማወቅህ ‘የይሖዋን ቀን ዘወትር እንድታስብ’ ሊያደርግህ ይገባል። (2 ጴጥሮስ 3:12) ይህ በሰይጣን ሥርዓት ሥር የሚተዳደረው ምድር ተደላድሎ የቆመ የሚመስለው ለጊዜው ብቻ ነው። በሰይጣን ሥር የሆኑትን የዓለማዊ ገዥዎች የሚያመለክተው ሰማይ ምንም ዓይነት የተሳካ ውጤት ያገኘ ቢመስልም በንኖ ይጠፋል። እነዚህ ሁሉ አላፊና ጠፊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። (ራእይ 21:1) ዘላቂና ቋሚ የሆኑት ይሖዋ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትተዳደረው መንግሥቱና ቃል የገባልን አዲስ ዓለም ብቻ ናቸው። ለአንድ አፍታ እንኳን ይህን መዘንጋት አይገባህም!1 ዮሐንስ 2:15-17

17. ስለ ይሖዋ ቅድስና ያለህ አድናቆት እንዴት ሊነካህ ይገባል?

17 እንግዲያውስ ከራእይ መጽሐፍ ጥናትህ ያገኘኸው ትምህርት ሕይወትህን በጥልቅ እንዲነካው ከልባችን እንመኛለን። ስለ ይሖዋ ሰማያዊ ሕልውናና ዙፋን የተመለከትከው ጭላንጭል ፈጣሪያችን እንዴት ያለ አንጸባራቂ ክብር እንዳለውና ቅድስናው በጣም ታላቅ እንደሆነ እንድታስተውል አላስቻለህምን? (ራእይ 4:1 እስከ 5:14) እንዲህ ያለውን አምላክ ማገልገል ምንኛ ታላቅ መብት ነው! ለአምላክ ቅድስና ያለህ አድናቆት ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የሰጠውን ምክር በጥሞና እንድትከተልና እንደ ፍቅረ ንዋይ፣ የጣዖት አምልኮ፣ ሥነ ምግባራዊ እርኩሰት፣ የክህደት ኑፋቄ ለዘብተኛ እንደመሆንና አገልግሎታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ከሚያደርጉ እነዚህን የመሰሉ ድርጊቶች እንድትርቅ ያድርግህ። (ራእይ 2:1 እስከ 3:22) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” በማለት ለዮሐንስ ክፍል የተናገረው ቃል ለእጅግ ብዙ ሰዎችም ይሠራል።—1 ጴጥሮስ 1:15, 16

18. በተቻለህ መጠን በምን ሥራ መካፈል ይኖርብሃል? ይህስ ሥራ በዘመናችን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 በተጨማሪም “የተወደደችውን የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ዓመት፣ አምላካችን የሚበቀልበትን ቀን” በምትናገርበት ጊዜ አዲስና ትኩስ ቅንዓት ይኑርህ። (ኢሳይያስ 35:4፤ 61:2) የታናሽ መንጋ ክፍልም ሆንክ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ሰባቱን የይሖዋ ቁጣ ጽዋዎች መፍሰስ በማሳወቅ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑርህ። በሰይጣን ዓለም ላይ የሚወርደውን የአምላክ ፍርድ ተናገር። በዚህ ላይ ደግሞ ስለተቋቋመችው የይሖዋና የክርስቶስ መንግሥት በሚነገረው የዘላለም ምሥራች ቃል ላይ የራስህን ድምፅ ጨምር። (ራእይ 11:15፤ 14:6, 7) ይህን ሥራ በትጋትና በጥድፊያ ስሜት አከናውን። በጌታ ቀን ውስጥ እንደምንኖር መገንዘባችን ገና ይሖዋን ማገልገል ያልጀመሩ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን በማወጅ ሥራ እንዲተባበሩ እንዲገፋፋቸው እንመኛለን። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት ደረጃ እንዲደርሱ እንመኛለን። ‘ዘመኑ ቅርብ መሆኑን’ አትዘንጋ!ራእይ 1:3

19. አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ ምን የመደምደሚያ ቃል ተናግሮአል? እነዚህንስ ቃላት እንዴት መቀበል ይኖርብሃል?

19 ስለዚህ ከዮሐንስ ጋር ሆነን “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” እያልን በጋለ ስሜት እንጸልያለን። አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ ደግሞ በመጨመር “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን” ይላል። (ራእይ 22:20ለ, 21) ይህን መጽሐፍ ለምታነቡ ሁሉ ይህንኑ እንመኛለን። ሁላችሁም ከልባችሁ “አሜን” ለማለት እንድትችሉ ታላቁ የራእይ መደምደሚያ ቅርብ ስለመሆኑ እምነት እንዲኖራችሁ እንመኛለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 314 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ውሻዎች . . . በውጭ አሉ”

[በገጽ 315 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በደጆችዋ ወደ ከተማይቱ የሚገቡ . . . ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው”