በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስመ ጥፉ በሆነችው አመንዝራ ላይ መፍረድ

ስመ ጥፉ በሆነችው አመንዝራ ላይ መፍረድ

ምዕራፍ 33

ስመ ጥፉ በሆነችው አመንዝራ ላይ መፍረድ

ራእይ 11--ራእይ 17:1-18

ርዕሰ ጉዳይ:- ታላቂቱ ባቢሎን በቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ ትጋልባለች። ይህም አውሬ በእርስዋ ላይ በመነሳት ያጠፋታል

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከ1919 እስከ ታላቁ መከራ ድረስ

1. ከሰባቱ መላእክት አንዱ ለዮሐንስ ምን ገለጸለት?

የይሖዋ የጽድቅ ቁጣ ጽዋ ሙሉ በሙሉ ማለትም ሰባቱም ጽዋ መፍሰስ ይኖርበታል። ስድስተኛው መልአክ የራሱን ጽዋ በጥንትዋ ባቢሎን ላይ ማፍሰሱ ሁኔታዎች ወደ መጨረሻ የአርማጌዶን ጦርነት በሚገሰግሱበት ጊዜ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ለሚደርሰው መቅሰፍት ምሳሌ መሆኑ ተገቢ ነበር። (ራእይ 16:1, 12, 16) አሁንም ይሖዋ የጽድቅ ፍርዱን ለምንና እንዴት እንደሚፈጽም የገለጸው ይኸው መልአክ ሳይሆን አይቀርም። ዮሐንስ ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተውና በሰማው ነገር በጣም ተደንቆአል። “ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ:- ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ።”—ራእይ 17:1, 2

2. “ታላቂቱ ጋለሞታ” (ሀ) የጥንትዋ ሮም እንዳልሆነች (ለ) ታላቅ የንግድ ድርጅት እንዳልሆነች (ሐ) ሃይማኖታዊ ድርጅት እንደሆነች የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለን?

2 “ታላቂቱ ጋለሞታ!” ይህን የመሰለ አስደንጋጭ ስም የተሰጣት ለምንድን ነው? እርስዋስ ማን ናት? አንዳንዶች ይህች ምሳሌያዊት አመንዝራ የጥንትዋ ሮም ናት ይላሉ። ይሁን እንጂ ሮማ የፖለቲካ ኃይል ነበረች። ይህች አመንዝራ ከምድር ነገሥታት ጋር የምትሴስን ናት። ከእነዚህም ነገሥታት መካከል የሮማ ነገሥታት እንደሚገኙበት የታወቀ ነው። ከዚህም በላይ ከጠፋች በኋላ “የምድር ነገሥታት” ስለጥፋትዋ ያለቅሱላታል። ስለዚህ የፖለቲካ ኃይል ልትሆን አትችልም። (ራእይ 18:9, 10) በተጨማሪም የምድር ነጋዴዎችም ስላዘኑላት ታላላቅ የንግድ ድርጅቶችን የምታመለክት ልትሆን አትችልም። (ራእይ 18:15, 16) ይሁን እንጂ ‘በአስማትዋ የምድር አሕዛብን ሁሉ እንዳሳተች’ እናነባለን። (ራእይ 18:23) ይህም ታላቋ አመንዝራ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ድርጅት እንደሆነች እንድንገነዘብ ያስችለናል።

3. (ሀ) ታላቂቱ ጋለሞታ ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወይም ከሕዝበ ክርስትና የበለጠ ነገር ማመልከት የሚኖርባት ለምንድን ነው? (ለ) በአብዛኞቹ የምሥራቃውያን ሃይማኖቶችም ሆነ በሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች ውስጥ እንዴት ያሉ ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶች ይገኛሉ? (ሐ) የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ የነበሩት ጆን ሄንሪ ኒውማን ስለ ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ልማዶች አመጣጥ ምን አምነዋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት)

3 ይሁን እንጂ የምታመለክተው የትኛውን ሃይማኖታዊ ድርጅት ነው? አንዳንዶች እንደሚሉት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ናትን? ወይም መላዋን ሕዝበ ክርስትና የምታመለክት ናትን? አሕዛብን በሙሉ ያሳተች ድርጅት ከሆነች ከዚህ የበለጠ ስፋት ያላት መሆን ይኖርባታል። መላውን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የምታጠቃልል መሆን ይኖርባታል። በምድር በሙሉ በሚገኙ ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶች በብዛት መኖራቸው ይህች ድርጅት ከባቢሎን ምሥጢሮች የመነጨች መሆኗን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል የሰው ነፍስ ዘላለማዊነት፣ የሲኦል ሥቃይና የአማልክት ሥላሴነት እምነት በአብዛኞቹ የሩቅ ምሥራቅ ሃይማኖችም ሆነ በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ ይገኛሉ። ከ4,000 ዓመታት በፊት በጥንትዋ የባቢሎን ከተማ ውስጥ የተጸነሰው የሐሰት ሃይማኖት በጣም አድጐ ትልቅ ድርጅት በመሆኑ ታላቂቱ ባቢሎን የሚል ስያሜ ማግኘቱ የተገባ ነው። * ይሁን እንጂ ቀፋፊ በሆነው “ታላቂቱ ጋለሞታ” በሚለው ስም የተጠራችው ለምንድን ነው?

4. (ሀ) የጥንትዋ እስራኤል ግልሙትና ትፈጽም የነበረው እንዴት ነው? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን የገለሞተችው በምን ጉልህ መንገድ ነው?

4 ባቢሎን (ወይም ዝብርቅ የሚል ትርጉም ያላት ባቤል) ታላቅነት ደረጃ ላይ የደረሰችው በናቡከደናፆር ዘመን ነበር። የጥንትዋ ባቢሎን ከሺህ የሚበልጡ ቤተ መቅደሶችና የጸሎት ቤቶች የነበሩአት ሃይማኖትና ፖለቲካ የተጣመረባት መንግሥት ነበረች። ቀሳውስቶችዋ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። ባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት መሆንዋ ከቀረ ብዙ ጊዜ የሆነው ቢሆንም ዛሬ ደግሞ የፖለቲካ ጉዳዮችን ለመምራትና ለመቆጣጠር የምትፈልግ ሃይማኖታዊት ታላቅ ባቢሎን አለች። ይሁን እንጂ ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቱን አምላክ ይደግፋልን? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እስራኤል በሐሰት አምልኮ በምትካፈልበትና በይሖዋ ከመታመን ይልቅ ከብሔራት ጋር ሽርክና በምትመሰርትበት ጊዜ አመንዝራ እንደሆነች ተገልጾአል። (ኤርምያስ 3:6, 8, 9፤ ሕዝቅኤል 16:28-30) ታላቂቱ ባቢሎንም አመንዝራለች። በምድር ነገሥታትና ገዥዎች ላይ ሥልጣን ለማግኘት ስትል የመሰላትን ሁሉ አድርጋለች።—1 ጢሞቴዎስ 4:1

5. (ሀ) ሃይማኖታዊ ቀሳውስት እንዴት ያለ ዝናና የከበሬታ ቦታ ይፈልጋሉ? (ለ) ዓለማዊ ከበሬታ ለማግኘት መፈለግ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናረውን በቀጥታ የሚቃወመው እንዴት ነው?

5 በዛሬው ጊዜ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት ሹመት ለማግኘት ይጣጣራሉ። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች የካቢኔ ሹመት በመቀበል በመንግሥት ሥልጣን ይካፈላሉ። በ1988 ሁለት የታወቁ የፕሮቴስታንት ቀሳውስት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ለመሆን ተወዳድረው ነበር። የታላቂቱ ባቢሎን መሪዎች ዝና ወዳዶች ሆነዋል። ከታላላቅ የፖለቲካ ሰዎች ጋር ሆነው የተነሱአቸው ፎቶግራፎች በታላላቅ ጋዜጦች ገጾች ላይ ብዙ ጊዜ ይወጣሉ። ኢየሱስ ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” በማለት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት እምቢተኛ ሆኖአል።—ዮሐንስ 6:15፤ 17:16፤ ማቴዎስ 4:8-10፤ በተጨማሪም ያዕቆብ 4:4 ተመልከት።

ዘመናዊ ‘ግልሙትና’

6, 7. (ሀ) የሂትለር ናዚ ፓርቲ በጀርመን አገር ሥልጣን ላይ የወጣው እንዴት ነው? (ለ) ቫቲካን ከሂትለር ናዚ ፓርቲ ጋር የተፈራረመችው የስምምነት ውል ሂትለር ዓለምን ለመግዛት ላደረገው ጥረት ድጋፍ የሆነው እንዴት ነው?

6 ታላቋ አመንዝራ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባትዋ ለሰው ልጆች ይህ ነው የማይባል ሥቃይ አምጥታለች። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ከታሪክ መጻሕፍት ፍቀው ሊያጠፉት የሚፈልጉትን በጀርመን አገር ሂትለር ወደ ሥልጣን የወጣበትን የሚያስጠላ ሁኔታ እንመልከት። በግንቦት 1924 የናዚ ፓርቲ ራይክስታግ በተባለው የጀርመን ምክር ቤት ውስጥ 32 መቀመጫዎች ነበሩት። በግንቦት 1928 ግን የነበረው መቀመጫ ብዛት አንሶ 12 ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት በ1930 ዓለምን ዋጣት፣ ከዚህ ዓመት በኋላ ናዚዎች በአስደናቂ ሁኔታ አንሰራርተው በሐምሌ 1932 በተደረገው የጀርመን ምርጫ ከ608 መቀመጫዎች መካከል 230 መቀመጫ አገኙ። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሊቀ ጳጳሱ የጀግንነት ማዕረግ የተቀበለው የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ፍራንዝ ፎን ፓፔን ናዚዎችን መርዳት ጀመረ። የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ፎን ፓፔን አዲስ ቅድስት የሮማ ግዛት የማቋቋም ሕልም ነበረው። ለአጭር ጊዜ የቆየበት የቻንስለርነት ሹመቱ ምንም ውጤት ስላላስገኘለት አሁን ደግሞ በናዚዎች በኩል ሥልጣን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመረ። እስከ ጥር 1933 ድረስ ለሂትለር የኢንዱስትሪ ከበርቴዎችን ድጋፍ አስገኝቶለት ነበር። ከዚህም በላይ ሂትለር በከፍተኛ ተንኮልና ሤራ ጥር 30 ቀን 1933 የጀርመን ቻንስለር እንዲሆን አስችሎታል። ፎን ፓፔን ራሱ ምክትል ቻንስለር ሆነና ሂትለር የጀርመን ካቶሊኮችን ድጋፍ እንዲያገኝ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ሂትለር ሥልጣን ላይ በወጣ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፓርላማውን አሰናበተ፣ በሺህ የሚቆጠሩ ተቃዋሚ መሪዎችን ወደ ማጎሪያ ካምፖች አስገባ። አይሁዳውያንን ለመጫንና ለመጨቆን የሚያስችለውንም ዘመቻ በይፋ ማንቀሳቀስ ጀመረ።

7 ቫቲካን ኃይል እያገኘ ከሄደው ከናዚዝም እንቅስቃሴ ጋር ሽርክና ለመፍጠር ያላት ፍላጐት ሐምሌ 20, 1933 ካርዲናል ፓቼሊ (በኋላ ሊቀ ጳጳስ ፓየስ 12ኛ የሆኑት ናቸው) በቫቲካንና በናዚ ጀርመን መካከል የተደረገውን ስምምነት በሮማ ከተማ በፈረሙ ጊዜ በግልጽ ታይቶአል። የሂትለር ወኪል በመሆን ስምምነቱን የፈረመው ፎን ፓፔን ሲሆን በዚህ ጊዜ ፓቼሊ ለፎን ፓፔን ከፍተኛውን የፓየስ መስቀል ኒሻን ሸልመውታል። * ቲቦር ኮኤቨስ ሴታን ኢን ቶፕ ሃት በተባለው መጽሐፋቸው ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “ስምምነቱ ለሂትለር ከፍተኛ ድል ነበር። ሂትለር ከውጪው ዓለም ካገኘው የሞራል ድጋፍ ይህ የመጀመሪያው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ክብር ከሚሰጠው አካል የተገኘ ድጋፍ ነበር።” በስምምነቱ መሠረት ቫቲካን ለጀርመን የካቶሊክ ማዕከላዊ ፓርቲ ትሰጥ የነበረውን ድጋፍ ለማንሳት ተስማማች። ይህን በማድረጓም የሂትለርን ባለ አንድ ፓርቲ “ፍጹማዊ መንግሥት” አድርጋ መቀበሏን አረጋገጠች። * ከዚህም በላይ ይህ ስምምነት በ14ኛው አንቀጽ ላይ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር:- “የሊቃነ ጳጳሳት፣ የመሳሰሉት ሹመቶች የሚጸድቁት ራይኩ (የናዚ መንግሥት) የሾመው ገዥ አጠቃላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የማይቃወም መሆኑን መርምሮ ካረጋገጠ በኋላ ነው።” በ1933 ፍጻሜ ላይ (ፓፓ ፓየስ 11ኛ “ቅዱስ ዓመት” ብለው የሰየሙት ዓመት ነበር) ሂትለር መላውን ዓለም ለመግዛት በሚያደርገው ጥረት የቫቲካን ድጋፍ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይዞ ነበር።

8, 9. (ሀ) ቫቲካን እንዲሁም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ቀሳውስትዋ የናዚን የጭቆና ግዛት እንዴት ተቀበሉት? (ለ) ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀመረበት ጊዜ የጀርመን ካቶሊክ ጳጳሳት ምን መግለጫ አውጥተው ነበር? (ሐ) የሃይማኖትና የፖለቲካ ሽርክና እንዴት ያለ ውጤት አስከትሎአል?

8 የሂትለርን ጭካኔ የተቃወሙና በመቃወማቸውም ምክንያት መከራ የተቀበሉ በጣት የሚቆጠሩ ቀሳውስትና መነኮሳት ቢኖሩም ቫቲካንም ሆነች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከቀሳውስት ጭፍሮችዋ ጋር የኮምኒዝምን መስፋፋት እንደሚገታ ታላቅ ኃይል አድርገው የተመለከቱትን የናዚ ጭካኔ ደግፈዋል። በቫቲካን የተመቻቸ ሥልጣን የያዙት ፓፓ ፓየስ 12ኛ በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው እልቂትና በይሖዋ ምሥክሮችና በሌሎች ሰዎች ላይ ይፈጸም የነበረው ስደት አለምንም ወቀሳ እንዲቀጥል ፈቅደዋል። ፓፓ ጆን ዳግማዊ በግንቦት ወር 1987 ጀርመንን በጎበኙ ጊዜ አንድ ቄስ ያሳየውን ፀረ ናዚ አቋም አሞግሰው መናገራቸው ግራ የሚገባ ነበር። በሂትለር የሰቆቃ አገዛዝ ዘመን የቀሩት በሺህ የሚቆጠሩ የጀርመን ቀሳውስት ምን ያደርጉ ነበር? የጀርመን ካቶሊክ ጳጳሳት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት በመስከረም ወር 1939 የጻፉት ደብዳቤ በዚህ ረገድ የፈጸሙትን ይገልጽልናል። ደብዳቤው በከፊል እንደሚከተለው ይነበባል:- “በዚህ ወሳኝ ሰዓት ካቶሊክ ወታደሮቻችን ፊውረሩን (ሂትለርን) በመታዘዝ ግዳጃቸውን እንዲፈጽሙና መላውን ስብዕናቸውን መሥዋዕት እንዲያደርጉ እንማጠናቸዋለን። ታማኞቻችን በሙሉ ይህ ጦርነት የተባረከ ውጤት እንዲያገኝ ጸሎት በማቅረብ እንዲተባበሩን እንጠይቃለን።”

9 ይህን የመሰለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዲፕሎማሲ ሃይማኖት ባለፉት 4,000 ዓመታት ከፖለቲካ መንግሥታት ሥልጣንና ጥቅም ለማግኘት ዝሙት ሲፈጽም እንዴት እንደቆየ ያሳየናል። ይህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጥምረት ጦርነትን፣ ስደትንና ብዙ ዓይነት መከራዎችን በሰው ልጆች ላይ ሲያስፋፋ ቆይቶአል። ይሖዋ በዚህች ታላቅ አመንዝራ የሚፈርድበት ጊዜ በጣም በመቃረቡ መላው የሰው ልጅ በጣም ሊደሰት ይገባዋል። ይኸው ፍርድ ፈጥኖ እንዲፈጸም ምኞታችን ነው!

በብዙ ውኃዎች ላይ ተቀምጣለች

10. ታላቂቱ ባቢሎን ለመከላከያዋ የምትተማመንባቸው “ብዙ ውኃዎች” ምንድን ናቸው? እነርሱስ ምን እየደረሰባቸው ነው?

10 የጥንትዋ ባቢሎን በብዙ ውኃዎች ላይ ማለትም በኤፍራጥስ ወንዝና በብዙ ቦዮች ላይ ተቀምጣ ነበር። እነዚህ ውኃዎች እስከ ደረቁበት ጊዜ ድረስ ለመከላከያዋና ብዙ ሀብት ለምታገኝበት የንግድ እንቅስቃሴዋ ያገለግሉአት ነበር። (ኤርምያስ 50:38፤ 51:9, 12, 13) ታላቂቱ ባቢሎንም ለብልጽግናዋና ለመከላከያዋ የምትተማመንባቸው ብዙ ውኃዎች አሉአት። እነዚህ ምሳሌያዊ ውኃዎች “ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም” ናቸው። እነዚህም እርስዋ የሰለጠነችባቸውና የገንዘብ ድጋፍ ያገኘችባቸው በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህም ውኃዎች በመድረቅ ላይ ወይም ድጋፋቸውን በማንሳት ላይ ናቸው።—ራእይ 17:15፤ ከ⁠መዝሙር 18:4⁠ና ከ⁠ኢሳይያስ 8:7 ጋር አወዳድር።

11. (ሀ) የጥንትዋ ባቢሎን ‘ምድርን ሁሉ ያሰከረችው’ እንዴት ነበር? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን ‘ምድርን በሙሉ ያሰከረችው’ እንዴት ነው?

11 ከዚህም በላይ የጥንትዋ ባቢሎን “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ” እንደሆነች ተነግሮአል። (ኤርምያስ 51:7) የጥንትዋ ባቢሎን አጎራባች አገሮችን በጦር ኃይልዋ በወረረችበት ጊዜ የይሖዋን የቁጣ ጽዋ እንዲጠጡ አስገድዳ ነበር። እንደ ሰከረ ሰው ደካሞች እንዲሆኑ አድርጋ ነበር። በዚህ ረገድ የይሖዋ መሣሪያ ሆና አገልግላለች። ታላቂቱ ባቢሎንም ዓለም አቀፍ ግዛት እስክትሆን ድረስ በወረራ ብዙ ድሎችን አግኝታለች፤ ቢሆንም የአምላክ መሣሪያ እንዳልሆነች ግልጽ ነው። ያገለገለችው ከአምላክ ይልቅ አብረዋት ሃይማኖታዊ ምንዝር የፈጸሙትን “የምድር ነገሥታት” ነው። በሐሰት መሠረተ ትምህርቶችዋና ሰዎችን በባርነት በሚያስገዙ ሃይማኖታዊ ልማዶች በመጠቀም “በምድር የሚኖሩትን” ሰፊ ሕዝቦች እንደ ሰከረ ሰው ደካማና የገዥዎቻቸውን ፈቃድ በጭፍን የሚፈጽሙ በማድረግ እነዚህን ነገሥታት አስደስታለች።

12. (ሀ) በጃፓን አገር ያለው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ ደም እንዲፈስስ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) በጃፓን አገር ታላቂቱ ባቢሎንን ይደግፉ የነበሩ “ውኃዎች” ድጋፋቸውን ያቋረጡት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሎአል?

12 በዚህ ረገድ የጃፓኑ የሺንቶ ሃይማኖት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በዚህ ሃይማኖት አዕምሮው የታጠበበት ጃፓናዊ ወታደር የሁሉ የበላይ የሆነ የሺንቶ አምላክ ለሆነው ለንጉሠ ነገሥቱ ሕይወቱን መሠዋቱን እንደ ታላቅ ክብር ይቆጥረዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 1,500,000 የሚያክሉ ጃፓናውያን ወታደሮች በጦር ሜዳ ላይ ተገድለዋል። እነዚህ ወታደሮች በሙሉ እጅ መስጠትን እንደ ታላቅ ውርደት ይቆጥሩ ነበር። ይሁን እንጂ ጃፓን በጦርነቱ በመሸነፍዋ ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ሂሮሂቶ የመለኮትነት ባሕርይ የሌላቸው መሆናቸውን ለመቀበል ተገደዋል። በዚህም ምክንያት የታላቂቱ ባቢሎን የሺንቶ ክፍል ድጋፍ ያስገኙለት የነበሩትን ብዙ “ውኃዎች” አጥቶአል። ይህ የሆነው ሺንቶይዝም በፓስፊክ የጦርነት መድረክ ላይ ብዙ ደም እንዲፈስስ ካደረገ በኋላ መሆኑ በጣም ያሳዝናል! በተጨማሪም የሺንቶ ተጽዕኖ መዳከሙ በ1991 በመጨረሻ ላይ ከ200,000 የሚበልጡ ጃፓናውያን የልዑሉ አምላክ የይሖዋ ውስንና የተጠመቁ አገልጋዮች እንዲሆኑ አስችሎአቸዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከዚህ በፊት ሺንቶይስቶችና ቡድሂስቶች የነበሩ ናቸው።

ጋለሞታይቱ በአውሬ ላይ ትጋልባለች

13. መልአኩ ዮሐንስን በመንፈስ ወደ ምድረ በዳ በወሰደው ጊዜ ምን አስደናቂ ነገር ተመለከተ?

13 ትንቢቱ ስለ ታላቂቱ አመንዝራና ስለሚደርስባት ዕጣ ምን የሚገልጸው ተጨማሪ ነገር አለ? ዮሐንስ የሚቀጥለውን ሲናገር በጣም አስደናቂ የሆነ ትዕይንት ልናይ ነው:- “በመንፈስም ወደ በረሐ [መልአኩ] ወሰደኝ የስድብም ስሞች በሞሉበት፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ።”—ራእይ 17:3

14. ዮሐንስ ወደ ምድረ በዳ መወሰዱ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

14 ዮሐንስ ወደ በረሐ (ምድረ በዳ) የተወሰደው ለምን ነበር? ከዚህ ቀደም ሲል በጥንትዋ ባቢሎን ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የተነገረው መግለጫ “በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም” ተብሎአል። (ኢሳይያስ 21:1, 9) ይህም የጥንትዋ ባቢሎን ያን የመሰለ ጠንካራ የውኃዎች መከላከያ ቢኖራትም ሕይወት የማይኖርባት ባድማ ሥፍራ እንደምትሆን የሚያስጠነቅቅ ነበር። ስለዚህ ዮሐንስ የታላቂቱን ባቢሎን ዕጣ እንዲያይ በራእይ ወደ ምድረ በዳ መወሰዱ ተገቢ ነው። ታላቂቱ ባቢሎንም ባድማና ወና መሆን ይኖርባታል። (ራእይ 18:19, 22, 23) ይሁን እንጂ ዮሐንስ በዚያ ሥፍራ በተመለከተው ነገር በጣም ተደንቆአል። ታላቂቱ ጋለሞታ ብቻዋን አልነበረችም። በአንድ አስፈሪ ግዙፍ አውሬ ላይ ተቀምጣለች።

15. በ⁠ራእይ 13:1 ላይና በ⁠ራእይ 17:3 ላይ የተገለጹት አራዊት ምን ልዩነት አላቸው?

15 ይህም አውሬ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ነበሩት። ታዲያ ይህ አውሬ ዮሐንስ ቀደም ሲል ከተመለከተው ባለ ሰባት ራስና ባለ አሥር ቀንድ አውሬ ጋር አንድ ነውን? (ራእይ 13:1) አይደለም፣ ልዩነት አላቸው። ይኸኛው አውሬ መልኩ ቀይ ሲሆን እንደ ፊተኛው አውሬ በራሶቹ ላይ ዘውዶች የሉትም። የስድብ ስም የተሸከመው በራሶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን “የስድብ ስሞች የሞሉበት” ነው። ሆኖም ግን በዚህ አዲስ አውሬና ቀደም ባለው አውሬ መካከል አንድ ዓይነት ዝምድና መኖር አለበት። በብዙ ሁኔታዎች መመሳሰላቸው እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም።

16. ቀዩ አውሬ ማን ነው? ዓላማውስ ምን እንደሆነ ተገልጾአል?

16 ታዲያ ይህ አውሬ ምንድን ነው? በግ የሚመስለው ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል እንዲቋቋም ያደረገው የአውሬው ምስል መሆን ይኖርበታል። የአውሬው ምስል ከተሠራ በኋላ ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተፈቅዶለታል። (ራእይ 13:14, 15) አሁን ዮሐንስ የተመለከተው ሕያው ሆኖ የሚተነፍሰውን ምስል ነው። ይህ አውሬ ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ በ1920 ወደ ሕይወት ያመጣውን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን ያመለክታል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የነበሩት ዊልሰን ማኅበሩ “ለሰዎች ሁሉ ሰላም የሚዳረስበትና የጦርነት ስጋት ለዘላለም ተጠርጎ የሚጠፋበት መድረክ እንደሚሆን” ተናግረው ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተብሎ ትንሣኤ ባገኘ ጊዜ በተቋቋመበት ቻርተር መሠረት የማኅበሩ ዓላማ “ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ” ነበር።

17. (ሀ) ምሳሌያዊው ቀይ አውሬ የስድብ ስሞች የሞሉበት የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) በቀዩ አውሬ ላይ ተቀምጣ የምትጋልበው ማን ነች? (ሐ) ባቢሎናዊው ሃይማኖት ከመጀመሪያው ጀምሮ ራሱን ከመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የእርሱ ተተኪ ከሆነው ድርጅት ጋር ያስተባበረው እንዴት ነው?

17 ይህ ምሳሌያዊ አውሬ የስድብ ስሞች የሞሉበት የሆነው በምን መንገድ ነው? ሰዎች ይህን ከብዙ ብሔራት የተውጣጣ ጣዖት የአምላክ መንግሥት ምትክ አድርገው ስለሚመለከቱትና አምላክ የእርሱ መንግሥት ብቻ እንደሚያከናውን የተናገረላቸውን ነገሮች ያከናውናል ብለው ስለሚያስቡ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 12:18, 21) ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ አስደናቂ የሆነበት ምክንያት ግን ታላቂቱ ባቢሎን በቀዩ አውሬ ላይ ስትጋልብ መታየትዋ ነው። ልክ በትንቢቱ እንደተገለጸው ባቢሎናዊ ሃይማኖቶች፣ በተለይም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶች ከመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የእርሱ ተተኪ ከሆነው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ራሳቸውን አዛምደዋል። ገና ከመጀመሪያው በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የክርስቶስ አቢያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ጉባኤ በመባል የሚታወቀው ድርጅት ታህሣሥ 18 ቀን 1918 በከፊል እንደሚከተለው የሚነበበውን መግለጫ አውጥቶ ነበር:- “እንዲህ ያለው ማኅበር ተራ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። እንዲያውም በምድር ላይ የአምላክ ፖለቲካዊ መንግሥት መግለጫ ነው። . . . ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጽናትና ሕልውና የግድ አስፈላጊ የሆነውን የበጎ ፈቃድ መንፈስ ልትሰጥ ትችላለች። . . . የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተመሠረተው በወንጌል ላይ ነው። የማኅበሩም ዓላማ ልክ እንደ ወንጌል ‘ሰላም በምድር፣ በጎ ፈቃድ ለሰዎች ሁሉ’ የሚል ነው።”

18. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን እንደሚደግፉ ያሳዩት እንዴት ነው?

18 ጥር 2 ቀን 1919 ሳንፍራንሲስኮ ክሮኒክል በመጀመሪያው ገጹ ላይ “ፓፓው የዊልሰንን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተቀባይነት እንዲያገኝ ይማጸናሉ” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። ጥቅምት 16 ቀን 1919 ከተለያዩ ታዋቂ የሃይማኖት ክፍሎች የተውጣጡ 14,450 ቀሳውስት ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት “የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን የሚያቋቁመውን የፓሪስ የሰላም ውል እዲያጸድቅ” የሚማጸን ማመልከቻ አቅርበው ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የፓሪሱን ውል ሳያጸድቀው ቢቀርም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ለማኅበሩ መከራከራቸውን አላቆሙም ነበር። የማኅበሩ መቋቋም የተበሰረው እንዴት ነበር? ህዳር 15 ቀን 1920 ከስዊዘርላንድ የተላለፈው ዜና እንዲህ ይነበባል:- “የመጀመሪያው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጠቅላላ ስብሰባ መከፈቱ የተበሰረው በጄኔቫ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የደወል ድምፅ ካሰሙ በኋላ ነበር።”

19. ቀዩ አውሬ በታየ ጊዜ የዮሐንስ ክፍል ምን አደረገ?

19 መጪውን መሲሐዊ መንግሥት ለመቀበል ብቸኛ የሆነው የዮሐንስ ክፍል ለቀዩ አውሬ በመስገድ ከሕዝበ ክርስትና ጋር ተባብሮአልን? በፍጹም አልተባበረም። መስከረም 7, 1919 እሁድ ዕለት በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው የይሖዋ ሕዝቦች ስብሰባ ላይ “ለተጨነቀው የሰው ዘር ተስፋ” የሚል የሕዝብ ንግግር ቀርቦ ነበር። በሚቀጥለው ቀን የሳንደስኪ ስታር ጆርናል እንደገለጸው ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 7,000 ለሚያክሉ ሰዎች ንግግር ሲያደርግ የሚከተለውን አረጋግጦአል። “የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የጌታ ቁጣ እንደሚጎበኘው የተረጋገጠ ነው። . . . ምክንያቱም የአምላክ ወኪሎች ነን የሚሉት የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ቀሳውስት የአምላክን ዕቅድ ትተው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን በምድር ላይ የክርስቶስ መንግሥት ፖለቲካዊ መግለጫ ነው ብለው ስለተቀበሉ ነው።”

20. ቀሳውስት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን “በምድር ላይ የአምላክ መንግሥት ፖለቲካዊ መግለጫ ነው” ማለታቸው ስድብ የሆነው ለምንድን ነው?

20 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በአሳዛኝ ሁኔታ መውደቁ ቀሳውስቱ ማንኛውም ሰው ሠራሽ ድርጅት የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ክፍል ሊሆን እንደማይችል ሊያስገነዝባቸው ይገባ ነበር። ይህን መናገር ብቻውን ትልቅ ስድብ ነው። የቃል ኪዳኑ ማኅበር ውትፍትፍ ተደርጐ ሲደራጅ አምላክም እንደተባበረ ያስመስላል። አምላክ ግን “ሥራው ሁሉ ፍጹም ነው።” ይሖዋ ሰላምን የሚያመጣውና በምድር ላይ ፈቃዱን የሚያስፈጽመው በክርስቶስ በምትተዳደረው ሰማያዊ መንግሥቱ ነው እንጂ በአብዛኛው አምላክ የለሾች የሆኑትና እርስ በርሳቸው በሚነታረኩ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ውህደት አይደለም።—ዘዳግም 32:4፤ ማቴዎስ 6:10

21. ታላቂቱ ጋለሞታ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተተኪ የሆነውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደምትደግፍና እንደምታደንቅ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለን?

21 በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እግር የተተካው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትስ? ይህ ማኅበር ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ ታላቋ ጋለሞታ ስትጋልብበት፣ ከእርሱም ጋር በይፋ ስትተባበርና አካሄዱንም ለመምራት ስትሞክር ታይታለች። ለምሳሌ ያህል የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት በሰኔ ወር 1965 ባከበረበት ጊዜ ሁለት ሺህ ሚልዩን የምድር ሕዝቦችን ይወክላሉ የተባሉ የሮማ ኮቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የፕሮቴስታንት፣ የአይሁድ፣ የቡድሂስትና የእስላም ሃይማኖት ተጠሪዎች በሳንፍራንሲስኮ ተሰብስበው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላቸውን ድጋፍና አድናቆት ገልጸዋል። ፓፓ ጳውሎስ 6ኛ በጥቅምት ወር 1965 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በጎበኙ ጊዜ “ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ የበለጠ ድርጅት” እንደሆነ ከገለጹ በኋላ “የምድር ሕዝቦች ሁሉ ለምድር ሰላምና ስምምነት ያመጣል ብለው ተስፋ የሚያደርጉት ይህንን ድርጅት ነው” ብለዋል። ሌላው ሊቀ ጳጳስ ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ደግሞ በጥቅምት ወር 1979 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በጎበኙበት ጊዜ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛው የሰላምና የፍትሕ መድረክ ሆኖ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። ሊቀ ጳጳሱ በንግግራቸው ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ለአምላክ መንግሥት እምብዛም ትኩረት አለመስጠታቸው ሊስተዋል የሚገባው ነው። በመስከረም ወር 1987 ዩናይትድ ስቴትስን በጎበኙበት ጊዜም ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጸው “ዮሐንስ ጳውሎስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ ዓለም አቀፍ ትብብር በማምጣት ረገድ ስለሚጫወተው ሚና በሰፊው ተናግረዋል።”

የምሥጢር ስም

22. (ሀ) ታላቂቱ ጋለሞታ የትኛውን አውሬ ለመጋለብ መርጣለች? (ለ) ዮሐንስ ምሳሌያዊት ጋለሞታ የሆነችውን ታላቂቱ ባቢሎን የገለጻት እንዴት ነው?

22 ሐዋርያው ዮሐንስ ብዙም ሳይቆይ ታላቂቱ ጋለሞታ ልትቀመጥበት የመረጠችው አውሬ በጣም አደገኛ መሆኑን ይገነዘባል። በመጀመሪያ ግን ትኩረቱ የተሳበው ወደ ታላቂቱ ባቢሎን ነው። ታላቂቱ ባቢሎን በብዙ ጌጦች የተንቆጠቆጠች ብትሆንም በጣም የሚያስጠላ መልክ ነበራት። “ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቆችም ተሸልማ ነበር፣ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ በግምባርዋም ምሥጢር የሆነ ስም:- ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተጻፈ። ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት።”—ራእይ 17:4-6ሀ

23. የታላቂቱ ባቢሎን ሙሉ ስም ማን ነው? ትርጉሙስ ምንድን ነው?

23 በጥንት ሮማውያን ልማድ መሠረት ይህች አመንዝራ የምትታወቀው በግንባርዋ ላይ ባለው ስም ነው። * ይህም ስም ረዘም ያለ ነው። “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር እርኩሰት እናት” የተባለ ስም ተሰጥቶአታል። ሥውር ትርጉም ያለው “የምሥጢር ስም” ነው። ይሁን እንጂ አምላክ በቀጠረው ቀን ምሥጢሩ ይገለጻል። እንዲያውም መልአኩ በዛሬው ዘመን የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህን ስም ሙሉ ትርጉም ለማስተዋል የሚያስችላቸውን በቂ መረጃ ለዮሐንስ ነግሮታል። ታላቂቱ ባቢሎን መላውን የሐሰት ሃይማኖት የምታመለክት እንደሆነች ተገንዝበናል። በዓለም ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ሃይማኖቶች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ኑፋቄዎች ጭምር እንደ ልጆችዋ ስለሆኑና መንፈሳዊ ግልሙትና በመፈጸም የእርስዋን መንገድ ስለሚከተሉ እንደ ልጆችዋ ናቸው። በዚህም ምክንያት “የጋለሞታዎች እናት” ናት። በተጨማሪም እንደ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስትነት፣ ጥንቆላ፣ ኮከብ ቆጠራ፣ የእጅ አሻራ ማንበብ፣ ሰዎችን መሠዋት፣ የቤተ መቅደስ ግልሙትና፣ ለሐሰት አማልክት ክብር ሲባል መስከርና እነዚህን የመሰሉትን ሌሎች አስነዋሪ ልማዶች ስለወለደች የእርኩሰት ሁሉ እናት ናት።

24. ታላቂቱ ባቢሎን “ሐምራዊና ቀይ ልብስ” ተጎናጽፋ “ወርቅ፣ ዕንቁና የከበረ ድንጋይ” አጊጣ መታየትዋ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

24 ታላቂቱ ባቢሎን “ሐምራዊና ቀይ” ልብስ ለብሳለች። እነዚህ የንጉሣዊ ልብስ ቀለሞች ናቸው። በተጨማሪም “በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁ” አጊጣለች። ይህም ትክክለኛ መግለጫ ነው። የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች ያከማቹአቸውን የተዋቡ ሕንፃዎች፣ ብርቅ ሐውልቶችና ሥዕሎች፣ ውድ ምስሎችና ሌሎች ሃይማኖታዊ የጌጥ ዕቃዎች መመልከት ብቻውን ይበቃል። ታላቂቱ ባቢሎን በቫቲካን ከተማም ሆነ ዩናይትድ ስቴትስን ማዕከሉ ባደረገው የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ዓለም፣ ወይም በሩቅ ምሥራቅ ቤተ መቅደሶችና ቤተ ጸሎቶች አልፎ አልፎ የከሰረችበት ጊዜ ቢኖርም መጠኑ በጣም የበዛ ሀብት አከማችታለች።

25. (ሀ) አስጸያፊ ነገር የሞላበት የወርቅ ጽዋ የምን ምሳሌ ነው? (ለ) ምሳሌያዊቱ ጋለሞታ ሰክራ የነበረው በምን መንገድ ነው?

25 አሁን ደግሞ ጋለሞታዋ በእጅዋ የያዘችውን እንመልከት። ዮሐንስ ይህን ሲመለከት በድንጋጤ አፉን ሳይከፍት አይቀርም። “በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ” ይዛ ነበር። ይህ ጽዋ አሕዛብን ሁሉ ያሰከረችበትን ‘የዝሙትዋን የወይን ጠጅ’ የያዘ ነበር። (ራእይ 14:8፤ 17:4) ጽዋው ከውጩ ያማረና ውድ ይመስላል፣ በውስጡ የያዘው ግን የሚያስጸይፍና እርኩስ ነገር ነው። (ከማቴዎስ 23:25, 26 ጋር አወዳድር።) ታላቋ ጋለሞታ ብሔራትን ለማሳትና በቁጥጥርዋ ሥር ለማስገባት የተጠቀመችባቸውን ውሸቶችና የቆሸሹ ድርጊቶች በሙሉ ይዞአል። ከዚህ በላይ የሚዘገንነውና የሚያስጸይፈው ደግሞ ጋለሞታይቱ ራስዋ በአምላክ አገልጋዮች ደም ሰክራ መታየትዋ ነው። እንዲያውም ወደፊት እንደምናነበው “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም” ተገኝቶባታል። (ራእይ 18:24) በጣም ከባድ የሆነ የደም ዕዳ አለባት።

26. ታላቂቱ ባቢሎን የደም ዕዳ እንዳለባት የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

26 ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ብዙ የደም ጎርፍ አፍስሳለች። ለምሳሌ ያህል “የቡድሃን ቅዱስ ስም” የሚጠሩ ጦረኛ መነኮሳት በመካከለኛው ዘመን በጃፓን አገር በኪዮቶ የሚገኙ ቤተ መቅደሶችን የጦርነት ምሽጎች በማድረግ እርስ በርሳቸው ተገዳድለዋል። በጣም ብዙ ደም በመፍሰሱ ምክንያት መንገዶች ቀለማቸው ተለውጦ ቀይ ሆነው ነበር። በ20ኛው መቶ ዘመን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ከየአገሮቻቸው ጦር ሠራዊቶች ጋር ተሰልፈው እርስ በርስ ተራርደዋል። በዚህም ምክንያት እጅግ ቢያንስ አንድ መቶ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎቸ ሞተዋል። በጥቅምት ወር 1987 የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ኒክሰን እንዲህ ብለው ነበር:- “በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከፍተኛ ደም የፈሰሰው በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ነው። ይህ መቶ ዘመን ከመጀመሩ በፊት በተደረጉት ጦርነቶች ከሞቱት ሰዎች ቁጥሩ በጣም ብዙ የሆነ ሕዝብ በዚህች መቶ ዘመን በተደረጉ ጦርነቶች ተገድለዋል።” የዓለም ሃይማኖቶች በዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ በመካፈላቸው አምላክ ይፈርድባቸዋል። ይሖዋ “ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆችን” ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) ከዚህ ቀደም ሲል ዮሐንስ ከመሠዊያው ሥር “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” የሚለውን ጩኸት ሰምቶ ነበር። (ራእይ 6:10) ይህ ጥያቄ የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ የጋለሞታዎችና የምድር እርኩሰት ሁሉ እናት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን የሚገባትን ብድራት ትቀበላለች።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ጆን ሄንሪ ኒውማን ስለ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች የተዘጋጀ ድርሰት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች፣ ክብረ በዓሎችና የአምልኮ ሥርዓቶች ከአረማውያን የመጡ መሆናቸውን ሲያመለክቱ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “በቤተ መቅደሶች ማገልገል፣ ቤተ መቅደሶችን በተለዩ ቅዱሳን ስም መሰየም፣ በዛፍ ቅርንጫፎች ማስጌጥ፣ ዕጣን ማጨስ፣ መብራቶችና ጧፎች ማብራት፣ ከበሽታ ሲዳን የስዕለት ቁርባን ማቅረብ፣ ጠበል፣ በዓላትና ዓውደ ዓመታት፣ የቀን መቁጠሪያዎች፣ እርሻዎችን መባረክ፣ የቅዱሳን ሥርዓተ ንግሥ፣ ልብሰ ተክህኖ፣ በጋብቻ ሥርዓት ቀለበት ማድረግ፣ ወደ ምሥራቅ መዞር፣ ከጊዜ በኋላም ሥዕልና ምስል፣ ምናልባትም የቅዳሴ መዝሙሮችና ኪርያላይሶን [ጌታ ሆይ፣ ማረን] የተባለው የምህላ ዝማሬ ከአረማውያን የመጡና ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ አድርጋ የተቀበለቻቸው ናቸው።”

“ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ” ግን እንዲህ ዓይነቱን የጣዖት አምልኮ ከመቀደስ ይልቅ ክርስቲያኖችን “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ . . . እርኩስንም አትንኩ” በማለት ይመክራል።—2 ቆሮንቶስ 6:14-18

^ አን.7 ዊልያም ኤል ሺረር የጻፉት የሦስተኛው ራይክ አነሳስና አወዳደቅ የተባለው የታሪክ መጽሐፍ ፎን ፓፔን “ለሂትለር ሥልጣን ላይ መውጣት ከማንኛውም ጀርመናዊ ግለሰብ ይበልጥ በኃላፊነት የሚጠየቅ ነው” ይላል። በጥር 1933 ፎን ሽላይሸር የተባሉት የቀድሞ የጀርመን ቻንስለር ስለ ፎን ፓፔን ሲናገሩ “በከሃዲነቱ ከይሁዳ አስቀሮቱ ጋር ቢወዳደር ይሁዳ አስቆሮቱ እንደ ቅዱስ ይቆጠራል” ብለዋል።

^ አን.7 ፓፓ ፓየስ 11ኛ ግንቦት 14 ቀን 1929 ለሞንድራጎን ኮሌጅ ንግግር ባደረጉበት ጊዜ “ለሰዎች ነፍሳት ጥቅም የሚያስገኝ ከሆነ ከዲያብሎስ ጋር እንኳን እደራደራለሁ” ብለዋል።

^ አን.23 ሴኔካ የተባለው የሮማ ደራሲ መልእክተኛው ለሆነች ሴት ካህን ከተናገራቸው ቃላት ጋር አወዳድር:- “አንቺ ሴት፣ ነውረኛ ድርጊት በሚፈጸምበት ቤት ውስጥ ተገኝተሻል። . . . ስምሽ ግንባርሽ ላይ ተንጠልጥሎ ነበር። ለእርኩስ ድርጊትሽ ገንዘብ ተቀበልሽ።” ኮንትሮቭ i2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 237 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቸርችል ‘ግልሙትናን’ አጋለጡ

ዊንስተን ቸርችል ዘ ጋዘሪንግ ስቶርም (በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው ማዕበል) (1948) በተባለው መጽሐፋቸው ሂትለር “በኦስትሪያ ፖለቲካ ውስጥ የአመራር ቦታ የነበራቸውን ሰዎች ለመበከል ወይም ወደራሱ ለመሳብ” ሲል ፎን ፓፔንን በቪየና የጀርመን ሚኒስቴር አድርጎ እንደሾመው ጽፈዋል። በቪየና የዩናይትድ ስቴትስ ሚኒስቴር የነበረ ሰው ስለ ፎን ፓፔን ሲናገር “ፓፔን ድፍረትና አስመሳይነት በተሞላ ሁኔታ . . . ጥሩ ካቶሊክ በመሆን ያተረፈውን መልካም ስም እንደ ካርዲናል ኢኒትዘር ባሉት ኦስትሪያውያን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እጠቀምበታለሁ ብሎ ነግሮኛል” ብለው ቸርችል ገልጸዋል።

ኦስትሪያ እጅዋን ከሰጠችና የሂትለር ሠራዊት ሰተት ብሎ ወደ ቪየና ከገባ በኋላ የካቶሊክ ካርዲናል ኢኒትዘር የኦስትሪያ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የስዋስቲካ ባንዲራ እንዲያውለበልቡ፣ ደውላቸውን እንዲደውሉና የአዶልፍ ሂትለርን የልደት በዓል ለማክበር ጸሎት እንዲያደርጉለት አዘዙ።

[በገጽ 238 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ ከላይ ባለው ርዕስ ሥር በታህሣሥ 7, 1941 የኒው ዮርክ ታይምስ የመጀመሪያ እትም ላይ ወጥቶ ነበር:-

ለራይኩ የተደረገ ‘የጦርነት ቡራኬ’

“በፉልዳ የካቶሊክ አቡኖች በረከትና ድል እንዲገኝ ለመኑ . . .

የጀርመን ካቶሊክ አቡኖች በፉልዳ ባደረጉት ስብሰባ በሁሉም መለኮታዊ ቅዳሴዎች መጀመሪያና መጨረሻ ላይ የሚነበብ ልዩ ‘የጦርነት ቡራኬ’ እንዳወጡ አስታወቁ። ቡራኬው አምላክ የጀርመንን የጦር ሠራዊት በመባረክ ድል እንዲሰጣቸውና የሁሉንም ወታደሮች ሕይወትና ጤንነት እንዲጠብቅ የተደረገ ልመና ነው። በተጨማሪም የካቶሊክ ቀሳውስት ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በልዩ የሰንበት ስብከት ላይ ‘በምድር፣ በባሕርና በአየር’ ያሉ የጀርመን ወታደሮችን እንዲያስቡ አቡኖች አዘዋል።”

[በገጽ 244 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የስድብ ስሞች”

ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እንዲቋቋም ባደረገ ጊዜ ብዙዎቹ ሃይማኖታዊ ወዳጆቹ ለዚህ ድርጊቱ ሃይማኖታዊ ድጋፍ ለመስጠት ፈልገው ነበር። በዚህም ምክንያት አዲሱ የሰላም ድርጅት “የስድብ ስሞች የሞሉበት” ሆነ።

“ክርስትና የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን በጎ ፈቃድ ሊያስገኝለት ይችላል። ይህም ሲሆን ስምምነቱ ተራ ብጣሽ ወረቀት ከመሆን አልፎ የአምላክ መንግሥት መሣሪያ ይሆናል።”ዘ ክርስቲያን ሴንቸሪ፣ ዩ ኤስ ኤ ሰኔ 19, 1919፣ ገጽ 15

“የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተቋቋመበት ዓላማ የአምላክ መንግሥት ለሚያመጣው የበጎ ፈቃድ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ተቀጽላ ነው። . . . ክርስቲያኖች ሁሉ ‘መንግሥትህ ትምጣ’ ብለው የሚጸልዩት ለዚህ ሥርዓት ነው።”—ዘ ክርስቲያን ሴንቸሪ፣ ዩ ኤስ ኤ መስከረም 25, 1919፣ ገጽ 7

“የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን የሚያስተሳስረው ማጣበቂያ የክርስቶስ ደም ነው።”—ዶክተር ፍራንክ ክሬን፣ የፕሮቴስታንት ቄስ ዩ ኤስ ኤ

“የኮንግርጌሽናል አብያተ ክርስቲያናት [ብሔራዊ] ጉባኤ [የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን] ቃል ኪዳን ይደግፋል። በአሁኑ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ የአሕዛብን ጉዳዮች ለመቆጣጠር ሰፊ ድርሻ የሚያገኝበት የፖለቲካ መሣሪያ ይህ ድርጅት ብቻ ነው።”—ዘ ኮንግሪጌሽናሊስት ኤንድ አድቫንስ፣ ዩ ኤስ ኤ ህዳር 6, 1919፣ ገጽ 642

“ጉባኤው የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አባሎች በሙሉ በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አማካኝነት የተገለጸውን የእግዚአብሔር አብንና የአምላክን ምድራዊ ልጆች ፈቃድ በከፍተኛ ደረጃ እንዲደግፉና እንዲያራምዱ ይጠይቃል።”—ዘ ዌስልያን ሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን፣ ብሪታንያ

“የዚህን ስምምነት ምኞት፣ አቅምና ቁርጥ ውሳኔ ስንመረምር የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ዋነኛ ሐሳብ እንደያዘ እንገነዘባለን። እርሱም የአምላክ መንግሥትና ጽድቁ ነው። . . . ከዚህ ያነሰ ግምት ሊሰጠው አይችልም።”—የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጠቅላላ ስብሰባ በጄኔቭ ከተማ በተከፈተበት ጊዜ የተናገሩት ቃለ ቡራኬ፣ ታህሳስ 3 ቀን 1922

“በዚህ አገር የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ከማንኛውም የሰው ልጅ ሚስዮናዊ ማህበር የማይተናነስ ቅዱስ መብት አለው። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የሰላም መስፍን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በብሔራት መካከል ለመግዛት የሚጠቀምበት ድርጅት ይህ ብቻ ነው።”—ዶክተር ጋርቪ፣ ኮንግሪጌሽናሊስት ቄስ፣ ብሪታንያ

[በገጽ 236 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በመላው ዓለም የሚታመንባቸው የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች በሙሉ ከባቢሎን የመነጩ ናቸው

ባቢሎን

ሥላሴዎች ወይም የሦስት አማልክት እምነት

የሰው ነፍስ ከሞት በኋላ በሕይወት ትኖራለች

መናፍስትነት፣ “ከሙታን” ጋር መነጋገር

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም

አጋንንትን ለመለማመን በድግምት መጠቀም

ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ቀሳውስት መገዛት

[በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንትዋ ባቢሎን በብዙ ውኃዎች ላይ ተቀምጣ ነበር

[በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬም ታላቂቱ ጋለሞታ “በብዙ ውኃዎች” ላይ ተቀምጣለች

[በገጽ 241 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቂቱ ባቢሎን አደገኛ በሆነ አውሬ ላይ ተቀምጣለች

[በገጽ 242 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሃይማኖታዊቷ ጋለሞታ ከምድር ነገሥታት ጋር አመንዝራለች

[በገጽ 245 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሴቲቱ “በቅዱሳን ደም ሰክራለች”