በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስምህ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛልን?

ስምህ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛልን?

ምዕራፍ 11

ስምህ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛልን?

ሰርዴስ

1. በሰርዴስ የነበረው ጉባኤ እንዴት ባለ መንፈሳዊ ሁኔታ ይገኝ ነበር? ኢየሱስስ መልእክቱን የጀመረው እንዴት ነው?

ታላቅ ክብር ከተቀዳጀው ኢየሱስ የተላከውን መልእክት የሚቀበለው ተከታይ ጉባኤ ከዘመናዊቷ አክሂሳር (ትያጥሮን) በስተደቡብ 48 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የሰርዴስ ከተማ የሚገኘው ጉባኤ ነው። ይህች ከተማ በስድስተኛው መቶ ዘመን የጥንቱ የልዳ መንግሥት ዝነኛ ዋና ከተማና በጣም ባለጠጋ የነበረው የንጉሥ ክሮሰስ መቀመጫ ነበረች። በዮሐንስ ዘመን ግን በችግር ላይ ወድቃ ስለነበር በክሮሰስ ዘመን የነበራት የቀድሞ ክብርዋ ሁሉ ጠፍቶ በታሪክ ብቻ የሚዘከር ሆኖአል። በዚያ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤም በመንፈሳዊ ደህይቶ ነበር። ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ መልእክቱን በምሥጋና ቃላት ሳይከፍት ቀርቶአል። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አላቸው:- “በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል:- ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል።”—ራእይ 3:1

2. (ሀ) ኢየሱስ ‘ሰባቱ መናፍስት’ ያሉት መሆኑ በሰርዴስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን የተለየ ትርጉም ነበረው? (ለ) የሰርዴስ ጉባኤ ምን ዓይነት ስም ነበረው? ይሁን እንጂ እውነተኛው ሁኔታ እንዴት ያለ ነበር?

2 ኢየሱስ ራሱን ሲያስተዋውቅ ‘ሰባቱ መናፍስት’ እንዳሉት የተናገረው ለምን ነበር? ይህ መንፈስ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በምልአት መፍሰሱን ስለሚያመለክት ነው። በሌላ ጊዜም ዮሐንስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለኢየሱስ የሰጠውን ጠልቆ የማየት ችሎታ ሲያመለክት በ“ሰባት ዓይኖች” መስሎታል። (ራእይ 5:6) ስለዚህ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢኖር ይፋ ሊያወጣውና ሊያስተካክለው ይችላል ማለት ነው። (ማቴዎስ 10:26፤ 1 ቆሮንቶስ 4:5) የሰርዴስ ጉባኤ ሕያው እንደሆነና ጥሩ ይንቀሳቀሳል የሚል ስም አለው። ኢየሱስ ግን በመንፈሳዊ በድን መሆኑን ሊገነዘብ ችሎአል። ከአባሎቹ መካከል ብዙዎቹ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ወደነበራቸው ቀዝቃዛ ስሜት እንደተመለሱ ግልጽ ነበር።—ከ⁠ኤፌሶን 2:1-3ና ከ⁠ዕብራውያን 5:11-14 ጋር አወዳድር።

3. (ሀ) ‘የሰርዴስ ጉባኤ መልአክ’ ኢየሱስ “ሰባቱ ከዋክብት” ያሉት መሆኑን በጥሞና መገንዘብ የነበረበት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በሰርዴስ ለነበረው ጉባኤ ምን ጠንካራ ምክር ሰጥቶአል?

3 በተጨማሪም ኢየሱስ ‘የሰርዴስን ጉባኤ መልአክ’ “ሰባቱ ከዋክብት” ያሉት መሆኑን አስገንዝቦታል። እነዚህን የጉባኤ ሽማግሌዎች በቀኝ እጁ ውስጥ ስለያዛቸው በእረኝነት ሥራቸው ሊመራቸውና ሊቆጣጠራቸው ሥልጣን አለው ማለት ነው። የመንጋውን መልክ ለማወቅ ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 27:23) ስለዚህ የሚቀጥለውን የኢየሱስ ቃል ልብ ብለው ቢያዳምጡ ይበጃቸዋል። “ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፣ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና፣ እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፣ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።”—ራእይ 3:2, 3

4. ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት የሰርዴስ ጉባኤ ‘የቀሩትን ነገሮች እንዲያጸና’ የሚረዳው እንዴት ነው?

4 በሰርዴስ የነበሩት ሽማግሌዎች መጀመሪያ እውነትን ባወቁበት ጊዜ የተሰማቸውን ደስታና በዚያ ጊዜ ያገኙትን በረከት ማሰብ ያስፈልጋቸው ነበር። አሁን ግን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ረገድ ሙታን ሆነዋል። የጉባኤ መብራታቸው የእምነት ሥራ ስለጎደለው ብልጭ እልም ይል ነበር። ከዓመታት በፊት ሐዋርያው ጴጥሮስ በእሥያ ለነበሩት ጉባኤዎች (ሰርዴስንም ሳይጨምር አይቀርም) ክርስቲያኖች ለተቀበሉት (በዮሐንስ ራእይ ውስጥ በሰባት መናፍስት በተመሰለው) ‘ከሰማይ የተላከ መንፈስ ቅዱስ’ ለታወጀው ታላቅ የምሥራች ያላቸውን አድናቆት እንዲያሳድጉ መክሮ ነበር። በተጨማሪም ጴጥሮስ እነዚህ የእስያ ክርስቲያኖች ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የጠራቸውን የእርሱን በጎነት እንዲነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን’ እንዲሆኑ አሳስቦአቸው ነበር። (1 ጴጥሮስ 1:12, 25፤ 2:9) የሰርዴስ ጉባኤ በእነዚህ መንፈሳዊ እውነቶች ላይ ቢያሰላስል ንስሐ ሊገባና “የቀሩትን ነገሮች” ሊያጸና ይችላል።—ከ⁠2 ጴጥሮስ 3:9 ጋር አወዳድር።

5. (ሀ) በሰርዴስ የነበሩት ክርስቲያኖች የአድናቆት ስሜት ምን ሆኖ ነበር? (ለ) የሰርዴስ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምክር ካልተቀበሉ ምን ይደርስባቸዋል?

5 በወቅቱ ለእውነት ያላቸው ፍቅርና አድናቆት ሊጠፋ እንደተቃረበ እሳት ሆኖ ነበር። ጥቂት ፍሞች ብቻ ቀርተው ነበር። ኢየሱስ ቸልተኝነታቸው ካስከተለባቸው ኃጢአት ንስሐ በመግባትና እንደገና መንፈሳዊ ሕይወት ያለው ጉባኤ በመሆን እነዚህን የቀሩትን ፍሞች እንዲቆሰቁሱና እንዲያራግቡ አበረታታቸው። (ከ⁠2 ጢሞቴዎስ 1:6, 7 ጋር አወዳድር።) አለዚያ ግን ኢየሱስ ፍርድ ለመስጠት ባልተጠበቀ ሁኔታ “እንደ ሌባ” በሚመጣበት ጊዜ በሰርዴስ የነበረው ጉባኤ ዝግጁ ሆኖ አይገኝም።—ማቴዎስ 24:43, 44

“እንደ ሌባ” ሆኖ መምጣት

6. ኢየሱስ በ1918 “እንደ ሌባ” በድንገት የመጣው እንዴት ነው? ተከታዮቹ ነን ይሉ በነበሩ ሰዎች መካከል እንዴት ያለ ሁኔታ አገኘ?

6 ኢየሱስ “እንደ ሌባ” እንደሚመጣ የሰጠው ማስጠንቀቂያ አስፈላጊነት እስከ ዘመናችን ድረስ ቆይቶአል። በተለይ በጌታ ቀን ውስጥ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም ነበረው። ከ1914 ብዙም ሳይቆይ የሚከተለው የሚልክያስ ትንቢት ተፈጸመ። “እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፣ የምትወድዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ እነሆ ይመጣል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” (ሚልክያስ 3:1፤ ራእይ 1:10) ኢየሱስ ‘የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ’ እንደመሆኑ መጠን ተከታዮቹ ነን የሚሉትን ሊቆጣጠርና ሊፈርድ መጣ። (1 ጴጥሮስ 4:17) በ1918 ሕዝበ ክርስትና በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ደም በማፋሰስ ተግባር ሙሉ በሙሉ ተውጣ ስለነበረ በመንፈሳዊ አነጋገር ፈጽሞ በድን ሆና ነበር። ከጦርነቱ በፊት በቅንዓት ይሰብኩ የነበሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች እንኳን መንፈሳዊ ሰመመን ይዞአቸው ነበር። ከግንባር ቀደም ሽማግሌዎቻቸው አንዳንዶቹ በእስር ላይ ይገኙ ስለነበረ የስብከቱ ሥራ ቆሞ ነበር። በሚቀጥለው ዓመት የይሖዋ መንፈስ እነዚህን ክርስቲያኖች ቀስቅሶ ባስነሳቸው ጊዜ ዝግጁ ሆነው የተነሱት ሁሉም ክርስቲያኖች አልነበሩም። አንዳንዶቹ በኢየሱስ ምሳሌ እንደተጠቀሱት ሞኝ ቆነጃጅት ይሖዋን የማገልገልን መብት ለመቀበል መንፈሳዊ ዝግጅት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ እንደ ልባሞቹ ቆነጃጅት “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ጠብቀው የተገኙ ብዙ ክርስቲያኖች ነበሩ።—ማቴዎስ 25:1-13

7. ዛሬ ክርስቲያኖች ነቅተው መጠባበቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

7 ለማንኛውም ክርስቲያን ንቁ ሆኖ የመጠበቅ አስፈላጊነት በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ አላበቃም። ኢየሱስ “ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድን ነው” በማለት ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ በተናገረው ታላቅ ትንቢት የሚከተለውን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል። “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት . . . የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንደሆነ አታውቁምና ተጠንቀቁ፣ ትጉ፣ ጸልዩም። ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፣ ትጉ።” (ማርቆስ 13:4, 32, 33, 37) አዎ፣ ሁላችንም ከቅቡዓን ክፍልም ሆንን ከእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል እስከዚያች ሰዓት ድረስ ንቁዎች ሆነን ለመኖርና መንፈሳዊ እንቅልፍ እንዳያሸልበን ለመከላከል ነቅተን መጠባበቅ ይኖርብናል። የይሖዋ ቀን ‘እንደ ሌባ በሌሊት ሲመጣ’ ጥሩ ፍርድ እንዲፈረድልን ነቅተን እንጠባበቅ።—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3፤ ሉቃስ 21:34-36፤ ራእይ 7:9

8. በዘመናችን የዮሐንስ ክፍል የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው እንዲኖሩ የቀሰቀሰው እንዴት ነው?

8 በዛሬው ዘመን ያለው የዮሐንስ ክፍል የአምላክ ሕዝቦችን በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው እንዲጠባበቁ መቀስቀስ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦአል። ለዚህም ሲባል በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ብዙ ታላላቅ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። በቅርብ ዓመት በተደረጉት 2,981 የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በጠቅላላው 10,953,744 ሰዎች ሲገኙ 122,701 አዳዲስ አማኞች ተጠምቀዋል። የዮሐንስ ክፍል ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት የይሖዋን ስምና ዓላማ ለማወጅ ሲጠቀምበት ቆይቶአል። በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ዓመታት ከባድ ስደት በተነሳ ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ ላይ “ደፋሮች የተባረኩ ናቸው” (1919)፣ “ለሥራ የመነሳት ጥሪ” (1925)፣ “የስደት መሸነፍ” (1942) እንደሚሉት ያሉትን ርዕሰ ትምህርቶች በማውጣት የይሖዋ ምሥክሮችን ቅንዓት በአዲስ ሁኔታ አነሳስተዋል።

9. (ሀ) ክርስቲያኖች ሁሉ ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል? (ለ) መጠበቂያ ግንብ እንዴት ያለ ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር?

9 በዛሬዎቹ ጉባኤዎች የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ በሰርዴስ ጉባኤ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ራሳቸውን መመርመር ያስፈልጋቸዋል። ሁላችንም ራሳችንን ‘ሥራዬ በአምላክ ዘንድ ፍጹም ሆኖ ይገኛልን?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በሌሎች ላይ ሳንፈርድ በየግላችን ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እየኮተኮትን አምላክን በሙሉ ነፍሳችን ለማገልገል እንጥራለንን? በዚህም ረገድ መጠበቂያ ግንብ “ራሳችሁን ፈትኑ” እና “ከእንግዲህ ለራሳችን አንኖርም” እንደሚሉት ያሉትን ትምህርቶች በማውጣት ማበረታቻ ሰጥቶአል። * እንደነዚህ ባሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታዎች በመጠቀም በይሖዋ ፊት ፍጹም አቋማችንን ጠብቀን በትህትናና በጸሎተኝነት መንፈስ ለመመላለስ በምንጥርበት ጊዜ ውስጣዊ ልቦናችንን ዘወትር እንመርምር።—መዝሙር 26:1-3፤ 139:23, 24

“ጥቂት ስሞች”

10. ኢየሱስ በሰርዴስ ጉባኤ ውስጥ ምን አበረታች ሁኔታ ተመልክቶ ነበር? ይህስ እኛን እንዴት ሊነካን ይገባል?

10 ኢየሱስ ቀጥሎ ለሰርዴስ ጉባኤ የተናገረው ቃል በጣም የሚያበረታታ ነው። እንዲህ አለ:- “ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ስሞች ከአንተ ጋር አሉ፣ የተገባቸውም ስለሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል፣ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፣ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።” (ራእይ 3:4, 5) እነዚህ ቃላት የሚያነቃቁንና በታማኝነት ለመጽናት ያደረግነውን ውሣኔ የሚያጠነክሩልን አይደሉምን? አንድ ጉባኤ በአጠቃላይ በሽማግሌዎቹ አካል ቸልተኝነት ምክንያት ከባድ መንፈሳዊ እንቅልፍ ሊወስደው ይችላል። ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ክርስቲያናዊ መለያቸው እንዳይቆሽሽባቸውና እንዳይበላሽባቸው በድፍረት ጥረት እያደረጉ በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም እንዲኖራቸው ለማድረግ ይችላሉ።—ምሳሌ 22:1

11, 12. (ሀ) በታላቁ የክህደት ዘመን እንኳን አንዳንድ ታማኝ ሰዎች በሰርዴስ እንደነበሩት ታማኝ “ጥቂት ስሞች” የሆኑት እንዴት ነበር? (ለ) በስንዴ የተመሰሉት ክርስቲያኖች በጌታ ቀን እንዴት ያለ እፎይታ አገኙ?

11 አዎ፣ “ልብሳቸው” አንድ ሰው ያለውን የክርስቲያንነት የጽድቅ አቋም ያመለክታል። (ከ⁠ራእይ 16:15⁠ና ከራእይ 19:8 ጋር አወዳድር።) አብዛኞቹ ቸልተኞች ቢሆኑም “ጥቂት ስሞች”፣ ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰርዴስ ጉባኤ የክርስትና መለያቸውን ጠብቀው ለመኖር መቻላቸው ኢየሱስን በጣም ሳያስደስተው አልቀረም። በተመሳሳይም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን በተዋጡበት የብዙ መቶ ዓመታት የክህደት ዘመን ያጋጠማቸውን ከባድ ችግር ሁሉ ተቋቁመው የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ይጣጣሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ሳይኖሩ አልቀረም። እነዚህ ሰዎች በመናፍቅነት አረም ውስጥ ተሰውሮ እንደሚኖር ስንዴ ጻድቃን ነበሩ።—ራእይ 17:3-6፤ ማቴዎስ 13:24-29

12 ኢየሱስ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” ከእነዚህ ስንዴ መሰል ክርስቲያኖች ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር። እርሱ ማንነታቸውንና ለራሳቸው እንዴት ያለ ስም እንዳበጁ ያውቃል። (ማቴዎስ 28:20፤ መክብብ 7:1) የጌታ ቀን በጀመረበት ጊዜ በሕይወት ይኖሩ የነበሩት “ጥቂት” ታማኞች እንዴት ያለ ደስታ እንደተሰማቸው መገመት ይቻላል። በመጨረሻው በመንፈሳዊ በድን ከነበረችው ሕዝበ ክርስትና ተለይተው እንደ ሰምርኔስ ጉባኤ ወዳለው ጻድቅ ጉባኤ ተሰብስበው ነበር።—ማቴዎስ 13:40-43

13. ‘መጎናጸፊያቸውን ያላረከሱ’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት በረከት ተዘጋጅቶላቸዋል?

13 እስከ መጨረሻው ጸንተው የተገኙትና ክርስቲያናዊ መታወቂያቸውን ያልጣሉት የሰርዴስ ክርስቲያኖች አስደናቂ ተስፋ መጨበጣቸው ይረጋገጣል። የኢየሱስ መሲሐዊት መንግሥት በ1914 ከተቋቋመች በኋላ መንፈሳዊ ሕይወት አግኝተው ከሙታን ተነስተዋል። ድል አድራጊዎች በመሆናቸውም ጉድለትና እንከን ለሌለበት የጽድቅ አቋማቸው ምሳሌ የሚሆን ነጭ መጎናጸፊያ ለብሰዋል። ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ ሲመላለሱ ስለቆዩ ዘላለማዊ ሽልማት ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 7:14፤ በተጨማሪም ራእይ 6:9-11 ተመልከት።

በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ለዘላለም መቆየት

14. “የሕይወት መጽሐፍ” ምንድን ነው? በዚያስ የተጻፉት የእነማን ስሞች ናቸው?

14 “የሕይወት መጽሐፍ” ምንድን ነው? በዚህስ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የሚኖረው የእነማን ስም ነው? የሕይወት መጽሐፍ ወይም ጥቅልል የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት የተገባቸው ሆነው የተገኙ ሰዎች የሚጻፉበት የይሖዋ አገልጋዮች መዝገብ ነው። (ሚልክያስ 3:16) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ስም በተለየ ሁኔታ ተጠቅሶአል። ይሁን እንጂ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሰዎችም ስም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይመዘገባል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ስሞች ከዚህ መዝገብ ሊሰረዙ ይችላሉ። (ዘጸአት 32:32, 33) ሆኖም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚቆዩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች በሰማይ ሞት የማይደፍረው የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ራእይ 2:10) ኢየሱስ በአባቱና በመላእክቱ ፊት የሚመሰክርላቸው ስሞች እነዚህ ናቸው። ይህ የታማኝነታቸው ዋጋ እንዴት ያለ አስደናቂ ሽልማት ይሆናል!

15. የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች ስሞቻቸውን በማይፋቅ ሁኔታ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚያስጽፉት እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቁን መከራ በሕይወት ይሻገራሉ። በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን በሙሉና ከዚያ በኋላ በሚመጣው ወሳኝ ፈተና እምነታቸውን ጠብቀው በመኖር በገነቲቱ ምድር የዘላለም ሕይወት የማግኘት ሽልማት ይቀበላሉ። (ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 7:9, 14፤ 20:15፤ 21:4) ከዚያ በኋላ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ ለዘላለም ይመዘገባል። የተዘጋጀው ሽልማት እንዴት ያለ እንደሆነ ካወቅህ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የቀረበውን የሚከተለውን የኢየሱስ ተደጋጋሚ ጥሪ ለመቀበል በግለት አትነሳሳምን? “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።”ራእይ 3:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 የሐምሌ 15, 2005 እና የመጋቢት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ እትሞችን ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 57 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስምህ ከሕይወት መጽሐፍ አይፋቅ