በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው የይሖዋ መቅሠፍት

በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው የይሖዋ መቅሠፍት

ምዕራፍ 21

በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው የይሖዋ መቅሠፍት

ራእይ 5--ራእይ 8:1 እስከ 9:21

ርዕሰ ጉዳይ:- ከሰባቱ መለከቶች የስድስቱ መነፋት

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ክርስቶስ ኢየሱስ በ1914 ዙፋን ላይ ከተቀመጠ ጀምሮ እስከ ታላቁ መከራ ድረስ

1. በጉ ሰባተኛውን ማኅተም ሲፈታ ምን ሆነ?

“አራቱ ነፋሳት” 144,000ዎቹ የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች እስኪታተሙና እጅግ ብዙ ሰዎች ለመዳን የሚበቁ መሆናቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ተገተው ነበር። (ራእይ 7:1-4, 9) ይሁን እንጂ የጥፋቱ ማዕበል በምድር ላይ ከመፈንዳቱ በፊት ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ላይ የሚያመጣው ፍርድ ለሰዎች ሁሉ መነገር አለበት። በጉ ሰባተኛውንና የመጨረሻውን ማኅተም በፈታ ጊዜ የሚገለጠውን ነገር ለማየት ዮሐንስ በጣም ሳይጓጓ አልቀረም። የተመለከተውን ነገር ለእኛም ይነግረናል:- “ሰባተኛውንም ማኅተም [በጉ] በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፣ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው።”—ራእይ 8:1, 2

ሞቅ ያለ ጸሎት የሚቀርብበት ጊዜ

2. በሰማይ የግማሽ ሰዓት ዝምታ በሆነ ጊዜ ምን ነገር ተፈጸመ?

2 ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ፍጹም ጸጥታ ነበር። አንድ እንደሚፈፀም የምትጠባበቁት ነገር ካለ ግማሽ ሰዓት በጣም ረዥም ጊዜ መስሎ ሊታይ ይችላል። በዚህ ጊዜ ያለማቋረጥ ይሰማ የነበረው ሰማያዊው የውዳሴ መዝሙር እንኳን አይሰማም ነበር። (ራእይ 4:8) ለምን እንዲህ ሆነ? ዮሐንስ ምክንያቱን በራእይ ተመልክቶ ነበር። “ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።”—ራእይ 8:3, 4

3. (ሀ) የዕጣን መጨስ ምን ነገር ያስታውሰናል? (ለ) በሰማይ የግማሽ ሰዓት ዝምታ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

3 ይህም በአይሁዳውያን ሥርዓት ዕጣን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ በኋላም በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይጨስ እንደነበረ ያስታውሰናል። (ዘጸአት 30:1-8) በዚህ ዕጣን በሚጨስበት ጊዜ ካህናት ያልሆኑ እስራኤላውያን ሁሉ የዕጣኑ ጢስ ለሚያርግለት አምላክ እየጸለዩ ከቅዱሱ ሥፍራ ውጭ ጸጥ ብለው ይቆሙ ነበር። (ሉቃስ 1:10) አሁን ደግሞ ዮሐንስ ይህን የሚመስል ነገር በሰማይ ሲከናወን ተመለከተ። መልአኩ ይዞት የነበረው ዕጣን “ከቅዱሳን ጸሎት” ጋር ግንኙነት እንዳለው ተገልጾአል። እንዲያውም ከዚህ ቀደም ባለው ራእይ ዕጣን እንዲህ ያለውን ጸሎት እንደሚያመለክት ተገልጾ ነበር። (ራእይ 5:8፤ መዝሙር 141:1, 2) ስለዚህ ምሳሌያዊው የሰማይ ዝምታ የተደረገው በምድር ላይ ያሉት ቅዱሳን የሚያቀርቡት ጸሎት እንዲሰማ ለማስቻል ነበር።

4, 5. ምሳሌያዊው የግማሽ ሰዓት ዝምታ የሆነበትን ጊዜ እንድናውቅ የሚረዳን የትኛው የታሪክ ክንውን ነው?

4 ይህ ዝምታ የሆነበትን ጊዜ ለማወቅ እንችላለንን? በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ከተፈጸሙት ታሪካዊ ክንውኖች ጋር በማነጻጸር ለማወቅ እንችላለን። (ራእይ 1:10) በ1918 እና በ1919 በምድር ላይ የተፈጸሙት ሁኔታዎች በ⁠ራእይ 8:1-4 ላይ ከተገለጹት ትዕይንቶች ጋር የሚስማሙ ነበሩ። ከ1914 በፊት በነበሩት 40 ዓመታት በዚያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የአሕዛብ ዘመናት በ1914 እንደሚፈጸሙ በድፍረት ሲያስታውቁ ቆይተው ነበር። ይህም ትክክል መሆኑ በ1914 በተፈጸሙት አስጨናቂ ሁኔታዎች ተረጋግጦአል። (ሉቃስ 21:24፤ ማቴዎስ 24:3, 7, 8) ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በ1914 ከዚህ ምድር ወደ ሰማያዊ ውርሻቸው የሚወሰዱ መስሎአቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ወደ ሰማይ አልተወሰዱም። ከዚህ ይልቅ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጣም ከባድ ስደት ደረሰባቸው። ጥቅምት 31 ቀን 1916 የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዚደንት ቻርልስ ቲ ራስል ሞተ። ሐምሌ 4 ቀን 1918 ደግሞ አዲሱ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድና ሌሎች ሰባት የማህበሩ ወኪሎች አግባብ ባልሆነ መንገድ የብዙ ዓመታት የእስራት ቅጣት ተፈርዶባቸው ወደ አትላንታ፣ ጆርጂያ ወህኒ ቤት ተወሰዱ።

5 ቅን የሆኑት የዮሐንስ ክፍል ክርስቲያኖች በሁኔታው ግራ ተጋብተው ነበር። አምላክ ከዚህ በኋላ ምን እንዲያደርጉ ይፈልግባቸው ነበር? ወደ ሰማይ የሚወሰዱት መቼ ነው? በግንቦት 1, 1919 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ “መከሩ ተፈጸመ፣ ከዚህ በኋላ ምን ይቀጥል ይሆን?” የሚል ርዕሰ ትምህርት ወጣ። ርዕሰ ትምህርቱ ተፈጥሮ የነበረውን ግራ መጋባት ከገለጸ በኋላ ታማኞች ሁሉ ጸንተው እንዲቆዩ ማበረታቻ ሰጣቸው። ቀጥሎም እንዲህ አለ:- “የመንግሥቱ ክፍል አባሎች መሰብሰብ ማብቃቱ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ እናምናለን። የመንግሥት ክፍል አባሎች በሙሉ ታትመው ስላለቁ በሩ ተዘግቶአል።” በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ የዮሐንስ ክፍል አባሎች ጸሎት እንደ ብዙ ዕጣን ጭስ ወደ ሰማይ ያርግ ነበር። ጸሎታቸውም ተደማጭነት እያገኘ ነበር።

እሳት ወደ ምድር ተጣለ

6. በሰማይ ዝምታ ከሆነ በኋላ ምን ተፈጸመ? ይህስ የተፈጸመው ለምን ነገር ምላሽ እንዲሆን ነው?

6 ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው ነጎድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።” (ራእይ 8:5) ከዝምታው በኋላ በድንገት ከፍተኛ ትርምስ ተፈጠረ። ትርምሱ የተቀጣጠለው ከዕጣኑ መሰዊያ በተወሰደ እሳት ስለሆነ ለቅዱሳኑ ጸሎት የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ ገልጽ ነው። በ1513 ከዘአበ ይሖዋ ትኩረቱን በምድር ላይ ወዳሉት አገልጋዮቹ ለመመለሱ ምልክት እንዲሆን በሲና ተራራ ላይ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ከፍተኛ ድምፅ፣ እሳትና የተራራ መንቀጥቀጥ ሆኖ ነበር። (ዘጸአት 19:16-20) ዮሐንስ የተመለከተው ተመሳሳይ መግለጫም ይሖዋ ትኩረቱን በምድር ላይ ወዳሉት አገልጋዮቹ ማዞሩን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ዮሐንስ የተመለከተው ነገር ሁሉ ምሳሌያዊ ነበር። (ራእይ 1:1) ስለዚህ ምሳሌያዊው እሳት፣ ነጎድጓድ፣ ድምፅ፣ መብረቅና የምድር መናወጥ በዘመናችን ምን ትርጉም ይኖረዋል?

7. (ሀ) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት የትኛውን ምሳሌያዊ እሳት በምድር ላይ አቀጣጥሎ ነበር? (ለ) የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እሳት ያቀጣጠሉት እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ “በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 12:49) በእውነትም እሳት አቀጣጥሎ ነበር። ኢየሱስ በቅንዓት በመስበክ በአይሁድ ሕዝብ ፊት የተደቀነው ዋነኛ ጥያቄ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ነበር። ይህ ስብከቱ በአይሁድ ሕዝብ በሙሉ የተፋፋመ ክርክር አስነስቶ ነበር። (ማቴዎስ 4:17, 25፤ 10:5-7, 17, 18) በ1919 በምድር ላይ የነበሩት የኢየሱስ ወንድሞች፣ ፈታኝ ከሆኑት ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ዓመታት ያለፉት ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተመሳሳይ እሳት አቀጣጥለው ነበር። በዚያው ዓመት በመስከረም ወር በሩቅና በቅርብ የነበሩ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩ.ኤስ.ኤ በተሰበሰቡ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ይመራቸው እንደነበረ በግልጽ ይታይ ነበር። በቅርቡ ከወህኒ ቤት ወጥቶ የነበረውና ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተመሠረቱበት ክሶች በሙሉ ሲነሱለት ለማየት የበቃው ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በዚህ ስብሰባ ላይ የሚከተለውን ንግግር አደረገ:- “ለጌታችን ትዕዛዝ ታዛዥ ስለሆንና ለረዥም ዘመናት ሰዎችን በባርነት አስሮ ያቆየውን የስህተት ምሽግ መዋጋት መብታችንና ግዴታችን መሆኑን ስለተገነዘብን ተግባራችን መጪውን ገናና መሲሐዊ መንግሥት ማወጅ ነበር፣ አሁንም ነው።” ዋናው አከራካሪ ጉዳይ የአምላክ መንግሥት ነበር።

8, 9. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች በአስቸጋሪዎቹ የጦርነት ዓመታት የነበራቸውን ፍላጎትና ዝንባሌ ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) እሳት ወደ ምድር የተጣለው እንዴት ነበር? (ሐ) ነጎድጓድ፣ ድምፅ፣ መብረቅና የምድር መናወጥ የሆነው እንዴት ነው?

8 ተናጋሪው በዚያን ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ደርሶ ስለነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲናገር እንዲህ አለ:- “ጠላት ያደረሰብን ጥቃት አዘኔታ የጎደለውና ጭካኔ የሞላበት ስለነበረ ከበጉ ተወዳጅ መንጋ መካከል ብዙዎቹ ተደናግጠውና የሚያደርጉት ጠፍቶአቸው ጌታ ፈቃዱን እንዲያሳውቃቸው ይጸልዩ ነበር። . . . ይሁን እንጂ ጊዜያዊ የሆነ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢኖርባቸውም የሚያንገበግብ የአምላክን መንግሥት የማወጅ ፍላጎት ነበራቸው።”—የመስከረም 15, 1919 የመጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 280 ተመልከት።

9 ይህ ፍላጎታቸው በ1919 ተሟላ። ይህ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ትጉህ የነበረው የክርስቲያኖች ቡድን ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ ለመጀመር በመንፈሳዊ ሁኔታ ተቃጠለ። (ከ1 ተሰሎንቄ 5:19 ጋር አወዳድር።) የአምላክ መንግሥት ዋነኛ አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነ እሳት ወደ ምድር እንደተጣለ ያህል ሆነ። እስከ አሁንም ይህ የመንግሥት ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም። ዝምታው የመንግሥቱን መልእክት በግልጽ በሚያስተጋቡ ጉልህ ድምፆች ተተካ። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግም ማስጠንቀቂያ መሰማት ጀመረ። ከትንቢታዊው የይሖዋ ቃል ብሩሕ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደ መብረቅ ብልጭታ መውጣት ጀመረ። ሃይማኖታዊው ዓለም በኃይለኛ የምድር መናወጥ እንደ ተመታ ያህል ከመሠረቱ መናወጥ ጀመረ። የዮሐንስ ክፍል አባሎች ገና የሚሠሩት ሥራ እንዳለ ተገነዘቡ። ይህም ሥራ እስከዚህች ቀን ድረስ በመላው ምድር ላይ በአስደናቂ ሁኔታ መስፋፋቱን ቀጥሎአል።—ሮሜ 10:18

ለመለከቶቹ መነፋት መዘጋጀት

10. ሰባቱ መላእክት ምን ለማድረግ ተዘጋጁ? ለምንስ?

10 ዮሐንስ በመቀጠል “ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ” ይላል። (ራእይ 8:6) የእነዚህ መለከቶች መነፋት ምን ትርጉም አለው? በእስራኤላውያን ዘመን የመለከት ድምፅ ታላላቅ ቀናትን ወይም አውደ ዓመታትን ያበስር ነበር። (ዘሌዋውያን 23:24፤ 2 ነገሥት 11:14) በተመሳሳይም ዮሐንስ የሚሰማቸው የመለከት ድምፆች የሞትና የሕይወትን ያህል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የሚያስገነዝቡ ናቸው።

11. ከ1919 እስከ 1922 በነበሩት ዓመታት የዮሐንስ ክፍል ምን ዓይነት የዝግጅት ሥራ ያከናውን ነበር?

11 መላእክቱ እነዚህን መለከቶች ሊነፉ በተዘጋጁ ጊዜ በምድር ላይ መከናወን ለነበረበት የዝግጅት ሥራም አመራር ይሰጡ እንደነበረ ግልጽ ነው። ከ1919 እስከ 1922 በነበሩት ዓመታት አዲስ ብርታት አግኝተው የነበሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ሕዝባዊውን አገልግሎት በማደራጀትና የጽሑፎች ማተሚያ ድርጅቶችን በማዘጋጀት ተግተው ሲሠሩ ቆይተው ነበር። በ1919 ዘ ጎልድን ኤጅ የተባለው በአሁኑ ጊዜ አዌክ! (ንቁ!) የሚባለው መጽሔት መታተም ጀመረ። ይህ መጽሔት “የሐቅ፣ የተስፋና የጽኑ እምነት መጽሔት” እንዲሆን የታቀደ ስለነበረ የሐሰት ሃይማኖት የሚያደርገውን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በማጋለጥ ረገድ እንደ መለከት ሆኖ አገልግሎአል።

12. እያንዳንዱ የመለከት ድምፅ ምን ነገር የሚያስታውቅ ነበር? ይህስ በሙሴ ዘመን የተፈጸመውን ምን ነገር ያስታውሰናል?

12 ቀጥለን እንደምንመለከተው እያንዳንዱ የመለከት ድምፅ የተወሰነ የምድር ክፍል በመቅሠፍት እንደ ተመታ የሚያሳይን አስደናቂ ትርዒት ያስተዋውቃል። ከእነዚህ መቅሰፍቶች አንዳንዶቹ ይሖዋ በሙሴ ዘመን ግብጻውያንን ለመቅጣት አምጥቶ የነበረውን መቅሰፍት ያስታውሱናል። (ዘጸአት 7:19 እስከ 12:32) እነዚህ መቅሰፍቶች በዚያ ሕዝብ ላይ የወረደው የይሖዋ የቅጣት ፍርድ መግለጫዎች ነበሩ። የይሖዋ ሕዝቦችም ከባርነት የሚወጡበትን መንገድ ጠርጎላቸዋል። ዮሐንስ የተመለከታቸው መቅሠፍቶችም ይህንኑ የሚመስል ዓላማ የሚያከናውኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ቃል በቃል መቅሰፍቶች አይደሉም። የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ የሚያመለክቱ ምልክቶች ናቸው።—ራእይ 1:1

“ሲሶውን” ለይቶ ማወቅ

13. የመጀመሪያዎቹ አራት መለከቶች ሲነፉ ምን ሆነ? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

13 ቀጥለን እንደምንመለከተው የመጀመሪያዎቹ አራት መለከቶች በተነፉ ጊዜ የምድሩ፣ የባሕሩ፣ የወንዞችና የምንጮች፣ እንዲሁም የምድር ብርሃን ሰጪዎች ሲሶ በመቅሠፍቶቹ ተጎድቶአል። (ራእይ 8:7-12) ሲሶ ሙሉውን ነገር ሳይሆን የአንድን ነገር ክፍል የሚያመለክት ነው። (ከ⁠ኢሳይያስ 19:24፤ ከ⁠ሕዝቅኤል 5:2⁠ና ከ⁠ዘካርያስ 13:8, 9 ጋር አወዳድር።) ታዲያ ይህ መቅሰፍት ሊወርድ የሚገባው በየትኛው ሲሶ ላይ ነው? አብዛኛው የሰው ልጅ በሰይጣንና በሰይጣን ዘሮች ታውሮ ተበላሽቶአል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ሁኔታው ልክ ዳዊት እንደገለጸው ነው። “ሁሉ ዓመጹ በአንድነትም ረከሱ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ አንድም ስንኳ የለም።” (መዝሙር 14:3) አዎ፣ መላው የሰው ልጅ የቅጣት ፍርድ የመቀበል አደጋ ተደቅኖበታል። ይሁን እንጂ ከሁሉም የበለጠ በደለኛ የሆነ አንድ ክፍል አለ። ይህ ክፍል ማለትም “ሲሶው” ክፍል ከቀሩት ሁሉ የተሻለ መሆን ነበረበት። ይህ “ሲሶ” ክፍል ምንድን ነው?

14. ከይሖዋ የተላከውን የመቅሰፍት መልእክት የተቀበለው ምሳሌያዊ የምድር ሲሶ ምንድን ነው?

14 ሕዝበ ክርስትና ናት! በ1920ዎቹ ዓመታት የሕዝበ ክርስትና ግዛት የሰው ልጆችን ሲሶ የሚያቅፍ ሆኖ ነበር። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት ኢየሱስና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በትንቢት የተናገሩለት በእውነተኛው ክርስትና ላይ የተደረገ ታላቅ ክህደት ውጤት ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30፤ ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነን፣ የክርስትናም አስተማሪዎች እኛ ነን ብለዋል። ይሁን እንጂ መሠረተ ትምህርታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፈጽሞ የራቀ ነው። ከዚህም በላይ በአምላክ ስም ላይ ብዙ ነቀፌታ አምጥተዋል። በምሳሌያዊው ሲሶ የተወከለችው ሕዝበ ክርስትና ከይሖዋ ኃይለኛ ቀሳፊ መልእክት ትቀበላለች። ይኸኛው የሰው ልጆች ሲሶ ክፍል ምንም ዓይነት መለኮታዊ ሞገስ ማግኘት የለበትም።

15. (ሀ) እያንዳንዱ የመለከት ድምፅ ለአንድ የተለየ ዓመት የተወሰነ ነውን? አስረዳ። (ለ) የይሖዋን ፍርድ በማወጅ ረገድ በዮሐንስ ክፍል ድምፅ ላይ ተጨምሮ የተሰማው የማን ድምፅ ነው?

15 መለከቶቹ በተከታታይ ከመሰማታቸው ጋር በሚስማማ ሁኔታ ከ1922 እስከ 1928 በተደረጉት ሰባት ታላላቅ ስብሰባዎች ላይ ልዩ የሆኑ ውሣኔዎች ተላልፈዋል። ይሁን እንጂ የመለከቶቹ ድምፅ በእነዚህ ዓመታት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። የጌታ ቀን ወደ ፍጻሜው እየቀረበ በሄደ መጠን የሕዝበ ክርስትና ክፋት አለማቋረጥ ሲጋለጥ ቆይቶአል። ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ጥላቻና ስደት ቢኖር የይሖዋ ፍርድ በምድር በሙሉ መነገር ይኖርበታል። የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋው ይህ ከሆነ በኋላ ብቻ ነው። (ማርቆስ 13:10, 13) እነዚህን ነጎድጓዳማ መግለጫዎች በዓለም በሙሉ እንዲታወቁ በማድረግ ሥራ ከዮሐንስ ክፍል አባሎች ጋር እጅግ ብዙ ሰዎቸ መተባበራቸው በጣም ያስደስታል።

የምድሩ ሲሶ ተቃጠለ

16. የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ከነፋ በኋላ ምን ተፈጸመ?

16 ዮሐንስ ስለ መላእክቱ ሲጽፍ እንዲህ አለ:- “ፊተኛውም መልአክ ነፋ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፣ ወደ ምድርም ተጣለ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ሲሶ ተቃጠለ።” (ራእይ 8:7) ይህ መቅሠፍት በግብጽ ላይ የወረደውን ሰባተኛ መቅሠፍት ይመስላል። ይሁን እንጂ ለዘመናችን ምን ትርጉም ይኖረዋል?—ዘጸአት 9:24

17. (ሀ) በ⁠ራእይ 8:7 ላይ “ምድር” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ክፍል የሆነው የምድር ሲሶ የተቃጠለው እንዴት ነው?

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምድር” የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ የሰው ልጆችን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 11:1፤ መዝሙር 96:1) ሁለተኛውም መቅሠፍት የወረደው የሰው ልጆችን በሚያመለክተው ባሕር ላይ ስለሆነ “ምድሩ” ሰይጣን የገነባውንና ጥፋት የተወሰነበትን የተረጋጋ የሚመስል የሰው ልጆች ክፍል የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። (2 ጴጥሮስ 3:7፤ ራእይ 21:1) የመቅሠፍቱ ትዕይንት የምድር ሲሶ የሆነው የሕዝበ ክርስትና ክፍል በይሖዋ የቁጣ ትኩሳት የተመታ እንደሆነ ያመለክታል። በመሐከልዋ እንደ ዛፍ ከፍ ብለው የሚታዩት ዋኖችዋ በይሖዋ የቁጣ ፍርድ መታወጅ ይቃጠላሉ። በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩት የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች በሙሉ የሕዝበ ክርስትናን ሃይማኖቶች በመደገፍ ከጸኑ በአምላክ ፊት በመንፈሳዊ ጠውልገው እንደ ነደደ የሣር ቅጠል ይሆናሉ።—ከ⁠መዝሙር 37:1, 2 ጋር አወዳድር። *

18. የይሖዋ የፍርድ መልእክት በ1922 በተደረገው የሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ ስብሰባ ላይ የተነገረው እንዴት ነው?

18 ይህ የፍርድ መልእክት የሚዳረሰው እንዴት ነው? የዓለም ክፍል በሆኑትና ብዙውን ጊዜ የአምላክን “ባሮች” በሚሰድቡት የዓለም ዜና ማሠራጫዎች አይደለም። (ማቴዎስ 24:45) መልእክቱ የአምላክ ሕዝቦች በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ መስከረም 10 ቀን 1922 ባደረጉት ሁለተኛ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ጉልህ በሆነ መንገድ ታውጆ ነበር። እነዚህ ተሰብሳቢዎች “ለዓለም መሪዎች የቀረበ ፈተና” የተባለውን የአቋም መግለጫ በአንድ ድምፅና በጋለ ስሜት አስተላለፉ። ግልጽ በሆኑ የድፍረት ቃላት ለዘመናዊው ምሳሌያዊ ምድር የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጡ። “ስለዚህ የምድር ብሔራት፣ ገዥዎቻቸውና መሪዎቻቸው፣ የምድር አብያተ ክርስቲያናት ቀሳውስት፣ ተከታዮቻቸውና ተባባሪዎቻቸው ሁሉ፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችና ትላልቅ ፖለቲከኞች በሙሉ፣ በምድር ላይ ሰላምና ብልጽግና፣ ለሰው ልጆችም ደስታ እናመጣለን በማለት የወሰዱት አቋም ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እንጠይቃቸዋለን። ማቅረብ ካልቻሉ ግን የጌታ ምሥክሮች በመሆን ለምንሰጠው ምሥክርነት ጆሮአቸውን እንዲሰጡና ምሥክርነታችን እውነት መሆኑንና አለመሆኑን እንዲነግሩን እንጠይቃቸዋለን።”

19. የአምላክ ሕዝቦች ለሕዝበ ክርስትና ስለ አምላክ መንግሥት ምን ምሥክርነት ሰጥተዋል?

19 እነዚህ ክርስቲያኖች የሰጡት ምሥክርነት ምን ነበር? የሚከተለው ነበር:- “ለሰው ልጆች ችግርና በሽታ ሁሉ ፈውስ የሚያስገኘውና የብሔራት ሁሉ ፍላጎት የሆነውን ሰላም ለምድር፣ ለሰዎችም በጎ ፈቃድ የሚያመጣው የመሲሑ መንግሥት እንደሆነ እናምናለን፣ ለሰዎችም እንናገራለን። በሥልጣን ላይ ለሚገኘው ለመሲሑ ግዛት ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያስገዙ ሁሉ በዘላለማዊ ሰላም፣ ሕይወትና ነጻነት እንዲሁም ማለቂያ በሌለው ደስታ እንደሚባረኩ እንመሰክራለን።” ይህ እንደ መለከት ድምፅ ደምቆ የሚሰማው ግድድር ከ1922 ይልቅ ሰው ሰራሽ መንግሥታት ሁሉ በተለይም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙት መንግሥታት የሰው ልጆችን ችግሮች ለመፍታት ፈጽሞ በተሳናቸው በዚህ ብልሹ ጊዜ በበለጠ ኃይል ጎልቶ ይሰማል። የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ በድል አድራጊው ክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት መሆኑ ምንኛ ተረጋግጦአል!

20. (ሀ) በ1922 እና ከዚያ በኋላ የተላለፈውን የፍርድ መልእክት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ሲያሰማ የቆየው በምን መንገድ ነው? (ለ) የመጀመሪያው የመለከት ድምፅ በሕዝበ ክርስትና ላይ ምን ውጤት አስከተለ?

20 ይኸኛውና ከዚህ በኋላ የወጡት ሌሎች መግለጫዎች በውሳኔዎች፣ በትራክቶች፣ በንዑሳን መጻሕፍት፣ በመጻሕፍትና በመጽሔቶች ላይ ታትመው እንዲሁም በተለያዩ ውሳኔዎችና ንግግሮች አማካኝነት በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤዎች ተሰራጩ። የመጀመሪያው የመለከት ጩኸት በሕዝበ ክርስትና ላይ በበረዶ ድንጋይ የመመታትን የመሰለ ውጤት አስከትሎ ነበር። ሕዝበ ክርስትና በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች በመካፈልዋ ምክንያት የተከመረባት የደም ወንጀል እርቃኑን ወጥቶ ስለ ተጋለጠ የይሖዋ ቁጣ ሊመጣባት የሚገባ መሆኑ ግልጽ ሆነ። የዮሐንስ ክፍል አባሎች ከጊዜ በኋላ ከእጅግ ብዙ ሰዎች ባገኙት እርዳታ እየታገዙ የመጀመሪያውን የመለከት ድምፅ ማሰማታቸውን ቀጠሉ። ይሖዋ ለሕዝበ ክርስትና ያለውን አመለካከትና ጥፋት የሚገባት መሆኗን አሳውቀዋል።—ራእይ 7:9, 15

የሚቃጠል ተራራ የሚመስል ነገር

21. ሁለተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ምን ሆነ?

21 “ሁለተኛውም መልአክ ነፋ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።” (ራእይ 8:8, 9) ይህ አስፈሪ ትዕይንት የምን ምሳሌ ነው?

22, 23. (ሀ) ሁለተኛው መለከት በመነፋቱ ምክንያት የተላለፈው የትኛው ውሳኔ ነው? (ለ) ‘የባሕሩ ሲሶ’ ምን ያመለክታል?

22 ይህን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመረዳት የምንችለው በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩ.ኤስ.ኤ. ነሐሴ 18-26, 1923 ተደርጎ ከነበረው የይሖዋ ሕዝቦች ስብሰባ ጋር ብናገናዝብ ነው። ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ቅዳሜ ዕለት ከሰዓት በኋላ ያደረገው ንግግር ርዕስ “በጎችና ፍየሎች” የሚል ነበር። “በጎቹ” የአምላክን መንግሥት ምድራዊ ግዛት የሚወርሱት የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ በግልጽ ተብራርቶ ነበር። ከዚያ በኋላ የተላለፈው ውሳኔ “የከሐዲዎቹን ቀሳውስትና ከፍተኛ የገንዘብና የፖለቲካ ኃይል ያላቸውን የመንጎቻቸውን ዋኖች” ግብዝነት የሚያጋልጥ ነበር። በተጨማሪም ውሳኔው “በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ሰላምና ሥርዓት ወዳድ ሕዝቦች . . . ጌታ ታላቂቱ ባቢሎን ብሎ ከሚጠራው ኃጢአተኛ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዲወጡና የአምላክን መንግሥት በረከቶች ለማግኘት” ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።

23 ይህ ውሳኔ የሁለተኛው መለከት መነፋት ውጤት እንደሆነ አያጠራጥርም። ይህን መልእክት የሚቀበሉ ሁሉ ኢሳይያስ “ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና ውኆቹም ጭቃና ጉድፍ ያወጣሉና” በማለት ከገለጻቸው ፍየል መሰል ሰዎች ራሳቸውን ይለያሉ። (ኢሳይያስ 57:20፤ 17:12, 13) ስለዚህ “ባሕሩ” ያለመረጋጋትንና የአብዮትን አረፋ የሚደፍቀውን እረፍት የለሽና ዓመጸኛ የሰው ልጆች ክፍል ማመልከቱ ተገቢ ነው። (ከ⁠ራእይ 13:1 ጋር አወዳድር።) ይህ “ባሕር” ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል። (ራእይ 21:1) ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ግን ይሖዋ በሁለተኛው መለከት አማካኝነት ሲሶ በሆነው በዚህ ክፍል ላይ ማለትም በሕዝበ ክርስትና ሥርዓት የለሽ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የማይገዛ ክፍል ላይ የፍርድ መልእክቱን ሲያሰማ ይቆያል።

24. ወደ ባሕሩ የተጣለው የሚቃጠል ተራራ መሰል ነገር የምን ምሳሌ ነው?

24 በዚህ “ባሕር” ውስጥ በእሳት የሚቃጠል ትልቅ ተራራ መሰል ነገር ተጥሎአል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራራ ብዙ ጊዜ መንግሥታትን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል የአምላክ መንግሥት በተራራ ተመስሎአል። (ዳንኤል 2:35, 44) አጥፊ የነበረችው ባቢሎን “የተቃጠለ ተራራ” ሆናለች። (ኤርምያስ 51:25) ዮሐንስ የተመለከተው ተራራ መሰል ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ በመቀጣጠል ላይ ነው። ወደ ባሕር መጣሉ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጊዜም ይሁን ከዚያ በኋላ የመንግሥት ጉዳይ በሰው ልጆች ዘንድ በተለይም በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ ዋነኛና አንገብጋቢ የመከራከሪያ ጉዳይ መሆኑን ያመለክታል። በኢጣልያ አገር ሙሶሎኒ የፋሺዝምን አገዛዝ አመጣ። ጀርመን የሂትለርን ናዚዝም (ብሔራዊ ሶሻሊዝም) ስትቀበል ሌሎች አገሮች ደግሞ የተለያዩ ዓይነት የሶሺያሊዝም አስተዳደሮችን መሞከር ጀመሩ። በሩሲያ አገር ሥር ነቀል ለውጥ ተካሂዶ የቦልሼቪኮች አብዮት የመጀመሪያይቱን ኮምኒስት መንግሥት አስገኘ። በዚህም ምክንያት የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በዚህች አገር ላይ የነበራቸውን ጠንካራ ኃይል አጡ።

25. ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ቢሆን የመንግሥት ጉዳይ በጣም አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ የቆየው እንዴት ነው?

25 የፋሽስቶችና የናዚዎች ሙከራ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ቢሆንም የመንግሥት ጉዳይ ዋነኛ አከራካሪ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም። የሰው ልጆች ባሕር አረፋ እየደፈቀ አዳዲስ አብዮታዊ መንግሥታትን ማውጣቱን አላቆመም። እንደነዚህ ያሉት መንግሥታት ከ1945 ወዲህ በነበሩት አሥርተ ዓመታት እንደ ቻይና፣ ቪየትናም፣ ኩባና ኒካራጉዋ ባሉት አገሮች ተቋቁመዋል። በግሪክ አገር ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት በማቋቋም የተደረገው የአገዛዝ ሙከራ ውድቅ ሆኖአል። በካምፑቺያ (ካምቦዲያ) ወደ መሠረታዊ የኮምኒስት አስተዳደር በመመለስ የተደረገው ሙከራ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት አሳጥቶአል።

26. ‘የሚቃጠለው ተራራ’ በሰው ልጆች ባሕር ውስጥ ማዕበል ማስነሳቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

26 ይህ “በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራ” በሰው ልጆች ባሕር ላይ ማዕበል ማስነሳቱ አሁንም አልቆመም። በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአሜሪካና በፓስፊክ ደሴት አገሮች በመንግሥት ጉዳይ ላይ የተፋፋመ ትግል እንደተደረገ ተዘግቧል። ከእነዚህ ትግሎች አብዛኛዎቹ የተካሄዱት በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ ወይም የሕዝበ ክርስትና ሚሲዮናውያን የዓመፅ አነሳሽ በሆኑባቸው አገሮች ነው። የሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት በኮምኒስት ሽምቅ ተዋጊ ቡድን ውስጥ ገብተው እስከ መዋጋት ደርሰዋል። በዚህ ጊዜ የፕሮቴስታንት ወንጌላውያን በመካከለኛው አሜሪካ አገሮች “ጭካኔ የተሞላበትና ርህራሄ የጎደለው የሥልጣን ጥማት” ብለው የጠሩትን የኮምኒስቶች እርምጃ ለመቋቋም እንቅስቃሴ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ የሰው ልጅ ባሕር ሞገዶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ሰላምና አስተማማኝ ሁኔታ ሊያመጡ አልቻሉም።—ከ⁠ኢሳይያስ 25:10-12⁠ና ከ⁠1 ተሰሎንቄ 5:3 ጋር አወዳድር።

27. (ሀ) ‘የባሕሩ ሲሶ’ ደም የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ‘በባሕሩ ውስጥ ከነበሩት ፍጥረታት ሲሶው’ የሞተው እንዴት ነው? ‘የጀልባዎቹ ሲሶስ’ ምን ደረሰበት?

27 የሁለተኛው መለከት ድምፅ ለአምላክ መንግሥት ከመገዛት ይልቅ በአብዮታዊ ግጭቶች የሚካፈሉ የሰው ልጅ ክፍሎች ሁሉ የደም ዕዳ እንዳለባቸው አጋልጦአል። በተለይ የሕዝበ ክርስትና ‘ሲሶ ባሕር’ እንደ ደም ሆኖ ነበር። በዚህ ባሕር ውስጥ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በአምላክ ዓይን በድኖች ናቸው። በባሕሩ ሲሶ ላይ እንደ ጀልባ ከሚንሳፈፉት አብዮተኛ ድርጅቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከመስጠም ሊድኑ አይችሉም። በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ በግ መሰል ሰዎች በዚህ ባሕር የብሔረተኝነት መንፈስና ደም አፍሳሽነት ከሚዋኙት ሰዎች መካከል ተነጥለው እንዲወጡ የቀረበላቸውን የመለከት ጥሪ መቀበላቸው በጣም ያስደስተናል።

አንድ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ

28. ሦስተኛው መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ ምን ሆነ?

28 “ሦስተኛውም መልአክ ነፋ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፣ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ፣ የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል። የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለ ተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።” (ራእይ 8:10, 11) አሁንም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህ ጥቅስ በጌታ ቀን እንዴት ያለ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው እንድናውቅ ይረዱናል።

29. ‘እንደ መብራት የሚነደው’ ትልቅ ኮከብ ምሳሌ የሆነው ለማን ነው? ለምንስ?

29 ከዚህ ቀደም ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ኮከብ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንደሚያመለክት ተመልክተን ነበር። * (ራእይ 1:20) ቅቡዓን “ኮከቦች” ከሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ሆነው ሰማያዊ ውርሻ የማግኘታቸው ምሳሌ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ የሚኖሩት በመንፈሳዊ አነጋገር በሰማይ ነው። (ኤፌሶን 2:6, 7) ይሁን እንጂ ከእነዚህ ኮከብ መሰል ሰዎች መካከል መንጋውን የሚያስቱ መናፍቃንና ከሃዲዎች እንደሚነሱ ሐዋርያው ጳውሎስ አስጠንቅቆ ነበር። (ሥራ 20:29, 30) እንዲህ ያለው የታማኝነት ጉድለት ትልቅ ክህደት ያስከትላል። እነዚህ የወደቁ ሽማግሌዎች እንደ አንድ አካል በመሆን ራሱን በሰው ልጆች መካከል በአምላክ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው የዓመፅ ሰው ክፍል ይሆናሉ። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 4) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በምድር መድረክ ላይ ብቅ ባሉ ጊዜ የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ ተፈጽሞአል። ይህ የቀሳውስት ቡድን “እንደ ችቦ የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ” በሚል ምሳሌ መጠራቱ ተገቢ ነው።

30. (ሀ) የባቢሎን ንጉሥ ከሰማይ እንደወደቀ መነገሩ ምን ትርጉም ነበረው? (ለ) ከሰማይ መውደቅ ምን ሊያመለክት ይችላል?

30 ዮሐንስ ይህ ኮከብ ከሰማይ ሲወድቅ ተመልክቶአል። እንዴት? በአንድ የጥንት ንጉሥ ላይ የደረሰ ነገር ይህን እንድንረዳ ያስችለናል። ኢሳይያስ ለባቢሎን ንጉሥ ሲናገር እንዲህ አለ:- “አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፣ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፣ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቆረጥህ!” (ኢሳይያስ 14:12) ይህ ትንቢት የተፈጸመው ባቢሎን በቂሮስ ሠራዊት ተገልብጣ ንጉሥዋም በድንገት ተዋርዶ ከዓለም ገዥነት ሥልጣኑ በወረደ ጊዜ ነበር። ስለዚህ ከሰማይ መውደቅ ከከፍተኛ ደረጃ ወርዶ ውርደት መቀበልን ሊያመለክት ይችላል።

31. (ሀ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት “ከሰማያዊ” ደረጃቸው የወደቁት መቼ ነበር? (ለ) በቀሳውስቱ ይሰጥ የነበረው ውኃ “እሬት” የሆነው እንዴት ነው? ይህስ በብዙ ሰዎች ላይ ምን ውጤት አስከትሎአል?

31 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ክርስትናን በካዱ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠ኤፌሶን 2:6, 7 ላይ ከገለጠው ከፍ ያለ ‘ሰማያዊ’ ስፍራ ወደቁ። ጣፋጭ የሆነውን የእውነት ውኃ ከማቅረብ ይልቅ እንደ “እሬት” መራራ የሆኑትን እንደ ሥላሴ፣ የሲኦል እሳት፣ መንጽሔና የአርባ ቀን እድል የመሰሉትን የሐሰት ትምህርቶች መመገብ ጀመሩ። ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች ነን እንደማለታቸው ሕዝብን ከማነጽ ይልቅ ወደ ጦርነት መሩአቸው። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በእነዚህ ውሸቶች የሚያምኑ ሁሉ መንፈሳዊነታቸው ተመረዘ። ሁኔታቸው በኤርምያስ ዘመን ከነበሩት ከሃዲ እስራኤላውያን ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይሖዋ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር:- “እነሆ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኩሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ፣ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።”—ኤርምያስ 9:15፤ 23:15

32. ሕዝበ ክርስትና ከመንፈሳዊ ሰማይ መውደቅዋ ግልጽ ሆኖ የታየው መቼ ነበር? ይህስ በሥዕላዊ ሁኔታ የተገለጸው እንዴት ነው?

32 ይህ መንፈሳዊ ውድቀት በ1919 በጣም ጥቂት የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምትክ በመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ በተሾሙ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ሆኖአል። (ማቴዎስ 24:45-47) ከ1922 ጀምሮ ደግሞ ይህ የክርስቲያኖች ቡድን የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት ውድቀት በይፋ ማጋለጥ ስለጀመረ ይህ ውድቀት ገሐድ ሆኖአል።

33. በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩ.ኤስ.ኤ. በ1924 ተደርጎ በነበረው ትልቅ ስብሰባ ላይ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የተጋለጡት እንዴት ነው?

33 በዚህ ረገድ ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት “በዘመናት ሁሉ ከተደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባዎች ሁሉ የሚበልጥ ስብሰባ” ሲል በጠራው ትልቅ ስብሰባ ላይ የወጣው መግለጫ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ስብሰባ የተደረገው በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ ከሐምሌ 20-27, 1924 ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተላለፈው ጠንከር ያለ ውሳኔ ሦስተኛውን መለከት በነፋው መልአክ መሪነት እንደነበረ አያጠራጥርም። ይህም ውሣኔ በ50 ሚልዮን የትራክት ቅጂዎች ታትሞ ተሰራጭቶአል። የትራክቱ ርዕስ አብያተ ክርስቲያናት ተወነጀሉ የሚል ነበር። ንዑስ ርዕሱ ደግሞ “የተስፋው ዘርና የእባቡ ዘር” የሚል ነበር። መግለጫው የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት በአጠቃላይ፣ ለራሳቸው ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጡ የማዕረግ ስሞችን በመያዛቸው፣ ከፍተኛ የንግድ ከበርቴዎችንና የፖለቲካ ሰዎችን ከመንጎቻቸው አስበልጠው በመመልከታቸው፣ በሰዎች ፊት ብርሃን መስለው ለመታየት በመፈለጋቸውና የመሲሑን መንግሥት መልእክት ለሰዎች ለመስበክ እምቢተኞች በመሆናቸው ወንጀለኞች መሆናቸውን የሚያጋልጥ ነበር። እያንዳንዱ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን ‘የአምላክን የበቀል ቀን የማወጅና የሚተክዙትን ሁሉ የማጽናናት’ ግዴታ የተቀበለ መሆኑን አጉልቶ የሚገልጽ ነበር።—ኢሳይያስ 61:2

34, 35. (ሀ) ሦስተኛው መልአክ መለከቱን መንፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቀሳውስት የነበራቸው ኃይልና ሥልጣን ምን ሆኖአል? (ለ) የወደፊቱ ጊዜ ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምን ይዞአል?

34 ሦስተኛው መልአክ መለከቱን መንፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ቀሳውስት በሰዎች ላይ የነበራቸውን የበላይነት ቀስ በቀስ እያጡ መጥተዋል። በቀደሙት መቶ ዘመናት የነበራቸውን አምላክ አከል ደረጃ አብዛኞቹ አጥተዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ስብከት ምክንያት በጣም ብዙ ሰዎች ቀሳውስት የሚያስተምሩአቸው መሠረተ ትምህርቶች በአብዛኛው መንፈሳዊ መርዝ ወይም “እሬት” መሆናቸውን ተገንዝበዋል። ከዚህም በላይ ቀሳውስት በሰሜን አውሮፓ የነበራቸው ሥልጣን ፈጽሞ ተዳክሞአል። በሌሎች ጥቂት አገሮችም የየአገሩ መንግሥታት የቀሳውስቱን እንቅስቃሴ በአብዛኛው አግደዋል። የካቶሊክ እምነት በተስፋፋባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮች ቀሳውስቱ በገንዘብ፣ በፖለቲካና በሥነ ምግባር ጉዳዮች የታየባቸው ቅሌትና ብልሹ ባሕርይ ስማቸውን አበላሽቶባቸዋል። ከእንግዲህም ወዲህ ሁኔታቸው ይባባሳል እንጂ አይሻሻልም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሐሰተኛ ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ይደርስባቸዋል።—ራእይ 18:21፤ 19:2

35 ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚያመጣው መቅሰፍት ገና አላለቀም። አራተኛው መለከት ከተነፋ በኋላ ምን እንደሚሆን እንመልከት።

ጨለማ!

36. አራተኛው መልአክ መለከቱን ከነፋ በኋላ ምን ሆነ?

36 “አራተኛውም መልአክ ነፋ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፣ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፣ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፣ እንዲሁም የሌሊት።” (ራእይ 8:12) በግብጽ ምድር ላይ የወረደው ዘጠነኛ መቅሰፍት ቃል በቃል እውነተኛ ጨለማ ነበር። (ዘጸአት 10:21-29) ታዲያ በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመን በሚኖሩት ሰዎች ላይ እንደ መቅሰፍት የወረደው ጨለማ ምንድን ነው?

37. ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩበትን መንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት በማለት ገልጸዋል?

37 ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ በጨለማ ውስጥ እንደነበሩ ተናግሮ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9) በተጨማሪም ጳውሎስ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎች የሚኖሩበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመግለጽ “ጨለማ” የሚለውን ቃል ተጠቅሞአል። (ኤፌሶን 5:8፤ 6:12፤ ቆላስይስ 1:13፤ 1 ተሰሎንቄ 5:4, 5) ይሁን እንጂ በአምላክ እናምናለን፣ ኢየሱስም አዳኛችን እንደሆነ ተቀብለናል የሚሉት የሕዝበ ክርስትና አባሎች የሚገኙበት ሁኔታ እንዴት ያለ ነው?

38. አራተኛው መልአክ ሕዝበ ክርስትና ስለምትሰጠው ብርሃን ምን ነገር አሳወቀ?

38 እውነተኛ ክርስቲያኖች በፍሬያቸው እንደሚታወቁና ተከታዮቹ ነን የሚሉ ብዙዎች ግን “ዓመፀኞች” እንደሆኑ ኢየሱስ ተናግሮአል። (ማቴዎስ 7:15-23) ሕዝበ ክርስትና የያዘችው የምድር ሲሶ የሚያፈራውን ፍሬ የተመለከተ ማንኛውም ሰው በድቅድቅ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እየዳከረች መሆኗን ሊክድ አይችልም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ክርስቲያን ነኝ ስለምትል ከማንኛውም ድርጅት የበለጠ ተነቃፊ ሆናለች። ስለዚህ አራተኛው መልአክ የሕዝበ ክርስትና “መብራት” የጨለመ መሆኑን በመለከት ድምፅ ማስታወቁ ተገቢ ነው። ‘የመብራትዋም’ ምንጭ ባቢሎናዊና ከክርስትና የራቀ ነው።—ማርቆስ 13:22, 23፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

39. (ሀ) በ1925 ተደርጎ በነበረው ትልቅ ስብሰባ ላይ የተላለፈው ውሳኔ የሕዝበ ክርስትናን የውሸት መብራት የገለጸው እንዴት ነበር? (ለ) በ1955 ምን ተጨማሪ የማጋለጥ እርምጃ ተወሰደ?

39 ከዚህ ሰማያዊ መግለጫ ጋር በመስማማት የአምላክ ሕዝቦች ነሐሴ 29 ቀን 1925 በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና፣ ዩ.ኤስ.ኤ ከፍተኛ ስብሰባ አድርገው “የተስፋ መልእክት” የተባለ ውሳኔ ታትሞ እንዲሰራጭ በአንድ ድምፅ አጸደቁ። ይህም ውሳኔ በተለያዩ ቋንቋዎች በ50 ሚልዮን ቅጂዎች ተዘጋጅቶ ተሰራጨ። የትርፍ አግበስባሽ ነጋዴዎች፣ የፖለቲካ መሪዎችና የሃይማኖታዊ ቀሳውስት ጥምረት የያዘው ሐሰተኛ መብራት ‘ሰዎችን ሁሉ በጨለማ ውስጥ እንደጣላቸው’ የሚያጋልጥ ውሳኔ ነበር። “የሰላም፣ የብልጽግና፣ የጤና፣ የሕይወት፣ የነፃነትና የዘላለማዊ ደስታ በረከቶችን” የሚያስገኘው እርግጠኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ገልጾአል። በቁጥር አነስተኛ ከነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ሲወዳደር በጣም ትልቅ በሆነው የሕዝበ ክርስትና ድርጅት ላይ ይህን የመሰለውን መልእክት ለማስተላለፍ ትልቅ ድፍረት ጠይቆባቸዋል። ቢሆንም ከ1920 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሳያቋርጡ ይህን የመሰለ መልእክት ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። በቅርብ ጊዜ ማለትም በ1955 እንኳን “የዓለም ብርሃን” ክርስትና ነው ወይስ ሕዝበ ክርስትና? የተባለ ንዑስ መጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች አዘጋጅተው በመላው ዓለም በማሰራጨት የቀሳውስቱን ክፍል አጋልጠዋል። በአሁኑ ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ግብዝነት ግልጽ ሆኖ የሚታይ ስለሆነ ብዙዎቹ የዓለም ሰዎች ራሳቸው አይተው ሊረዱ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሶአል። ቢሆንም የይሖዋ ሕዝቦች የጨለማ መንግሥት መሆኗን ከማጋለጥ ተቆጥበው አያውቁም።

የሚበርር ንሥር

40. አራቱ የመለከት ድምፆች ሕዝበ ክርስትና ምን መሆኗን አሳይተዋል?

40 እነዚህ የመጀመሪያዎቹ አራት የመለከት ድምፆች በእርግጥም የሕዝበ ክርስትናን ባድማነትና ነፍሰ ገዳይነት ለማጋለጥ ችለዋል። እርስዋ የምትገኝበት የምድር ክፍል የይሖዋ ፍርድ ሊወርድበት የሚገባ መሆኑ በግልጽ ታይቶአል። በራስዋ አገሮች ውስጥና በሌሎች ሥፍራዎች የተነሱ አብዮታዊ መንግሥታት ለመንፈሳዊ ሕይወት ጠላቶች መሆናቸው ታይቶአል። የቀሳውስትዋ ወራዳነት ግልጽ ሆኖ ታይቶአል። የመንፈሳዊ ሁኔታዋ አጠቃላይ ጨለማነት ማንም ሰው ሊያስተውለው በሚችል ሁኔታ ተጋልጦአል። በእርግጥም ሕዝበ ክርስትና ከሰይጣን ሥርዓት ክፍሎች ሁሉ ይበልጥ ነውረኛ ክፍል ነች።

41. ተከታታይ የሆኑት የመለከቶቹ ድምፆች በመሐል ቆም ባሉበት ጊዜ ዮሐንስ ምን ተመለከተ? ምንስ አዳመጠ?

41 ሌላስ ምን የሚገለጽ ተጨማሪ ነገር አለ? የዚህን ጥያቄ መልስ ከማግኘታችን በፊት በተከታታይ ይሰማ የነበረው የመለከት ድምፅ ለጥቂት ጊዜ ቆም ይላል። ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተውን ነገር እንደሚከተለው ይገልጻል:- “አየሁም፣ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ:- በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።”—ራእይ 8:13

42. በራሪው ንሥር የምን ምሳሌ ሊሆን ይችላል? የእርሱስ መልእክት ምን ነበር?

42 ከፍ ብሎ በሰማይ የሚበርር አንድ ንስር በሰፊ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ሊታይ ይችላል። በጣም ኃይለኛ የሆነ የማየት ችሎታ ስላለው ከፊቱ ያለውን ሩቅ ነገር ሁሉ ለማየት ይችላል። (ኢዮብ 39:29) በአምላክ ዙፋን ዙሪያ ከነበሩት አራት ኪሩቤላዊ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል አንደኛው በሚበር ንስር ተመስሎ ነበር። (ራእይ 4:6, 7) ይኸኛው ኪሩቤል ይሁን ወይም አርቆ ተመልካች የሆነ ሌላ የአምላክ አገልጋይ ጮክ ብሎ “ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው” የሚል ጠንካራ መልእክት አሰምቶአል። የምድር ነዋሪዎች ሁሉ እነዚህን ሦስት ወዮታዎች የሚገልጹት ሦስት የመለከት ድምፆች ሲጮሁ ልብ ብለው ያዳምጡ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 እጅግ ብዙ ሰዎች ከዚህ በተለየ ሁኔታ በ⁠ራእይ 7:16 ላይ እንደተገለጸው የይሖዋ የቁጣ ትኩሳት አይወርድባቸውም።

^ አን.29 በኢየሱስ እጅ ውስጥ የነበሩት ሰባት ከዋክብት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾችን የሚያመለክቱ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በምድር በሙሉ በሚገኙት ከ100,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙት የበላይ ተመልካቾች የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ናቸው። (ራእይ 1:16፤ 7:9) ታዲያ የእነዚህ ደረጃ ምንድን ነው? ሹመታቸውን ያገኙት በተቀባው ታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ከመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ እነርሱም በኢየሱስ ቀኝ እጅ ቁጥጥር ሥር ያሉ የበታች እረኞች ናቸው። (ኢሳይያስ 61:5, 6፤ ሥራ 20:28) ብቃት ያላቸው ቅቡዓን በማይገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለሚያገለግሉ ‘ለሰባቱ ከዋክብት’ ድጋፍ ይሰጣሉ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የሕዝበ ክርስትና ውኃ እንደ እሬት የመረረ መሆኑ ተገለጠ

የሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ

እምነቶችና አቋሞች ግን ምን ይላል?

የአምላክ ስም ይህን ያህል ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲቀደስ ጸልዮአል።

አስፈላጊነት የለውም:- “ብቸኛ የሆነውንና ጴጥሮስ “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] አምላክ በተፀውኦ ስም መጥራት . . . ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ሥራ 2:21፤ ኢዩኤል 2:32

ለጠቅላላው የክርስትና ብሎአል።

ቤተ ክርስቲያን ማቴዎስ 6:9

እምነት አስፈላጊነት የለውም።” ዘጸአት 6:3 የ1879 ትርጉም፤

(የሪቫይዝድ ስታንዳርድ ራእይ 4:11፤ 15:3፤ 19:6)

ቨርሽን መቅድም)

አምላክ ሥላሴ ነው:- መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ

“አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ፣

መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው። የክርስቶስ ራስና አምላክ

ቢሆንም አንድ አምላክ ነው እንደሆነ ይናገራል። ዮሐንስ 14:28፤ 20:17

እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።” 1 ቆሮንቶስ 11:3)

(የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ፣ የ1912 እትም) መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አንቀሳቃሽ

ኃይል ነው። (ማቴዎስ 3:11፤;

ሉቃስ 1:41፤ ሥራ 2:4)

የሰው ነፍስ አትሞትም:- ሰው ራሱ ነፍስ ነው።

“ሰው ሲሞት ነፍሱና ሥጋው ይለያያሉ። ሰው ሲሞት ነፍሱ ምንም

ሥጋው. . . ይበሰብሳል ዓይነት ስሜት ወይም ሐሳብ አይኖረውም።

. . . ነፍሱ ግን ፈጽሞ ወደ ተፈጠረበት አፈር ይመለሳል።

አትሞትም።” (ከሞት በኋላ (ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19

ምን ይሆናል? የሮማ መዝሙር 146:3, 4 NW፤

ካቶሊክ ጽሑፍ) መክብብ 3:19, 20፤ 9:5, 10

ሕዝቅኤል 18:4, 20)

ክፉዎች ከሞቱ በኋላ በሲኦል የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው

ውስጥ ቅጣት ይቀበላሉ:- “በባህላዊ የክርስትና እንጂ የሥቃይ ሕይወት ይደለም።

እምነት መሠረት ሲኦል ፍጻሜ (ሮሜ 6:23) ሙታን ምንም ዓይነት ስሜት

የሌለው መከራና ሥቃይ የሚገኝበት ሳይኖራቸው በሲኦል (ሔድስ፣ ሺኦል)

ሥፍራ ነው።” ( ውስጥ ትንሣኤ ይጠብቃሉ። (መዝሙር 89:48

(ዘ ወርልድ ቡክ ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:24, 25

ኢንሳይክሎፒድያ፣ የ1987 እትም) ራእይ 20:13, 14)

“የጭንቅ አማላጂቱ የሚለው የማዕረግ ስም በአምላክና በሰው መካከል ያለው

የተሰጠው ለእመቤታችን ነው።” መካከለኛ ወይም አማላጅ ኢየሱስ ብቻ ነው።

(ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ፣ (ዮሐንስ 14:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5

የ1967 እትም) ዕብራውያን 9:15፤ 12:24)

ሕጻናት መጠመቅ ይገባቸዋል:- መጠመቅ የሚገባቸው ደቀ መዛሙርት

“ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ለሕጻናት ለመሆን የኢየሱስን ትዕዛዛት እንዲፈጽሙ

ሥርዓተ ጥምቀት ስትፈጽም ቆይታለች። የተማሩ ብቻ ናቸው።

ስትፈጽም ቆይታለች። ማንኛውም ሰው ከመጠመቁ በፊት

ይህ ልማድ ሕጋዊ የአምላክን ቃል መረዳትና ማመን ይኖርበታል።

ከመሆኑም በላይ (ማቴዎስ 28:19, 20

ለመዳን ፍጹም ሉቃስ 3:21-23

አስፈላጊ ነው።” ሥራ 8:35, 36)

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ፣

የ1967 እትም)

አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች

በምዕመናንና ምዕመናኑን በሙሉ አገልጋዮች ነበሩ።

በሚያገለግሉ የካህናት ሁሉም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ተካፍለዋል።

ክፍል የተከፈሉ ናቸው። (ሥራ 2:17, 18

ካህናቱ ለሚሰጡት አገልግሎት ሮሜ 10:10-13፤16:1)

ደመወዝ የሚከፈላቸው ሲሆን ክርስቲያን “በነጻ መስጠት”

“ብጹዕነታቸው” “አባታችን” “ቅዱስ” ይኖርበታል እንጂ ደመወዝ መቀበል የለበትም።

በሚሉ የማዕረግ ስሞች እየተጠሩ ራሳቸውን (ማቴዎስ 10:7, 8 NW)

ከምዕመናኑ በላይ ከፍ ያደርጋሉ። ኢየሱስ በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች

መጠራትን በጥብቅ ከልክሎአል።

(ማቴዎስ 6:2፤ 23:2-12

1 ጴጥሮስ 5:1-3)

ሥዕሎችን፣ ምስሎችንና መስቀሎችን ክርስቲያኖች ከማንኛውም

ለአምልኮ መጠቀም:- “የክርስቶስ . . .፣ ዓይነት ጣዖት አምልኮ፣

የድንግልዋ የወላዲተ አምላክና መጠነኛ አምልኮ ይሰጣቸዋል

የሌሎቹ ቅዱሳን ምስል . . . ከሚባሉትም ጭምር መሸሽ ይኖርባቸዋል።

በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ (ዘጸአት 20:4, 5

ሊኖሩና ተገቢው ክብርና ቅድስና 1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21)

ሊሰጣቸው ይገባል።” አምላክን የሚያመልኩት በመንፈስና

የትራንት [1545-63]) በእውነት ነው እንጂ በማየት አይደለም።

ጉባኤ መግለጫ (ዮሐንስ 4:23, 24፤ 2 ቆሮንቶስ 5:7)

የቤተ ክርስቲያን አባሎች የአምላክ ፈቃድ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ይሰብክ

በፖለቲካ አማካኝነት እንደሚፈጸም ነበር እንጂ አንድ ዓይነት የፖለቲካ

ትምህርት ተሰጥቶአቸዋል። ሟቹ ካርዲናል ስፔልማን ሥርዓት የሰው ልጅ ተስፋ እንደሆነ

“ሰላም የሚገኘው በአንድ መንገድ ነው አላስተማረም። (ማቴዎስ 4:23

. . . እርሱም በዲሞክራሲ 6:9, 10) በፖለቲካ ጉዳዮች

አውራ ጎዳና ብቻ ነው” ብለዋል። ለመካፈል እምቢ ብሎአል።

ሃይማኖተኞች በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች (ዮሐንስ 6:14, 15) የእርሱ መንግሥት

ስለሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ከዜና ማሰራጫዎች የዚህ ዓለም ክፍል አልነበረም።

መስማት ይቻላል። ሃይማኖታውያን የደፈጣ ተከታዮቹም የዚህ ዓለም ክፍል መሆን

ውጊያን ይደግፋሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት አልነበረባቸውም። (ዮሐንስ 18:36፤ 17:16)

ድርጅትም “የመጨረሻው የስምምነትና ያዕቆብ የዓለም ወዳጅ መሆን ተገቢ እንዳልሆነ

የሰላም ተስፋ” እንደሆነ ያምናሉ። አስጠንቅቆ ነበር። (ያዕቆብ 4:4)

[በገጽ 132 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰባቱ ማኅተሞች መፈታት ሰባቱ መለከቶች እንዲነፉ አድርጓል

[በገጽ 140 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ለዓለም መሪዎች የቀረበ ፈተና” (1922)

ይህ መግለጫ ይሖዋ “በምድሪቱ” ላይ የሚያመጣውን መቅሰፍት ለማሳወቅ ረድቶአል

[በገጽ 140 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ለክርስቲያኖች በሙሉ የቀረበ ማስጠንቀቂያ” (1923)

ይሖዋ “በባሕሩ ሲሶ” ላይ የሚያስፈጽመው የቅጣት ፍርድ በዚህ መግለጫ አማካኝነት ታውጆአል

[በገጽ 141 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አብያተ ክርስቲያናት ተወነጀሉ” (1924)

ይህ ትራክት ያገኘው ሠፊ ስርጭት በኮከብ የተመሰሉት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የደረሰባቸውን ውድቀት ለበርካታ ሕዝቦች አሳውቆአል

[በገጽ 141 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የተስፋ መልእክት” (1925)

ይህ ግልጽ የሆነ መግለጫ ብርሃን ያስገኛሉ ተብለው የሚታሰቡት የሕዝበ ክርስትና የብርሃን ምንጮች የጨለማ ምንጮች መሆናቸውን አጋልጦአል