በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት

በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት

ምዕራፍ 35

በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት

1. መልአኩ ቀዩን አውሬ የገለጸው እንዴት ነው? የራእይን ምልክቶች ለመረዳት የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ጥበብ ነው?

መልአኩ በ⁠ራእይ 17:3 ላይ ስለተጠቀሰው ቀይ አውሬ ተጨማሪ መግለጫ ሲሰጥ ለዮሐንስ እንዲህ አለው:- “ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፣ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፣ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” (ራእይ 17:9, 10) እዚህ ላይ መልአኩ ያሳወቀው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን ምልክቶች ለማስተዋል የሚያስችለውን ከላይ የሚመጣ ጥበብ ነው። (ያዕቆብ 3:17) ይህ ጥበብ የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ባልንጀሮቻቸው ይህ የምንኖርበት ጊዜ ምን ያህል አሳሳቢ ጊዜ መሆኑን እንዲያስተውሉ ያስችላቸዋል። ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ የተወሰኑ ልቦች አሁን ሊፈጸም የተቃረበውን የይሖዋ ፍርድ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ለይሖዋም ጤናማ ፍርሐት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ምሳሌ 9:10 እንደሚለው “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] መፍራት ነው፣ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።” ታዲያ ይህ መለኮታዊ ጥበብ ስለ አውሬው ምን ነገር ይገልጥልናል?

2. የቀዩ አውሬ ሰባት ራሶች ትርጉም ምንድን ነው? ‘አምስቱ የወደቁትና አንዱ የኖረው’ እንዴት ነው?

2 የዚህ አስፈሪ አውሬ ሰባት ራሶች ሰባት “ተራሮችን” ወይም ሰባት “ነገሥታትን” ያመለክታሉ። ሁለቱም ቃሎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መንግሥታዊ ሥልጣናትን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ኤርምያስ 51:24, 25፤ ዳንኤል 2:34, 35, 44, 45) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ የነበራቸው ስድስት የዓለም ኃያል መንግሥታት እንደነበሩ ተገልጾአል። እነርሱም ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ-ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ናቸው። ከእነዚህ መካከል ዮሐንስ ራእዩን በተቀበለበት ጊዜ አምስቱ መጥተው ያለፉ ሲሆን ሮም ገና ከዓለም ኃያልነቱ አልወረደም ነበር። ይህም “አምስቱ ወድቀዋል፣ አንዱም አለ” ከሚለው ቃል ጋር ይስማማል። ይሁን እንጂ ገና የሚመጣው “የቀረው” መንግሥትስ?

3. (ሀ) የሮማ ግዛት የተከፈለው እንዴት ነው? (ለ) በምዕራቡ ክፍል ምን ነገሮች ተፈጸሙ? (ሐ) ቅዱሱ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት እንዴት መታየት ይኖርበታል?

3 የሮማ መንግሥት ከዮሐንስ ዘመን በኋላ እንኳን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ግዛቱን ሲያስፋፋ ቆይቶአል። በ330 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ መናገሻ ከተማውን ከሮማ ወደ ባይዛንቲየም አዛወረና የከተማይቱን ስም ለውጦ ኮንስታንቲኖፕል አላት። በ395 እዘአ የሮማ ግዛት ሁለት ቦታ ላይ በምሥራቅና በምዕራብ ተከፈለ። በ410 እዘአ ራሷ ሮማ አላሪክ በተባለው የቪሲጎቶች (ወደ አርያውያን “ክርስትና” የተለወጡ የጀርመን ጎሣዎች ናቸው) ንጉሥ እጅ ወደቀች። የጀርመን ጎሣዎች (“ክርስቲያን” ነን የሚሉት) ስፓኝንና በሰሜን አፍሪካ የሚገኙትን አብዛኞቹን የሮማ ግዛቶች ወረሩ። በአውሮፓ ለብዙ መቶ ዓመታት አለመረጋጋት፣ የግዛት ሽግሽግና ብጥብጥ ሰፍኖ ቆየ። በምዕራቡ ክፍል ታላላቅ ነገሥታት ተነስተው ነበር። ከእነዚህም መካከል በ9ኛው መቶ ዓመት ከሊቀ ጳጳስ ሊዮ ሣልሳዊ ጋር የትብብር ውል ፈርሞ የነበረው ሻርለማኝና በ13ኛው መቶ ዘመን ተነስቶ የነበረው ዳግማዊ ፍሬደሪክ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ግዛታቸው ቅዱሱ የሮማ ግዛት ተብሎ ቢጠራም በስፋቱ ከቀድሞው የሮማ ግዛት በጣም ያነሰ ነበር። የቀድሞው የሮማ ግዛት ቀጠለ እንጂ አዳዲስ ኃያል መንግሥታት አልሆኑም።

4. የምሥራቁ ግዛት እንዴት ያለ የተሳካ ውጤት አግኝቶ ነበር? ይሁን እንጂ የጥንቱ የሮማ መንግሥት የቀድሞ ግዛቶች የነበሩት የሰሜን አፍሪካ፣ የስፔንና የሶሪያ አብዛኞቹ ክፍሎች ምን ሆነው ነበር?

4 በኮንስታንቲኖፕል የተመሠረተው ምሥራቃዊ የሮማ ግዛት ከምዕራቡ ግዛት ብዙም ሳይጣጣም ኖረ። በስድስተኛው መቶ ዘመን የምሥራቁ ንጉሥ የነበረው ንጉሠ ነገሥት ዩስቲንያን ቀዳማዊ አብዛኛውን የሰሜን አፍሪካ ክፍል እንደገና ወርሮ ለመያዝና እስከ ስፓኝና ኢጣልያ ዘልቆ ለመግባት ችሎ ነበር። በሰባተኛው መቶ ዘመን ዳግማዊ ዩስቲንያን በእስላቭ ጎሣዎች ተወስዶ የነበረውን የመቄዶንያ አካባቢ ወደ ግዛቱ ለመመለስ ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ቀድሞ የሮማ መንግሥት ግዛት የነበረው የሰሜን አፍሪካ፣ የስፓኝ፣ የሶርያ ክፍል በአዲሱ የእስልምና ግዛት ሥር ወድቆ ስለነበረ ከኮንስታንቲኖፕል ሆነ ከሮማ ግዛት ውጭ ሆኖ ነበር።

5. የሮማ ከተማ የወደቀችው በ410 እዘአ ቢሆንም የፖለቲካዊው የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ከዓለም መድረክ ሳይጠፋ ለብዙ ዘመናት የቆየው እንዴት ነው?

5 የኮንስታንቲኖፕል ከተማ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይታ ነበር። በ1203 በእስላሞች እጅ ሳይሆን ከምዕራብ በመጡ የመስቀል ጦረኞች እጅ እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ በፋርሳውያን፣ በአረቦች፣ በቡልጋሮችና በሩሲያውያን ተወርራ ነበር። በ1453 ግን በእስላሙ የኦቶማን ገዥ በዳግማዊ መህመድ እጅ ወደቀችና የኦቶማን ወይም የቱርክ ግዛት ዋና ከተማ ሆነች። ስለዚህ የሮማ ከተማ የወደቀችው በ410 እዘአ ቢሆንም የሮማ መንግሥት ርዝራዥ ከዓለም መድረክ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ ብዙ መቶ ዘመናት ፈጅቶ ነበር። ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ እንኳን ቢሆን የሮማ መንግሥት በዓለም ጉዳዮች ላይ የነበረው ተጽዕኖ በሮማ መንበረ ጵጵስናና በምሥራቃዊው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተመሠረቱት ሃይማኖታዊ መንግሥታት ውስጥ በጉልህ ይታይ ነበር።

6. የትኞቹ አዳዲስ ግዛቶች ተቋቁመዋል? ከሁሉም በላይ የተሳካለት የትኛው ነበር?

6 ከ15ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግን አንዳንድ አገሮች ፈጽሞ አዳዲስ የሆኑ መንግሥታትን ማቋቋም ጀምረው ነበር። ከእነዚህ አዲስ ግዛት አስፋፊ ኃይላት አንዳንዶቹ ቀድሞ የሮማ ቅኝ ግዛት በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ ቢሆኑም ግዛታቸው የሮም ግዛት ቅጥያ አልነበረም። ፖርቱጋል፣ ስፓኝ፣ ፈረንሣይና ሆላንድ የሠፊ ግዛት ባለቤቶች ሆኑ። ከሁሉም በላይ የተሳካላት ግን ‘ፀሐይ አይጠልቅበትም’ የተባለ ሠፊ ግዛት ልትመሠርት የቻለችው የብሪታንያ መንግሥት ነበረች። የብሪታንያ ግዛት በሰሜን አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በሕንድ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያና እስከ ፓስፊክ ውቅያኖስ ድረስ የተስፋፋ ነበረ።

7. ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት የተቋቋመው እንዴት ነው? ሰባተኛው ራስ ወይም ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ዮሐንስ ተናገረ?

7 በ19ኛው መቶ ዘመን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ቅኝ ግዛቶች አንዳንዶቹ ከብሪታንያ ተገንጥለው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የሚባል ነጻ መንግሥት መሠረቱ። በአዲሱ ብሔርና በቀድሞው እናት አገር መካከል የፖለቲካ ግጭት መኖሩ አልቀረም ነበር። ቢሆንም አንደኛው የዓለም ጦርነት ሁለቱም አገሮች የጋራ ጥቅም እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ስላስገደዳቸው በመካከላቸው ልዩ የሆነ ዝምድና ተመሠረተ። በዚህም መንገድ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በብልጽግናው ተወዳዳሪ በሌለው በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካና በዓለም በስፋቱ አንደኛ የሆነ የንጉሠ ነገሥት ግዛት እምብርት በሆነችው በብሪታንያ የተቋቋመ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ተመሠረተ። ስለዚህ እስከ መጨረሻው ጊዜ የሚቆየውና የዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋሙበትን ክልል ጭምር የሚገዛው ሰባተኛው ራስ ወይም የዓለም ኃያል መንግሥት ይህ ነው። ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሚቆየው የአምላክ መንግሥት ብሔራዊ ግዛቶችን ሁሉ እስከሚያጠፋበት ጊዜ ድረስ ብቻ ስለሆነ የግዛቱ ዘመን ከስድስተኛው ራስ ጋር ሲወዳደር “ጥቂት ጊዜ” ነው።

ስምንተኛ ንጉሥ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

8, 9. መልአኩ ምሳሌያዊውን ቀይ አውሬ ምን ብሎ ጠርቶታል? ከሰባቱስ የወጣው በምን መንገድ ነው?

8 መልአኩ ቀጥሎ ለዮሐንስ ያብራራለታል። “የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፣ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።” (ራእይ 17:11) ምሳሌያዊው ቀይ አውሬ የወጣው ከሰባቱ ራሶች ነው። የተገኘው ወይም የተወለደው ‘ከባሕር ከወጣው’ የመጀመሪያና ቀዩ አውሬ ምስል ከሆነለት አውሬ ነው። ለሕልውናው ምክንያት የሆነለት በምን መንገድ ነው? በ1919 ትልቁ ራስ የአንግሎ አሜሪካ መንግሥት ነበር። የቀደሙት ስድስት ራሶች ወድቀዋል። በዓለም ላይ የነበራቸውም የበላይነት ተወስዶባቸው ለዚህ ጥምር መንግሥት ተሰጥቶአል። ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር መቋቋም ዋነኛ ኃይል የነበረውና አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነኛ ጠበቃና የገንዘብ ደጋፊ የሆነው ይኸው በጊዜው የዓለም ኃያል መንግሥታት መስመር ተወካይ የሆነው ሰባተኛ ራስ ነው። ስለዚህ በምሳሌያዊ አነጋገር ስምንተኛ ንጉሥ የሆነው ቀይ አውሬ ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ራሶች የወጣ ነው። ነገሩን በዚህ መንገድ ስንመለከት ስምንተኛው አውሬ ከሰባቱ እንደወጣ መነገሩ ቀደም ባለው ራእይ በግ የሚመስል ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ (የአንግሎ አሜሪካ ኃያል መንግስት፣ የመጀመሪያው አውሬ ሰባተኛ ራስ) ምስል እንዲሠራ እንዳሳሰበና ለምስሉም ሕይወት እንደሰጠው ከተገለጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ራእይ 13:1, 11, 14, 15

9 በተጨማሪም የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የመጀመሪያ አባሎች ከሆኑት መንግሥታት መካከል ታላቂቱ ብሪታንያን ጨምሮ የመንግሥት መቀመጫቸውን አንዳንዶቹ የቀድሞ ራሶች ይገዙባቸው በነበሩት ቦታዎች ላይ ያደረጉ መንግሥታት ነበሩ። እነዚህም መንግሥታት ግሪክ፣ ኢራን (ፋርስ) እና ኢጣልያ (ሮም) ናቸው። ቆየት ብሎም የቀደሙት ስድስት የዓለም ኃያል መንግሥታት ይገዙአቸው የነበሩትን አገሮች የሚያስተዳድሩ መንግሥታት የአውሬው ምስል ደጋፊ አባላት ሆኑ። በዚህም ረገድ ይህ ቀይ አውሬ ከሰባቱ የዓለም ኃይላት የወጣ ነው ሊባል ይችላል።

10. (ሀ) ቀዩ አውሬ ራሱ “ስምንተኛው ንጉሥ ነው” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት መሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደግፈው የተናገሩት እንዴት ነው?

10 ቀዩ አውሬ “ራሱ ስምንተኛ ንጉሥ” እንደሆነ መገለጹን አስተውል። በዛሬው ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም መንግሥት እንዲመስል ሆኖ የተዋቀረ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንደ መንግሥት ሆኖ በኮሪያ፣ በሲና ባሕረ ሰላጤና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዳደረገው በብሔራት መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች የጦር ኃይል ልኮአል። ይሁን እንጂ የንጉሥ ምስል ብቻ ነው። እንደ ሃይማኖታዊ ምስል ሁሉ እርሱም በፈጠሩትና በሚያመልኩት ሰዎች ከተሰጠው በስተቀር የራሱ የሆነ እውነተኛ ኃይልም ሆነ ሥልጣን የለውም። ይህ ምሳሌያዊ አውሬ በጣም ደካማ መስሎ የታየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አምባገነን አባል መንግሥታት ጨርሶ ጥለውት ወደ ጥልቁ እንደወረደበት እንደ ፊተኛው ጊዜ ፈጽሞ የወደቀበት ጊዜ አልነበረም። (ራእይ 17:8) በ1987 አንድ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ስመ ጥር መሪ በሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተጻራሪ አቋም ቢኖራቸውም ከሮማ ጳጳሳት ጋር አንድ ሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚደግፍ መግለጫ አውጥተዋል። እንዲያውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የተመሠረተ “ሁሉን አቀፍ የኅብረ ብሔራት የፀጥታ ጥበቃ ሥርዓት” እንዲቋቋም ጥሪ አድርገዋል። ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚገለጽለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውነተኛ ሥልጣን ኖሮት እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል። ከዚያ በኋላ እርሱ ራሱ “ወደ ጥፋት ይሄዳል።”

ለአንድ ሰዓት የሚቆዩ አሥር ነገሥታት

11. የይሖዋ መልአክ በምሳሌያዊው ቀይ አውሬ ላይ ስላሉት አሥር ቀንዶች ምን ተናግሮአል?

11 በቀደመው የራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ ላይ ስድስተኛውና ሰባተኛው መላእክት የአምላክን የቁጣ ጽዋ አፍስሰው ነበር። የምድር ነገሥታትም በአርማጌዶን ወደሚደረገው የአምላክ ጦርነት በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑና ‘ታላቂቱ ባቢሎንም’ በአምላክ ፊት እንደምትታሰብ ተነግሮናል። (ራእይ 16:1, 14, 19) አሁን ደግሞ የአምላክ ፍርድ በእነዚህ ላይ እንዴት እንደሚፈጸም በተብራራ ሁኔታ እንማራለን። የይሖዋ መልአክ ዮሐንስን ሲያነጋግረው እናዳምጥ:- “ያየሃቸውም አሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አሥር ነገሥታት ናቸው፣ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፣ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፣ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።”—ራእይ 17:12-14

12. (ሀ) አሥሩ ቀንዶች ምን ያመለክታሉ? (ለ) ምሳሌያዊዎቹ አሥር ቀንዶች ‘ገና መንግሥት ያልተቀበሉት’ እንዴት ነው? (ሐ) ምሳሌያዊዎቹ አሥር ቀንዶች አሁን መንግሥት የተቀበሉት እንዴት ነው? የሚቆዩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?

12 አሥሩ ቀንዶች በአሁኑ ጊዜ የዓለምን መድረክ የሚቆጣጠሩትንና የአውሬውን ምስል የደገፉትን የፖለቲካ ኃይላት በሙሉ ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ ካሉት አገሮች ብዙዎቹ በዮሐንስ ዘመን አይታወቁም ነበር። ይታወቁ የነበሩት እንደ ግብፅና ፋርስ (ኢራን) ያሉት አገሮችም ቢሆኑ አሁን ያላቸው ፖለቲካዊ መዋቅር ከቀድሞው ፈጽሞ የተለየ ነው። ስለዚህ አሥሩ ‘ቀንዶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ገና መንግሥት አልተቀበሉም’ ነበር። በዚህ በአሁኑ የጌታ ቀን ግን “መንግሥት” ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ተቀብለዋል። ታላላቆቹ ቅኝ ገዥ መንግሥታት ከወደቁ በኋላ በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አዳዲስ ብሔራት ተወልደዋል። እነዚህ አዳዲስ ብሔራትም ሆኑ ብዙ ዘመን የቆዩት የፖለቲካ ኃይላት ከአውሬው ጋር ይሖዋ ዓለማዊ የፖለቲካ ኃይላትን በሙሉ እስከሚያጠፋበት እስከ አርማጌዶን ድረስ “ለአንድ ሰዓት” ማለትም ለአጭር ጊዜ ብቻ መግዛት ይኖርባቸዋል።

13. አሥሩ ቀንዶች “አንድ አሳብ” የኖራቸው በምን መንገድ ነው? ይህስ በበጉ ላይ ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዲኖር አድርጎአል?

13 በዛሬው ጊዜ እነዚህን አሥር ቀንዶች ከሚያንቀሳቅሱት ጠንካራ ኃይሎች አንዱ ብሔራዊ ስሜት ነው። የአምላክን መንግሥት ከመቀበል ይልቅ ብሔራዊ ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ስለሚፈልጉ “አንድ አሳብ” አላቸው። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት የሆኑትም ለዚህ ዓላማ ነው። የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅና በዚያውም ሕልውናቸውን ለማስከበር ነው። ቀንዶቹ እንዲህ ያለ አቋምና ዝንባሌ ስላላቸው “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” የሆነውን በጉን እንደሚቃወሙ የታወቀ ነው። ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እነዚህን መንግሥታት በሙሉ አጥፍቶ እርሱ ብቻውን በቦታቸው እንዲቆም የይሖዋ ዓላማ ነው።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 24:30፤ 25:31-33, 46

14. የዓለም ገዥዎች ከበጉ ጋር ሊዋጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?

14 እርግጥ፣ የዚህ ዓለም ገዥዎች በኢየሱስ ላይ ምንም ለማድረግ አይችሉም። እርሱ የሚኖረው እነርሱ ሊደርሱ በማይችሉበት በሰማይ ነው። ይሁን እንጂ ከሴቲቱ ዘር የቀሩት የኢየሱስ ወንድሞች አሁንም በምድር ላይ ናቸው። ለጥቃትም የተጋለጡ መስለው የሚታዩ ናቸው። (ራእይ 12:17) ከቀንዶቹ መካከል ብዙዎቹ እነዚህን ቀሪዎች አምርረው እንደሚጠሉ አሳይተዋል። ይህንንም በማድረጋቸው በጉን ወግተውታል። (ማቴዎስ 25:40, 45) ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአምላክ መንግሥት ‘እነዚህን ሁሉ መንግሥታት የምትፈጭበትና የምታደቅበት’ ጊዜ ይመጣል። (ዳንኤል 2:44) በቅርቡ እንደምንመለከተው በዚያ ጊዜ የምድር ነገሥታት በሙሉ እስከ መጨረሻው ድረስ ከበጉ ጋር ይዋጋሉ። (ራእይ 19:11-21) ሆኖም ግን ብሔራት በዚህ ጥቃታቸው እንደማይሳካላቸው የሚያስገነዝብ በቂ መረጃ ተሰጥቶናል። እነዚህ ነገሥታትም ሆኑ ቀይ አውሬ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “አንድ አሳብ” ቢኖራቸውም ታላቁን “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ሊያሸንፉ አይችሉም። ‘የተመረጡትንና ከእርሱ ጋር በታማኝነት የጸኑትን’ ገና በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓንንም ቢሆን ሊያሸንፉ አይችሉም። እነዚህም ቢሆኑ በፍጹም አቋማቸው ጸንተው የሰይጣንን ክስ ሐሰተኛነት በማረጋገጥ ድል ይነሳሉ።—ሮሜ 8:37-39፤ ራእይ 12:10, 11

ጋለሞታይቱን ማጥፋት

15. መልአኩ ስለ አመንዝራዋ እንዲሁም አሥሩ ቀንዶችና አውሬው ለዚህች አመንዝራ ስላላቸው ዝንባሌና ስለሚወስዱባት እርምጃ ምን ብሎአል?

15 የአሥሩ ቀንዶች ጠላትነት የተቃጣው በአምላክ ሕዝቦች ላይ ብቻ አይደለም። መልአኩ አሁን የዮሐንስን ትኩረት ወደ ጋለሞታይቱ ዞር እንዲል ያደርጋል:- “አለኝም:- ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፣ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።”—ራእይ 17:15, 16

16. ታላቂቱ ባቢሎን የፖለቲካ መንግሥታት በሚነሱባት ጊዜ መከላከያና ድጋፍ ለማግኘት በውኃዎችዋ ልትተማመን የማትችለው ለምንድን ነው?

16 የጥንትዋ ባቢሎን ለመከላከያዋ ትመካ የነበረው በውኃዎችዋ እንደነበረ ሁሉ ታላቂቱ ባቢሎንም የምትመካው አባሎችዋ በሆኑት “ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም ቋንቋዎችም” ነው። መልአኩ ስለሚቀጥለው አስደንጋጭ እርምጃ ከመናገሩ በፊት ስለ እነዚህ ሕዝቦችና ወገኖች መናገሩ ተገቢ ነበር። የምድር ፖለቲካዊ መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በታላቅ ቁጣ ይነሳሉ። በዚያ ጊዜ እነዚህ “ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብና ቋንቋዎች” ምን ያደርጋሉ? የአምላክ ሕዝቦች የኤፍራጥስ ወንዝ ውኃ እንደሚደርቅ ታላቂቱ ባቢሎንን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። (ራእይ 16:12) ይህ ውኃ በመጨረሻ ላይ ፈጽሞ ይደርቃል። ይህች አስጸያፊ ባልቴት አመንዝራ ከፍተኛ ችግር በሚያጋጥማት ጊዜ ድጋፍ ሊሆናት አይችልም።ኢሳይያስ 44:27፤ ኤርምያስ 50:38፤ 51:36, 37

17. (ሀ) የታላቂቱ ባቢሎን ሀብት ሊያድናት የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) የታላቂቱ ባቢሎን ፍጻሜ ክብር ያለው የማይሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) አሥሩ ቀንዶች ወይም ብሔራት በተናጠል ከሚወስዱት እርምጃ በተጨማሪ የትኞቹ ሌሎች ኃይሎች ታላቂቱ ባቢሎንን ቦጫጭቆ በማጥፋቱ ድርጊት ተካፋይ ይሆናሉ?

17 የታላቂቱ ባቢሎን ሰፊ ብልጽግና ሊያድናት አይችልም። እንዲያውም ራእዩ እንደሚገልጸው አውሬውና አሥሩ ቀንዶች በጣም ተቆጥተው በሚጣሉአት ጊዜ የማዕረግ ልብስዋንና ጌጦችዋን ሁሉ ስለሚያወልቁባት ጥፋትዋን ሊያፋጥንባት ይችላል። ሀብትዋን ሁሉ ይዘርፉባታል። በአሳፋሪ ሁኔታ እውነተኛ ባሕርይዋ በግልጽ እንዲታይ ስለሚያደርጉ “ራቁትዋን ያደርጉአታል።” እንዴት ያለ ታላቅ ጥፋት ነው! ፍጻሜዋም ቢሆን የውርደት ፍጻሜ ይሆናል። “ሥጋዋንም” ሁሉ በልተው ባዶና ሕይወት የሌለበት አጽም ያደርጓታል። በመጨረሻም “በእሳት ያቀጥሉአታል።” ክብር ያለው ቀብር ሳይደረግላት በሽታ አስተላላፊ እንደሆነ ነገር በእሳት ትቃጠላለች። ታላቂቱን አመንዝራ የሚያጠፉት በአሥሩ ቀንዶች የተወከሉት ብሔራት ብቻ አይደሉም። “አውሬውም” ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በዚህ ከፍተኛ ጥፋት ይተባበራል። የሐሰት ሃይማኖት እንዲጠፋ ፈቃድ ይሰጣል። አሁንም እንኳን ቢሆን ከ190 ከሚበልጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት መካከል ብዙ መንግሥታት በድምፅ አሰጣጣቸው ለሃይማኖት፣ በተለይም ለሕዝበ ክርስትና ጥላቻ እንዳላቸው አሳይተዋል።

18. (ሀ) አሁንም እንኳን ቢሆን ብሔራት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲነሱ የሚያስችሉ ምን በቂ ምክንያቶች ታይተዋል? (ለ) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ አጠቃላይ ጥቃት የሚፈጸምበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

18 ብሔራቱ በቀድሞ ወዳጃቸው ላይ ይህን በሚያክል ቁጣ የተነሳሱት ለምንድን ነው? በቅርቡ ከተፈጸሙ ሁኔታዎች እንኳን በባቢሎናዊ ሃይማኖቶች ላይ ለመነሳት የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ተመልክተናል። እንደ ቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረትና ቻይና ባሉት አገሮች የተቋቋሙ መንግሥታት በወሰዱት የተቃውሞ እርምጃ ምክንያት ሃይማኖት ያለው ተጽዕኖና ተደማጭነት በጣም ቀንሶአል። በአውሮፓ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ክፍሎች በጣም የተስፋፋው ሃይማኖታዊ ግድየለሽነትና ጥርጣሬ አብያተ ክርስቲያናትን ባዶ አስቀርቶአቸዋል። ሃይማኖት ጨርሶ በድን ሆኖአል። በጣም ሰፊ የሆነው የካቶሊክ ግዛትም ቢሆን መሪዎቿ ሊገድቡት ባልቻሉት ዓመፅና ብጥብጥ እርስበርሱ ተለያይቶአል። ይሁን እንጂ ይህ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመው የመጨረሻ አጠቃላይ ጥፋት የሚመጣው አምላክ በዚህች ታላቅ አመንዝራ ላይ በሚያስፈጽመው ሊለወጥ የማይችል ፍርድ ምክንያት እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም።

የአምላክን አሳብ መፈጸም

19. (ሀ) ይሖዋ በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የሚያስፈጽመው ፍርድ በ607 ከዘአበ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ላይ ካስፈጸመው ፍርድ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከዘአበ ከ607 በኋላ የታየው የኢየሩሳሌም የመፈራረስና የባድማነት ሁኔታ ለዘመናችን ጥላ የሚሆነው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ ፍርዱን የሚያስፈጽመው እንዴት ነው? ይህን ለመረዳት ይሖዋ በጥንት ዘመን በከዳተኛ ሕዝቦቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ ልንመለከት እንችላለን። ስለነዚህ ሕዝቦቹ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፣ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፣ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፣ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ።” (ኤርምያስ 23:14) በ607 ከዘአበ ይሖዋ በናቡከደናፆር በመጠቀም ይህችን መንፈሳዊ አመንዝራ የሆነች ከተማ ‘ልብስዋ እንዲገፈፍ፣ የክብርዋ ጌጥ እንዲወሰድና ዕራቁትዋንና እርቃንዋን’ እንድትቀር አድርጎ ነበር። (ሕዝቅኤል 23:4, 26, 29) የዚያ ዘመንዋ ኢየሩሳሌም ለዛሬዋ ሕዝበ ክርስትና አምሳያ ነች። ዮሐንስ ቀደም ባሉት ራእዮች እንደተመለከተው ይሖዋ በሕዝበ ክርስትናም ሆነ በሌሎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ተመሳሳይ ቅጣት ይፈጽማል። ከዘአበ ከ607 በኋላ የነበረው የኢየሩሳሌም ባድማነትና ባዶነት ሃይማኖታዊቷ ሕዝበ ክርስትና ልብስዋን ተገፍፋና ጌጦችዋን ተነጥቃ በአሳፋሪ ሁኔታ ዕርቃንዋን ከቀረች በኋላ ምን እንደምትመስል ያመለክታል። የቀረው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍልም ቢሆን ከዚህ የተሻለ ዕጣ አያጋጥመውም።

20. (ሀ) ይሖዋ አሁንም እንደገና ፍርዱን ለማስፈጸም በሰብዓዊ ገዥዎች እንደሚጠቀም ዮሐንስ ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ “አሳብ” ምንድን ነው? (ሐ) ብሔራት የራሳቸውን “አንድ አሳብ” የሚፈጽሙት በምን መንገድ ነው? ይሁን እንጂ የሚፈጸመው የማን አሳብ ነው?

20 ይሖዋ ዳግመኛ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም በሰብዓዊ ገዥዎች ይጠቀማል። “እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።” (ራእይ 17:17) የአምላክ “አሳብ” ምንድን ነው? የታላቂቱ ባቢሎን አጥፊዎች ሙሉ በሙሉ ሊያጠፉአት እንዲችሉ ተጣምረው አንድ ሠራዊት እንዲሆኑ ነው። እርግጥ ገዢዎቹ እርሷን ለማጥቃት የሚነሳሱበት ምክንያት የራሳቸውን “አንድ አሳብ” ለመፈጸም ነው። በታላቂቱ ባቢሎን ላይ መነሳት ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያራምድላቸው ይመስላቸዋል። በግዛት ክልሎቻቸው ውስጥ የተደራጀ ሃይማኖት መኖሩ ሉዓላዊነታቸውን ሥጋት ላይ የሚጥል ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እርምጃቸውን ሁሉ የሚቆጣጠረውና የሚመራው ይሖዋ ነው። ለብዙ ዘመናት የቆየችውን አመንዝራ ጠላቱን በአንድ ምት ጨርሶ በመደምሰስ የእርሱን አሳብ ይፈጽማሉ።—ከ⁠ኤርምያስ 7:8-11, 34 ጋር አወዳድር።

21. ቀዩ አውሬ ታላቂቱ ባቢሎንን ለማጥፋት የሚያገለግል በመሆኑ ብሔራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምን ያደርጉለታል?

21 አዎ፣ ብሔራት ታላቂቱን ባቢሎን ለማጥፋት ቀዩን አውሬ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መሣሪያ አድርገው ይጠቀማሉ። ይህን እርምጃ የሚወስዱት ግን “አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ . . . መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው” ይሖዋ ስለሚያስገባ ነው እንጂ በራሳቸው ፈቃድ ተነሳስተው አይደለም። ጊዜው ሲደርስ ብሔራቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይገነዘባሉ። ያላቸውን ኃይልና ሥልጣን አውሰውት የሚያኝክና የሚያጠፋ ጥርስ እንዲኖረው በማድረግ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ተነስቶ “የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ” እንዲዋጋና እንዲያሸንፍ ያስችሉታል። በዚህ መንገድ ይህች ጥንታዊት አመንዝራ ሙሉ በሙሉ ትደመሰሳለች። አዎ፣ ፈጽማ ትጥፋ!

22. (ሀ) መልአኩ በ⁠ራእይ 17:18 ላይ የተናገረው የመደምደሚያ ምስክርነት ምን ያመለክታል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የምሥጢሩን መገለጥ እንዴት ተቀብለዋል?

22 መልአኩ በሐሰት ሃይማኖት ዓለም አቀፍ ግዛት ላይ የሚፈጸመው የይሖዋ የቅጣት ፍርድ የማይቀርና የተረጋገጠ መሆኑን አበክሮ ሲገልጽ ምስክርነቱን እንዲህ በማለት ያጠቃልላል። “ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።” (ራእይ 17:18) ታላቂቱ ባቢሎንም በብልጣሶር ዘመን እንደነበረችው ባቢሎን ‘በሚዛን ተመዝና ቀልላ ተገኝታለች።’ (ዳንኤል 5:27) የሚመጣባት ጥፋት ፈጣንና የማያዳግም ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች የታላቂቱ አመንዝራና የቀዩ አውሬ ምሥጢር ስለ መፈታቱ ምን ይሰማቸዋል? የይሖዋን የፍርድ ቀን በቅንዓት ያውጃሉ። ከልባቸው እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎችም “በጸጋ” ይመልሳሉ። (ቆላስይስ 4:5, 6፤ ራእይ 17:3, 7) የሚቀጥለው ምዕራፍ እንደሚያብራራልን ታላቂቱ አመንዝራ በምትጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ ለመዳን የሚፈልጉ ሁሉ አሁኑኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 252 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በተከታታይ የተነሱት ሰባት የዓለም ኃያል መንግሥታት

ግብፅ

አሦር

ባቢሎን

ሜዶ-ፋርስ

ግሪክ

ሮማ

አንግሎ-አሜሪካ

[በገጽ 254 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ንጉሥ ነው”

[በገጽ 255 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀርባቸውን ወደ በጉ አዙረው “ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ይሰጣሉ”

[በገጽ 257 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ሙሉ በሙሉ በመጥፋት የጥንቷን ኢየሩሳሌም እንድትመስል ይደረጋል