በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተዋጊው ንጉሥ አርማጌዶን ላይ ድል ይቀዳጃል

ተዋጊው ንጉሥ አርማጌዶን ላይ ድል ይቀዳጃል

ምዕራፍ 39

ተዋጊው ንጉሥ አርማጌዶን ላይ ድል ይቀዳጃል

ራእይ 13--ራእይ 19:11– 21

ርዕሰ ጉዳይ:- ኢየሱስ የሰይጣንን ሥርዓት ለማጥፋት የሰማይ ጭፍሮችን ያዘምታል

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ

1. አርማጌዶን ምንድን ነው? ወደዚያስ የሚመራው ነገር ምንድን ነው?

አርማጌዶን፣ ብዙዎችን የሚያስፈራ ቃል ነው። ጽድቅን ለሚወዱ ሰዎች ግን ይሖዋ በብሔራት ላይ የመጨረሻ ፍርዱን የሚፈጽምበትን ለረዥም ዘመናት ሲናፈቅ የቆየውን ቀን የሚያበስር ነው። “ሁሉን የሚችለው አምላክ የጦርነት ቀን” ነው እንጂ የሰው ጦርነት አይደለም። የምድር ገዥዎችን አምላክ የሚበቀልበት ጦርነት ነው። (ራእይ 16:14, 16፤ ሕዝቅኤል 25:17) ታላቁ መከራ በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ይጀምራል። ከዚያም በኋላ ቀዩ አውሬና አሥር ቀንዶቹ በሰይጣን አነሳሽነት የይሖዋን ሕዝቦች ለማጥቃት ይነሳሉ። ዲያብሎስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በአምላክ ሴት መሰል ድርጅት ላይ ስለሚቆጣ በወኪሎቹ በመጠቀም ከዘርዋ የቀሩትን እስከ መጨረሻው ለመውጋትና ፈጽሞ ለማጥፋት ቆርጦ ይነሳል። (ራእይ 12:17) ይህ ለሰይጣን የመጨረሻው ዕድል ይሆንለታል።

2. የማጎጉ ጎግ ማን ነው? ይሖዋስ ሕዝቡን እንዲያጠቃ የሚያነሳሳው እንዴት ነው?

2 ሰይጣን የሚፈጽመው የጭካኔ ጥቃት በ⁠ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ተገልጾአል። በዚህ መግለጫ ላይ ሰይጣን “የማጎጉ ጎግ” ተብሎ ተጠርቶአል። ይሖዋ በጎግ መንጋጋ ምሳሌያዊ ልጓም ያስገባበትና እጅግ ብዙ ከሆኑት ወታደራዊ ጭፍሮቹ ጋር ወደ ጥቃቱ ይመራዋል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? የአምላክ ምሥክሮች ምንም ዓይነት መከላከያ የሌላቸውና ‘ከአሕዛብ የተሰበሰበ ከብትና ዕቃንም ያገኘ፣ በምድርም መካከል የተቀመጠ’ ሕዝብ ሆነው እንዲታዩት ያደርጋል። አውሬውንና ምስሉን ለማምለክ እምቢተኛ የሆኑት እነዚህ ሕዝቦች ብቻ ስለሆኑ ‘በምድር መካከል’ ወይም በምድር መድረክ መካከለኛውን ቦታ ይዘው ነበር። መንፈሣዊ ጥንካሬያቸውና ብልጽግናቸው ጎግን ያስቆጣዋል። ስለዚህ ጎግና እጅግ ብዙ የሆኑት ወታደራዊ ጭፍሮቹ፣ ከባሕር የወጣው ባለ አሥር ቀንድ አውሬ ጭምር የአምላክን ሕዝቦች ለመዋጥ ይጎርፋሉ። ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን በተለየ ሁኔታ መለኮታዊ ጥበቃ ያገኛሉ።—ሕዝቅኤል 38:1, 4, 11, 12, 15፤ ራእይ 13:1

3. ይሖዋ የጎግን ወታደራዊ ኃይሎች የሚያስወግደው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ ጎግንና ጭፍሮቹን በሙሉ የሚያጠፋቸው እንዴት ነው? እናዳምጥ:- “በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፣ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” ይሁን እንጂ በዚህ የእርስ በርስ መተላለቅ ማንኛውም የኑክሌርም ሆነ ሌላ ዓይነት የጦር መሣሪያ ድል አድራጊ አይሆንም። ምክንያቱም ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎአል:- “በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፣ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። ታላቅ እሆናለሁ፣ እቀደስማለሁ፣ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፣ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደሆንሁ ያውቃሉ።”—ሕዝቅኤል 38:21-23፤ 39:11፤ ከ⁠ኢያሱ 10:8-14፤ ከ⁠መሳፍንት 7:19-22፤ ከ⁠2 ዜና 20:15, 22-24⁠ና ከ⁠ኢዮብ 38:22, 23 ጋር አወዳድር።

“የታመነና እውነተኛ” የተባለው

4. ዮሐንስ የውጊያ ልብስ የለበሰውን ኢየሱስን የገለጸው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ ሠይፍ ጠርቶአል። ይሁን እንጂ ይህን ሠይፍ የሚሰነዝረው ማን ነው? ወደ ራእይ መጽሐፍ ስንመለስ የዚህን ጥያቄ መልስ በአንድ ሌላ አስደናቂ ራእይ ውስጥ እናገኛለን። ዮሐንስ እየተመለከተ እንዳለ ሰማያት ተከፈቱና በጣም የሚያስደንቅና የሚያስፈራ ነገር ታየ። ኢየሱስ ክርስቶስ የውጊያ ልብስ ለብሶ ብቅ አለ። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፣ እነሆም አምባላይ ፈረስ፣ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፣ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፣ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ።”—ራእይ 19:11, 12ሀ

5, 6. (ሀ) “ነጩ ፈረስ” (ለ) “የታመነና እውነተኛ” የሚለው ስም (ሐ) ‘እሳት’ የመሰለው ዓይን (መ) “ብዙዎቹ ዘውዶች” ምን ያመለክታሉ?

5 ከዚህ ቀደም ስንል በአራቱ ፈረሰኞች ራእይ እንደተመለከትነው ይህ “ነጭ ፈረስ” የጽድቅ ውጊያ ተስማሚ ምሳሌ ነው። (ራእይ 6:2) ከአምላክ ልጆች መካከል ከዚህ ኃያል ተዋጊ ይበልጥ ጻድቅ የሆነ ማን ሊኖር ይችላል? “የታመነና እውነተኛ” ተብሎ ስለ ተጠራ “የታመነውና እውነተኛው ምስክር” ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊኖር አይችልም። (ራእይ 3:14) የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ ለማስፈጸም ሲል ውጊያ ያካሂዳል። ስለዚህ ይሖዋ የሾመው ፈራጅና “ኃያል አምላክ” የመሆን ሥልጣኑን በመጠቀም እርምጃ ይወስዳል። (ኢሳይያስ 9:6) ዓይኖቹ “እንደ እሳት ነበልባል” ስለሆኑ በጣም ያስፈራሉ። በጠላቶቹ እሳታማ ጥፋት ላይ አተኩረዋል።

6 ይህ ተዋጊ ንጉሥ በራሱ ላይ ዘውዶች ደፍቶአል። ዮሐንስ ከባሕር ሲወጣ የተመለከተው አውሬ አሥር ዘውዶች ነበሩት። ይህም በምድር መድረክ ላይ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆየውን ጊዜያዊ ገዥነቱን ያመለክታል። (ራእይ 13:1) ኢየሱስ ግን “ብዙ ዘውዶች” አሉት። እርሱ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ስለሆነ ክብራማ ገዥነቱ ተወዳዳሪና አቻ የለውም።—1 ጢሞቴዎስ 6:15

7. ኢየሱስ ምን ዓይነት ስም ተጽፎበታል?

7 የዮሐንስ መግለጫ ይቀጥላል:- “ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው።” (ራእይ 19:12ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ልጅ ኢየሱስ፣ አማኑኤል እና ሚካኤል በሚባሉ የተለያዩ ስሞች ይጠራዋል። ይህ ያልተገለጸልን “ስም” ግን ኢየሱስ በዚህ በጌታ ቀን የሚኖረውን ልዩ ማዕረግና መብት የሚያመለክት ይመስላል። (ከ⁠ራእይ 2:17 ጋር አወዳድር።) ኢሳይያስ ከ1914 ወዲህ ኢየሱስ የሚኖረውን ደረጃ ሲገልጽ “ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ [“መስፍን፣” NW] ይባላል” ብሎአል። (ኢሳይያስ 9:6) ሐዋርያው ጳውሎስም የኢየሱስን ስም ከሚሰጠው ከፍተኛ የአገልግሎት መብት ጋር በማዛመድ “እግዚአብሔር [ኢየሱስን] ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው። ይህም . . . ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው” ሲል ጽፎአል።—ፊልጵስዩስ 2:9, 10

8. የተጻፈውን ስም ሊያውቅ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው? በጣም ከፍተኛ ከሆኑት መብቶቹ አንዳንዶቹን ለማን ያካፍላል?

8 ኢየሱስ ለማንም ያልተሰጡ ልዩ የሆኑ መብቶች ተሰጥተውታል። እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ማዕረግ መቀበል ምን ትርጉም እንደሚኖረው ሊረዳ የሚችለው ከይሖዋ ሌላ ኢየሱስ ብቻ ነው። (ከማቴዎስ 11:27 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ከአምላክ ፍጥረታት መካከል ይህን ስም ሙሉ በሙሉ ሊረዳ የቻለ ኢየሱስ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከእነዚህ መብቶች አንዳንዶቹን ለሙሽራው ያካፍላል። በዚህም ምክንያት “ድል ለነሣው . . . አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ” የሚል ተስፋ ሰጥቶአል።—ራእይ 3:12

9. ኢየሱስ (ሀ) “ደም የተረጨበት መጎናጸፊያ” መልበሱ (ለ) “የአምላክ ቃል” ተብሎ መጠራቱ ምን ያመለክታል?

9 ዮሐንስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “በደምም የተረጨ ልብስ ተጎናጽፎአል፣ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።” (ራእይ 19:13) ይህ “ደም” የማን ነው? ለሰው ልጅ ሲባል የፈሰሰው የኢየሱስ ደመ ሕይወት ሊሆን ይችላል። (ራእይ 1:5) እዚህ ላይ ከሰፈሩት ሐሳቦች አንጻር ግን በይበልጥ የሚያመለክተው የይሖዋ ፍርድ በሚፈጸምበት ጊዜ የሚፈስሰውን የጠላቶች ደም ነው። ይህም የምድር ወይን ዘለላ የታጨደበትንና በአምላክ ቁጣ የወይን መጥመቂያ ‘ደሙ እስከ ፈረሶች ልጓም እስኪደርስ ድረስ’ የተረገጠበትን ቀደም ያለ ራእይ ያስታውሰናል። ይህም በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚገኘውን ታላቅ ድል የሚያመለክት ነበር። (ራእይ 14:18-20) በኢየሱስ መጎናጸፊያ ላይ የተፈናጠቀው ደምም በተመሳሳይ የሚጎናጸፈው ድል የተሟላና የማያዳግም እንደሚሆን ያመለክታል። (ከ⁠ኢሳይያስ 63:1-6 ጋር አወዳድር።) አሁን ደግሞ ኢየሱስ በሌላ ስም እንደተጠራ ዮሐንስ ይነግረናል። ይህ ስም ግን በሰፊው የታወቀ ነው። “የእግዚአብሔር ቃል” ተብሎአል። ተዋጊው ንጉሥ የይሖዋ ዋነኛ ቃል አቀባይና ለእውነት የሚሟገት ጠበቃ መሆኑን ያመለክታል።—ዮሐንስ 1:1፤ ራእይ 1:1

ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ ጦረኞች

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ በውጊያው የሚሰለፈው ብቻውን እንዳልሆነ ዮሐንስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ፈረሶቹ ነጭ መሆናቸውና ፈረሰኞቹ “ንጹሕ ነጭ የተልባ እግር ልብስ” መልበሳቸው ምን ያመለክታል? (ሐ) የሰማያዊው “ጭፍራ” አባሎች እነማን ናቸው?

10 በዚህ ውጊያ ኢየሱስ ብቻውን አይደለም። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።” (ራእይ 19:14) ፈረሶቹ “አምባላዮች” ወይም ነጮች መሆናቸው ውጊያው የጽድቅ ውጊያ መሆኑን ያመለክታል። የንጉሡ ፈረሰኞች ነጭ የተልባ እግር ልብስ መልበሳቸው ተገቢ ነው። የልብሱ ብሩሕነትና ንጣት በይሖዋ ፊት ያላቸውን ንጹሕ የጽድቅ አቋም ያመለክታል። ታዲያ እነዚህ ጭፍራዎች እነማን ናቸው? ቅዱሳን መላእክት እንደሚኖሩበት አያጠራጥርም። ቀደም ሲል በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ሚካኤልና መላእክቱ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ወርውረዋቸው ነበር። (ራእይ 12:7-9) ከዚህም በላይ ኢየሱስ የምድርን አሕዛብና ወገኖች ለመፍረድ ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ “መላእክቱ ሁሉ” ዙፋኑን አጅበው ያገለግሉታል። (ማቴዎስ 25:31, 32) ወሳኝ በሆነው በዚህ ውጊያ የአምላክ ፍርድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲፈጸም ኢየሱስ በመላእክቱ እንደሚታጀብ የተረጋገጠ ነው።

11 በዚህ ውጊያ ተካፋዮች የሚሆኑ ሌሎችም አሉ። ኢየሱስ ለትያጥሮን የላከውን መልእክት በተናገረ ጊዜ የሚከተለውን ቃል ገብቶ ነበር:- “ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፣ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፣ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ።” (ራእይ 2:26, 27) በሰማይ የሚገኙት የክርስቶስ ወንድሞች ጊዜው ሲደርስ ሕዝቦችንና ብሔሮችን በዚህ የብረት በትር እንደ እረኛ ሆነው በመምራቱ ሥራ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም።

12. (ሀ) በምድር ላይ የሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮች በአርማጌዶን በሚደረገው ውጊያ ይካፈላሉን? (ለ) በምድር ላይ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች በጦርነቱ ረገድ ምን አቋም ይኖራቸዋል?

12 በዚህች ምድር ላይ የሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮችስ? የዮሐንስ ክፍል በአርማጌዶን በሚደረገው ጦርነት ተካፋይ አይሆንም። ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ የአምልኮ ቤት ሲጎርፉ የቆዩት ታማኝ ተባባሪዎቻቸውም ቢሆኑ በውጊያው አይካፈሉም። እነዚህ ሰላማዊ ሰዎች ቀደም ሲሉ ሠይፋቸውን ማረሻ አድርገው ቀጥቅጠዋል። (ኢሳይያስ 2:2-4) ቢሆንም ጦርነቱ በተለያዩ መንገዶች ይነካቸዋል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በጎግና በጭፍሮቹ የሚጠቁት ምንም ዓይነት መከላከያ የሌላቸው የሚመስሉት የይሖዋ ሕዝቦች ናቸው። በሰማይ ባሉት ጭፍሮች የሚደገፈው የይሖዋ ተዋጊ ንጉሥ በእነዚህ ብሔራት ላይ አውዳሚ ጦርነት እንዲያካሂድ የሚያነሳሳው ይህ ጥቃት ነው። (ሕዝቅኤል 39:6, 7, 11፤ ከ⁠ዳንኤል 11:44 እስከ 12:1 ጋር አወዳድር።) የአምላክ ሕዝቦች በምድር ላይ ሆነው ሁኔታውን በትኩረት ይከታተላሉ። አርማጌዶን ለእነርሱ መዳን ይሆንላቸዋል። የይሖዋ ታላቅ የቅድስና ጦርነት የዓይን ምስክሮች ሆነው ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ይኖራሉ።

13. የይሖዋ ምሥክሮች ማንኛውንም መንግሥት እንደማይቃወሙ እንዴት እናውቃለን?

13 ታዲያ እንዲህ ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም መንግሥታት ይቃወማሉ ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ይከተላሉ። ይህ የአሁኑ ሥርዓት እስካልጠፋ ድረስ እነዚህ “የበላይ ባለ ሥልጣኖች” በሰብዓዊው ማኅበረሰብ ውስጥ መጠነኛ ሥርዓት እያስጠበቁ እንዲኖሩ አምላክ እንደፈቀደላቸው ይገነዘባሉ። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ግብር ይከፍላሉ፣ ሕጎችን ይታዘዛሉ፣ የትራፊክ ደንቦችን ያከብራሉ፣ ስለ ምዝገባ የሚወጡ ትእዛዞችን ያከብራሉ፣ ወዘተ። (ሮሜ 13:1, 6, 7) በተጨማሪም እውነተኛና ሐቀኛ በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠብቃሉ። ጎረቤቶቻቸውን ይወዳሉ፣ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ያለው ቤተሰብ ይገነባሉ፣ ልጆቻቸውም በምሳሌነት የሚጠቀሱ ዜጎች እንዲሆኑ ያሰለጥኑአቸዋል። ይህንንም በማድረግ “የቄሣርን ለቄሣር” ብቻ ሳይሆን “የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” ይሰጣሉ። (ሉቃስ 20:25፤ 1 ጴጥሮስ 2:13-17) የዚህም ዓለም መንግሥታዊ ሥልጣናት የሚቆዩት ለጊዜው ብቻ እንደሆነ የአምላክ ቃል ስለሚያመለክት የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት ሥር ለሚገኘው እውነተኛና የተሟላ ሕይወት ይዘጋጃሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) የይሖዋ ምሥክሮች የዚህን ዓለም ባለ ሥልጣኖች ለመገልበጥ የሚያደርጉት ነገር ባይኖርም በመንፈስ የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በአርማጌዶን ስለሚፈጽመው ፍርድ የሚናገረውን በታላቅ አክብሮትና ፍርሐት ይከታተላሉ።—ኢሳይያስ 26:20, 21፤ ዕብራውያን 12:28, 29

ወደ መጨረሻው ጦርነት!

14. ከኢየሱስ አፍ የሚወጣው ‘ረዥሙ ስለታም ሠይፍ’ የምን ምሳሌ ነው?

14 ኢየሱስ ውጊያውን የሚፈጽመው ከማን ባገኘው ሥልጣን ነው? ዮሐንስ ይነግረናል:- “አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል።” (ራእይ 19:15ሀ) ይህ ረዥም “ስለታም ሰይፍ” ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ አሻፈረኝ የሚሉ ሁሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ለመስጠት አምላክ የሰጠውን ሥልጣን ያመለክታል። (ራእይ 1:16፤ 2:16) ይህ ሥዕላዊ መግለጫ ከኢሳይያስ ቃል ጋር ይመሳሰላል። “አፌንም እንደተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፣ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል እንደተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል።” (ኢሳይያስ 49:2) እዚህ ላይ ኢሳይያስ የአምላክን ፍርድ ለሚናገረውና ዒላማውን እንደማይስት ፍላጻ ፍርዱን በትክክል ለሚያስፈጽመው ለኢየሱስ ጥላ ሆኖአል።

15. በዚህ ወቅት የሚጋለጠውና የሚፈረድበት ማን ነው? ይህስ የምን ነገር መጀመሪያ ይሆናል?

15 ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ላይ ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ይፈጽማል:- “በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም በመገለጡ [“በመገኘቱ፣” NW] የሚሽረው ዓመጸኛ ይገለጣል።” አዎ፣ የኢየሱስ መገኘት (በግሪክኛ ፓሩሲያ) የዓመጽ ሰው፣ ማለትም የሕዝበ ክርስትና የቀሳውስት ክፍል በመጋለጡና ፍርድ በመቀበሉ ከ1914 ጀምሮ ግልጽ ሆኖ ታውቆአል። የቀዩ አውሬ አሥር ቀንዶች ይህን ፍርድ በሚፈጽሙበትና ሕዝበ ክርስትናን ከቀሩት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች ጋር ጠራርገው በሚያጠፉበት ጊዜ ይህ መገኘቱ በይበልጥ ግልጽ ይሆናል። (2 ተሰሎንቄ 2:1-3, 8) ይህ በሚሆንበት ጊዜ ታላቁ መከራ ጀመረ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ቀሪው የሰይጣን ድርጅት ያዞራል። ይህም የሚሆነው “በአፉም በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል” በሚለው ትንቢት መሠረት ነው።—ኢሳይያስ 11:4

16. የመዝሙርና የኤርምያስ መጻሕፍት የይሖዋ ተዋጊ ንጉሥ የሚኖረውን ሚና የገለጹት እንዴት ነው?

16 ተዋጊው ንጉሥ በይሖዋ የተሾመ እንደመሆኑ መጠን በሕይወት ተጠብቀው የሚያልፉትንና የሚገደሉትን ሰዎች ይለያል። ይሖዋ ለዚህ ልጁ በትንቢት ሲናገር የምድር ገዥዎችን “በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፣ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ” ብሎአል። ኤርምያስ ስለ እነዚህ ምግባረ ብልሹ የመንግሥት መሪዎችና ስለ ተባባሪዎቻቸው ሲናገር እንዲህ ብሎአል:- “ትታረዱና ትበተኑ ዘንድ ቀናችሁ ደርሶአልና፣ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች አልቅሱ፣ ጩኹም። እናንተ የመንጋ አውራዎች በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ።” እነዚህ ገዥዎች ለዚህ ክፉ ዓለም ምንም ያህል ተፈላጊዎች መስለው ቢታዩ የንጉሡ የብረት በትር አንድ ጊዜ ብቻ ሲያርፍባቸው እንደውድ የሸክላ ዕቃ ስብርብራቸው ይወጣል። ዳዊት ስለ ጌታ ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው ይሆናል። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፣ በጠላቶችህም መካከል ግዛ። እግዚአብሔር [“ይሖዋ” NW] በቀኝህ ነገሥታትን በቁጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፣ ሬሳዎችንም ያበዛል፣ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል።”—መዝሙር 2:9, 12፤ 83:17, 18፤ 110:1, 2, 5, 6፤ ኤርምያስ 25:34

17. (ሀ) ዮሐንስ ተዋጊው ንጉሥ የሚወስደውን የግድያ እርምጃ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ቁጣ ምን ያህል ከፍተኛ ጥፋት በብሔራት ላይ እንደሚያመጣ የሚገልጹ አንዳንድ ትንቢቶችን ግለጽ።

17 ይህ ኃያል ተዋጊ ንጉሥ በሚቀጥለውም የራእይ ትዕይንት ውስጥ በድጋሚ ታይቶአል። “እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል።” (ራእይ 19:15ለ) ዮሐንስ ቀደም ባለው ራእይ “የእግዚአብሔር የብርቱ ቁጣ ወይን መጥመቂያ” ሲረገጥ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 14:18-20) ኢሳይያስም ክፉ አድራጊዎች ስለሚገደሉበት የወይን መጥመቂያ ተናግሮአል። ሌሎች ነቢያትም የአምላክ የቁጣ ቀን ለብሔራት ሁሉ ከፍተኛ የእልቂት ቀን እንደሚሆን ተናግረዋል።—ኢሳይያስ 24:1-6፤ 63:1-4፤ ኤርምያስ 25:30-33፤ ዳንኤል 2:44፤ ሶፎንያስ 3:8፤ ዘካርያስ 14:3, 12, 13፤ ራእይ 6:15-17

18. ይሖዋ በብሔራት ላይ ስለመፍረዱ ነቢዩ ኢዩኤል ምን ተናግሮአል?

18 ነቢዩ ኢዩኤል የወይን መጥመቂያን ይሖዋ አሕዛብን ሁሉ ለመፍረድ ከሚነሳበት ቀን ጋር አዛምዶአል። ለተባባሪው ፈራጅ ለኢየሱስና ለሰማያዊው ሠራዊት የሚከተለውን ትዕዛዝ የሚሰጠው ይሖዋ እንደሆነ አያጠራጥርም። “መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ። መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ። ክፋታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈስሶአል። የእግዚአብሔር [“የይሖዋ” NW] ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል። ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮሃል። በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል። ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ። እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”—ኢዩኤል 3:12-17

19. (ሀ) 1 ጴጥሮስ 4:17 ላይ የተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) በኢየሱስ መጎናጸፊያ ላይ የተጻፈው ምን የሚል ስም ነው? ይህስ ስም ትክክለኛ ስም የሆነው ለምንድን ነው?

19 ይህ ቀን በእውነትም ለዓመፀኞቹ ብሔራትና ሰዎች የጥፋት ቀን ይሆናል። ይሖዋንና ተዋጊ ንጉሡን መጠጊያቸውና መሸሸጊያቸው ላደረጉ ግን የትልቅ እፎይታ ቀን ይሆናል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) በ1918 ከአምላክ ቤት የጀመረው ፍርድ ቀጥሎ መጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ይህም በ⁠1 ጴጥሮስ 4:17 ላይ “ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስገኛል። ታላቁ ድል አድራጊ ተዋጊ የወይኑን መጥመቂያ እስከ መጨረሻው ድረስ ይረግጣል። በእርግጥ ዮሐንስ “በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው” ሲል የተናገረለት ባለታላቅ ክብር ገዥ እርሱ መሆኑን ያረጋግጣል። (ራእይ 19:16) ከማንኛውም ምድራዊ ገዥ፣ ከማንኛውም ሰብዓዊ ንጉሥና ጌታ በጣም፣ እጅግ በጣም የበለጠ ኃይል ያለው መሆኑን ያረጋግጣል። ግርማውና ክብሩ እጅግ ያንጸባርቃል። “ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት [“ትሕትና” NW] ስለ ጽድቅም” ወደፊት ገስግሶ ለዝንተ ዓለም ድል ነስቶአል! (መዝሙር 45:4) ደም በተረጨበት ልብሱ ላይ እውነተኛነቱን ያረጋገጠለት የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ የሰጠው ስም ተጽፎበታል።

ታላቁ የእግዚአብሔር እራት

20. ዮሐንስ ‘የእግዚአብሔርን ታላቅ እራት’ የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ የትኛውን ቀደም ያለ ተመሳሳይ ትንቢት ያስታውሰናል?

20 በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የጎግ ሠራዊት ከጠፋ በኋላ አእዋፍና የዱር አራዊት ለድግስ ተጋብዘው ነበር። የይሖዋን ጠላቶች አስከሬን በልተው የምድሪቱን ገጽ ከበድን ያጸዳሉ። (ሕዝቅኤል 39:11, 17-20) ዮሐንስ ቀጥሎ የሚነግረን ቃል ይህንኑ ትንቢት ሥዕላዊ በሆነ መንገድ በድጋሚ ይገልጽልናል:- “አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፣ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ:- መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።”—ራእይ 19:17, 18

21. (ሀ) መልአኩ ‘በፀሐይ ውስጥ መቆሙ’ (ለ) የሞቱት በመሬት ላይ ሳይቀበሩ መጣላቸው (ሐ) አስከሬናቸው በምድር ላይ የሚጣለው ሰዎች ዝርዝር (መ) ‘ታላቁ የእግዚአብሔር እራት’ ምን ያመለክታሉ?

21 መልአኩ የአዕዋፉን ትኩረት ለመሳብ በጣም አመቺ በሆነበት “በፀሐይ ውስጥ ቆሞ” ነበር። በተዋጊው ንጉሥና በሰማያዊ ጭፍሮቹ የሚገደሉትን ሰዎች ሥጋ እስኪበቃቸው እንዲበሉ ይጋብዛቸዋል። የእነዚህ ሰዎች አስከሬን በምድር ላይ ተጥሎ የሚቆይ መሆኑ በሕዝብ ፊት ተዋርደው የሚገደሉ መሆናቸውን ያመለክታል። በጥንት ዘመን ትኖር እንደነበረችው ኤልዛቤል ክብር ያለው ቀብር አያገኙም። (2 ነገሥት 9:36, 37) አስከሬናቸው በምድር ላይ ተጥለው ከሚቀሩት ሰዎች መካከል ነገሥታት፣ የጦር አዛዦች፣ ኃያላን ሰዎች፣ ነፃ የሆኑና ባሮች በዝርዝር መጠቀሳቸው የጥፋቱ መጠን ምን ያህል ሰፊ መሆኑን ያመለክታል። በጥፋቱ የማይነካ የኅብረተሰብ ክፍል አይኖርም። ይሖዋን ተቃውሞ የተነሳው ዓመፀኛ ዓለም እስከ መጨረሻው ርዝራዥ ድረስ ይጠፋል። ከዚያ በኋላ ግራ የተጋቡ ሰዎች ዕረፍት ያጣ ተነዋዋጭ ባሕር አይኖርም። (ራእይ 21:1) ወፎቹን ለግብዣ የጠራው ይሖዋ ስለሆነ ይህ “ታላቁ የእግዚአብሔር እራት” ነው።

22. ዮሐንስ የመጨረሻውን ጦርነት ሂደት አጠቃልሎ የገለጸው እንዴት ነው?

22 ዮሐንስ የጦርነቱን የመጨረሻ ሂደት ሲያጠቃልል እንዲህ ይላል:- “በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ። አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፣ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።”—ራእይ 19:19-21

23. (ሀ) “ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” አርማጌዶን ላይ የሚደረገው በምን መንገድ ነው? (ለ) የምድር ነገሥታት ሳይቀበሉ የቀሩት የትኛውን ማስጠንቀቂያ ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስከትልባቸዋል?

23 ስድስተኛው የይሖዋ ቁጣ ጽዋ ከፈሰሰ በኋላ “የምድርና የመላው ዓለም ነገሥታት” በአጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳ አማካኝነት “ሁሉን ወደሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” እንደሚሰበሰቡ ዮሐንስ ተናግሮ ነበር። ይህ ጦርነት የሚደረገው አርማጌዶን ላይ ነው። አርማጌዶን ይሖዋ ፍርዱን እንዲያስፈጽም የሚያስገድደው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ነው እንጂ ቃል በቃል አንድ የተወሰነ ቦታ አይደለም። (ራእይ 16:12, 14, 16 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን) አሁን ደግሞ ዮሐንስ የጦር ግንባሩን ሁኔታ ተመለከተ። በአንድ በኩል “የምድር ነገሥታትና ጭፍራዎቻቸው” በአምላክ ላይ ተሰልፈዋል። ይሖዋ ላነገሠው ንጉሥ ለመገዛት እምቢተኞች በመሆን አንገታቸውን አደንድነዋል። በሚከተለው በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረ መልእክት ማስጠንቀቂያ ስለሰጣቸው በፍርድ አጉዳይነት ሊወቀስ አይችልም። “ይሖዋ እንዳይቆጣ በመንገዱም እንዳትጠፉ ልጁን ሳሙት።” ራሳቸውን ለክርስቶስ አገዛዝ ስላላስገዙ መሞት ይገባቸዋል።—መዝሙር 2:12 NW

24. (ሀ) በአውሬውና በሐሰተኛው ነቢይ ላይ የሚፈጸመው የትኛው ፍርድ ነው? “በሕይወት ሳሉ” የተባለውስ እንዴት ነው? (ለ) የእሳቱ ባሕር ምሳሌያዊ ባሕር መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው?

24 የሰይጣንን ፖለቲካዊ ድርጅት የሚያመለክተው ከባሕር የወጣ ባለ ሰባት ራስና ባለ አሥር ቀንድ አውሬ ዳግመኛ ሊታይ በማይችልበት ሁኔታ ይጠፋል። ከእርሱም ጋር ሐሰተኛው ነቢይ ማለትም ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት አብሮት ይጠፋል። (ራእይ 13:1, 11-13፤ 16:13) “በሕይወት ሳሉ” ወይም አንድ ሆነው የአምላክን ሕዝቦች ተቃውመው በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ “ወደ እሳት ባሕር” ይጣላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ቃል በቃል የእሳት ባሕር ነውን? አውሬውም ሆነ ሐሰተኛው ነቢይ ቃል በቃል አራዊት እንዳልሆኑ ሁሉ የእሳቱም ባሕር ቃል በቃል የእሳት ባሕር አይደለም። ሙሉ በሙሉ ለመጨረሻ ጊዜ መጥፋትን፣ መመለሻ የሌለበትን ሥፍራ ያመለክታል። በኋላም ሞትና ሔድስ እንዲሁም ዲያብሎስ የሚወረወሩት ወደዚህ ሥፍራ ነው። (ራእይ 20:10, 14) ክፉዎች የዘላለም ሥቃይ የሚቀበሉበት ገሃነመ እሳት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ምክንያቱም እንዲህ ያለ ሥፍራ መኖሩን እንኳን ይሖዋ ይጸየፈዋል።—ኤርምያስ 19:5፤ 32:35፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 16

25. (ሀ) በፈረሱ ላይ በተቀመጠው “ረዥም ሰይፍ የሚገደሉት” እነማን ናቸው? (ለ) “ከሚገደሉት” መካከል ትንሣኤ የሚያገኙ ይኖራሉ ብለን ለማሰብ እንችላለንን?

25 የመንግሥት ክፍል ባይሆኑም ይህን ብልሹ የሰው ልጆች ዓለም የሙጥኝ ያሉ ሁሉ “በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ።” ኢየሱስ ሞት የሚገባቸው እንደሆኑ አድርጎ ይፈርድባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ እሳት ባሕር እንደሚጣሉ አለመነገሩ ትንሣኤ ይኖራቸዋል ብለን እንድናስብ ምክንያት ይሆነናልን? በዚያ ጊዜ በይሖዋ ፈራጅ የሚገደሉት ትንሣኤ እንደሚኖራቸው የተገለጸበት አንድም ቦታ አናገኝም። ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው “በጎች” ያልሆኑት ሁሉ ‘ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው የዘላለም እሳት’ ይጣላሉ። ይህም ማለት ወደ ‘ዘላለም ጥፋት’ ይጣላሉ ማለት ነው። (ማቴዎስ 25:33, 41, 46) ይህ እርምጃ ‘አምላክ የለሽ ሰዎች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ የመጨረሻ ክንውን ይሆናል።—2 ጴጥሮስ 3:7፤ ናሆም 1:2, 7-9፤ ሚልክያስ 4:1

26. የአርማጌዶንን ውጤት በአጭሩ ግለጽ።

26 በዚህ መንገድ መላው የሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ይጠፋል። የፖለቲካ ገዥዎች “የቀደመው ሰማይ” አልፎአል። ባለፉት መቶ ዘመናት ሰይጣን ሲገነባ የኖረው ሊናወጥ የማይችል የሚመስለው “ምድር” በዚያን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወድሞአል። ይሖዋን የሚቃወመው ክፉ የሰው ልጆች “ባሕር” ጠፍቶአል። (ራእይ 21:1፤ 2 ጴጥሮስ 3:10) ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሰይጣን ያዘጋጀለት ፍርድ ምንድን ነው? ዮሐንስ ከዚህ ቀጥሎ ይነግረናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]