በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት

ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት

ምዕራፍ 2

ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት

ቅዱሳን ጽሑፎችን መተርጎም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተሰውረው የተቀመጡት ምሥጢሮች ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ለብዙ ዘመናት ግራ ሲያጋቡ ቆይተዋል። እነዚህ ምሥጢሮች አምላክ በወሰነው ጊዜ መገለጽ ነበረባቸው። ግን የሚገለጹት እንዴት፣ መቼና ለማን ነው? የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ትርጉሞቹን የሚያሳውቀው የአምላክ መንፈስ ብቻ ነው። (ራእይ 1:3) እነዚህ ቅዱስ ምሥጢሮች የሚገለጹት በምድር ላይ ለሚገኙት የአምላክ ቀናተኛ ባሮች ነው። ይህም ፍርዱን እንዲያሳውቁ ያበረታቸዋል። (ማቴዎስ 13:10, 11) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ማብራሪያዎች ስህተት ሊኖርባቸው አይችልም አንልም። በጥንት ዘመን ይኖር እንደነበረው እንደ ዮሴፍ “የሚተረጉም እግዚአብሔር አይደለምን?” እንላለን። (ዘፍጥረት 40:8) ቢሆንም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ሁሉ በዚህ መቅሰፍት በበዛበት በእኛ ዘመን አስደናቂው መለኮታዊ ትንቢት እንዴት እየተፈጸመ እንዳለ በማሳየት ከጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ እንደሚሆን አጥብቀን እናምናለን።

1. ትልቁ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል” ይላል። (መክብብ 7:8) ይሖዋ ስሙን ለመቀደስ ያለውን ታላቅ ዓላማ በፍጥረቶቹ ሁሉ ፊት እንዴት እንደሚፈጽም የምናነበው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ነው። አምላክ ቀደም ባለው ነቢዩ አማካኝነት “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] መሆኔን ያውቃሉ” በማለት ደጋግሞ ገልጾአል።—ሕዝቅኤል 25:17፤ 38:23

2. የራእይ መጽሐፍ ቀደም ካሉት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጋር ሆኖ ምን ዓይነት አጥጋቢ እውቀት ይሰጠናል?

2 የራእይ መጽሐፍ የነገሮችን በድል መፈጸም እንደገለጸልን ሁሉ የነገሮች አጀማመርም በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጻሕፍት ተገልጾልናል። ይህንን ቅዱስ መዝገብ በመመርመር ስለጉዳዩ በጥልቅ ለመረዳትና የአምላክን ዓላማ አጠቃላይ መልክ ለማስተዋል እንችላለን። ይህም ትልቅ እርካታ የሚያስገኝልን ይሆናል። ከዚህም በላይ የሰው ልጅ ከሚጠብቀው አስደናቂ ተስፋ ተካፋዮች እንድንሆን የሚያስችለንን እርምጃ እንድንወስድ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል። (መዝሙር 145:16, 20) እዚህ ላይ በሰው ልጆች ሁሉ ፊት ስለተደቀነው ዋነኛ ጥያቄና አምላክም ይህን ጥያቄ ለመፍታት ስላወጣው ዓላማ በሚገባ ለማስተዋል እንድንችል የመላውን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክትና ሐሳቦቹ የተመሠረቱባቸውን ከበስተኋላ ያሉ ሁኔታዎች መመርመር የተገባ ይመስላል።

3. ለመላው መጽሐፍ ቅዱስ ለራእይም መጽሐፍ ጭምር አጠቃላይ መልእክት የሆነውን ነገር የሚገልጽልን የትኛው የዘፍጥረት መጽሐፍ ትንቢት ነው?

3 የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ የሆነው ዘፍጥረት “በመጀመሪያ” ብሎ ይጀምርና ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች፣ የምድራዊ ፍጥረቱ መደምደሚያ ስለሆነው ስለ ሰው አፈጣጠር ጭምር ይገልጽልናል። በተጨማሪም የዘፍጥረት መጽሐፍ አምላክ ራሱ ከ6,000 ዓመታት በፊት በኤደን ገነት የተናገረውን የመጀመሪያውን መለኮታዊ ትንቢት መዝግቦልናል። ትንቢቱ ከመነገሩ በፊት የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን በአንድ እባብ መሣሪያነት ተታልላ ነበር። ሔዋንም በተራዋ ባልዋ አዳም “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” በመብላት በአመጽዋ እንዲተባበራት አግባብታዋለች። አምላክ በኃጢአተኞቹ ባልና ሚስት ላይ የፍርድ ውሣኔውን ሲበይን ለእባቡ የሚከተለውን አለ:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ የእርሷ ዘርና የአንተ ዘርም ዘወትር ጠላቶች እንደሆኑ ይኖራሉ። የእርስዋ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል፤ አንተም የእርስዋን ዘር ተረከዝ ትነክሳለህ።” (ዘፍጥረት 1:1፤ 2:17፤ 3:1-6, 14, 15 የ1980 ትርጉም) የመላው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የራእይም መጽሐፍ ጭምር አጠቃላይ መልእክት በዚህ ትንቢት ተገልጾአል።

4. (ሀ) አምላክ የመጀመሪያውን ትንቢት ከተናገረ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ላይ ምን ደረሰባቸው? (ለ) የመጀመሪያውን ትንቢት በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ? መልሶቹንስ ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4 አምላክ ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ ወዲያውኑ የመጀመሪያ ወላጆቻችንን ከኤደን አስወጣቸው። ከዚያ በኋላ በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም። የቀረውን ዕድሜያቸውን ጠፍ በሆነችው ያልለማች ምድር መግፋት ነበረባቸው። የሞትን ፍርድ እንደተሸከሙ የኃጢአት ቀንበር የተጫናቸው ልጆች ወለዱ። (ዘፍጥረት 3:23 እስከ 4:1፤ ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ የኤደናዊው ትንቢት ትርጉም ምንድን ነው? ትንቢቱስ የሚመለከተው እነማንን ነው? ከራእይስ ጋር የሚዛመደው በምን መንገድ ነው? በዚህ ዘመን ለምንኖረውስ ምን መልእክት ይዞልናል? ይሖዋ ይህንን ትንቢት እንዲናገር ምክንያት የሆነው አሳዛኝ ድርጊት ካመጣብን መጥፎ ውጤት ለመገላገል ከፈለግን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ በጣም ያስፈልገናል።

የድራማው ዋነኛ ተዋናዮች

5. እባቡ ሔዋንን ካሳታት በኋላ በአምላክ ሉዓላዊነትና ስም ረገድ ምን ሁኔታ ተፈጠረ? ይህስ አወዛጋቢ ጉዳይ የሚፈታው እንዴት ነው?

5 የ⁠ዘፍጥረት 3:15 ትንቢት የተነገረው ሔዋን ትዕዛዙን ብትጥስ እንደማትሞትና እንዲያውም ነፃ የሆነች አምላክ እንደምትሆን በመናገር ለዋሸው እባብ ነበር። እባቡ በዚህ መንገድ ይሖዋን ውሸታም አደረገው። በተጨማሪም ሰዎች የአምላክን ሉዓላዊ አገዛዝ አንቀበልም በማለት የተሻለ ኑሮ ሊኖሩ እንደሚችሉ አመለከተ። (ዘፍጥረት 3:1-5) የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት አጠያያቂ ሆነ፣ መልካም ስሙም ጎደፈ። የራእይ መጽሐፍ ጻድቁ ፈራጅ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ አገዛዝ በመጠቀም እንዴት ሉዓላዊነቱን እንደሚያረጋግጥና እንዴት ከስሙ ላይ ማንኛውንም ነቀፌታ እንደሚያስወግድ ይገልጽልናል።—ራእይ 12:10፤ 14:7

6. ሔዋንን በእባብ አማካኝነት ያነጋገራት ማን እንደሆነ የራእይ መጽሐፍ የሚገልጽልን እንዴት ነው?

6 ይህ “እባብ” የሚለው ቃል በቀጥታ አንድን እባብ የሚያመለክት ነውን? በፍጹም አይደለም። ራእይ ከእባቡ በስተጀርባ ሆኖ የተናገረው ወራዳ መንፈሣዊ ፍጡር ማን እንደሆነ ያሳውቀናል። እርሱም “ታላቁም ዘንዶ . . . ሰዎችን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው።” “ሔዋንን በተንኮሉ” ያታለላትም እርሱ ነው።—ራእይ 12:9 የ1980 ትርጉም፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3

7. በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የምትገኝ ሴት መሆኗን የሚያመለክተን ምንድን ነው?

7 ዘፍጥረት 3:15 ቀጥሎ ስለ “ሴቲቱ” ይናገራል። ይህች ሴት ሔዋን ናትን? ሔዋን እንደዚያ መስሎአት ሊሆን ይችላል። (ከዘፍጥረት 4:1 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ሔዋን የሞተችው ከ5,000 ዓመታት በፊት ስለሆነ በእርስዋና በሰይጣን መካከል ለረዥም ዘመን የቆየ ጠላትነት ሊኖር አልቻለም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ያናገረው እባብ የማይታይ መንፈሣዊ ፍጡር ስለነበረ ሴቲቱም የመንፈሳዊው ዓለም ክፍል መሆን እንደሚገባት መገመት እንችላለን። ይህች ምሳሌያዊት ሴት የይሖዋ መንፈሣዊ ፍጥረታት ሰማያዊ ድርጅት እንደሆነች ራእይ 12:1, 2 ያረጋግጥልናል።—በተጨማሪም ኢሳይያስ 54:1, 5, 13 ተመልከት።

እርስ በርሳቸው የሚጻረሩ ሁለት ዘሮች

8. ስለ ሁለት ዘሮች ስለተነገረው ጉዳይ ለማወቅ የጠለቀ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

8 ቀጥሎም በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ ሁለት ዘሮች ተጠቅሰዋል። እነዚህ ዘሮች ስለ ትክክለኛው የምድር የበላይ ገዥነት ከተነሳው ጥያቄ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ስለሆኑ ማንነታቸውን ለማወቅ የጠለቀ ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። ይህ ሽማግሌዎችም ሆንን ወጣቶች ሁላችንንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። ከእነዚህ ሁለት ዘሮች መካከል የምትደግፈው የትኛውን ነው?

9. የእባቡ ዘር እነማንን የሚጨምር መሆን ይኖርበታል?

9 በመጀመሪያ የተጠቀሰው የእባቡ ዘር ወይም ልጅ ነው። ይህ ዘር ምንድን ነው? ሰይጣንን በአመፁ የተባበሩትንና በመጨረሻም ከእርሱ ጋር ወደ ምድር አካባቢ የተጣሉትን መንፈሳዊ ፍጡሮች እንደሚጨምር የተረጋገጠ ነው። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ወይም ብዔል ዜቡል “የአጋንንት ገዥ” ስለሆነ የማይታየው ድርጅቱ የተገነባው በእነርሱ እንደሆነ ግልጽ ነው።—ማርቆስ 3:22፤ ኤፌሶን 6:12

10. መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎቹን የሰይጣን ዘሮች ለይቶ የሚያሳውቃቸው እንዴት ነው?

10 ከዚህም በላይ ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ፈቃድ ልታደርጉ ትወዳላችሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 8:44) እነዚህም ሃይማኖታዊ መሪዎች የአምላክን ልጅ ኢየሱስን በመቃወማቸው የሰይጣን ልጆች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ምሳሌያዊ አባታቸውን የሚያገለግሉ የሰይጣን ዘር ክፍል ሆነዋል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሌሎች ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ የሰይጣንን ፈቃድ በማድረግ፣ በተለይም የኢየሱስን ደቀመዛሙርት በመቃወምና በማሳደድ የሰይጣን ዘር ክፍል መሆናቸውን አስመስክረዋል። እነዚህ የሰው ልጆች አንድ ላይ ተጠቃለው በምድር ላይ የሚገኘው የሰይጣን የሚታይ ድርጅት አባሎች ናቸው ሊባሉ ይችላሉ።—ዮሐንስ 15:20ን፤ 16:33ን፤ 17:15ን ተመልከት።

የሴቲቱ ዘር ታወቀ

11. ባለፉት መቶ ዘመናት አምላክ ስለ ሴቲቱ ዘር ምን ነገር ገልጾ ነበር?

11 በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት በመጨረሻ የሚጠቅሰው የሴቲቱን ዘር ነው። ሰይጣን የራሱን ዘር በሚያስፋፋበት ጊዜ ይሖዋም “ሴቲቱ” ወይም ሚስት መሰል ሰማያዊ ድርጅቱ ዘር እንድታፈራ ያዘጋጃት ነበር። ይሖዋ 4,000 ለሚያክሉ ዓመታት ታዛዥ ለሆኑና ፈሪሐ አምላክ ላላቸው ሰዎች ስለ ዘሩ አመጣጥ ተከታታይ መግለጫ ሲሰጣቸው ቆይቶአል። (ኢሳይያስ 46:9, 10) በዚህም ምክንያት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ዘሩ ከራሳቸው የዘር ግንድ እንደሚመጣ በተሰጣቸው ተስፋ ላይ እምነታቸውን ሊገነቡ ችለዋል። (ዘፍጥረት 22:15-18፤ 26:4፤ 28:14) ሰይጣንና ወኪሎቹም እነዚህን ሰዎች በእምነታቸው በመጽናታቸው ምክንያት አሳደዋቸዋል።—ዕብራውያን 11:1, 2, 32-38

12. (ሀ) የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል የመጣው መቼና ከምን ሁኔታ ጋር ነው? (ለ) ኢየሱስ የተቀባው ለምን ዓላማ ነበር?

12 በመጨረሻም በ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ራሱን አቀረበና ተጠመቀ። በዚያ ሥፍራ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ ወለደው። “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል አወጀለት። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስ በሰማይ ካለው የአምላክ መንፈሳዊ ድርጅት የተላከ መሆኑ ታወቀ። በተጨማሪም በይሖዋ ስም የሚገዛውን አስተዳደር ወደ ምድር የሚመልሰው ሰማያዊ መንግሥት እጩ ንጉሥ ሆኖ ተቀብቶአል። ይህም መንግሥት ስለ አገዛዝና ስለ ሉዓላዊነት ለተነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ያስገኛል። (ራእይ 11:15) ስለዚህ የሴቲቱ ዋነኛ ዘርና ተስፋ የተደረገው መሲሕ ኢየሱስ ነው።—ከ⁠ገላትያ 3:16⁠ና ከ⁠ዳንኤል 9:25 ጋር አወዳድር።

13, 14. (ሀ) የሴቲቱ ዘር አንድ ሰው ብቻ እንደማይሆን ማወቃችን ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ከሰው ልጆች መካከል ሁለተኛ ደረጃ የሴቲቱ ዘሮች እንዲሆኑ የመረጣቸው ስንት ናቸው? የየትኛውስ ድርጅት አባሎች ሆነዋል? (ሐ) ከዘሩ ክፍሎች ጋር በመተባባር የሚያገለግሉትስ እነማን ጭምር ናቸው?

13 ታዲያ የሴቲቱ ዘር የሚሆነው አንድ ታዋቂ ግለሰብ ብቻ ነውን? የሰይጣንስ ዘር አንድ ብቻ ነውን? የሰይጣን ዘር የክፉ መላእክትን ሠራዊትና አምላክን የማያከብሩ ሰዎችን እንደሚያጠቃልል መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ስለዚህ አምላክ ከመሲሐዊው ዘር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎችና ካህናት የሚሆኑ 144,000 ፍጹም አቋም ጠባቂ የሆኑ ሰዎችን ከሰው ልጆች መካከል ለመምረጥ ዓላማ እንዳለው ማወቃችን ሊያስገርመን አይገባም። የራእይ መጽሐፍ ዲያብሎስ በአምላክ ሴት መሰል ድርጅት ላይ ባለው ጠላትነት ተነሳስቶ “ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ” ያለው ስለእነዚህ ሰዎች ሲናገር ነበር።—ራእይ 12:17፤ 14:1-4

14 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የኢየሱስ ወንድሞች እንደሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾአል። ስለሆነም የጋራ አባትና እናት አላቸው ማለት ነው። (ዕብራውያን 2:11) አባታቸው ይሖዋ አምላክ ነው። እናታቸው ደግሞ የአምላክ ሚስት መሰል ሰማያዊ ድርጅት የሆነችው ‘ሴቲቱ’ መሆን ይኖርባታል። ክርስቶስ ኢየሱስ ዋነኛው ዘር ሲሆን እነዚህ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ዘሮች ናቸው። ይህ በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች ጉባኤ በሰማይ በሚገኘው ሴት መሰል ድርጅት ሥር የሚያገለግል ምድራዊ የሚታይ የአምላክ ድርጅት ሆኖአል። ከሙታን ሲነሱም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በሰማይ ይተባበራሉ። (ሮሜ 8:14-17፤ ገላትያ 3:16, 29) ከአሕዛብ የተውጣጡት በሚልዮን የሚቆጠሩ በግ መሰል ሰዎች የዘሩ ክፍል ባይሆኑም በምድር ከሚገኘው የአምላክ ድርጅት ጋር በአንድነት ለማገልገል በመሰብሰብ ላይ ናቸው። አንተ የእነዚህ “ሌሎች በጎች” ክፍል ነህን? ከሆንክ በገነቲቱ ምድር ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ አለህ።—ዮሐንስ 10:16፤ 17:1-3

ጠላትነቱ እንዴት እንደተስፋፋ

15. (ሀ) የሰይጣን ሰብዓዊና መላእክታዊ ዘሮች እንዴት እየጨመሩ እንደመጡ ግለጽ። (ለ) በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜ የሰይጣን ዘሮች ምን ሆኑ?

15 የሰይጣን ሰብዓዊ ዘር መገለጥ የጀመረው ቀደም ባለው የሰው ልጅ የታሪክ ዘመን ነው። ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያ ሰብዓዊ ልጅ የነበረው ቃየን ‘ከክፉው ስለነበረ’ ወንድሙን አቤልን ገድሎአል። (1 ዮሐንስ 3:12) ከዚያም ቆየት ብሎ ሔኖክ ስለ ይሖዋ መምጣት ሲናገር “ከብዙ ሺህ ቅዱሳን ጋር ይመጣል። የሚመጣውም በሰው ሁሉ ላይ ሊፈርድ ዓመፀኞችንና ኃጢአተኞችን ሁሉ በዓመፃ ሥራቸው ሁሉና በእግዚአብሔር ላይ በተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ ሊወቅስ ነው” ብሎአል። (ይሁዳ 14, 15 የ1980 ትርጉም) ከዚህም በላይ ዓመፀኛ መላእክት ከሰይጣን ጋር ተባብረው የዘሩ ክፍል ሆነዋል። እነዚህ ክፉ መላእክት ሥጋዊ አካል ለብሰው የሰዎችን ሴቶች ልጆች ለማግባት ሲሉ በሰማይ የሚገኘውን ‘ትክክለኛ መኖሪያቸውን ትተዋል።’ የሰውና የመላእክት ዲቃላ የሆኑ ግዙፍና ጠበኛ ልጆች አፈሩ። በዚያ ዘመን የነበረው ዓለም በክፋትና በዓመፅ ስለተሞላ አምላክ በውኃ መጥለቅለቅ አጠፋው። ከጥፋቱ የተረፉት ሰብዓዊ ሥጋ ለባሾች ኖህና ቤተሰቦቹ ብቻ ነበሩ። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የገቡ አጋንንት የሆኑት ዓመፀኛ መላእክት ጥፋት የተፈረደባቸውን ሚስቶቻቸውንና ዲቃላ ልጆቻቸውን ትተው ለመሄድ ተገደዱ። ለብሰውት የነበረውን ሥጋ ጥለው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። በዚያም ሆነው አምላክ በሰይጣንና በዘሮቹ ላይ የሚያመጣውን ፍርድ ይጠባበቃሉ።—ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:4-12፤ 7:21-23፤ 2 ጴጥሮስ 2:4, 5

16. (ሀ) ከጥፋት ውኃ በኋላ የትኛው ጨካኝ ገዥ ተነሳ? የሰይጣን ዘር ክፍል መሆኑን ያሳየውስ እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የባቢሎንን ግንብ ለመስራት የተነሱትን ሰዎች ዕቅድ ያጨናገፈው እንዴት ነው?

16 ከታላቁ የጥፋት ውኃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ላይ ናምሩድ የተባለ ጨካኝ ሰው ተነሳ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” እንደነበረ የሚናገርለት ይህ ሰው የእባቡ ዘር ክፍል ሆነ። ልክ እንደ ሰይጣን ያለ የዓመፅ መንፈስ በማሳየት ይሖዋ አምላክ የሰው ዘር በመላዋ ምድር ላይ በመሰራጨት ምድርን እንዲሞላት የነበረውን ዓላማ ተቃውሞ የባቤልን ወይም የባቢሎንን ከተማ ሠራ። አምላክ የግንበኞቹን ሥራ ባያጨናግፍ ኖሮ የባቢሎን እምብርት የሚሆን ‘ጫፉ እስከ ሰማይ የሚደርስ’ ግንብ ለመሥራት ታቅዶ ነበር። ቋንቋቸውን በመዘበራረቅ በምድር ሁሉ ላይ እንዲበታተኑ አደረጋቸው። ባቢሎን ግን ሳትፈርስ እንድትቆይ ፈቀደ።—ዘፍጥረት 9:1፤ 10:8-12 NW፤ ዘፍጥረት 11:1-9

የፖለቲካ ኃይሎች ብቅ አሉ

17. የሰው ዘር እየተባዛ ሲሄድ የትኛው የተበላሸ የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ገጽታ መታየት ጀመረ? በዚህስ ምክንያት የትኞቹ ትላልቅ ግዛቶች ተቋቋሙ?

17 በባቢሎን የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙ የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ገጽታዎች ታይተው ነበር። ከእነዚህም አንዱ ፖለቲካዊ ባሕርይ ነበረው። የሰው ልጆች እየበዙ በሄዱ መጠን የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ ሌሎች ሰዎች የናምሩድን ምሳሌ በመከተል የገዥነት ሥልጣን ጨብጠዋል። ሰው ሰውን ለጉዳቱ መግዛት ጀመረ። (መክብብ 8:9) ለምሳሌ ያህል በአብርሃም ዘመን ሰዶም፣ ገሞራና በዚያ አካባቢ የነበሩ ከተሞች ከሰናኦርና ከሌሎች ሩቅ አገሮች በመጡ ነገሥታት ግዛት ሥር ወድቀው ነበር። (ዘፍጥረት 14:1-4) ቆየት ብሎም ከፍተኛ ወታደራዊና ድርጅታዊ ችሎታ የነበራቸው ሰዎች ከፍተኛ ብልጽግናና ክብር የሚያስገኙላቸው ታላላቅ ግዛቶችን ለራሳቸው አቋቁመዋል። ከእነዚህም አንዳንዶቹ የግብፅ፣ የአሦር፣ የባቢሎን፣ የሜዶ ፋርስ፣ የግሪክና የሮም መንግሥታት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።

18. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ለፖለቲካ መሪዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ አላቸው? (ለ) የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ዓላማ ያስፈጸሙት እንዴት ነው? (ሐ) ብዙ ገዥዎች የእባቡ ዘር ክፍሎች መሆናቸውን ያስመሰከሩት እንዴት ነው?

18 ይሖዋ የእነዚህን የፖለቲካ ኃይሎች መኖር ታግሦአል። ሕዝቦቹም በእነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባሉ አገሮች ውስጥ በኖሩበት ጊዜ ሁሉ ገደብ ያለው ታዛዥነት አሳይተዋል። (ሮሜ 13:1, 2) እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች የአምላክን ዓላማዎች ለማስፈጸም ወይም ሕዝቡን ለመጠበቅ አገልግለዋል። (ዕዝራ 1:1-4፤ 7:12-26፤ ሥራ 25:11, 12፤ ራእይ 12:15, 16) ይሁን እንጂ ብዙ የፖለቲካ ገዥዎች እውነተኛውን አምልኮ ክፉኛ ተቃውመዋል። በዚህም የእባቡ ዘር ክፍል እንደሆኑ አሳይተዋል።—1 ዮሐንስ 5:19

19. የዓለም ኃያል መንግሥታት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት እንዴት ነው?

19 የሰው አገዛዝ በአብዛኛው ለእኛ ለሰው ልጆች ደስታ ሊያስገኝልን ወይም ችግሮቻችንን ሊፈታልን አልቻለም። የሰው ልጆች የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን እንዲሞክሩ ይሖዋ ፈቅዶአል። ይሁን እንጂ መንግሥታት በሰዎች ላይ የፈጸሙትን የአስተዳደር በደል አይደግፈውም። (ምሳሌ 22:22, 23) የራእይ መጽሐፍ የዓለም ኃይላት የአንድ ትዕቢተኛና አስፈሪ አውሬ ክፍል እንደሆኑ ይገልጻል።—ራእይ 13:1, 2

ስግብግብ የንግድ ከበርቴዎች

20, 21. “ከወታደራዊ አዛዦች” እና “ኃያላን ሰዎች” ጋር የሰይጣን ክፉ ዘሮች ክፍል መሆን የሚገባው የትኛው ሁለተኛ ቡድን ነው? ለምንስ?

20 ከፖለቲካ ገዥዎች ጋር በቅርብ የሚተባበሩ በሐቅ የማይሠሩ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎችም መታየት ጀመሩ። ከጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሾች ተቆፍረው የወጡት ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዚያ ዘመን ሰዎች ሲቸገሩ አጋጣሚውን ትርፍ ለማጋበስ መጠቀም በጣም የተለመደ ነገር ሆኖ ነበር። የዓለም ነጋዴዎች እስከ ዘመናችን ድረስ የስስት ትርፍ ለማካበት ሲጥሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት በብዙ አገሮች አብዛኛው ሕዝብ በችግር ሲማቅቅ ጥቂቶቹ በጣም ሀብታም ሆነዋል። በዚህ የኢንዱስትሪ ዘመን ውስጥ ነጋዴዎችና ባለ ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ የሆኑትን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጨምሮ ብዙ ዲያብሎሳዊ የጥፋት መሣሪያዎችን ለፖለቲካ ኃይላት በማቅረብ ብዙ ትርፍ አጋብሰዋል። እነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎችና ሌሎች መሰሎቻቸው “ከሻለቃዎችና ከኃያላን” ጋር ተደምረው የሰይጣን ክፉ ዘር ክፍሎች መሆን ይገባቸዋል። እነዚህ ሁሉ አምላክና ክርስቶስ የጥፋት ፍርድ የሚበይኑበት ምድራዊ ድርጅት አባሎች ናቸው።—ራእይ 19:18

21 ከተበላሸው ፖለቲካና ስግብግብ ከሆነው የንግድ ሥርዓት በተጨማሪ የአምላክን ፍርድ መቀበል የሚገባው ሦስተኛ የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ክፍልም አለ። ይህ ድርጅት ምንድን ነው? የራእይ መጽሐፍ ስለዚህ እውቅ ምድር አቀፍ ድርጅት የሚናገረው ሊያስገርማችሁ ይችላል።

ታላቂቱ ባቢሎን

22. በጥንትዋ ባቢሎን ምን ዓይነት ሃይማኖት ተፈጠረ?

22 የጥንትዋ ባቢሎን የታነጸችው ለፖለቲካ ጉዳዮች ብቻ አልነበረም። ይህች ከተማ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በመቃወም የተቆረቆረች ስለነበረች የሃይማኖትም ጉዳይ ነበረባት። በእውነትም የጥንትዋ ባቢሎን የጣዖት አምልኮ መፍለቂያ ምንጭ ሆና ነበር። ቀሳውስትዋ የሰው ነፍስ ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርዋን እንደምትቀጥል፣ ከሞት በኋላ ያለው ኑሮ ዘላለማዊ ሥቃይና ጭንቀት የተሞላበትና በአጋንንት የሚተዳደር መሆኑንና የመሳሰሉትን አምላክን የሚያዋርዱ ትምህርቶች ያስተምሩ ነበር። ፍጥረታትና ለቁጥር የሚያታክቱ ወንድና ሴት አማልክት እንዲመለኩ ይቀሰቅሱ ነበር። ምድርና የሰው ልጆች እንዴት እንደተገኙ ለማስረዳት ተረቶችንና አፈታሪኮችን ፈልስፈዋል። ብዙ ልጆች ለመውለድ፣ አዝርዕት እንዲያድጉ ለማስቻልና በጦርነት ድል ለማግኘት ይረዳሉ የሚሉአቸውን ወራዳና አስጸያፊ አምልኮታዊ ሥርዓቶች ይፈጽሙና መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ነበር።

23. (ሀ) ሕዝቦቹ ከባቢሎን በሚበተኑበት ጊዜ ምን ነገር ይዘው ተሰራጩ? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) የራእይ መጽሐፍ ምድር አቀፉን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በምን ስም ይጠራዋል? (ሐ) የሐሰት ሃይማኖት ያለማቋረጥ ከምን ጋር ሲዋጋ ቆይቶአል?

23 ከባቢሎን የተነሱ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድኖች በምድር ላይ ሲበተኑ ባቢሎናዊ ሃይማኖታቸውንም ይዘው ተሰራጩ። በዚህ መንገድ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በሩቅ ምሥራቅና በደቡብ ባሕሮች ይኖሩ በነበሩ የጥንት ነዋሪዎች መካከል የጥንቱን ባቢሎን የሚመስሉ እምነቶችና የአምልኮ ሥርዓቶች ተስፋፉ። ከእነዚህም እምነቶች ብዙዎቹ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይተዋል። ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ ዓለም አቀፍ የሆነውን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ታላቂቱ ባቢሎን የተባለች ከተማ ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው። (ራእይ ምዕራፍ 17 እና 18) የሐሰት ሃይማኖት በተዘራበት አገር ሁሉ ጨቋኝ ቀሳውስትን፣ አጉል እምነቶችን፣ ድንቁርናንና ብልግናን አብቅሎአል። የሐሰት ሃይማኖት የሰይጣን ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሎአል። ታላቂቱ ባቢሎን የጽንፈ ዓለሙን ጌታ የይሖዋን እውነተኛ አምልኮ በቁርጠኝነት ስትዋጋ ቆይታለች።

24. (ሀ) እባቡ የሴቲቱን ዘር ተረከዝ ለማቁሰል የቻለው እንዴት ነው? (ለ) የሴቲቱ ዘር መቁሰል የተረከዝ ቁስል ብቻ እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው?

24 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ክፍል የነበሩት ጸሐፊዎችና ፈሪሣውያን የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ወኪል የሆነውን በማሳደዳቸውና በመጨረሻም በመግደላቸው ታላቅ ነቀፌታ የሚገባቸው የእባቡ ዘር ሆነዋል። በዚህ መንገድ እባቡ የዘሩን ‘ተረከዝ ሊነክስ’ ችሎአል። (ዘፍጥረት 3:15፤ ዮሐንስ 8:39-44፤ ሥራ 3:12, 15) የተረከዝ ቁስል ብቻ እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው? ይህ ቁስል ያሳመመው ለጥቂት ጊዜና በዚህ ምድር ላይ ብቻ ስለሆነ ነው። ይሖዋ ኢየሱስን በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነስቶ ወደ መንፈሣዊ ሕይወት ከፍ ስላደረገው ዘላቂ ጉዳት አላስከተለበትም።—ሥራ 2:32, 33፤ 1 ጴጥሮስ 3:18

25. (ሀ) በክብር ከፍ የተደረገው ኢየሱስ በሰይጣንና በመላእክቱ ላይ እርምጃ የወሰደው እንዴት ነው? (ለ) የሰይጣን ምድራዊ ዘር የሚወገደው መቼ ነው? (ሐ) የአምላክ ሴት ዘር እባቡን ሰይጣንን “ጭንቅላቱን” ሲቀጠቅጠው ምን ይሆናል?

25 በክብር ከፍ የተደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ቀኝ ተቀምጦ በአምላክ ጠላቶች ላይ በመፍረድ ላይ ነው። ቀደም ብሎ በሰይጣንና በመላእክቱ ላይ እርምጃ በመውሰድ ወደ ምድር ስለጣላቸው በዚሁ አካባቢ ብቻ እንዲወሰኑ አድርጎአል። በዘመናችን ሥቃይና መከራ የበዛው በዚህ ምክንያት ነው። (ራእይ 12:9, 12) አምላክ በታላቂቱ ባቢሎንና በምድር ላይ በሚገኙት በሁሉም የሰይጣን ድርጅት ክፍሎች ላይ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ በትንቢት እንደተነገረው የሰይጣን ምድራዊ ዘሮች ይወገዳሉ። በመጨረሻም የአምላክ ሴት ዘር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የጥንት እባብ፣ ሰይጣን ዲያብሎስን ‘ራሱን ይቀጠቅጠዋል።’ ይህም ሲፈጸም በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ፈጽሞ ይወገዳል፣ ለዘላለምም ይጠፋል።—ሮሜ 16:20

26. በራእይ ውስጥ የተገለጸውን ትንቢት መመርመር በጣም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

26 ይህ ሁሉ የሚፈጸመው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ የተገለጸልን ይህ ጉዳይ ነው። በታላላቅ ምሳሌዎችና ምልክቶች በደመቁ ተከታታይ ራእዮች ተገልጾልናል። ይህንን ኃያል ትንቢት በጉጉት እንመርምር። የራእይን ቃላት ብንሰማና ብንጠብቅ እውነትም ደስተኞች ነን። ይህንንም በማድረጋችን የልዑል ጌታ የይሖዋን ስም በማስከበር ሥራ እንካፈላለን። ዘላለማዊ በረከቱንም እንወርሳለን። እባክህ፣ መጽሐፉን ማንበብህን ቀጥልና የተማርካቸውን ነገሮች በሥራ ለማዋል ተጣጣር። በዚህ የሰው ልጆች ታሪክ የመጨረሻ ወቅት ደህንነት ሊያስገኝልህ ይችላልና።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጥንት ኪዩኒፎርም የንግድ ሰነዶች

በጀምስ ቢ ፕሪቻርድ የተዘጋጀው የቅርብ ምሥራቅ የጥንት ሰነዶች የተባለው መጽሐፍ በጥንት ባቢሎናውያን ዘመን ሐሙራቢ ያወጣቸውን 300 የሚያክሉ ሕጎች ይዘረዝራል። እነዚህ ሕጎች በዚያ ዘመኑ የንግድ ዓለም የተስፋፋውን አጭበርባሪነት መቆጣጠር አስፈልጎ እንደነበረ ያመለክታሉ። አንድ ምሳሌ እንውሰድ። “አንድ ጌታ ብር ወይም ወርቅ፣ ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ወይም በሬ፣ በግ ወይም አህያ ወይም ማንኛውንም ነገር ከሌላው ጌታ ልጅ ወይም ባሪያ ምስክር በሌለበትና ውለታ ሳይፈርም ቢገዛ ወይም አደራ ቢቀበል የገዛው ወይም አደራ የተቀበለው ጌታ ሌባ ነውና ይገደል።”