በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ

ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ

ምዕራፍ 36

ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ

ራእይ 12--ራእይ 18:1 እስከ 19:10

ርዕሰ ጉዳይ:- የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀትና ጥፋት፤ የበጉ ሰርግ ስለመከናወኑ ማስታወቂያ ተነገረ

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከ1919 ጀምሮ ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ እስካለው ጊዜ ድረስ

1. የታላቁ መከራ መክፈቻ የሚሆነው ምንድን ነው?

የታላቂቱ ባቢሎን አጠፋፍ ድንገተኛ፣ አስደንጋጭና አውዳሚ ይሆናል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከፍተኛ እልቂት ካስከተሉት ታላላቅ ክንውኖች አንዱ በመሆን ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ላልሆነውና ወደ ፊትም ለማይሆነው ታላቅ መከራ’ መክፈቻ ይሆናል።—ማቴዎስ 24:21

2. የፖለቲካ ግዛቶች ሲነሱና ሲወድቁ የቆዩ ቢሆንም እስከ ዛሬ ጸንቶ የቆየው ምን ዓይነት ግዛት ነው?

2 የሐሰት ሃይማኖት ከተቋቋመ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ይሖዋን ተቃውሞ በመነሳት ሰዎች የባቤልን ግንብ እንዲሠሩ ካደረገው የደም ጥማት ከነበረው፣ ከናምሩድ ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ ኖሮአል። ይሖዋ የእነዚህን ዓመፀኛ ሰዎች ልሳን ዘባርቆ በምድር ሁሉ እንዲበተኑ ባደረገ ጊዜ የባቢሎንም የሐሰት ሃይማኖት አብሮአቸው በምድር በሙሉ ተሰራጨ። (ዘፍጥረት 10:8-10፤ 11:4-9) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ግዛቶች ሲነሱም ሲወድቁም ኖረዋል። ባቢሎናዊ ሃይማኖት ግን እስከ አሁን ሳይጠፋ እንዳለ ቀጥሏል። ብዙ ዓይነት ቅርጽና መልክ በመያዝ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ወይም ትንቢት የተነገረለት ታላቂቱ ባቢሎን ሆኖአል። የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የጥንቱ ባቢሎናዊ ትምህርትና የክህደት “ክርስትና” መሠረተ ትምህርት ጥምረት ውጤት የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ናት። ታላቂቱ ባቢሎን እጅግ በጣም ረዥም የሆነ ታሪክ ስላላት ብዙ ሰዎች የመጥፋትዋን ሐሳብ ለመቀበል ያዳግታቸዋል።

3. የራእይ መጽሐፍ የሐሰት ሃይማኖትን መጥፋት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

3 በዚህም ምክንያት የራእይ መጽሐፍ መጀመሪያ ስለ ሐሰት ሃይማኖት ውድቀትና በኋላ ደግሞ ወደ ፍጹም ጥፋት ስለሚያደርሱአት ክንውኖች ሁለት ዝርዝር መግለጫዎችን በመስጠት ስለሚደርስባት ጥፋት አስተማማኝ ማረጋገጫ መስጠቱ ተገቢ ነው። ቀደም ብለን እርስዋ “ታላቂቱ ጋለሞታ” ስለመሆንዋና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ ወዳጆችዋ ስለሚያደርሱባት ጥፋት ተመልክተን ነበር። (ራእይ 17:1, 15, 16) አሁን ደግሞ በሌላ ራእይ የጥንትዋ ባቢሎን አምሳያ በሆነች በአንዲት ከተማ እንደተመሰለች እንመለከታለን።

ታላቂቱ ባቢሎን ትወድቃለች

4. (ሀ) ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ራእይ ምንድን ነው? (ለ) የመልአኩን ማንነት ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው? እርሱስ የታላቂቱን ባቢሎን መውደቅ ማስታወቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ታሪኩን ይገልጽልናል:- “ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፣ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ:- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች” ብሎ ጮኸ። (ራእይ 18:1, 2ሀ) ዮሐንስ ይህን የመልአኩን ማስታወቂያ ሲሰማ ሁለተኛ ጊዜው ነው። (ራእይ 14:8 ተመልከት።) በዚህ ጊዜ ግን የሰማዩ መልአክ ክብር ምድርን በሙሉ ሲያበራ ስለታየና ግርማው ከፍተኛ እንደሆነ ስለተገለጸ ለማስታወቂያው ከፍተኛ ክብደት ተሰጥቶአል። ታዲያ ይህ መልአክ ማን ሊሆን ይችላል? ነቢዩ ሕዝቅኤል ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ስለ አንድ ሰማያዊ ራእይ ሲጽፍ “ከክብሩም [ከይሖዋ] የተነሣ ምድር ታበራ ነበር” ብሎአል። (ሕዝቅኤል 43:2) ከይሖዋ ክብር ጋር ሊወዳደር በሚችል ክብር ሊያበራ የሚችል መልአክ የይሖዋ “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” የሆነው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው። (ዕብራውያን 1:3) በ1914 ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ተባባሪ ንጉሥና ፈራጅ በመሆን በምድር ላይ በሥልጣኑ ሲጠቀም ቆይቷል። በዚህ ምክንያት የታላቂቱ ባቢሎንን ውድቀት የሚያሳውቀው መልአክ ኢየሱስ መሆኑ ተገቢ ነበር።

5. (ሀ) መልአኩ የታላቂቱ ባቢሎንን መውደቅ ለማወጅ የሚጠቀመው በማን ነው? (ለ) ‘የአምላክ ቤት’ ነን በሚሉት ላይ ፍርድ በሚጀምርበት ጊዜ ሕዝበ ክርስትና ምን ይደርስባታል?

5 ይህ ታላቅ ሥልጣን የተሰጠው መልአክ እንዲህ ያለውን አስደናቂ ዜና ለሰው ልጆች ለማሰማት የሚጠቀመው በማን ነው? ታላቂቱ ባቢሎን በመውደቅዋ ምክንያት ነፃ በወጡት ቅቡዓን ቀሪዎች ወይም በዮሐንስ ክፍል አባላት እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። እነዚህ ቀሪዎች ከ1914 እስከ 1918 በነበረው ጊዜ ከታላቂቱ ባቢሎን ብዙ መከራ ደርሶባቸው ነበር። በ1918 ግን ጌታ ይሖዋና ‘የአብርሃም ቃል ኪዳን መልእክተኛ’ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “በአምላክ ቤት ላይ” ወይም ክርስቲያን ነን ይሉ በነበሩት ሕዝቦች ላይ ፍርድ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ከዳተኛዋ ሕዝበ ክርስትና ለፍርድ ቀረበች። (ሚልክያስ 3:1፤ 1 ጴጥሮስ 4:17) በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ተጨማልቃ የነበረችበት የደም አፍሳሽነት ወንጀል፣ የይሖዋን ታማኝ ምሥክሮች በማሳደድ ድርጊት መካፈልዋና ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችዋ በዚህ ፍርድ ቀን ከቅጣት ለመዳን አልረዳትም። ማንኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አልቻለም።—ከ⁠ኢሳይያስ 13:1-9 ጋር አወዳድር።

6. ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 ወድቃለች ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ስለዚህ በ1919 ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃ ስለነበረ የአምላክ ሕዝቦች ነጻ ወጥተው መንፈሳዊ ብልጽግና በሚያገኙበት መንፈሣዊ ርስታቸው እንደ አንድ ቀን በሚቆጠር አጭር ጊዜ ውስጥ የሚቋቋሙበት መንገድ ተከፍቶላቸው ነበር። (ኢሳይያስ 66:8) በዚህ ዓመት ታላቁ ዳርዮስ ይሖዋ አምላክና ታላቁ ቂሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐሰት ሃይማኖት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንዳይኖረው የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርገው ነበር። ከዚያ በኋላ ይሖዋን ከማገልገል፣ አመንዝራይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ለጥፋት የተወሰነች መሆንዋንና የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ጊዜ በጣም ቅርብ መሆኑን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ከማሳወቅ ምንም ሊያግዳቸው አልቻለም።—ኢሳይያስ 45:1-4፤ ዳንኤል 5:30, 31

7. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 ባትጠፋም ይሖዋ እንዴት ተመልክቶአታል? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 በወደቀች ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ምን አገኙ?

7 እርግጥ ነው ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 አልጠፋችም። የጥንትዋ የባቢሎን ከተማም ብትሆን በፋርሳዊው ቂሮስ ሠራዊት እጅ በወደቀችበት ዓመት በ539 ከዘአበ አልጠፋችም። በይሖዋ አመለካከት ግን ይህች ድርጅት ወድቃለች። የተፈረደባት ድርጅት ስለሆነች ጥፋትዋን ብቻ ትጠብቃለች። ስለዚህ የሐሰት ሃይማኖት የይሖዋን ሕዝቦች በምርኮ ይዛ ልታቆይ አትችልም። (ከ⁠ሉቃስ 9:59, 60 ጋር አወዳድር።) እነዚህ የይሖዋ ሕዝቦች ከምርኮ የተለቀቁት መንፈሣዊ ምግብ በጊዜው እያቀረቡ የጌታ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ነበር። ‘ጥሩ አድርጋችኋል’ የሚል የፍርድ ብይን ስለተሰጣቸው በይሖዋ ሥራ በትጋት የሚካፈሉበት ሹመት ተሰጥቶአቸዋል።—ማቴዎስ 24:45-47፤ 25:21, 23፤ ሥራ 1:8

8. ኢሳይያስ 21:8, 9 ላይ የተጠቀሰው ጉበኛ ወይም ጠባቂ ምን ሁኔታ እንደሚኖር አውጆ ነበር? በዛሬው ጊዜ የዚህ ጉበኛ ጥላ የሆነው ማን ነው?

8 ይሖዋ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ ስለሆነው ስለዚህ ክንውን በሌሎች ነቢያት አማካኝነት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢሳይያስ እንደ አንበሳ ባለ ድፍረት “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፣ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክዬአለሁ” በማለት ስለ ተናገረ ጉበኛ ወይም ጠባቂ ገልጾ ነበር። ይህ ጠባቂ ያስተዋለውና እንደ አንበሳ ባለ ድፍረት ያወጀው ክንውን ምን ነበር? “ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።” (ኢሳይያስ 21:8, 9) ይህ ጠባቂ በዘመናችን ዓይኑን በሰፊው ከፍቶ ሁኔታዎችን የሚከታተለውን የዮሐንስ ክፍል ያመለክታል። ይህ ጠባቂ ዛሬ በመጠበቂያ ግንብ እና በሌሎች ቲኦክራቲካዊ ጽሑፎች እየተጠቀመ ባቢሎን ወድቃለች የሚለውን ዜና በሰፊው በማሰራጨት ላይ ላለው ከፍተኛ ሁኔታ ነቅቶ ለሚሠራው የዮሐንስ ክፍል ጥላ ነው።

የታላቂቱ ባቢሎን ማሽቆልቆል

9, 10. (ሀ) ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወዲህ የባቢሎናዊ ሃይማኖት ተጽዕኖ የቀነሰው እንዴት ነው? (ለ) ኃያሉ መልአክ ታላቂቱ ባቢሎን የደረሰባትን ውድቀት የገለጸው እንዴት ነው?

9 በ539 ከዘአበ የደረሰው የጥንትዋ ባቢሎን ውድቀት ለበርካታ ዓመታት ለቀጠለው ማሽቆልቆልና በመጨረሻ ለደረሰባት ፍጹም ባድማነት መጀመሪያ ነበር። በተመሳሳይም የባቢሎናዊው ሃይማኖት ተጽዕኖ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስገራሚ ሁኔታ ሲያሽቆለቁል ቆይቶአል። በጃፓን አገር የሺንቶዎች የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ እየከሰመ መጥቶአል። በቻይና ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሹመት የሚቆጣጠረው መንግሥቱ ነው። በሰሜን አውሮፓ በሚገኙት ፕሮቴስታንት አገሮች አብዛኞቹ ሰዎች ለሃይማኖት ግድየለሾች ሆነዋል። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በውስጥዋ በተነሳው መከፋፈልና መለያየት ምክንያት ምድር አቀፍ ግዛትዋ ተዳክሞአል።—ከ⁠ማርቆስ 3:24-26 ጋር አወዳድር።

10 እነዚህ አዝማሚያዎች በሙሉ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ለሚመጣው ወታደራዊ ጥቃት መንገድ የሚጠርገው ‘የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ’ ክፍል ናቸው። ሊቀ ጳጳሳቱ በጥቅምት ወር 1986 ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ኪሣራ ስለደረሰባት “ዳግመኛ ለማኝ መሆን ሊኖርባት ነው” ሲሉ ማስታወቃቸው የዚህን ድርቀት መጠን የሚያሳይ ነው። (ራእይ 16:12) በተለይ ከ1919 ወዲህ ታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ባድማ መሆንዋ በገሐድ መታየት ጀምሮአል። ይህም ሁኔታ ኃያሉ መልአክ እንደሚከተለው በማለት በተናገረው መሠረት ተፈጽሞአል። “የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፣ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች።” (ራእይ 18:2ለ) በቅርቡ ታላቂቱ ባቢሎን በዘመናዊቷ ኢራቅ ምድር እንደምትገኘው የጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሽና ፍጹም ባድማ ትሆናለች።—በተጨማሪ ኤርምያስ 50:25-28ን ተመልከት።

11. ታላቂቱ ባቢሎን “የአጋንንት ማደሪያ” እና ‘የእርኩስ ትንፋሽና የእርኩሳን ወፎች መዘዋወሪያ’ የሆነችው በምን መንገድ ነው?

11 እዚህ ላይ “አጋንንት” የሚለው ቃል ኢሳይያስ ስለወደቀችው ባቢሎን ሲገልጽ የጠቀሰውን “ፍየል መሰል አጋንንት” [(ሴኢሪም) NW] የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ይላል:- “በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፣ ጉጉቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፣ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ። በዚያም አጋንንት [“ፍየል መሰል አጋንንት፣” NW] ይዘፍናሉ።” (ኢሳይያስ 13:21) እነዚህ ፍጥረታት ለተመለከታቸው ሰው አጋንንት መስለው የሚታዩ አስቀያሚና ፀጉራም የምድረ በዳ አራዊት ናቸው እንጂ ቃል በቃል አጋንንት ላይሆኑ ይችላሉ። በታላቂቱ ባቢሎን ፍርስራሽ ውስጥ እንደነዚህ ያሉ አራዊትና የሸተተና የገማ አየር (“እርኩስ ትንፋሽ”) እንዲሁም እርኩሳን ወፎች መኖራቸው በመንፈሣዊ በድን የመሆንዋን ሁኔታ ያመለክታል። ለሰው ልጅ ምንም ዓይነት የሕይወት ተስፋ አትሰጥም።—ከ⁠ኤፌሶን 2:1, 2 ጋር አወዳድር።

12. የታላቂቱ ባቢሎን ሁኔታ በኤርምያስ ምዕራፍ 50 ላይ ከተነገረው ትንቢት ጋር አንድ የሆነው እንዴት ነው?

12 በተጨማሪም የታላቂቱ ባቢሎን ሁኔታ በኤርምያስ ትንቢት ከተገለጸው ጋር ይመሳሰላል። “ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] . . . እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፣ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል። እነርሱም ይደርቃሉ። ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኩላዎች ጋር ይቀመጡባታል። ሰጎኖችም ይቀመጡባታል። ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይቀመጥባትም። እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም።” የጣዖት አምልኮትዋና የድግምት ጸሎትዋ ታላቂቱ ባቢሎንን አምላክ ሰዶምንና ገሞራን በገለበጠ ጊዜ ከፈጸመው የቅጣት ፍርድ ጋር ከሚመሳሰለው ቅጣት ሊያድናት አይችልም።—ኤርምያስ 50:35-40

የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይን ጠጅ

13. (ሀ) ኃያሉ መልአክ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው የትኛው በጥንትዋ ባቢሎን ውስጥ የነበረ የፆታ ብልግና ነው?

13 ኃያሉ መልአክ ከዚህ ቀጥሎ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ ስለመሆኑ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ *ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፣ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም [“ተጓዥ፣” NW] ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ” (ራእይ 18:3) እርኩስ በሆነው ሃይማኖታዊ አካሄድዋ የምድርን አሕዛብ በሙሉ በክላለች። በጥንትዋ ባቢሎን ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ እንደጻፈው እያንዳንዷ ልጃገረድ በቤተ መቅደሱ ይፈጸም በነበረው የአምልኮ ሥርዓት ድንግልናዋን እንድትሰጥ ይፈለግባት ነበር። በጦርነት በፈራረሰችው በካምፑቺያ አገር በአንጎር ዋት ለማየት የሚያስነውሩ የፆታ ግንኙነቶችን የሚያሳዩ ምስሎች እስከ ዛሬ ድረስ ይታያሉ። በሕንድ አገር በካጁራሆ በሚገኙ ቤተ መቅደሶች ደግሞ ቪሽኑ የተባለው የሂንዱዎች አምላክ አስጸያፊ በሆኑ የፆታ ግንኙነት ስሜት ቀስቃሽ ትርዒቶች ተከቦ የሚያሳዩ ምስሎች አሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በ1987 እና በ1988 የቴሌቪዥን ወንጌላውያንን ዓለምን ያናጋው የፆታ ብልግና መጋለጡና የሃይማኖት መሪዎች በግብረ ሰዶም ልማድ የተበከሉ መሆናቸው መታወቁ ሕዝበ ክርስትናም በጣም አስነዋሪ የሆኑ የዝሙት ድርጊቶችን የምትፈቅድ መሆኑን አረጋግጦአል። ይሁን እንጂ ብሔራት በሙሉ ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነ የዝሙት ድርጊት የፈጸሙበት መንገድ አለ።

14-16. (ሀ) በፋሽስት ኢጣልያ ውስጥ ምን ዓይነት ሕገወጥ የሃይማኖትና የፖለቲካ ዝምድና ተመስርቶ ነበር? (ለ) ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ምን መግለጫ አውጥተው ነበር?

14 ሂትለርን በናዚ ጀርመን የሥልጣን እርካብ ላይ ስላቆናጠጠው ሕገወጥ የሆነ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጥምረት ቀደም ስንል ተመልክተናል። ሌሎች ብሔራትም ቢሆኑ ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች በመዘባረቅዋ ምክንያት ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የካቲት 11 ቀን 1929 የቫቲካንን ከተማ ሉዓላዊ መንግሥት ያደረገው የላተራን ውል የተባለው ስምምነት በሙሶሎኒና በካርዲናል ጋስፓሪ ተፈረመ። በዚህ ጊዜ ፓፓ ፓየስ 11ኛ “ኢጣልያን ለአምላክ መልሼ አስረክቤአለሁ፣ አምላክም ወደ ኢጣልያ ተመልሶአል” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነበርን? ከስድስት ዓመት በኋላ የሆነውን ነገር እንመልከት። ጥቅምት 3 ቀን 1935 ኢጣልያ “አሁንም የባሪያ ንግድ የሚፈጸምባት የአረመኔዎች አገር ነች” የሚል ሰበብ በማቅረብ ኢትዮጵያን ወረረች። ይሁን እንጂ የአረመኔ ድርጊት የፈጸመው ማን ነበር? የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሙሶሎኒን አረመኔያዊ ድርጊት አውግዛ ነበርን? ፓፓው ግልጽ አቋም ያልያዘ መግለጫ ቢሰጡም ጳጳሶቻቸው “የአባት አገራቸውን” የኢጣልያን ጦር ኃይል በይፋ ባርከዋል። አንቶኒ ሮድስ ዘ ቫቲካን ኢን ዘ ኤጅ ኦፍ ዘ ዲክታተርስ (ቫቲካን በአምባገነኖች ዘመን) በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለው ነበር:-

15 “የኡዲን [ኢጣልያ] ጳጳስ ጥቅምት 19 ቀን [1935] በጻፉት የጵጵስና መልእክታቸው ‘እርምጃው ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ መናገር ለእኛ ተገቢም ወቅታዊም አይደለም። የኢጣልያዊነትም ሆነ የክርስቲያንነት ግዴታችን ለጦር ኃይላችን ድል ማግኘት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው’ ሲሉ ጽፈዋል። የፓዱዋ ጳጳስ ደግሞ ጥቅምት 21 ቀን ‘በዚህ በተደቀነብን አስቸጋሪ ጊዜ በመሪዎቻችንና በጦር ኃይላችን ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራችሁ እንጠይቃለን’ ሲሉ ጽፈዋል። ጥቅምት 24 ቀን የክሬሞና ጳጳስ የበርካታ ክፍለ ጦሮችን የዘመቻ አርማ ከባረኩ በኋላ ‘በአፍሪካ ምድር ለኢጣልያውያን ሊቅ ሕዝቦች ለም መሬት በሚያስገኙትና ለአፍሪካውያኑም የሮማንና የክርስትናን ወግና ባሕል በሚያደርሱት በእነዚህ ወታደሮች ላይ የእግዚአብሔር በረከት ይኑር። ኢጣልያ ለመላው ዓለም የክርስትና ጠባቂና ሞግዚት ሆና እንደገና ትቁም’ ብለዋል።”

16 ኢትዮጵያ በሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት ቡራኬ ተወረረች። ከእነዚህ ቀሳውስት መካከል አንዳቸው እንኳን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹህ ነኝ” ሊሉ ይችላሉን?—ሥራ 20:26

17. ስፓኝ ቀሳውስትዋ “ሰይፋቸውን ማረሻ” አድርገው ባለመቀጥቀጣቸው ምክንያት ምን ዓይነት ችግር ደርሶባታል?

17 ከጀርመን፣ ከኢጣልያና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የታላቂቱ ባቢሎን ምንዝር ሰለባ የሆነች አንዲት ሌላ አገር እንጨምር። እርስዋም ስፓኝ ናት። በዚያች አገር ከ1936 እስከ 1939 ለተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በአብዛኛው ምክንያት የሆነው ዲሞክራሲያዊው መንግሥት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ሥልጣንና ኃይል ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ነበር። ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ የአብዮታዊው ሠራዊት ፋሽስታዊ መሪ የነበሩት ካቶሊኩ ፍራንኮ ራሳቸውን “የቅዱስ መስቀል ሠራዊት ክርስቲያን ጄኔራል” ብለው ይጠሩ ነበር። በኋላ ግን ይህን የማዕረግ ስማቸውን ትተውታል። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስፓኞች በጦርነቱ ሞቱ። በጦርነቱ ከሞቱት ከእነዚህ ሰዎች ሌላ የፍራንኮ ብሔረተኞች በአነስተኛ ግምት 40, 000 የሚያክሉ የሕዝባዊ ግንባር አባሎችን ሲገድሉ ሕዝባዊው ግንባር ደግሞ 8, 000 መነኮሳትን፣ ቀሳውስትንና ደናግሎችን ገድለዋል። ማንኛውም የእርስበርስ ጦርነት ይህን የመሰለ አሳዛኝ ሁኔታና መከራ ያስከትላል። ይህም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ” ሲል የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። (ማቴዎስ 26:52) ሕዝበ ክርስትና እንዲህ ባለው ደም መፋሰስ መካፈልዋ በጣም የሚዘገንን ነገር ነው። ቀሳውስትዋ “ሠይፋቸውን ማረሻ” ለማድረግ እንዳልቻሉ ግልጽ ነው።—ኢሳይያስ 2:4

ተጓዥ ነጋዴዎች

18. “የምድር ተጓዥ ነጋዴዎች” የተባሉት እነማን ናቸው?

18 ተጓዥ “የምድር ነጋዴዎች” የተባሉት እነማን ናቸው? በዘመናችን አጠራር ከበርቴ ነጋዴዎች፣ ትልቅ የንግድ ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅሱ ከበርቴዎች፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። ይሁን እንጂ በሕጋዊ የንግድ ሥራ መሰማራት ስህተት ነው ማለታችን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የንግድ ሰዎች ከሸፍጥ፣ ከስግብግብነትና ከመሳሰሉት መጥፎ ድርጊቶች እንዲጠበቁ እያስጠነቀቀ ጥሩ ምክር ይሰጣቸዋል። (ምሳሌ 11:1፤ ዘካርያስ 7:9, 10፤ ያዕቆብ 5:1-5) ከሁሉ የሚበልጠው ትርፍ “ያለኝ ይበቃኛል” እያሉ ለአምላክ ማደር ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:6, 17-19) ይሁን እንጂ የሰይጣን ዓለም በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች አይገዛም። ምግባረ ብልሹነት በጣም ተስፋፍቶአል። ሃይማኖቶች፣ ፖለቲካዊ ድርጅቶችና ታላላቅ የንግድ ተቋሞች ምግባረ ብልሹዎች ሆነዋል። ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ስለፈጸሙት ምዝበራ፣ በሕገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ስለማስተላለፍና ስለመሳሰሉት ቅሌቶች ብዙ ጊዜ ከዜና ማሠራጫዎች እንሰማለን።

19. የምድር ነጋዴዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በመጥፎ የተጠቀሱበትን ምክንያት እንድንረዳ የሚያስችለን የትኛው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ነው?

19 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የጦር መሣሪያ ንግድ በዓመት ከ1,000,000,000,000 ዶላር በላይ ሆኖአል። ይህን የሚያክል ወጪ ለጦር መሣሪያዎች የሚውለው በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሕይወት ማቆያ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እየተነጠቁ ነው። በጣም የሚያስከፋ ሁኔታ ቢሆንም የዓለም ኢኮኖሚ ዋነኛ ደጋፊ ሆኖ የተገኘው የጦር መሣሪያ ንግድ የሆነ ይመስላል። ሚያዝያ 11 ቀን 1987 በለንደን ስፔክታተር ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ የሚከተለውን ዘገባ አስፍሮ ነበር። “ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሲቆጠሩ በዩናይትድ ስቴትስ 400, 000 የሚያክሉ ሠራተኞች በአውሮፓ ደግሞ 750, 000 የሚያክሉ ሠራተኞች በጦር መሣሪያ ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። የሚያስገርመው ግን የጦር መሣሪያዎች ግንባታ ሥራ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለው ድርሻ እየሰፋ በሄደ መጠን የመሣሪያዎቹ አምራቾች በቂ መከላከያ ያላቸው የመሆኑና ያለመሆኑ ጥያቄ ወደ ጎን ገሸሽ የተደረገ መሆኑ ነው።” ቦምቦችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በምድር በሙሉ፣ ለጠላት አገሮችም ሳይቀር ሲሸጡ ብዙ ትርፍ ይገኛል። እነዚህ ቦምቦች አንድ ቀን ተመልሰው ሻጮቻቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉ አይታሰብም። ምንኛ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነው! በዚህ ሁሉ ላይ በጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ አካባቢ የሚታየውን ሸፍጥና አጭበርባሪነት እንመልከት። ስፔክታተር ጋዜጣ እንደገለጸው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ “የአሜሪካ መንግሥት በየዓመቱ 900 ሚልዮን ዶላር ግምት ያለው የጦር መሣሪያና ትጥቅ ባልታወቀ ምክንያት ይጠፋበታል።” የምድር ነጋዴዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በክፉ አድራጊነት መጠቀሳቸው አያስደንቅም።

20. ሃይማኖት ምግባረ ብልሹ በሆነ የንግድ ሥራ እንደሚካፈል ማስረጃ የሚሆን ምን ምሳሌ አለን?

20 ክብር የተጎናጸፈው መልአክ እንደተናገረው የሃይማኖት ድርጅቶች እንደዚህ ባለው ምግባረ ብልሹ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሰፊው ተካፍለዋል። ለምሳሌ ያህል በ1982 የኢጣልያው ባንኮ አምብሮዚያኖ ከስሮ በተዘጋበት ድርጊት ቫቲካን ከፍተኛ ሚና ነበራት። ጉዳዩ በ1980ዎቹ ዓመታት በሙሉ በእንጥልጥል ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ገንዘቡ የት ደረሰ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊገኝ አልቻለም። በየካቲት ወር 1987 የሚላን ዳኞች ሦስት የቫቲካን ቀሳውስትና አንድ አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ ታስረው እንዲቀርቡ ማዘዣ አውጥተው ነበር። ባንኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ከስሮ እንዲዘጋ በማድረግ ወንጀል ተካፋዮች ነበሩ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቫቲካን የሃይማኖት መሪዎቹን አሳልፋ ለመስጠት እምቢተኛ ሆናለች። በ1987 በሐምሌ ወር ከፍተኛው የኢጣልያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በቫቲካንና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ተደርጎ የነበረ የቆየ ስምምነት በመጥቀስ ማዘዣው ውድቅ እንዲሆን በይኖአል።

21. ኢየሱስ በዘመኑ ከነበረው አጠያያቂ የንግድ ሥራ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበረው እንዴት እናውቃለን? በዛሬው ጊዜ በባቢሎናዊ ሃይማኖት ውስጥ ምን ነገር እንመለከታለን?

21 ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው አጠያያቂ የንግድ እንቅስቃሴ ተካፍሎ ነበርን? በፍጹም አልተካፈለም። እንዲያውም ምንም ዓይነት ንብረት አላበጀም ነበር። “ራሱን የሚያስጠጋበት” አልነበረውም። ኢየሱስ አንዱን ሀብታም ወጣት “ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ” ሲል መክሮት ነበር። ይህ ሰው ኢየሱስ እንደመከረው ቢያደርግ ኖሮ በንግድ ጉዳይ ከመጨነቅ ነፃ ሊሆን ይችል ስለ ነበረ ጥሩ ምክር ነበር። (ሉቃስ 9:58፤ 18:22) ባቢሎናዊው ሃይማኖት ግን ከዚህ በተለየ ሁኔታ ከትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ጋር ተቆራኝቶአል። ለምሳሌ ያህል አልባኒ ታይምስ ዩኒየን በ1987 እንደዘገበው የማያሚ ፍሎሪዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ የፋይናንስ አስተዳዳሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን በሚያመርቱ፣ የብልግና ፊልሞችን በሚሠሩና ሲጋራ አምራች በሆኑ ኩባንያዎች ውስጥ አክሲዮኖች እንዳሉአት አምነዋል።

“ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእርስዋ ዘንድ ውጡ”

22. (ሀ) ከሰማይ የመጣው ድምፅ ምን አለ? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች በ537 ከዘአበ እና በ1919 እዘአ በጣም ያስደሰታቸው ሁኔታ ያጋጠማቸው እንዴት ነው?

22 ዮሐንስ ቀጥሎ የሚናገረው ቃል በጥንትዋ ባቢሎን ላይ ከተፈጸመው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ትንቢታዊ ቃል ነው። “ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል:- ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።” (ራእይ 18:4) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ስለ ጥንትዋ ባቢሎን አወዳደቅ ከሚናገሩት ትንቢቶች መካከል ይሖዋ ለሕዝቦቹ “ከባቢሎን መካከል ሽሹ” ሲል የሰጠው ትዕዛዝ ይገኝበታል። (ኤርምያስ 50:8, 13) ዛሬም በተመሳሳይ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ታላቅ ጥፋት ስለሚመጣ የአምላክ ሕዝቦች ከመካከልዋ እንዲወጡ ተመክረዋል። በ537 ከዘአበ ታማኞቹ እስራኤላውያን ከባቢሎን ለመውጣት መቻላቸው ትልቅ ደስታ አስገኝቶላቸው ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ከባቢሎናዊ ምርኮ ለመውጣት መቻላቸው ብዙ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ራእይ 11:11, 12) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ሽሹ የሚለውን ትዕዛዝ ተቀብለዋል።

23. ከሰማይ የተሰማው ድምፅ ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽቶ መውጣት በጣም አጣዳፊ መሆኑን አጠንክሮ የገለጸው እንዴት ነው?

23 ከዓለማዊ ሃይማኖቶች አባልነት በመውጣትና ፈጽሞ በመለየት ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሽ በእርግጥ አጣዳፊ ጉዳይ ነውን? ለዚህች አስቀያሚ አሮጊት፣ ለታላቂቱ ባቢሎን ከአምላክ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ሊኖረን ስለሚገባ በእርግጥም አጣዳፊ ነው። አምላክ ታላቂቱ ጋለሞታ ብሎ ለመጥራት ቅር አልተሰኘም። በዚህም ምክንያት ከሰማይ የመጣው ድምፅ ስለዚህች አመንዝራ ተጨማሪ መግለጫ ለዮሐንስ ሰጥቶታል። “ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ። እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፣ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኃዘን ስጡአት። በልብዋ፣ ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኃዘንንም ከቶ አላይም ስላለች፣ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጣሉ፣ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ብርቱ ነውና።”—ራእይ 18:5-8

24. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሽ የሚኖርባቸው ከምን ለመዳን ነው? (ለ) ከታላቂቱ ባቢሎን ሳይሸሹ የቀሩ ሁሉ በምን ኃጢአት ተካፋዮች ይሆናሉ?

24 በጣም ከባድ ቃላት ናቸው! ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ኤርምያስ በዘመኑ የነበሩ እስራኤላውያን እርምጃ እንዲወስዱ ሲያሳስብ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ። . . . የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] በቀል ጊዜ ነውና። እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። ሕዝቤ ሆይ፣ ከመካከልዋ ውጡ። እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ጽኑ ቁጣ ራሳችሁን አድኑ።” (ኤርምያስ 51:6, 45) ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ከሰማይ የመጣው ድምፅ የአምላክ ሕዝቦች ከመቅሰፍትዋ እንዳይቀበሉ ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽተው መውጣት እንደሚኖርባቸው ያስጠነቅቃል። ይሖዋ በዚህ ዓለም ላይ፣ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጭምር የሚያወርደው መቅሰፍት መሰል ፍርድ በአሁኑ ጊዜ በመታወጅ ላይ ነው። (ራእይ 8:1 እስከ 9:21፤ 16:1-21) የአምላክ ሕዝቦች በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚደርሰው መቅሰፍት እንዳይደርስባቸውና ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር እንዳይሞቱ ከፈለጉ ራሳቸውን ከሐሰት ሃይማኖት መለየት ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ በዚህች ድርጅት ውስጥ መቆየታቸው በኃጢአትዋ ተካፋዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ልክ እንደርስዋ በመንፈሳዊ ምንዝርና “በምድር የታረዱ ሁሉ ደም” ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል።—ራእይ 18:24፤ ከ⁠ኤፌሶን 5:11⁠ና ከ⁠1 ጢሞቴዎስ 5:22 ጋር አወዳድር።

25. የአምላክ ሕዝቦች ከጥንትዋ ባቢሎን የወጡት እንዴት ነበር?

25 ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚወጡት እንዴት ነው? በጥንትዋ ባቢሎን የነበሩት አይሁዶች ከባቢሎን ከተማ ወጥተው እስከ ተስፋይቱ ምድር ድረስ የእግር ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ከጉዞው የበለጠ ነገር ያስፈልግ ነበር። ኢሳይያስ ለእስራኤላውያን በትንቢታዊ አነጋገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “እናንተ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩስን ነገር አትንኩ። ከመካከልዋ ውጡ፣ ንጹሐን ሁኑ።” (ኢሳይያስ 52:11) አዎ፣ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ሊያረክሱባቸው የሚችሉትን ርኩስ የባቢሎን ሃይማኖት ልማዶች መተው ነበረባቸው።

26. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘ከመካከልዋ ውጡ፣ እርኩስንም አትንኩ’ የሚለውን ቃል የታዘዙት እንዴት ነው?

26 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደሚከተለው በማለት የኢሳይያስን ቃል ጠቅሶ ነበር:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ስለዚህም ጌታ [“ይሖዋ፣” NW]:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ፣ ርኩስንም አትንኩ ይላል።” የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህንን ትዕዛዝ ለመፈጸም ከቆሮንቶስ ከተማ መውጣት አላስፈለጋቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ከሐሰት ሃይማኖት የረከሱ ቤተ መቅደሶች መራቅና እነዚያ የጥንት ጣዖት አምላኪዎች ይፈጽሙ ከነበረው እርኩስ ተግባራት ራሳቸውን መለየት ነበረባቸው። ንጹሕ ሕዝቦች ሆነው ይሖዋን ሊያገለግሉ የሚችሉት ይህን ቢያደርጉ ብቻ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17፤ 1 ዮሐንስ 3:3

27. በጥንትዋ ባቢሎን ላይ የተፈጸመውና በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመው ፍርድ ተመሳሳይነት ያለው እንዴት ነው?

27 የጥንትዋ ባቢሎን የወደቀችውና በመጨረሻም ባድማ የሆነቸው ለኃጢአትዋ መቀጫ እንዲሆናት ነበር። “ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና።” (ኤርምያስ 51:9) በተመሳሳይም የታላቂቱ ባቢሎን ኃጢአት ይሖዋ እስኪያየው ድረስ ‘ወደ ሰማይ ደርሶአል።’ የፍትሕ አጉዳይነት፣ የጣዖት አምልኮ፣ የሥነ ምግባራዊ ብልግና፣ የጭቆናና የግድያ ወንጀል ተከምሮባታል። የጥንትዋ ባቢሎን የወደቀችው በከፊል በይሖዋ ቤተ መቅደስና በእውነተኛ አምላኪዎቹ ላይ ላደረሰችው ጉዳት በቀል እንዲሆን ነበር። (ኤርምያስ 50:8, 14፤ 51:11, 35, 36) በተመሳሳይም የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀትና የመጨረሻ ጥፋት ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ ለፈጸመችው በደል የበቀል መግለጫ ነው። በእርግጥም “አምላካችን የሚበቀልበት ቀን” የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ነው።—ኢሳይያስ 34:8-10፤ 61:2፤ ኤርምያስ 50:28

28. ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጽመው የትኛውን የፍትሕ ማስፈጸሚያ ደረጃ ነው? ለምንስ?

28 በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ እሥራኤላዊ ከአገሩ ሰዎች የአንዱን ንብረት ቢሰርቅ እጅግ ቢያንስ የሰረቀውን ንብረት እጥፍ አድርጎ መመለስ ነበረበት። (ዘጸአት 22:1, 4, 7, 9) በመጪው የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ጊዜም ይሖዋ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፍርድ እንዲፈጸም ያደርጋል። እርስዋ ካደረገችው በእጥፍ የሚበልጥ እንድትቀበል ይደረጋል። ታላቂቱ ባቢሎን ለበደለቻቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ምህረት ስላላሳየች ለእርሷም ምህረት አይደረግላትም። ‘በአሳፋሪ የቅምጥልነት ኑሮ’ ለመኖር ስትል የምድር ሕዝቦችን ስትቦጠቡጥ ኖራለች። አሁን ግን መከራና ሐዘን ይመጣባታል። የጥንትዋ ባቢሎን ምንም ነገር ሊነካት እንደማይችል ትተማመን ስለነበረ “መበለትም ሆኜ አልኖርም፣ የወላድ መካንነትም አላውቅም” እያለች ትታበይ ነበር። (ኢሳይያስ 47:8, 9, 11) ታላቂቱ ባቢሎንም ልክ እንደርስዋ ምንም ነገር ሊደርስባት እንደማይችል ተማምናለች። ይሁን እንጂ “ብርቱ” የሆነው ፈራጅዋ ይሖዋ የበየነባት ጥፋት “በአንድ ቀን” እንደሆነ ያህል ፈጥኖ ይመጣባታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 በባለ ማጣቀሻው አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 236 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ”

በ18 መቶዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ነጋዴዎች መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኦፒየም ወደ ቻይና በድብቅ ያስገቡ ነበር። ቻይናውያን ባለ ሥልጣኖች በመጋቢት ወር 1839 ላይ 20, 000 ሳጥን ዕጽ ከብሪታንያ ነጋዴዎች በመንጠቅ ይህን ሕገወጥ ንግድ ለማቆም ሞክረው ነበር። በዚህም ምክንያት በቻይናና በብሪታንያ መካከል ግጭት ተፈጠረ። በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት እየተበላሸ በሄደበት ጊዜ የፕሮቴስታንት ሚሲዮኖች እንደሚከተሉት ያሉትን መግለጫዎች በማሰማት ብሪታንያ ውጊያ እንድትጀምር ይቀሰቅሱ ነበር:-

“የእንግሊዝ መንግሥት ተቆጥቶ የሚነሳና አምላክም በዚህ በመጠቀም የክርስቶስ ወንጌል ወደ ቻይና እንዳይገባ የከለከሉትን እንቅፋቶች የሚያስወግድ ስለሚመስለኝ እነዚህ ችግሮች መቀስቀሳቸው በጣም ያስደስተኛል።”—ሄንሪየታ ሹክ፣ የደቡብ ባፕቲስት ሚሲዮናዊ።

በመጨረሻም ጦርነቱ ተጀመረ። ይህም ጦርነት በዛሬው ዘመን የኦፒየም ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ነው። ሚሲዮናውያን እንደሚከተሉት ያሉትን ቃላት በማሰማት ከብሪታንያ ጎን በሙሉ ልባቸው ተሰልፈው ነበር:-

“በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ እንደ ኦፒየም ወይም እንደ እንግሊዝ ጉዳይ ሳይሆን አምላክ በሰው ልጅ የክፋት ድርጊት በመጠቀም ቻይና የተገለለችበትን ግድግዳ አፍርሶ ምህረቱን ሊያወርድላት ያሰበውን ዓላማ ለማስፈጸም ያደረገው ጉዳይ እንደሆነ አድርጌ ለመመልከት እገደዳለሁ።”—ፒተር ፓርከር፣ ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ።

ሌላው ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ሳሙኤል ደብልዩ ዊልያምስ ደግሞ በመጨመር “በተደረገው ነገር ሁሉ የአምላክ እጅ እንዳለበት ግልጽ ነው። በምድር ላይ ሠይፍ ይዤ መጥቼአለሁ ያለው [ኢየሱስ] ጠላቶቹን በአፋጣኝ እርምጃ ለማጥፋትና የራሱን መንግሥት ለማቋቋም እንደመጣ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። አምላክ የሰላሙን መስፍን በቦታው እስኪያስቀምጥ ድረስ እየደጋገመ ይገለባብጣቸዋል” ብለዋል።

ሚሲዮናዊው ጄ ሉዊስ ሹክ በቻይናውያን ብሔረተኞች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንዲህ ያለውን ትዕይንት . . . አምላክ መለኮታዊው እውነት እንዳይስፋፋ እንቅፋት የሆኑትን ጥራጊ ቆሻሻዎች ለማስወገድ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ።

ኤላይጃ ሲ ብሪጅማን የተባሉት ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ደግሞ እንዲህ በማለት አክለዋል:- “አምላክ ብዙ ጊዜ ጠንካራ ክንድ ያላቸውን የሕዝብ ባለ ሥልጣናት በመጠቀም ለመንግሥቱ ጥርጊያ መንገድ አዘጋጅቶአል። . . . በእነዚህ ታላላቅ ጊዜያት ሁሉ መሣሪያ የሆኑት ሰዎች ሲሆኑ አስፈጻሚው ኃይል ግን መለኮታዊ ነበር። የብሔራት ሁሉ የበላይ ገዥ የሆነው አምላክ እንግሊዝን መሣሪያ በማድረግ ቻይናን ቀጥቶአል፣ አዋርዶአል።” ጥቅሱ የተወሰደው ዘ ሚሽነሪ ኢንተርፕራይዝ ኢን ቻይና ኤንድ አሜሪካ (በጆን ኬ ፌይርባንክ የታተመ የሃርቫርድ ጥናት) በተባለው ጽሑፍ ላይ ከሰፈረው “ኢንድስ ኤንድ ሚንስ” ከተባለው የስትዋርት ክሬይተን ሐተታ ነው።

[በገጽ 264 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ተጓዥ ነጋዴዎችም . . . ባለጠጋዎች ሆኑ”

“ከ1929 እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍንዳታ ድረስ [የቫቲካን የፋይናንስ አስተዳዳሪ የነበሩት] [ቤርናንዲኖ] ኖጋራ የቫቲካን መዋዕለ ንዋይና የቫቲካን ወኪሎች በተለይ በኤሌክትሪክ፣ በቴሌፎን መገናኛ፣ በብድርና በባንክ፣ በትናንሽ የባቡር መስመሮች፣ የእርሻ መሣሪያዎችን በማምረት፣ በሲሚንቶ፣ በሰው ሠራሽ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችና በመሳሰሉት የተለያዩ የኢጣልያ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሠሩ አድርገው ነበር። አብዛኞቹም ከፍተኛ ትርፍ አስገኝተዋል።

“ኖጋራ ብዙ ኩባንያዎችን ውጠዋል። ከእነዚህም መካከል ላ ሶቺዬታ ኢታልያና ዴላ ቪስኮዛ፣ ላ ሱፐርቴዚሌ፣ ላ ሶቺዬታ ሜሪዲዮናሌ ኢንዱስትርዬ ቴሲሌ እና ላ ቺዛራዮን የተባሉት ኩባንያዎች ይገኛሉ። እነዚህን ኩባንያዎች በሙሉ በአንድ ኩባንያ አጣምረው ሲ አይ ኤስ ኤ ቪስኮዛ ብለው ከሰየሙ በኋላ አዲሱ ኩባንያ በጣም የታመኑ የቫቲካን ተከታይ በነበሩት በባሮን ፍራንቼስኮ ማሪያ ኦዳሶ ሥር እንዲተዳደር አደረጉ። ከዚያም ይህ አዲስ ኩባንያ ኤስ ኤን አይ ኤ ቪስኮዛ ከተባለው በጣም ትልቅ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ጋር እንዲቀላቀል አደረጉ። ቫቲካን በኤስ ኤን አይ ኤ ቪስኮዛ ውስጥ የነበራት ድርሻ በጣም ከፍተኛ ሆነ። በመጨረሻም ሁሉን በቁጥጥሯ ሥር አደረገች። በዚህም ምክንያት ባሮን ኦዳሶ ምክትል ፕሬዚደንት ሆኑ።

“በዚህም መንገድ ኖጋራ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን በቁጥጥራቸው ውስጥ አስገቡ። ኖጋራ በጣም ዘዴኛና መሰሪ ሰው ስለነበሩ በተለያዩ ዘዴዎች ሌሎች ኢንዱስትሪዎችንም ለመቆጣጠር ችለዋል። በኢጣልያ ታሪክ ውስጥ የኢጣልያን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ረገድ ከእኚህ ታታሪ ሰው የበለጠ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሰው አይገኝም። . . . ቤኒቶ ሙሶሎኒ ያለመውን ሰፊ ግዛት ለማግኘት አልቻለም። ቢሆንም ቫቲካንና ቤርናንዲኖ ኖጋራ ሌላ ዓይነት ሰፊ ግዛት እንዲያቋቁሙ አስችሎአቸዋል።”—ዘ ቫቲካን ኢምፓየር በኒኖ ሎ ቤሎ፣ ገጽ 71–3

ይህ በምድር ነጋዴዎችና በታላቂቱ ባቢሎን መካከል ያለውን የቅርብ ትብብር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። እነዚህ ነጋዴዎች የንግድ ሸሪካቸው ስትጠፋ ማዘናቸው የሚያስደንቅ ነገር አይደለም።

[በገጽ 259 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች በመላዋ ምድር ላይ በሚሰራጩበት ጊዜ ባቢሎናዊ ሃይማኖታቸውን ይዘው ሄዱ

[በገጽ 261 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የዮሐንስ ክፍል እንደ አንድ ጠባቂ በመሆን የባቢሎንን መውደቅ ያስታውቃል

[በገጽ 266 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሽ መጪውን የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት ያመለክታል