በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድን ቅዱስ ምሥጢር መፍታት

አንድን ቅዱስ ምሥጢር መፍታት

ምዕራፍ 6

አንድን ቅዱስ ምሥጢር መፍታት

1. በ⁠ራእይ 1:10-17 ላይ ስለተገለጸው አንጸባራቂ ሥዕል እንዴት ሊሰማን ይገባል?

በእውነትም በክብር ከፍ የተደረገው የኢየሱስ ራእይ በጣም የሚያስደንቅና የሚያስፈራ ነበር። እኛም በዚያ ሥፍራ ተገኝተን ሐዋርያው ዮሐንስ ያየውን ብንመለከት ኖሮ እንደ ዮሐንስ በዚህ ታላቅ ግርማ ተሸንፈን እንወድቅ ነበር። (ራእይ 1:10-17) ይህ ታላቅ ራእይ እስከ ዛሬ ተመዝግቦ የቆየልን ለሥራ እንዲያነሳሳንና እንዲቀሰቅሰን ነው። እኛም እንደ ዮሐንስ ለራእዩ ትርጉም ትህትና የተሞላበት አድናቆት ማሳየት ይኖርብናል። ኢየሱስ በዙፋን ላይ የተቀመጠ ንጉሥ፣ ሊቀ ካህንና ፈራጅ በመሆን ለያዘው ቦታ ሁልጊዜ ቅድስና የሞላበት አክብሮት እናሳይ።—ፊልጵስዩስ 2:5-11

“የመጀመሪያውና የመጨረሻው”

2. (ሀ) ኢየሱስ ራሱን የገለጸው እንዴት ባለ የማዕረግ ስም ነው? (ለ) ይሖዋ “የመጀመሪያና የመጨረሻ እኔ ነኝ” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ሐ) “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የሚለው የኢየሱስ የማዕረግ ስም የሚያመለክተው ምንን ነው?

2 ይሁን እንጂ አድናቆታችን ከልክ ወዳለፈ ፍርሐትና መርበትበት መድረስ አይኖርበትም። ሐዋርያው ቀጥሎ እንደሚነግረን ኢየሱስ ዮሐንስን አበረታቶት ነበር። “ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፣ እንዲህም አለኝ፣ ‘አትፍራ፣ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ።’” (ራእይ 1:17ለ, 18ሀ) ይሖዋ በ⁠ኢሳይያስ 44:6 ላይ የራሱን ደረጃ ሲገልጽ “እኔ ፊተኛ ነኝ፣ እኔም ኋለኛ ነኝ፣ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” ብሎ ነበር። * ኢየሱስ ራሱን “ፊተኛውና መጨረሻው” ሲል ራሱን ከታላቁ ፈጣሪ ከይሖዋ ጋር ማስተካከሉ አልነበረም። አምላክ የሰጠውን የማዕረግ ስም መጠቀሙ ነበር። ይሖዋ በኢሳይያስ ላይ የተናገረው ቃል በእውነተኛ አምላክነት ደረጃው ረገድ ያለውን ብቸኛና ልዩ ቦታ የሚያመለክት ነበር። ይሖዋ የዘላለም አምላክ ሲሆን ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ኢየሱስ ግን በራእይ ላይ ያለውን ቃል የተናገረው የተሰጠውን የማዕረግ ስም ለመጥቀስና ስለተሰጠው ልዩ ዓይነት ትንሣኤ ለማመልከት ነበር።

3. (ሀ) ኢየሱስ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ “የሞትና የሲኦል ቁልፍ” መያዙ ምን ትርጉም አለው?

3 በእውነትም ወደማይሞት ሰማያዊ ሕይወት ለመነሳት “የመጀመሪያው” ሰው ኢየሱስ ነበር። (ቆላስይስ 1:18) ከዚህም በላይ ይሖዋ በግል ያስነሳው ኢየሱስን ብቻ ስለሆነ እርሱ “የመጨረሻው” ነው። በዚህም መንገድ “ሕያው” ሆኖአል። “ከዘላለም እስከ ዘላለምም ሕያው” ነው። ያለመሞት ባሕርይ ተሰጥቶታል። በዚህም ባሕርዩ “ሕያው አምላክ” ከተባለው ከአባቱ ጋር ይመሳሰላል። (ራእይ 7:2፤ መዝሙር 42:2) ለቀሩት የሰው ዘሮች ግን ኢየሱስ “ትንሣኤም ሕይወትም” ነው። (ዮሐንስ 11:25) ከዚህም ጋር በመስማማት ለዮሐንስ እንዲህ ብሎታል:- “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ። የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።” (ራእይ 1:18ለ) ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን ሰጥቶታል። ኢየሱስም በሞትና በሲኦል (በመቃብር) የታሰሩትን ከፍቶ የሚለቅበት ቁልፍ እንዳለው የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው።—ከማቴዎስ 16:18 ጋር አወዳድር።

4. ኢየሱስ በድጋሚ የተናገረው የትኛውን ትዕዛዝ ነው? ለማንስ ጥቅም ሲል?

4 ኢየሱስ ዮሐንስ ራእዩን እንዲጽፍ ቀደም ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ እዚህ ላይ ይደግማል። እንዲህም አለው:- “እንግዲህ ያየኸውን፣ አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።” (ራእይ 1:19) ዮሐንስ ለትምህርታችን የሚጠቅሙ ምን አስደናቂ ነገሮችን ይገልጽልን ይሆን?

ኮከቦቹና መቅረዞቹ

5. ኢየሱስ “ሰባቱን ከዋክብትና” “ሰባቱን መቅረዞች” የገለጸው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ በሰባት የወርቅ መቅረዞች መካከል እንደቆመና ሰባት ከዋክብት በቀኝ እጁ እንደያዘ ዮሐንስ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 1:12, 13, 16) አሁን ደግሞ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ያብራራል:- “በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው። ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት [“ጉባኤዎች፣” NW] መላእክት ናቸው። ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት [“ጉባኤዎች፣” NW] ናቸው።”—ራእይ 1:20

6. ሰባቱ ከዋክብት ምን ነገር ያመለክታሉ? መልእክቱስ በተለይ ለእነዚህ የተነገረው ለምንድን ነው?

6 ‘ከዋክብቱ’ “የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት [“ጉባኤዎች፣” NW] መላእክት ናቸው።” በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከዋክብት የመላእክት ምሳሌ የሆኑበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለማይታዩ መንፈሣዊ ፍጡሮች ለመጻፍ ዮሐንስን ጸሐፊው አድርጎ ይጠቀምበታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ‘ከዋክብቱ’ እንደ ኢየሱስ መልእክተኞች ይቆጠሩ የነበሩት የጉባኤዎች ሰብዓዊ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች ናቸው። * መልእክቶቹ የተላኩት ለከዋክብቱ ነበር። ይህም የሆነው ስለ ይሖዋ መንጋ አጠባበቅ በኃላፊነት የሚጠየቁት እነርሱ ስለሆኑ ነው።—ሥራ 20:28

7. (ሀ) ኢየሱስ በእያንዳንዱ ጉባኤ ለአንድ መልአክ ብቻ መናገሩ እያንዳንዱ ጉባኤ አንድ ሽማግሌ ብቻ እንደነበረው የሚያመለክት አለመሆኑን የሚያሳየን ምንድን ነው? (ለ) በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ በነበሩት ሰባት ከዋክብት የተወከሉት እነማን ናቸው?

7 ኢየሱስ የተናገረው በጉባኤው ውስጥ ለሚገኝ አንድ “መልአክ” ብቻ መሆኑ እያንዳንዱ ጉባኤ አንድ ሽማግሌ ብቻ ነበረው ማለት ነውን? አይደለም። በጳውሎስ ዘመንም እንኳ በኤፌሶን ጉባኤ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሽማግሌዎች ነበሩ። (ራእይ 2:1፤ ሥራ 20:17) ስለዚህ በዮሐንስ ዘመን በጉባኤዎቹ (በኤፌሶን ጉባኤ ጭምር) የሚነበቡ መልእክቶች ለሰባቱ ከዋክብት ሲላኩ ከዋክብቱ በይሖዋ የቅቡዓን ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉትን የሽማግሌዎች አካላት በሙሉ የሚያመለክቱ መሆን ይገባቸዋል። በተመሳሳይም የዘመናችን የበላይ ተመልካቾች በኢየሱስ ራስነት ሥር የሚያገለግሉ ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች ከሚገኙበት የአስተዳደር ክፍል ደብዳቤ ሲደርሳቸው ደብዳቤውን ለጉባኤያቸው ያነባሉ። በየጉባኤው ያሉት ሽማግሌዎች ጉባኤያቸው ኢየሱስ የሰጠውን ምክር በሥራ የሚያውል መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ምክሩም ሽማግሌዎቹን ብቻ ሳይሆን የጉባኤውን አባላት በሙሉ የሚጠቅም ነበር።—ራእይ 2:11ሀ ተመልከት።

8. ሽማግሌዎቹ በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ መሆናቸው ምን ያመለክታል?

8 ኢየሱስ የጉባኤው ራስ በመሆኑ ሽማግሌዎቹ በቀኝ እጁ ውስጥ እንዳሉ ማለትም በኢየሱስ ቁጥጥርና አመራር ሥር እንዳሉ መነገሩ ተገቢ ነበር። (ቆላስይስ 1:18) እርሱ የእረኞች አለቃ ሲሆን ሽማግሌዎቹ ደግሞ የበታች እረኞች ናቸው።—1 ጴጥሮስ 5:2-4

9. (ሀ) ሰባቱ መቅረዞች ምን ያመለክታሉ? እነዚህስ በመቅረዝ መመሰላቸው ትክክል የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ራእዩ ሐዋርያው ዮሐንስን ስለምን ነገር አሳስቦት ሊሆን ይችላል?

9 ሰባቱ መቅረዞች ዮሐንስ የራእይን መጽሐፍ የጻፈላቸው ሰባቱ ጉባኤዎች ናቸው። እነርሱም:- ኤፌሶን፣ ሰምርኔስ፣ ጴርጋሞን፣ ትያጥሮን፣ ሰርዴስ፣ ፊልድልፍያ እና ሎዶቅያ ናቸው። ጉባኤዎች በመቅረዝ የተመሰሉት ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃም ሆነ በአጠቃላይ በጉባኤ ደረጃ በዚህ በጨለማ በተዋጠው ዓለም ውስጥ ‘ብርሃናቸው በሰው ፊት እንዲታይ ማድረግ’ ስለሚኖርባቸው ነው። (ማቴዎስ 5:14-16) በተጨማሪም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ ከነበሩት ዕቃዎች መካከል መቅረዞች ይገኙ ነበር። ስለዚህ ጉባኤዎቹ መቅረዞች ተብለው መጠራታቸው እያንዳንዱ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በምሳሌያዊ ሁኔታ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ” ማለትም የአምላክ መንፈስ መኖሪያ መሆኑን ለዮሐንስ ያስገነዝበዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:16) ከዚህም በላይ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ጥላ በሆነለት የይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ የቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ የቅቡዓን ጉባኤ አባሎች “የንጉሥ ካህናት” ሆነው ያገለግላሉ። ይህም ቤተ መቅደስ ይሖዋ ራሱ በሰማያዊው ቅድስተ ቅዱሳን የሚኖርበትና ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚያገለግልበት ነው።—1 ጴጥሮስ 2:4, 5, 9፤ ዕብራውያን 3:1፤ 6:20፤ 9:9-14, 24

ታላቁ ክህደት

10. በ70 እዘአ በአይሁድ ሥርዓትና ንሥሐ ባልገቡት የሥርዓቱ ደጋፊዎች ላይ ምን ነገር ደረሰ?

10 ዮሐንስ የራእይን መጽሐፍ በጻፈበት ጊዜ ክርስትና ከ60 ዓመት የበለጠ ዕድሜ ነበረው። ክርስትና ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለ40 ዓመታት ያህል ከአይሁድ እምነት የደረሰበትን ያልተቋረጠ ተቃውሞ ችሎ ሥራውን ቀጥሎ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን በ70 እዘአ ንሥሐ ለመግባት እምቢተኛ የሆኑት አይሁድ ብሔራዊ ሕልውናቸውን ባጡና እንደ ጣዖት ያመልኩት የነበረው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በጠፋ ጊዜ የአይሁዳውያን ሥርዓት ፈጽሞ ወደመ።

11. የእረኞች አለቃ መከሰት ስለ ጀመሩ ሁኔታዎች ጉባኤዎችን ማስጠንቀቁ ወቅታዊ የነበረው ለምንድን ነው?

11 ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ በቅቡዓን—ክርስቲያኖች መካከል ክህደት እንደሚነሳ ተንብዮ ነበር። የኢየሱስም መልእክት በዚህ በዮሐንስ የሽምግልና ዕድሜ ይኸው ክህደት መካሄድ ጀምሮ እንደነበረ ያመለክታል። ሰይጣን የሴቲቱን ዘር ለማበላሸት የሚያደርገውን ይህን ጥረት ይከላከሉ ከነበሩት ሰዎች በሕይወት የቀረው ዮሐንስ ብቻ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:3-12፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3፤ 2 ዮሐንስ 7-11) ስለዚህ የይሖዋ ዋነኛ እረኛ በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ መጠንሰስ ስለጀመረው ሁኔታ እንዲጠነቀቁና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለጽድቅ የጸና አቋም እንዲይዙ የሚጽፍበት ተገቢ ጊዜ ነበር።

12. (ሀ) ከዮሐንስ ዘመን በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ክህደቱ እየተስፋፋ የሄደው እንዴት ነበር? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ወደ ሕልውና የመጣችው እንዴት ነው?

12 በ96 እዘአ የነበሩት ጉባኤዎች ለኢየሱስ መልእክት እንዴት ምላሽ እንደሰጡ አናውቅም። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ክህደቱ በፍጥነት እንደተስፋፋ እናውቃለን። “ክርስቲያኖች” በይሖዋ ስም መጠቀማቸው ቀርቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎቻቸው ውስጥ “ጌታ” ወይም “አምላክ” የሚለውን ቃል መተካት ጀመሩ። በአራተኛው መቶ ዘመን ሐሰት የሆነው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ወደ ጉባኤዎች ሰርጎ ገባ። በዚሁ ጊዜ ላይ የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘት ጀምሮ ነበር። በመጨረሻም ቆስጠንጢኖስ የተባለው የሮማ ንጉሠ ነገሥት “የክርስትና” ሃይማኖት በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ። ይህም ድርጊት ለሕዝበ ክርስትና መስፋፋት ምክንያት ከመሆኑም ሌላ ቤተ ክህነትና መንግሥት ሰዎችን ለሺህ ዓመት ለመግዛት ኃይላቸውን አጣመሩ። አዲሱን “ክርስትና” ለመቀበል በጣም ቀላል ነበር። የተለያዩ ጎሣዎች ቀድሞ ይከተሉ የነበረውን አረመኔያዊ እምነት ከዚህ ሃይማኖት ጋር አስማምተው እንዲቀበሉ ተፈቀደላቸው። አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የክህደት አስተሳሰባቸውን በሠይፍ አስገዳጅነት የሚያሳምኑ ጨቋኝ የፖለቲካ ገዥዎች ሆኑ።

13. ኢየሱስ ስለ ኑፋቄ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ከሃዲዎቹ ክርስቲያኖች እንዴት ያለ መንገድ ተከተሉ?

13 ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የተናገራቸው ቃላት በከሃዲዎቹ ክርስቲያኖች ፈጽመው ተዘነጉ። ኢየሱስ የኤፌሶንን ክርስቲያኖች ቀድሞ ወደነበራቸው ፍቅር እንዲመለሱ አስጠንቅቆአቸው ነበር። (ራእይ 2:4) የሕዝበ ክርስትና አባላት ግን ቀድሞውንም ቢሆን ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር የተባበሩ ስላልሆኑ እርስበርሳቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተዋግተዋል፣ አንዳቸው ሌላውን አሳድደዋል። (1 ዮሐንስ 4:20) ኢየሱስ በጴርጋሞን የነበረውን ጉባኤ ስለመናፍቅነት አስጠንቅቆ ነበር። ቢሆንም ገና በሁለተኛው መቶ ዘመን ላይ እንኳን የተለያዩ ኑፋቄዎች ብቅ ማለት ጀምረው ነበር። በአሁኑ ጊዜም ሕዝበ ክርስትና እርስበርሳቸው የሚነታረኩ በሺህ የሚቆጠሩ ኑፋቄዎችና ሃይማኖቶች አሏት።—ራእይ 2:15

14. (ሀ) ኢየሱስ በመንፈሳዊ በድን ስለመሆን ቢያስጠነቅቅም የስም ክርስቲያኖች እንዴት ያለ አካሄድ ተከትለዋል? (ለ) የስም ክርስቲያኖች ኢየሱስ ስለ ጣዖት አምልኮና ስለ ሥነ ምግባር እርኩሰት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳይከተሉ የቀሩት እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ የሰርዴስን ጉባዔ በመንፈሣዊ በድን ስለመሆን አስጠንቅቆ ነበር። (ራእይ 3:1) የስም ክርስቲያኖችም በሰርዴስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስቲያናዊ ሥራዎችን ፈጥነው በመዘንጋት በጣም አስፈላጊ የሆነውን የስብከት ሥራ በቁጥር ጥቂት ለሆኑ ደመወዝተኛ ቀሳውስት አስረከቡት። ኢየሱስ በትያጥሮን የነበረውን ጉባኤ ስለ ጣዖት አምልኮና ስለ ምንዝር አስጠንቅቆ ነበር። (ራእይ 2:20) ሕዝበ ክርስትና ግን ሥዕሎችንና ምስሎችን ማምለክን በግልጽ ከመደገፍዋም በላይ ይበልጥ ስውር የሆነውን የብሔራዊ ስሜትና የፍቅረ ንዋይ ጣዖት አምልኮ አስፋፍታለች። ዝሙትና ምንዝር መጥፎ እንደሆነ አልፎ አልፎ ቢሰበክም በአብዛኛው በግድየለሽነት ታልፎአል።

15. ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የተናገራቸው ነገሮች ስለሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ምን ነገሮችን አጋልጠዋል? የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትስ ምን መሆናቸውን አሳይተዋል?

15 ስለዚህ ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላካቸው መልእክቶች የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በሙሉ የይሖዋ ልዩ ሕዝቦች ለመሆን አለመቻላቸውን አጋልጠዋል። እንዲያውም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ዋነኞቹ የእባቡ ዘር ክፍሎች ሆነዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የቀሳውስት ክፍል ‘የዓመፅ ሰው’ ብሎ በመጥራት “የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው” በማለት ተንብዮአል።—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10

16. (ሀ) የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የተለየ ጥላቻ የሚያሳዩት ለእነማን ነው? (ለ) በመካከለኛው ዘመን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ምን ሆኖ ነበር? (ሐ) የፕሮቴስታንት ዓመፅ ወይም ተሐድሶ የሕዝበ ክርስትናን የክህደት መንገድ ለውጦት ነበርን?

16 የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊም ሆኑ ዓለማዊ መሪዎች የአምላክ መንጋ እረኞች ነን እያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ለሚያበረታታ ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች የማይስማሙ ድርጊቶቻቸውን ለሚያጋልጥባቸው ማንኛውም ሰው ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው አሳይተዋል። ጆን ሁስና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነው ዊልያም ታይንደል ከባድ ስደት ደርሶባቸው በሰማዕትነት ሞተዋል። ፍጹም በሆነ ጨለማ በተዋጠው የመካከለኛ ዘመን ዲያብሎሳዊው የካቶሊክ ኢንኩዚሽን ስለተጀመረ የክህደቱ አገዛዝ ጣሪያ ደርሶ ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣን ወይም ትምህርት የተቃወመ ማንኛውም ሰው ምህረት በሌለው ሁኔታ ይታፈን ነበር። መናፍቃን ናቸው የሚባሉ ሰዎች እየተሠቃዩ ይገደሉ ነበር ወይም በእንጨት ላይ ታስረው ይቃጠሉ ነበር። ሰይጣን በዚህ መንገድ የአምላክ ሴት መሰል ድርጅት አባል የሆነ ማንኛውም እውነተኛ ዘር ፈጥኖ እንዲጨፈለቅ የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። የፕሮቴስታንቶች ዓመፅ ወይም ተሐድሶ ከተጀመረ በኋላም (ከ1517 ጀምሮ) ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ተመሳሳይ የጭቆና መንፈስ አሳይተዋል። እነርሱም ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ ለመሆን የጣሩትን ሰዎች በሰማዕትነት በመግደል በራሳቸው ላይ የደም ዕዳ ከምረዋል። በእውነትም “የቅዱሳን ደም” በብዛት ፈስሶአል።—ራእይ 16:6፤ ከማቴዎስ 23:33-36 ጋር አወዳድር።

ዘሩ ጸንቶ ቆመ

17. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ስንዴና እንክርዳድ የሰጠው ምሳሌ ምን እንደሚሆን ተንብዮ ነበር? (ለ) በ1918 ምን ነገር ተፈጸመ? ይህስ እነማን እንዲወድቁና ማን እንዲሾም ምክንያት ሆነ?

17 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ሕዝበ ክርስትና የበላይ ሆና በምትገዛበት ዘመን ስለሚኖረው የጨለማ ጊዜ ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ ክህደቱ በቆየባቸው መቶ ዘመናት ሁሉ ስንዴ መሰል የሆኑ ግለሰብ ክርስቲያኖች ወይም እውነተኛ ቅቡዓን መገኘት ነበረባቸው። (ማቴዎስ 13:24-29, 36-43) ስለዚህ የጌታ ቀን በጠባበት በጥቅምት ወር 1914 በምድር ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ነበሩ። (ራእይ 1:10) ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በ1918 ይሖዋ “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” የሆነውን ኢየሱስን አስከትሎ ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ለፍርድ” የመጣ ይመስላል። (ሚልክያስ 3:1፤ ማቴዎስ 13:47-50) ይህም ጌታው ሐሰተኛ ክርስቲያኖችን አስወግዶ በንብረቱ ሁሉ ላይ “ታማኝና ልባም ባሪያውን” የሚሾምበት ጊዜ ሆነ።—ማቴዎስ 7:22, 23፤ 24:45-47

18. በ1914 የምን “ሰዓት” ሆነ? ባሪያው ምን የሚያደርግበት ጊዜ ሆነ?

18 በተጨማሪም ለሰባቱ ጉባኤዎች ከተጻፈው መልእክት ለመረዳት እንደምንችለው ይህ ባሪያ ለዚህ የኢየሱስ መልእክት ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ጊዜ ደረሰ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ጉባኤውን ለመፍረድ እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር። ይህም ፍርድ በ1918 ጀምሮአል። (ራእይ 2:5, 16, 22, 23፤ 3:3) የፊልድልፍያን ጉባኤ ‘በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው የፍርድ ሰዓት እንደሚጠብቅ’ ተናግሮ ነበር። (ራእይ 3:10, 11) ይህ “የፍርድ ሰዓት” የመጣው በ1914 የጌታ ቀን እንደጀመረ ነው። ከጌታ ቀን በኋላ ክርስቲያኖች ሁሉ ለተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት ባላቸው ታማኝነት ረገድ ይፈተናሉ።—ከማቴዎስ 24:3, 9-13 ጋር አወዳድር።

19. (ሀ) ዛሬ ሰባቱ ጉባኤዎች ምን ያመለክታሉ? (ለ) ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር የተባበሩ እነማን ናቸው? ኢየሱስ የሰጠው ምክርና የገለጸው ሁኔታ እነርሱንም የሚመለከት የሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) ኢየሱስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰባት ጉባኤዎች የላከውን መልእክት እንዴት መመልከት ይኖርብናል?

19 በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ ኢየሱስ ለጉባኤዎቹ የተናገራቸው ቃላት ዋነኛ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ከ1914 ጀምሮ ነው። በዚህ ዘመን ሰባቱ ጉባኤዎች በጌታ ቀን ያሉትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤዎች በሙሉ ያመለክታሉ። ከዚህም በላይ ባለፉት ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ቁጥራቸው በጣም የበዛ አማኞች በዮሐንስ ከተመሰሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ተባብረዋል። ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ምክርና ሰባቱን ጉባኤዎች በመረመረበት ጊዜ የተገነዘበው ሁኔታ ለእነዚህም አማኞች እኩል ተፈጻሚነት አለው። ምክንያቱም ለይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ የወጣው የጽድቅና የታማኝነት ደረጃ አንድ ዓይነት ነው። (ዘጸአት 12:49፤ ቆላስይስ 3:11) ስለዚህ ኢየሱስ በታናሽቱ እስያ ለነበሩት ሰባት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎች የጻፈው መልእክት ታሪክን ለመስማት ያለንን ጉጉት ለማርካት የተዘጋጁ አይደሉም። ለእያንዳንዳችን ሞት ወይም ሕይወት ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። እንግዲያው ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ እናዳምጥ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 በጥንቱ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ በ⁠ኢሳይያስ 44:6 ላይ “የመጀመሪያ” እና “የመጨረሻ” በሚሉት ቃላት መጨረሻ ላይ “ው” የሚለው ጠቃሽ አመልካች አይገኝም። ኢየሱስ ስለራሱ በተናገረበት በጥንቱ የግሪክኛ ጽሑፍ በ⁠ራእይ 1:17 ላይ ግን “ው” የሚል ጠቃሽ አመልካች አለ። ስለዚህ የሰዋስው አገባቡ እንደሚያመለክተው ራእይ 1:17 የማዕረግ ስምን የሚያመለክት ሲሆን ኢሳይያስ 44:6 ግን የይሖዋን አምላክነት የሚያመለክት ነው።

^ አን.6 አንጄሎስ የተባለው የግሪክኛ ቃል “መልእክተኛ”ም “መልአክ”ም የሚል ትርጉም አለው። በ⁠ሚልክያስ 2:7 ላይ አንድ ሌዋዊ ካህን “መልእክተኛ” (በዕብራይስጥ ማላክ) ተብሎአል።—ባለማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የፈተናና የፍርድ ጊዜ

ኢየሱስ እጩ ንጉሥ ሆኖ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀውና የተቀባው በ29 እዘአ በጥቅምት ወር አካባቢ ነበር። ይህ ከሆነ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በ33 እዘአ በኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተ መቅደስ መጥቶ ቤተ መቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ ያደረጉትን ሰዎች አባረረ። ኢየሱስ ጥቅምት 1914 በሰማይ ከነገሠ በኋላ፣ ፍርድ ከአምላክ ቤት ስለሚጀምር ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩትን ሁሉ ለመመርመር እስኪመጣ ድረስ ሶስት ዓመት ተኩል ማለፉ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ 1 ጴጥሮስ 4:17) የይሖዋ ሕዝቦች ያካሂዱት የነበረው የመንግሥት የሥራ እንቅስቃሴ በ1918 መጀመሪያ ላይ ትልቅ ተቃውሞ ደርሶበት ነበር። በምድር በሙሉ የፈተና ጊዜ ሆኖ ነበር። ፍርሐት የነበራቸው ሁሉ በዚህ ጊዜ ተበጥረዋል። በግንቦት ወር 1918 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የመጠበቂያ ግንብ ማህበርን ባለ ሥልጣኖች አሳስረው ነበር። ከዘጠኝ ወር በኋላ ግን ከእሥራት ተፈቱ። በኋላም የቀረቡባቸው የሐሰት ክሶች ሁሉ ተነሱላቸው። ከ1919 ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች ድርጅት ከተፈተነና ከተጣራ በኋላ የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ በክርስቶስ ኢየሱስ መሪነት የሚገዛው የአምላክ መንግሥት መሆኑን ለማወጅ በቅንዓት ወደፊት መገስገስ ጀመረ።—ሚልክያስ 3:1-3

ኢየሱስ ምርመራውን በ1918 ሲጀምር የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የጥፋተኛነት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስደት በማነሳሳት ብቻ ሳይወሰኑ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እርስበርሳቸው ይዋጉ የነበሩትን መንግሥታት በመደገፍ በራሳቸው ላይ ከባድ የደም ዕዳ ጭነዋል። (ራእይ 18:21, 24) እነዚህ ቀሳውስት ተስፋቸውን የጣሉት ሰው ሠራሽ በሆነው በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ላይ ነበር። በ1919 ሕዝበ ክርስትና ከመላው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ጋር ከአምላክ ሞገስ ውጭ በመሆን ወድቃለች።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኤፌሶን

ሰምርኔስ

ጴርጋሞን

ትያጥሮን

ሰርዴስ

ፊልድልፍያ

ሎዶቂያ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስን የተረጎሙትን፣ ያነበቡትን ወይም በእጃቸው የተገኘባቸውን በማሳደድና በመግደል ከባድ የደም ዕዳ ተሸክማለች