በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ አስገራሚ ምሥጢር ተፈታ

አንድ አስገራሚ ምሥጢር ተፈታ

ምዕራፍ 34

አንድ አስገራሚ ምሥጢር ተፈታ

1. (ሀ) ዮሐንስ ታላቂቱን ጋለሞታና የተቀመጠችበትን አስፈሪ አውሬ በተመለከተ ጊዜ ምን ተሰማው? ለምንስ? (ለ) የዮሐንስ ክፍል የትንቢታዊው ራእይ ፍጻሜ የሆኑ ነገሮች መፈጸማቸውን ሲመለከት ምን ተሰማው?

ዮሐንስ ታላቂቱን ጋለሞታና የተቀመጠችበትን ግዙፍ አውሬ ሲመለከት ምን ተሰማው? ዮሐንስ ራሱ ይነግረናል:- “ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ” (ራእይ 17:6ለ) ተራ የሆነ የሰው አእምሮ እንዲህ ያለውን ትዕይንት ከራሱ ግምት ሊያፈልቅ አይችልም። በአንድ ምድረ በዳ ውስጥ በስካር የደነዘዘች አመንዝራ ሴት በሚያስጠላ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣለች። (ራእይ 17:3) የዮሐንስ ክፍልም እንዲሁ የትንቢታዊውን ራእይ ፍጻሜ ሲመለከት እጅግ ይደነቃል። የዓለም ሰዎች ይህን ሊያዩ ቢችሉ ኖሮ በጣም ተደንቀው ‘የማይታመን ነገር ነው!’ ይሉ ነበር። የዓለም ገዥዎችም ‘የማይታሰብ ነገር ነው!’ በማለት አድናቆታቸውን ያስተጋቡ ነበር። ይሁን እንጂ ራእዩ በዘመናችን በአስገራሚ ሁኔታ እውነት ሆኖአል። የአምላክ ሕዝቦች በራእዩ አፈጻጸም ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው። ይህም ራእዩ ወደ ከፍተኛ ፍጻሜው እንደሚደርስ ማረጋገጫ ይሆንላቸዋል።

2. (ሀ) መልአኩ የዮሐንስን መገረም ተመልክቶ ምን ነገረው? (ለ) ለዮሐንስ ክፍልም ምን ነገር ተገልጦአል? ይህስ የተደረገው እንዴት ነው?

2 መልአኩ የዮሐንስን መደነቅ ተመለከተ። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “መልአኩም አለኝ:- የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምሥጢርና የሚሸከማትን ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምሥጢር እኔ እነግርሃለሁ።” (ራእይ 17:7) አዎ፣ አሁን መልአኩ ምሥጢሩን ይፈታለታል። ዓይኑን አፍጥጦ ለሚመለከተው ለዮሐንስ የራእዩን የተለያዩ ገጽታዎችና የሚገለጹትን አስደናቂ ክንውኖች ይገልጽለታል። ነገሮችን በትጋት የሚከታተለው የዮሐንስ ክፍልም የሚያገለግለው በመላእክት መሪነት እንደመሆኑ መጠን ስለትንቢቶች አፈጻጸም እንዲያስተውል ተደርጎአል። “ሕልምን የሚፈታ እግዚአብሔር አይደለምን?” እንደ ታማኙ ዮሴፍ የራእይ ፍቺ የሚገኘው ከይሖዋ እንደሆነ እናምናለን። (ዘፍጥረት 40:8፤ ከ⁠ዳንኤል 2:29, 30 ጋር አወዳድር።) የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋ ራእዩንና የራእዩ ፍጻሜ በሕይወታቸው ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በሚገልጽላቸው ጊዜ የመድረኩን ዋነኛ ክፍል ይይዛሉ። (መዝሙር 25:14) የሴቲቱንና የአውሬውን ምሥጢር በተገቢው ጊዜ አብራርቶላቸዋል።—መዝሙር 32:8

3, 4. (ሀ) ወንድም ኤን ኤች ኖር በ1942 ምን የሕዝብ ንግግር አድርጎ ነበር? ይህስ ንግግር የቀዩን አውሬ ማንነት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) እርሱ ያብራራውስ መልአኩ ለዮሐንስ የነገረውን የትኛውን ቃል ነበር?

3 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ከመስከረም 18 እስከ 20, 1942 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የአዲሱን ዓለም ቲኦክራቲካዊ ስብሰባ አደረጉ። የስብሰባው ማዕከል የነበረው የክሌቭላንድ ኦሃዮ ከተማ ከ50 ከሚበልጡ ሌሎች ከተሞች ጋር በስልክ መስመር ተያይዞ ስለነበረ 129,699 የሚያክሉ ሰዎች ስብሰባውን ለመከታተል ችለው ነበር። በጊዜው የነበረው የጦርነት ሁኔታ በፈቀደባቸው ሌሎች የዓለም አካባቢዎችም ይኸው የስብሰባ ፕሮግራም ተደርጎአል። በዚያ ጊዜ ብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች ጦርነቱ ተፋፍሞ በአምላክ የጦርነት ቀን በአርማጌዶን ይደመደማል ብለው ይጠባበቁ ነበር። በዚህም ምክንያት “ሰላም፣ ዘላቂ ሊሆን ይችላልን?” በሚል ርዕስ የቀረበው የሕዝብ ንግግር የብዙ ሰዎችን ፍላጎት ቀስቅሶ ነበር። በብሔራት ፊት ተደቅኖ የነበረው ሁኔታ ከሰላም ፈጽሞ የተለየ ሆኖ በሚታይበት ጊዜ አዲሱ የመጠበቂያ ግንብ ፕሬዚደንት ኤን ኤች ኖር ስለ ሰላም ደፍሮ ሊናገር የቻለው እንዴት ነው? * የዮሐንስ ክፍል የአምላክን የትንቢት ቃል ‘ከወትሮው በተለየ ትኩረት’ ይከታተል ስለነበረ ነው።—ዕብራውያን 2:1፤ 2 ጴጥሮስ 1:19

4 “ሰላም፣ ዘላቂ ሊሆን ይችላልን?” የተባለው ንግግር ስለ ትንቢቱ ምን ያብራራው ነገር ነበር? ወንድም ኤን ኤች ኖር በ⁠ራእይ 17:3 ላይ የተጠቀሰው ቀይ አውሬ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር መሆኑን በግልጽ ካመለከተ በኋላ መልአኩ ቀጥሎ ለዮሐንስ በተናገረው ቃል መሠረት በፍጻሜው ስለሚደርስበት ዕጣ አብራራ። መልአኩ ለዮሐንስ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፣ አሁንም የለም፣ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፣ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።”—ራእይ 17:8ሀ

5. (ሀ) አውሬው ‘የነበረው’ እና በኋላም ‘የሌለው’ እንዴት ነው? (ለ) ወንድም ናታን ኖር “የቃል ኪዳኑ ማኅበር ጉድጓዱ ውስጥ እንደገባ ይቀራልን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጠው እንዴት ነው?

5 “ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ።” አዎ፣ ይህ አውሬ ከጥር 10, 1920 ጀምሮ 63 ብሔራትን አሰባስቦ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ ጃፓን፣ ጀርመንና ኢጣልያ ከማኅበሩ ሲወጡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረትም ከማኅበሩ እንድትወጣ ተደረገ። በመስከረም ወር 1939 የጀርመኑ የናዚ አምባገነን መንግሥት ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ቀሰቀሰ። * የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ ስላልቻለ ምንም ሊንቀሳቀስ ወደማይችልበት ጥልቅ ወረደ። በ1942 ነበር ብቻ የሚባልለት ድርጅት ሆነ። ይሖዋ የዚህን ራእይ ሙሉ ትርጉም ለሕዝቦቹ ያብራራው በዚህ ወሳኝ ጊዜ ነበር እንጂ ከዚህ በፊት ወይም ከዚህ በኋላ አልነበረም። ወንድም ኤን ኤች ኖር በአዲሲቱ ዓለም ቲኦክራቲካዊ ስብሰባ ላይ በትንቢቱ መሠረት አውሬው “አሁን የለም” ለማለት ችሎ ነበር። ከዚያም በኋላ “ታዲያ ማኅበሩ ጥልቁ ውስጥ እንደወደቀ ይቀራልን?” ሲል ጠየቀ። ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ ራእይ 17:8ን ጠቅሶ “የዓለማዊ ብሔራት ማኅበር እንደገና ያንሰራራል” አለ። ልክ እንደተናገረው ስለተፈጸመ የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል እውነት መሆኑ ተረጋግጦአል።

ከጥልቁ መውጣት

6. (ሀ) ቀዩ አውሬ ከጥልቁ የወጣው መቼ ነው? ምንስ አዲስ ስም ይዞ ወጣ? (ለ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ ሕይወት የተሰጠው ቀይ አውሬ የነበረው ለምንድን ነው?

6 ቀዩ አውሬ በእርግጥም ከጥልቁ ወጣ። ሰኔ 26, 1945 በሳንፍራንሲስኮ ዩ ኤስ ኤ 50 ብሔራት በብዙ ውካታና ፈንጠዝያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር ተቀበሉ። ይህ ድርጅት “ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት” እንዲያስጠብቅ የተቋቋመ ነበር። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመሳሳሉበት ብዙ መንገድ ነበር። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል:- “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመውን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የሚመስልበት አንዳንድ መንገድ አለ። . . . የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ካቋቋሙት ብሔራት ብዙዎቹ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርንም ያቋቋሙ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ መንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በብሔራት መካከል ሰላም እንዲኖር ለማገዝ የተቋቋመ ድርጅት ነበር። ዋናዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት ከቃል ኪዳኑ ማኅበር አካላት ጋር በብዙ ይመሳሰላሉ።” ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀዩ አውሬ ከሞት ተቀስቅሶ የተቋቋመ ድርጅት ነው ለማለት ይቻላል። 190 የሚያክሉ አገሮችን በአባልነት የያዘ ስለሆነ 63 ከነበሩት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አባል ብሔራት ቁጥር በጣም ይበልጣል። በተጨማሪም ከእርሱ በፊት ከነበረው የቃል ኪዳን ማኅበር ይበልጥ ሰፊ የሆነ የሥራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

7. (ሀ) የምድር ነዋሪዎች አዲስ ሕይወት ያገኘውን ቀይ አውሬ ያደነቁት በምን መንገድ ነው? (ለ) የተባበሩት መንግሥታት ሳይደርስበት የቀረው ግብ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ምን ብለዋል?

7 በመጀመሪያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎ ነበር። ይህም የሆነው መልአኩ በተናገረው ትንቢታዊ ቃል መሠረት ነው። “ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደ ነበረ አሁንም እንደሌለ፣ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።” (ራእይ 17:8ለ) የምድር ነዋሪዎች ሁሉ በኒውዮርክ ከተማ በኢስት ሪቨር ከሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን የሚያካሂደውን ይህን አዲስ ግዙፍ ድርጅት አድንቀዋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፈጽሞ ርቆአል። በ20ኛው መቶ ዘመን በአብዛኞቹ ዓመታት የዓለም ሰላም የተጠበቀው በእንግሊዝኛ MAD በሚል ምህጻረ ቃል በሚታወቀው “የተረጋገጠ የእርስ በርስ መጠፋፋት” (mutual assured destruction) ፍርሐት ስለያዛቸው ብቻ ነው። የጦር መሣሪያዎች እሽቅድምድም በከፍተኛ ፍጥነት በመገስገስ ላይ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለ40 ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በወቅቱ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ የነበሩት ያቭዬር ፔሬዝ ደ ኮያር በ1985 “አሁን የምንኖረው የጭፍን እምነት ያላቸው ግትር ሰዎች በበዙበት ዘመን ነው። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች ምን ማድረግ እንደሚሻለን የምናውቀው ነገር የለም” በማለት በሐዘኔታ ተናግረዋል።

8, 9. (ሀ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዓለም ችግሮች መፍትሔ ሊያገኝ የማይችለው ለምንድን ነው? አምላክ በተናገረው መሠረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምን ነገር ይደርስበታል? (ለ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያቋቋሙና የሚያደንቁ ሰዎች ስማቸው በአምላክ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የማይገኘው ለምንድን ነው? (ሐ) የይሖዋ መንግሥት ምን ነገር በተሳካ ሁኔታ ያስፈጽማል?

8 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለችግሩ መፍትሔ አላገኘም። መፍትሔ ሊያገኝ ያልቻለው ለምንድን ነው? ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕይወት የሰጠው ለሰው ልጆች ሕይወት የሰጠው አምላክ ስላልሆነ ነው። ይህ ድርጅት የአምላክ ቃል እንደሚለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ‘ወደ ጥፋት ስለሚሄድ’ የሕይወት ዘመኑ በጣም አጭር ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ያቋቋሙትና ድርጅቱንም የሚያደንቁት ሰዎች ስማቸው በአምላክ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አይጻፍም። ይሖዋ አምላክ ራሱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ሳይሆን በክርስቶስ መንግሥት አማካኝነት እንደሚያስፈጽም የተናገረውን ዓላማ ኃጢአተኛ፣ ሟችና በአብዛኛው በአምላክ ስም ላይ የሚዘባበቱ ሰዎች እንዴት ሊፈጽሙ ይችላሉ?—ዳንኤል 7:27፤ ራእይ 11:15

9 እንዲያውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመስፍናዊ አገዛዙ ፍጻሜ በሌለውና የሰላም መስፍን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ቦታ የቆመ አስመሳይ ድርጅት ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንዳንድ የሰላም እርምጃዎችን በመውሰድ አንዳንድ የሰላም ቀዳዳዎችን ሊደፍን ቢችልም ብዙም ሳይቆይ ጦርነቶች ይፈነዳሉ። ይህ ደግሞ የኃጢአተኛው የሰው ልጅ ባሕርይ እስካለ ድረስ መኖሩ አይቀርም። “ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ” አልተጻፈም። በክርስቶስ የሚተዳደረው የይሖዋ መንግሥት በምድር ላይ ዘላለማዊ ሰላም ከማስፈኑም በላይ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ የሚገኙትን ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኛ ሙታን ያስነሳል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ከሙታን ከሚነሱት ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሰይጣንና ዘሮቹ ያመጡባቸውን ጥቃቶች ተቋቁመው በታማኝነት የጸኑ ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ ገና ወደፊት ታዛዥነታቸውን ማረጋገጥ የሚኖርባቸው ናቸው። በአምላክ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር የሙጥኝ ብለው የቆዩ ሰዎች ወይም አውሬውን ሲያመልኩ የቆዩ ሰዎች አይኖሩም።—ዘጸአት 32:33፤ መዝሙር 86:8-10፤ ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 16:2፤ 17:5

የሰላምና የደህንነት ተስፋ፣ ከንቱ ተስፋ ነው

10, 11. (ሀ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1986 ምን አውጆ ነበር? የተገኘው ምላሽስ ምን ነበር? (ለ) በኢጣልያ አሲዚ ስለ ሰላም ለመጸለይ ስንት “ሃይማኖታዊ ቤተሰቦች” ተሰብስበው ነበር? እንደዚህ ያለውን ጸሎት አምላክ ይሰማልን? ግለጽ።

10 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰው ልጆችን ተስፋ ለማጠናከር ሲል 1986 “የሰው ልጆችን ሰላምና የወደፊት ሕልውና ማስጠበቅ” በሚል መርሕ “ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት” ተብሎ እንዲከበር አውጆ ነበር። እርስ በርሳቸው ይዋጉ የነበሩ ብሔራት እጅግ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል እንኳን የጦር መሣሪያዎቻቸውን እንዲያሳርፉ ተጠይቀው ነበር። ታዲያ የተገኘው ምላሽ እንዴት ያለ ነበር? ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም እንደዘገበው በ1986 ብቻ በተደረጉት ጦርነቶች ምክንያት አምስት ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል። ልዩ ሣንቲሞችና የመታሰቢያ ቴምብሮች ቢታተሙም እንኳን አብዛኞቹ ብሔራት የሰላምን መንገድ ለመከታተል በዚያ ዓመት ለተጀመረው ጥረት ምንም ያደረጉት አስተዋጽኦ አልነበረም። ይሁን እንጂ ምን ጊዜም ቢሆን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ለመወዳጀት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የዓለም ሃይማኖቶች ይህ ዓመት በተለያዩ መንገዶች እንዲታወቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጥር 1 ቀን 1986 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሥራ ካሞገሱ በኋላ ዓመቱን የሰላም ዓመት ብለው ሰይመዋል። ጥቅምት 27 ቀን ደግሞ አብዛኞቹን የዓለም ሃይማኖት መሪዎች በኢጣልያ አገር በአሲዚ ተሰብስበው ስለ ሰላም እንዲጸልዩ አድርገዋል።

11 አምላክ እንደዚህ ያለውን የሰላም ጸሎት ይሰማልን? እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የጸለዩት ለየትኛው አምላክ ነበር? እያንዳንዱን የሃይማኖት ቡድን ብትጠይቁ የተለያየ መልስ ይሰጣችኋል። በብዙ የተለያዩ መንገዶች የቀረቡትን ጸሎቶች የሚሰሙ ይህን የሚያክሉ ብዙ አማልክት አሉን? ከሥርዓተ ጸሎቱ ተካፋዮች መካከል ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትናን ሥላሴ የሚያመልኩ ናቸው። * ቡድሂስቶች ሂንዱዎችና ሌሎቹ ጸሎታቸውን የደገሙት ቁጥር ስፍር ለሌላቸው አማልክቶቻቸው ነው። በአጠቃላይ 12 “ሃይማኖታዊ ቤተሰቦች” ተሰብስበው ነበር። ሃይማኖታዊ ድርጅቶቻቸውን ወክለው ከተገኙት መካከል የአንግሊካኑ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ፣ የቡድሂዝም ዳላይ ላማ፣ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ፣ የቶክዮ የሺንቶ ቤተ ጸሎቶች ማኅበር ፕሬዚደንት፣ የአፍሪካ ጣዖት አምላኪዎችና፣ በቀለማት ያሸበረቀ የራስ ጥምጥም ያደረጉ ሁለት የአሜሪካ ሕንዶች ይገኙ ነበር። ግፋ ቢል ያደረጉት ነገር ቢኖር በቴሌቪዥን ላይ ሲታዩ የሰው ዓይን የሚስቡ መሆናቸው ነው። ከመካከላቸው አንደኛው ቡድን በአንድ ጊዜ ብቻ ሳያቋርጥ ለ12 ሰዓታት ጸልዮአል። (ከ⁠ሉቃስ 20:45-47 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ከእነዚህ ጸሎቶች መካከል አንዱም እንኳን ከስብሰባው ሥፍራ በላይ ካንዣበበው ደመና አልፎ ሄዶ ይሆን? አልሄደም። ይህም የሆነው በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሣ ነው:-

12. አምላክ የዓለም ሃይማኖታዊ መሪዎች ስለ ሰላም ያደረጉትን ጸሎት ያልመለሰው በምን ምክንያቶች ነው?

12 ከእነዚህ ሃይማኖተኞች አንዱም እንኳን ሕያው አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አልጸለየም። ይህም ‘በይሖዋ ስም ከሚመላለሱት ሰዎች’ የተለዩ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ ውስጥ 7,000 ያህል ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። (ሚክያስ 4:5፤ ኢሳይያስ 42:8, 12) * ሁሉም አንድ ሆነው በኢየሱስ ስም ወደ አምላክ አልቀረቡም። እንዲያውም አብዛኞቻቸው በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ነበሩ። (ዮሐንስ 14:13፤ 15:16) አምላክ ለዘመናችን ያለው ፈቃድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይሆን መጪው የአምላክ መንግሥት ብቸኛው የሰው ልጅ ተስፋ መሆኑን ማወጅ ነው። አንዳቸውም ቢሆኑ የአምላክን ፈቃድ አያደርጉም። (ማቴዎስ 7:21-23፤ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) ሃይማኖታዊ ድርጅቶቻቸው በአብዛኛው በታሪክ ዘመናት ውስጥ በደም አፋሳሽ ጦርነቶች ተካፍለዋል። ከእነዚህም ጦርነቶች መካከል በ20ኛው መቶ ዘመን የተደረጉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች ይገኙበታል። አምላክ እንደነዚህ ላሉት ሃይማኖተኞች እንዲህ ይላቸዋል:- “ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፣ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።”—ኢሳይያስ 1:15፤ 59:1-3

13. (ሀ) የዓለም ሃይማኖታዊ መሪዎች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር የሰላም ጥሪ ማድረጋቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) ለሰላም የሚደረገው ጩኸት የሚደመደመው በየትኛው መለኮታዊ ትንቢት ፍጻሜ ነው?

13 ከዚህም በላይ የዓለም ሃይማኖት መሪዎች በዚህ ዘመን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ተቀናጅተው የሰላም ጥሪ ማድረጋቸው በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። በተለይ ከሕዝቦቻቸው መካከል አብዛኞቹ ከሃይማኖት እየራቁ በሄዱበት በዚህ ዘመናዊ ዓለም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለራሳቸው ጥቅም ሊገለገሉበት ይፈልጋሉ። በጥንትዋ እሥራኤል እንደነበሩት ከዳተኛ መሪዎች “ሰላም ሳይሆን ሰላም፣ ሰላም ይላሉ።” (ኤርምያስ 6:14) ለሰላም የሚያደርጉት ጩኸት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተነበየለትን ታላቅ ክንውን በመደገፍ ሲሰማ እንደሚቆይ ምንም አያጠራጥርም። “የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም።”—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3

14. “ሰላምና ደኅንነት” የሚለው ጩኸት ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው ይችላል? በዚህስ ከመታለል ለመዳን የሚቻለው እንዴት ነው?

14 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፖለቲካ ሰዎች፣ የተለያዩ ሰብዓዊ እቅዶችን ለመግለጽ “ሰላምና ደኅንነት” በሚለው ሐረግ ሲጠቀሙ ይሰማል። የዓለም መሪዎች ሰላም ለማስፈን የሚያደርጓቸው እንደነዚህ ያሉት ጥረቶች 1 ተሰሎንቄ 5:3 ፍጻሜውን ማግኘት መጀመሩን ያመለክቱ ይሆን? ወይስ ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ሲጽፍ የዓለምን ትኩረት በሙሉ የሚስብ አንድ አስደናቂ ክንውን እንደሚኖር መጠቆሙ ነበር? አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚቻለው ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ አሊያም እየተፈጸሙ እያሉ ብቻ በመሆኑ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መታገስ ይኖርብናል። እስከዚያው ድረስ ግን መንግሥታት ሰላምና ደኅንነት በማስፈን ረገድ የቱንም ያህል የተሳካላቸው ቢመስልም ያን ያህል ትልቅ ለውጥ እንደማያመጡ ክርስቲያኖች ያውቃሉ። ራስ ወዳድነት፣ ጥላቻ፣ ወንጀል፣ የቤተሰብ መፈራረስ፣ ብልግና፣ በሽታ፣ ሐዘንና ሞት መኖራቸው አይቀርም። ስለዚህ የዓለም ሁኔታዎችን ትርጉም የምትከታተልና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ልብ የምትል ከሆነ “ሰላምና ደኅንነት ነው” የሚለው ጩኸት አንተን ሊያስትህ አይገባም።—ማርቆስ 13:32-37፤ ሉቃስ 21:34-36

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ጥር 8 ቀን 1942 ሲሞት ወንድም ኤን ኤች ኖር በእርሱ ምትክ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚደንት ሆነ።

^ አን.5 ህዳር 20 ቀን 1940 ጀርመን፣ ኢጣልያ፣ ጃፓንና ሃንጋሪ “አዲስ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር” ለማቋቋም ተፈራረሙ። ይህ ከሆነ ከአራት ቀን በኋላ ቫቲካን ለሃይማኖታዊ ሰላምና ለአዲስ የነገሮች ሥርዓት የቅዳሴና የጸሎት ሥርዓት በሬዲዮ አስተላለፈች። ይህ “አዲስ የቃል ኪዳን ማኅበር” ሊቋቋም አልቻለም።

^ አን.11 የሥላሴ ጽንሰ ሐሳብ የመጣው ከጥንትዋ ባቢሎን ነው። በዚያ አገር የፀሐይ አምላክ የሆነው ሻማሽ፣ የጨረቃ አምላክ የሆነው ሲንና የኮከብ አምላክ የሆነው ኢሽታር በሥላሴነት ይመለኩ ነበር። ግብፅም ይህንኑ የሚመስል የአምልኮ ሥርዓት በመከተል ኦሲሪስን፣ አይሲስንና ሆረስን ታመልክ ነበር። የአሶር ዋነኛ አምላክ የነበረው አሱር ሦስት ራሶች እንዳሉት ሆኖ ተስሎአል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ሥርዓት በመከተል በየአብያተ ክርስቲያናትዋ አምላክ ሦስት ራሶች እንዳሉት ሆኖ እንዲሳል አድርጋለች።

^ አን.12 በ1993 የወጣው የዌብስተር ሦስተኛ አዲስ ኢንተርናሽናል መዝገበ ቃላት ይሖዋ አምላክን “የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ የሚያመልኩት ከሁሉም በላይ የሆነ አምላክ” በማለት ይገልጸዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 250 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የሰላም” እንቆቅልሽ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1986ን ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት ብሎ ቢሰይምም ራስን በራስ ለማጥፋት የሚደረገው የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም ተፋፍሞአል። የ1986 የዓለም ወታደራዊና ማኅበራዊ ወጪ የሚከተሉትን አሳሳቢ ዝርዝር መግለጫዎች ሰጥቶአል:-

በ1986 የዓለም ወታደራዊ ወጪ 900 ሺህ ሚልዮን ዶላር ደርሶአል።

ለአንድ ሰዓት ወታደራዊ ወጪ የዋለው ገንዘብ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ በሚችሉ ተዛማጅ በሽታዎች የሞቱትን 3.5 ሚልዮን ሰዎች ለመክተብ ይበቃ ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ በከባድ ድህነት የሚኖር ነው። ዓለም በሁለት ቀናት ውስጥ ለጦር መሣሪያዎች የሚያወጣው ገንዘብ እነዚህን ሰዎች በሙሉ ለአንድ ዓመት ሊቀልብ ይችል ነበር።

በዓለም የጦር መሣሪያ መጋዘኖች የተቆለሉት የኑክሌር መሣሪያዎች የፍንዳታ ኃይል ከቸርኖብል ፍንዳታ 160,000,000 ጊዜ ይበልጥ ነበር።

በ1945 በሂሮሺማ ላይ ከፈነዳው ቦምብ 500 ጊዜ የሚበልጥ የፍንዳታ ኃይል ያለው ቦምብ ማቅረብ ተችሏል።

የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ከሚሊዮን ሂሮሺማዎች የሚበልጡ ለማጥፋት ኃይል ነበራቸው። 38 ሚልዮን ሰዎች በሞቱበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጣሉት ፈንጂዎች 2,700 ጊዜ የሚበልጥ የፍንዳታ ኃይል ነበራቸው።

ጦርነቶች በጣም ብዙዎችና ብዙ እልቂት የሚያስከትሉ ሆነው ነበር። በ18ኛው መቶ ዘመን በጦርነት ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 4.4 ሚልዮን ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን 8.3 ሚልዮን ሰዎች ሲሞቱ በ20ኛው መቶ ዘመን በመጀመሪያዎቹ 86 ዓመታት ውስጥ 98.8 ሚልዮን ሰዎች ሞተዋል። ከ18ኛው መቶ ዓመት ወዲህ በጦርነት የሞቱ ሰዎች ቁጥር እድገት ከዓለም ሕዝብ ቁጥር እድገት ከስድስት ጊዜ በሚበልጥ ፍጥነት ጨምሯል። በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረገ በእያንዳንዱ ጦርነት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በ19ኛው መቶ ዘመን ከሞቱት አሥር ጊዜ የሚበልጥ ነበር።

[በገጽ 247 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ስለ ቀዩ አውሬ በትንቢት እንደ ተነገረው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ጥልቁ ገብቶ እንደገና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተብሎ ብቅ አለ

[በገጽ 249 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን “የሰላም ዓመት” በመደገፍ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሃይማኖቶች ተወካዮቻቸው በኢጣልያ አሲዚ ተገኝተው ባቢሎናዊ ጸሎቶችን አቅርበዋል። ይሁን እንጂ አንዳቸውም እንኳን ሕያው ለሆነው አምላክ ለይሖዋ አልጸለዩም