በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንጸባራቂዋ ከተማ

አንጸባራቂዋ ከተማ

ምዕራፍ 43

አንጸባራቂዋ ከተማ

ራእይ 16--ራእይ 21:9 እስከ 22:5

ርዕሰ ጉዳይ:- ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተሰጠ መግለጫ

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከታላቁ መከራና ከሰይጣን መታሰር በኋላ

1, 2. (ሀ) መልአኩ ዮሐንስን አዲሲቱ ኢየሩሳሌምን እንዲመለከት የወሰደው ወዴት ነበር? እዚህስ ላይ አስቀድሞ ተመልክቶት ከነበረው የተለየ ምን ሁኔታ አየን? (ለ) ይህ የራእይ መጽሐፍ ታላቅ መደምደሚያ የሆነው ለምንድን ነው?

አንድ መልአክ ታላቂቱ ባቢሎንን ሊያሳየው ዮሐንስን ወደ ምድረ በዳ ወስዶት ነበር። አሁን ደግሞ ከዚሁ የመላእክት ቡድን የወጣ መልአክ ዮሐንስን ወደ ታላቅ ተራራ ወሰደው። ቀድሞ ከተመለከተው በጣም የተለየ ሁኔታ ተመለከተ። በዚህ ቦታ የተመለከተው እንደ ጋለሞታይቱ ባቢሎን ያለች እርኩስና አመንዝራ ከተማ ሳይሆን ንጹሕ፣ ቅድስት የሆነችውንና ከሰማይ የወረደችውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ነው።—ራእይ 17:1, 5

2 ምድራዊት ኢየሩሳሌም እንኳን ይህን የመሰለ ክብር አግኝታ አታውቅም። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሰባቱም ኋለኛዎቹ መቅሰፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ:- ወደዚህ ና፣ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፣ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።” (ራእይ 21:9-11ሀ) ዮሐንስ በዚህ ከፍተኛ ተራራ አናት ላይ ሆኖ የዚህችን ውብ ከተማ የተለያዩ የውበት ገጽታዎች በዝርዝር ተመልክቶአል። የሰው ልጅ በኃጢአትና በሞት ባርነት ሥር ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ የእምነት ሰዎች የዚህችን ከተማ መምጣት በናፍቆት ሲጠባበቁ ኖረዋል። አሁን በመጨረሻ ላይ ከተማይቱ ታየች። (ሮሜ 8:19፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22, 23፤ ዕብራውያን 11:39, 40) ከ144,000 ፍጹም አቋም ጠባቂዎች የተውጣጣች፣ በቅድስና የምታንጸባርቅና የይሖዋ ክብር ነጸብራቅ የሆነች ታላቅ ግርማ ያላት ከተማ ነች። ታላቁ የራእይ መደምደሚያ ይህ ነው።

3. ዮሐንስ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ውበት የገለጸው እንዴት ነው?

3 የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውበት በጣም አስደናቂ ነው። “ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፣ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፣ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፣ በሰሜንም ሦስት ደጆች፣ በደቡብም ሦስት ደጆች፣ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት። በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።” (ራእይ 21:11ለ-14) ዮሐንስ በመጀመሪያ ያስደነቀውና የመዘገበው የከተማይቱን ድምቀትና ብርሃን መሆኑ ተገቢ ነው። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እንደ አዲስ ሙሽራ ደምቃ ስለነበር ለክርስቶስ የምትገባ ሙሽራ ሆናለች። ‘የብርሃናት ሁሉ አባት’ በሆነው አምላክ የተፈጠረች ስለሆነች በታላቅ ብርሃን የምታንጸባርቅ መሆንዋ ተገቢ ነው።—ያዕቆብ 1:17

4. አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሥጋዊ የእስራኤል ብሔር እንዳልሆነች እንዴት እናውቃለን?

4 በ12ቱ በሮች ላይ የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸዋል። ስለዚህ ይህች ምሳሌያዊት ከተማ ‘ከእስራኤል ልጆች ነገዶች ሁሉ በታተሙት’ 144,000 ሰዎች አባልነት የተገነባች ናት። (ራእይ 7:4-8) የመሠረት ድንጋዮቹም ከዚህ ጋር በመስማማት የበጉ አሥራ ሁለት ሐዋርያት ስሞች ተጽፈውባቸዋል። አዎ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በ12ቱ የያዕቆብ ልጆች ላይ የተመሠረተችው ሥጋዊት ብሔር አይደለችም። “በሐዋርያትና በነቢያት” ላይ የተመሠረተችው መንፈሣዊት እስራኤል ነች።—ኤፌሶን 2:20

5. የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ትልቅና ከፍተኛ ቅጥር’ ምን ያመለክታል? በእያንዳንዱ በር ላይ መላእክት መቆማቸውስ?

5 ምሳሌያዊቷ ከተማ በጣም ትልቅ ቅጥር አላት። በጥንት ዘመናት ከተማዎችን ከጠላት ጥቃት ለመጠበቅ ቅጥሮች ይሠሩ ነበር። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም “ታላቅና ረዥም ቅጥር” ያላት መሆኑ ከተማይቱ በመንፈሣዊ የምትሰጋበት ምንም ምክንያት እንደሌላት ያመለክታል። የጽድቅ ጠላት የሆነ ወይም ንጹሕና ሐቀኛ ያልሆነ ሊገባባት አይችልም። (ራእይ 21:27) ወደዚህች የተዋበች ከተማ እንዲገቡ ለተፈቀደላቸው ግን ወደ ገነት እንደገቡ ይቆጠራል። (ራእይ 2:7) አዳም ከገነት ከተባረረ በኋላ ንጹሕ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይገቡበት ለማገድ በመጀመሪያው ገነት መግቢያ በር ላይ ኪሩቤሎች እንዲቆሙ ተደርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 3:24) በተመሳሳይም የቅድስቲቱ ከተማ የኢየሩሳሌም መንፈሣዊ ደህንነቷ እንዲጠበቅ በእያንዳንዱ በር ላይ መላእክት ቆመው ነበር። በዚህ የፍጻሜ ዘመንም ቢሆን መላእክት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚሆነውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በባቢሎናዊ እርኩሰት እንዳይበከል ሲጠብቁ ቆይተዋል።—ማቴዎስ 13:41

ከተማይቱን መለካት

6. (ሀ) ዮሐንስ የከተማይቱን መለካት እንዴት በማለት ገልጾአል? ይህስ መለካት ምን ያመለክታል? (ለ) መለኪያው ‘የሰው ልክና የመላእክት ልክ’ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።)

6 ዮሐንስ ትረካውን በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፣ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው። ቅጥርዋንም ለካ፣ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፣ እርሱም በመልአክ ልክ።” (ራእይ 21:15-17) የቤተ መቅደሱ መለካት ይሖዋ ለቤተ መቅደሱ ያወጣው ዓላማ ስለመፈጸሙ ዋስትና እንደሚሆን ተገልጾአል። (ራእይ 11:1) አሁን ደግሞ መልአኩ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም መለካቱ ይሖዋ ለዚህች ታላቅ ከተማ ያወጣው ዓላማ የማይለወጥ መሆኑን ያመለክታል። *

7. የከተማይቱ ልክ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ይህች ከተማ በጣም አስደናቂ የሆነች ከተማ ነች። ቁመትዋ፣ ስፋትዋና ከፍታዋ እኩል ሲሆን ዙሪያዋ 12,000 ምዕራፍ ወይም 2,200 ኪሎ ሜትር ነው። ዙሪያዋን 144 ክንድ ወይም 210 ጫማ ከፍታ ባለው ቅጥር ታጥራለች። እንዲህ ያለ መጠን ያለው እውነተኛ ከተማ ሊኖር አይችልም። ዘመናዊቱን ኢየሩሳሌም 14 ጊዜ የሚያጥፍ ስፋት ያለውና 560 ኪሎ ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ሰማይ ጠቀስ ከተማ ይሆናል። የራእይ መጽሐፍ የተገለጸው በምልክቶች ነው። ታዲያ እነዚህ ልኮች ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን ያመለክታሉ?

8. (ሀ) የከተማይቱ ቅጥር 144 ክንድ ከፍታ ያለው መሆኑ (ለ) የከተማይቱ ልክ 12,000 ምዕራፍ መሆኑ (ሐ) የከተማይቱ ቅርጽ በሁሉም በኩል የተስተካከለ ኩብ መሆኑ ምን ያመለክታል?

8 144 ክንድ ከፍታ ያለው ቅጥር ከተማይቱ የተገነባችው በ144,000ዎቹ የአምላክ መንፈሣዊ ልጆች አባልነት እንደሆነ ያሳስበናል። የዚህ ከተማ ቁመት፣ ስፋትና ከፍታ 12,000 ምዕራፍ ነው። አስራ ሁለት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የድርጅታዊ ዝግጅት ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። ስለዚህ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የአምላክን ዘላለማዊ ዓላማ ለማስፈጸም በከፍተኛ ደረጃ የተዋቀረች ድርጅታዊ ዝግጅት ነች። አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋን መንግሥታዊ ድርጅት ይመሠርታሉ። በተጨማሪም የከተማይቱ ቅርጽ ማለትም ርዝመት፣ ስፋትና ከፍታ እኩል ነው። በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ የይሖዋ መገኘት ምሳሌ የሆኑት ነገሮች የሚገኙበት ቅድስተ ቅዱሳን ርዝመቱ፣ ስፋቱና ከፍታው እኩል ነበር። (1 ነገሥት 6:19, 20) የይሖዋ ክብር ያበራባት አዲሲቱ ኢየሩሳሌምም ርዝመቱ፣ ስፋቱና ከፍታው እኩል የሆነ የኩብ ቅርጽ ያላት መሆንዋ በጣም ተገቢ ነው። ልኮችዋ ሁሉ የተመጣጠኑ ናቸው። ምንም ዓይነት ጉድለት ወይም ወጣ ገባ የሆነ ነገር የሌለባት ከተማ ነች።—ራእይ 21:22

በጣም ውድ የሆኑ የሕንጻ መሥሪያ ዕቃዎች

9. ዮሐንስ ከተማይቱ የታነጸችባቸውን የግንባታ ዕቃዎች ምን በማለት ገልጾአል?

9 ዮሐንስ መግለጫውን በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ቅጥርዋም ከኢያስጲድ የተሠራ ነበረ፣ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች። የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፣ ፊተኛው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አሥራ አንደኛው ያክንት፣ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፣ እያንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።”—ራእይ 21:18-21

10. ከተማይቱ የተሰራችው በኢያስጲድ፣ በወርቅና በተለያዩ ‘የከበሩ ድንጋዮች’ መሆኑ ምን ያመለክታል?

10 የከተማይቱ አሠራር በእውነትም በጣም አንጸባራቂ ነው። ርካሽና ተራ ስለሆኑ እንደ ሸክላና እንደ ድንጋይ ስላሉት ምድራዊ የሕንጻ መሣሪያዎች ሳይሆን ስለ ኢያስጲድ፣ ስለተጣራ ወርቅና ስለተለያዩ ‘የከበሩ ድንጋዮች’ እናነባለን። እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ሁሉ ሰማያዊ የሕንጻ መሣሪያዎችን የሚያመለክቱ መሆናቸው ተገቢ ነው። ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነና የተዋበ ነገር ሊኖር አይችልም። የጥንቱ የቃል ኪዳን ታቦት በወርቅ የተለበጠ ነበር። በተጨማሪም ወርቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ውድና ጥሩ የሆኑ ነገሮችን ያመለክታል። (ዘጸአት 25:11፤ ምሳሌ 25:11፤ ኢሳይያስ 60:6, 17) መላዋ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ አደባባዮችዋ እንኳን ሳይቀሩ እንደ መስተዋት ከጠራ ወርቅ የተሠሩ ናቸው። ለግምት እንኳን የሚያስቸግር ከፍተኛ ዋጋና ውበት እንዳላት ያመለክታል።

11. የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባሎች በጣም ከፍተኛ በሆነ መንፈሳዊ ንጽሕና የሚያበሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?

11 እንዲህ ያለ ጥራት ያለው ወርቅ ሊያነጥር የሚችል ሰብዓዊ አንጥረኛ ሊኖር አይችልም። ታላቁ አንጥረኛ ይሖዋ አምላክ ነው። ብር አንጣሪና አጣሪ ሆኖ ተቀምጦአል። የመንፈሳዊ እስራኤልን ታማኝ ግለሰብ አባሎች ‘እንደ ብርና እንደ ወርቅ’ በማንጠር ማንኛውንም ዓይነት እድፈትና ጉድፍ ያስወግድላቸዋል። የመጨረሻዎቹ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባሎች የሚሆኑት በዚህ ዓይነት የነጠሩና የተጣሩ ግለሰቦች ብቻ ናቸው። በዚህም መንገድ ይሖዋ ከፍተኛ የመንፈሳዊ ጥራት ደረጃ ባላቸው ሕያዋን የሕንጻ መሣሪያዎች ከተማይቱን ያንጻል።—ሚልክያስ 3:3, 4

12. (ሀ) የከተማይቱ መሠረቶች በ12 የከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ መሆናቸው (ለ) የከተማይቱ በሮች ዕንቁ መሆናቸው ምን ያመለክታል?

12 የከተማዋ መሠረቶች እንኳን በ12 የከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ስለሆኑ በጣም የተዋቡ ናቸው። ይህም በበዓል ቀናት እዚህ ላይ ከተገለጹት ጋር በሚመሳሰሉ አሥራ ሁለት የተለያዩ እንቁዎች ያጌጠ ኤፉድ ይለብስ የነበረውን የአይሁድ ሊቀ ካህናት ያስታውሰናል። (ዘጸአት 28:15-21) ይህ በአጋጣሚ ብቻ የሆነ መመሳሰል አይደለም። ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ “መብራት” የሆነላት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የምታከናውነውን ክህነታዊ አገልግሎት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። (ራእይ 20:6፤ 21:23፤ ዕብራውያን 8:1) በተጨማሪም የኢየሱስ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ጥቅሞች ለሰው ልጆች የሚተላለፉት በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በኩል ነው። (ራእይ 22:1, 2) እያንዳንዳቸው ከፍተኛ ውበት ካላቸው ዕንቁዎች የተሠሩት የከተማይቱ 12 በሮችም ኢየሱስ መንግሥቱን ከፍተኛ ዋጋ ባለው ዕንቁ በመመሰል የተናገረውን ምሳሌ ያስታውሰናል። በእነዚህ በሮች የሚገባ ሁሉ ለመንፈሣዊ ነገሮች ከፍተኛ ዋጋና ትልቅ አድናቆት ያሳየ ሰው ነው።—ማቴዎስ 13:45, 46፤ ከ⁠ኢዮብ 28:12, 17, 18 ጋር አወዳድር።

የብርሃን ከተማ

13. ዮሐንስ ቀጥሎ ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን ተናገረ? ከተማይቱ ግዑዝ የሆነ ቤተ መቅደስ የማያስፈልጋት ለምንድን ነው?

13 በሰሎሞን ዘመን በኢየሩሳሌም ከተማ ጎላ ብሎ ይታይ የነበረው ከከተማይቱ በስተሰሜን በኩል ትልቅ ከፍታ በነበረው በሞሪያ ተራራ ላይ የተሠራው ቤተ መቅደስ ነበር። አዲሲቱ ኢየሩሳሌምስ? ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሁሉን የሚገዛ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ፣ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።” (ራእይ 21:22, 23) በእውነትም በዚህ ሥፍራ ቤተ መቅደስ መሥራት አስፈላጊ አይደለም። የጥንቱ የአይሁድ ቤተ መቅደስ በጥላነት የሚያገለግል ምሳሌ ብቻ ነበር። የዚህ ጥላ እውነተኛ አካል ደግሞ ማለትም ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ይሖዋ ኢየሱስን ሊቀ ካህናት አድርጎ ከቀባበት ከ29 እዘአ ጀምሮ ሕልውናውን አግኝቶአል። (ማቴዎስ 3:16, 17፤ ዕብራውያን 9:11, 12, 23, 24) በተጨማሪም ቤተ መቅደስ ከኖረ ስለ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት የሚያቀርብ የካህናት ክፍል መኖር ይገባዋል። ይሁን እንጂ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል የሆኑት ሁሉ ካህናት ናቸው። (ራእይ 20:6) በተጨማሪም ታላቁ መሥዋዕት፣ የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ለአንዴና ለሁልጊዜ ተሰጥቶአል። (ዕብራውያን 9:27, 28) ከዚህም በላይ በዚህች ከተማ የሚኖር ሁሉ በቀጥታ ወደ ይሖዋ ሊቀርብ ይችላል።

14. (ሀ) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ፀሐይና ጨረቃ እንዲያበሩላት የማያስፈልጋት ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ ስለ ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር? ይህስ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም የሚመለከተው እንዴት ነው?

14 የይሖዋ ክብር በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አጠገብ ባለፈ ጊዜ የሙሴ ፊት በድምቀት እንዲያበራ ስላደረገ ሙሴ በወገኖቹ በእስራኤላውያን አጠገብ ሲሆን ፊቱን ለመሸፈን ተገድዶ ነበር። (ዘጸአት 34:4-7, 29, 30, 33) እንዲህ ከሆነ ዘወትር የይሖዋ ክብር የሚያበራባት ከተማ ምን ዓይነት ድምቀት ሊኖራት እንደሚችል መገመት ይቻላል። እንዲህ ያለችው ከተማ የጨለማ ጊዜ ሊኖራት አይችልም። ቃል በቃል ፀሐይ ወይም ጨረቃ አያስፈልጋትም። ከዘላለም እስከ ዘላለም ብርሃንዋ እንደፈነጠቀ ይኖራል። (ከ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:16 ጋር አወዳድር።) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እንዲህ ባለው ብርሃንና ድምቀት የተጥለቀለቀች ነች። ይህች ሙሽራና ሙሽራው ንጉሥ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ማዕከል፣ የአምላክ “ሴት”፣ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ይሆናሉ። ስለ እርስዋም ኢሳይያስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሮአል:- “ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የዘላለም ብርሃንሽ፣ አምላክሽ፣ ክብርሽ ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም። የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያበራልሽም። እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፣ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም፣ ጨረቃሽም አይቋረጥም።”—ኢሳይያስ 60:1, 19, 20፤ ገላትያ 4:26

ለአሕዛብ ብርሃን

15. ከኢሳይያስ ትንቢት ጋር የሚመሳሰለው የትኛው የራእይ ቃል ነው?

15 ይኸው ትንቢት “አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ፀዳል ይመጣሉ” ሲል ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 60:3) እነዚህ ቃላት አዲሲቱ ኢየሩሳሌምንም የሚመለከቱ እንደሚሆኑ የራእይ መጽሐፍ ያመለክታል:- “አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፣ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፣ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ።”—ራእይ 21:24-26

16. በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ብርሃን የሚመላለሱት “አሕዛብ” እነማን ናቸው?

16 በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ብርሃን የሚመላለሱት እነዚህ “አሕዛብ” እነማን ናቸው? በአንድ ወቅት የዚህ ክፉ ዓለም ሕዝቦች ክፍል የነበሩና “ከሕዝብ ከነገድና ከቋንቋ” ተውጣጥተው ከዮሐንስ ክፍል ጋር በመተባበር አምላክን ቀንና ሌሊት የሚያመልኩ ሕዝቦች ናቸው። (ራእይ 7:9, 15) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ስትወርድና ኢየሱስ በሞትና በሲኦል ቁልፍ ተጠቅሞ ሙታንን ሲያስነሳ ቀድሞ “አሕዛብ” የነበሩ ወደፊት ግን ይሖዋንና የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በግ መሰል ባል የሆነውን ልጁን የሚወዱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይተባበሩአቸዋል።ራእይ 1:18

17. ክብራቸውን ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚያመጡት “የምድር ነገሥታት” እነማን ናቸው?

17 ታዲያ ‘ክብራቸውን ይዘው የሚመጡት’ “የምድር ነገሥታት” እነማን ናቸው? ቃል በቃል የምድር ነገሥታት የነበሩት ከአምላክ መንግሥት ጋር በአርማጌዶን ተዋግተው ወደ ጥፋት ወርደዋል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:17, 18) እነዚህ ነገሥታት በአሕዛብ መካከል ከፍተኛ ከበሬታ ይሰጣቸው የነበሩና የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑ ሰዎች ወይም በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ራሳቸውን ለአምላክ መንግሥት የሚያስገዙ ከሙታን የተነሱ ነገሥታት ሊሆኑ ይችላሉን? (ማቴዎስ 12:42) ሊሆኑ አይችሉም፣ ምክንያቱም የእነዚህ ነገሥታት ክብር በአብዛኛው ዓለማዊ ከመሆኑም በላይ ከጠፋና ከተረሳ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ስለዚህ ክብራቸውን ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚያመጡት “የምድር ነገሥታት” ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነገሥታት ሆነው እንዲገዙ “ከነገድ ከሕዝብና ከቋንቋ” የተዋጁት 144,000ዎች ናቸው። (ራእይ 5:9, 10፤ 22:5) ለከተማይቱ አንጸባራቂነት ድምቀት ለመጨመር ሲሉ አምላክ የሰጣቸውን ክብር ይዘው ይመጣሉ።

18. (ሀ) ከአዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚገለሉት እነማን ናቸው? (ለ) ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው እነማን ብቻ ናቸው?

18 ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፣ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።” (ራእይ 21:27) የሰይጣን ሥርዓት እድፍ የነካው ማንኛውም ነገር የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል ሊሆን አይችልም። በሮችዋ ሁልጊዜ የተከፈቱ ቢሆኑም “ርኩሰትና ውሸት” የያዘ ሰው እንዲገባባት አይፈቀድለትም። በዚያች ከተማ ውስጥ ከሃዲዎች ወይም የታላቂቱ ባቢሎን አባሎች የሆኑ ሰዎች አይኖሩም። ገና በምድር ላይ የቀሩትን የከተማይቱን የወደፊት አባሎች በማበላሸት ከተማይቱን ለማርከስ የሚሞክሩ ቢኖሩ ሙከራቸው አይሳካላቸውም። (ማቴዎስ 13:41-43) በመጨረሻ ላይ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚገቡት “በበጉ የሕይወት መጽሐፍ” የተጻፉት 144, 000ዎች ብቻ ናቸው። *ራእይ 13:8፤ ዳንኤል 12:3

የሕይወት ውኃ ወንዝ

19. (ሀ) ዮሐንስ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለሰው ልጆች በሙሉ በረከት አስተላላፊ እንደምትሆን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) “የሕይወት ውኃ ወንዝ” የሚፈሰው መቼ ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

19 አንጸባራቂዋ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በምድር ላይ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ታላላቅ በረከቶችን ታስተላልፋለች። ለዮሐንስም ቀጥሎ የተነገረው ነገር ይህ ነው:- “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።” (ራእይ 22:1) ይህ “ወንዝ” የሚፈሰው መቼ ነው? ወንዙ የሚፈስስው “ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን” ስለሆነ የጌታ ቀን ከጀመረበት ከ1914 በኋላ መሆን ይኖርበታል። በሰባተኛው መለከት መነፋት የታወጀውና “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ክርስቶስ ሆነች” የሚለው ማስታወቂያ የተነገረለት ይህ ጊዜ ነበር። (ራእይ 11:15፤ 12:10) በመጨረሻው ዘመን፣ መንፈስና ሙሽራይቱ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ ሲጋብዙ ቆይተዋል። የወንዙ ውኃ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ እንደዚህ ላሉት ሰዎች የሚቀርብ ሲሆን ከዚያም በኋላ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምትወርድበት’ ጊዜም መፍሰሱን ይቀጥላል።—ራእይ 21:2

20. አሁንም እንኳን መጠነኛ የሕይወት ውኃ ለሰዎች በመቅረብ ላይ እንዳለ ምን ማስረጃ አለን?

20 ሕይወት ሰጪ ውኃ ለሰው ልጆች ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የዘላለም ሕይወት ስለሚሰጥ ውኃ ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 4:10-14፤ 7:37, 38) ከዚህም በላይ ዮሐንስ የሚከተለውን ፍቅራዊ ግብዣ ሊሰማ ነው:- “መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፣ የሚሰማም ና ይበል። የተጠማም ይምጣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 22:17) ይህ ግብዣ በአሁኑ ጊዜም እንኳ በመሰማት ላይ ነው። ይህም አሁንም እንኳን ቢሆን መጠነኛ ውኃ ለሰዎች በመቅረብ ላይ እንዳለ ያመለክታል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ግን ይህ ውኃ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በኩልና ከአምላክ ዙፋን ትልቅ ወንዝ ሆኖ ይፈስሳል።

21. “የሕይወት ውኃ ወንዝ” የምን ምሳሌ ነው? ሕዝቅኤል የተመለከተው ራእይ ይህንን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

21 ይህ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ምንድን ነው? ቃል በቃል ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነው። የሰው ልጅ ያለምግብ ብዙ ሳምንታት ሊቆይ ይችላል። ያለውኃ ግን ከአንድ ሳምንት በላይ ሊኖር አይችልም። በተጨማሪም ውኃ የማጠብና የማጽዳት አገልግሎት ስላለው ለጤና በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የሕይወት ውኃ ለሰው ልጅ ሕይወትና ጤንነት አስፈላጊ የሆነን ነገር የሚያመለክት መሆን አለበት። ነቢዩ ሕዝቅኤልም ስለዚህ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ራእይ ተመልክቶ ነበር። ወንዙ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ወደ ሙት ባሕር ይፈስስ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን የተአምራት ሁሉ ተአምር ተፈጽሞአል። ሕይወት አልባ የሆነውና በጨው የተሞላው ባሕር ጥሩ ውኃ ሆኖ ዓሦች የሚርመሰመሱበት ባሕር ሆነ። (ሕዝቅኤል 47:1-12) አዎ፣ በራእይ የታየው ወንዝ ቀድሞ በድን የነበረን ነገር ወደ ሕይወት መልሶአል። ይህም የሕይወት ውኃ ወንዝ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በድን ለሆነው የሰው ዘር ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት መልሶ ለመስጠት ያለውን ዝግጅት የሚያመለክት መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ ውኃ እንደ ብርጭቆ የጠራ ውኃ ነው። ይህም የአምላክ ዝግጅት በጣም ንጹሕና ቅዱስ መሆኑን ያመለክታል። እንደ ሕዝበ ክርስትና ውኃ በደም የተበከለና ሕይወት የሚያሳጣ አይደለም።—ራእይ 8:10, 11

22. (ሀ) ወንዙ የሚመነጨው ከየት ነው? ይህስ ተገቢ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) አንደኛው የሕይወት ውኃ ክፍል ምንድን ነው? ሌሎች ምን ነገሮችንስ ይጨምራል?

22 ወንዙ የሚፈልቀው “ከይሖዋና ከበጉ ዙፋን” ነው። እንዲህም መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም የይሖዋ ሕይወት ሰጪ ዝግጅት የተመሠረተው በቤዛው መሥዋዕት ላይ በመሆኑና ይህም ቤዛ የተገኘው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ” ስለወደደ ነው። (ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም የሕይወት ውኃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ውኃ ተብሎ የሚጠራውን የአምላክ ቃል ይጨምራል። (ኤፌሶን 5:26) ይሁን እንጂ የሕይወት ውኃ ምንጭ የሚያመለክተው እውነትን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳንና የዘላለም ሕይወት ለማስገኘት አምላክ ያዘጋጃቸውን በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ የተመሠረቱ ዝግጅቶች በሙሉ ነው።—ዮሐንስ 1:29፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

23. (ሀ) የሕይወት ውኃ ወንዝ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አደባባዮች መፍሰሱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የሕይወት ውኃ ወንዝ በብዛት ሲፈስስ የትኛው ለአብርሃም የተሰጠ መለኮታዊ ተስፋ ይፈጸማል?

23 በሺው ዓመት ግዛት ዘመን የቤዛው ጥቅሞች ሙሉ በሙሉ ለሰው ልጆች የሚዳረሱት በኢየሱስና በ144,000ዎቹ የበታች ካህናት ክህነት አማካኝነት ነው። ስለዚህ የሕይወት ውኃ ወንዝ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አደባባይ መካከል መፍሰሱ ተገቢ ነው። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተገነባችው እውነተኛዎቹ የአብርሃም ዘሮች በሆኑት በኢየሱስና በመንፈሣዊ እስራኤላውያን አባልነት ነው። (ገላትያ 3:16, 29) ስለዚህ የሕይወት ውኃ ወንዝ በምሳሌያዊቱ ከተማ አደባባይ መካከል ሞልቶ ሲፈስስ “የምድር አሕዛብ ሁሉ” በአብርሃም ዘር አማካኝነት ራሳቸውን የመባረክ አጋጣሚ ያገኛሉ። ይሖዋ ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።—ዘፍጥረት 22:17, 18

የሕይወት ዛፎች

24. ዮሐንስ በሕይወት ውኃ ወንዝ ዳርና ዳር ምን ተመለከተ? እነርሱስ ምን ያመለክታሉ?

24 በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ወንዙ ትልቅ ጎርፍ ሆኖ ነበር። ነቢዩም በወንዙ ዳርና ዳር ብዙ ዓይነት ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን ተመልክቶአል። (ሕዝቅኤል 47:12) ዮሐንስስ ምን ተመለከተ? “በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ [አሕዛብ] መፈወሻ ነበሩ።” (ራእይ 22:2) እነዚህ የሕይወት ዛፎችም ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት በከፊል ማመልከት ይኖርባቸዋል።

25. ይሖዋ ለታዛዥ የሰው ልጆች በምድር አቀፉ ገነት ምን የተትረፈረፈ ዝግጅት ያደርግላቸዋል?

25 ይሖዋ ስጦታዎቹን ለሚቀበሉ ሰዎች በጣም ብዙ የሆነ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። ከዚህ ጥም አርኪ ከሆነ ውኃ ለመጠጣት ከመቻላቸውም በላይ ከእነዚህ ሕይወት አዳሽ ከሆኑ ዛፎች የተለያዩ ፍሬዎች እየቀነጠሱ ሊበሉ ይችላሉ። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን ገነት ቀርቦላቸው በነበሩት ዝግጅቶች ረክተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ የተሻለ ነበር! (ዘፍጥረት 2:9) አሁን ግን ምድር አቀፍ ገነት ተዘርግቶአል። እንዲያውም ይሖዋ በእነዚህ ምሳሌያዊ ዛፎች ፍሬዎች አማካኝነት ‘አሕዛብ እንዲፈወሱ’ ዝግጅት አድርጎአል። * ዛሬ ከሚሰጡት የዕፅዋትም ሆነ ሌሎች መድኃኒቶች በጣም የበለጠ ፈዋሽነት ያላቸው እነዚህ ምሳሌያዊ ቅጠሎች ያመኑትን የሰው ልጆች ወደ መንፈሣዊና አካላዊ ፍጽምና ያደርሱአቸዋል።

26. የሕይወት ዛፎች የምን ሌላ ነገር ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ? ለምንስ?

26 እነዚህ ከወንዙ የሚጠጡት ዛፎች የበጉን ሚስት 144,000 አባሎች ሊጨምሩ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከተደረገላቸው የሕይወት ዝግጅት ጠጥተው ነበር። በመንፈስ የተቀቡት እነዚህ የኢየሱስ ወንድሞች በትንቢት “የጽድቅ ዛፎች” ተብለው መጠራታቸው ትኩረት የሚስብ ነው። (ኢሳይያስ 61:1-3፤ ራእይ 21:6) ቀደም ብሎም ቢሆን ለይሖዋ ውዳሴ ብዙ መንፈሣዊ ፍሬ አፍርተዋል። (ማቴዎስ 21:43) በሺው ዓመት ግዛት ዘመን ደግሞ አሕዛብን ከኃጢአትና ከሞት የሚፈውሰውን የቤዛ ዝግጅት ለሰው ልጆች በማዳረስ ሥራ ይካፈላሉ።—ከ⁠1 ዮሐንስ 1:7 ጋር አወዳድር።

ከእንግዲህ ሌሊት አይሆንም

27. ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የመግባት መብት ያገኙ ሰዎች ምን ተጨማሪ በረከቶች እንደሚያገኙ ዮሐንስ ገልጾአል? በዚያም ‘መርገም’ አይኖርም የተባለው ለምንድን ነው?

27 ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የመግባትን ያህል በጣም አስደናቂ የሆነ መብት ሊገኝ አይችልም! በአንድ ወቅት በጣም ዝቅተኛና ፍጽምና የጎደላቸው የነበሩ ሰዎች የዚህ ታላቅ ዝግጅት ክፍል ለመሆን ኢየሱስን ተከትለው ወደ ሰማይ መግባታቸው እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንደሆነ እንገምት። (ዮሐንስ 14:2) እነዚህ ስለሚያገኙት በረከት ዮሐንስ ሲገልጽ እንደሚከተለው ተናግሮአል:- “ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፣ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፣ ፊቱንም ያያሉ፣ ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል።” (ራእይ 22:3, 4) የእሥራኤላውያን ክህነት በተበላሸ ጊዜ የይሖዋ መርገም ደርሶበት ነበር። (ሚልክያስ 2:2) እምነት የለሹ የእስራኤል “ቤት” የተፈታና የተተወ መሆኑን ኢየሱስ ተናገሮ ነበር። (ማቴዎስ 23:37-39) በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ግን “ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም።” (ከ⁠ዘካርያስ 14:11 ጋር አወዳድር።) ነዋሪዎችዋ በሙሉ በዚህ ምድር ላይ በመከራ እሳት ተፈትነው ድል ስለነሱ ‘ያለመሞትንና ያለመበስበስን ባሕርይ’ ያገኛሉ። እንደ ኢየሱስ ሁሉ ይሖዋም ፈጽሞ ወደ ክህደት መንገድ እንደማይሄዱ ያውቃል። (1 ቆሮንቶስ 15:53, 57) ከዚህም በላይ “የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን” በከተማይቱ ውስጥ ስለሚሆን ከተማይቱ ለዘላለም ጸንታ ትቆማለች።

28. የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባሎች በግምባራቸው ላይ የአምላክ ስም የተጻፈባቸው ለምንድን ነው? እነርሱስ ምን አስደሳች ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

28 የዚህች ሰማያዊት ከተማ አባሎች በሙሉ እንደ ዮሐንስ የአምላክ “ባሪያዎች” ናቸው። በዚህም ምክንያት የአምላክ ስም በግንባሮቻቸው ላይ በጉልህ ተጽፎአል። ይህም ይሖዋ ባለቤታቸው መሆኑን ያመለክታል። (ራእይ 1:1፤ 3:12) የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል በመሆን እርሱን ለማገልገል መቻል ከግምት ሁሉ የላቀ ትልቅ መብት እንደሆነ ይቆጥራሉ። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለእነኚህ እጩ ገዢዎች “ልበ ንጹሖች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና” በማለት በጣም የሚያስደስት ተስፋ ሰጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 5:8) እነዚህ ባሮች ይሖዋን በገሐድ ለማየትና ለማምለክ በመቻላቸው ምን ያህል ይደሰቱ ይሆን!

29. ዮሐንስ ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘በዚያም ሌሊት አይኖርም’ ያለው ለምንድን ነው?

29 ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፣ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም።” (ራእይ 22:5ሀ) የጥንትዋ ኢየሩሳሌም እንደማንኛውም የጥንት ከተማ የቀን ብርሃን የምታገኘው ከፀሐይ፣ የሌሊት ብርሃን ደግሞ የምታገኘው ከጨረቃና ከሰው ሠራሽ መብራቶች ነበር። በሰማያዊቱ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ግን እንደነዚህ ያሉት ብርሃኖች አያስፈልጉም። ይሖዋ ራሱ የከተማይቱ መብራት ይሆናል። በተጨማሪም “ሌሊት” ከይሖዋ የመለየት ወይም የመከራ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። (ሚክያስ 3:6፤ ዮሐንስ 9:4፤ ሮሜ 13:11, 12) ሁሉን የሚችለው አምላክ በታላቅ ግርማና ብርሃን በሚገኝበት ሥፍራ እንዲህ ያለ ሌሊት ሊኖር አይችልም።

30. ዮሐንስ ይህንን አስደናቂ ራእይ የደመደመው እንዴት ነው? የራእይ መጽሐፍ ስለ ምን ነገር ዋስትና ይሰጠናል?

30 ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ይህንን አስደናቂ ራእይ ሲያጠቃልል እነዚህ የአምላክ ባሮች “ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ” ይላል። (ራእይ 22:5ለ) እርግጥ ነው፣ በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ የቤዛው ጥቅሞች ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ይውላሉ። ኢየሱስም ፍጹም የሆነ የሰው ዘርን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:25-28) ከዚያ በኋላ ግን ይሖዋ ለኢየሱስና ለ144,000ዎቹ ምን እንዳዘጋጀላቸው አናውቅም። ይሁን እንጂ ለይሖዋ የሚያቀርቡት የቅዱስ አገልግሎት መብት እስከ ዘላለም እንደሚቀጥል የራእይ መጽሐፍ ያረጋግጥልናል።

የራእይ አስደሳች መደምደሚያ

31. (ሀ) የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ራእይ የምን ነገር መደምደሚያ ሆኖአል? (ለ) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለሌሎች ታማኝ የሰው ልጆች ምን ውጤት ታስገኝላቸዋለች?

31 የራእይ መጽሐፍ የሚጠቁመን አስደሳች መደምደሚያ የዚህን የአዲሲቱ ኢየሩሳሌምን ማለትም የበጉን ሙሽራ ራእይ እውን መሆን ነው። ይህም መሆኑ ተገቢ ነው። መጽሐፉ በመጀመሪያ ደረጃ በቀጥታ የተጻፈላቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የዮሐንስ ክርስቲያን ባልንጀሮች ሁሉ የማይሞቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ተባባሪ ወራሾች ሆነው ወደዚህች ከተማ የሚገቡበትን ጊዜ በተስፋ ይጠባበቁ ነበር። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩት ቅቡዓን ቀሪ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ተስፋ አላቸው። ስለዚህ የሙሽራይቱ አባላት በሙሉ አንድ ላይ ተሰባስበው በዚህ መንገድ ከበጉ ጋር አንድ ሲሆኑ ራእይ ወደ ከፍተኛ መደምደሚያው ይደርሳል። ቀጥሎም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አማካኝነት የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች በሰው ልጆች ላይ እንዲሠሩ ይደረጋል። በዚህም አማካኝነት ታማኝ የሆኑ ሁሉ ወደ ዘላለም ሕይወት ይገባሉ። በዚህ መንገድ ሙሽራይቱ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሙሽራው ንጉሥ ታማኝ ረዳት በመሆን ለጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ የሚያመጣ አዲስ የጽድቅ ምድር በመገንባት ሥራ ትካፈላለች።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 10:10, 16፤ ሮሜ 16:27

32, 33. ከራእይ መጽሐፍ ምን ትምህርት አግኝተናል? ይህንንስ እንዴት ባለ ስሜት መቀበል ይኖርብናል?

32 ስለዚህ በራእይ መጽሐፍ ላይ ስናደርግ የቆየነውን ምርመራ ልናጠናቅቅ ስንቃረብ በጣም ከፍ ያለ ደስታ ይሰማናል። ሰይጣንና ዘሮቹ ለመጨረሻ ጊዜ የሚያደርጉት ሙከራ እንደሚከሽፍና የይሖዋ የጽድቅ ፍርድ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጸም ተመልክተናል። ታላቂቱ ባቢሎን ለዘላለም መጥፋት ይኖርባታል። ከእርስዋ በኋላ ደግሞ ሊሻሻሉ በማይችሉበት ሁኔታ የተበላሹት የሰይጣን ዓለም ክፍሎች በሙሉ ይጠፋሉ። ሰይጣንና አጋንንቱም በጥልቁ ውስጥ ታስረው ከቆዩ በኋላ ይጠፋሉ። የትንሣኤውና የፍርዱ ጊዜ ወደፊት እየቀጠለ በሄደ መጠን አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር ሆና ትገዛለች። በመጨረሻም ወደ ፍጽምና ደረጃ የደረሰው የሰው ልጅ በገነቲቱ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት አግኝቶ ይኖራል። የራእይ መጽሐፍ እነዚህን ክንውኖች በሙሉ በጣም ግልጽና ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ይገልጻል። ይህ ሁሉ ‘በምድር ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ’ ምሥራቹን ለመስበክ የበለጠ ቆራጥነትና ጥንካሬ የሚሰጠን ነው! (ራእይ 14:6, 7) በዚህ ታላቅ ሥራ በሚቻልህ ሁሉ በመካፈል ላይ ነህን?

33 ልባችን እንዲህ ባለው የአመስጋኝነት መንፈስ ተሞልቶ የራእይን የመጨረሻ ቃላት በትኩረት እንከታተል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 እዚህ ላይ ያገለገለው መለኪያ “የሰው ልክ” እና “የመልአክ ልክ” መሆኑ ከተማይቱ በአባልነት የተገነባችው መጀመሪያ ሰዎች በነበሩትና በኋላ እንደ መላእክት መንፈሳዊ ፍጥረቶች በሚሆኑት 144,000ዎች ከመሆኑ ጋር ዝምድና ያለው ሊሆን ይችላል።

^ አን.18 “በበጉ የሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ የሚገኙት የ144,000ዎቹ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ስሞች ብቻ እንደሆኑ አስተውል። ስለዚህ በምድር ላይ ሕይወት የሚሰጣቸው ሰዎች ከተጻፉበት ‘የሕይወት መጽሐፍ’ የተለየ ነው።— ራእይ 20:12

^ አን.25 “አሕዛብ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው መንፈሳዊ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎችን እንደሆነ አስተውል። (ራእይ 7:9፤ 15:4፤ 20:3፤ 21:24, 26) ይህ ቃል እዚህ ላይ መጠቀሱ የሰው ዘር በሺው ዓመት ግዛት በተለያዩ ብሔሮች እንደሚደራጅ አያመለክትም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]