በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዲሱን የድል መዝሙር መዘመር

አዲሱን የድል መዝሙር መዘመር

ምዕራፍ 29

አዲሱን የድል መዝሙር መዘመር

ራእይ 9--ራእይ 14:1-20

ርዕሰ ጉዳይ:- 144,000ዎቹ ከበጉ ጋር በጽዮን ተራራ መቆማቸው፣ የመላእክት መግለጫዎች በምድር በሙሉ መሰማታቸው፣ የመከሩ መሰብሰብ

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከ1914 እስከ ታላቁ መከራ

1. እስከ አሁን ድረስ ስለ ራእይ ምዕራፍ 7፣ ራእይ ምዕራፍ 12 እና ራእይ ምዕራፍ 13 ምን አውቀናል? አሁን ደግሞ ስለ ምን ነገር እንማራለን?

የሚቀጥለውን የዮሐንስ ራእይ መመልከት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! አሁን ከዘንዶው አስፈሪና አስቀያሚ አውሬ መሰል ድርጅት የተለዩትን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችና እነርሱ በዚህ የጌታ ቀን የሚያደርጉትን የሥራ እንቅስቃሴ እንመለከታለን። (ራእይ 1:10) ቀደም ሲል ራእይ 7:1, 3 እነዚህ 144,000 ቅቡዓን ታትመው እስኪያልቁ ድረስ አራቱ ነፋሳት ታግደው እንደሚቆዩ ገልጾልን ነበር። ራእይ 12:17 ደግሞ እነዚህ ‘ከሴቲቱ ዘር የቀሩት’ በዚህ ጊዜ የዘንዶው የሰይጣን ጥቃት ልዩ ዒላማዎች እንደሚሆኑ አስታውቆአል። በተጨማሪም ራእይ ምዕራፍ 13 ሰይጣን በምድር ላይ ያስነሳቸው ፖለቲካዊ ድርጅቶች በይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ላይ ታላቅ ተጽዕኖና አስከፊ ስደት እንደሚያመጣ በሥዕላዊ መግለጫ ገልጾአል። ይሁን እንጂ ይህ ቀንደኛ ጠላት የአምላክን ዓላማ ሊያከሽፍ አይችልም። ሰይጣን ምንም ዓይነት የባላጋራነት ድርጊት ቢፈጽም ሁሉም 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በድል አድራጊነት እንደሚሰበሰቡ አሁን እንማራለን።

2. ዮሐንስ በራእይ ምዕራፍ 14:1 ላይ ምን አስደሳች መቅድማዊ ትዕይንት ገልጾልናል? በጉስ ማን ነው?

2 ዮሐንስና የዮሐንስ ክፍል አባሎች ስለዚህ አስደሳች ውጤት መቅድማዊ ትዕይንት ተመልክተዋል። “አየሁም፣ እነሆም፣ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።” (ራእይ 14:1) ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ይህ በግ ዲያብሎስንና አጋንንትን በማባረር ሰማይን ያጸዳው ሚካኤል ነው። ዳንኤል “ለሕዝብህ [ለአምላክ ሕዝብ] ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ” ሲል የገለጸው ሚካኤል ይህ በግ ነው። እርሱም የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ ለማስፈጸም ተዘጋጅቶ ቆሞአል። (ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 12:7, 9) ከ1914 ጀምሮ ይህ ራሱን መሥዋዕት የማድረግ ባሕርይ ያለው በግ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞአል።

3. በጉና 144,000ዎቹ የቆሙበት “የጽዮን ተራራ” ምንድን ነው?

3 ይሖዋ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው ነው:- “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ፣ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ።” (መዝሙር 2:6፤ 110:2) ይህ ቃል የዳዊት ዘሮች ይነግሡባት የነበረችው ምድራዊት ኢየሩሳሌም የምትገኝበትን የጽዮን ተራራን መልክዓ ምድር አያመለክትም። (1 ዜና 11:4-7፤ 2 ዜና 5:2) ኢየሱስ በ33 እዘአ ከሞተና ከተነሳ በኋላ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ የተቀመጠው ይሖዋ “የሕያው እግዚአብሔር ከተማ” የሆነችውን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ለመቆርቆር በወሰነበት ሰማያዊ ሥፍራ ማለትም በሰማያዊ የጽዮን ተራራ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ የተጠቀሰው “የጽዮን ተራራ” የመንግሥቱ ምሳሌ የሆነው የሰማያዊ ኢየሩሳሌም አባላት የሆኑት ኢየሱስና ተባባሪ ወራሾቹ የሚኖራቸውን ከፍተኛ ደረጃ ያመለክታል። (ዕብራውያን 12:22, 28፤ ኤፌሶን 3:6) ይሖዋ በዚህ የጌታ ቀን የሚሰጣቸውን ክብራማ የንጉሥነት ቦታና ማዕረግ ያመለክታል። ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ሕያዋን ድንጋዮች” እንደመሆናቸው መጠን ክብር ከተቀዳጀው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግርማዊ መንግሥት ተባብረው በዚህ ሰማያዊ የጽዮን ተራራ ላይ የሚቆሙበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ሲጠብቁ ኖረዋል።—1 ጴጥሮስ 2:4-6፤ ሉቃስ 22:28-30፤ ዮሐንስ 14:2, 3

4. 144,000ዎቹ በሙሉ በጽዮን ተራራ ላይ የቆሙት እንዴት ነው?

4 ዮሐንስ ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን መላውን የ144,000 የመንግሥት ወራሾች ክፍል በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ተመልክቶአል። ራእዩ በሚያመለክተው ጊዜ ሰማያዊ ቦታቸውን የያዙት የ144,000 ክፍል አባሎች ብዙ ቢሆኑም ገና ሁሉም ወደ ሰማይ አልሄዱም ነበር። በዚሁ ራእይ ውስጥ አንዳንዶቹ ቅዱሳን እስከ መጨረሻው መጽናትና እስከ ሞት ድረስ ታማኞች መሆን እንደሚኖርባቸው ለዮሐንስ ተነግሮታል። (ራእይ 14:12, 13) ስለዚህ አንዳንድ የ144,000 ክፍል አባሎች በምድር ላይ እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ታዲያ ዮሐንስ ሁሉም የ144,000 ክፍሎች ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ ጽዮን ቆመው ሊመለከት የቻለው እንዴት ነው? * የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባሎች እንደመሆናቸው መጠን “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ” በመድረሳቸው ነው። (ዕብራውያን 12:22) ጳውሎስ በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንዳጋጠመው በመንፈሳዊ ሁኔታ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ኅብረት እንዲያገኙ ወደ ሰማያዊ ሥፍራ ከፍ ተደርገዋል። (ኤፌሶን 2:5, 6) በተጨማሪም በ1919 “ወደዚህ ውጡ” የሚለውን ጥሪ ተቀብለው በምሳሌያዊ ሁኔታ “ወደ ሰማይ በደመና” ወጥተዋል። (ራእይ 11:12) እነዚህን ጥቅሶች ሁሉ ስናገናዝብ ሁሉም የ144,000 ክፍል አባሎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመንፈሳዊ አባባል በሰማያዊቱ ጽዮን እንዳሉ ልንገነዘብ እንችላለን።

5. በ144,000ዎቹ ግንባር ላይ የተጻፈው የእነማን ስም ነው? የስሞቹስ ትርጉም ምንድን ነው?

5 144,000ዎቹ ምሳሌያዊውን የ666 ቁጥር ምልክት ከተቀበሉት የአውሬው አምላኪዎች ጋር ምንም ዓይነት ተካፋይነት የላቸውም። (ራእይ 13:15-18) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከእነዚህ ሰዎች ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ በግንባራቸው ላይ የአምላክና የበጉ ስም ተጽፎባቸዋል። ዮሐንስ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን የአምላክ ስም יהוה በሚሉት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ እንደተመለከተ አያጠራጥርም። * የኢየሱስ አባት ስም በምሳሌያዊ ሁኔታ በግንባራቸው ላይ የተጻፈላቸው በመሆናቸው እነዚህ የታተሙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችና የእሱ ባሮች መሆናቸውን ለሰው ሁሉ ያሳውቃሉ። (ራእይ 3:12) በተጨማሪም የኢየሱስ ስም በግንባራቸው ላይ መታየቱ የኢየሱስ ንብረቶች መሆናቸውን እንደሚቀበሉ ያመለክታል። እርሱ የወደፊት “ባላቸው” ሲሆን እነርሱ ደግሞ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ያላቸው የአምላክ አገልጋዮችና “አዲስ ፍጥረት”፣ የወደፊት “ሙሽራው” ናቸው። (ኤፌሶን 5:22-24፤ ራእይ 21:2, 9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:17) ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው የተቀራረበ ዝምድና አስተሳሰባቸውንና እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ ይነካዋል።

አዲስ የሚመስል ቅኔ መዘመር

6. ዮሐንስ ምን መዝሙር ሰማ? ይህንንስ መዝሙር የገለጸው እንዴት ነው?

6 ዮሐንስ ከዚህ ጋር በመስማማት የሚከተለውን ይነግረናል:- “እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጎድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፣ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ። በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።” (ራእይ 14:2, 3) ዮሐንስ 144,000 ድምፆች በአንድ ላይ አንድ ዓይነት ጣፋጭ ዝማሬ ባሰሙበት ጊዜ የሚያስገመግም የፏፏቴ ድምፅና ታላቅ ነጎድጓድ ድምፅ ማስታወሱ ሊያስደንቀን አይገባም። ዝማሬውን ያጀበው የበገና ድርደራም በጣም የሚያስደስት ነበር። (መዝሙር 81:2) ከዚህ ሰማያዊ ዝማሬ ጋር የሚወዳደር ታላቅና ባለግርማ ዝማሬ ሊያሰማ የሚችል የመዘምራን ቡድን በምድር ላይ ሊገኝ አይችልም።

7. (ሀ) በ⁠ራእይ 14:3 ላይ የተጠቀሰው አዲስ መዝሙር ምንድን ነው? (ለ) የ⁠መዝሙር 149:1 መዝሙር ለዘመናችን አዲስ መዝሙር የሆነው እንዴት ነው?

7 ይህ “አዲስ ቅኔ” ምንድን ነው? ስለ ራእይ 5:9, 10 ስንወያይ እንደተገነዘብነው ቅኔው ወይም መዝሙሩ ስለ ይሖዋ የመንግሥት ዓላማና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት መንፈሳዊ እስራኤልን “ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት” ለማድረግ ስላዘጋጀው ዝግጅት የሚገልጽ ነው። በአምላክ እስራኤል አማካኝነትና ለአምላክ እስራኤል ሲል የሚፈጽማቸውን አዳዲስ ነገሮቸ የሚያስታውቅ ለይሖዋ የቀረበ የውዳሴ መዝሙር ነው። (ገላትያ 6:16) የዚህ መንፈሳዊ እስራኤል አባሎች የሚከተለውን የመዝሙራዊ ግብዣ ተቀብለዋል:- “ሃሌ ሉያ! ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው። እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፣ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያድርጉ።” (መዝሙር 149:1, 2) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ቃላት የተጻፉት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ነው። ቢሆንም በዘመናችን ሲዘመሩ አዲስ ትርጉም ይዘዋል። በ1914 መሲሐዊው መንግሥት ተወለደ። (ራእይ 12:10) በ1919 በምድር ላይ የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች “የመንግሥቱን ቃል” በአዲስ ቅንዓት ማወጅ ጀመሩ። (ማቴዎስ 13:19) ለ1919 በተመረጠው የዓመት ጥቅስ (ኢሳይያስ 54:17) ተነቃቅተውና ወደ መንፈሳዊ ገነት በመመለሳቸው ተጽናንተው ለይሖዋ ‘በልባቸው መቀኘትና መዘመር’ ጀመሩ።—ኤፌሶን 5:19

8. የ⁠ራእይ 14:3ን አዲስ መዝሙር ሊማሩ የቻሉት 144,000ዎቹ ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ በ⁠ራእይ 14:3 ላይ የተጠቀሰውን መዝሙር ሊማሩ የቻሉት 144,000ዎቹ ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ምርጥ ወራሾች በመሆን ከሚያጋጥማቸው የግል ተሞክሮ ጋር ተዛምዶ ያለው መዝሙር ስለሆነ ነው። የአምላክን ልጅነት ያገኙትና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት እነርሱ ብቻ ናቸው። የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ክፍሎች እንዲሆኑ ከምድር የተዋጁት እነርሱ ብቻ ናቸው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ‘ካህናትና ነገሥታት’ ሆነው ለሺህ ዓመት በመግዛት የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና የሚመልሱት እነርሱ ብቻ ናቸው። በይሖዋ ፊት “አዲስ ቅኔ” ሲዘምሩ የታዩት እነርሱ ብቻ ናቸው። * ይህ የሚያገኙት ልዩ የሆነ የግል ተሞክሮና የወደፊት ተስፋ ለመንግሥቱ ከፍተኛ አድናቆት እንዲሰማቸውና ማንም ሊዘምር በማይችለው መንገድ ስለ መንግሥቱ እንዲዘምሩ አስችሎአቸዋል።—ራእይ 20:6፤ ቆላስይስ 1:13፤ 1 ተሰሎንቄ 2:11, 12

9. እጅግ ብዙ ሰዎች የቅቡዓንን መዝሙር እንዴት ተቀብለዋል? ይህንንስ በማድረጋቸው የትኛውን ምክር ፈጽመዋል?

9 ይሁን እንጂ መዝሙራቸውን የሚያዳምጡና በአድናቆት የሚቀበሉ ሰዎች ይኖራሉ። ከ1935 ጀምሮ እጅግ ብዙ ሰዎች የድል አድራጊነት መዝሙራቸውን ሰምተው ከእነርሱ ጋር በመተባበር የአምላክን መንግሥት ለማወጅ ተነሳስተዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) እርግጥ ነው፣ እነዚህ አዲስ መጪዎች የወደፊቶቹ የአምላክ መንግሥት ገዥዎች የሚዘምሩትን መዝሙር ልክ እንደነርሱ አድርገው ሊዘምሩ አይችሉም። ቢሆንም እነርሱም ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ማለትም ይሖዋ ለሚሠራቸው አዳዲስ ነገሮች የሚያወድሰው ጥሩ ዝማሬ ያሰማሉ። ይህን በማድረጋቸውም የሚከተለውን የመዝሙራዊ ምክር ይፈጽማሉ። “ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ፣ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] አመስግኑ። እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] አመስግኑ ስሙንም ባርኩ። ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤ የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] አምጡ፣ ክብርንና ምስጋናን፣ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] አምጡ። በአሕዛብ መካከል:- እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነገሠ በሉ።”—መዝሙር 96:1-3, 7, 10፤ 98:1-9

10. 144,000ዎቹ በምሳሌያዊዎቹ 24 ሽማግሌዎች “ፊት” ለመዘመር የቻሉት እንዴት ነበር

10 24ቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ የግርማ ቦታቸውን የተቀበሉትን 144,000 ክፍሎች የሚያመለክቱ ከሆነ 144,000ዎቹ በሽማግሌዎቹ ፊት ሊዘምሩ የሚችሉት እንዴት ነው? በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የሞቱ ሁሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት በመሆን ከሙታን ተነስተው ነበር። ስለዚህ ድል የነሱ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት በሰማይ ነው። ከ24ቱ ካህናዊ ሽማግሌዎች ሥራ ጋር የሚመሳሰል ሥራ በምሳሌያዊ ሁኔታ በማከናወን ላይ ናቸው። ስለ ይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት በታየው ራእይ ውስጥም ገብተዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:15, 16፤ 1 ዜና 24:1-18፤ ራእይ 4:4፤ 6:11) ስለዚህ ገና በምድር ላይ የሚኖሩት የ144,000 ቀሪዎች አዲሱን መዝሙር ከሙታን ተነስተው ወደ ሰማይ በተወሰዱት ወንድሞቻቸው ፊት በመዘመር ላይ ናቸው።

11. ድል አድራጊዎቹ ቅቡዓን 24 ሽማግሌዎችና 144,000 ተብለው የተጠሩት ለምንድን ነው?

11 እዚህ ላይ እነዚህ ቅቡዓን ድል አድራጊዎች ምሳሌያዊ 24 ሽማግሌዎችም 144,000ዎችም ተብለው የተጠሩት ለምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የራእይ መጽሐፍ ይህን አንድ ቡድን ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ስለሚመለከት ነው። ምን ጊዜም ቢሆን 24ቱ ሽማግሌዎች በሰማይ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ነገሥታትና ካህናት ሆነውና ከፍተኛ ቦታ ይዘው ታይተዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ144,000ዎቹ የቀሩ ጥቂት ቀሪዎች በምድር ላይ ቢኖሩም እነዚህ 24 ሽማግሌዎች ሰማያዊ ቦታቸውን የተቀበሉትን 144,000ዎች በሙሉ ያመለክታሉ። (ራእይ 4:4, 10፤ 5:5-14፤ 7:11-13፤ 11:16-18) ይሁን እንጂ ራእይ ምዕራፍ 7 የሚያተኩረው 144,000ዎቹ ከሰው ልጆች መካከል ስለመውጣጣታቸው ነው። ይሖዋ መንፈሳዊ እስራኤላውያን የሚሆኑትን ግለሰቦች በሙሉ ለማተምና ቁጥራቸው ላልተወሰነ እጅግ ብዙ ሰዎች መዳንን ለመስጠት ያወጣውን እቅድ ይገልጻል። ራእይ ምዕራፍ 14 ደግሞ 144,000 ግለሰብ ድል አድራጊዎች ከበጉ ጋር በጽዮን ተራራ ላይ እንደሚሰበሰቡ የሚያረጋግጥ ሥዕላዊ መግለጫ ነው። በተጨማሪም ሰዎች ከ144,000ዎቹ መካከል ለመቆጠር ማሟላት ስለሚኖርባቸው ብቃት ተገልጾአል። ይህንንም ቀጥለን እንመለከታለን። *

የበጉ ተከታዮች

12. (ሀ) ዮሐንስ ስለ 144,000 የሚሰጠውን መግለጫ የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) 144,000ዎቹ ድንግሎች የተባሉት በምን መንገድ ነው?

12 ዮሐንስ ከምድር ስለተዋጁት 144,000ዎች የሚሰጠውን መግለጫ በመቀጠል የሚከተለውን ይነግረናል:- “ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፣ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።” (ራእይ 14:4, 5) 144,000ዎቹ “ድንግሎች” ናቸው መባሉ እነዚህ ሰዎች የግድ በሥጋ ያላገቡ መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሰማያዊ ጥሪ ለነበራቸው ክርስቲያኖች ሲጽፍ በነጠላነት መኖር ለአንድ ክርስቲያን ጥቅም ያለው ቢሆንም በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን ማግባት የተሻለ እንደሚሆን ገልጾአል። (1 ቆሮንቶስ 7:1, 2, 36, 37) ይህን ክፍል የተለየ የሚያደርገው መንፈሳዊ ድንግልናው ነው። ከዓለማዊ ፖለቲካና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ከመፈጸም ተጠብቀው ኖረዋል። (ያዕቆብ 4:4፤ ራእይ 17:5) ለክርስቶስ የታጩ ሙሽራዎች እንደመሆናቸው መጠን “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካካል ያለ ነቀፋ” ሆነው በንጽሕና ኖረዋል።—ፊልጵስዩስ 2:15

13. የ144,000ዎቹ ክፍል ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባ ሙሽራ የሆነው ለምንድን ነው? “በጉን በሄደበት ሁሉ የሚከተሉት” እንዴት ነው?

13 በተጨማሪም “ሐሰትም በአፋቸው አልተገኘም።” በዚህም ንጉሣቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:21, 22) 144,000ዎቹ ነውር የሌለባቸውና እውነተኞች በመሆናቸው ለይሖዋ ታላቅ ሊቀ ካህናት የሚገቡ ሙሽራዎች ሆነው ተዘጋጅተዋል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንዲከተሉት ጋብዞ ነበር። (ማርቆስ 8:34፤ 10:21፤ ዮሐንስ 1:43) ግብዣውን የተቀበሉ ሁሉ የኢየሱስን አኗኗር ተከትለዋል፣ ትምህርቱንም ታዝዘዋል። ስለዚህ በምድራዊ ሕይወታቸው ጊዜ በጉ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ሲመራቸው “በሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል።”

14. (ሀ) 144,000ዎቹ “ለአምላክና ለበጉ በኩራት” የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎችም በኩራት የሆኑት በምን መንገድ ነው?

14 144,000ዎቹ “በምድር ላይ ከሚገኙት የሰው ልጆች መካከል የተዋጁ” ናቸው። የአምላክ ልጆች ሆነው ተቆጥረዋል። ከሙታን ከተነሱ በኋላም ሥጋና ደም የሆኑ ሰዎች ሆነው አይኖሩም። በቁጥር 4 ላይ እንደተገለጸው “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት” ይሆናሉ። እርግጥ ነው፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ “በሞት ላንቀላፉት በኩራት” ሆኖ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:20, 23) 144,000ዎቹ ግን በኢየሱስ መሥዋዕት የተዋጁ ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች “በኩራት” ናቸው። (ያዕቆብ 1:18) ይሁን እንጂ ከሰው ልጆች መካከል የሚሰበሰበው ፍሬ በእነርሱ ብቻ ተወስኖ አይቀርም። የራእይ መጽሐፍ ቀደም ሲል ጮክ ብለው “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው” የሚሉ ቁጥራቸው ያልተወሰነ እጅግ ብዙ ሰዎች እንደሚሰበሰቡ ገልጾልናል። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ከታላቁ መከራ በሕይወት ያልፋሉ። “ከሕይወት ውኃ ምንጭ” እየጠጡ ሰብአዊ ፍጽምና አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ። ከታላቁ መከራ በኋላ ጥቂት ጊዜ ቆይቶ ሔድስ ባዶውን ይቀራል። ቁጥር ሥፍር የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሙታን ተነስተው ከዚሁ የሕይወት ውኃ የመጠጣት እድል ያገኛሉ። በዚህ መሠረት እጅግ ብዙ ሰዎችን የሌሎች በጐች በኩራት ናቸው ብንል ትክክል ነው። በበጉ ደም ልብሳቸውን አጥበው ለማንጻትና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ለማግኘት የመጀመሪያዎቹ እነርሱ ናቸው።—ራእይ 7:9, 10, 14, 17፤ 20:12, 13

15. በሙሴ ሕግ መሠረት ይከበሩ የነበሩት ሦስት በዓላትና ሦስቱ የተለያዩ በኩራት ምን ተመሳሳይነት አላቸው?

15 እነዚህ ሦስት በኩራት (ኢየሱስ ክርስቶስ፣ 144,000ዎችና እጅግ ብዙ ሰዎች) በሙሴ ሕግ መሠረት ይከበሩ ከነበሩት በዓላት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። የቂጣ በዓል በሚከበርበት በኒሣን 16 ቀን ከገብስ አዝመራ የተሰበሰበው የበኩራት ነዶ ለይሖዋ ይቀርብ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:6-14) ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው ደግሞ ኒሣን 16 ቀን ነው። ከኒሣን 16 በ50ኛው ቀን ወይም በሦስተኛው ወር የስንዴ አዝመራ በኩራት የሚሰበሰብበት በዓል ይከበር ነበር። (ዘጸአት 23:16፤ ዘሌዋውያን 23:15, 16) ይህ በዓል የጰንጠቆስጤ በዓል (“ሃምሳኛ” ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው) ተብሎ መጠራት ጀምሮ ነበር። የ144,000ዎቹ የመጀመሪያ አባሎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ነበር። በመጨረሻም በሰባተኛው ወር መላው አዝመራ ተሰብስቦ ካለቀ በኋላ እስራኤላውያን ከዘንባባና ከሌሎች ቅጠሎችና ጭራሮዎች በተሠሩ ዳሶች ውስጥ ተቀምጠው የሚያከብሩት የደስታና የምሥጋና ማቅረቢያ በዓል የሆነው የዳስ በዓል ይከበራል። (ዘሌዋውያን 23:33-43) የታላቁ አዝመራ ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎችም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ “የዘንባባ ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው” በዙፋኑ ፊት ምሥጋናቸውን ያቀርባሉ።—ራእይ 7:9

የዘላለሙን ምሥራች ማወጅ

16, 17. (ሀ) ዮሐንስ አንድ መልአክ የት ሲበር ተመለከተ? ይህስ መልአክ የትኛውን አዋጅ እየተናገረ ነበር? (ለ) በመንግሥቱ ስብከት ሥራ እነማን ይካፈላሉ? ይህንንስ የሚያሳዩ ምን ዓይነት ተሞክሮዎች አሉ?

16 ቀጥሎ ዮሐንስ የሚከተለውን ጽፎአል:- “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም:- የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።” (ራእይ 14:6, 7) መልአኩ ይበር የነበረው አዕዋፍ በሚበሩበት “በሰማይ መካከል” ነው። (ከ⁠ራእይ 19:17 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ድምፁ በዓለም በሙሉ ሊደመጥ ይችላል ማለት ነው። የዚህ መልአክ ዓለም አቀፋዊ አዋጅ ከማንኛውም የቴሌቪዥን ዜና የበለጠ ሰፊ ስርጭት ይኖረዋል።

17 ሰው ሁሉ አውሬውንና ምስሉን ሳይሆን ከማንኛውም በሰይጣን ቁጥጥር ከሚንቀሳቀስ ምሳሌያዊ አውሬ እጅግ በጣም የበለጠ ኃይል ያለውን ይሖዋን እንዲፈራ ተመክሮአል። ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ይሖዋ ነው። አሁን ደግሞ ምድርን የሚፈርድበት ጊዜ ደርሶአል። (ከዘፍጥረት 1:1⁠ና ከ⁠ራእይ 11:18 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ስለ ዘመናችን የሚከተለውን ትንቢት ተናግሮ ነበር። “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ይህን የሥራ ግዴታ በመፈጸም ላይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:16፤ ኤፌሶን 6:15) በዚህ የስብከት ሥራ የማይታዩ መላእክትም ተካፋዮች እንደሆኑ የራእይ መጽሐፍ ገልጾልናል። መላእክት የይሖዋ ምሥክሮችን መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ሲጸልዩ ወይም በጣም ሲፈልጉ ከቆዩ ሰዎች ጋር እንዲገናኙ ያደረጉባቸው ብዙ ጊዜያት ስላሉ በዚህ ሥራ የመላእክት አመራር እንዳለበት ግልጽ ሆኖአል።

18. በሰማይ ይበር የነበረው መልአክ እንደተናገረው የምን ሰዓት ቀርቦአል? ተጨማሪ አዋጅ የሚናገሩትስ እነማን ናቸው?

18 በሰማይ መካከል ይበር የነበረው መልአክ እንደተናገረው የፍርዱ ሰዓት ቀርቦአል። አሁን አምላክ የሚያስፈጽመው ፍርድ ምንድን ነው? ከዚህ ቀጥሎ ሁለተኛው፣ ሦስተኛው፣ አራተኛውና አምስተኛው መላእክት የሚናገሩት ማስታወቂያ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነው።—ኤርምያስ 19:3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 1 ቆሮንቶስ 4:8 እንደሚያመለክተው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ነገሥታት ሆነው አይገዙም። ይሁን እንጂ ራእይ 14:3, 6, 12, 13 እንደሚያመለክተው እስከ ምድራዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ጸንተው በመቆም ምሥራቹን ሲሰብኩ አዲሱን ቅኔ በመዘመር ይካፈላሉ።

^ አን.5 ይህ አስተሳሰብ በሌሎቹ ራእዮች የዕብራይስጥ ስሞች በመጠቀሳቸው ተረጋግጦአል። ለኢየሱስ “አብዶን” የተባለ የዕብራይስጥ ስም ተሰጥቶታል። (“ጥፋት” ማለት ነው።) ፍርዱን የሚፈጽመው ደግሞ በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባለው ሥፍራ ነው።—ራእይ 9:11፤ 16:16

^ አን.8 ጥቅሱ “እንደ አዲስ መዝሙር” [NW] የሚለው መዝሙሩ በጥንት ዘመን በተነገረ ትንቢት ውስጥ ተጽፎ ስለሚገኝ ነው። ይሁን እንጂ መዝሙሩን ለመዘመር ብቃት ያገኘ አልነበረም። አሁን መንግሥቱ ከተቋቋመና ቅዱሳን ከሙታን ከተነሱ በኋላ ግን የትንቢቱ ፍጻሜ የሆኑት ክንውኖች እውን ሆኑ። መዝሙሩ በድምቀት የሚሰማበት ጊዜ ሆነ።

^ አን.11 ሁኔታው ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው ከሚሰጠው ታማኝና ልባም ባሪያ ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ማቴዎስ 24:45) ባሪያው እንደ አንድ አካል በመሆን ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ሲኖርበት ቤተሰቦቹ ማለትም የአካሉ ግለሰብ አባሎች ከመንፈሳዊው ዝግጅት በመካፈል ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው ይኖራሉ። የአንድ ቡድን አባላት ሲሆኑ የተገለጹት ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ነው። በቡድንና በግለሰብ ተገልጸዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 202, 203 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

144,000

24 ሽማግሌዎች

የበጉ የክርስቶስ ኢየሱስ ተባባሪ ወራሾች ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ሲታዩ