ኢየሱስ የሚያበረታታ መልእክት ይዞ መጣ
ምዕራፍ 4
ኢየሱስ የሚያበረታታ መልእክት ይዞ መጣ
1. አሁን ዮሐንስ የጻፈው ለማን ነው? በአሁኑ ጊዜ እርሱ ስለጻፈው መልእክት አጥብቀው ማሰብ የሚኖርባቸው እነማን ናቸው?
ቀጥሎ የሆነው ነገር ዛሬ ከአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ ጋር የተባበሩትን ሁሉ ከልብ የሚነካ ነገር ነው። ከዚህ በታች ተከታታይ የሆኑ መልእክቶች ቀርበዋል። እነዚህ መልእክቶች “ዘመኑ” እየቀረበ በሄደ መጠን የተለየ ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። (ራእይ 1:3) እነዚህን መግለጫዎች ማስተዋላችን የዘላለም በረከት ያስገኝልናል። የተመዘገበው መልእክት እንዲህ ይላል:- “ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣ . . . ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።”—ራእይ 1:4, 5ሀ
2. (ሀ) “ሰባት” ቁጥር ምን ያመለክታል? (ለ) “ለሰባቱ ጉባኤዎች” የተላከው መልእክት በዚህ በጌታ ቀን የሚመለከተው ማንን ነው?
2 እዚህ ላይ ዮሐንስ የጻፈው “ለሰባት ጉባኤዎች” እንደሆነ ገልጾአል። ቆየት ብሎም በትንቢቱ ውስጥ በስም ይጠቅሳቸዋል። “ሰባት” ቁጥር በራእይ ውስጥ ተደጋግሞ ይጠቀሳል። ሙሉነትን፣ በተለይም አምላክንና የቅቡዓንን ጉባኤ በሚመለከቱ ጉዳዮች የተሟላ መሆንን ያመለክታል። በጌታ ቀን በዓለም በሙሉ የሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስለሆኑ ‘ለሰባቱ የቅቡዓን ጉባኤዎች’ የተነገረው ሁሉ በዘመናችን ላሉት የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ እንደሚሠራ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ራእይ 1:10) አዎ፣ ዮሐንስ ለይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ሁሉና ከጉባኤዎቹ ጋር ለተባበሩት በማንኛውም የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት አለው።
3. (ሀ) ዮሐንስ በሰላምታው እንደገለጸው “ጸጋና [“የማይገባ ደግነትና፣” NW] ሰላም” የሚገኘው ከየት ነው? (ለ) ከዮሐንስ ሰላምታ ጋር የሚመሳሰለው የትኛው የሐዋርያው ጳውሎስ አነጋገር ነው?
3 “ጸጋና [“የማይገባ ደግነትና፣” NW] ሰላም” በተለይ ከየት እንደሚገኙ ስናስተውል በጣም ተፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን እንገነዘባለን። “ጸጋና ሰላም” የሚፈስሰው “የዘላለም ንጉሥ” ከሆነውና “ከዘላለም እስከ ዘላለም” ከሚኖረው ሉዓላዊ ገዥ ከይሖዋ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ መዝሙር 90:2) እዚህ ላይ “ሰባቱ መናፍስት” ተጠቅሰዋል። ይህም ቃል የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስ ትንቢቱን ለሚከታተሉት ሁሉ ማስተዋልና በረከት በሚያመጣበት ጊዜ በተሟላ ሁኔታ እንደሚሠራ ያመለክታል። በተጨማሪም ለኢየሱስ ክርስቶስ ቁልፍ ቦታ ተሰጥቶታል። ስለ እርሱም ዮሐንስ “ጸጋና እውነት” የተሞላ እንደሆነ ጽፎአል። (ዮሐንስ 1:14) ስለዚህ የዮሐንስ ሰላምታ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ የጻፈውን ሁለተኛ መልእክቱን ሲደመድም “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ [“የማይገባ ደግነት፣” NW]፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን” በማለት ከተናገረው ጋር ተመሳሳይነት አለው። (2 ቆሮንቶስ 13:14) ይህ ቃል ዛሬ እውነትን ለምናፈቅር ሁሉ እንዲፈጸምልን ከልብ እንመኛለን።—መዝሙር 119:97
“ታማኙ ምስክር”
4. ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ መግለጫ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ከይሖዋ ቀጥሎ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ታላቅ ግርማ ያለው አካል ኢየሱስ ነው። ዮሐንስም ይህን በመረዳት “የታመነው ምስክር፣ የሙታንም በኩር፣ የምድርም ነገሥታት ገዥ” ሲል ገልጾታል። (ራእይ 1:5ለ) በሰማያት እንዳለው ጨረቃ ለይሖዋ አምላክነት ታላቅ ምሥክር በመሆን በማይናወጥ ሁኔታ ተመሥርቶአል። (መዝሙር 89:37) መሥዋዕት ሆኖ እስከመሞት ድረስ ፍጹም አቋሙን ከጠበቀ በኋላ ከሰው ልጆች መካከል ከሙታን ተነስቶ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ለማግኘት የመጀመሪያው ሆነ። (ቆላስይስ 1:18) አሁን ደግሞ በይሖዋ ፊት ቀርቦ “በሰማይና በምድር ሁሉ ሥልጣን” ስለተሰጠው ከምድር ነገሥታት ሁሉ በላይ ከፍ ተደርጎአል። (ማቴዎስ 28:18፤ መዝሙር 89:27፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:15) በ1914 የምድር አሕዛብን ሁሉ እንዲገዛ ንጉሥ ሆኖ ተሹሞአል።—መዝሙር 2:6-9
5. (ሀ) ዮሐንስ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ የሚጠቀሙት እነማን ናቸው? ቅቡዓን ክርስቲያኖችስ ልዩ በሆኑ በረከቶች የተካፈሉት እንዴት ነው?
5 ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን አድናቆት መግለጹን በመቀጠል የሚከተሉትን ሞቅ ያሉ ቃላት ተናግሯል:- “ለወደደን፣ ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፣ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (ራእይ 1:5ሐ, 6) ኢየሱስ በእርሱ የሚያምነው የሰው ልጆች ዓለም በሙሉ ፍጹም ሕይወት መልሶ ለማግኘት እንዲችል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አደረገ። አንተም ውድ አንባቢ፣ ከዚህ ክፍል ለመሆን ትችላለህ! (ዮሐንስ 3:16) ይሁን እንጂ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት እንደ ዮሐንስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሚሆኑት ሁሉ ልዩ በረከት ለማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቶላቸዋል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምክንያት ጻድቃን ሆናችኋል ተብሎ ተነግሮላቸዋል። የታናሹ መንጋ አባሎች ልክ እንደ ኢየሱስ በምድር ላይ የመኖር ዕድላቸውን በመተው በአምላክ መንፈስ ቅዱስ ተወልደዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋርም በመንግሥቱ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ለማገልገል ከሙታን እንደሚነሱ ተስፋ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 12:32፤ ሮሜ 8:18፤ 1 ጴጥሮስ 2:5፤ ራእይ 20:6) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ዮሐንስ በጋለ ስሜት ክብርና ኃይል የኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ማረጋገጡ አያስደንቅም።
“ከደመና ጋር ይመጣል”
6. (ሀ) ዮሐንስ ኢየሱስ ‘ከደመናት ጋር ስለመምጣቱ’ ምን አሳውቆአል? ዮሐንስ የትኛውን የኢየሱስ ትንቢት ሊያስታውስ ይችላል? (ለ) ኢየሱስ ‘የሚመጣው’ እንዴት ነው? በምድር ላይ ታላቅ መከራ የሚደርስባቸው ወይም ዋይ! ዋይ! የሚሉት እነማን ናቸው?
6 ከዚህ ቀጥሎ ዮሐንስ የሚከተለውን በታላቅ ደስታ ያስታውቃል:- “እነሆ፤ ከደመና ጋር ይመጣል፣ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፣ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፣ አሜን።” (ራእይ 1:7) እዚህ ላይ ዮሐንስ ኢየሱስ ስለ ሥርዓቱ ፍጻሜ የተናገረውን ትንቢት አስታውሶ እንደነበረ አያጠራጥርም። ኢየሱስ በዚያ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።” (ማቴዎስ 24:3, 30) ስለዚህ ኢየሱስ ትኩረቱን የይሖዋን ፍርድ በአሕዛብ ላይ ወደ መፈጸም ዞር በማድረግ ‘ይመጣል።’ ይህም በምድር ላይ ታላላቅ ለውጦችን ያስከትላል። “የምድር ወገኖች ሁሉ” የኢየሱስን ንግሥና እውነታ ስላልተቀበሉ “ሁሉን የሚችለው የአምላክ ቁጣ” ይወርድባቸዋል።—ራእይ 19:11-21፤ መዝሙር 2:2,3, 8, 9
7. “ዓይን ሁሉ” ኢየሱስን ለመታዘዝ እምቢተኛ የሆኑትም ጭምር ኢየሱስን የሚያዩት እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት “ገና ጥቂት ዘመን አለ፣ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 14:19) ታዲያ ዓይን ሁሉ የሚያየው እንዴት ነው? የኢየሱስ ጠላቶች እንደገና በሥጋዊ ዓይናቸው ያዩታል ብለን መጠበቅ የለብንም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከአረገ በኋላ የሚኖረው “ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ነው።” “አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም።” (1 ጢሞቴዎስ 6:16) ዮሐንስ ‘ማየት’ ያለው የማስተዋል ስሜትን ለመግለጽ እንደሆነ ግልፅ ነው። የአምላክን የማይታዩ ባሕርያት ከፍጥረቶቹ ለማየት ወይም ለማስተዋል እንደምንችለው ማለት ነው። (ሮሜ 1:20) ኢየሱስ “ከደመና ጋር ይመጣል” መባሉ በደመና የተሸፈነች ፀሐይ እንደማትታይ ሁሉ በሥጋዊ ዓይን በማይታይ ሁኔታ ይመጣል ማለት ነው። ቀን ላይ ፀሐይ በደመና ብትሸፈንም እንኳን ዙሪያውን ብራ ስለሆነ እንዳለች እናውቃለን። በተመሳሳይም ጌታ ኢየሱስ ሊታይ የማይችል ቢሆንም ‘የእርሱን ወንጌል በማይታዘዙት ላይ በቀሉን ሲያወርድ እንደሚንበለበል እሳት ሆኖ ይገለጣል።’ የማይታዘዙትም ቢሆኑ እንዲያዩት ይገደዳሉ።—2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ 2:8
8. (ሀ) በ33 እዘአ ኢየሱስን “የወጉት” እነማን ነበሩ? ዛሬስ እነዚህን ሰዎች የሚመስሉት እነማን ናቸው? (ለ) ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ስለማይኖር ሰዎች ሊወጉት የሚችሉት እንዴት ነው?
8 በተጨማሪም ኢየሱስን “የወጉት ያዩታል።” እነዚህ የወጉት ሰዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? ኢየሱስ በ33 እዘአ በተገደለበት ጊዜ ሮማውያን ወታደሮች ቃል በቃል ወግተውት ነበር። አይሁዳውያንም የዚህ ግድያ ወንጀል ተካፋዮች ነበሩ። ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ለእነዚህ አይሁዳውያን ሲናገር “እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም” አደረገው ብሎአል። (ሥራ 2:5-11, 36፤ ከዘካርያስ 12:10ና ከዮሐንስ 19:37 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ሮማውያንና አይሁዳውያን ከሞቱ 2,000 ዓመት ሊሞላ ተቃርቦአል። ስለዚህ በዘመናችን ‘የወጉት’ ሰዎች ኢየሱስ በተሰቀለበት ጊዜ የታየውን የመሰለ የጥላቻ ዝንባሌ የሚያሳዩትን ብሔራትና ሕዝቦች የሚያመለክቱ መሆን ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ አሁን በምድር ላይ የለም። ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች ስለ ኢየሱስ የሚመሰክሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው በቀጥታ ሲያሳድዱም ሆነ የሚደርስባቸውን ስደት ዝም ብለው በቸልታ ሲመለከቱ ኢየሱስን እንደወጉት ይቆጠራል።—ማቴዎስ 25:33, 41-46
“አልፋና ኦሜጋ”
9. (ሀ) አሁን መናገር የጀመረው ማን ነው? እርሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በቀጥታ የተናገረው ስንት ጊዜ ነው? (ለ) ይሖዋ ራሱን “አልፋና ኦሜጋ” እንዲሁም “ሁሉን የሚችል” ብሎ መጥራቱ ምን ትርጉም አለው?
9 አሁን በጣም አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። ልዑላዊው ገዥ ይሖዋ ራሱ ተናገረ። ይህም ለሚገለጠው ራእይ መግቢያ መሆኑ በጣም ተገቢ ነው። ምክንያቱም ታላቁ አስተማሪያችንና የራእይ ሁሉ ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ነው። (ኢሳይያስ 30:20) አምላካችን እንዲህ አለ:- “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ:- አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ።” (ራእይ 1:8) ይህ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ ራሱ በሰማይ ሆኖ ከተናገረባቸው ሦስት ጊዜያት የመጀመሪያው ነው። (በተጨማሪም ራእይ 21:5-8፤ 22:12-15 ተመልከት።) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አልፋና ኦሜጋ የመጀመሪያና የመጨረሻ የግሪክኛ ፊደላት መሆናቸውን በቀላሉ ሊገነዘቡ ይችሉ ነበር። ይሖዋ ራሱን በእነዚህ ሁለት የግሪክኛ ፊደላት መጥራቱ ከእርሱ በፊት ሁሉን የሚችል ሌላ አምላክ እንዳልነበረና ከእርሱም በኋላ እንደማይኖር አጥብቆ መግለጹ ነበር። ስለ አምላክነት የተነሳውን ጥያቄ በተሳካ ሁኔታ ወደ ፍጻሜ ያመጣዋል። አንዱና ብቸኛው ሁሉን የሚችል አምላክ፣ የመላው ፍጥረት ሉዓላዊ ገዥ መሆኑ ለዘላለም ይረጋገጣል።—ከኢሳይያስ 46:10ና ከ55:10, 11 ጋር አወዳድር።
10. (ሀ) ቀጥሎ ዮሐንስ ስለራሱ ምን ተናገረ? የትስ ይገኝ ነበር? (ለ) ዮሐንስ የጻፈው ጥቅልል ወደ ጉባዔዎች የደረሰው በማን ትብብር መሆን ይኖርበታል? (ሐ) በዘመናችንም መንፈሳዊ ምግብ በምን ዓይነት ሁኔታ ሲቀርብ ቆይቶአል?
10 ዮሐንስ የነገሮችን አፈጻጸም ይሖዋ ራሱ እንደሚመራ እርግጠኛ በመሆን እንደርሱ ባሮች ለሆኑት ጓደኞቹ እንዲህ አለ:- “እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ራእይ 1:9) ለምሥራቹ ሲል በፍጥሞ (በጳጥሞስ) እሥረኛ የሆነው፣ ከወንድሞቹ ጋር መከራ ይቀበል የነበረውና፣ በመጪው መንግሥት ለመካፈል ጠንካራ ተስፋ የነበረው አረጋዊዉ ዮሐንስ አሁን የመጀመሪያውን ራእይ ይመለከታል። በዘመናችን የዮሐንስ ክፍል የትንቢቶቹን ፍጻሜ ሲመለከት እንደሚበረታታ ሁሉ ዮሐንስም በእነዚህ ራእዮች በጣም ተበረታትቶ እንደነበረ አያጠራጥርም። ዮሐንስ በእስር ላይ ስለ ነበረ የራእይን መጽሐፍ ጥቅልል እንዴት ለጉባኤዎች እንዲደርስ እንዳደረገ አናውቅም። (ራእይ 1:11፤ 22:18, 19) ይህን ሥራ ለማስፈጸም የይሖዋ መላእክት ሳይረዱት አልቀሩም። ዛሬም ቢሆን እነዚህ መላእክት በእገዳ ሥር የሚያገለግሉ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮችን ይጠብቁአቸዋል። እውነትን ለሚራቡ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው መንፈሳዊ ምግብ እንዲያደርሱም ይረዱአቸዋል።—መዝሙር 34:6, 7
ቃልና ስለ ኢየሱስ ምሥክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ።” (11. በዛሬው ዘመን የሚገኙት የዮሐንስ ክፍል አባሎች እንደ ውድ ሀብት የሚቆጥሩት የትኛውን ጥንት ዮሐንስ ያገኘውን መብት ነው?
11 ይሖዋ ከጉባኤዎች ጋር ለመገናኘት ዮሐንስን መገናኛ መሥመር አድርጎ ስለተጠቀመበት በዚህ ባገኘው መብት ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! በተመሳሳይ የዮሐንስም ክፍል በዘመናችን ለአምላክ ቤተሰቦች ‘በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ’ የመስጠት መብቱን እንደ ታላቅ ሀብት ይቆጥረዋል። (ማቴዎስ 24:45) አንተም ከዚህ መንፈሣዊ ምግብ ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው የዘላለም ሕይወትን ግብ ከሚያገኙት ሰዎች መካከል እንድትሆን ከልብ እንመኛለን።—ምሳሌ 3:13-18፤ ዮሐንስ 17:3
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በአስቸጋሪ ጊዜያት መንፈሣዊ ምግብ ማግኘት
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ስደትና መከራ ስለ ደረሰባቸው በእምነት ጠንክረው እንዲኖሩ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት በጣም አስፈልጎአቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ይሖዋ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ኃይሉን ስለ ገለጠ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ማግኘት ችለዋል።
ለምሳሌ፣ በሂትለር ትገዛ በነበረችው በጀርመን አገር የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ባለ ሥልጣኖች የታገደውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ቅጂዎች በማባዣ መኪና አባዝተው ያሰራጩ ነበር። በሃምበርግ ከተማ ጌስታፖ የሚባሉት የምሥጢር ፖሊሶች መጽሔት ይባዛበት የነበረውን ቤት ከብበው መፈተሽ ጀመሩ። ቤቱ በጣም ትንሽ ስለ ነበረ ምንም ነገር ሊያስደብቅ የሚችል አልነበረም። የታይፕ መጻፊያ መኪናው ቁምሳጥን ውስጥ፣ ትልቁ የማባዣ መኪና ደግሞ ምድር ቤት ውስጥ በድንች ማስቀመጫ ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በተጨማሪም ከድንቹ ማስቀመጫ ቦታ በስተጀርባ ሻንጣ ሙሉ መጽሔት ተቀምጦ ነበር። መጋለጥ የማይቀር ነገር መስሎ ታየ። ይሁን እንጂ ምን ሆነ? ቁምሳጥኑን የከፈተው ወታደር በሩን የከፈተው የታይፕ መጻፊያ መሣሪያውን ሊያይ በማያስችለው ሁኔታ ነበር። ስለ ምድር ቤቱ ደግሞ የቤቱ ባለቤት እንዲህ ሲል ይናገራል:- “ሦስቱ ወታደሮች በምድር ቤቱ መሃል ለመሃል ቆመው ነበር። እዚህ ላይ ልብ በሉ፣ መጠበቂያ ግንብ የሞላበት ሻንጣ ከተቀመጠበት ከድንቹ ማስቀመጫ አጠገብ ነበር የቆሙት። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ልብ አላሉትም ነበር። እንደታወሩ ያህል ነበር።” በዚህ ዓይነት ይሖዋ ስለጠበቃቸው በዚህ አስቸጋሪና አደገኛ ጊዜ መንፈሳዊው ምግብ ከዚሁ ቤት እየተዘጋጀ እንዲቀርብ አስችሎአል።
በ1960ዎቹ ዓመታት፣ በናይጄሪያና በተገንጣይዋ ክፍለ ሀገር በቢያፍራ መካከል ጦርነት ይደረግ ነበር። ቢያፍራ በናይጄሪያ ግዛት ሥር ባሉ ክልሎች ሙሉ በሙሉ የተከበበች ስለነበረች ከውጭው ዓለም የምትገናኘው በአንድ የአውሮፕላን ማረፊያ አማካኝነት ብቻ ነበር። በ1968 መጀመሪያ ላይ የቢያፍራ ባለ ሥልጣኖች ከመንግሥት ሠራተኞቻቸው አንዱን በአውሮፓ ውስጥ ቁልፍ የሆነ ሥራ ላይ ሲመድቡት ሌላውን ደግሞ በቢያፍራ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሠራ መደቡ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ ሁለት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነርሱም ቢያፍራን ከውጭው ዓለም ጋር በሚያገናኘው ብቸኛ መስመር ጫፍና ጫፍ ላይ ተገኙ። ሁለቱም ይህ የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ ተገነዘቡ። በዚህም ምክንያት አደገኛና አሰቸጋሪ የነበረውን ጽሑፍ ወደ ቢያፍራ የማስገባት ሥራ ለመጀመር ፈቃደኞች ሆኑ። በጦርነቱ ዓመታት በሙሉ ይህንኑ ሥራቸውን ለማከናወን ችለዋል። አንደኛው ሲናገር:- “ዝግጅቱ ሰዎች ሊያቅዱ ከሚችሉት በላይ ነበር” ብሎአል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ ምሳሌያዊ ቁጥሮች
ቁጥር ምሳሌያዊ ትርጉም
2 አንድን ጉዳይ አጠንክሮ ማረጋገጥን ያመለክታል
(ራእይ 11:3, 4፤ ከዘዳግም 17:6 ጋር አወዳድር።)
3 ማጉላትን፣ ማጥበቅን በተጨማሪም የአንድን ነገር ክብደት ያመለክታል።
4 አጠቃላይነትን ወይም አራት ማዕዘን መሆንን ያመለክታል።
(ራእይ 4:6፤ 7:1, 2፤ 9:14፤ 20:8፤ 21:16)
6 አለፍጽምናን፣ ጤናማ ያልሆነና አስቀያሚ የሆነን ነገር ያመለክታል።
(ራእይ 13:18፤ ከ2 ሳሙኤል 21:20 ጋር አወዳድር።)
7 በይሖዋ ወይም በሰይጣን ዓላማ ረገድ በመለኮት የተወሰነ ሙሉነትን ያመለክታል።
(ራእይ 1:4, 12, 16፤ 4:5፤ 5:1, 6፤ 10:3, 4፤ 12:3)
10 በምድራዊ ነገሮች ረገድ በአካላዊ ሁኔታ ሙሉ ወይም ፍጹም መሆንን ያመለክታል።
(ራእይ 2:10፤ 12:3፤ 13:1፤ 17:3, 12, 16)
12 በመለኮታዊ ኃይል የተቋቋመን በሰማያት ወይም በምድር ላይ የሚገኝ ድርጅት ያመለክታል።
(ራእይ 7:5-8፤ 12:1፤ 21:12, 16፤ 22:2)
24 ሙላት ያለውን (እጥፍ የሆነን) የይሖዋ ድርጅታዊ ዝግጅት ያመለክታል።
(ራእይ 4:4)
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ቁጥሮች አንዳንዶቹን ቃል በቃል መረዳት ይኖርብናል። አብዛኛውን ጊዜ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የቁጥሩን ትርጉም ይወስነዋል።
(ራእይ 7:4, 9፤ 11:2, 3፤ 12:6, 14፤ 17:3, 9-11፤ 20:3-5 ተመልከት።)