በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁለት አስፈሪ አራዊት ጋር መታገል

ከሁለት አስፈሪ አራዊት ጋር መታገል

ምዕራፍ 28

ከሁለት አስፈሪ አራዊት ጋር መታገል

ራእይ 8--ራእይ 13:1-18

ርዕሰ ጉዳይ:- ባለ ሰባት ራሱ አውሬ፣ ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ፣ እና የአውሬው ምስል

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከናምሩድ ዘመን እስከ ታላቁ መከራ

1, 2. (ሀ) ዮሐንስ ስለ ዘንዶው ምን ተናገረ? (ለ) በምሳሌያዊ አነጋገር ዘንዶው ስለሚጠቀምበት የሚታይ ድርጅት ዮሐንስ የገለጸው እንዴት ነው?

ታላቁ ዘንዶ ወደ ምድር ተጥሎአል! እባቡም ሆነ አጋንንት ተከታዮቹ ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ሰማይ እንዲመለሱ እንደማይፈቀድላቸው ከራእይ መጽሐፍ ጥናታችን ተገንዝበናል። ይሁን እንጂ ‘ዓለሙን ሁሉ ስለሚያስተው ስለ ሰይጣን ዲያብሎስ’ የምናደርገውን ውይይት ገና አልጨረስንም። ታሪኩ ሰይጣን ሴቲቱንና ዘሮችዋን የሚዋጋበትን መሣሪያ በዝርዝር ይነግረናል። (ራእይ 12:9, 17) ዮሐንስ ስለዚህ ዘንዶ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።” (ራእይ 12:17ለ) ስለዚህ ቆም እንበልና ዘንዶው የሚገለገልበትን መሣሪያ እንመርምር።

2 ቅዱሳን ሰማያት በሰይጣንና በአጋንንቱ መታወካቸው ቀርቶአል። እነዚህ ክፉ መናፍስት ከሰማይ ተባርረው በምድር አካባቢ ብቻ ተወስነዋል። በዚህ ዘመን የመናፍስትነት ሥራ በጣም የተስፋፋው በዚህ ምክንያት እንደሆነ አያጠራጥርም። ተንኮለኛው እባብ አሁንም ብልሹ የሆነ መንፈሳዊ ድርጅት አለው። ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን ለማሳት የሚገለገልበት የሚታይ ድርጅት ይኖረው ይሆንን? ዮሐንስ ይነግረናል:- “አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፣ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፣ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፣ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፣ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።”—ራእይ 13:1, 2

3. (ሀ) ነቢዩ ዳንኤል የትኞቹን የሚያስፈሩ አራዊት በራእይ ተመልክቶ ነበር? (ለ) በ⁠ዳንኤል 7 ላይ የተገለጹት ግዙፍ አራዊት ምን ያመለክቱ ነበር?

3 ይህ የሚያስፈራ አውሬ ምንድን ነው? መልሱን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይነግረናል። ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከመውደቋ በፊት ዳንኤል የተባለው አይሁዳዊ ነቢይ ስለ አስፈሪ አራዊት ራእይ ተመልክቶ ነበር። በ⁠ዳንኤል 7:2-8 ላይ አራት አራዊት ከባሕር ሲወጡ እንደተመለከተ፣ የመጀመሪያው አንበሳ፣ ሁለተኛው ድብ፣ ሦስተኛው ደግሞ ነብር ይመስል እንደነበረና “እነሆም የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች . . . አሥር ቀንዶች” ያሏት አራተኛ አውሬ እንደተመለከተ ገልጾአል። ይህም ዮሐንስ በ96 እዘአ ገደማ ካየው አውሬ ጋር የሚያስደንቅ ተመሳሳይነት አለው። ያም አውሬ የአንበሳ፣ የድብና የነብር መልክ ነበረው። በተጨማሪም አሥር ቀንዶች ነበሩት። ዳንኤል ያያቸው ታላላቅ አውሬዎች ምንድን ናቸው? ዳንኤል “እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሱ አራት ነገሥታት ናቸው” በማለት ይገልጽልናል። (ዳንኤል 7:17) አዎ፣ እነዚህ አራዊት የ“ነገሥታት” ወይም የፖለቲካዊ ኃይላት ምሳሌ ናቸው።

4. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 8 ላይ የተገለጸው አውራ በግና አውራ ፍየል የምን ምሳሌዎች ነበሩ? (ለ) የአውራው ፍየል ቀንድ መሰበርና በአራት ቀንዶች መተካት ምን ያመለክት ነበር?

4 በሌላ ራእይ ደግሞ ዳንኤል ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ ትልቅ ቀንድ ባለው አውራ ፍየል ተወግቶ ሲወድቅ ተመልክቶአል። የዚህን ትርጉም መልአኩ ገብርኤል ነግሮት ነበር። “አውራው በግ . . . የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው።” ገብርኤል በመቀጠል የአውራው ፍየል ትልቅ ቀንድ እንደሚሰበርና በሌሎች አራት ቀንዶች እንደሚተካ ትንቢት ተናገረ። ይህ የተፈጸመው ከ200 ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ታላቁ እስክንድር ሲሞትና መንግሥቱ በእርሱ ምትክ በተነሱ አራት ጄኔራሎቹ በሚገዙ አራት መንግሥታት በተከፋፈለ ጊዜ ነበር።—ዳንኤል 8:3-8, 20-25 *

5. (ሀ) አውሬ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል እንዴት ያለ ሁኔታ ይገልጻል? (ለ) የ⁠ራእይ 13:1, 2 አውሬና ሰባት ራሶቹ ምን ያመለክታሉ?

5 ስለዚህ በመንፈስ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የምድርን የፖለቲካ ኃይላት እንደ አራዊት እንደሚመለከታቸው ግልጽ ነው። እንዴት ያሉ አራዊት ናቸው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ በ⁠ራእይ 13:1, 2 ላይ ያሉትን አራዊት “ጨካኞች” ካለ በኋላ “ቴሪዮን [በግሪክኛ አውሬ] የተባለው ቃል የሚሰጠውን ትርጉምና ሐሳብ ሁሉ እንቀበላለን። ጨካኝ፣ አጥፊ፣ አስፈሪ፣ በልቶ የማይጠግብ፣ ግዙፍ ፍጥረትን ያመለክታል።” * በእርግጥም ይህ ቃል ሰይጣን የሰው ልጆችን ለመግዛት መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበትን በደም የተጨማለቀ የፖለቲካ ሥርዓት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ቃል ነው። የዚህ አውሬ ሰባት ራሶች እስከ ዮሐንስ ዘመን ድረስ የተነሱትንና ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን ስድስት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ያመለክታሉ። እነርሱም ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ናቸው። ሰባተኛ የዓለም ኃያል መንግሥት ደግሞ ቆየት ብሎ እንደሚነሳ ተተንብዮአል።—ከ⁠ራእይ 17:9, 10 ጋር አወዳድር።

6. (ሀ) የአውሬው ሰባት ራሶች ግንባር ቀደም የሆኑት በምን ድርጊት ነው? (ለ) ይሖዋ የሮምን መንግሥት በአይሁድ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርዱን እንዲያስፈጽም የተጠቀመበት እንዴት ነው? በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖችስ እንዴት ያለ ሁኔታ አጋጠማቸው?

6 እርግጥ ነው፣ ከእነዚህ ሰባት መንግሥታት በተጨማሪ በታሪክ ዘመናት ውስጥ የተነሱ ሌሎች የዓለም ኃያል መንግሥታት ነበሩ። ዮሐንስ የተመለከተው አውሬ ከሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች በተጨማሪም ሌላ አካል ያለው መሆኑ ይህን የሚያመለክት ነው። ሰባቱ ራሶች ግን በየተራ የአምላክን ሕዝቦች በግንባር ቀደምትነት የጨቆኑትን የዓለም ኃያላን መንግሥታት ያመለክታሉ። ሰይጣን የሮም መንግሥት ይገዛ በነበረበት በ33 እዘአ በዚህ የአውሬ ራስ መሣሪያነት የአምላክን ልጅ አስገድሎአል። በዚያ ጊዜ አምላክ እምነት የለሹን የአይሁዳውያን ሥርዓት ጨርሶ ትቶት ነበር። በ70 እዘአ ደግሞ የሮምን መንግሥት ተጠቅሞ በዚህ ብሔር ላይ የቅጣት ፍርድ አመጣ። ይሁን እንጂ እውነተኛው የአምላክ እስራኤል ወይም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ስለነበረ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የነበሩት ክርስቲያኖች የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው በመሸሽ ከጥፋቱ ሊያመልጡ ችለው ነበር።—ማቴዎስ 24:15, 16፤ ገላትያ 6:16

7. (ሀ) የሥርዓቱ ፍጻሜ ሲደርስና የጌታ ቀን ሲጀምር ምን ነገር መፈጸም ነበረበት? (ለ) የ⁠ራእይ 13:1, 2 አውሬ ሰባተኛ ራስ የሆነው ማን ነው?

7 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ በተቃረበበት ጊዜ ግን የዚህ የጥንቱ ጉባኤ አባሎች ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ ከእውነት ፈቀቅ ብለው ነበር። እውነተኛ የክርስትና ስንዴዎች የነበሩት “የመንግሥት ልጆች”፣ “የክፉው ልጆች” በሆኑት እንክርዳዶች በአብዛኛው ተውጠው ነበር። የሥርዓቱ የመጨረሻ ቀን በመጣ ጊዜ ግን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሚገባ ተደራጅተው ብቅ አሉ። በጌታ ቀን ጻድቃን “እንደ ፀሐይ የሚያበሩ” መሆን ነበረባቸው። ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ለሥራ ተደራጅቶ ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) በዚህ ጊዜ የሮም መንግሥት ጠፍቶ ነበር። በዓለም መድረክ ላይ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይዞ የነበረው ሰፊ የነበረው የብሪታንያ መንግሥትና ኃያሉ የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ መንግሥት ነበር። ይህ ጣምራ መንግሥት የአውሬው ሰባተኛ ራስ ሆነ።

8. የእንግሊዝና የአሜሪካ ጥምር የዓለም ኃይል በአውሬ መመሰሉ ሊያስደነግጠን የማይገባው ለምንድን ነው?

8 የሰው ልጆችን የሚያስተዳድሩትን የፖለቲካ ባለሥልጣናት በአውሬ መመሰል የሚያስደነግጥ ነገር አይደለምን? የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅታዊና ግለሰባዊ ሕልውና በየፍርድ ቤቶች አጠያያቂ በነበረበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ያቀርቡባቸው ከነበሩት ክሶች አንዱ ይህ ነበር። ይሁን እንጂ እስቲ ቆም ብለን እናስብ! ብሔራት ራሳቸው አራዊትን ወይም እንስሳትን ብሔራዊ ምልክታቸው አድርገው ይጠቀሙ የለምን? ለምሳሌ ያህል ብሪታንያ አንበሳን፣ አሜሪካ ንሥርን እንዲሁም ቻይና ዘንዶን ብሔራዊ ምስል አድርገው ይጠቀማሉ። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ደራሲ አራዊትን የዓለም ኃያል መንግሥታት ምሳሌ አድርጎ ቢጠቀም ምን የሚነቀፍበት ምክንያት አለ?

9. (ሀ) አንድ ሰው ሰይጣን ለአውሬው ታላቅ ሥልጣን እንደሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ መግለጹን መቃወም የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣን እንዴት ተገልጾአል? በመንግሥታትስ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

9 ከዚህም በላይ አንዳንዶች ለአውሬው ታላቅ ሥልጣን የሰጠው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩን የሚቃወሙት ለምንድን ነው? ይህን የተናገረው አምላክ ነው። ብሔራት ደግሞ በአምላክ ፊት በእንስራ ውስጥ እንዳለ የውኃ ጠብታ ወይም እንደ አቧራ ቅንጣት ናቸው። እነዚህ ብሔራት የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ስለ እነርሱ በሚናገረው ቃል ቅር ከመሰኘትና ከማኩረፍ ይልቅ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ቢጣጣሩ ይሻላቸዋል። (ኢሳይያስ 40:15, 17፤ መዝሙር 2:10-12) ሰይጣን የተኮነኑ ነፍሳትን ሩቅ በሚገኝ የሲኦል እሳት ለማሠቃየት የተመደበ አፈ ታሪክ የወለደው ፍጥረት አይደለም። እንዲህ ያለ የሥቃይ ቦታ የለም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን “የብርሃን መልአክ” እንደሚመስል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጾአል። በጠቅላላው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ግፊት የሚያደርግ ታላቅ አታላይ ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:3, 14, 15፤ ኤፌሶን 6:11-18

10. (ሀ) በእያንዳንዱ አሥር ቀንዶች ላይ ዘውድ መኖሩ ምን ያመለክታል? (ለ) አሥሩ ቀንዶችና አሥሩ ዘውዶች የምን ምሳሌዎች ናቸው?

10 አውሬው በሰባቱ ራሶቹ ላይ አሥር ቀንዶች አሉት። አራቱ ራሶች አንድ አንድ ቀንድ ሲኖራቸው ሦስቱ ራሶች ደግሞ ሁለት ሁለት ቀንዶች ያሉአቸው ይመስላል። ከዚህም በላይ በቀንዶቹ ላይ አሥር ዘውዶች አሉ። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ አስፈሪ አራዊት የተገለጹ ሲሆን የቀንዶቹም ቁጥሮች ቃል በቃል ትርጉም ነበራቸው። ለምሳሌ በአውራው በግ ላይ የነበሩት ሁለት ቀንዶች ከሁለት ጣምራ መንግሥታት የተውጣጣውን የሜዶንና ፋርስ ኃያል መንግሥት ያመለክቱ ነበር። የአውራው ፍየል አራት ቀንዶች ደግሞ ከታላቁ እስክንድር የግሪክ መንግሥት የወጡትን አራት አቻ መንግሥታት ያመለክቱ ነበር። (ዳንኤል 8:3, 8, 20-22) ይሁን እንጂ ዮሐንስ በተመለከተው አውሬ ላይ የነበሩት አሥር ቀንዶች ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ይመስላል። (ከ⁠ዳንኤል 7:24⁠ና ከ⁠ራእይ 17:12 ጋር አወዳድር።) እነዚህ አሥር ቀንዶች የመላው የሰይጣን ፖለቲካዊ ድርጅት አባላት የሆኑትን ሉዓላዊ መንግሥታት በጠቅላላ ያመለክታሉ። እነዚህ ቀንዶች በሙሉ ተዋጊዎችና ጠበኞች ቢሆኑም የበላይነት ወይም የራስነት ቦታ የሚይዙት ግን በሰባቱ ራሶች እንደተመሰለው በየተራ ነው። አሥሩም ዘውዶች በተመሳሳይ ሉዓላዊ መንግሥታት በሙሉ በዘመኑ ካለው ኃያል መንግሥት ጋር የየራሳቸው ግዛትና ሥልጣን እንደሚኖራቸው ያመለክታሉ።

11. አውሬው በራሶቹ ላይ “የስድብ ስሞች” ያሉት መሆኑ ምን ያመለክታል?

11 አውሬው “በራሱ ላይ የስድብ ስሞች” አሉበት። ይህም የማይገባ ነገር በመናገር ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን እንደማያከብርና እንደሚያቃልል ያሳያል። የፖለቲካ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም በአምላክና በክርስቶስ ስም አለአግባብ ተጠቅሞአል። የሐሰት ሃይማኖት አጫፋሪ በመሆን ቀሳውስት በፖለቲካ ጉዳዮቹ ውስጥ ገብተው እንዲካፈሉ እስከ መፍቀድ ደርሶአል። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝ አገር ውስጥ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ ጳጳሳት በአባልነት ይገኛሉ። የካቶሊክ ሊቃነ ጳጳሳት በፈረንሳይና በኢጣልያ አገር ከፍተኛ የፖለቲካ ሚና ተጫውተው ነበር። በቅርብ ጊዜ ደግሞ ቀሳውስት በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ የፖለቲካ ሹመት ተቀብለዋል። መንግሥታት በወረቀት ገንዘቦቻቸው ላይ “በአምላክ እንታመናለን” የሚሉትን የመሰሉ ሃይማኖታዊ መፈክሮችን ያትማሉ። በሳንቲሞቻቸው ላይ ደግሞ ገዥዎቻቸው “በእግዚአብሔር ጸጋ” የተሾሙ እንደሆኑ የሚገልጽ ቃል በመቅረጽ መለኮታዊ ሞገስና ድጋፍ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህ ሁሉ አምላክን ወደ ብሔራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ለማስገባት የሚደረግ ሙከራ ስለሆነ ለአምላክ እንደ ስድብ ይቆጠራል።

12. (ሀ) አውሬው “ከባሕር” የወጣ መሆኑ ምን ያመለክታል? መውጣት የጀመረውስ መቼ ነው? (ለ) ዘንዶው ለምሳሌያዊው አውሬ ታላቅ ሥልጣን መስጠቱ ምን ያመለክታል?

12 አውሬው የወጣው “ከባሕር” ውስጥ ነው። ባሕር ደግሞ ሰብአዊ መንግሥታት የሚወጡበትን ተነዋዋጭ ሕዝብ ያመለክታል። (ኢሳይያስ 17:12, 13) ይህ አውሬ ከተነዋዋጭ የሰው ልጅ ባሕር ውስጥ ብቅ ማለት የጀመረው ጥንት በናምሩድ ዘመን (በ21ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ገደማ) ከኖህ የጥፋት ውኃ በኋላ ይሖዋን የሚጻረር ሰብአዊ ኅብረተሰብ መገኘት በጀመረ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 10:8-12፤ 11:1-9) ይሁን እንጂ ከሰባቱ ራሶቹ የመጨረሻው ራስ ሙሉ በሙሉ የተገለጠው በጌታ ቀን ነው። በተጨማሪም ለአውሬው ‘ኃይል፣ ሥልጣንና ዙፋን የሰጠው’ ዘንዶው እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል። (ከሉቃስ 4:6 ጋር አወዳድር።) አውሬው በሰው ልጆች ላይ የተቀመጠ የሰይጣን ፖለቲካዊ ፍጥረት ነው። በእውነትም ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” ነው።—ዮሐንስ 12:31

ለሞቱ የሆነው ቁስል

13. (ሀ) በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ በአውሬው ላይ ምን ጉዳት ደረሰበት? (ለ) በአንደኛው ራስ ላይ ለሞት የሚያደርስ ጉዳት በደረሰ ጊዜ መላው አውሬ የታመመው እንዴት ነው?

13 በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ አውሬው ከፍተኛ ውድቀት ደርሶበት ነበር። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ከራሶቹም ለሞት እንደታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፣ ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ።” (ራእይ 13:3) ይህ ቁጥር ከአውሬው ራሶች በአንደኛው ላይ ለሞት የሆነ ቁስል እንደ ደረሰበት ይናገራል። ቁጥር 12 ግን ሙሉው አውሬ እንደቆሰለ ያመለክታል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የአውሬው ራሶች በአንድ ጊዜ ብቅ አላሉም። እያንዳንዳቸው በሰው ልጆች ላይ በተለይም በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሰለጠኑት በየተራ ነው። (ራእይ 17:10) ስለሆነም የጌታ ቀን በጀመረበት ጊዜ ዋነኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ይገዛ የነበረው አንድ ራስ ብቻ ማለትም ሰባተኛው ራስ ብቻ ነበር። በዚህ ራስ ላይ የደረሰው ቁስል መላውን አውሬ የሚያሳምም ይሆናል።

14. ለሞት የሚያደርስ ጉዳት የደረሰበት መቼ ነበር? አንድ ወታደራዊ መኮንን ይህ ጉዳት በሰይጣን አውሬ ላይ ያስከተለውን ውጤት የገለጹት እንዴት ነው?

14 ለሞት የሆነው ቁስል ምን ነበር? አውሬው በሠይፍ እንደተመታ ቆየት ብሎ ተገልጾአል። ሠይፍ ደግሞ የጦርነት ምሳሌ ነው። ይህ በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ የደረሰበት የሠይፍ ምት የሰይጣንን ፖለቲካዊ አውሬ ፈጽሞ አዳክሞት የነበረውን የመጀመሪያ የዓለም ጦርነት የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። (ራእይ 6:4, 8፤ 13:14) ሞሪስ ዠነቭዋ የተባሉት ደራሲ በዚህ የጦርነት ጊዜ ወታደራዊ መኮንን ነበሩ። እርሳቸውም ስለዚህ ጦርነት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በመላው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የነሐሴ 2, 1914ን ያህል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ቀን እንደሌለ ሁሉ ሰው ይስማማል። በመጀመሪያ አውሮፓ፣ ወዲያው ብዙ ሳይቆይ ደግሞ መላው የሰው ልጅ በጣም አሰቃቂ በሆነ ማጥ ውስጥ ተዋጠ። መሠረታዊ ስምምነቶች፣ ውሎች፣ የሥነ ምግባር ሕጎች ሁሉ ከሥራቸው ተናጉ። ከቀን ወደ ቀን ማንኛውም ነገር አጠያያቂ መሆን ጀመረ። በዚያ ጊዜ የተፈጸመው ሁኔታ የሰው ልጅ ሊያስብና ሊገምት ከሚችለው በላይ የከፋ ሆነ። በጣም ከፍተኛ፣ አሸባሪና አስደንጋጭ ነበር። ትዝታው እስከ አሁን ድረስ ያባንነናል።”—ሞሪስ ዠነቭዋ የአካዳሚ ፍራንሴዝ አባል፣ ፕሮሚስ ኦፍ ግሬትነስ የተባለውን መጽሐፍ ጠቅሶ እንደጻፈው (1968)

15. የአውሬው ሰባተኛ ቀንድ ለሞት የሚያደርስ ቁስል የደረሰበት እንዴት ነው?

15 ከአውሬው ራሶች ዋነኛ ለሆነው ሰባተኛ ራስ ይህ ጦርነት ከፍተኛ ውድቀት ሆኖበት ነበር። ብሪታንያና ሌሎቹ የአውሮፓ ብሔራት ቁጥራቸው የበዛ ወጣት ዜጎቻቸውን አጥተዋል። በ1916 ተደርጎ በነበረው የሶም ወንዝ ጦርነት ብቻ የተገደሉትና ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው እንግሊዝ 420,000፣ ፈረንሳይ 194,000 የሚያህል፣ ጀርመን 440,000 ነበር። የሞቱትና ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ጠቅላላ ቁጥር ከ1,000,000 ይበልጣል! በኢኮኖሚ ረገድም ቢሆን ብሪታንያም ሆነች ሌሎቹ የአውሮፓ አገሮች ደቀዋል። በጣም ግዙፍ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት በከባድ ሁኔታ ቆስሎ ነበር። ከዚህም ቁስሉ አሁንም ሙሉ በሙሉ አላገገም። በእውነትም ይህ 28 ታላላቅ መንግሥታት የተካፈሉበት ጦርነት መላውን ዓለም ለሞት እንደሚያደርስ ቁስል አሳምሞት ነበር። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ ከ65 ዓመት በኋላ የለንደኑ ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት በነሐሴ 4, 1979 እትሙ ላይ “ዓለም በ1914 የነበራትን ውህደትና ስምምነት አጣች። ከዚያ ወዲህ ያንን መልሳ ለማግኘት አልቻለችም” የሚል ሐተታ አስፍሮ ነበር።

16. ዩናይትድ ስቴትስ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጊዜ የአንድ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ክፍል መሆንዋን ያሳየችው እንዴት ነው?

16 በጊዜው ታላቁ ጦርነት ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ ጦርነት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት አንደኛ ክፍል ሆኖ ብቅ እንዲል መንገዱን ከፍቶለታል። በጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ በሕዝብ አስተያየት ተቃውሞ ምክንያት ወደ ጦርነቱ ለመግባት አልቻለችም ነበር። ይሁን እንጂ የታሪክ ሊቅ የሆኑት ኤስሜ ዊንግፊልድ ስትራትፎርድ እንደጻፉት “በዚያ ጊዜ የተነሳው ዋነኛ ጥያቄ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ የከፍተኛ ችግር ሰዓት የህብረት በላይነታቸውንና የጋራ ባለአደራነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ያስወግዱ ይሆንን የሚል ነበር።” በኋላ እንደታየው ለማስወገድ ችለዋል። በ1917 ዩናይትድ ስቴትስ የተባባሪዎቹን መንግሥታት ወታደራዊ አቅም ለማደርጀት ሀብትዋንና የሰው ኃይልዋን ሰጥታለች። በዚህም ምክንያት ብሪታንያንና ዩናይትድ ስቴትስን ያጣመረው ሰባተኛ ራስ በድል አድራጊነት ለመውጣት ቻለ።

17. ከጦርነቱ በኋላ በሰይጣን ምድራዊ ሥርዓት ላይ ምን ደረሰ?

17 ከጦርነቱ በኋላ የተገኘው ዓለም ቀድሞ ከነበረው ዓለም በጣም የተለየ ነበር። የሰይጣን ምድራዊ ሥርዓት ለሞት በሚያደርስ ቁስል ቢመታም እንደገና አንሰራርቶ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ኃይል አግኝቶአል። እንዲህ ባለ ፍጥነት ለማገገም በመቻሉ ከሰው ልጆች ከፍተኛ አድናቆት አትርፎአል።

18. የሰው ልጅ በአጠቃላይ አውሬውን በአድናቆት ተከትሎታል ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?

18 ታሪክ ጸሐፊው ቻርልስ ኤል ሚ ጁንየር እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “አሮጌው ሥርዓት [በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት] መፈራረሱ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የአዳዲስ ብሔራትና መደቦች መገኘትና ነጻ መውጣት፣ አዲስ ዓይነት ነጻነት መገኘት በጣም እንዲስፋፋ መንገድ ጠርጎ ነበር።” ለዚህ የድህረ ጦርነት ዘመን ምስረታ ግንባር ቀደም መሪ የነበረው ቁስሉ የዳነለትና ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካን በዋነኛ ኃያልነት ያጣመረው የአውሬው ሰባተኛ ራስ ነው። ይህ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅትም ሆነ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መቋቋም ዋነኛ ምክንያት ነበር። በ2005 የዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ኃይል የበለጸጉ አገሮች ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ እንዲያገኙ፣ የተለያዩ በሽታዎችን እንዲያሸንፉና በቴክኖሎጂ እንዲያድጉ አስችሎአል። እንዲያውም 12 ሰዎችን በጨረቃ ለማሳረፍ ችሎአል። ስለዚህ የሰው ልጅ በአጠቃላይ “አውሬውን እየተከተለ” መደነቁ የሚያስገርም አይደለም።

19. (ሀ) የሰው ልጅ አውሬውን ከማድነቅም የበለጠ ነገር ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለው ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (ሐ) ሰይጣን ለአውሬው ሥልጣን የሚሰጠው እንዴት ነው? ይህስ አብዛኛው የሰው ልጅ ምን እንዲያደርግ ምክንያት ሆኖአል?

19 ይሁን እንጂ የሰው ልጅ አውሬውን በማድነቅ ብቻ አላበቃም። ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚነግረን “ለዘንዶውም ሰገዱለት፣ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም:- አውሬውን ማን ይመስለዋል፣ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት።” (ራእይ 13:4) ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰይጣን በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ተናግሮ ነበር። ኢየሱስም ይህን አላስተባበለም። ይልቁንም ሰይጣን የዓለም ገዥ እንደሆነ ተናግሮ በዘመኑ በነበረው የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እምቢተኛ ሆኖአል። ዮሐንስም ስለ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ብሎአል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ሉቃስ 4:5-8፤ ዮሐንስ 6:15፤ 14:30) ሰይጣን ለአውሬው ሥልጣን በውክልና ሰጥቶታል። ይህንንም ሥልጣን የሚሰጠው ለየብሔሩ አከፋፍሎ ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ በአምላካዊ ፍቅር ከመተሳሰር ይልቅ በዘር፣ በጎሣና በብሔር ኩራት ተከፋፍሎአል። አብዛኞቹ የሰው ልጆች በሚኖሩበት አገር ሥልጣን የተረከበውን የአውሬ ክፍል ያመልካሉ። በዚህም መንገድ መላው አውሬ አድናቆትንና አምልኮን ይቀበላል።

20. (ሀ) ሰዎች አውሬውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች እንዲህ ባለው የአውሬ አምልኮ የማይካፈሉት ለምንድን ነው? የማንንስ አርዓያ ይከተላሉ?

20 ግን የሚመለከው በምን መንገድ ነው? የአገርን ፍቅር ከአምላክ ፍቅር በማስቀደም ነው። አብዛኞቹ ሰዎች የተወለዱበትን አገር ይወዳሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ጥሩ ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን የሚኖሩባቸውን አገሮች ገዥዎችና ብሔራዊ ምልክቶች ያከብራሉ ሕጎቹንም ይታዘዛሉ። ለሚኖሩበት ማኅበረሰብና ለጎረቤቶቻቸውም ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። (ሮሜ 13:1-7፤ 1 ጴጥሮስ 2:13-17) ይሁን እንጂ ሌላውን አገር ሁሉ ትተው ለአንድ አገር ብቻ በጭፍን መላ ሕይወታቸውን አይሰዉም። “ትክክልም ይሁን ስህተት ከማንኛውም ነገር አገሬ ትቀድማለች” ማለት ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ አይደለም። ስለዚህ ይሖዋን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች ሁሉ ለማንኛውም የአውሬ ክፍል የኩራትና የአርበኝነት አምልኮ አይሰጡም። ይህን ቢያደርጉ የአውሬው የሥልጣን ምንጭ የሆነውን ዘንዶ ማምለክ ይሆንባቸዋል። በአድናቆት ተነሳስተው “አውሬውን ማን ይመስለዋል?” ብለው ሊጠይቁ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ደግፈው በሚቆሙበት ጊዜ የስሙ ትርጉም “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት የሆነውን የሚካኤልን አርዓያ ይከተላሉ። ይህ ሚካኤል ወይም ክርስቶስ ኢየሱስ ሰይጣንን ከሰማይ በማባረር ድል እንደነሳ ሁሉ አምላክ በቀጠረው ጊዜ ከአውሬው ጋርም ተዋግቶ ድልን ይቀዳጃል።—ራእይ 12:7-9፤ 19:11, 19-21

ቅዱሳንን መውጋት

21. ሰይጣን አውሬውን ወደፈለገው አቅጣጫ እንደሚያሽከረክረው ዮሐንስ የገለጸው እንዴት ነው?

21 መሰሪው ሰይጣን ዲያብሎስ አውሬውን የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም ወደፈለገው አቅጣጫ ያሽከረክረዋል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል:- “ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ [ለባለ ሰባት ራሱ አውሬ] ተሰጠው፣ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፣ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።”—ራእይ 13:5-8

22. (ሀ) 42ቱ ወራት የሚያመለክቱት የትኛውን ጊዜ ነው? (ለ) በእነዚህ 42 ወራት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ድል የተነሱት እንዴት ነው?

22 እዚህ ላይ የተጠቀሰው 42 ወር በዳንኤል ትንቢት ላይ ከተገለጹት አራዊት መካከል ከአንደኛው አውሬ በወጣው ቀንድ ቅዱሳኑ መከራ ከተቀበሉበት ከሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ጋር አንድ ይመስላል። (ዳንኤል 7:23-25፤ በተጨማሪም ራእይ 11:1-4ን ተመልከት።) ስለዚህ ከ1914 መገባደጃ እስከ 1918 በነበረው ጊዜ ጦረኞቹ ብሔራት እንደ ዱር አራዊት እርስ በርሳቸው በሚቦጫጨቁበት ጊዜ የብሔራቱ ዜጎች አውሬውን እንዲያመልኩ፣ በብሔር አምልኮ እንዲካፈሉና ለአገራቸው እስከ መሞት ድረስ ዝግጁ እንዲሆኑ ተጽእኖ ተደርጎባቸው ነበር። ይህ ተጽእኖ ከሁሉ በላይ መታዘዝ የሚገባቸው አምላክንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነ ያምኑ በነበሩት በብዙዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ከባድ መከራ አድርሶባቸዋል። (ሥራ 5:29) ይህ ፈተና ድል በተነሱበት ዓመት ማለትም በሰኔ ወር 1918 ከፍተኛውን ደረጃ ያዘ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ዋነኛ ሹማምንትና ሌሎች ተጠሪዎች አለአግባብ ታሠሩ። ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ያከናውኑ የነበረው የስብከት ሥራ በአብዛኛው ታገደ። አውሬው “በነገድ፣ በቋንቋና በሕዝብ” ሁሉ ላይ ሥልጣን ስላለው የአምላክን ሥራ በዓለም በሙሉ አግዶት ነበር።

23. (ሀ) የበጉ ‘የሕይወት መጽሐፍ’ ምንድን ነው? ከ1918 ጀምሮ ሊጠናቀቅ የተቃረበው ሥራ ምንድን ነው? (ለ) የሚታየው የሰይጣን ድርጅት “በቅዱሳን” ላይ እንዳገኘ የመሰለው ድል መናኛና ጊዜያዊ የሆነው ለምንድን ነው?

23 ሰይጣንና ድርጅቱ ድል ያገኙ መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጊዜያዊ ድል ዘላቂ ጥቅም ሊያመጣላቸው አይችልም። ምክንያቱም በሚታየው የሰይጣን ድርጅት ውስጥ “በበጉ መጽሐፍ ውስጥ” ስሙ የተጻፈለት አንድም ሰው የለም። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት የሚገዙ ሰዎች ስም በምሳሌያዊ ሁኔታ ተመዝግቦአል። የመጀመሪያዎቹ ስሞች የተመዘገቡት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በነበሩት ዓመታት ሁሉ ተጨማሪ ስሞች ሲመዘገቡ ቆይተዋል። ከ1918 ጀምሮ ደግሞ ከ144, 000ዎቹ የመንግሥት ወራሾች የቀሩትን የማተሙ ሥራ ሲካሄድ ቆይቶ ወደ ፍጻሜው ተዳርሶአል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሁሉም ስም በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ ይመዘገባል። አውሬውን ከሚያመልኩት ተቃዋሚዎች መካከል ግን የአንዳቸው ስም እንኳን በመጽሐፉ ጥቅልል ውስጥ አይመዘገብም። ስለዚህ በቅዱሳኑ ላይ ምንም ዓይነት ጊዜያዊና የይስሙላ ድል ቢያገኙ ዘላቂነት የሌለውና ባዶ ድል ነው።

24. ዮሐንስ የሚያስተውሉ ሁሉ ምን እንዲሰሙ ጠይቆአል? የተሰሙትስ ቃላት ለአምላክ ሕዝቦች ምን ትርጉም አላቸው?

24 አሁን ደግሞ ዮሐንስ አስተዋዮች የሆኑ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲያዳምጡ ይጠይቃል:- “ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና [“ጽናትና፣” NW] እምነት በዚህ ነው።” (ራእይ 13:9, 10) ኤርምያስ ከ607 ከዘአበ በነበሩት ዓመታት በከዳተኛይቱ የኢየሩሳሌም ከተማ ላይ የመጣው የይሖዋ ፍርድ ሊመለስ የማይችል መሆኑን ሲያመለክት ተመሳሳይ ቃላት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 15:2፤ በተጨማሪም ኤርምያስ 43:11⁠ንና ዘካርያስ 11:9ን ተመልከት።) ኢየሱስ መከራ ይቀበል በነበረበት ጊዜ “ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት ተከታዮቹ በዚህ ረገድ ጽኑ አቋም እንዲይዙ በግልጽ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 26:52) በዚህ በጌታ ቀንም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አጽንተው መጠበቅ ይኖርባቸዋል። አለምንም ንስሐና ጸጸት አውሬውን በማምለክ የሚጸኑ ሁሉ ከጥፋቱ ሊያመልጡ አይችሉም። ሁላችንም ከፊታችን የተደቀነብንን ስደትና መከራ ተቋቁመን ለማለፍ ከፈለግን ጽናትና የማይናወጥ እምነት ያስፈልገናል።—ዕብራውያን 10:36-39፤ 11:6

ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ

25. (ሀ) ዮሐንስ ወደ ዓለም መድረክ ስለ ወጣ ሌላ ምሳሌያዊ አውሬ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአዲሱ አውሬ ሁለት ቀንዶችና አውሬው ከምድር መውጣቱ ምን ያመለክታሉ?

25 አሁን ደግሞ አንድ ሌላ አውሬ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ አለ። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፣ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል። እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል።” (ራእይ 13:11-13) ይህ አውሬ ሁለት ቀንዶች አሉት። ይህም የሁለት ፖለቲካዊ ኃይላት ጥምር መሆኑን ያመለክታል። በተጨማሪም ይህ አውሬ የወጣው ከባሕር ሳይሆን ከምድር እንደሆነ ተገልጾአል። ስለዚህ ቀድሞውኑ ተቋቁሞ ከነበረው ከሰይጣን ምድራዊ ሥርዓት ውስጥ የወጣ ነው። ከዚህ በፊት የነበረና በጌታ ቀን ደግሞ ግንባር ቀደም የሥራ ድርሻ የሚኖረው የዓለም ኃያል መንግሥት መሆን ይኖርበታል።

26. (ሀ) ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ምንድን ነው? ከመጀመሪያውስ አውሬ ጋር ምን ዝምድና አላቸው? (ለ) የአውሬው ሁለት ቀንዶች የበግ ቀንድ የሚመስሉ የሆኑት በምን መንገድ ነው? ሲናገርስ “እንደ ዘንዶ” የሆነው እንዴት ነው? (ሐ) ብሔራዊ ስሜት ያላቸው ሰዎች የሚያመልኩት ማንን ነው? ብሔራዊ ስሜትስ በምን ተመስሎአል? (የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።)

26 ታዲያ የትኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ሊሆን ይችላል? የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። በሌላ አነጋገር የመጀመሪያው አውሬ ሰባተኛ ራስ ሲሆን እዚህ ላይ ልዩ ሚና ይኖረዋል። በራእዩ ውስጥ የተለየ አውሬ ሆኖ ተነጥሎ መታየቱ በዓለም መድረክ በተናጠል የሚፈጽማቸውን ነገሮች በግልጽ እንድንመለከት ያስችለናል። ይህ ምሳሌያዊ ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ አብረው ከሚኖሩ፣ ነጻና የፖለቲካ ኃይላቸውን ለማስተባበር ፈቃደኛ በሆኑ ሁለት መንግሥታት የተቋቋመ ነው። ሁለቱ ቀንዶቹ “የበግ ቀንዶች የሚመስሉ” መሆናቸው ሰዎችን የማይጋፋና ልዝብ፣ ዓለም በሙሉ በምሳሌነት የሚመለከተው የሰለጠነ መንግሥት እንደሆነ አድርጐ ራሱን ማቅረቡን ያመለክታል። ይሁን እንጂ የአገዛዝ ሥርዓቱ ተቀባይነት ባላገኘባቸው ሥፍራዎች በኃይል፣ በዛቻና በተለያየ ተጽእኖ ስለሚጠቀም “እንደ ዘንዶ” ይናገራል። ሰዎች ሁሉ በአምላክ በግ ለሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት እንዲገዙ አይገፋፋም። እንዲያውም የታላቁን ዘንዶ የሰይጣንን ዓላማና ፍላጎት ያስፈጽማል። ብሔራዊ ጥላቻንና መከፋፈልን ያስፋፋል። ይህ ሁሉ ድርጊት የመጀመሪያውን አውሬ አምልኮ የሚያስፋፋ ነው። *

27. (ሀ) ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ከሰማይ እሳት እንዲወርድ ማድረጉ ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዳለው ያመለክታል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ለዘመናችን ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ እንዴት ያለ አስተያየት አላቸው?

27 ይህ ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ ታላላቅ ድንቆችን ይፈጽማል። እንዲያውም ከሰማይ እሳት እንዲወርድ ያደርጋል። (ከማቴዎስ 7:21-23 ጋር አወዳድር።) ይህ የኋለኛው ምልክት ከበኣል ነቢያት ጋር የተገዳደረውን የጥንት የአምላክ ነቢይ ኤልያስን ያስታውሰናል። ኤልያስ በይሖዋ ስም ከሰማይ እሳት ለማውረድ በቻለ ጊዜ እርሱ እውነተኛ የአምላክ ነቢይ እንደሆነና የበኣል ነቢያት ደግሞ ሐሰተኛ መሆናቸው በማያጠራጥር ሁኔታ ተረጋግጦአል። (1 ነገሥት 18:21-40) ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬም እንደነዚህ የበኣል ነቢያት የነቢይነት ብቃትና ሹመት እንዳለው ይሰማዋል። (ራእይ 13:14, 15፤ 19:20) እንዲያውም በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች አማካኝነት የክፋት ኃይሎችን አጥፍቼአለሁ ይላል። ደግሞም አምላክ የለሽ በሚባለው ኮምኒዝም ላይ ድል እንደተቀዳጀ ይናገራል! በእርግጥም ብዙ ሰዎች ዘመናዊው ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ የነፃነትና የኑሮ ብልጽግና ጠባቂና ተከላካይ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

የአውሬው ምስል

28. ባለ ሁለቱ ቀንድ አውሬ የበግ ቀንድ የሚመስሉ ቀንዶች ቢኖሩትም እንደ በግ የዋህ አለመሆኑን ዮሐንስ ያመለከተው እንዴት ነው?

28 ይህ ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ የበግ ቀንድ ያለው መሆኑ እንደሚያሳየው በእርግጥ ቅንነት ያለው ነውን? ዮሐንስ በመቀጠል ይነግረናል:- “በአውሬው ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቁስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል። የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፣ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው።”—ራእይ 13:14, 15

29. (ሀ) የአውሬው ምስል ዓላማ ምንድን ነው? ይህስ ምስል የተቋቋመው መቼ ነው? (ለ) የአውሬው ምስል ሕይወት የሌለው በድን ሐውልት ያልሆነው ለምንድን ነው?

29 ይህ “የአውሬው ምስል” ምንድን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? ዓላማው ምስል የሆነለትን የባለ ሰባት ራሱን አውሬ አምልኮ ማስፋፋት ነው። ይህን በማድረጉም የዚህን አውሬ ሕልውና ያራዝማል። ይህ ምስል የተሰራው ባለ ሰባት ራሱ አውሬ ከሰይፍ ቁስሉ ከዳነ በኋላ ማለትም የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ካለቀ በኋላ ነበር። ይህ ምስል ናቡከደነፆር በዱራ ሜዳ አሰርቶት እንደነበረው ምስል ሕይወት የሌለው በድን ምስል አይደለም። (ዳንኤል 3:1) ባለ ሁለቱ ቀንድ አውሬ ትንፋሽ ስለሚሰጠው ሊንቀሳቀስና በዓለም ታሪክ ውስጥ የሥራ ድርሻ ሊኖረው ይችላል።

30, 31. (ሀ) የታሪክ ሐቅ ይህ ምስል ምን መሆኑን ያመለክታል? (ለ) ይህን ምስል አናመልክም በማለታቸው ምክንያት የተገደሉ ሰዎች አሉን? አስረዳ።

30 ከታሪክ ሂደት እንደምንረዳው ይህ ምስል በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ አሳሳቢነት፣ ደጋፊነትና ጠባቂነት የተቋቋመው የቀድሞ ስሙ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተባለው ድርጅት ነው። ይህ ምስል በ⁠ራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የራሱ ነፃ ሕልውና ያለው ሕያውና የሚተነፍስ ቀይ አውሬ ሆኖ በሌላ ምሳሌ ይቀርባል። ይህ ዓለም አቀፍ አካል ለሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ለማምጣት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ብሎ በጉራ ስለሚናገር ከመጠን በላይ “ይናገራል።” እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለአባል ብሔራት የመነታረኪያና የመሰዳደቢያ መድረክ ከመሆን አላለፈም። ለሥልጣኑ በማይገዛ በማንኛውም ሕዝብ ወይም ብሔር ላይ የውግዘት ቃል ያስተላልፋል። እንዲያውም ይህ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የእርሱን ርዕዮተ ዓለም ሳይቀበሉ የቀሩ ብሔራትን ከአባልነት አስወግዶአል። ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ደግሞ የዚህ የአውሬ ምስል ጦረኛ “ቀንዶች” የአጥፊነት ሥራቸውን ይፈጽማሉ።—ራእይ 7:14፤ 17:8, 16

31 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመሆን የተከሰተው የአውሬ ምስል ቃል በቃል ሰዎችን ገድሎአል። ለምሳሌ ያህል በ1950 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ኃይል በደቡብ ኮሪያና በሰሜን ኮሪያ መካከል በተደረገው ጦርነት ዘምቶ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ከደቡብ ኮሪያውያን ጋር ሆኖ በግምት 1, 420, 000 ሰሜን ኮሪያውያንንና ቻይናውያንን ገድሎአል። በተመሳሳይም ከ1960 እስከ 1964 በነበሩት ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ሠራዊት በኮንጎ ውስጥ (በአሁኑ ጊዜ ዛይር) ዘመቻ አካሂዶ ነበር። ከዚህም በላይ ፓፓ ፖል ስድስተኛንና ጆን ፖል ዳግማዊን ጨምሮ የዓለም መሪዎች ይህ የአውሬ ምስል ከሁሉ የተሻለውና የመጨረሻው የሰው ልጅ የሰላም ተስፋ እንደሆነ አበክረው መናገራቸውን ቀጥለዋል። የሰው ልጅ ይህን ድርጅት ማገልገሉን ከተወ የሰው ዘር ራሱን በራሱ ያጠፋል ይላሉ። ይህን በማለታቸውም በምሳሌያዊ ሁኔታ ከምስሉ ጋር ለመተባበርና እርሱን ለማምለክ እምቢተኛ የሆኑትን ሰዎች አስገድለዋል።—ዘዳግም 5:8, 9

የአውሬው ምልክት

32. ሰይጣን የሚታይ ድርጅቱን የፖለቲካ ክፍል በመቆጣጠር ከአምላክ ሴት ዘር በቀሩት ላይ ብዙ መከራ እንዲደርስባቸው ማድረጉን ዮሐንስ የገለጸው እንዴት ነው?

32 አሁን ደግሞ ዮሐንስ ሰይጣን የሚታየውን ድርጅቱን የፖለቲካ ክፍል እንዴት እየተቆጣጠረ ከአምላክ ሴት ዘሮች በቀሩት ላይ የተቻለውን ከፍተኛ መከራ እንደሚያመጣ ይመለከታል። (ዘፍጥረት 3:15) ስለ አውሬው የሚከተለውን መግለጫ ይሰጣል:- “ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፣ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፣ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።”—ራእይ 13:16-18

33. (ሀ) የአውሬው ስም ማን ነው? (ለ) ስድስት ቁጥር ከምን ነገር ጋር ይዛመዳል? አስረዳ።

33 አውሬው ስም አለው። ስሙም ቁጥር ነው። ይኸውም 666 ነው። ስድስት ቁጥር ከይሖዋ ጠላቶች ጋር ተዛምዶ ያለው ቁጥር ነው። ከራፋይም የተወለደው አንድ ፍልስጥኤማዊ ሰው በጣም ግዙፍ ሲሆን “በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት . . . ጣቶች” ነበሩት። (1 ዜና 20:6) ንጉሥ ናቡከደነፆር የፖለቲካ ሹማምንቱን በአንድ አምልኮ ለማስተባበር ሲል ወርዱ ስድስት ክንድ፣ ከፍታው ስድሳ ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አቁሞ ነበር። የአምላክ አገልጋዮች ምስሉን ለማምለክ እምቢተኞች በሆኑ ጊዜ ንጉሡ በእሳታማ እቶን ውስጥ ጣላቸው። (ዳንኤል 3:1-23) ስድስት ቁጥር በአምላክ አንጻር ሙሉነትን ከሚያመለክተው ከሰባት ቁጥር በአንድ ቁጥር የጎደለ ነው። ስለዚህ ሦስቱ ስድስት ቁጥር ከባድ አለፍጽምናን ያመለክታል።

34. (ሀ) የአውሬው ቁጥር “የሰው ቁጥር” መሆኑ ምን ያመለክታል? (ለ) 666 ለሰይጣን ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት ተስማሚ ስም የሆነው ለምንድን ነው?

34 ስም የአንድን ሰው ማንነት ያሳውቃል። ታዲያ ይህ ቁጥር የአውሬውን ማንነት የሚያሳውቀው እንዴት ነው? ዮሐንስ ቁጥሩ የመንፈሳዊ አካል ሳይሆን “የሰው ቁጥር” እንደሆነ ተናግሮአል። ስለዚህ ስሙ አውሬው ሰብአዊ መንግሥትን የሚያመለክት ምድራዊ ድርጅት መሆኑን እንድናውቅ ይረዳናል። ስድስት ቁጥር ከሰባት ጋር ሊመጣጠን እንደማይችል ሁሉ 666 ወይም ሦስት እጥፍ የሆነ ስድስት ከአምላክ የፍጽምና ደረጃ ጋር ፈጽሞ ሊመጣጠን የማይችለውን ሰፊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚያመለክት ስም መሆኑ ተገቢ ነው። የዓለም ፖለቲካዊ አውሬ 666 የሚለውን የቁጥር ስም ይዞ በበላይነት ሲገዛ ትላልቆቹ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የንግድ ድርጅቶች ደግሞ አውሬው በሰው ልጆች ጨቋኝነቱና በአምላክ ሕዝቦች አሳዳጅነቱ እንዲቀጥል አስችለውታል።

35. የአውሬውን ምስል በግንባር ላይ ወይም በቀኝ እጅ ላይ መቀበል ማለት ምን ማለት ነው?

35 የአውሬውን ስም በግንባር ላይ ወይም በቀኝ እጅ ላይ መቀበል ምን ማለት ነው? ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሕጉን በሰጠ ጊዜ “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፣ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው። በዓይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁኑ” ብሎ ነበር። (ዘዳግም 11:18) ይህ ማለት እስራኤላውያን እንቅስቃሴያቸውና አስተሳሰባቸው በሙሉ በሕጉ እንዲመራ ሕጉን ዘወትር ማሰብ ነበረባቸው ማለት ነው። 144, 000ዎቹ ቅቡዓን የአብና የኢየሱስ ስም በግንባራቸው ላይ እንደተጻፈ ተነግሮአል። ይህም የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረቶች መሆናቸውን ያሳውቃል። (ራእይ 14:1) ሰይጣንም ይህንኑ በመኮረጅ የአውሬውን አጋንንታዊ ምልክት ይጠቀማል። እንደ መሸጥና መግዛት በመሰሉት ዕለታዊ ተግባራት የተሰማራ ሰው ሁሉ አውሬው የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንዲያደርግ ይገደዳል። ከእነዚህም ድርጊቶች አንዱ በዓላትን ማክበር ነው። የአውሬውን ምልክት ለመቀበል እንዲችሉ አውሬው ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠር በመፍቀድ እንዲያመልኩት ይጠበቅባቸዋል።

36. የአውሬውን ምስል ለመቀበል እምቢተኛ የሆኑ ሁሉ ምን ዓይነት ችግሮች አጋጥመዋቸዋል?

36 የአውሬውን ምልክት ለመቀበል እምቢተኛ የሆኑ ሁሉ ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ተጋድሎ ለማድረግ ተገደዋል። ብዙ ረብሻ፣ ድብደባና ስደት ደርሶባቸዋል። በአምባገነን መሪዎች በሚገዙ አገሮች በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረዋል። ብዙዎችም እዚያው እንዳሉ ሞተዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ብዙ ወጣቶች ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ለመጣስ አሻፈረን በማለታቸው ለረዥም ጊዜ ታስረዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ብዙ ሥቃይ ከተቀበሉ በኋላ ተገድለዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ ክርስቲያኖች ቃል በቃል እንዳይገዙ ወይም እንዳይሸጡ ተከልክለዋል። አንዳንዶች ንብረት የመያዝ መብት ተነፍጎአቸዋል። ሌሎች ደግሞ በግብረ ሥጋ ተነውረዋል፣ ተገድለዋል አለበለዚያም ከትውልድ አገራቸው ተባርረዋል። ይህ ሁሉ የደረሰባቸው ለምንድን ነው? ለሕሊናቸው በመገዛት የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ካርድ ለመግዛት እምቢ ስላሉ ነው። *ዮሐንስ 17:16

37, 38. (ሀ) ይህ ዓለም የአውሬውን ምስል ለመቀበል እምቢተኛ ለሆኑ ሁሉ አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው የተገኙት እነማን ናቸው? ምንስ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?

37 በአንዳንድ አገሮች ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ሕይወት ውስጥ ጠልቆ የሰረጸ ስለሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የሚቆም ሰው በቤተሰቦቹና በቀድሞ ወዳጆቹ ይወገዛል። እንደዚህ ባለው ሁኔታ ጸንቶ ለመቆም ትልቅ እምነት ያስፈልጋል። (ማቴዎስ 10:36-38፤ 17:22) አብዛኞቹ ሰዎች ቁሳዊ ብልጽግናን በሚያመልኩበትና ማጭበርበር በተስፋፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በጀመረበት የቀና ጎዳና ጸንቶ ለመቆየት በይሖዋ ብቻ ለመታመን ይገደዳል። (መዝሙር 11:7፤ ዕብራውያን 13:18) በሥነ ምግባራዊ እርኩሰት በተጨማለቀው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕና አለነውር ሆኖ ለመኖር ትልቅ ቆራጥነት ይጠይቃል። በበሽታ የተያዙ ክርስቲያኖች አምላክ ስለ ደም ቅድስና የሰጠውን ሕግ እንዲጥሱ ዶክተሮችና ነርሶች ይጫኑአቸዋል። ከእምነታቸው ጋር የሚቃረኑ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን እንኳን ለመቃወም ተገድደዋል። (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 4:3, 4) ከዚህም በላይ ሥራ አጥነት እየተስፋፋ በሄደበት በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ያላቸውን ፍጹም አቋም ከሚያበላሽባቸው የሥራ ዓይነት ለመራቅ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቶአል።—ሚክያስ 4:3, 5

38 አዎ፣ በእርግጥም ዓለም የአውሬውን ምልክት ላልተቀበሉ ሰዎች በጣም አስቸጋሪ ሥፍራ ሆናለች። ከሴቲቱ ዘር የቀሩትና ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡት እጅግ ብዙ ሰዎች የአምላክን ሕግጋት እንዲጥሱ ይህ ሁሉ ተጽእኖ እየተደረገባቸው በፍጹም አቋማቸው ጸንተው ለመኖር መቻላቸው የይሖዋን ኃይልና በረከት በግልጽ ያረጋግጣል። (ራእይ 7:9) ሁላችንም የአውሬውን ምልክት ለመቀበል እምቢተኞች እየሆንን በአንድነትና በኅብረት በመላው ምድር ላይ ይሖዋንና የጽድቅ መንገዶቹን በማክበር እንቀጥል።—መዝሙር 34:1-3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ትርጉም በአር. ሲ. ኤች. ሌንስኪ፣ ገጽ 390-1

^ አን.26 የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ብሔራዊ ስሜት ከሃይማኖት ተለይቶ የሚታይ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ብሔራዊ ስሜት ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት አገር የሚወከለውን የአውሬ ክፍል ያመልካሉ ማለት ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስላለው ብሔራዊ ስሜት እንዲህ እናነባለን:- “ከሃይማኖት ተለይቶ የማይታየው ብሔራዊ ስሜት ከሌሎቹ ታላላቅ ሃይማኖቶች ጋር የሚመሳሰልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉት። . . . ዘመናዊው የብሔራዊ ስሜት ሃይማኖተኛ በብሔራዊ አምላኩ ላይ እንደሚተማመን ይሰማዋል። የዚህ አምላክ ኃያል እርዳታ እንደሚያስፈልገው ይገነዘባል። ከዚህ አምላክ ፍጹምነትና ደስታ እንደሚያገኝ ያስባል። በሃይማኖታዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ ይገዛለታል። . . . ብሔሩ ዘላለማዊ እንደሆነና የታማኝ ልጆቹም ሞት ለማይሞተው ብሔራዊ ዝናና ክብር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያምናል።”—ካርልተን ጄ ኤፍ ሄይስ ዋት አሜሪካንስ ቢሊቭ ኤንድ ሀው ዜይ ዎርሽፕ በተባለው የጄ ፖል ዊልያምስ መጽሐፍ በገጽ 359 ላይ እንደጠቀሱት።

^ አን.36 ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን የመጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እትሞች ተመልከት። መስከረም 1, 1971 ገጽ 520፤ ሰኔ 15, 1974 ገጽ 373፤ ሰኔ 1, 1975 ገጽ 341፤ የካቲት 1, 1979 ገጽ 23፤ ሰኔ 1, 1979 ገጽ 20፤ ግንቦት 15, 1980 ገጽ 10

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 195 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአውሬው ምስል ትንፋሽ ይሰጠው ዘንድ ተሰጠው