በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች” መጸየፍ

“የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች” መጸየፍ

ምዕራፍ 10

“የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች” መጸየፍ

ትያጥሮን

1. የትያጥሮን ከተማ አቀማማጥ ከሌሎች ከተሞች አንጻር እንዴት ያለ ነበር? እንዴት ባለ ሃይማኖታዊ አካባቢ የምትገኝ ከተማ ነበረች?

ከቤርጋማ (ጴርጋሞን) ደቡብ ምሥራቅ 64 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ አኪሳር የምትባለው ሞቅ ያለች የቱርክ ከተማ ትገኛለች። ከ1,900 ዓመታት በፊት የትያጥሮን ከተማ ትገኝ የነበረው በዚህ ሥፍራ ነበር። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወደ ትያጥሮን ከደረሰ በኋላ በእግር መንገድ በራእይ ምዕራፍ 3 ውስጥ ወደተጠቀሱት ሦስት ሌሎች ጉባኤዎች ማለትም ወደ ሰርዴስ፣ ወደ ፊልድልፍያና ወደ ሎዶቅያ በቀላሉ ሊደርስ ይችል ነበር። ትያጥሮን እንደ ጴርጋሞን የንጉሠ ነገሥት አምልኮ የሚካሄድባት ትልቅ ማዕከል ባትሆንም አረማውያን አማልክት የሚመለኩባቸው መሰዊያዎችና ቤተ መቅደሶች ነበሩባት። ትያጥሮን በጣም የታወቀች የንግድ ማዕከል ነበረች።

2, 3. (ሀ) ቀደም ሲል ስለ አንዲት ክርስቲያን የሆነች የትያጥሮን ሴት ምን ነገር ተጽፎ ነበር? (ለ) ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” መሆኑና “እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች” ያለው መሆኑ በትያጥሮን ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ትርጉም ነበረው?

2 ጳውሎስ በመቄዶንያ ይሰብክ በነበረበት ጊዜ ሊድያ የምትባል ቀይ ሐር ትሸጥ የነበረች የትያጥሮን ሴት አግኝቶ ነበር። ሊድያና የቤትዋ ሰዎች በሙሉ ጳውሎስ ይሰብክ የነበረውን መልእክት በደስታ ከተቀበሉ በኋላ በጣም አስደናቂ የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይታለች። (ሥራ 16:14, 15) እርስዋም በትያጥሮን ክርስትናን ለመቀበል የመጀመሪያዋ የተመዘገበች ሴት ሆነች። ከጊዜ በኋላ በዚህች ከተማ የክርስቲያኖች ጉባኤ ተቋቋመ። ኢየሱስ ከሁሉም ይበልጥ ረዥም የሆነውን መልእክት ያስተላለፈው ለዚህ ጉባኤ ነበር። “በትያጥሮን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል:-”—ራእይ 2:18

3 ኢየሱስ ይሖዋን “አባቴ” ብሎ የጠራባቸው ሌሎች ጊዜያት ቢኖሩም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ግን “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው አገላለጽ የሚገኘው በዚህ ቦታ ብቻ ነው። (ራእይ 2:27፤ 3:5, 21) ይህ አገላለጽ እዚህ ላይ መጠቀሱ የትያጥሮንን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ስላለው ቅርበት ሳያሳስባቸው አልቀረም። ይህ የይሖዋ ልጅ “እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች” ያሉት እንደሆነ ተገልጾአል። ይህም በትያጥሮን የነበሩትን ክርስቲያኖች የኢየሱስ ዓይን የጉባኤውን ንጽሕና ሲበክል በሚመለከተው በማንኛውም ነገር ላይ የፍርዱ እሳት እንደሚነድድ ያስጠነቅቃቸዋል። “የጋለ ነሐስ” ስለሚመስሉት እግሮቹ ለሁለተኛ ጊዜ በመናገሩ ደግሞ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረበት ጊዜ ስላሳየው አንጸባራቂ የታማኝነት ምሳሌ አጉልቶአል። በትያጥሮን የነበሩት ክርስቲያኖች ምክሩን ተቀብለው እንደነበር አያጠራጥርም። በዚህ ዘመን የምንኖረው እኛም ብንሆን የኢየሱስን ምክር መቀበል ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 2:21

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ በትያጥሮን የነበሩትን ክርስቲያኖች ሊያመሰግናቸው ይችል የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) የትያጥሮን ጉባኤ በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በትያጥሮን የነበሩትን ክርስቲያኖች ሊያመሰግናቸው መቻሉ በጣም ያስደስታል። እንዲህም አላቸው:- “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።” (ራእይ 2:19) በትያጥሮን የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በኤፌሶን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ለይሖዋ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር አላጡም። እምነታቸው ጠንካራ ነበር። ከዚህም በላይ የትያጥሮን ክርስቲያኖች የኋለኛው ሥራቸው ከፊተኛው ሥራቸው የበዛ ሲሆን ቀደም ብለን እንዳየናቸው ሦስት ጉባኤዎች ጸንተው ቆመዋል። ይህም በአሁኑ ጊዜ በምድር በሙሉ በሚገኙት 100,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር እንዴት የሚመሳሰል ነው! በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነው የአገልግሎት ቅንዓት ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ የገፉትን ሲቀሰቅሳቸው የይሖዋ ፍቅር ብሩሕ ሆኖ ይታያል። ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ክርስቲያኖች አቅኚዎች በመሆን በትጋት እየሠሩ ነው። ይህንንም በማድረጋቸው የቀረውን አጭር ጊዜ መጪውን የአምላክ መንግሥት በማወጅ በጥበብ እየተጠቀሙበት ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10

5 የቅቡዓን ቀሪዎችም ሆነ የእጅግ ብዙ ሰዎች ታማኝ አባላት በዙሪያቸው ያለው ዓለም ተስፋ ወደ ሌለው ድቅድቅ ጨለማ በጣም እየዘቀጠ ሲሄድ በአምላክ አገልግሎት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በመቆየት ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ጽናት አሳይተዋል። ሁላችንም ድፍረት ይኑረን። የራእይ መጽሐፍ ቀደም ያሉት የአምላክ ነቢያት የሰጡትን ምሥክርነት ያረጋግጥልናል። “ታላቁ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቀርቦአል። የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ድምፅ ቀርቦአል፣ እጅግም ፈጥኖአል።”—ሶፎንያስ 1:14፤ ኢዩኤል 2:1፤ ዕንባቆም 2:3፤ ራእይ 7:9፤ 22:12, 13

“ያችን ሴት ኤልዛቤልን”

6. (ሀ) የትያጥሮን ጉባኤ ብዙ የሚመሰገንበት ምክንያት ቢኖረውም አፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ምን ዓይነት ችግር እንዳለ ኢየሱስ አስተውሎ ነበር? (ለ) ኤልዛቤል ማን ነበረች? ነቢይ ነኝ ለማለት የሚያስችላት መሠረት ነበራትን?

6 እንደ እሳት የሚንበለበለው የኢየሱስ ዓይን በይበልጥ ጠልቆ በማየት አፋጣኝ ትኩረት የሚያስፈልገው ነገር እንዳለ ተገነዘበ። በትያጥሮን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ አላቸው:- “ዳሩ ግን:- ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ።” (ራእይ 2:20) በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የእሥራኤል ንጉሥ የአክዓብ ሚስት የነበረችው ጣዖት አምላኪዋ ንግሥት ኤልዛቤል በነፍሰ ገዳይነትዋ፣ በምንዝርዋና የበላይ ለመሆን በምታደርገው ጥረት በጣም የታወቀች ሆና ነበር። በኋላም የይሖዋ ቅቡዕ የነበረው ኢዩ ገደላት። (1 ነገሥት 16:31፤ 18:4፤ 21:1-16፤ 2 ነገሥት 9:1-7, 22, 30, 33) ጣዖት አምላኪ የነበረችው ኤልዛቤል ነቢይ ነኝ ለማለት የሚያስችላት ምንም መሠረት አልነበራትም። በእሥራኤል ምድር ነቢያት ሆነው በታማኝነት እንዳገለገሉት እንደ ዲቦራና እንደ ሚርያም አልነበረችም። (ዘጸአት 15:20, 21፤ መሳፍንት 4:4፤ 5:1-31) የይሖዋ መንፈስ አሮጊትዋን ሐናንና የወንጌላዊው ፊሊጶስን አራት ሴት ልጆች ትንቢት እንዳናገረ ኤልዛቤልን አላናገራትም።—ሉቃስ 2:36-38፤ ሥራ 21:9

7. (ሀ) ኢየሱስ “ያች ሴት ኤልዛቤል” ሲል እንዴት ስላለ ገፋፊ ኃይል መናገሩ ነበር? (ለ) አንዳንድ ከጉባኤው ጋር የተባበሩ ሴቶች በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተውን አካሄዳቸውን ትክክል ለማስመሰል ምን ዓይነት ምክንያት ሊያቀርቡ ይችላሉ?

7 ስለዚህ በትያጥሮን የነበረችው “ያቺ ሴት ኤልዛቤል” ነቢይ ነኝ የምትለው በውሸት ነበር። የአምላክ መንፈስ ድጋፍ አልነበራትም። ይህች ሴት ማን ነበረች? ጉባኤውን በመበከል ላይ ያለች አንዲት እፍረት የለሽ ሴት ወይም የሴቶች ቡድን ሳትሆን አትቀርም። በጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሴቶች በገዛ ፈቃዳቸው የሚፈጽሙት ድርጊት ትክክል መሆኑን ለማሳየት ጥቅሶችን እያጣመሙ ሌሎች የጉባኤው አባሎች በሴሰኝነት ድርጊት እንዲካፈሉ ይገፋፉ ነበር። በእውነትም የውሸት ነቢያት ነበሩ። ሌሎች ክርስቲያኖች “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት” በመፈጸም የራሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ ይገፋፉ ነበር። (ቆላስይስ 3:5) በአሁኑ ጊዜ በብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በቸልታ የሚታዩትን በመሰሉ የሴሰኝነትና የራስ ወዳድነት አኗኗር እንዲጠመዱ ለማድረግ ይፈልጋሉ።

8. (ሀ) ኢየሱስ በትያጥሮን ስለነበረችው “ኤልዛቤል” ምን ውሳኔ አስተላልፎ ነበር? (ለ) በዘመናችን ተገቢ ያልሆነ የሴቶች ተጽዕኖ የታየው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በመቀጠል በትያጥሮን ለነበሩት ሽማግሌዎች እንዲህ ይላቸዋል:- “ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፣ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ።” (ራእይ 2:21, 22) የመጀመሪያዋ ኤልዛቤል በአክዓብ ላይ እንደሰለጠነችና የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ የነበረውን ኢዩን እንደናቀች ሁሉ ይህም በትያጥሮን ጉባኤ የነበረው የሴቶች ተጽእኖ ባሎችንና ሽማግሌዎችን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ሞክሮ ነበር። በትያጥሮን ጉባኤ የነበሩትም ሽማግሌዎች ይህን ትህትና የጎደለውን የኤልዛቤል ተጽእኖ በቸልታ የተመለከቱት ይመስላል። ኢየሱስ እዚህ ላይ ለእነርሱም ሆነ በዘመናችን ላለው ምድር አቀፍ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል። በዘመናችን አንዳንድ ቦታቸውን የማይጠብቁ ሴቶች ባሎቻቸው ከሃዲዎች እንዲሆኑ ገፋፍተዋል። እንዲያውም በይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ላይ ክስ እንዲመሠረት አድርገዋል።—ከ⁠ይሁዳ 5-8 ጋር አወዳድር።

9. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ኤልዛቤል የተናገረው ቃል በጉባኤ ውስጥ ባሉት ሴቶች ላይ በሙሉ በመጥፎ ሁኔታ የማይንጸባረቀው እንዴት ነው? (ለ) ኤልዛቤላዊ ተጽእኖ የሚነሳው ምን ሲሆን ብቻ ነው?

9 ይህ አገላለጽ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉት ታማኝ ሴቶች ላይ በምንም መንገድ በመጥፎ ሁኔታ አይንጸባረቅም። በአሁኑ ጊዜ የምሥክርነቱ ሥራ በአብዛኛው የሚከናወነው ታማኝ በሆኑ እህቶች ነው። እነርሱም በሚመሩአቸው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አማካኝነት በጣም ብዙ ሰዎችን ወደ ጉባኤው በማምጣት ላይ ናቸው። መዝሙር 68:11 እንደሚያመለክተው ይህን ዝግጅት አምላክ ራሱ ባርኮታል። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ” [የ1980 ትርጉም] ሚስቶች ዝግተኛ በሆነና አክብሮት በተሞላበት ጠባያቸው በባሎቻቸው ላይ በጎ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ጠባይ “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ” ነው። (1 ጴጥሮስ 3:1-4) ንጉሥ ልሙኤልም ትጉህና ባለሞያ የሆነችውን ሴት አመስግኖአል። (ምሳሌ 31:10-31) ሴቶች እንደ ኤልዛቤል የሚሆኑት ወንዶችን ለማሳት ሲነሱና የራስነትን ሥልጣን አልቀበል በማለት ከመስመር ሲወጡ ብቻ ነው።—ኤፌሶን 5:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3

10. (ሀ) ኤልዛቤልና ልጆችዋ ፍርድ የተቀበሉት ለምንድን ነው? (ለ) የኤልዛቤል ልጆች የሚሆኑ ሁሉ እንዴት ባለ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

10 ኢየሱስ ‘ስለዚህች ሴት ኤልዛቤል’ ሲናገር ቀጥሎ እንዲህ ብሎአል:- “ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፣ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።” (ራእይ 2:23) ኢየሱስ ኤልዛቤልና ልጆችዋ ንስሐ የሚገቡበት ጊዜ ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከሴሰኝነት መንገዳቸው ፈቀቅ ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፍርዳቸውን መቀበል ይኖርባቸዋል። እዚህ ላይ በዘመናችን የሚኖሩትን ክርስቲያኖች በሙሉ የሚያሳስብ ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ አለ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስን የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ወይም የሥነ ምግባር ሕግ በመጣስ ወይም በትዕቢተኛነት ቲኦክራቲካዊ ሥርዓቶችን በመቃወም የኤልዛቤልን ምሳሌ በመከተል ልጆችዋ ከሆኑ አደገኛ መንፈሳዊ በሽታ ይዞአቸዋል ማለት ነው። እውነት ነው፣ እንደዚህ ያለው ሰው በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሽማግሌዎች ጠርቶ እንዲጸልዩለት ቢጠይቃቸው “የእምነት ጸሎት ድውዩን ያድናል። ጌታም [“ይሖዋም፣” NW] ያስነሳዋል።” ይህ የሚሆነው ግን ከቀረበለት ጸሎት ጋር ተስማምቶ በትህትና ሲኖር ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ማንም ቢሆን የፈጸመውን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት በመሰወር ወይም በቅንዓት እንደሚያገለግል በማስመሰል አምላክን ወይም ክርስቶስን ለማታለል እችላለሁ ብሎ ማሰብ አይኖርበትም።—ያዕቆብ 5:14, 15

11. የዘመናችን ጉባኤዎች ሕገወጥ የሆነ የሴቶች ተጽእኖ እንዳይኖር ነቅተው መጠበቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

11 በዘመናችን ያሉት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ለዚህ አደገኛ ሁኔታ ንቁ መሆናቸው በጣም ያስደስታል። ሽማግሌዎች ቲኦክራቲካዊ ያልሆነ ዝንባሌ ወይም መጥፎ ሥነ ምግባር እንዳይስፋፋ ተጠንቅቀው ይጠባበቃሉ። በአደገኛ ጎዳና ላይ የሚገኙ ወንዶች ወይም ሴቶች ርቀው ከመሄዳቸው በፊት መንፈሳዊነታቸውን ገንብተው እንዲስተካከሉ ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ገላትያ 5:16፤ 6:1) እነዚህ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እንደ ሴቶች ነፃነት እንቅስቃሴ የመሰለ ጠባብ ዓላማ ያለው የሴቶች ቡድን እንዳይፈጠር በፍቅርና በቆራጥነት ያግዳሉ። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች አማካኝነት ከወቅቱ ጋር የሚስማማ ትምህርት በየጊዜው ይሰጣል። *

12. የዮሐንስ ክፍል በዘመናችን የኢዩን የመሰለ ቅንዓት ያሳየው በምን መንገድ ነው?

12 ይሁን እንጂ ከባድ ኃጢአት ከተሠራ ይህን ኃጢአት የሠሩ ሰዎች በተለይም ኃጢአትን ልማዳቸው ያደረጉና ንስሐ ለመግባት የማይፈልጉ ከሆኑ መወገድ ይኖርባቸዋል። ኢዩ የኤልዛቤልን ግፊት ከእሥራኤል ምድር ፈጽሞ ለማጥፋት ያሳየውን ቅንዓት እናስታውሳለን። የዘመናችን የዮሐንስ ክፍልም በተመሳሳይ ተባባሪው ለሆነው ‘የኢዮናዳብ’ ክፍል ምሳሌ የሚሆንና ልቅ መሆንን ከሚፈቅዱት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል።—2 ነገሥት 9:22, 30-37፤ 10:12-17

13. ለተሳሳተ የሴቶች ተጽእኖ የሚሸነፉ ሁሉ ምን ይሆናሉ?

13 የአምላክ ልጅ የይሖዋ መልእክተኛና ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ዘመናዊቷ ኤልዛቤል ማን መሆንዋን ለይቶ ማሳወቁና በበሽታ ተመትታ የአልጋ ቁራኛ እንድትሆን ማድረጉ ተገቢ ነው። በእርግጥም መንፈሳዊ በሽታዋ በጣም የበረታና ስር የሰደደ ነው። (ሚልክያስ 3:1, 5) ለዚህ ዓይነቱ የተሳሳተ የሴቶች ግፊት የተሸነፉ ሁሉ እንደ ሙታን ተቆጥረው ከክርስቲያን ጉባኤ የመወገድ ሐዘንና ታላቅ መከራ ይደርስባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ንስሐ ገብተው ካልተመለሱና ጉባኤው እንደገና ካልተቀበላቸው ተቀስፈው ሥጋዊ ሞት ሳይሞቱ የሚቆዩት እጅግ ቢበዛ እስከ ታላቁ መከራ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ በፊት ሙሉ በሙሉ ከበደላቸው ተጸጽተው ንስሐ ቢገቡ እንደገና ሊስተካከሉ ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:21, 22፤ 2 ቆሮንቶስ 7:10

14. (ሀ) ኢየሱስ የኤልዛቤልን ተጽእኖ እንደማስወገድ ለመሳሰሉ አንዳንድ ችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት በሽማግሌዎች የሚጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) ጉባኤዎች በእነዚህ ጉዳዩች ላይ ሽማግሌዎች የሚወስዱትን እርምጃ መደገፍ የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

14 ‘ሁሉም ጉባኤዎች’ ኢየሱስ የውስጣዊ ጥልቅ ስሜት ግፊት ምሳሌ የሆነውን “ኩላሊት” እንዲሁም የውስጠኛው ሰው (ለአንድ ነገር የሚገፋፋው ውስጣዊ ዓላማ መኖር) ምሳሌ የሆነውን ‘ልብ’ እንደሚመረምር ማወቅ ይገባቸዋል። ይህንንም ዓላማ ለማስፈጸምና የኤልዛቤልን ግፊት የመሰለ ችግር ሲያጋጥም ችግሩን ለመፍታት በታመኑ ኮከቦች ወይም ሽማግሌዎች ይጠቀማል። (ራእይ 1:20) እነዚህ ሽማግሌዎች ይህን የመሰለውን ጉዳይ በጥልቅ ከመረመሩና ፍርድ ከሰጡ በኋላ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ግለሰቦች እርምጃ የተወሰደው ለምንና እንዴት እንደሆነ መመርመር አያስፈልጋቸውም። ሁሉም የሽማግሌዎቹን እርምጃ በትህትና መቀበልና የእነዚህን የጉባኤ ከዋክብት ሥራ መደገፍ ይኖርባቸዋል። ለይሖዋና ለድርጅታዊ ዝግጅቱ ታማኝ መሆን ሽልማት ያሰጣል። (መዝሙር 37:27-29፤ ዕብራውያን 13:7, 17) አንተም በበኩልህ ኢየሱስ ለሁሉም እንደ ሥራው በሚከፍልበት ጊዜ በረከት የምትቀበል ያድርግህ።—ገላትያ 5:19-24፤ 6:7-9

“ያላችሁን ጠብቁ”

15. (ሀ) ኢየሱስ በኤልዛቤል ላልተበከሉት ክርስቲያኖች ምን ተናገረ? (ለ) በ1918 ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ሁሉ በከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ተበላሽተው እንዳልነበረ እንዴት እናውቃለን?

15 ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረው ቃል በጣም የሚያጽናና ነው። “ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፣ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ።” (ራእይ 2:24, 25) በትያጥሮን ከተማ የኤልዛቤል ተጽእኖ ያላበላሻቸው ታማኝ ነፍሳት ነበሩ። ከ1918 በፊት በነበሩት 40 ዓመታትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በስፋት ተስፋፍቶ የሚታየውን እርኩሰት በቸልታ የተመለከቱት ሁሉም ክርስቲያን ነን ባዮች አልነበሩም። የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ክርስቲያናዊ ያልሆነ መሠረት እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ ይጣጣር የነበረውና በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው የሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አነስተኛ ቡድን ከከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና የተወረሱትን ባቢሎናዊ እምነቶችና ልማዶች በሙሉ ለማስወገድ ተነሳስቶ ነበር። ይህም ‘የዚያችን ሴት የኤልዛቤልን’ ስድ መሆንን የሚፈቅድ ትምህርት ይጨምር ነበር።

16. ኢየሱስም ሆነ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያኖች አስተዳደር ክፍል ምንም ተጨማሪ ሸክም ስላልጫኑ ከምን ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋል?

16 በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የዮሐንስ ክፍል አባሎች ባልንጀሮቻቸው የሆኑትን የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በመዝናኛው ዓለም ውስጥ እንደሚታዩት ከመሰሉት የሴሰኝነት ስሜት የሚቀሰቅሱ ግፊቶች እንዲጠነቀቁ አበረታተዋቸዋል። ነገሩ ምን እንደሚመስል ለማወቅ በመጓጓት ወይም ምን ነገሮችን ማስወገድ እንደሚገባ ለማወቅ ሲባል ምግባረ ብልሹነትን መመልከት ወይም መሞከር አስፈላጊ አይደለም። “የሰይጣንን ጥልቅ ነገር” መሸሽ የጥበብ መንገድ ነው። ኢየሱስ “ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም” ብሎአል። ይህ አባባሉ የመጀመሪያውን መቶ ዘመን የክርስቲያኖች የአስተዳደር አካል ውሣኔ ያስታውሰናል። “ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ።” (ሥራ 15:28, 29) መንፈሣዊ ብልጽግና እንድታገኙ ከሐሰት ሃይማኖት፣ ከደም (ደምን በደም ስር እንደመውሰድ ካለው ድርጊት)፣ ከዝሙት ራቁ። ይህን ከፈጸማችሁ አካላዊ ጤንነታችሁም ሊጠበቅ ይችል ይሆናል።

17. (ሀ) ሰይጣን ሰዎችን በጥልቅ ነገሮች የሚፈትነው እንዴት ነው? (ለ) ለዚህ የተወሳሰበ የሰይጣን ዓለም ጥልቅ ነገሮች እንዴት ያለ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?

17 ሰይጣን ዛሬም ቢሆን የመፈላሰፍ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች የሚሸነግሉ ሌሎች ‘ጥልቅ ነገሮች’ ማለትም የተወሳሰቡ ግምታዊ አስተሳሰቦችና ፍልስፍናዎች አሉት። እነዚህ ፍልስፍናዎች ከሥነ ምግባር ውጭ ከሆኑ አስተሳሰቦች በተጨማሪ መናፍስትነትንና የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳቦች ይጨምራሉ። ለጥበቡ ዳርቻ የሌለው ፈጣሪ እነዚህን “ጥልቅ ነገሮች” እንዴት ይመለከታቸዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ” እንዳለ ጠቅሶአል። በአንጻሩ ደግሞ “የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር” ቀላል፣ ብሩሕና ልብ የሚነካ ነው። ጥበበኛ ክርስቲያኖች የሰይጣንን ውስብስብ ዓለም “ጥልቅ ነገሮች” ይርቃሉ። አስታውሱ፣ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ቆሮንቶስ 1:19፤ 2:10፤ 1 ዮሐንስ 2:17

18. ኢየሱስ እስከ መጨረሻ ድረስ ለሚጸኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን በረከት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር? እነዚህ ቅቡዓን ከሙታን ከተነሱ በኋላ በአርማጌዶን እንዴት ያለ መብት ያገኛሉ?

18 አሁን ደግሞ ኢየሱስ በትያጥሮን ለነበሩት ክርስቲያኖች ልባቸውን ሞቅ የሚያደርግላቸው ቃል ነገራቸው። ይህ ቃል በዘመናችን ያሉትንም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያጽናና ነው። “ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፣ በብረትም በትር ይገዛቸዋል። እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ።” (ራእይ 2:26, 27) በእርግጥም ይህ በጣም ትልቅ መብት ነው። ቅቡዓን ድል አድራጊዎች ከሙታን ከተነሱ በኋላ አመጸኞቹን ብሔራት በአርማጌዶን ከኢየሱስ ጋር ሆነው በብረት በትር ቀጥቅጦ የማጥፋት ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ክርስቶስ ጠላቶቹን እንደ ሸክላ ዕቃ በሚሰባብርበት ጊዜ የእነዚህ ብሔራት የኑክሌር መሣሪያዎች እንደ እርጥብ እንጨት ብልጭ ብሎ ከመጥፋት የበለጠ ምንም ዓይነት ጉዳት አያደርሱም።—መዝሙር 2:8, 9፤ ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-13, 15

19. (ሀ) “የንጋት ኮከብ” ማን ነው? ድል ለሚነሱት ራሱን የሚሰጠውስ እንዴት ነው? (ለ) ለእጅግ ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት ማበረታቻ ተሰጥቶአል?

19 በተጨማሪም ኢየሱስ “የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ” ብሎአል። (ራእይ 2:28) ይህ ኮከብ ምን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ሲገልጽ እንዲህ ብሎአል:- “እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” (ራእይ 22:16) አዎ፣ ይሖዋ የበለዓምን ከንፈር አስገድዶ ያስነገረውን ትንቢት የሚፈጽመው ኢየሱስ ነው። ትንቢቱ “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፣ ከእስራኤል በትር ይነሳል” ይላል። (ዘኍልቁ 24:17) ኢየሱስ ድል ለሚነሱት “የንጋት ኮከብ” የሚሰጣቸው እንዴት ነው? ራሱን ለእነርሱ በመስጠት፣ ከእነርሱ ጋር በጣም ቅርብ የሆነ ዝምድና በመመሥረት ነው። (ዮሐንስ 14:2, 3) ይህም ጸንቶ ለመቆም በኃይል የሚገፋፋ ነገር ነው። በተጨማሪም እጅግ ብዙ ሰዎች “የንጋት ኮከብ” በቅርብ ጊዜ ውስጥ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ በምድር ላይ ገነትን መልሶ እንደሚያቋቁም ማወቃቸው የሚያነቃቃቸው ነው።

ፍጹም አቋም እየጠበቁ መኖር

20. በትያጥሮን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ድክመቶችን የሚያስታውሰን የትኛው በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኝ ሁኔታ ነው?

20 ይህ መልእክት በትያጥሮን የነበሩትን ክርስቲያኖች በጣም ሳያበረታታ አልቀረም። ታላቅ ክብር የተቀዳጀውና በሰማይ የሚኖረው የአምላክ ልጅ በትያጥሮን ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ስለ አንዳንድ ችግሮቻቸው ራሱ ተናግሯቸዋል። እጅግ ቢያንስ ጥቂት የጉባኤው አባሎች ያደረገላቸውን የፍቅራዊ እረኝነት ጥየቃ ተቀብለው እንደነበረ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ይህ ከሰባቱ መልእክቶች በሙሉ ረዥም የሆነው መልእክት በዛሬው ጊዜ እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። ኢየሱስ በ1918 ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ለፍርድ በመጣ ጊዜ አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ድርጅቶች በጣዖት አምልኮና በመንፈሳዊ ሴሰኝነት ተውጠው ነበር። (ያዕቆብ 4:4) አንዳንዶቹ ትምህርቶቻቸውን የመሠረቱት የሰባተኛው ቀን አክባሪ አድቬንቲስት እንደ ነበረችው ኤለን ኋይትና ክርስቲያን ሳይንቲስት እንደ ነበረችው ሜሪ ቤከር ኤዲ በመሰሉ የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ትዕቢተኛ ሴቶች ላይ ነበር። በቅርብ ጊዜም ሴቶች መድረክ ላይ ወጥተው መስበክ ጀምረዋል። (ከ⁠1 ጢሞቴዎስ 2:11, 12 ጋር አነፃፅር።) በተለያዩት የካቶሊክ ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ ለማርያም ከአምላክና ከክርስቶስ የሚበልጥ ክብር ይሰጣል። ኢየሱስ ግን ይህን የሚያክል ክብር አልሰጣትም ነበር። (ዮሐንስ 2:4፤ 19:26) ይህን የመሰለ ሕጋዊ ያልሆነ አክብሮት ለሴቶች የሚሰጡ ድርጅቶች ክርስቲያኖች ናቸው ሊባሉ ይችላሉን?

21. ግለሰቦች ኢየሱስ ለትያጥሮን ጉባኤ ከላከው መልእክት ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

21 የዮሐንስ ክፍል ወይም የሌሎች በጎች አባል የሆኑ ግለሰብ ክርስቲያኖች ይህን መልእክት ልብ ማለት ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 10:16) አንዳንዶች በትያጥሮን የነበሩት የኤልዛቤል ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉት የሚቀልለውን መንገድ ለመከተል ይፈተኑ ይሆናል። አቋማችንን እንድናላላ የሚገፋፋ ፈተና ያጋጥማል። በዛሬው ዘመን ከደም የተሰሩ ምግቦችን የመብላት ወይም ደም በደም ሥር የመውሰድ ፈተና ያጋጥማል። አንዳንዶች ደግሞ በመስክ አገልግሎት ቀናተኞች በመሆናቸው ወይም በጉባኤ ፊት ንግግር ለመስጠት በመቻላቸው በሌሎች ጉዳዮች ማለትም የዓመፅ ወይም የሴሰኝነት ፊልሞችን ወይም የቪድዮ ክሮችን እንደመመልከትና ከመጠን በላይ አልኮል እንደመውሰድ በመሰሉት ጉዳዮች ብዙም ጥብቅ መሆን እንደማያስፈልጋቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ኢየሱስ ለትያጥሮን ክርስቲያኖች የሰጠው ማስጠንቀቂያ በእነዚህ ጉዳዮች ግድየለሾች እንዳንሆን ያሳስበናል። ይሖዋ በትያጥሮን እንደነበሩት ብዙ ክርስቲያኖች ንጹሖችና ያልተከፋፈለ ሙሉ ልብ ያለን እንድንሆን ይፈልግብናል።

22. ሰሚ ጆሮ አስፈላጊ መሆኑን ኢየሱስ አጠንክሮ የተናገረው እንዴት ነው

22 በመጨረሻም ኢየሱስ “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” ይላል። (ራእይ 2:29) ኢየሱስ ይህን ቀስቃሽ ማስጠንቀቂያ ደጋግሞ ሲናገር አራተኛ ጊዜው ነው። ወደ ፊት የምናያቸውንም ሦስት መልእክቶች የሚደመድመው በዚህ ማስጠንቀቂያ ነው። አንተስ ሰሚ ጆሮ አለህን? ካለህ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት ራሱ ባቋቋመው መገናኛ መስመር በኩል የሚሰጠውን ምክር መስማትህን አታቋርጥ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 51 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዛሬው ጊዜ አብዛኛው የምሥክርነት ሥራ የሚከናወነው ቲኦክራቲካዊ ሥልጣንን በሚያከብሩና በሚደግፉ ታማኝ እህቶች ነው